የዚህ ምንባብ ተለምዶአዊ ገለጻ የክርስቲያን ሕይወትን ስለሚያንጽ ነገር ማውሳቱ ነው። ሁላችንም በክርስቶስ ላይ እናንጻለን፥ ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች መልካም የሆኑ ቁሳቁሶችን፥ ሌሎች ደግሞ መናኛ ቁሳቁሶችን ለእነጻው ይጠቀማሉ። የምትጠቀመው ቁሳቁስ የምታገኘውን ዋጋ ይወስናል።
ይህ የዚህ ምንባብ ትክክለኛው ተዛምዶ ቢሆንም፥ መሠረታዊው ትርጓሜ ግን አይደለም። ጳውሎስ ያወሳ የነበረው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሆነችውን የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ስለማነጽ ነው። (ከ 6፡19-20 ባለው እንደተመለከተው እያንዳንዱ አማኝ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው፤ እዚህ ላይ ግን የሚታየው የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ነው። በኤፌ. 2፡19-22፥ እንዳለች ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ጋር ተነጻጽራለች።) ጳውሎስ የሚያመለክተው አንድ ቀን እግዚአብሔር ሥራችንን ከአጥቢያ ጉባኤ ጋር በማገናዘብ እንደሚፈርድ ነው። «የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል» (1ኛ ቆሮ. 3፡13)።
እግዚአብሔር በጥራት እንድናንጽ ተቆርቋሪነቱን ይገልጻል። ቤተ ክርስቲያን የሰባኪው ወይም የምእመናኑ አይደለችም። እርሷ የእግዚአብሔር ናት። «እናንተ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናቸሁ» (ቁ9)። አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ማነጽ ከፈለግን፥ የተወሰኑ ሁኔታዎችን ማሟላት አለብን።
በመጀመሪያ፥ በትክክለኛው መሠረት ላይ ማነጽ አለብን (3፡10-11)። ያ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ በመጣ ጊዜ የተሰቀለውን ክርስቶስን ብቻ ለመስበክ ወሰነ (2፡1-2)። ዘለቄታ ያለውን ብቸኛ መሠረት ጣለ። ከ30 ዓመታት በሚያልፈው አገልግሎቴ፥ «አብያተ ክርስቲያናት» በታወቀ ሰባኪ፥ ወይም ልዩ በሆነ ዘዴ፥ ወይም ትክክል ነው ብለው ዓይናቸውን በጣሉበት ዶክትሪን ላይ ለማነጽ ሲጥሩ ተመልክቼአለሁ። ነገር ግን እነዚህ አገልግሎቶች አልዘለቁም። ቆሮንቶሳውያን ክርስቶስን ማክበር ሲገባቸው በግለሰቦች በጳውሎስ፥ በጴጥሮስና በአጵሎስ ላይ ዓይናቸውን ጣሉ።
መሠረቱ የሚጣለው የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በማወጅ ነው። መሠረት የሕንፃው በጣም አስፈላጊ ክፍል ነው። ምክንያቱም ከላይ ለሚታነጸው አካል መጠኑን፥ ቅርጹንና ጥንካሬውን የሚወስነው እርሱ ስለሆነ ነው። አንድ አገልግሎት ለጊዜው የተሳካ ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን በክርስቶስ ላይ ካልተመሠረተ በመጨረሻ ይፍረከረክና ይጠፋል።
አሁን እያሰብሁ ያለሁት ስለ አንድ መጋቢ ነው። ይህ ሰው ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ ሲል ከመጽሐፍ ቅዱስ አገኘሁ ያለውን (እውነቱ ግን ከሌሎች መጻሕፍት ያነበበውን ነው) «አንድ ታላቅ እውነት ለማራመድ ወሰነ። ለዚህ ላገኘው «እውነት የተሰጡትን» የያዘ አንድ ቡድን ከቤተ ክርስቲያን ገምሶ ይዞ ወጣ። ነገር ግን ይህ አዲሱ ቤተ ክርስቲያን ፍጹም መጽናት አልቻለም። አሁን ቡድኑ ብትንትኑ ስለ ወጣ መጋቢው ለዓላማው አማኝ የሆኑትን ለመሰብሰብ ከቤተ ክርስቲያን ወደ ቤተ ክርስቲያን ይንከራተታል። የገነባው በተሳሳተ መሠረት ላይ ነበረ!
ብር፥ ወርቅ፥ የከበሩ ድንጋዮች – ዘላቂ፣ ውብ፣ የከበረ/ውድ፣ ለማግኘት ከባድ
እንጨት፥ ሣር፥ አገዳ – አላፊ፥ ጊዜያዊ፣ ተራ፥ እንዲያውም አስቀያሚ፣ ርካሽ በቀላሉ የሚገኝ
ሁለተኛ፥ በትክክለኞቹ ቁሳቁሶች ማነጽ አለብን (3፡12-17)። ሠንጠረዥ እንደሚያሳየው ጳውሎስ ሁለት ዓይነት ተቃራኒ ቁሳቁሶችን ይገልጻል።
ጳውሎስ በእነዚህ የቁሳቁሶች አመራረጡ ለማመልከት የፈለገው ምንድን ነው? ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለመሆን የሚገጣጠሙ «ሕያዋን ድንጋዮች» ስለሆኑ የሚናገረው ስለ ሰዎች አይደለም (1ኛ ጴጥ. 2፡5)። በግሌ እንደማምነው ጳውሎስ የሚያመለክተው ወደ እግዚአብሔር ቃል ዶክትሪን ነው። በዚህ ምዕራፍ እያንዳንዱ ክፍል፥ ቃሉ ለምልክትነት የተቀመጠው ጳውሎስ ለቤተ ክርስቲያን የሰጠውን ምስል በሚስማማ መልኩ ነው። ቃሉ ለቤተሰብ ምግብ፥ ለማሣ ዘር፥ ለሕንፃ ደግሞ የማነጫ ቁሳቁስ ነው።
የምሳሌ መጽሐፍ የእግዚአብሔር ቃል ጥበብን ሊፈለግ፥ ሊጠበቅ፥ እና በዕለታዊ ሕይወት ሥራ ላይ ሊውል እንደሚገባ ገንዘብ ያስቀምጠዋል። እነዚህን ምንባቦች አጢን፡-
«ጥበብን የሚያገኝ ሰው ምስጉን ነው፥ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ፤ በወርቅና በብር ከመነገድ ይልቅ በእርስዋ መነገድ ይሻላልና። ከቀይ ዕንቍም ትከብራለች» (3፡13-15)።
«ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ብትቀበል፥ ትእዛዜንም በእንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፥ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፥ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፥ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፥ እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፥ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤ የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፥ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ» (2፡1-5)።
«ተግሣጼን እንጂ ብርን አትቀበሉ፥ ከምዝምዝ ወርቅም ይልቅ እውቀትን ተቀበሉ። ጥበብ ከቀይ ዕንቍ ትበልጣለችና፤ የከበረ ነገር ሁሉ አይተካከላትም» (8፡10-11)።
ጳውሎስ በእነዚህ ሦስት ምዕራፎች ስለ ጥበብ ያስተምር እንደነበር በምታስታውስበት ጊዜ፥ በቀላሉ ግንኙነቱን ማየት ትችላለህ። ቆሮንቶሳውያን በቃሉ ውስጥ ባለው የእግዚአብሔር ጥበብ ላይ መመካት ሲገባቸው ቤተ ክርስቲያናቸውን ለመገንባት ይሞክሩ የነበሩት በሰው ጥበብ፥ በዓለም ጥበብ አማካኝነት ነበር።
ይህ ለእኔ የሚገባኝ የቃሉ አገልጋዮች በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በጥልቀት ምሰው በመግባት ውድ የሆኑ ወርቅ፥ ብር እና ዕንቁዎችን በማውጣት እነዚህን እውነቶች በሕዝቡ ሕይወት ውስጥ መገንባት እንደሚገባቸው ነው። ዲ. ኤል ሙዲ አማኞች ተገቢው አክብሮትና ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል የሚል አባባል ነበራቸው። እግዚአብሔር ጥራትንም ሆነ ብዛትን ይፈልጋል። ጳውሎስ ደግሞ ሁለቱንም መያዝ እንደሚቻል ግልጽ አድርጎአል። ታማኙ አገልጋይ በማሣው በመሥራት እድገቱን ማየት ይችላል። እንዲሁም በእግዚአብሔር ቃል በማነጽ ውበትን እና ዘላቂ በረከትን ማየት ይችላል።
የእግዚአብሔር ሕንጻ አንዱ ክፍል መሆን ጽኑ ነገር ነው። ርካሽ ቁሳቁሶችን በመጠቀም የእግዚአብሔርን ቤተመቅደስ «ካረከስን»፥ እግዚአብሔር እንደሚያፈርሰን ቁ 16-17 ያስጠነቅቀናል! ይህ ደግሞ የዘላለም ፍርድ ማለት እይደለም። ምክንያቱም ቁ 15 እያንዳንዱ ሠራተኛ ምንም እንኳ ሽልማት ቢያጣም እንደሚድን ያረጋግጥልናል። ለእኔ እንደሚመስለኝ ጳውሎስ የሚለው እያንዳንዳችን በገዛ ራሳችን ሕይወት የምንገነባውን በቤተ ክርስቲያን ውስጥም እንደ ምንገነባ ነው። በሕንድ አገር ብዙ የሠራ ሚሲዮናዊ ኤሚ ካርማይክል «እኛ ከጠለቅነው ይበልጥ ሥራው የጠለቀ ሊሆን አይችልም» ይሉ ነበር። ስለዚህ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዘላቂ የሆኑ እሴቶችን የማንገነባ ከሆነ መጨረሻችን ሕይወታችንን ማፈራረስ ነው። ለሰዎች በጣም ስኬታማ የሆንን ብንመስልም፥ ነገር ግን «ቀኑ ይገልጠዋል»፥ በመሆኑም በዚያን ዕለት አንዳንድ አገልጋዮች ከጭስ ጋር በንነው ይቀራሉ።
አገልግሎቶችን ማወዳደር አላዋቂነት ነው። ስለዚህ ጳውሎስ በቁጥር 4፡5 ላይ «ጊዜው ሳይደርስ አንዳች አትፍረዱ» በማለት ያስጠነቅቃል።
ወጣት አገልጋዮች ዶክተር ካምቤል ሞርጋንን የመድረክ አገልግሎታቸውን ስኬታማነት ምሥጢር ብዙ ጊዜ ጠይቀዋቸው ነበር። ሞርጋን እንዲህ ሲሉ መለሱ፥ «ሁል ጊዜም አንድ ነገር እነግራቸዋለሁ- ሥራ በርትተህ ሥራ፤ እና እንደገና ሥራ!» ሞርጋን ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሀብትን ለመማስ በጥናት ላይ ይሆን ነበር። እንጨት፥ ሣር እና አገዳን ከጓሮህ ስለምታገኝ ለመልቀም ብዙ ልፋት አይኖርብህም። ነገር ግን ወርቅን ብርን እና ዕንቁን ከፈለግህ መማስ አለብህ። ሰነፍ ሰባኪዎች እና የሰንበት ትምህርት ቤት እስተማሪዎች በኢየሱስ ክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ምላሽ የሚሰጡበት ብዙ ነገር አላቸው- እንደዚሁም ለራሳቸው ከማጥናት ና የግላቸው ከማድረግ ይልቅ የሌሉችን ሥራ የሚሰርቁ ሰባኪዎች ና አስተማሪዎች የሚጠብቃቸው አንድ ዓይነት ዕጣ ነው።
ሦስተኛ፥ ትክክለኛውን ዕቅድ ይዘን ማነጽ አለብን (3፡18-20)። አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን አንድን የንግድ ድርጅት እንደምታንቀሳቅስ አትመራውም ሲባል መስማት ለአንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባላት አስደንጋጭ ነው። ይህ ማለት ጥሩ የሆኑ የንግድ መርሆዎችን አንጠቀምም ማለት ሳይሆን፥ ነገር ግን አሠራሩ ፍጹም የተለየ መሆኑን ለመግለጽ ነው። ለዓለም የሚሠራ የዚህ ዓለም ጥበብ አለ፤ ነገር ግን ለቤተ ክርስቲያን አይሠራም።
ዓለም የምትመካው በማስታወቂያ፥ በክብር፥ በገንዘብ ና በታዋቂ ሰዎች አማካኝነት ጫና በመፍጠር ነው። ቤተ ክርስቲያን ግን በጸሎት፥ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል፥ በትሕትና እና በመሥዋዕትነት ተደግፋ ትሠራለች። ዓለምን የምትኮርጅ ቤተ ክርስቲያን ለጊዜው ስኬታማ ልትመስል ትችላለች፤ ነገር ግን በዘላለማዊው የምታተርፈው እመድን ነው። በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የተገለጸችው ቤተ ክርስቲያን ለዛሬ ዘመን አስፈላጊ የሚመስሉ «የስኬታማነት ምሥጢራት» እንዱም ንብረት አልነበራቸውም፤ በመንግሥት በኩል የሚያደርጉት ተጽዕኖ አልነበረም፤ ገንዘብ አልነበራቸውም («ብርና ወርቅ የለኝም» ብሏል ጴጥሮስ)፤ መሪዎቻቸው በታወቁ ትምህርት ቤቶች ያገኙት ልዩ ትምህርት ያልነበራቸው ተራ ሰዎች ነበሩ፤ ተሳታፊ ለማግኘት ያካሄዱት ውድድር አልነበራቸውም፤ ታዋቂ ሰዎችን አማካሪ አላደረጉም፤ ይህ ሁሉ ሆኖ ዓለምን ገለባበጧት!
እግዚአብሔር ለእያንዳንዲቱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የተለየ ዕቅድ አለው (ፊልጵ. 2፡12-13)። እያንዳንዱ መጋቢ እና የቤተ ክርስቲያን መሪ ለሚያስፈልገው ጥበብ የእግዚአብሔርን ልብ መሻት አለበት። ቁጥር 19 የሰው ጥበብ ባለቤቱን እንደሚያጠምድ (ከኢዮብ 5፡13 የተወሰደ ጥቅስ) ያስጠነቅቃል፤ ቁጥር 20 ደግሞ የሰዎች ጥበብ ወደ ከንቱነትና ወደ ድካም ብቻ እንደሚመራ [ከመዝ. (94)፡11 የተወሰደ ጥቅስ] ያስጠነቅቃል። ቤተ ክርስቲያን ምንም እንኳ የዓለምን ችግሮች ብትጋራም፥ የዓለምን ጥበብ መኮረጅ የለባትም።
በመጨረሻም፥ በትክክለኛው አቋመ ልቡና ማነጽ አለብን (3፡21-23)። ያ አቋመ ልቡና የእግዚአብሔር ክብር ነው። የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን አባላት በሰዎች ላይ ይመኩ ነበር፤ ይህ ደግሞ ስሕተት ነበር። ሰዎችን ያወዳድሩ (4፡6) ነበር፤ በዚህ ሥጋዊ ተግባራቸውም ቤተ ክርስቲያንን ይከፋፍሉአት ነበር። በእግዚአብሔር ላይ ብቻ መመካት የሚሹ ቢሆኑ ኖሮ በጉባኤያቸው መስማማት በሰፈነ ነበር።
ጳውሎስ እያንዳንዱ አማኝ በክርስቶስ ሁሉ ነገር እንዳለው በማመልከት ይህን ጥያቄ ይዘጋዋል። እያንዳንዱ የእግዚአብሔር አገልጋይ ለእያንዳንዱ አማኝ የተሰጠ ነው። ማንም የቤተ ክርስቲያን አባል «እኔ የጳውሎስ ነኝ!» ወይም «እኔ ጴጥሮስን እወዳለሁ!» ማለት አይገባውም፤ ምክንያቱም እያንዳንዱ አገልጋይ እኩል የእያንዳንዱ ምእመን ነው። የተለያዩ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል የሚያቀርቡበትን ሁኔታ ተከትለን የግል ምርጫ ከመያዝ ልንታቀብ እንችል ይሆናል። ነገር ግን እነዚህ የግል ምርጫዎቻችን ከፋፋይ የሆኑ ዝንባሌዎችን እንዲይዙ መልቀቅ የለብንም። እንዲያውም፥ በአነስተኛው የሚያረካኝ ሰባኪ እጅግ የሚያስፈልገኝ እርሱ ሊሆን ይችላል!
«ሁሉም የእናንተው ነው»– ዓለምም ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን በክርስቶስ ምንኛ ባለጠጋዎች ነን! ሁሉም ነገር ለሁሉም አማኞች የተሰጠ ከሆነ ውድድር እና ፉክክር የሚሆኑት ለምንድን ነው? «ዓይኖቻችሁን ከሰዎች ላይ አንሡ! በማለት ጳውሎስ ይገሥጻል። «ዓይኖቻችሁን በክርስቶስ ላይ አድርጉ፥ ቤተ ክርስቲያንን በማነጽም ከእርሱ ጋር አብራችሁ ሥሩ!»
«እናንተ የክርስቶስ ናችሁ» -ይህ ነገሮችን በልክ ያደርጋል። ሁሉም ነገር በክርስቶስ አለኝ፥ ነገር ግን ግድየለሽ መሆን ወይም አርነቴን ያለጥበብ መጠቀም አይገባኝም። «ሁሉ የእናንተ ነው» -ይህ የክርስቲያን አርነት ነው። «እናንተም የክርስቶስ ናችሁ»– ይህ የክርስቲያን ኃላፊነት ነው። እሳት ሲወድቅበት ወደ አመድ የማይለወጥ ቤተ ክርስቲያን መሥራት ካለብን ሁለቱም ያስፈልጉናል።
ለቃሉ አገልጋዮች እንዴት መጸለይ ይገባናል! ቤተሰብን መመገብ ና ልጆችንም ወደ ብስለት ማሸጋገር አለባቸው። ዘሩን በማሣ ላይ መዝራት ና እንዲበዛም መጸለይ አለባቸው። የቃሉን መዝገብ መማስ እና እነዚህኑ መዝገቦችም ቤተመቅደስ አድርገው ማነጽ አለባቸው። «ለእነዚህ ነገሮች የሚበቃ ማን ነው?» ብሎ ጳውሎስ ማስተጋባቱ የሚያስደንቅ አይደለም። ነገር ግን ምላሹን ራሱ ሰጠ- «ብቃታችን በእግዚአብሔር ነው» (2ኛ ቆሮ. 2፡16፤ 3፡5)።
ጽሑፍ – በዋረን ዌርዝቢ፣ ትርጉም – በፈቃዱ ገብሬ፣ እርማት–በጌቱ ግዛው