በክርስቶስ ሞት የተገኙ አንዳንድ ጥቅሞች

ከአያሌ የድነት (ደኅንነት) በረከቶች ውስጥ ብዙዎቹ፣ ለምሳሌ ጸሎትን የመሳሰሉት በአማኞች ልምምድ ስለሚታዩ ግልጥ ናቸው። ነገር ግን ልንለማመዳቸው የማይቻለን ሌሎች በረከቶችም አሉ፥ ለምሳሌ ጽድቅ (ውጤታቸውን ግን እናውቀዋለን)። እዚህ የማንለማመዳቸው በረከቶች ቢሆኑም፥ ለትክክለኛው የክርስትና ሕይወት ልምምድ መሠረቶች ናቸው። 

የክርስቶስ ሞት በእግዚአብሔር ዘንድ ለሚኖረን ተቀባይነት መሠረት ነው

የክርስቶስ ሞት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የሚያስገኝልን መሆኑ በብዙ የክርስትና ትምህርቶች ተገልጧል። በመዋጀት (ሮሜ 3፡24)፥ በእርቅ (2ኛ ቆሮ. 5፡19-21)፥ በይቅርታ (ሮሜ 3፡25)፣ ከኃጢአት አርነት በመውጣት (ቁላ. 1፡13)፣ በውድ ልጁ ተቀባይነት (ኤፌ. 1፡6)፣ በወደፊቱ ክብር እርግጠኞት(ሮሜ 8፡30)፥ እና ሰጽድቅ (ሮሜ 3፡24)፡፡

ጽድቅ የሚለው ቃል ሌላ ማብራሪያ ይሻ ይሆናል። ማጽደቅ እንድን ሰው ጻድቅ ነው ብሎ ማወጅ ነው። በፍርድ ቤት ቋንቋ ወስደን ስንመለከተው፥ አንድን ተከሳሽ ጥፋተኛ አይደለም ብሎ ከማንኛውም ቅጣት ወይም ፍርድ ነጻ ማድረግን ያመለክታል። እርግጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጽድቅ የፍርድ ተቃራኒ ስለመሆኑ ተገልጧል (ዘዳግ. 25፡1፤ ሮሜ 5፡16፥ 8፡33-34)። መጽደቅ በጽድቅ መንገድ ነው የሚከናወነው፤ ማለትም ከእግዚአብሔር ሕግ የሚፈለግበትን ሁሉ አሟልቷል። ጽድቅ የተገኘው እግዚአብሔር ኃጢአትን አይቶ እንዳላየ ስለሆነ፥ ወይም ፍርድን ስላቆየ ወይም ጽድቁን ስለለወጠ ሳይሆን፥ ሕግጋቱ ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ስለተሟሉ ብቻ ነው። የክርስቶስ ለሕግጋቱ ፍጹም ታዛዥ መሆንና ቅጣቱን የከፈለው ቤዛዊ ሞቱ ለጽድቃችን መሠረት ናቸው (ሮ 5፡9)። እግዚአብሔር ሰው ጨርሶ የማይቻለውን ፍጹም ታዛዥነት ስለሚጠይቅ፥ ጽድቅ በእኛ መልካም ሥራ ላይ እይመሠረትም። 

የጽድቅ ማግኛው መንገድ እምነት ነው (ሮሜ 3፡22፥ 25፥ 28፥ 30)። ይሁን እንጂ እምነት የጽድቅ መሠረት አይደለም። እምነት በእግዚአብሔር ጸጋ አማካይነት ኃጢአተኛ የነበረው አማኝ ዕዳ በክርስቶስ ጽድቅ የተከፈለበት መንገድ ነው። በምናምንበት ጊዜ እግዚአብሔር በክርስቶስ ያለውን ሁሉ ለእኛ ይቆጥርልናል፤ ከፍርድም ነጻ አድርጎ ጽድቃችንን በትክክለኛው መንገድ ያውጃል። መጽሐፍ ቅዱስ የጸደቅነው በማመናችን ነው አይልም፤ ይህ ከሆነ እንግዲያው ጽድቅ በሥራ ሊሆን ነው። እምነት የክርስቶስን ጽድቅ የምንቀበልበት መንገድ ነው። በዚህ አኳኋን በክርስቶስ ውስጥ ስለሆን ነው አማኙ የሚጸድቀው። በክርስቶስ ውስጥ ሲሆን፥ እግዚአብሔር ጽድቁን ያረጋግጥለታል፤ ይህ ነው ጽድቃችን ማለት። 

በክርስቶስ ማመን አዲስ ስፍራ ያሰጣል 

የሰማይ ዜግነትን (ፊልጵ. 3፡20)፣ በንጉሣዊው ክህነትና (1ኛ ጴጥ. 2፡5፥ 9)፥ በእግዚአብሔር ቤተሰብ አባልነትን (ኤፌ. 2፡19)፥ መንፈሳዊ ልደትን (ዮሐ. 3፡5)፥ በበጉ ሰርግ መታደምን (ራእይ 19፡7) እና ልጅነትን (ገላ. 4፡5) ይጨምራል። 

እነዚህ በእግዚአብሔርና እርሱን በሚያምኑት መካከል የተመሠረተውን አዲስ የቅርብ ግንኙነት ለማሳየት የቀረቡ ምሳሌዎች ናቸው። 

በ“አዲስ ልደት” እና “በማደጎ ልጅነት” መካከል ልዩነት እንዳለ ማስተዋል ያስፈልጋል። ሐዋርያው ዮሐንስ በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ የእግዚአብሔር ልጅ (በግሪክ “ፓይዲዮን” ወይም “ቴክኖን”0 ስለመሆናችን ብዙ ይናገራል። ይህ ግንኙነት የሚመሠረተው “እንደገና በመወለድ” ነው (ዮሐንስ ምዕራፍ 1 እና 2)። የሚያመለክተውም ልደቱንና የበሰለ ሰው እስከሚሆን ድረስ ያለውን እድገት ይሆናል። 

ሆኖም ሐዋርያው ጳውሎስ የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን (በግሪክ “ሁዮስ”) ወደ እግዚአብሔር ቤተሰብነት በማደጎ መስጠት” የሚል ሌላ ምሳሌ ይጠቅሳል። ይህም ቤተሰብነት፥ አንድ ሰው የራሱ ያልሆነን ሕጻን እንደ እውነተኛ ልጆቹ ባለመብትና ወራሽ ሲያደርገው የሚታይ ዓይነት አዲስ ግንኙነት ነው (የማደጎ ልጅ የሚባለው ዓይነት)። በዚህ አኳኋን የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ሁሉ፥ በልደቱ በእድገቱ፥ በብስለቱ ሁሉ ለልጅ የሚሰጠውን ማንኛውንም ጥቅሞችና መብቶች ከእግዚአብሔር ቤተሰብ ጋር ይካፈላል። ይህ ዓይነቱ ልጅነት ክርስቶስን ለሚቀበሉ ሁሉ የሚሰጥ አዲስ ሥልጣን ነው። 

የልጅነት መብት ውጤቶች፥ ከባርነት፥ ከሞግዚቶች፥ ከሥጋ ኃጢአት ነጻ መውጣት (ገላ. 4፡1-5፤ ሮሜ 8፡14-17) ሲሆን፥ ከዚህ መብት እንድንካፈልና እንድንረካበት የሚያደርገን ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ነው። 

የክርስቶስ ሞት ለአማኙ ውርስ ያስገኛል 

ይህም በክርስቶስ ሙሉ መሆንን (ቁላ. 2፡9-10)። መንፈሳዊ በረከትን ሁሉ ማግኘትን (ኤፌ. 1፡3)፥ ስለ መንግሥተ ሰማይ ውርስ እርግጠኛ መሆን (1ኛ ጴጥ. 1፡4) ያጠቃልላል። 

ለክርስትና ሕይወት አስፈላጊ የሆነው ብርታትና ኃይል በክርስቶስ ምት ተረጋግጧል 

የድነት (ደኅንነት) በረከት ከጸጋ በታች መሆንን (በኃጢአት እንዳንቀጥል ሮሜ 6፡14)፥ ከሕግ ነጻ መሆንን (2ኛ ቆሮ 3፡6-13)፥ በእያንዳንዱ የሥላሴ አካላት መሞላትን (ኤፌ. 4፡6፤ ገላ. 2፡20፤ 1ኛ ቆሮ. 6፡19) ይጨምራል። 

ከክርስቶስ ሞት የሚገኝ ሌላ በረከት ቅድስና ነው 

“መቀደስ” የሚለው ቃል፥ “መለየት” ማለት ሲሆን፥ ቅድስና ለክርስቲያን ሦስት ትርጉም አለው። አንደኛ፥ አማኙ የእግዚአብሔር ቤተሰብ ሆኖ ተለይቷል። ይህ ስፍራዊ ቅድስና ይባላል። አማኙ ከእግዚአብሔር ቤተሰብ እንደ አንዱ ተቆጠረ ማለት ነው። መንፈሳዊ ሁኔታ ምንም ይሁን ምን መንፈሳዊ ስፍራን ይመለከታልና ይህ ለማንኛውም አማኝ እውነት ነው። 1ኛ ቆሮ. 6፡11ን በማንበብ የአማኞችን ሥጋዊ ሁኔታ ያስታውሱ። ይህ ስፍራዊ ቅድስና በክርስቶስ ሞት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ዕብ. 10፡10 ግልጥ ያደርገዋል። 

ተግባራዊ (ልምምዳዊ) ቅድስና ደግሞ ሌላው ጉዳይ ነው። አማኞች የተለየን ስለሆንን፥ የተለየ ሰው ኑሮ እንኖራለን (1ኛ ጴጥ. 1፡16ን። በቅድስና የሚገኝ ስፍራን በተመለከተ ማንም ከማንም በላይ ቅዱስ አይደለም። አንድ አማኝ ከሌላው በቅድስና አኗኗሩ የሚበልጥ መሆኑን ግን መናገር ይቻላል። የአዲስ ኪዳን ምክሮች ሁሉ በመንፈሳዊ እድግት ሊታይ ስለሚገባው ተግባራዊ ቅድስና የተጻፉ ናቸው። 

በተጨማሪም ስፍራችንና ተግባራችን አንድ እስካልሆነ ድረስ ለእግዚአብሔር በፍጹም ቅድስና ተለይተናል ለማለት አንችልም። ይህ እውነት የሚሆነው ከርስቶስን ስናየውና እንደ እርሱ ስንሆን ብቻ ነው (1ኛ ዮሐ. 3፡1-3)። ስለዚህ አንዱ የቅድስና መልክ የወደፊት ቅድስና የሚባል ሲሆን፥ ይህም የትንሣኤ አካል በመልበስ ከሌሎች ቅዱሳን ጋር በሙሉ ክብር የምንገኝበት ጊዜ ነው (ኤፌ. 5፡26-273 ይሁዳ 24-25)። 

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading