የመጽሐፈ ኢዮብ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያን አንዳንድ ጊዜ መከራ የሚቀበልባቸውን ምክንያቶች ጥቀስ። ለ) በክርስቲያን ላይ የሚደርሰው መከራ ሁልጊዜ የኃጢአት ውጤት ነውን? መልስህን አብራራ። ሐ) አንድ ክርስቲያን በበሽታ በሚሠቃይበት ወይም የሚወደው ሰው በሞት በሚለይበት ጊዜ የምትሰጠው ምክር ወይም ማበረታቻ ምንድን ነው?

የምንኖረው መከራና ሥቃይ በሞላበት ዓለም ውስጥ ነው። ትንንሽ ልጆች ራሳቸውን በሕይወት ለማቆየት የሚችሉበትን ዕድል ሙሉ በሙሉ በማጣት፥ በየቀኑ በበሽታና በራብ ይረግፋሉ። ወታደሮች ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ሰላማዊ ሰዎች የሚያልቁባቸው በርካታ ጦርነቶች በምድራችን ይካሄዳሉ። እግዚአብሔር በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀምባቸው ታላላቅና ታዋቂ ክርስቲያኖች ይታመማሉ ይሞታሉም። ይህ ሁሉ ክርስቲያኖችን «ለምን?» የሚል ጥያቄ እንዲሰነዝሩ ያስገድዳቸዋል። ለመረዳት በጣም አስቸጋሪ ከሆኑ ነገሮች አንዱ መከራን የመቀበል ጉዳይ ነው። እጅግ ጻድቅ የሚመስሉ ሰዎች መከራን የሚቀበሉት ለምንድን ነው? በሌላ አንጻር ደግሞ እጅግ ክፉ የሆኑ ሰዎች መልካም ሕይወትን የሚኖሩት ለምንድን ነው? ይህ ጉዳይ እንዴት ትክክል ሊሆን ይችላል? እግዚአብሔር ምንም ሳናደርግ በዚች ዓለምና በሕይወታችን ላይ ብዙ መከራ እንዲመጣ በማድረጉ ትክክል ነውን?

የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ከተፈጠረና በኃጢአት ከወደቀ ጀምሮ ይህ ጥያቄ ራስ ምታት ሆኖበታል። ጉዳዩ በጣም የተወሳሰበ ስለሆነ ሰዎችን ሁሉ የሚያረካ መልስ መስጠት እጅግ አዳጋች ነው። በተለይ ደግሞ መከራን ለሚቀበሉ ሰዎች ለዚህ ጉዳይ መልስ መስጠት ከባድ ነው።

እግዚአብሔር መጽሐፈ ኢዮብን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲጨመር ያደረገው ይህንን መከራ መቀበልን በሚመለከት የሚሰነዘር የምንጊዜም ጥያቄ ለመመለስ ይረዳ ዘንድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፥ ሰዎች በተለይ ደግሞ ጥፋተኛ ያልሆኑት መከራ ስለሚቀበሉበት ምክንያት ሁሉ መልስ ባይሰጥም፥ በመከራ ጊዜ በእምነታችን ጸንተን እንድንኖር የሚያደርጉንን የተወሰኑ መልሶች ይሰጠናል። መጽሐፈ ኢዮብ ስለ አንድ ጻድቅ ሰው መከራ መቀበል የሚናገር ነው። ይህ ሰው ሁሉን ነገር ቢያጣም እንኳ በእግዚአብሔር ላይ ስለነበረው ጽኑ እምነት እናነባለን። በተጣማሪም በመከራ ውስጥ ሳለ ስለ እግዚአብሔር የጽድቅ ፍርድ ቢገረምም በግሉ ስለ ፈጸመው ትግል እንመለከታለን። 

የመጽሐፈ ኢዮብ ጸሐፊ

በመጽሐፈ ኢዮብ ውስጥ የምናገኘው ታሪካዊ ዘገባ አነስተኛ በመሆኑ መቼ እንደተጻፈና ማን እንደጻፈው ለመናገር አንችልም። ልናደርግ የምንችለው የመመራመር ግምትን ማቅረብ ነው። የመጽሐፈ ኢዮብ አጻጻፍ በሁለት ደረጃዎች የተከናወነ ሳይሆን አይቀርም።

በመጀመሪያ፥ የመጽሐፈ ኢዮብን ታሪካዊ ድርጊት እናገኛለን። መጽሐፉን በጥንቃቄ በምንመለከትበት ጊዜ የምንረዳው ነገር፥ ኢዮብ እስራኤላዊ እንዳልሆነና በኤዶም ወይም በዓረብ ምድር የኖረ ሰው እንደሆነ ነው። ኢዮብ የኖረው የእስራኤል ሕዝብ አባቶች የሚባሉት አብርሃም፥ ይስሐቅና ያዕቆብ በኖሩበት ዘመን ይመስላል። ይህ ማለት መጽሐፈ ኢዮብ የተጻፈው ከ3000-2000 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር ማለት ነው። ብዙ ምሁራን ይህን አቋም የያዙባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ፡- 

1) የኢዮብ ዕድሜ በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ ከምናያቸው የእስራኤል ሕዝብ አባቶች ዕድሜ ጋር ተቀራራቢ ነው። 

2) ኢዮብ ከብት አርቢ ነበርና ሀብቱም በከብቶቹ ላይ የተመሠረተ ነበር፤ ይህም ከአብርሃም ጋር ይመሳሰላል። 

3) ኢዮብ ቤተሰቡን እንደ ሊቀ ካህን የሚያገለግልና እንደ አብርሃም መሥዋዕት የሚያቀርብ ሰው ነበር። 

4) በመጽሐፈ ኢዮብ ውስጥ ስለ ሙሴ ሕግ፥ ስለ መገናኛው ድንኳን ወይም ስለ ቤተ መቅደሱ የሚናገር አንዳችም ነገር አልተጠቀሰም።

5) በነቢያት ዘመን እንደነበረው የእግዚአብሔርን ቃል ያስተምሩ ስለነበሩ የአይሁድ ነቢያት የተጠቀሰ አንዳችም ነገር የለም፤ ስለዚህ ኢዮብ ይኖር የነበረው ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው ሺህ ዓመት ይመስላል። 

ሁለተኛው፥ መጽሐፈ ኢዮብ ከፍተኛ ትምህርትና ችሎታ በነበረው በአንድ ባልታወቀ ሰው የመጻፉ ነገር ነው። መጽሐፈ ኢዮብ በጥንታዊ ዓለም ከተገኙ ከፍተኛ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች ወይም ግጥሞች ውስጥ አንዱ ነው። ጸሐፊው መልእክቱን ለማስተላለፍ የሚያስችለውን ግጥም ለመጻፍ ከፍተኛ ችሉታውን ተጠቅሟል። እንደ አንዳንዶቹ ግምት ደግሞ መጽሐፈ ኢዮብ የተጻፈው ከሙሴ እስከ ዕዝራ ባለው ዘመን (1440-450 ዓ.ዓ.) በማንኛውም ጊዜ ውስጥ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም አንዳንድ ምሁራን የመጽሐፉ ጸሐፊ ሙሴ እንደሆነ ቢናገሩም፥ ለዚህ አመለካከት ምንም ማስረጃ የለንም። ጸሐፊው ማን እንደሆነ አይታወቅም ማለቱ የተሻለ ነው። መጽሐፉ በአይሁድ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተካተተ ጸሐፊው እስራኤላዊ እንደሆነ መገመት እንችላለን። ጽሑፉንና የተጻፈበትን ቋንቋ ስንመለከት፥ ጸሐፊው በጣም የተማረ ሰው እንደነበረ እንገነዘባለን። ጸሐፊው ስለ መከራና እግዚአብሔርም ከመከራ ጋር ስላለው ግንኙነት የሚያስብ ፈላስፋ ነበር። እርግጠኞች መሆን ባንችልም፥ ጸሐፊው ይህንን ታሪክ በቃል ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣ ትውፊት ሰምቶታል ወይም የተጠቀመበት ሌላ መጽሐፍ አለ። ብዙ ምሁራን መጽሐፉ የተጻፈው ከንጉሥ ሰሎሞን በኋላ (970 ዓ.ዓ.) ከእስራኤል ምርኮ በፊት (586 ዓ.ዓ.) እንደሆነ ይመስላቸዋል። 

የመጽሐፉ ርእስ

መጽሐፈ ኢዮብ የተሰየመው በታሪኩ ዋና ገጸ ባሕርይ ስም ነው። መጽሐፉ የሚናገረው በመከራ ውስጥ ስላለፈው፥ ስለ ጻድቁ ሰው ስለ ኢዮብ ነው። ታሪኩ የሚያንጸባርቀው ኢዮብ በመከራ ውስጥ እያለ የጠየቃቸውን ጥያቄዎችና ሌሎች ሰዎች ስለ መከራ የሰጡዋቸውን የተለመዱ መልሶች ነው።

መጽሐፈ ኢዮብ በሥነ-ጽሑፍነቱ

መጽሐፈ ኢዮብ፡- በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ከሚገኙ እጅግ ምርጥ ከሆኑ የግጥም መጻሕፍት መካከል አንዱ ቢሆንም፥ ለመተርጐም እጅግ አስቸጋሪ ከሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አንዱ ነው። ምሁራን ስለ ትርጕማቸው እርግጠኞች ያልሆኑባቸው በርካታ ቃላትና ዐረፍተ ነገሮች የሚገኙበት መጽሐፍ ነው። ስለተለያዩ የመጽሐፈ ኢዮብ ትርጒሞች ያሰብን እንደሆነ በትርጕም ብዙ የሚለያዩበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው።

መጽሐፈ ኢዮብ ባለሙያ በሆነ ጸሐፊ በጥንቃቄ ታቅዶ የተጻፈ መጽሐፍ ነው። ጽሑፉ በአብዛኛው በሕጋዊ የችሎት ክርክር መልክ የቀረበ ሲሆን፥ በዚህ ክርክር ጸሐፊው ኢዮብን ከሳሽ አድርጎ በማቅረብ የእግዚአብሔርን ቅን ፍርድ ያሳያል። መጽሐፈ ኢዮብን በምታነብበት ወቅት የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡-

1. መጽሐፈ ኢዮብ የሚጀምረው የግጥም መልክ በሌለው የአጻጻፍ ስልት ሲሆን (ኢዮብ 1-2)። የሚጠቃለለውም በዚሁ ዓይነት ሥነ-ጽሑፍ ነው (ኢዮብ 42)፤ ዳሩ ግን በመካከል ያሉት ምዕራፎች በሙሉ በግጥም መልክ የቀረቡ ናቸው። 

2. በመጽሐፉ መጀመሪያ ላይ ኢዮብን የምናገኘው እጅግ ደስተኛና በረከት የበዛለት ሆኖ ሲሆን (ኢዮብ 1፡1-5)። በመጽሐፉም መጨረሻ የምናገኘው በዚሁ መልክ ነው (ኢዮብ 42፡7-17)። በመካከል ያሉት ምዕራፎች ግን ስለ ኢዮብ መከራ ይናገራሉ። 

የመጽሐፈ ኢዮብ አስተዋጽኦ

1. የታሪኩ መግቢያ (ኢዮብ 1-2) 

2. ኢዮብ ከሦስቱ ጓደኞቹ ጋር ያደረጋቸው ንግግሮች (ኢዮብ 3-31)

ሀ. የመጀመሪያው ውይይት ዑደት (ኢዮብ 4-14)

1. የኢዮብ እንጉርጉሮ መግቢያ (ኢዮብ 3) 

2. የኤልፋዝ ንግግር (ኢዮብ 4-5) 

3. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 6-7) 

4. የበልዳዶስ ንግግር (ኢዮብ 8) 

5. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 9-10)

6. የሶፋር ንግግር (ኢዮብ 11)

7. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 12-14) 

ለ. ሁለተኛው የውይይት ዑደት (ኢዮብ 15-21)

1. የኤልፋዝ ንግግር (ኢዮብ 15)

2. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 16-17) 

3. የበልዳዶስ ንግግር (ኢዮብ 18) 

4. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 19) 

5. የሶፋር ንግግር (ኢዮብ 20)

6. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 2) 

ሐ. ሦስተኛው የውይይት ዑደት (ኢዮብ 22-31)

1. የኤልፋዝ ንግግር (ኢዮብ 22) 

2. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 23-24) 

3. የበልዳዶስ ንግግር (ኢዮብ 25)

4. የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 26-3) 

3. የኤሊሁ ንግግር (ኢዮብ 32-37) 

4. የእግዚአብሔር ንግግርና የኢዮብ መልስ (ኢዮብ 38-41) 

5. ማጠቃለያ (ኢዮብ 42) 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading