ከመጽሐፈ ነህምያ ልንማራቸው የምንችለው በርካታ ነገሮች ቢኖሩም፥ ሦስቱ ግን በጣም አስፈላጊና ከሌሉቹ የላቁ ናቸው።
- አንዲት ቤተ ክርስቲያን ልትገነባና ጤነኛ ልትሆን ከተፈለገ ተገቢ የሆኑ መሪዎች ያስፈልጓታል። እነዚህ መሪዎች ከሁሉ በፊት ተገቢ መንፈሳዊ መመዘኛዎችን ማሟላት አለባቸው። እግዚአብሔርን መውደድ አለባቸው፤ ለእግዚአብሔር ሕግ ሊገዳቸው ያስፈልጋል፤ ኃጢአትን ሊጠሉና የጸሎት ሰዎች ሊሆኑም ይገባል።
- መሪዎች እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን የሰጣትን ሥራ እንዲሠሩና ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲፈጽሙ ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሊያደራጁትና ሊያቅዱ ይገባል። ቤተ ክርስቲያን በሚገባ መደራጀት አለባት። እንዲሁም እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን አባል የተሰጠውን መንፈሳዊ ስጦታ አካሉን ለማነጽ እንዲያውለው በተናጠል የተለየ ኃላፊነት ሊሰጠው ይገባል።
- ቤተ ክርስቲያን ለእግዚአብሔር ልታደርግ የገባችውን ግዴታ ዘወትር ልታድስ ያስፈልጋታል። አይሁድ ኃጢአታቸውን በግልጥ እንደተናዘዙ እኛም ኃጢአታችንን በመናዘዝ ራሳችንን በግልና በቡድን ማንጻት አለብን። ለእግዚአብሔርም በመታዘዝ ግልጽ ቃል ኪዳን ማድረግ አለብን። ወደ ኃጢአት ላለመመለስም ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ለእግዚአብሔር የገባነውንም ግዴታ ያለማቋረጥ ልናድሰው ያስፈልጋል። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በተለይ የሕዝባቸውን የሕይወት ንጽሕና ለመጠበቅ ጠንቃቆች መሆን አለባቸው።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እነዚህን ሦስት እውነቶች ማወቅና ከሕይወታቸው ጋር ማዛመድ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ የእዚህን ሦስት እውነቶች መኖር ወይም አለመኖር የምታየው እንዴት ነው? ሐ) በአሁኑ ጊዜ በቤተ ክርስቲያንህ ከእነዚህ ሦስት እውነቶች በጣም አስፈላጊ የሆነውና የሚፈለገው የትኛው ነው? መ) ይህን ያልክበት ምክንያት ምንድን ነው?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)