ኢየሱስ በሁሉም ቦታ ይገኛል 

ጥያቄ፡- ሀ) መዝሙር 139፡7-10 አንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች መሠረት እግዚአብሔር የት ነው? ለ) ማቴዎስ 18፡20፤ 28፡20፤ ዮሐንስ 14፡23 አንብቡ። እንደ እነዚህ ጥቅሶች እገላለጽ ኢየሱስ የት ነው? 

እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ስፍራ በማንኛውም ጊዜ በሙሉ ማንነቱ ይገኛል። መዝሙር 139 እኛ ሰብአዊ ፍጡራን የትም ብንሄድ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ቀድሞ እዚያ እንደሚገኝ ይነግረናል። ወደ ሰማይ ብንወጣ፥ ወደ ጥልቁ ምድር ብንወርድ እግዚአብሔር እዚያም መኖሩን ያስታውሰናል። ወደ ምሥራቅ ወይም ወደ ምዕራብ፥ ወደ ሰሜን ወይም ወደ ደቡብ ብንሄድም እግዚአብሔር እዚያ አለ። ስለዚህ እግዚአብሔር በሁሉም ስፍራ ይገኛል። 

ኢየሱስም ቢሆን በተመሳሳይ ሁኔታ በየትም ስፍራ ይገኛል። ማቴዎስ 18፡20 ሁለት ወይም ሦስት አማኞች በሚሰበሰቡበት ስፍራ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር እንደሚሆን ያስረዳል። በዓለም ውስጥ በየትም ስፍራ በሚሰበሰቡ አማኛች መካከል በአንድ ጊዜ ይገኛል። ኢየሱስ በየትኛውም ስፍራ የሚገኝ ከሆነ በአማኞቹም መካከል ይገኛል። በማቴዎስ 28፡20 ላይ አማኞች ወንጌሉን እስከ ዓለም ዳርቻ በሚወስዱበት ጊዜ እንኳን አብሮአቸው እንደሚሆን ተስፋ ሰጥቶአቸዋል። በዚህ ምድር ላይ ወዴትም ይሂዱ፥ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ይሆናል። በዮሐንስ 14፡23 ላይ እግዚአብሔር አብ በየትኛውም ስፍራ ይሁን ከሚወዳቸው ሁሉ ጋር እንደሚሆን ኢየሱስም እንዲሁ ከሚወዳቸው ሁሉ ጋር እንደሚሆን ተስፋ ሰጥቶአል። እግዚአብሔር በየትኛውም ስፍራ እንደሚገኝ ሁሉ፥ ኢየሱስም በየትኛውም ስፍራ ይገኛል። 

መደምደሚያው፡- ኢየሱስ አምላክ ነው! 

ጥያቄ፡- የኢየሱስ በአንድ ጊዜ በሁሉም ስፍራ መገኘቱ እንዴት ያጽናናችኋል፣ ቢያንስ ሁለት መንገዶችን ጻፉ። 

ኢየሱስ በሁሉም ስፍራ ስለሚገኝ በብዙ መንገድ ልንጽናና እንችላለን፡፡ በሩቅ ስፍራ ከሚገኙ ወዳጆቻችንና ዘመዶቻችን ዘንድ ተገኝተን ልንረዳቸው በማንችልበት ሁኔታ ኢየሱስ እነርሱ ዘንድ ተገኝቶ በሚያስፈልጋቸው ያገለግላቸዋል፡፡ እንደዚሁም ወደ አንድ አዲስ ስፍራ በምንሄድበት ጊዜ ቦታውን ሊያዘጋጅልን እርሱ ከእኛ ቀድሞ እዚያ መገኘቱን ማወቅ ያጽናናናል። በእምነታችን ምክንያት ከምንወዳቸው ወዳጆቻችን ብንለይም፤ በምንሄድበት ሁሉ አብሮን እንደሚሆን መረዳታችን ኃይልንና ብርታትን ይሰጠናል። 

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading