አብዛኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሥነ ግጥማዊ የአጻጻፍ ስልት መጻፉን ቀደም ሲል ተመልክተናል። ይህ በተለይ በመዝሙረ ዳዊት፥ በመኃልይ መኃልየ ዘሰሎሞን፥ እንዲሁም በአንዳንድ የትንቢት መጻሕፍት ውስጥ የምናየው እውነታ ነው። የጥበብ ጽሑፎች የሥነ- ግጥምና ቅኔ ጽሑፎች ክፍል ቢሆኑም፥ «የጥበብ» ጽሑፎች ብለን ልንጠራቸው የምንችለው ልዩ ዓይነት ግጥሞች ናቸው። ከመዝሙረ ዳዊት አንዳንድ ክፍሎችና እንደዚሁም አብዛኛዎቹ የመጽሐፈ መክብብና የመጽሐፈ ምሳሌ ክፍሎች የጥበብ ጽሑፎች የሚገኙባቸው ናቸው።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአማርኛ ቋንቋ «ጥበብ» የምንለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው? ለ) በኅብረተሰብህ ውስጥ እንደ ጠቢብ የሚቆጠር አንድ ሰው ጥቀስ። ሐ) ጠቢብ ያደረገው ምንድን ነው? መ) ከሌሎች ሰዎች የሚለየው እንዴት ነው?
ባለንበት ዘመን፥ ብዙዎቻችን ጥበብ የሚገኘው በትምህርት ቤት እንደሆነ አድርገን እናስባለን። ጥበብ የበርካታ እውነቶች ስብስብ እውቀት እንደሆነ እንቆጥራለን፤ ስለዚህ ጥበብ የሚገኘው ባልተማሩ ሳይሆን፥ በሚገባ በተማሩ ሰዎች ዘንድ እንደሆነ አድርገን እንገምታለን።
አይሁድ ግን «ጥበብ» ሲሉ ይህን ማለታቸው አይደለም። የብሉይ ኪዳን ጸሐፊዎች «ጥበብ» የሚለውን ቃል በተለያዩ መንገዶች ተጠቅመውበታል፡-
1. የተለየ ሙያ ወይም ችሎታ ስላላቸው ሰዎች ለመናገር አገልግሏል። ለምሳሌ የመገናኛውን ድንኳን የሠሩት ባስልኤልና ኤልያብ የተባሉት ሁለት ሰዎች «ጠቢባን» የተባሉት ድንኳኑን በመሥራት ረገድ ልዩ ችሎታ ስለነበራቸው ነው (ዘጸአት 31፡1-11)።
2. አንዳንድ ጊዜ ይህ ቃል አገልግሎት ላይ ውሎ የምናየው ለጐበዞችና ጥሩ የአእምሮ ችሎታ ላላቸው ሰዎች ነው (ኢዮብ 38፡36)።
3. ጥበብ የሚለው ቃል ጥሩ የተፈጥሮ እውቀት ላላቸውና አንድን ጉዳይ አመዛዝኖ በማቅረብ ችሎታቸው ጠቢባን ተብለው ለተጠሩ ሰዎች አገልግሉአል (ኢዮብ 32፡7)።
4. ከሁሉ በላይ ግን፥ ጥበብ እውቀትን በትክክለኛ መንገድ የመጠቀም ችሎታ ነው (ምሳሌ 1፡5)። አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ የተሳካ ኑሮ ለመኖር የሚችለው ጠንቃቃና ሚዛናዊ የመሆን ችሉታ ሲኖረው ነው። ይኸውም ትክክለኛና ሚዛናዊ የሆኑ ነገሮችን ማድረግ ሲችል ነው (ምሳሌ 3፡1-6)።
የውይይት ጥያቄ፥ መዝሙረ ዳዊት (11)፡10፤ ምሳሌ 1፡7፤ 2፡5-6፤ 19፡10፤ ያዕቆብ 1፡5፤ 3፡17 አንብብ። ሀ) የጥበብ መጀመሪያ ምንድን ነው? ለ) እውነተኛ ጥበብ የሚመጣው ከየት ነው? ሐ) የዚህ ዓይነቱ ጥበብ በሕይወትህ ለመኖሩ ማስረጃ የሚሆኑ መንገዶችን ግለጽ።
ስለዚህ የጥበብ ሥነ-ጽሑፎች የምንላቸው ለሕይወታችን ጥቅም በሚያስገኙ መንገዶች እንዴት መኖር እንዳለብን የሚያስተምሩን የብሉይ ኪዳን ሥነ-ጽሑፎች ናቸው። የተመሠረቱትም ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት በማድረግ ሲሆን፥ ያለዚህ ግንኙነት ለእግዚአብሔር ፍርድ የተጋለጥንና እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ መንገድ ለመኖር የማንችል ነን። የጥበብ ሥነ-ጽሑፍ ሕይወታችንን ስለሚለውጥ፥ ተግባራዊ ነው። ለሕይወታችን ያለው ጠቀሜታ ከሁሉም የላቀ ነው። እውነተኛ እውቀትን ከሕይወታችን ጋር በማዛመድ እንዴት የተሻለ ሕይወት መኖር እንዳለብን ለመማር የሚያስችለን ነው። የጥበብ ሥነ-ጽሑፍ ዓላማ የአንድን ሰው ዝንባሌ፥ ባሕርይና አኗኗር በመለወጥ፥ በልቡ ውስጥ ሊኖር የሚገባውን ፈሪሀ እግዚአብሔር እንዲያንጸባርቅ የሚያደርግ ነው። ይህም ወደ በጎነት ሕይወት ይመራል (ምሳሌ 2፡20)።
ጥበብና እውቀት እንደ ሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ካለው ግንኙነት ጋር በጥብቅ የተቆራኙ መሆናቸውን አይሁድ ተገንዝበው ነበር። እግዚአብሔር የጥበብ ሁሉ ምንጭ በመሆኑ ለእርሱና ለፈቃዱ ታዝዘው ለመኖር ለወሰኑ ሰዎች ሁሉ ጥበብን ለመስጠት ቃል ገብቶአል (ኢዮብ 12:13፤ ምሳሌ 2፡5-6)፤ ስለዚህ ማንኛውም ሰው ጥበብን ለማግኘት ወደ ትምህርት ቤት አልሄደም፤ ወይም ጥበበኞችን አላማከረም፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር በመነጋገር እንደፈቃዱ ተጓዘ። ስለዚህ ሰው በእውነት ጠቢብ ነው የሚባለው መሠረታዊ በሆነ ጉዳይ ነው።
የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ጥበብ በትምህርት ቤት ከምንማረው «ጥበብ» የሚለየው እንዴት ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስን ጥበብ ለመረዳት መሠረቱ፡- ሕይወት ሁለት ዋና ዋና መንገዶችን የያዘች መሆንዋን መገንዘብ ነው። ወደ ጽድቅ የሚያደርስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መንገድ አለ፤ ወይም ወደ ጥፋት የሚያደርስ የኃጢአት መንገድ አለ (ማቴዎስ 7፡13-14)። አንደኛው መንገድ የጠቢብ (ምሳሌ 10፡8፥14)፥ የቅንና (ምሳሌ 11፡3) የጻድቅ መንገድ ነው (ምሳሌ 10፡16)። ሌላው የሞኞች ወይም የሰነፎች (ምሳሌ 10፡1፥8፥14)፤ የኃጥአንና (ምሳሌ 10፡3) ታማኝ ያልሆኑ ሰዎች ወይ የወስላቶች መንገድ ነው (ምሳሌ 11፡3)።
የጥበብ መጻሕፍትን በምንተረጕምበት ጊዜ ልናስታውሳቸው የሚገባን ሁለት ዓይነት የጥበብ ሥነ-ጽሑፎች አሉ። መጀመሪያ፥ ልንከተላቸው የሚገባን ተግባራዊ ጥበባትን የሚያስተምሩን ምሳሌዎችና አባባሎች አሉ። እነዚህ ጥሩ ልማዶችን፥ ጥሩ ሙያዎችንና መልካም ባሕርያትን የሚያስተዋውቁን ናቸው (ለምሳሌ፥ ምሳሌ 21፡23፤ 22፡3)።
ሁለተኛ፥ በዚያን ዘመን ይነገሩ የነበሩ ምርጥ አባባሎችን የሚያንጸባርቁ፥ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ግን ሊከተላቸው የማያስፈልጉ ምሳሌዎች አሉ፤ ወይም እነዚህ ከቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጋር የማይስማማ ፍልስፍና የሚያንጸባርቁ ናቸው። መጽሐፈ ኢዮብና መክብብ ከያዛቸው የጥበብ አነጋገሮች መካከል ትክክል ያልሆኑና ልንከተላቸው የማያስፈልጉ ዐረፍተ ነገሮች ይገኛሉ። የኢዮብ ወዳጆች ለኢዮብ ያካፈሉት ምክር በአብዛኛው ትክክለኛ አልነበረም። በመጽሐፈ መክብብ ውስጥ የምናገኛቸው የሰሎሞን አስተሳሰቦች ላይ ላዩን በምንመለከታቸው ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት በትክክል የሚያንጸባርቁ አይደሉም። በውስጡ የሚገኘውን የጥበብ ትምህርት የምናስተውለው መጽሐፉን በተገቢው መንገድ ስንረዳ ነው።
የጥበብ ሥነ-ጽሑፎችን ብዙ ጊዜ በተሳሳተ መንገድ የምንተረጉምበት አንዱ ምክንያት በውስጡ ያሉትን ልዩ ቃላት ካለመረዳታችን ነው። ቀጥለን በእነዚህ ጽሑፎች ውስጥ ያሉትን ዋና ዋና ቃላት እንመለከታለን፡-
1. ጥበብ፡- ልዩ እውቀትን ማግኘት ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ያገኘነውን እውቀት እግዚአብሔርን ለማስከበር በሚያስችል ትክክለኛ መንገድ ለመኖር መጠቀም ማለት ነው።
2. ጠቢብ ሰው:- በመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዛት መሠረት የሚኖር ሰው ማለት ነው።
3. ሞኝ ወይም ሰነፍ፡- ያልሠለጠነና ማንም ሰው በቀላሉ ሊያሞኘው የሚችል (ምሳሌ 14፡15)፣ ሕይወቱን በብልሃት የማይመራ፥ ዓመፀኛና ያልተገራ፥ ተግሣጽን የማይቀበልና እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰው ነው። ሞኝ ወይም ሰነፍ በአእምሮው ደካማ የሆነ ሰው ማለት ሳይሆን እግዚአብሔርን በሕይወቱ የማያከብር ሰው ማለት ነው።
4. ኃጥእ፡- ሆን ብሉ እግዚአብሔርንና ቃሉን ያልተቀበለ፥ በእግዚአብሔር ትእዛዛት ላይ ያመፀና ሌሉችም ከእውነት እንዲርቁ የሚፈልግ ሰው ነው።
5. ፌዘኛ ወይም ቀልደኛ፡- እውነትን በተጠራጣሪነት የሚጠይቅ፥ ተግሣጽንና ምክርን የሚጠላ ሰው ነው። የጥበብ ሥነ-ጽሑፎች ዓይነቶች የተለያዩ ናቸው። በመጀመሪያ፥ እንዴት መኖር እንዳለብን የሚያስረዱ «ተግባራዊ ጥበባት አሉ።» ይህ በተለይ የሚገኘው በመጽሐፈ ምሳሌ ነው። ሁለተኛው፥ የከንቱነት ጥበብ የምንለው ሲሆን፥ ትንሽ አዎንታዊ ትምህርት ኖሮት ነገር ግን የዚህን ዓለም ጥበብና ዘይቤ እንዳንከተል የሚያስጠነቅቀን ነው። ይህን የምናገኘው በመጽሐፈ መክብብ ውስጥ ነው። ሦስተኛ፣ «መከራ የሚኖረው ለምንድን ነው? መከራ ሁልጊዜ የኃጢአት ውጤት ነውን? » የሚሉትንና የመሳሰሉትን ዐበይት ጥያቄዎች የሚመረምር የፍልስፍና ጥበብ አለ። ይህም የሚገኘው በመጽሐፈ ኢዮብ ውስጥ ነው።
የተለያዩ የመዝሙር ዓይነቶች እንዳሉ ሁሉ፥ የጥበብ ጽሑፎችም በዓይነታቸው የተለያዩ ናቸው።
1. ምሳሌ፡- በጥበብ ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ከሁሉም የላቀ አስፈላጊና የተለመደው መሣሪያ ምሳሌያዊ አነጋገር ነው። ምሳሌ፥ ሰፊ የሆነ እውነትን በአጭር አነጋገር የሚገልጽ ነው። በምሳሌ ውስጥ ያለውን እውነት ሰዎች በቀላሉ ሊያስታውሱት በሚችሉት መንገድ በአጭሩ የቀረበ የቃላት ቅንብር ነው። የሕይወትን ሰፊ ክፍል በመውሰድ ዓለም አቀፋዊ በሆነ መመሪያ አሳጥሮ ለማቅረብ ይሞክራል። ብዙውን ጊዜ ምሳሌያዊ አነጋገርን ለመረዳት ቀላል ቢሆንም፥ እውነቱ ግን በጣም ጥልቅና በርካታ የሕይወት ተዛምዶዎችን ሊያካትት የሚችል ነው። ምሳሌያዊ አነጋገር ብዙ ጊዜ ነገሮችን በማነጻጸር ውይም በማመሳሰል ይቀርባል። ለምሳሌ፡- «እንቁላል ቀስ በቀስ በእግሩ ይሄዳል» በሚለው የተለመደ የአማርኛ ምሳሌያዊ አነጋገር ውስጥ እንቁላሉ በሕይወት ውስጥ ያለውን የተለመደ መሠረታዊ እውነታ ለመግለጥ የቀረበ ነው። ይህም መሠረታዊ እውነታ ነገሮች በመሆን ሂደት ውስጥ ለማለፍ ጊዜን ይጠይቃሉ ማለት ነው። ምሳሌዎች የሰውን ሕይወትና እውነት በአጭሩ ስለሚያቀርቡ መቶ በመቶ ትክክል ሊሆኑ አይችሉም። ይልቁንም አጠቃላይ የሆኑ መግለጫዎች ወይም የሕይወት ዝንባሌዎች ናቸው። ለምሳሌ፡- በፍጥነት የሚፈጸሙ ጉዳዮች አሉ። ሁሉም ነገር በዝግታ የሚፈጸም አይደለም፤ ይህም ማለት ከላይ የተመለከትነው ምሳሌ ሙሉ በሙሉ ትክክል ሊሆን አይችልም።
የውይይት ጥያቄ ሀ) ከምታውቃቸው የኢትዮጵያ ምሳሌዎች አምስቱን ጥቀስ። ) ምሳሌነቱ ምንድን ነው? ሐ) ምሳሌው ሊገልጠው የሚፈልገው የሕይወት መሠረታዊ እውነታ ምንድን ነው?
ልዩ ልዩ ዓይነት ምሳሌያዊ አነጋገሮች አሉ። አንዳንዶቹ እንደሞኝ ወይም ሰነፍ ሰው በኃጢአት እንዳንወድቅ ልንጠነቀቅባቸው ስለሚገባን ነገሮች የሚያሳስቡ ናቸው (ምሳሌ 6፡20-35)። ሌላው ዓይነት ምሳሌ ሥልጣን ያለው እውነት ሆኖ የቀረበ ነው (ምሳሌ 3፡ 27)። በመጨረሻ ስለ ጥበብ መንገድ የሚናገሩ አጠቃላይ መግለጫዎች ደግሞ አሉ (ምሳሌ 18፡18፤ 20፡19)።
2. እንቆቅልሾች፡- የጥበብ ሥነ-ጽሑፎች በውስጣቸው የተሰወሩ ትርጕሞችን ያዘሉ፥ አእምሮን የሚያሠሩ ጥያቄዎች ሆነው የሚቀርቡበት ጊዜ አለ። ከእንደነዚህ ዓይነት ጽሑፎች እጅግ የታወቀው ሶምሶን ስለ አንበሳና ስለ ማር ያቀረበው እንቆቅልሽ ነው (መሳፍንት 14፡14)።
3. ተረቶች፡- ተረት ስለ እንስሳት ወይም አዝዕርት የሚናገርና በውስጡ ትምህርት ወይም እውነት የያዘ ታሪክ ነው(መሳፍንት 9፡7-20)።
የምሳሌዎች አተረጓጐም
የምናነበውን ጽሑፍ በተገቢው መንገድ ለመረዳት ጽሑፉ በየትኛው የሥነ-ጽሑፍ ዓይነት ውስጥ እንደሚመደብ ማወቅ አስፈላጊ ነው። ምሳሌዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በጣም የተለመዱ ስለሆኑ፥ ይህን ማድረግ ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ አይደለም። ምሳሌዎችንና የጥበብ ጽሑፎችን በምናነብበትና ለመረዳት በምንሞክርበት ጊዜ ልንከተላቸው የሚገቡን እንዳንድ መመሪያዎችን ቀጥለን እንመለከታለን፡-
1. በሕይወት ውስጥ የመከሠት ዝንባሌ ያላቸውን ነገሮች በሚገልጡና (ለምሳሌ መክብብ 8፡1)፥ በሕይወት ውስጥ ምን መሆን እንዳለበት (ምሳሌ 23፡4) በሚናገሩ ምሳሌዎች መካከል ግልጽ የሆነ ልዩነት ለማድረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርግ። ብዙ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምሳሌን ወይም ድርጊትን በመውሰድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጻፈ ብቻ ልንከተለው ይገባል ብለው ያስባሉ። ጉዳዩ ግን እንደዚያ አይደለም።
2. ምሳሌዎች ሁልጊዜ መፈጸም ያለባቸው፥ ከእግዚአብሔር የተገኙ ቃል ኪዳኖች ወይም ዋስትናዎች አይደሉም። ይልቁንም የተለመዱ ዝንባሌዎች ወይም ባጠቃላይ የሚሆነውን ነገር የሚያንጸባርቁ ናቸው። በምሳሌ 15፡25 እግዚአብሔር የትዕቢተኞችን ቤት እንደሚነቅልና የባልቴትን ዳርቻ እንደሚያጸና ተጽፎአል፤ ዳሩ ግን በዚህ ምድር ላይ ትዕቢተኞችና ሀብታሞች መከራና ጉዳት እንደማይደርስባቸውና ድሆች ደግሞ ለኑሮአቸው የሚፈልጉትን ነገር እንደማያገኙ ሁላችንም እናውቃለን፤ ይህ ምሳሌ ግን እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን እንደሚቃወምና በመጨረሻም እንደሚፈርድባቸው የሚናገር አጠቃላይ መግለጫ ነው። ድሆችንም በማሰብ ይጠነቀቅላቸዋል።
3. ማንኛውም ምሳሌ ራሱን ችሉ የሚቆም አይደለም፡፡ እውነትን በተሻለ መንገድ ለመረዳት አንድን ምሳሌ በሌላ ምሳሌና በአጠቃላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መመዘን ያሻናል።
4. ምሳሌዎች በቀላሉ ልናስታውሳቸው እንችል ዘንድ አጠር ባለ ቅንብር የተጻፉ ናቸው፤ ስለዚህ ትክክል ሊሆኑ የማይችሉበትና የማይሠሩት ጊዜ አለ። ምሳሌዎች የመሆን ዝንባሌ ያላቸው አጠቃላይ እውነታዎች ናቸው።
5. አንዳንድ ምሳሌዎች ለባህላችን እንግዳ የሆኑ ማነጻጸሪያዎችን ይጠቀማሉ፤ ስለዚህ እነዚያ ማነጻጸሪያዎች ለአይሁድ ምን ማለት እንደሆኑ መረዳት ያስፈልገናል። ከዚህ በኋላ በራሳችን ባህል በታወቁ ማነጻጸሪያዎች ያንን እውነት እንገልጠዋለን። ለምሳሌ፥ በኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በኋላ ንጉሥ ላይኖር ይችላል፤ ነገር ግን መሪዎች አሉ፤ ስለዚህ ስለ ነገሥታት የተጠቀሱ ነገሮች ለመሪዎችም ይሠራሉ (ለምሳሌ፡- ምሳሌ 22፡1)።
6. ምሳሌዎችን ለመተርጐም በምንሞክርበት ጊዜ፥ በመጀመሪያ ማነጻጸሪያዎችን ወይም የተጻፉትን መግለጫዎች ለመረዳት መሞከር አለብን። በእነዚህ ማነጻጸሪያዎች መሠረት፥ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድና በተሻለ ሁኔታ ለመኖር የሚረዱ አጠቃላይ እውነተችን ፈልግ።
የውይይት ጥያቄ፥ ምሳሌ 20፡1-10 አንብብ። ሀ) በእያንዳንዱ ምሳሌ ውስጥ የሚገኙትን ማነጻጸሪያዎች ጥቀስ። ለ) በማነጻጸሪያዎች ውስጥ የሚገኙትን አጠቃላይ እውነቶች ጥቀስ። ሐ) እነዚህ ምሳሌዎች ከሕይወትህ ጋር ሊዛመዱ የሚችሉት እንዴት ነው?
የውይይት ጥያቄ፥ መዝሙረ ዳዊት 1 እና 121 አንብብ። እያንዳንዱን መዝሙር በሚመለከት ግጥሞችን ስለ መተርጐም በሁለተኛው ቀን ትምህርት ያየሃቸውን መመሪያዎች በመከተል፡- ሀ) በእያንዳንዱ ጥቅስ ውስጥ ምን ዓይነት ተነጻጻሪነት (ፓራለሊዝም) እንዳለ ግለጥ። ለ) በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ የሚታየው ስሜት ምንድን ነው? ሐ) [የተጠቀምክባቸውን ተምሳሌቶችን ዘርዝር። እያንዳንዳቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ ተመልከታቸው። መ) እነዚህ ተምሳሌታዊ መግለፃዎች ጸሐፊው ማስተማር የፈለገውን መንፈሳዊ እውነት የሚገልጹት እንዴት ነው? ሠ) እነዚህን መንፈሳዊ እውነቶች ለቤተ ክርስቲያንህ አባሎች እንዴት ታስተምራቸዋለህ?
የውይይት ጥያቄ፥ መጽሐፈ ምሳሌ 10ን አንብብ። ሀ) ከምሳሌዎቹ ውስጥ ምን እንደተፈጸመ የሚናገሩትንና እንዴት መኖር አንዳለብን የሚናገሩትን ለይተህ ግለጽ። ለ) በምሳሌው ውስጥ ለመንፈሳዊ እውነት መሠረት በመሆን ያገለገለው ማነጻጸሪያ ምንድን ነው? ሐ) ማነጻጸሪያ መንፈሳዊ እውነቱን የሚገልጸው እንዴት ነው? መ) በእያንዳንዱ ምሳሌ ውስጥ የሚተላለፈው መንፈሳዊ እውነት ምንድን ነው? ሠ) ይህ መንፈሳዊ እውነት ከራስህ ሕይወት ወይም በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች ሕይወት ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)