ኢዮብ 32-42

በከፍተኛ ችግርና ሥቃይ ውስጥ በምናልፍበት ጊዜ ምንም ዓይነት ችግር ይሁን ብዙ ጊዜ የሚኖረን የመገረም ጥያቄ «ለምን?» የሚል ነው። ይህ ወደ አእምሮአችን የሚመጣ ግራ መጋባት የሚያሳየው የእግዚአብሔርን መንገዶችና ዓላማዎች ለመረዳት ብቁ አለመሆናችንን ነው፡፡ ይህ እጅግ የሚያስፈራ ነገር ነው። በተለይ በዚያ ችግር ውስጥ እያለን «ለምን?» ብለን ለምንጠይቀው ጥያቄ በአብዛኛው መልስ እናገኝም። መልሱ በእግዚአብሔር ጥበብና ዓላማ ውስጥ የተሰወረ ብዙ ጊዜ ዓመታት አልፈው ወደኋላ ስንመለከት ነው እግዚአብሔር ያደርጋቸው ከነበሩት ነገሮች ውስጥ አንዳንዶቹን የምንገነዘበው። 

እኛ ክርስቲያኖች ጨርሶ ልንዘነጋው የማይገባ አንድ የተስፋ ቃል አለን። እግዚአብሔር በቃሉ የሚከተለውን ተስፋ ሰጥቶናል። «እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን» (ሮሜ 8፡28-29)። እግዚአብሔር ወደ ሕይወታችን ምንም ዓይነት ክፉ ነገር ይመጣ ዘንድ እንደማይፈቅድ አይናገርም። ስደት፥ ሞት፥ በሽታ ይኖራል። እምነታችንን ልንጥልበት የሚገባን ነገር ግን እነዚህን ክፉ ነገሮች እግዚአብሔር በሕይወታችን መልካም ነገርን ለማምጣት የሚጠቀምባቸው መሆኑ ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ክርስቲያን በመከራ ውስጥ በሚያልፍበት ጊዜ ይህን ታላቅ የተስፋ ቃል ማወቅ ጠቃሚ የሚሆነው እንዴት ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ ኢዮብ 32-42 አንብብ። ሀ) የኤሊሁን የመከራከሪያ አሳብ አሳጥረህ ጻፍ። ለ) እግዚአብሔር ለኢዮብ የሰጠውን መልስ አሳጥረህ ጻፍ። ሐ) ኢዮብ ለእግዚአብሔር የሰጠው ምላሽ ምን ነበር? መ) ኢዮብ በሕይወቱ ዘመን መጨረሻ የተባረከው እንዴት ነበር? ) እግዚአብሔር ስለ ኢዮብ ወዳጆች ክርክር የተናገረው ነገር ምን ነበር? 

ኢዮብ 32-37 የኤሊሁ ንግግር 

ኤሊሁ ወጣት ስለነበር ለረጅም ሰዓታት ቁጭ ብሎ በኢዮብና ታላላቆቹ በሆኑት በሦስቱ ወዳጆች መካከል የተደረገውን ውይይት አዳመጠ። ሦስቱ የኢዮብ ወዳጆች የወከሉት በዕድሜ የገፉ ሰዎችን ጥበብ ሲሆን ጥበባቸው ምን ያህል ደካማ እንደሆነም እንመለከታለን። ኤሊሁ አንዳንድ ጊዜ በዕድሜ ከገፋ ሰዎች ይልቅ ወጣቶች ጠቢባን ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ኤሊሁ፥ በኢዮብም ሆነ በሦስቱ ወዳጆቹ ላይ እጅግ ተቆጣ። ኤሊሁ በእርሱ አመለካከት ኢዮብ ጻድቅ ሰው እንደሆን ያምን ነበር፤ ነገር ግን ቢያንስ እግዚአብሔርን በመክሰሱ ምክንያት የተሳሳተ መስሎታል፡፡ ሦስቱ የኢዮብ ወዳጆቹ አንዳችም ማስረጃ ሳያግኙ ኢዮብን በመክሰሳቸው ጥፋተኞች እንደሆኑ ይናገራል። 

ኤሊሁ የኢዮብን ስሕተት ለማረጋገጥ ሞክሯል። ኤሊሁ፥ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ጻድቅ እንደሆነና ዓለምንም የሚገዛው በቅን ፍርድ እንደሆነ ተናግሯል። እግዚአብሔር ለጽድቅ ዋጋ እንደሚሰጥና ክፋትን እንደሚቀጣ ከሚያመለክተው መመሪያ ጋር ተስማምቷል፤ ዳሩ ግን መከራ ሁሉ የእግዚአብሔር ቅጣት አይደለም የሚል አሳብ አክሉበታል። ይልቁንም እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ቅጣትን ሰው ወደተሳሳተ ተግባር እንዳይሄድ ለመመለስ ይጠቀምበታል። መከራ የምሕረት ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ እግዚአብሔር በታላቅ ጥበቡ ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ ፈሪሀ-እግዚአብሔር እንዲያድርባቸው ለማድረግ መከራን ይጠቀምበታል። እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች በመከራቸው ጊዜ ሳይቀር፥ እግዚአብሔርን መታመናቸውና መደገፋችውን መቀጠል አለባቸው። 

ኢዮብ 38-41 የእግዚአብሔርና የኢዮብ ንግግር 

በመጨረሻ እግዚአብሔር ራሱን ለኢዮብ ገለጠ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የኢዮብን ጥያቄ አልመለሰለትም፤ ወይም መከራ የሚቀበለው ለምን እንደሆነ አልገለጠለትም። ስለ ሰይጣን ክስ እንኳ አነገረውም። እግዚአብሔር ቅን ፍርድን እንዳላደረገ በኢዮብ የቀረበበትን ክስ ለማስተባበል አልሞከረም። እግዚአብሔር ኢዮብን ስሕተት ሠርቷል ብሎ በቀጥታ አልወነጀለውም፤ ነገር ግን ኢዮብ የእግዚአብሔርን ሥራ በመጠየቁ እንደተሳሳተ ትንሽ ፍንጭ ሰጥቷል። ኢዮብን በኃጢአት በመክሰሳቸውና ንስሐ እንዲገባ ለማድረግ በመሞከራቸው ሦስቱ ወዳጆቹ እንደተሳሳቱ እግዚአብሔር ተናግሯል። 

እግዚአብሔር በመጀመሪያ ታላቅ ኃይሉን በማሳየት ወደ ኢዮብ ቀረበ። እግዚኣብሔር በታላቅ ዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ወደ ኢዮብ መጣ። እግዚአብሔር ምን ያህል ታላቅና ኃያል እንደሆነ ለኢዮብ ሊያስታውሰው ፈልጎ ነበር። እግዚአብሔር ሊፈራና ሊከበር እንጂ በሚያደርገው ነገር የጥርጥር ጥያቄ ሊነሳበት የማይገባ ታላቅና ኃይለኛ እንደሆነ ለኢዮብ ለማስታወስ ፈልጎ ነበር። ፈጣሪ እግዚአብሔር በፍጥረታቱ የጥርጥር ጥያቄ ሊሰነዘርበት አይገባም። እግዚአብሔር ስለተግባሩ በችሎት ፊት ቀርቦ አይመረመርም። እግዚአብሔር ፈራጅ ነው፤ የሰው ልጅም ለእርሱ መልስ ሊሰጥ የሚገባው ነው፡፡ 

ቀጥሉ እግዚአብሔር ለኢዮብ ጥበቡን አስታወሰው። እግዚአብሔር የማንንም ጥበብ ሳይፈልግ ዓለምን በሙሉ ፈጥሯል። በመከራ ውስጥ ይህን ለምን አደረገ? ብሉ እግዚአብሔርን መጠየቅ ጥበባችን ከእግዚአብሔር ጥበብ እኩል ነው ወይም ይበልጣል ብሎ መገመት ነው። የሰው ልጅ ጥበብ እጅግ ውሱንና ከእግዚአብሔር ጥበብ ጋር ጨርሶ የማይወዳደር ነው። ኢዮብና ሦስቱ ወዳጆቹ ግን የማያውቁትን ነገር ለመናገር በመሻታቸው ስሕተት ሠርተዋል። 

ኢዮብ 42 ማጠቃለያ 

ኢዮብ የእግዚአብሔርን ኃይል አይቶ ዝም ማለት ሲገባው በንግግር ለሠራው ስሕተት ኃጢአተኛነቱን አመነ። በመከራ ውስጥ ቢሆንም እንኳ በእግዚአብሔር ላይ ጥያቄ ማንሣቱ ስሕተት ነበር። ጸጥታ በሰፈነበት አክብሮት ወደ መሬት ወድቆ ለእግዚአብሔር ሰገደ። 

እግዚአብሔር ኢዮብን ወደ ቀድሞ ክብሩ መለሰው። ጻድቃን በመከራ ውስጥ እንኳ በታማኝነት እንደሚቆዩ በማሳየት እግዚአብሔር የሰይጣንን ስሕተት አረጋገጠ። ኢዮብም ከዚህ ቀደም ከነበረው የላቀ ብዙ ሀብትና በረከትን አገኘ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በዚህኛው የመጽሐፈ ኢዮብ ክፍል የሚገኙትን እጅግ ጠቃሚ እውነቶች ዘርዝር። ለ) ከዚህ ንባብና ጥናት ስለ መከራ ምክንያቶችና በመከራ ውስጥ ያሉ ሰዎችን እንዴት መምከር እንደሚገባ ምን ልንማር እንችላለን? 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply