የኢየሱስ ትንሣኤና ዕርገት (ሉቃስ 24፡1-53)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የኢየሱስ ትንሣኤ ወሳኝ እንደሆነ የምታስበው ለምንድን ነው? ለ) 1ኛ ቆሮ. 5፡12-32 አንብብ። ጳውሎስ ትንሣኤ አስፈላጊ ነው የሚለው ለምንድን ነው? ሠ) በትንሣኤው ላይ ብዙ ትኩረት እየሰጠን ትንሣኤውን እምብዛም የማናነሣው ለምንድን ነው?

ከታሪክ ምሑሩ አመለካከት አንጻር፣ የኢየሱስ ትንሣኤ በታሪክ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ቀደም ሲል ሰዎች በመስቀል ላይ ሲሞቱ ኖረዋል። ከእነዚህም አንዳንዶቹ የእግዚአብሔር ሕዝብ መሪዎች ናችሁ ተብለው ነበር የተሰቀሉት። ነገር ግን ከኢየሱስ በስተቀር ያለ ሌላ አካል እገዛ ከሞት የተነሣ ማንም ሰው በታሪክ ውስጥ የለም።

በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ የኢየሱስ ስቅለትና ትንሣኤ ሁለቱም አስፈላጊዎች ነበሩ። በስቅለቱ ኢየሱስ የኃጢአት ዋጋችንን ከፍሏል። ትንሣኤው ደግሞ ለአያሌ ምክንያቶች አስፈላጊ ነበር። አንደኛው፥ እግዚአብሔር ኢየሱስ ያቀረበውን የኃጢአት መሥዋዕት እንደ ተቀበለ ያረጋግጣል። እግዚአብሔር በኢየሱስና በመሥዋዕቱ ደስ ባይሰኝና የኃጢአት መሥዋዕቱ በቂ ባይሆን ኖሮ፣ ኢየሱስን ከሞት አያስነሣውም ነበር። ሁለተኛው፣ ትንሣኤው የእግዚአብሔር ልጆች ሁሉ ትንሣኤ በኩር ነው። የክርስቶስ ትንሣኤ እግዚአብሔር እኛንም ከሞት እንደሚያስነሳን የሰጠን የተስፋ ቃል ነው። የኢየሱስ ትንሣኤ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ የክርስትና አስተምህሮ ሁሉ በዚህ እውነት ላይ ይመሠረታል። ለዚህ ነው ጳውሎስ ኢየሱስ ከሞት ካልተነሣ እምነታችን ከንቱ ነው ያለው (1ኛ ቆሮ. 5፡12-19)።

ከሌሎቹ የወንጌላት ጸሐፊዎች በላይ ሉቃስ በኢየሱስ ትንሣኤ ላይ አትኩሯል። ሌሎች የወንጌል ጸሐፊዎች በትንሣኤው እሑድ ጠዋት ምን እንደ ተፈጸመ አልገለጹም። ሉቃስ ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ ያቀረባቸው ታሪኮች ሁሉ የትንሣኤውን እርግጠኝነት የሚያስገነዝቡ ናቸው። ትንሣኤው እውነተኛ ታሪካዊ ክስተት እንጂ አፈ ታሪክ አይደለም። ከሞት የተነሣውን ጌታ የተመለከቱ የዐይን ምስክሮች ገና አልሞቱም። ስለሆነም አንዳንድ ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሰዎች ቢሳለቁም (የሐዋ. 17፡32)፣ ኢየሱስ በእርግጥ ከሞት ተነሥቷል!

ሀ. ኢየሱስ ከሞት እንደ ተነሣ መላእክት ለሴቶቹ ነገሯቸው (ሉቃስ 24፡1-12)። ሉቃስ ሴቶች በኢየሱስ አገልግሎት ውስጥ ስለነበራቸው ትልቅ ድርሻ፥ ትኩረት ሰጥቶ መዘገቡን ቀደም ብለን ተመልክተናል። እሑድ ማለዳ ለኢየሱስ አካል ልዩ ቅመሞች ይዘው የሄዱት ሴቶቹ ነበሩ። ነገር ግን መቃብሩ ባዶ ሆኖ ሲያገኙት ደነገጡ። ሁለት መላእክት ከሞቱና ከትንሣኤው በፊት የነገራቸውን አስታወሷቸው። ሴቶቹ ከመላእክት የሰሙትን ለደቀ መዛሙርቱ ሲናገሩ ሊያምኗቸው አልቻሉም። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ራሱ አይቶ ሊያረጋግጥ ፈለገ። ወደ ባዶው መቃብር ውስጥ ሮጦ ቢገባም፣ የተከሰተውን ነገር ሊገነዘብ አልቻለም።

በታሪክ ሁሉ የማያምኑ ሰዎች የትንሣኤውን እውነት ለመካድ የሚያቀርቡት ምክንያት ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን ለማግኘት ከመጠን በላይ ስለ ተመኙ እርሱን ሳይሆን ራእይ ነው ያዩት የሚል ነው። ኢየሱስ እንዲሞት ስላልፈለጉ የትንሣኤውን ሕልም እንዳዩ ይናገራሉ። ሕልሙ በጣም ጠንካራ ስለነበር ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ከሞት ተነሥቷል ብለው አሰቡ። ነገር ግን ሉቃስና ሌሎች ጸሐፊዎች ያቀረቡት አሳብ ከዚህ ፍጹም የሚቃረን ነው። ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ኢየሱስ ከሞት ይነሣል ብሎ የጠበቀ አልነበረም። መላእክትና የዐይን ምስክሮች ቢነግሯቸውም እንኳ ለእነርሱ ተገልጦ አሳባቸውን ከመለወጡ በፊት ተነሥቷል ብለው አላመኑም ነበር። የደቀ መዛሙርቱን የአመለካከት መለወጥና ኢየሱስ ከሞት የተሣ ጌታ ነው እንዲሉና ራሳቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ ያደረጋቸውን ነገር ሊያብራራ የሚችለው ትንሣኤው ብቻ ነው።

ለ. ኢየሱስ በኤማሁስ መንገድ ለሁለት ደቀ መዛሙርት ታየ (ሉቃስ 24፡13-35)። በዚያን እሑድ ዕለት ሁለት ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሩሳሌም 11 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ወደምትገኘው ወደ ኤማሁስ በመጓዝ ላይ ነበሩ። ስለ ኢየሱስ ስቀለትና ስለ ትንሣኤው የሰሙት ነገር አእምሯቸውን እያናወጠው ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ በመካከላቸው ተገኘ። ኢየሱስን ለመለየት ያልቻሉት በሁለት ምክንያት ሊሆን ይችላል። አንደኛው፣ ኢየሱስ እንደ ሞተ እርግጠኞች በመሆናቸው በመካከላቸው እንደሚገኝ አልጠረጠሩም ነበር። አእምሯቸው ከእነርሱ ጋር የሚነጋገረው ኢየሱስ እንደሆነ እንዳይቀበሉ አድርጓቸዋል። ሁለተኛው፣ ምናልባትም የኢየሱስ የትንሣኤ አካል በብዙ መንገዶች ቀደም ሲል ከሚያውቁት ተለይቶባቸው ይሆናል። የቀድሞውን የሚመስሉና የተለዩም ነገሮች ነበሩ።

በዚህ ታሪክ ሉቃስ ኢየሱስ ሞቱና ትንሣኤው የእግዚአብሔር ዕቅድ መሆኑን እንዴት እንዳረጋጋጠ ገልጾአል። መላእክቱ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ስለተነበየው ጉዳይ ለሴቶቹ እንደተናገሩት ሁሉ፣ ኢየሱስ እነዚህንም ሰዎች ወደ ብሉይ ኪዳን ታሪኮች በመውሰድ ሁሉም ነገር እንዴት እርሱን፣ ሞቱንና ትንሣኤውን እንደሚያመለክት አስነዘባቸው። ኢየሱስ የብሉይ ኪዳን መልእክት ማዕከላዊ ነው። እነዚህ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን ያወቁት ለምግቡ እግዚአብሔርን በማመስገን ከጸለየ በኋላ ነበር።

ሐ. ኢየሱስ ለሁሉም ደቀ መዛሙርት ታየ (ሉቃስ 24፡36-49)። የማያምኑ ሰዎች ለኢየሱስ ትንሣኤ የሚያቀርቡት ሌላው ማብራሪያ ደቀ መዛሙርቱ መንፈስን እንዳዩ የሚያስረዳ ነው። የኢየሱስ መንፈስ ለደቀ መዛሙርቱ የታየበትን ሁኔታ ልክ የሳኦል መንፈስ ለሳሙኤል ከታየበት ጋር ያዛምዳሉ (1ኛ ሳሙ. 28)። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ እንዳልሆነ በዚህ ታሪክ ውስጥ እንመለከታለን። በመጀመሪያ ደቀ መዛሙርቱ ድንገት በመካከላቸው ቆሞ ሲያዩት መንፈስን እንዳዩ ነበር ያሰቡት። ኢየሱስ ግን የትንሣኤ አካሉን ዳስሰው መንፈስ እንዳልሆነ እንዲያረጋግጡ ነገራቸው። ይህ አንዳንዶችን ሊያሳምን ባለመቻሉ ምግብ ለመብላት ማንነቱን ሊያሳያቸው ሞከረ። መስቀሉና የኢየሱስ ትንሣኤ ቀደም ብለው የተተነበዩ መሆናቸውን ለደቀ መዛሙርቱ ለማሳየት ሉቃስ ኢየሱስ ብሉይ ኪዳንን የጠቀሰበትን ሁኔታ ለሁለተኛ ጊዜ አመልክቷል።

ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የመጨረሻውን ትእዛዝ ሰጣቸው። አገልግሎታቸውን በአገራቸው ወይም በነገዳቸው ሳይወስኑ ወደ ዓለም ሁሉ እንዲሄዱ አዘዛቸው። ሰዎች ንስሐ ገብተው በኢየሱስ በማመን የኃጢአት ይቅርታ እንዲያገኙ ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ መስበክ ነበረባቸው። ነገር ግን ታላቁን ትእዛዝ ተግባራዊ የሚያደርጉበትን ኃይል ከየት ያገኛሉ? ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ እንደሚወርድላቸው ቃል ገብቷል። ይኸው መንፈስ ቅዱስ እስኪመጣ ድረስ አገልግሎታቸውን እንዳይጀምሩ ተነግሯቸዋል። የሐዋርያት ሥራ የሚጀምረው የሉቃስ ወንጌል ካቆመበት ነው። የመንፈስ ቅዱስ መሰጠት፣ ደቀ መዛሙርቱ የኢየሱስን ትእዛዝ ተቀብለው ወንጌሉን ወደ ሮም ግዛቶች ሁሉ መውሰዳቸው በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ተብራርቷል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ለሆንን ሰዎች ይህ ትእዛዝ ዛሬም ተግባራዊ ሊሆን ይገባዋል። ዛሬ ከ2000 ዓመታት በኋላ፣ የኢየሱስን ወንጌል ወደ ሁሉም ሕዝቦችና ብሔሮች ዘንድ አላዳረስንም። ራስ ወዳድነት የአብዛኞቹን ክርስቲያኖችና አብያተ ክርስቲያናት ሕይወት ማበላሸቱን እንደቀጠለ ነው። ከቤተሰቦቻችንና ከቤተ ክርስቲያናችን፣ ሳንነጠል በአገራችን ተደላድለን ለመኖር እንፈልጋለን። ይህ ግን የኢየሱስን ልብ ያስጨንቃል። እርሱ ወደ ሰማይ የሄደው እኛ የምሥራቹን ቃል ሰምተን የእግዚአብሔር ልጆች እንሆን ዘንድ ነው። እኛ ግን ከአገራችን ወጥተን ለሌሎች ወንጌልን ለመናገር አንሻም። ቤተ ክርስቲያን በወንጌሉ ብርሃን ደስ ብትሰኝም፣ ብዙውን ጊዜ ወንጌሉን ለሌሎች ለማዳረስ የሚያስፈልገውን ዋጋ ለመክፈል አንፈልግም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖችና አብያተ ክርስቲያናት ራስ ወዳድ በመሆን መልካሙን የምሥራች ወደ ዓለም ሁሉ እንዳናዳርስ የሚጠይቀውን የኢየሱስን ትእዛዝ ችላ ሊሉ የሚችሉባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) ስለ ቤተ ክርስቲያንህ አስብ። ቤተ ክርስቲያንህ ራስ ወዳድነትን ለመቆጣጠርና ወንጌሉን ወዳልሰሙት ለማድረስ ምን እያደረገች ነው? ሐ) ይህንን ለተከታዮቹ ሁሉ የተሰጠውን የኢየሱስን ትእዛዝ ለመጠበቅ ምን እያደረግህ ነው?

መ. ኢየሱስ ወደ ሰማይ ዐረገ (ሉቃስ 24፡50-53)። ቀጥሉ የተከሰተውን ነገር በዚህ ወንጌልና በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የሚተርክልን ሉቃስ ብቻ ነው። ኢየሱስ ለ40 ቀናት ያህል ለደቀ መዛሙርቱ ከታየ በኋላ ሁሉም እያዩ ወደ ሰማይ ወጣ። የኢየሱስ ምድራዊ ታሪክ በዚሁ ይጠናቀቃል። ነገር ግን በሰማይ ሆኖ በደቀ መዛሙርቱ ሕይወት ውስጥ መሥራቱን እንደሚቀጥል የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ያስረዳል። ይሁንና ኢየሱስ አንድ ቀን ወደ ምድር ተመልሶ ይመጣል። ምጽአቱ ምንኛ የተለየ ነው! ያን ጊዜ የሚመለሰው እንደ ሕጻን ልጅ ወይም አምላክነቱን ደብቆ አይደለም። ኢየሱስ እንደ ድል እድራጊና ገዥ ንጉሥ በክብር አሸብርቆ ይመለሳል። አሁን እየተጨነቅንና እየተጨቆንን እንገኝ ይሆናል። ነገር ግን ኢየሱስ በሚመጣበት በዚያን ታላቅ ቀን የዓለም ክፋትና መከራ ሁሉ ያበቃል። እነሆ ተስፋችን ይህ ነው። በደስታ እንድንኖር የሚያደርገንም ይኸው ነው። ነገር ግን አሁን ከሞት የተነሣው ኢየሱስ ምን እየሠራ ነው? ለድሀውና ለተጨነቀው ርኅራኄን እያሳየ በምድር ላይ የተመላለሰው ኢየሱስ አሁን በሰማይ በሊቀ ካህንነት እንደሚያገለግል የዕብራውያን መልእክት ይነግረናል። አሁንም ርኅራኄው አልተለየውም። ምንም እንኳን የሚያደርገውን ነገር ባናይና ባንግዘብ እንኳ፥ ይህም ደግሞ ለደስታችን ምክንያት ይሆንልናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ኢየሱስ በእኛ ፈንታ በሰማይ መሥራቱ የሚያበረታታትን ለምንድን ነው? ለ) በሕይወትህ፣ በአገርህ ወይም በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚከሰቱ ነገሮች እየተፈታተኑህ ሳለ፥ ኢየሱስ የዘላለም መንግሥት ይዞ በክብር የመመለሱ ነገር በተስፋ እንድትጓዝ የሚያደርግህ እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ሉቃስ 22፡39-23፡56

 1. እግዚአብሔር ከመስቀሉ እንዲያድነው ኢየሱስ ጸለየ (ሉቃስ 22፡39-46)

ሉቃስ ብዙውን ጊዜ የኢየሱስን ፍጹም ሰው መሆን አጉልቶ ያሳያል። ኢየሱስ መስቀሉን የተሸከመው ኃይሉን ሁሉ እንደተላበሰ አምላክ ሳይሆን፤ በሁላችንም ላይ በሚያንዣብብ የፍርሃት ስሜት ነበር፡፡ ደቀ መዛሙርት በዘመናት ሁሉ በኢየሱስ በማመናቸው ምክንያት ለሞት በሚዳረጉበት ጊዜ ሁሉ ሲያስጨንቃቸው ይኖራል። ስለሆነም ፍርሃት ተፈጥሯዊ የሰው ልጆች ስሜት ነው። ዋናው ነገር ፍርሃትን የምንቋቋምበት መንገድ ነው ኢየሱስ ከመስቀል ሞት ለመዳን እንደ ጸለየው እኛም ይህንኑ ልናደርግ እንችላለን። ነገር ግን ኢየሱስ ራሱን ለእግዚአብሔር ፈቃድ አሳልፎ እንደ ሰጠ ሁሉ፥ እኛም ይህንኑ ልናደርግ ይገባናል። አንዳንድ ጊዜ በዚህ መንገድ ልንተርፍ እንችላለን። ሌላ ጊዜ ደግሞ ልንሞት እንችላለን። እግዚአብሔር ለልጁ የ«አይሆንም» መልስ እንደ ሰጠው ሁሉ፣ ለእኛም ይህንኑ ሊያደርግ ይችላል። ነገር ግን እግዚአብሔር መልአኩን በመላክ፥ (ሉቃስ እንደ ጠቀሰው) ኢየሱስን እንዳበረታታው፣ እኛንም በጨለማው ሰዓት እንደሚያበረታታን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።

ሉቃስ የኢየሱስን ሥቃይ ለማሳየት ሲል፥ ላቡ እንደ ደም መውረዱን ገልጿል። ይህም ጣታችንን በምንቆረጥበት ጊዜ ደም በፍጥነት እንደሚወርድ ሁሉ፣ ኢየሱስም ከፍተኛ ሥቃይ ላይ ላለነበረ ብዙ ላብ እንደ ወረደው የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አንዳንድ ምሑራን ሉቃስ ሊያስተላለፍ የፈለገው መልእክት ከዚህ በላይ እንደሆነ ያስባሉ። በሰዎች ላይ ከፍተኛ ሥቃይ በሚደርስበት ጊዜ አነስተኛ የደም ሥሮች የሚበጠሱበት ሁኔታ ያጋጥማል። ስለሆነም ኢየሱስ በሚጸልይበት ጊዜ ደሙ ከላቡ ጋር አብሮ ይወርድ እንደነበር ይገልጻሉ።

ሉቃስ በተለይ በስደት ጊዜ ወደ ኋላ መመለስ እንደሌለብን ያስጠነቅቀናል። ጸሎት እጅግ የሚያስፈልገን በዚህ ጊዜ ነው። በጸሎት ጊዜ የተጋረጠብንን ፈተና የምናሸንፍበትን ኃይል እናገኛለን።

 1. የኢየሱስ መታሰር፣ መመርመር፣ መሰቀልና መሞት ሉቃስ 22፡47-23፡56)

ሉቃስ ስለ ኢየሱስ መሰቀል ያቀረበው ታሪክ ከሌሎቹ ተመሳሳይ ወንጌላት ጋር ተመሳሳይ ነው። ቀደም ሲል በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ የተሟላ ማብራሪያ ስላቀረብን፣ በዚህ ክፍል ክስተቶቹን ጠቅለል አድርጎ ከማቅረብ ያለፈ ነገር አናደርግም። ሉቃስ ስለ ኢየሱስ ሞት እንዳንድ ጠቃሚ እውነቶችን ይገልጻል።

ሀ. ሉቃስ በኢየሱስ ሞት በተፈጸመው የእግዚአብሔር ፈቃድ ላይ ያተኩራል። ሉቃስ ሰባት ጊዜ ኢየሱስ “ሊሞት ይገባ ነበርና” የሚል ዐረፍተ ነገር ጠቅሷል (ሉቃስ 9፡22፤ 13፡33፤ 17፡25፤ 22፡37)።

ለ. ሉቃስ በተጨማሪም ኢየሱስ መስቀል ከፊቱ ሆኖ እየታየው እያለ እንኳ ሁልጊዜ ለሌሎች የሚያስብ አዳኝ እንደሆነ አመልክቷል። ወደ መስቀል በሚወስደው መንገድ ላይ ሲያለቅሱ ለነበሩት ሴቶች አዝኖ ነበር። በመስቀሉ ላይ ለነበረው ሌባ ራርቶ ነበር። ለሰቀሉት ሰዎችም ስለራራ፣ እግዚአብሔር ይቅር እንዲላቸው ጸልዮአል። የሃይማኖት መሪዎች፣ «ሌሎችን አዳነ፡ እስኪ አሁን ራሱን ያድን» እያሉ ተሳለቁበት። ይህ ኢየሱስ ሁልጊዜ እንዴት ራሱን ለሌሎች አሳልፎ እንደሚሰጥ ያመለክታል። እነርሱ ያልተረዱት ነገር ቢኖር ኢየሱስ በሞት ራሱን አሳልፎ በመስጠት የሰዎች ዋንኛ አዳኝ ለመሆን እንደ በቃ ነው።

ሐ. ሉቃስ ኢየሱስ ምንም ኃጢአት እንዳልሠራ ገልጾአል። ሉቃስ ሦስት ጊዜ ኢየሱስ ንጹሕ መሆኑን መስክሯል፡፡ ሄሮድስ፣ በመስቀል ላይ ተሰቅለው ከነበሩት ወንበዴዎች አንዱ፤ እንዲሁም የሮሙ የመቶ አለቃ ኢየሱስ ኃጢአት የሌለበት ሰው መሆኑን መስክረዋል። እርሱ ሞት የሚገባው ወንጀለኛ አልነበረም፡፡

መ. ሉቃስ የሀብታሞችንና የሃይማኖት መሪዎችን አመለካከት ከተራ ሰዎች ጋር ያነጻጽራል። ሉቃስ ለኢየሱስ ሞት በዋነኛነት ተጠያቂ ያደረገው የአይሁድ አለቆችን፣ ሀብታሞችና ኀይል ያላቸውን ሰዎች ነው። ይህም በመጽሐፉ ውስጥ ሀብታሞች ምን ያህል የክፋት ምንጭ እንደሆኑ ከሚያሳይበት ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል። ኢየሱስ እንዲሞት የገፋፉት የሃይማኖት መሪዎች ናቸው። በመስቀል ላይ በነበረ ጊዜ ኢየሱስን ይሳደቡ የነበሩትም እርሱው ናቸው። በአንጻሩም ኢየሱስ ወደ መስቀል ሞት በወሰድበት ጊዜ ሴቶች ያለቅሱለት ነበር። ሌሎችም ሰዎች የመስቀል ላይ ሥቃዩን ቆመው ከተመለከቱ በኋላ፥ በኀዘን ደረታቸውን እየመቱ ወደ ቤታቸው ተመለሱ።

ሠ. ሉቃስ እንደ ማቴዎስና ማርቆስ ደቀ መዛሙርቱን ብዙም አላብጠለጠላቸውም። ደቀ መዛሙርቱ በኅዘን ምክንያት መተኛታቸውን እንጂ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ሦስት ጊዜ በእንቅልፍ መሸነፋቸውን አልገለጸም። ሉቃስ ደቀ መዛሙርቱ እንዴት ከኢየሱስ እንደ ራቁ አልገለጸም። ነገር ግን ከሴቶች ጋር ሆነው በርቀት ስቅለቱን ይመለከቱ እንደ ነበር ጽፎአል።

 1. የኢየሱስ አልፎ መሰጠትና መታሰር (ሉቃስ 22፡47-53)።

ኢየሱስ ይህንን የመታሰርና የመሰቀል ጊዜ ጨለማ የሚነግሥስበት ጊዜ ሲል ጠርቶታል። እግዚአብሔር ሰይጣን ኢየሱስን ለሞት አሳልፎ እንዲሰጠው ፈቀደለት፡፡ ሰይጣን ለጊዜው የሥልጣኑን በትር የጨበጠ ይመስላል። ሰዎች ሁሉ የከፋ ተግባር እንዲያደርጉ በማነሣሣት፣ ደቀ መዛሙርቱ እንዲሸሹ፣ የሃይማኖት መሪዎችና አይሁዶች ኢየሱስን አንቀበልም በማለት እንዲወስኑና ኢየሱስ አልፎ እንዲሰቀል እንዲጠይቁ፣ ጲላጦስ ድፍረቱን እንዲያጣ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል። ነገር ግን ሰይጣን ክርስቶስን አሸንፍሁበት ባለው መስቀል አማካይነት፥ እግዚአብሔር ዓለምን አድኗል። ሰይጣን ከሁሉም የከፋ የጭካኔ ተግባር ሊፈጽምብን ቢችልም፣ ሊያደርግ የሚችለው ነገር ቢኖር የእግዚአብሔርን ሥራ ማፋጠን ነው! አምላካችን ምንኛ አስደናቂ ነው!

የውይይት ጥያቄ፡- ) ሰይጣን በአንተ ወይም በቤተ ክርስቲያን ላይ የጨለማን ጊዜ ሲያመጣ የተመለከትከው እንዴት ነው? ለ) እነዚህ የጨለማ ጊዜዎች የእግዚአብሔርን ዕቅዶች እንደ ማፍረስ የበለጠ የሚያጠናክሩ ሆነው የተገኙት እንዴት ነው? ሐ) ይህ ስለ እግዚአብሔር ሉዓላዊነት ምን ዐይነት ልበ ሙሉነትን ይሰጠናል?

 1. ጴጥሮስ ኢየሱስን ካደ (ሉቃስ 22፡54-65)።

ጴጥሮስ ለኢየሱስ ሰይፍ ይዞ ሊዋጋና ሊሞት መድፈሩ ይታወሳል። በኋላ ግን አንዲት ሴት ባደረገችው ጥቆማ እጅግ ፈራ። አንዳንድ ጊዜ በሌሎች ፊት ምስክርነታችንን ከመስጠት ይልቅ ለእምነታችን መሞቱ ቀላል ነው። ሉቃስ ሁለቱም ማለትም ጴጥሮስና ኢየሱስ በአንድ ግቢ ውስጥ እንደ ነበሩ ገልጾአል። ጴጥሮስ ለሦስተኛ ጊዜ ሲክደው ኢየሱስ ዘወር ብሎ ተመለከተው። ኢየሱስ ምን እያሰበ ይሆን? ኀዘን? ይቅርታ? ኩሩው ጴጥሮስ ደካማነቱን በመገንዘብ ልቡ ተሰበረ። እግዚአብሔር ጴጥሮስን ለቤተ ክርስቲያኑ መታነጽ መሠረት አድርጎ የሚጠቀመው በራሱ ላይ የነበረው ልበ ሙሉነት ከተወገደ በኋላ ነበር።

 1. ኢየሱስ በአይሁዶች ፊት ተመረመረ (ሉቃስ 22፡66-71)።

ከሌሎች ወንጌሎች በተቃራኒው፣ ሉቃስ በአይሁዶች ፊት ስለተደረገው ምርመራ ብዙም የገለጸው አሳብ የለም። ሉቃስ ታሪኩን ያጠቃለለው ኢየሱስ በክብር በእግዚአብሔር ቀኝ የሚቀመጥ መለኮታዊ «የሰው ልጅ» እንደሆነ በመግለጽ ነው። ይህ አሳብና ኢየሱስ በግልጽ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ማለቱ አይሁዶች በኢየሱስ ላይ የስቅላት ጥያቄ እንዲያቀርቡ አነሣሥቷቸዋል። ፍትሐዊ ባልሆነ ምርመራ፣ ወንጀለኛ ተብሎ ተከሰሰ።

 1. ኢየሱስ በጲላጦስ ፊት (ሉቃስ 23፡1-25)።

ሉቃስ በጲላጦስ ፊት ስለተደረገው ምርመራ ትኩረት ሰጥቷል። ለአንድ ሰው፥ ኢየሱስ እንዳደረገው፥ እኔ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ ብሎ ማለቱ፥ የሮም መንግሥትን እንደ መክዳት ይቆጠርበታል። ጲላጦስ ግን የሃይማኖት መሪዎቹን ቅንዓት ከተመለከተ በኋላ፥ የኢየሱስ መንግሥት መንፈሳዊ እንደሆነ ተገነዘበ። ስለዚህም ጲላጦስ ኢየሱስ ምንም ጥፋት እንደሌለበት ተናገረ። ቢሆንም ግን ጲላጦስ ፈርቶ ነበር። ኢየሱስን ወደ ሄሮድስ ለፍርድ በመላክ አስቸጋሪውን ሁኔታ ለማለፍ ሞከረ። ኢየሱስ ሄሮድስ አንቲጳስ ይገዛ በነበረው የገሊላ አውራጃ ውስጥ ይኖር ነበር። ሉቃስ ቀደም ሲል ሄሮድስ በተደጋጋሚ ከኢየሱስ ጋር ለመገናኘት ጥረት ሲያደርግ እንደ ነበር ገልጾአል። በዚህ ጊዜ ተከሶ እፊቱ ሊቀርብ ንጉሡ የተመኘውን አገኘ። ኢየሱስ ግን መልስ ሊሰጠው አልፈለገም። ሄሮድስ ያደረገው ነገር ቢኖር ኢየሱስን፥ ንጉሥ እያለ ጠርቶ በእርሱ ላይ መሳለቅ ነበር። ከዚያም ኢየሱስን ወደ ጲላጦስ መልሶ ሰደደው። እርሱም ኢየሱስን ፈራው። ጲላጦስና ሄሮድስ ሁለቱም ኢየሱስን ስለፈሩት በአንድ ወቅት ባላንጦች የነበሩት ገዥዎች ፍርሃቱ በመታቸው ሁኔታ ወዳጅነትን መሠረቱ። ኢየሱስ ዓለማዊ ንጉሥ ከሆነ ሥልጣኔን ይነጥቀኛል ብሎ ይፈራ የነበረው ሄሮድስ እንኳ የኢየሱስን ንጽሕ እንደሆነ ተገንዝቧል (ሉቃስ 23፡5)።

ኢየሱስ ተመልሶ ሲመጣ ጲላጦስ ኢየሱስን ነፃ ለማድረግ ሌላ አማራጭ ፈለገ። አይሁዶች በርባን የተባለውን ወንጀለኛ እንደሚጠሉት ያውቅ ነበር። ስለሆነም ከበርባን ይልቅ ኢየሱስ እንዲለቀቅ እንደሚፈልጉ አልተጠራጠረም። አይሁዶች ኢየሱስ እንዲሞትና በርባን እንዲለቀቅ በጠየቁ ጊዜ ሳይደነቅ አልቀረም። ከዚያም ጲላጦስ ሌላ ነገር አሰበ። ኢየሱስ ከፊታቸው ሲገረፍ ቢያዩ ልባቸው ይራራ ይሆናል የሚል ግምት አደረበት። እንዳሰበው ግን አልሆነም። ቢያንስ ሦስት ጊዜ ጲላጦስ ኢየሱስ በደል የሌለበት ንጹሕ ሰው መሆኑን ደጋግሞ ቢያውጅም፣ በመጨረሻ ፍርሃቱ ስላሸነፈው ለኢ-ፍትሐዊ ፍርድ አሳልፎ ሰጠው። ከዚያም ኢየሱስ ይሰቀል ዘንድ ተስማማ።

ብዙውን ጊዜ የመንግሥትና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጲላጦስ በተያዘበት ወጥመድ ውስጥ ይያዛሉ። ሰዎችን በመፍራት ለፍትሕ አልባ አመራር ስፍራ ይለቅቃሉ። ይህም የእግዚአብሔር የጽድቅ መሣሪያ እንደ መሆን፥ የሰይጣን የኃጢአት መሣሪያ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ጳውሎስ እንደገለጸው ሰዎችን ፈርቶ ለፍትሕ አልባ አመራር ስፍራ መልቀቅ የሰዎች ባሪያ መሆን ነው (ገላ. 1፡10)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ሰዎችን በመፍራቱ እንዴት ለፍትሕ አልባ አመራር ፈቃዱን እንደ ሰጠ ከገጠመህ ሁኔታ በመነሣት አብራራ። ለ) አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ሰዎችን በመፍራቱ ኃጢአት እንዲራባ የፈቀደው እንዴት ነው?

 1. የኢየሱስ መሰቀል፣ መሞትና መቀበር (ሉቃስ 23፡26-56)።

አይሁዶች ሁሉ በኢየሱስ መሰቀል ተስማምተው ነበር? አልነበረም። ሉቃስ ሴቶች ለኢየሱስ ራርተው እንዳለቀሱለት ገልጾአል። ኢየሱስ በዚህ ጊዜ ሮማውያን ከ40 ዓመት በኋላ ኢየሩሳሌምን በሚደመስሱበት ጊዜ ስለሚሆነው መከራ አስጠንቅቋቸዋል።

ሉቃስ ሌሎች የወንጌላት ጸሐፊዎች ያልተጠቀሙባቸውንና ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሆኖ የተናገራቸውን አያሌ ቃላት በመጽሐፉ ውስጥ አስፍሯል። ኢየሱስ በመስቀል ላይ የቁጣ፣ የጥላቻ ወይም የዕርዳታ ጥሪ አላቀረበም። በከፍተኛ ሥቃይ ውስጥ ሆኖ እየማቀቀ ሳለ እግዚአብሔር ሕዝቡን ይቅር እንዲል ነበር የጠየቀው። ብዙም ሳይቆይ ሌላው ሰማዕት እስጢፋኖስም ተመሳሳይ የይቅርታ ጥያቄ አቅርቧል (የሐዋ. 7፡60)። በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ በደል እየፈጸሙ ሳለ እንኳ ለሰዎች የይቅርታ ጸሎት እንድናቀርብ ኢየሱስ ምሳሌ ትቶልናል።

ሉቃስ በመስቀል ላይ በነበሩት ሁለት ሌቦችም ላይ ትኩረት ሰጥቷል። ከሁለቱ ወንበዴዎች አንደኛው ከሕዝቡ ጋር አብሮ በኢየሱስ ላይ ሲሳለቅ፣ ሌላው ግን ገሥጾታል። ሁለተኛው ወንበዴ ወንጀለኛ በመሆኑ የሞት ፍርድ እንደሚገባው ተገንዝቧል። ነገር ግን ከኢየሱስ መስቀል ባሻገር ሊመለከትና ኢየሱስ ንጹሕ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ለመረዳት ችሏል። ወደ ኢየሱስ ፊቱን መልሶ በመንፈሳዊ መንግሥቱ አብሮት ለመሆን መፈለጉን አስታውቋል። ኢየሱስ በመስቀል ላይ የተናገረው ሁለተኛው ቃል ለወንበዴው በገነት አብረው እንደሚሆኑ ተስፋ መስጠት ነበር። ገነት የጻድቃን ነፍስ ማደሪያ ናት።

ሉቃስ ከ6 እስከ 9 ሰዓት ድረስ ፀሐይ እንደ ጨለመች ይነግረናል። ይህ ምናልባትም የፀሐይ ግርዶሽ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ መንፈሱን ለእግዚአብሔር ሰጥቶ ሲሞት፣ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ለሁለት ተቀደደ። ስቅለቱን ሲያስፈጽም የነበረው የመቶ አለቃ ይህንን ሁሉ ድንቅ ሁኔታ ከተመለከተ በኋላ፣ ኢየሱስ «ጻድቅ ሰው» እንደ ነበር ተናግሯል።

ሉቃስ ከገሊላ ጀምሮ ከኢየሱስ ጋር በነበሩት ሴት ደቀ መዛሙርት ላይም እትኩሯል። እነዚህ ሴቶች የጌታቸውን ሞት ለመመልከት በመስቀሉ አካባቢ ሲጠባበቁ ቆዩ። ኢየሱስ ወደ ተቀበረበት ስፍራ የአርማትያሱን ዮሴፍ ተከትለው የሄዱት እነዚህ ሴቶች ነበሩ። ሉቃስ፥ ዮሴፍን የገለጸው እጥር ምጥን ባለ መንገድ ነበር። ዮሴፍ በኢየሱስ ላይ የሞትን ፍርድ የፈረደው የአይሁድ ሸንጎ አባል ቢሆንም እንኳ፥ በውሳኔው አልተስማማም ነበር። ዮሴፍ እግዚአብሔርን የሚወድና በምሥጢር ኢየሱስን የሚከተል እውነተኛ ሰው ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የፋሲካ ምግብን በላ (ሉቃስ 22፡1-38)

ሀ. ሰይጣን ኢየሱስን አሳልፎ በሚሰጠው በይሁዳ ልብ ውስጥ ሰርጎ ገባ (ሉቃስ 22፡1-6)። ሉቃስ የእግዚአብሔር መንፈስ እንዴት መልካሙን ተግባር ለመፈጸም በሰዎች ሕይወት ውስጥ እንደሚሠራ ገልጾአል። ነገር ግን ሌላም ኃይል አለ። ይህም ክፋትን በመሥራት በእግዚአብሔር ላይ በደልን እንድንፈጽም የሚያነሣሣን ሰይጣን ነው። ይሁዳ መንፈስ ቅዱስ ሕይወቱን እንዲቆጣጠርለት አልፈቀደም ነበር፡፡ ምክንያቱን ባናውቀውም፣ ሕይወቱ ከእውነት ርቆ እንዲቅበዘበዝ አድርጓል። የግብዝነት ሕይወት መምራት ጀመረ፡፡ ታማኝ የኢየሱስ ተከታይ ለመምሰል ቢሞክርም፣ ገንዘብ ይሰርቃ ነበር (ዮሐ 12፡6)። ኃጢአትን በሕይወቱ ውስጥ ካሳደረበት ጊዜ አንሥቱ ሰይጣን ወደ ሕይወቱ ለመግባት ዕድል አገኘ። ከዚያም ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ ይቀሰቅሰው ጀመር፡፡ ሰይጣን አንድ ክርስቲያን በር ካልከፈተለት በስተቀር በራሱ ኃይል ወደ ሕይወቱ ገብቶ ያለፈቃዱ አንዳች ሊያደርስ አይችልም። ነገር ግን ኃጢአት በሕይወታችን ውስጥ እንዲራባ ከፈቀድን፣ ሰይጣን በሕይወታችን ውስጥ ጠንካራ ይዞታ ስለሚኖረው የበለጠ ክፋት እንድንሠራ ሊያበረታታን ይችላል። ይሁዳ ወደ ሊቀ ካህናት በመሄድ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ተስማማ። ሰይጣን ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ በማነሣሣቱ፣ ይሁዳ ተሸንፎ በሰይጣን እግር ሥር ሊወድቅ ችሏል። ኢየሱስ ሰይጣን በሰዎች ላይ የነበረውን ኃይል ኢየሱስ ያሸነፈው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ነው (ቆላስይስ 2፡14-15 አንብብ)።

ለ. ኢየሱስ የመታሰቢያ በዓል ጀመረ (ሉቃስ 22፡7-23)። ፋሲካ፥ አይሁዶች ከግብጽ ባርነት የወጡበትን ጊዜ የሚያስታውሱበት እጅግ ታላቅ በዓል ነበር። በእግዚአብሔር ዕቅድ መሠረት ሌላው ፋሲካ፣ ማለትም የኢየሱስ በመስቀል ላይ መሞት የተከናወነው በዚሁ የፋሲካ መታሰቢያ ዕለት ነበር። ኢየሱስ የአይሁዶችን የፋሲካ ባሕል መሠረት በማድረግ ሌላውን የመታሰቢያ ምግብ፣ ማለትም የጌታን እራት ሥርዐት መሠረተ፡ እንጀራው (ኅብስቱ) በመስቀል ላይ የተቆረሰ ሥጋውን ሲያመለክት፤ ወይኑ ለኃጢአታችን የፈሰሰውን ደሙን ያመለክታል። ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የበላው እራት የመጨረሻው ነበር። በወደፊት መንግሥቱ መጀመሪያ ላይ እስከሚደረግው በዓል ድረስ፥ ሌላ የፋሲካ ምግብ አብሯቸው እንደማይበላ ገልጾላቸዋል (ኢሳ. 5፡6-8 አንብብ)። ኢየሱስ ሞቱ ድንገተኛ ሳይሆን የታሰበበት ድርጊት ስለመሆኑ ሲገልጽ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ አሳልፎ እንደሚሰጠው ተናግሯል።

ሐ. ደቀ መዛሙርቱ ከመካከላቸው ማን ነው ታላቅ በማለት ተሟገቱ (ሉቃስ 22፡24-38)። ኢየሱስ በእነርሱና በእግዚአብሔር መካከል ስለሚመሠረተው አዲሱ ኪዳን ለማስተማር በሚሞክርበት ልዩ የእራት ሥነ ሥርዐት ላይ፥ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ሥልጣንና ክብር ማሰባቸው አስገራሚ ነበር። ኢየሱስ ምድራዊ መንግሥትን ለማቋቋም የሚጀምር ለለ መሰላቸው የትኛውን ሥልጣን እንደሚይዙ ያውጠነጥኑ ነበር። ፕሬዚዳንቱ ማን ሊሆን ነው? ጠቅላይ ሚኒስትሩስ? የመከላከያ ሚኒስትሩስ? ምንም እንኳ ኢየሱስ አመራር ማለት አገልግሎት መስጠት እንደሆነ ያስረዳቸው ቢሆንም፣ የኢየሱስ መንግሥት በምድር ላይ ከሚታየው የተለየ አሠራር እንዳለው አልተገነዘቡም ነበር።

ኢየሱስ ቀደም ሲል የተሰጣቸውን ትምህርት ባለመቀበላቸው እያዘነ፥ በመንግሥቱ ውስጥ ስለሚኖረው አገልግሎት እንደገና አስተማራቸው። መንግሥቱን ከአሕዛብ መንግሥት ጋር አነጻጸረ። አሕዛብ በሰዎች ላይ ኃይልና ሥልጣን እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። ከአመራር የሚገኘውን ክብር ይወዳሉ። ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ማዘዝ ያስደስታቸዋል። የሰዎችን ክብርና ታዛዥነት አጥብቀው ይሻሉ። በአንጻሩም፣ በእግዚአብሔር መንግሥት አመራር የሚለካው በትሕትና ነው። በትሕትና ራሱን ዝቅ አድርጎ ሌሎችን የሚያገለግል ሰው እርሱ ከሁሉም የበለጠ ነው። ሁላችንም በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ታላላቆቹን እንደሚያከብር ታናሽ ልጅ መሆን ስላለብን፣ አንድ ሰው በዕድሜ መግፋቱ ሌሎችን የሚያዝበት መስፈርት አይሆንም። ባሪያዎቻቸውን ከሚያዙ ጌቶች በተቃራኒ፣ እኛ ለሌሎች ፈቃደኛ ባሪያዎች በመሆን ልናገለግላቸው ይገባል። በመንፈሳዊው መንግሥት ሥልጣንንና ኃይልን ሳይሆን እግዚአብሔርንና ሌሎች ሰዎችን ማገልገልን መሻት አለብን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የዓለምን የአመራር መንገድ የሚከተል መሪና የክርስቶስን መንገድ የሚከተል መሪ ከበታቻቸው ያሉትን ሰዎች እንዴት እንደሚያስተዳድሩ እነጻጽር። በአመራራቸው ውስጥ የሚለየው ነገር ምንድን ነው? ለ) ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ኢየሱስ እንደሚፈልጋቸው መሆን የሚያስቸግረው ለምንድን ነው?

ነገር ግን ሌላ የኃይል መንግሥት ይመጣል። በዚያ መንግሥት ውስጥ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ ይሾማቸዋል። ይህ ጥቅስ የሚተረጎምባቸው ሁለት መንገዶች አሉ።

አንደኛው፣ ኢየሱስ ወደ ምድር ተመልሶ በመምጣት በኢየሩሳሌም መንግሥቱን እንደሚመሠርት የሚናገሩ ምሑራን የሚከተሉት አቅጣጫ ነው። በዚህ ጊዜ በእስራኤልና በዓለም ሁሉ እንደሚገዛ ያምናሉ። በዚያ መንግሥት ውስጥ ደቀ መዛሙርቱ በእስራኤል ላይ የመግዛት ሥልጣን ይኖራቸዋል። ሁለተኛው፣ ሌሎች «የእስራኤል ነገዶች» የሚለው ሐረግ፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚል አሳብ እንዳለው የሚያስቡ ምሑራን አሉ። ከኢየሱስ ሞት በኋላ እግዚአብሔር አይሁዶችንና አሕዛብን አንድ ስላደረጋቸው ለአይሁዶች የሚደረግ የተለየ ሞገስ አይኖርም ብለው ያምናሉ (ኤፌ 2፡11-22)። አማኞች ሁሉ መንፈሳዊ አይሁዶች ናቸው። ስለሆነም ኢየሱስ የብሉይ ኪዳንን የአነጋገር ዘይቤ በመጠቀም ሐዋርያቱ በአዲሱ የእግዚአብሔር ሕዝብ፣ ማለትም በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚገዙበትን መንፈሳዊ ሥልጣን ማመልከቱ ነው ሲሉ ያስተምራሉ።

ኢየሱስ በአሠራራቸው ውስጥ ልዩነት እንደሚኖር አሳይቷል። ቀደም ሲል ደቀ መዛሙርቱ በሌሎች ሰዎች ላይ የተመሠረተ ሕይወት ይመሩ ስለነበር ቦርሳም ሆነ ሻንጣ አያስፈልጋቸውም ነበር። የኢየሱስ ስም እየገነነ ሲሄድ ለተከታዮቹ ከፍተኛ መስተንግዶ ይደረግላቸው ነበር። አሁን ግን ሰዎች በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ የሚኖራቸው አመለካከት መቀየር ጀምሯል። በሰዎች የሚጠሉበት ጊዜ ስለደረሰም፥ የራሳቸውን ፍላጎቶች ያሟሉ ዘንድ ቦርሳና ሻንጣ መያዝ አስፈለጋቸው፡፡

ነገር ግን ኢየሱስ ሰይፍ እንዲገዙ የነገራቸው ለምንድን ነው? ለመንግሥቱ እንዲዋጉ ይፈልግ ስለነበር ነው? አይደለም። ምክንያቱም ደቀ መዛሙርቱ ሁላት ሰይፍ እንዳላቸው ሲናገሩ፤ ይህ በቂ እንደሆነ ገልጾላቸዋል። ኢየሱስ የሚሞትበት ጊዜ እንደ ደረሰና በሰይፍ ተዋግተው ሮማውያንን እንደማያሸንፉ ያውቅ ነበር። ለእንዲህ ዐይነቱ ውጊያ ሁለት ሰይፎች አይበቁም፡፡ ነገር ግን ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ሰዎች ሊገድሏቸው እንደሚፈልጉና ከዚህም የተነሣ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደሚገጥሟቸው ለመግለጽ ሲል ጠንካራ አገላለጽ የተጠቀመ ይመስላል። ኢየሱስ እንደ ወንጀለኛ እንደሚቆጠር ሁሉ ተከታዮቹም ይህንኑ ስም የሚጎናጸፉበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር። ምናልባትም ሰይፉ የመዋጊያ ሳይሆን፣ ራስን ከሌቦች የመከላከያ መሣሪያ ሳይሆን አይቀርም።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ሉቃስ 21፡1-38

ትንቢቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ከሚረዷቸው የሥነ ጽሑፍ ዐይነቶች መካከል የሚመደቡ ናቸው። ትንቢት የተሰጠው ወደፊት ስለሚፈጸሙት ክስተቶች ዝርዝር መረጃዎችን እንድናገኝ ነውን? እንደዚያ ከሆነ፣ የእያንዳንዱን ትንቢት ትርጉም አስመልክቶ የተለያዩ አመለካከቶች የሚንጸባረቁት ለምንድን ነው? ምንም እንኳ ብዙዎቻችን ነቢይ ወደፊት የሚከሰተውን አስቀድሞ የሚተነብይ አገልጋይ እንደሆነ ብናስብም፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነቢይ ከእግዚአብሔር ዘንድ መልእክት የተቀበለ ሰው ነው። አንዳንድ ጊዜ መልእክቱ የወደፊት ክስተቶችን የሚመለከት ሊሆን ይችላል፤ ብዙውን ጊዜ ግን በዘመኑ ለነበሩት ሰዎች የሚያገለግል ነው። ወደፊት ነገሮች እንዴትና መቼ እንደሚፈጸሙ የሚያብራሩ ዝርዝር መረጃዎችን የያዙ ትንቢቶች ጥቂቶች ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናገኛቸው ትንቢቶች ዋናው መልእክት ምንም ይሁን ምን እግዚአብሔር ነገሮችን በመቆጣጠር ላይ እንደሚገኝ ማሳየት ነው። እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ታሪክን በመቆጣጠር ላይ ነው። አገሮችና ነገሥታት በእርሱ ቁጥጥር ሥር ናቸው። መጨረሻው ደግሞ በመከራ ጊዜ ታምነን የምንወርሰው የእግዚአብሔር መንግሥት ነው።

በሉቃስ 21 ላይ ነቢይ የሆነው ኢየሱስ ለተከታዮቹ ወደፊት የሚመጣውን ዘመን አንዳንድ ባሕርያት ነግሯቸዋል። ምንም እንኳ ከኢየሱስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዳግም ምጽአቱ ድረስ ከተተነበዩት ነገሮች መካከል አንዳንዶቹን መረዳት ብንችልም፣ እነዚህ ነገሮች መቼ ወይም እንዴት እንደሚፈጸሙ አናውቅም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ዳግም ተመልሶ በመምጣት በታማኝነት የሚጠባበቁትን ወደ መንግሥተ ሰማይ እንደሚወስዳቸው እናውቃለን። ስለሆነም ዋናው ጥያቄ፣ «እኛን ለመውሰድ በሚመለስበት ጊዜ በታማኝነት በፊቱ ስንመላለስ ያገኘን ይሆን?» የሚለው ነው።

 1. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እግዚአብሔር መስጠትን እንዴት እንደሚመለከት አስተማረ (ሉቃስ 21፡1-4) እግዚአብሔር አንድን ስጦታ የሚመዝነው በትልቅነቱ ወይም በትንሽነቱ ሳይሆን፣ ስጦታው ልባዊ ሆኖ በመሰጠቱ ነው። ስለሆነም የዚያች መበለቲቱ አሥር ሣንቲም (እኛ እንደ አንድ ሣንቲም የምንመለከተውና ምንም የማይጠቅም የአይሁዶች ገንዘብ)፣ በእግዚአብሔር ዐይን ፊት አንድ ነጋዴ ከሚሰጠው መቶ ብር በላይ የሚገመት ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ለእግዚአብሔር በልግስና በመስጠትህ ምክንያት የገንዘብ አቅምህ ስለተጎዳበት ጊዜ ተናገር።

 1. ኢየሱስ በሚመለስበት ጊዜ ስለሚከሰቱት ምልክቶች ተናገረ (ሉቃስ 21፡5-38)

ኢየሱስ ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስ የተናገረው አሳብ፥ ደቀ መዛሙርቱ ቤተ መቅደሱ ስለሚፈርስበት ጊዜና ከዚያ በፊት ስለሚከሰቱት ምልክቶች እንዲጠይቁ አነሣሣቸው። ኢየሱስ በትንቢቱ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚፈጸሙትን (የኢየሩሳሌም በ70 ዓ.ም. መደምሰስ)፣ በዘመናት ሁሉ የሚሆነውን የሕይወት ዕጣ ፈንታና ኢየሱስ ዳግም ሊመለስ ሲል በመጨረሻ ዘመን የሚከሰቱትን ነገሮች በሙሉ አካትቷል። ምሑራን ኢየሱስ በተለያዩ ክፍሎች የሚጠቅላቸው ነገሮች በየትኛው ጊዜ እንደሚፈጸም በትክክል ስለማያውቁ በአሳብ አይስማሙም። አስፈላጊው ነገር እያንዳንዱ ትንቢት የትኛውን ጊዜ እንደሚያመለክት ማወቁ ሳይሆን፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ የጊዜውን ባሕርይ እንዲያውቁ ማዘጋጀቱ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ እስከ መጨረሻው ድረስ ነገሮችን ሁሉ እንደሚቆጣጠር መረዳቱ ጠቃሚ ነው። (ከእነዚህ ትንቢቶች የተወሰዱትን የተለያዩ ግንዛቤዎች ማቴዎስ ምዕራፍ 24 ላይ የተሰጠውን ማብራሪያ ተመልከት።)

ሀ. መጨረሻው የኢየሩሳሌም መፍረስም ይሁን ወይም የዘመን መጨረሻ ገና ከብዙ ዘመን በኋላ የሚፈጸም ስለሆነ፣ ደቀ መዛሙርቱ በፍጥነት ይሆናል ብለው መጨነቅ አልነበረባቸውም። በመጀመሪያ ሰዎችን የሚያታልሉ ሐሰተኛ መሢሖች ከመነሣታቸውም በላይ፣ ብዙ ጦርነቶች ይካሄዳሉ። ኢየሩሳሌም ልትፈርስ አቅራቢያ የተለያዩ መሢሖች የተነሡ ሲሆን፣ ብዙ ውጣ ውረዶችና ጦርነቶችም ተካሂደው ነበር። ኢየሱስ በትምህርቱ ላይ ለማመልከት የፈለገው ይህንኑ ሁኔታ ሳይሆን አይቀርም። ወይም ደግሞ ሊመለስ ሲል የሚከሰቱትን ሁኔታዎች መጥቀሱ ይሆናል። (ይህ እጥፍ ፍጻሜ በመባል ይታወቃል።)  

ለ. በአገሮች፣ በተፈጥሮና በሰማይ ላይ እንኳ ሳይቀር የመጨረሻውን ዘመን የሚያሳዩ ብጥብጦች ይፈጸማሉ።

ሐ. ፍጻሜው ከመድረሱ በፊት፣ የኢየሱስ ተከታዮች ከአይሁዶች (ምኩራብ) እና ከአሕዛብ (ነገሥታት፣ ጎዥዎች) ብዙ ስደት ይደርስባቸዋል፡ በተጨማሪም ለማመን ከማይፈልጉ ወገኖች ብርቱ ቤተሰባዊ ስደት ይከሰታል። ሰዎች ክርስቲያኖችን ይጠላሉ። ነገር ግን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ስለሚሆን፣ መንፈስ ቅዱስ ምን እንደምንል ያስተምረናል። ኢየሱስ ሳይፈቅድ ከራሳችን ፀጉር እንኳ አንድ አይነቀልም። የኢየሱስ ተከታዮች የሆንን ሁላችንም በእምነታችን ጸንተን ለመኖር መቁረጥ ይኖርብናል። ይህ ለዘላለም ሕይወት ያበቃናልና!

መ. ኢየሩሳሌም በሠራዊት በምትከበብበት ጊዜ፣ ውድመቱ ፈጣንና ዘግናኝ ይሆናል። ይህም በኢየሩሳሌም ከሮም ሠራዊት የሚሰነዘረውን አደጋ ወይም በመጨረሻው ዘመን የሚደርስባትን ውድመት የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ሮም ኢየሩሳሌምን ከደመሰሰች በኋላ፣ እግዚአብሔር እስራኤልን ዳግም እስኪጎበኝ ድረስ አሕዛብ ከተማይቱን ይቆጣጠሯታል። (ይህም የአሕዛብ ዘመን በመባል ይታወቃል።)

ሠ. ኢየሱስ ሊመለስ ሲል በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ምልክት ይሆናል። (ማስታወሻ፡ አንዳንድ ምሑራን ይህ የአገርችን ከፍተኛ ውዝግብ እንጂ በፀሐይ፣ በጨረቃና በከዋክብት ላይ የሚደርሰውን ሁኔታ አያመለክትም ይላሉ።)

ረ. ኢየሱስ በክብር ደመና ይመለሳል። ይህ ከዚህ ክፉ ዓለም ነፃ መውጣታችንን የሚያመለክት ይሆናል።

እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? ኢየሱስ ስለ መጨረሻው ዘመን በሚያስተምርበት ጊዜ ሁሉ ደቀ መዛሙርቱን ያስተምር ወደነበረው አሳብ ይመለሳል። ኢየሱስ እስኪመለስ ድረስ በታማኝነት ልናገለግለው ይገባል። በዓለም ፍቅር ተተብትበን ኢየሱስን ለመጠበቅ መቸገር አይገባንም። ወይም ደግሞ ከሚገባው በላይ ተጨንቀን ተስፋ መቁረጥ አይገባንም። ነገር ግን የኢየሱስን ዳግም ምጽአት ተግተን እንድንጠብቅና በእምነታችን እንድንጸና አጥብቀን መጸለይ ይገባናል። የኢየሱስ ተከታዮች የምጽአቱን ጊዜ ሳይዘነጉ ተግተው መጠበቅ ይሻሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቅርቡ ስለ መጨረሻው ዘመን ሲሰበክ የሰማኸው መቼ ነው? ለ) የኢየሱስን ምጽአት እየጠበቅህ ሳለህ የምታከናውናቸው ተግባራት ምንድን ናቸው? ሐ) የኢየሱስ መመለስ የጸሎት ሕይወትህን የሚነካው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ከተለያዩ ቡድኖች ጋር ተከራከረ (ሉቃስ 20፡1-47)

ሀ. ኢየሱስ ሥልጣኑን አስመልክቶ ከካህናት ጋር ተከራከረ (ሉቃስ 20፡1-19)። ሥልጣን አስፈላጊ ነገር ነው። አንድ ሰው ወደ አንተ መጥቶ ወደ ጦር ሜዳ መሄድ እንዳለብህ ቢነግርህ፣ የመጀመሪያው ጥያቄህ ሰውዬው ማን ነው? የሚል ይሆናል። ይህን ያለህ የመንግሥት ሥልጣን የሌለው ተራ ሰው ከሆነ፣ የሚነግርህን ችላ ብለህ ልትተው ትችላለህ። ነገር ግን ሌላ ሁለተኛ ሰው መጥቶ ቢናገርህ ሰውዩው የመንግሥት ባለሥልጣን ከሆነ፣ ከመጀመሪያው ሰውዩ ያነሰ ትምህርትና የአለባበስ ሁኔታ ቢታይበትም እንኳ አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት ትገደዳለህ። ለዚህ ሰውዬ ከመጀመሪያው የተለየ ምላሽ እንድትሰጥ ያደረገህ ወደ ቤትህ የመጣው ሰውዬ በራሱ ሥልጣን አይደለም። የመንግሥት ሥልጣን ሁሉ ከእርሱ ኋላ እንዳለ በመገንዘብህ እንጂ። ለዚህ ነበር የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች የኢየሱስን የሥልጣን ምንጭ ለማወቅ የፈለጉት። ኢየሱስ ተራ ሰው ነው ወይስ የእግዚአብሔር እንደራሴ? ኢየሱስ ቀደም ብሎ ይህንኑ እውነት የነገራቸው ሲሆን በሠራቸው ተአምራት ጭምር ሥልጣኑ ከእግዚአብሔር እንደሚመነጭ ገልጾላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን የሚያዩትንና የሚሰሙትን ለማመን ስላልፈለጉ፣ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር እንደገና መከራከሩ አስፈላጊ መስሎ አልታየውም። በዚህ ፈንታ ኢየሱስ አይሁዶቹ የእግዚአብሔር ሥልጣን በየትኛውም መልክ ቢመጣ ለመቀበል ባለመፈለጋቸው በመጥምቁ ዮሐንስ አማካይነት የሠራውን የእግዚአብሔርን እጅ ለማመን አለመፍቀዳቸውን በመግለጽ፣ የራሳቸውን ጥያቄ ተጠቅሞ ሞገታቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ኢየሱስ ብቸኛ የደኅንነት መንገድ ነው የሚለው እሳብህቶ ሥልጣን ከየት እንደመነጨ ብትጠየቅ፣ ምላሽህ ምን ይሆናል?

ኢየሱስ ምሳሌ በመጠቀም ሊሆን ስላለው ነገር ለካህናቱ ብርቱ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል። እንደ የወይን አትክልተኞች ሁሉ፣ እነርሱም ለእግዚአብሔር ሕዝብ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔርን ለመስማትና መልእክተኞቹን (መጥምቁ ዮሐንስንና ኢየሱስን)፥ ለመቀበል ባለመፈለጋቸው፣ የእግዚአብሔርን አገልጋይ ብቻ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርንም ልጅ አንቀበልም አሉ። ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር በቅርብ ጊዜ በእነርሱ ላይ በመፍረድ ወይኑን ለሌሎች ሠራተኞች ይሰጣል። ሌሎች፥ የተባሉት በኋላ መንፈሳዊ አመራሩን የተቀበሉት ሐዋርያት ሳይሆኑ አይቀሩም። ክፍሉ የሚያመለክተው ግን የእግዚአብሔር የወይን በረከት ወደ አሕዛብ እንደሚዞር ሳይሆን አይቀርም። አይሁዶች ሁሉ ይህ በእነርሱ ላይ የተሰነዘረ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ መሆኑን ስለተገነዘቡ፣ እንዲህ ያለውንስ አያምጣው» ሲሉ ተቃወሙ። ኢየሱስ ብሉይ ኪዳን እንኳ አይሁዶች እንዴት የእግዚአብሔርን ድንጋይ ለመቀበል እምቢ እንደሚሉና፥ እግዚአብሔር ግን እነርሱ ያልተቀበሉትን ድንጋይ የማዕዘን ራስ እንደሚያደርገው የተናገረ መሆኑን ገለጸላቸው። የዚያ ድንጋይ ተምሳሌት የሆነው ኢየሱስ፥ ለእግዚአብሔር ሕዝብ አዲስ ሕንጻ አካል ይሆናል።

የውይይት ጥያቄ- እግዚአብሔር ሕዝቡ ንስሐ እንዲገባ ለዘላለም አይጠብቅም። አንዳንድ ጊዜ የበለጠ ትሑትና ተገዥ ለሆነው ሌላ ሰው ወይም ቤተ እምነት በረከቱን አሳልፎ እስከሚሰጥ ድረስ ታላቅ ፍርዱን ያመጣል። ይህ ምሳሌ ለእኛ በግልና በቤተ ክርስቲያን ደረጃ ማስጠንቀቂያ የሚሰጠን እንዴት ነው?

ለ. ስለ ቀረጥ መክፈል ከፖለቲካ መሪዎች ጋር የተካሄደ ክርክር (ሉቃስ 20፡20-26)። አይሁዶች በሁለተኛ ደረጃ ኢየሱስን ችግር ውስጥ ለመክተት የሞከሩት፥ ከሮም ባለሥልጣናት የሚጋጭበትን ሁኔታ በማመቻቸት ነበር። ኢየሱስ ቀረጥ አልከፍልም ቢል፣ በመንግሥት ላይ ዐመፅ ቀስቅሷል ተብሎ ይታሰር ነበር። ኢየሱስ ግን ሰዎች ታማኝነታቸውን ሊገልጹ የሚችሉባቸው ሁለት መንግሥታት እንዳሉ ገልጾአል። አንዱ ሮም የምትገዛበት ዐይነት ምድራዊ መንግሥት ነበር። እንዲሁም ደግሞ ሌላው ሰማያዊ የእግዚአብሔር መንግሥት ነበር። ሁለቱንም ማክበርና መታዘዝ ያስፈልጋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ታዛዥ እንጂ ዐማጺ አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከምድራዊ መንግሥት ትእዛዝ ይልቅ የሰማያዊውን መንግሥት ትእዛዝ የሚያስበልጡት፣ ከሰማያዊ መንግሥት ሥር ያለው ምድራዊ መንግሥት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በሚጥስበት ጊዜ ብቻ ነው።

ሐ. ከሰዱቃውያን ጋር ስለ ጋብቻና ስለ ሙታን ትንሣኤ የተደረገ ክርክር (ሉቃስ 20፡27-40)። ኢየሱስን ለማጥመድ የተደረገው የመጨረሻው ጥረት ሥነ መለኮታዊ ክርክርን በመክፈት ነበር። ሥነ መለኮት እግዚአብሔር ስለ አንድ ርእሰ ጉዳይ የሚያስተምረውን እውነት ለመረዳት የሚደረግ ጥረት በመሆኑ ጠቃሚ ነው። ብዙውን ጊዜ ግን ነገረ መለኮት ትርጉም ወደማይሰጡ አለመስማማቶች ይመራል። ይህም ጊዜ ከማባከኑ በተጨማሪ፣ ሰዎች እርስ በርሳቸው ተጣልተው ኅብረት እንዲያቋርጡ በማድረግ ለኃጢአት ይዳርጋቸዋል። በዐበይት ቤተ እምነቶች ውስጥ የተፈጸሙት አብዛኞቹ መከፋፈሎች በእግዚአብሔር ዐይን ፊት ክርስቲያኖችን ሊያጣሉ በማይገቡ ነገረ መለኮታዊ ጉዳዮች ላይ ካለመስማማት የመነጩ ናቸው፡፡ ለእውነት መፋለም ያለብን የእግዚአብሔርን ቃል በግልጽ የሚያፋልስ ነገር ከተገኘ ብቻ ሊሆን ይገባል። ኢየሱስ ስለ ጋብቻ ሥርዓት በቀረበው ሙግት ውስጥ ለመሳተፍ ባለመፈለጉ፣ የሰዱቃውያን ዋንኛ ችግርና ውዥንብር ወደሆነው ጉዳይ አመራ። እነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ አስተምህሮ የሆነውን የሙታን ትንሣኤ አይቀበሉም ነበር።

መ. ኢየሱስ ስለ ዳዊት ልጅ የሃይማኖት መሪዎችን ጠየቃቸው (ሉቃስ 20፡41-47)። አይሁዶች መሢሑን ታላቅ ሰብአዊ መሪ ብቻ አድርገው ያስቡ ነበር። ስለሆነም ኢየሱስ ዳዊት መሢሑን ጌታዬ ብሎ እንደጠራው በመጥቀስ፣ አምላክነቱን ገለጻላቸው ይህም የዳዊት ልጅ ከዳዊት የዘር ሐረግ የመጣ ሰው ከመሆኑም በላይ፥ የዳዊት አምላክ መሆኑን ያሳያል፡፡ እነዚህን ሁለቱንም መስፈርቶች የሚያሟላው ኢየሱስ ብቻ ነው። ኢየሱስ በዚህ አኳኋን በሰጠው ማብራሪያ፥ መልስና ትምህርት የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች እርሱን ለማጥመድ ያደርጉትን ጥረት ሁሉ ውድቅ አደረገ። ከሁሉም በላይ ያስቆጣው እርሱን ለማጥመድ መሞከራቸው ሳይሆን፣ በቀላሉ ሰዎችን የሚጎዳው የግብዝነት ሃይማኖታቸው ነበር። ስለሆነም ሕዝቡ እነዚህን የሃይማኖት መሪዎች በእግዚአብሔር ፊት እንዴት መመላለስ እንዳለባቸው የሚያሳዩ እንደ መልካም ምሳሌዎች አድርገው እንዳይመለከቱዋቸው አስጠነቀቃቸው። እነዚህ ሰዎች ሃይማኖታዊ መሪዎቻቸው ቢሆኑም እንኳ፥ እግዚአብሔርን የሚያስከብር ሕይወት አልነበራቸውም። መሪዎቹ ከሕዝቡ እየተደበቁ እንደ መበለቶች ያሉትን ሴቶች በመበዝበዝ የራሳቸውን ብልጽግና ያሳድዱ ነበር። ለእነዚህ ሰዎች ሃይማኖት በምኩራብ ውስጥ ወይም ሰዎች በሚያዩአቸው ስፍራ የሚያከናውኑት ተግባር ነበር። ሃይማኖት መሪዎቹ በሌላ ጊዜ የሚኖሩትን ሕይወታቸውን አልለወጠውም።

የውይይት ጥያቄ:- እኛም ግብዝ በመሆን እንዴት የፈሪሳውያንን አመለካከት ልንጋራ እንደምንችል የተለያዩ መንገዶችን በመጥቀስ አብራራ።

ነገሮችን ‹ሃይማኖታዊ› እና ‹ተራ› ብሎ መነጣጠሉ ቀላል ነው። በቤተ ክርስቲያን አምልኮ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ በምንሆንበት ጊዜ፥ ሃይማኖታዊ ተግባርን እያደረግን ነው ብለን እናስባለን። አንዳንድ ጊዜ እነዚህን ነገሮች ከልባችን በማንፈጽምበት ጊዜ እንኳ ሰዎች መንፈሳውያን እንደሆንንና ከልባችን እንዳደረግነው ያስባሉ። እርግጥ ነው ሁልጊዜ እግዚአብሔርን ለማምለክ የሚሻ እውነተኛ ፍላጎት ሊኖረን ይችል ይሆናል። ያም ሆኖ ከዚያ በኋላ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ ወይም በቤታችን የምናከናውነው ተግባር እግዚአብሔርን የሚያሳስበው አይመስለንም። እንዲህ ስናደርግ በዚህም በአምልኮና እግዚአብሔር በሚያየው ሕይወት መካከል ክፍተት እንፈጥራለን። እውነተኛው አምልኮ ለድሆች ማሰብ እንደሆነ ከያዕቆብ መልእክት እንረዳለን (ያዕ. 1፡26-27)። ዝማሬያችንና አምልኳችን ብቻ ሳይሆን፣ እያንዳንዱን የሕይወት እርምጃችን እግዚአብሔርን በሚያከብር መንገድ ልንኖር ይገባናል። ስለዚህ በሥራ ቦታችሁ፣ በትምህርት ቤታችሁ ወይም በመኖሪያ ቤታችሁ እግዚአብሔርን ለማክበር ምን እያደረጋችሁ ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ሉቃስ 19፡11-48

 1. የአሥሩ ምናን (ብር) ምሳሌ (ሉቃስ 19፡11-27)

የውይይት ጥያቄ፡- 2ኛ ተሰሎ. 2፡1-12 አንብብ። ሰዎች ኢየሱስ ስለሚመለስበት ጊዜ ምን ያስባሉ?

አይሁዶችና የቀድሞ ክርስቲያኖች ከሚጠብቋቸው ነገሮች መካከል አንዱ፥ ኢየሱስ በፍጥነት ተመልሶ መሢሑ በዓለም ሁሉ የሚገዛበትን ምድራዊ መንግሥት መመሥረቱ ነበር። ምናልባትም ወደ ኢየሩሳሌም እየቀረበ ሲመጣ፣ አይሁዶች አሁን የመሢሑን አገዛዝ በጳለስቲና እንደሚጀምር በማሰብ ሳይደሰቱ አልቀሩም። ስለሆነም ኢየሱስ ለአይሁዶች ምድራዊ መንግሥቱን ገና ወደፊት እንደሚመሠርት ለማሳየት ፈለገ። ይህ ደግሞ ለክርስቲያኖችም የሚያስፈልግ ትምህርት ነው። ጳውሎስ በተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን ከመሠረተ ብዙም ሳይቆይ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ዳግም መጥቶ ሳናውቅ ሄዶ ይሆናል በሚል አሳብ ተሸብረው ነበር። ኢየሱስ በምሳሌው ለማስተማር የፈለገው ዋንኛ ትምህርት የሚመለስበት ጊዜ ገና ወደፊት እንደሆነና ዋናው ነገር እርሱ እስኪመለስ ድረስ በታማኝነት እያገለገሉ መኖር መሆኑን ነው።

ከንጉሣዊ ቤተሰብ የተወለደ ሰው ኢየሱስን ይወክላል፤ እርሱም ወደ ሰማይ በመሄድ የንጉሥነትን ሹመት ተቀብሎ ወደ ምድር ይመለሳል። ደቀ መዛሙርቱ ደግሞ ኢየሱስ ለክብሩ ይጠቀሙበት ዘንድ ገንዘብ ሰጥቶ የሾማቸው አሥር አገልጋዮች ነበሩ። ገንዘቡ ደግሞ የኢየሱስ ተከታዮች ንብረት የሆነው አካላቸው፣ ትምህርታቸው፣ ጊዜያቸው፣ ገንዘባቸው ነበር። ያን ጊዜ አንድ ብር የሦስት ወር ደመወዝ ያህል ገንዘብ ስለ ነበር፣ እሥር ብር የሁለት ዓመት ተኩል ደመወዝ ያህል ነበር። (ማስታወሻ፡ በማቴ. 25፡14-30 በተጠቀሰው ምሳሌ ውስጥ ሦስት ባሪያዎች ብቻ ሲጠቀሱና ለእያንዳንዱ ባሪያ የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ ሲሰጥ፣ እዚህ ላይ ግን እኩል ገንዘብ የተሰጣቸው አሥር ባሪያዎች ተጠቅሰዋል። ማቴዎስ ያተኮረው የተለያዩ ስጦታዎችንና ችሎታዎችን በታማኝነት በመጠቀሙ ጉዳይ ላይ ሲሆን፣ በዚህ ስፍራ ሉቃስ እግዚአብሔር ሕይወታችንን ሁሉ ለእርሱ ክብር እንድንጠቀምበት አጽንኦት ሰጥቶ ያስተምራል። የሁለቱም ትኩረት ታማኝነት የታከለበትን አገልግሎት ማበርከት እንደሚገባ መግለጽ ነው።) ከዚህ ምሳሌ የሚቀስሙ በርካታ ጠቃሚ እውነቶች አሉ።

ሀ. ኢየሱስ፥ አይሁዶች ንጉሥ እንዲሆን ባይፈልጉም፣ እርሱ መሢሕ ነበር። የንግሥና አክሊል እንዳይደፋና አንድ ቀን ወደ ምድር ተመልሶ እንዳይገዛ ሊከለክሉት አይችሉም። (አንዳንድ ምሑራን ከዚህ ክፍል አርከሉስ በተባለ የሄርድስ ልጅ ላይ የደረሰውን ሁኔታ የሚመስል ነገር ይመለከታሉ። አባቱ ታላቁ ሄሮድስ አርኬላውስን ንጉሥ አድርጎ ሲሾመው፣ አይሁዶች ወደ ሮም የልዑካን ቡድን በመላክ ከዙፋኑ አስወርደውት ነበር። በኢየሱስ ላይ ግን ይህንን ሊያደርጉ አልቻሉም። እግዚአብሔር ኢየሱስን ወይም ሌላ ንጉሥ የመምረጥ ዕድል አልሰጠንም። ስለዚህ ኢየሱስ ብቸኛው ንጉሥ ስለሆነ፣ አማራጫችን እርሱ ንጉሥ መሆኑን አምነን ግንኙነታችንን ከእርሱ ጋር ማድረግ ብቻ ነው።

ለ. አሥሩ ሰዎች እኩል መጠን ያለው ገንዘብ እንደተሰጣቸው ሁሉ እኛም የተለያዩ ስጦታዎችና ችሎታዎች አሉን የሁላችንም ሕይወት የእግዚአብሔር ነው። ስለሆነም እግዚአብሔርን የማገልገል ብቃታችን እኩል ነው።

ሐ. እግዚአብሔር ለሰዎች የተለያየ ስጦታ እንዳላቸው ያውቃል፤ ስጦታዎቹን የሰጣቸው እርሱ ነው። ስለሆነም እያንዳንዱ ባሪያ እግዚአብሔር ከሰጠው ውስጥ የተወሰነውን እንደሚመልስ ያውቃል።

መ. ዋናው ነገር ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማወዳደር ሳይሆን፣ በሰጠን ነገር ኢየሱስን በታማኝነት ማገልገል ነው። ኢየሱስን የሚያገለግሉ ሁሉ ዋጋቸውን ሲቀበሉ፣ ስጦታዎቻቸውንና ችሎታዎቻቸውን ያባከኑት ሰዎች ግን ከፍተኛ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

ሠ. እግዚአብሔር እርሱን ለሚያገለግሉ ሰዎች ያለው መርሕ ትጋትን ላሳዩ ሰዎች የበለጠ ኃላፊነት መስጠት ነው። የሥልጣን ደረጃ የሚወሰነው በሁለት ነገሮች ነው። አንደኛው፥ ያለንን በታማኝነት በመያዛችን ላይ ይመሠረታል። ሁለተኛው፣ እግዚአብሔር በሰጠን ችሎታ ላይ ይመሠረታል። አንድ ባሪያ አሥሩን ብር ወደ ሃያ ብር ለማድረስ በታማኝነት የሚሠራ ከሆነ፡ ከዚያ የበለጠ ኃላፊነት ይስጠዋል። ነገር ግን ታማኝነት ባይጎድልበትም እንኳ የባሪያው ችሎታ አምስት ብር ብቻ እንዲያተርፍ ካደረገ፣ የሚሰጠውም ኃላፊነት እንደዚያው ይቀንሳል።

ረ. እግዚአብሔር የሰጣቸውን ነገር ለመጠቀም በማይፈልጉ ሰዎች ላይ የሚፈርድ ሲሆን፣ ያላቸውም እንኳ ይወሰድባቸዋል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ችሎታ ለእርሱ ክብር የማይጠቀሙ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔር የሰጠውን ብር እንደ ደበቀው ሰው ናቸው። እነዚህ ሰዎች እሑድ እሑድ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው ከምእመናኑ ጋር ይዘምራሉ እንጂ፣ በሥራ ቦታ አይመሰክሩም፤ በልግስና አይሰጡም፤ ድሆችን አይረዱም፣ ወይም በሆነ መንገድ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አያገለግሉም። እግዚአብሔር የሰጣቸውን መክሊት ይደብቁታል። ኢየሱስ በእነዚህ ሰዎች እጅ ያለውን ነገር ወስዶ ለክብሩ ለሚጠቀሙት እንደሚሰጥ ተናግሯል። ብዙ ሰዎች የመሪነትን አገልግሎት ቢመኙም፣ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ተጠቅመው ሊያገለግሉትና በፈቀደም ጊዜ ከፍ ለማለት አይሹም። እግዚአብሔር በታማኝነት ያላገለገለውን ሰው ከፍ አያደርግም፣ እነዚህ ሰዎች ረዥም ጊዜ መጠበቅ አይሆንላቸውም፤ እንዲያውም የበለጠ ዝቅ ያደርጋቸዋል።

የውይይት ጥያቄ- ሀ) እግዚአብሔር የሰጠህ አንዳንድ ስጦታዎችና ችሎታዎች ምንድን ናቸው? ለ) የትኞቹን ለእግዚአብሔር እየተጠቀምህ ነው? እንዴት? ሐ) ያልተጠቀምህባቸው የትኞቹ ናቸው? ለምን? መ) ብዙ ሰዎች ያላቸውን ስጦታና ችሎታ እግዚአብሔርን ለማገልገል የማይጠቀሙት ለምን ይመስልሃል? ሠ) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያንዳንዱ ሰው ለጦታውን በሥራ ላይ የሚያውልበትን መንገድ በማሳየቱ ረገድ የመሪዎች ኃላፊነት ምንድን ነው? ይህ መሪዎች ሌሎችን በአገልግሎት ማሳተፍ እንዳለባቸው የሚያመለክተው እንዴት ነው?

 1. ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በድል ገባ (ሉቃስ 19፡28-44)

አምልኮን የምንገመግመው እንዴት ነው? በስሜቶች፣ በእንቅስቃሴዎች፣ በጭብጨባዎችና በዕልልታዎች ነውን? ወይስ በሆነ መንገድ በምስጋናና በውዳሴ ራሱን የሚገልጽ ሕይወት ከእግዚአብሔር ጋር በመምራት ነው? ብዙውን ጊዜ ሰዎች በአምልኮ ጊዜ ስሜታውያን ሆነው ሊታዩና በእግዚአብሔር ላይ ጽኑ እምነት ላይኖራቸው ይችላል። ኢየሱስ በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም በተጓዘበት ጊዜ እንዲህ ዐይነት ሁኔታ ተከስቷል። ብዙ ሰዎች ደስታቸውን በጩኸት፣ በጭፈራና በዝማሬ ከመግለጻቸውም በላይ፣ እግዚአብሔርንም አመስግነዋል። ነገር ግን ከስድስት ቀናት በኋላ እነዚሁ ሰዎች «ስቀለው!» እያሉ ጮኸዋል። ስሜታዊ አምልኳችን ከእግዚአብሔር ጋር ካለን ትክክለኛ ዓላማ መመንጨቱን ማረጋገጥ አለብን።

ኢየሱስ የሕዝቡን ውዳሴ አዳመጠ። ነገር ግን ኢየሩሳሌምን ሲመለከትና ቀጥሎ የሚሆነውን ሁኔታ ሲያስብ ልቡ በኀዘን ተመታ። መሢሑ ንጉሣቸው መጥቷል። ነገር ግን አይሁዶች ኢየሱስን ለመቀበል ስላልፈለጉ፣ የእግዚአብሔር ፍርድ እየመጣባቸው ነበር። ብዙም ሳይቆይ ከተማይቱ ትደመሰሳለች። በ70 ዓ.ም. የሮም ወታደሮች የኢየሩሳሌምን ከተማ በወረሩ ጊዜ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች እንደ ተገደሉ ይገመታል።

 1. ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን አጸዳ (ሉቃስ 19፡45-48)

የኢየሱስ ደስታ ወደ እንባ፣ ከዚያም ወደ ቁጣ ተቀየረ። ይህ ሁሉ የሆነው በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ነበር። ኢየሱስ የቤተ መቅደስ ውስጥ ነጋዴዎች የሚያደርጉትን የሙስና ተግባር በመመልከቱ እጅግ ተቆጥቶ አባረራቸው። የስግብግብነት ባሕርይ በፍጥነት ሰዎቹን በመቆጣጠሩ አምልኳቸውን ለሚያቀርቡ ሰዎች (እንስሳትን ለመሥዋዕትነት፣ ገንዘብን ደግሞ ለቤተ መቅደስ ቀረጥ ማቅረብ) እንዲያገለግል የታሰበው ነገር የመበዝበዣ መሣሪያ ሆነ። ይኸው ተመሳሳይ ዝንባሌ ሰዎች የውጭ አገር ዜጎችን ወይም አቅመ ደካሞችን በማታለል ለአንድ ነገር ከሚገባው በላይ ዋጋ ሲወስዱ የሚከሰት ነው። ይህ ልናደርግ የሚገባን ነገር ተገላቢጦሽ ነው። ምክንያቱም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ልናገለግል እንጂ በሰዎች ጉዳት ልንጠቀም አይገባም።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ቀራጩ ዘኬዎስ ደኅንነት አገኘ (ሉቃስ 19፡1-10)

ሉቃስ ታሪኩን የተናገረው፥ ኢየሱስ አንድን ሰው በሚነካበት ጊዜ በሕይወቱ ውስጥ ምን እንደሚከሰት ለማብራራት መሆኑ ግልጽ ነው። ወጣቱ ገዥ ሕይወቱን የተቆጣጠረውን ገንዘብ ትቶ፥ ኢየሱስን ለመከተል አልፈለገም ኃጢአተኛውና የተናቀው ቀራጭ ግን ገንዘቡን ትቶ ከኢየሱስ ኋላ ለመሮጥ ፈቅዷል። የእግዚአብሔር መንገድ ከእኛ የተለየ ነው። በጥሩ ሕይወታቸው፤ ችሎታቸውና ገንዘባቸው በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ሊኖሩ የሚገባቸው ሰዎች ሳይገቡ ይቀራሉ፡፡ ነገር ግን እኛ ዘወር ብለን የማናያቸውን ሰዎች እግዚአብሔር ዳስሶ ወደ ቤቱ ያመጣቸዋል።

ዘኬዎስ አጭር ሰውና ቀራጭ ነበር። ይህ ሰው ብዙ ገንዘብ ነበረው። ነገር ግን መንፈሳዊ ረሃብ በልቡ ውስጥ ስለ ነበረ፣ ኢየሱስን ያይ ዘንድ በጉጉት ከዛፍ ላይ ወጣ። ኢየሱስ የዘኬዎስን ልብ ያውቅ ነበርና ወንጌሉን ይበልጥ ያብራራለት ዘንድ ወደ ቤቱ ገብቶ በእንግድነት ተቀመጠ። ኢየሱስ ወደ ቤትህ ለመግባት እፈልጋለሁ በማለት ፈንታ ወደ ቤትህ መግባት አለብኝ ማለቱ አስገራሚ ነው። ይህ እግዚአብሔር የወሰነው ስብሰባ ነበር። ኢየሱስ ይህን ሲያደርግ ከዘኬዎስ ጋር አብሮ በመብላት ዝናን ለማግኘት የወሰደው እርምጃ አልነበረም። ተራ አይሁዶች እንኳ ከእንዲህ ዐይነት ሰው ጋር መቀራረብ አይፈልጉም ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ የነፍስ ሐኪም በመሆኑ፣ የደኅንነትን መድኃኒት የሚፈልግ ሰው ወዳለበት ስፍራ ሁሉ ይገባል። ምንም እንኳ ዘኬዎስ በሥጋ ከአይሁድ ወገን የተወለደና የአብርሃም ልጅ ቢሆንም፣ እውነተኛው የአብርሃም ልጅ የሆነው ገና ከኢየሱስ ጋር ከተገናኘ በኋላ ነበር። በመንፈሳዊ ሕይወቱም የአብርሃምን እምነት አግኝቷል።

የዘኬዎስን ሕይወት መለወጡን ወይም አለመለወጡን እንዴት እናውቃለን? ኢየሱስ ባይነግረውም፣ ዘኬዎስ ሕይወቱ መለወጥ እንዳለበት ያውቅ ነበር። ገንዘቡን ለመተው ካልፈቀደው ወጣት ጎዥ በተቃራኒ፣ ዘኬዎስ ከገንዘቡ ግማሹን እርዳታ ለሚፈልጉት ለመስጠትና ቀራጭ ሆኖ በሚሠራበት ጊዜ ላታለላቸው ሰዎች ሁሉ የወሰደውን ገንዘብ እንደሚመልስላቸው ተናግሯል። ዘኬዎስ ይህንን ያደረገው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቅርታን ለማግኘት ሳይሆን፣ ይቅርታን ስላገኘ ነው። እውነተኛ ንስሐ ማለት ሁሉንም ነገር እንደ አዲስ መጀመር ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ኋላ በመመልከት ያበላሹትን ማስተካከል ጭምር ነው።

በብሉይ ኪዳን እንደምናነበው፥ እግዚአብሔር የአንድን ሰው ልብ በሚነካበት ጊዜ ሰውየው የሰረቃቸውን ነገሮች ሁሉ ለመመለስ ጥረት ሲያደርግ እንመለከታለን። ሰዎችን የጎዳባቸውንና ከእነርሱ ጋር የነበረውን ግንኙነት ያቋረጠባቸውን መንገዶች መለስ ብሎ በማጤን፣ እንደገና ግንኙነቱ የሚታደስበትን መንገድ ያፈላልጋል። በዘመናችን ግን ይቅርታ ማለት ሕይወትን እንደ አዲስ መጀመር ብቻ ነው ብለን እንሳሳታለን። ይቅርታ ሲባል ቀደም ሲል የተደረጉትን ነገሮች እንረሳለን ብለን እናስባለን። ይህ ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይቅርታ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይቅርታን በምንከተልበት ጊዜ፥ የተበላሹትን ግንኙነቶች ማስተካከል፣ ከሌሎች የሰረቅነውን ገንዘብ ወይም ሌላ ነገር መመለስ ይጠበቅብናል። ምናልባትም ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኃጢአት ተቆልሎ የሚታየው፥ እግዚአብሔር ክርስቲያኖች የቀድሞ ሕይወታቸውን እንዲያስተካክሉና ከተቻለም በሌሎች ወገኖች ላይ ላደረሷቸው ጉዳቶች ካሳ እንዲከፍሉ እንደሚፈልግ ባለማስተማራችን ይሆናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ ሰዎች ወደ ክርስትና ሊመጡ ወይም በኃጢአት ሲወድቁ፣ ቀደም ሲል የሰረቋቸውን ነገሮች ወይም የወሰዱትን ገንዘብ መመለስ እንደሌለባቸው የሚያስቡት ለምን ይመስልሃል? ለ) ዘሌዋ. 6፡1-7 አንብብ። እግዚአብሔር ለሚሰርቁ ሰዎች የሰጠው መመሪያ ምንድን ነው? ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ይህንን እውነት እንዴት ተግባራዊ እንድናደርግ የሚፈልግ ይመስልሃል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ሉቃስ 18፡1-43

ሙላቱ የአንዲት ፍሬያማ ቤተ ክርስቲያን መሪ ነበር። ለብዙ ዓመታት ክርስቲያን ሆኖ ስለኖረ ከመዳኑ በፊት፡ ኃጢአት በሕይወቱ ውስጥ የነበረውን ኃይል ዘንግቷል። ስለሆነም ክርስቲያኖች በኃጢአት በሚወድቁበት ጊዜ ትዕግሥት በማጣት በብርቱ ቃላት ይገሥጻቸዋል። ገና ከኃጢአት እስራት ላልወጡት ዓለማውያንም ትዕግሥት የለውም። «ሁሉም ሰው ለምን እንደ እኔ አይሆንም? የጽድቅ ኑሮን የማይኖሩት ለምንድን ነው? እኔ በቤተ ክርስቲያኔ ውስጥ ካሉት አብዛኞቹ ሰዎች እሻላለሁ። እርግጠኛ ነኝ እግዚአብሔር በእኔ ሕይወት ኩራት ይሰማዋል» እያለ ያስባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ለክርስቲያኖች በሕይወታቸው ትዕቢት የሚሰማቸውና እንደ እነርሱ ያልሆኑትን ሌሎች ሰዎች መናቅ የሚቀናቸው ለምንድን ነው?

በክርስትና ሕይወታችን ረዥም ዘመን ያስቆጠርነውን ሰዎች ሰይጣን ሊያሸንፍ ከሚችልባቸው አደገኛ መንገዶች አንዱ፥ በጽድቃችን እንድንመካ በማድረግ ነው። ራሳችንን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚገኙት ሌሎች ሰዎች ጋር ማነጻጸር እንጀምርና የተሻልን ነን ብለን እናስባለን። ከዚያም መታበይ እንጀምራለን። ፈሪሳውያን እንደዚህ ዐይነት አመለካከት ነበራቸው። ራሳቸውን ኃጢአተኞች ናቸው ብለው ከሚቆጥሯቸው እንደ ቀራጮች ካሉት ሰዎች ጋር ያነጻጽሩና፣ «እግዚአብሔር በእኔ ሕይወት ኩራት ሳይሰማው አይቀርም። ብለው ያስባሉ። ነገር ግን ራሳችንን ማነጻጸር ያለብን ከእግዚአብሔር የጽድቅ መመዘኛ እንጂ፥ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሊሆን አይገባም። ይህንን በምናደርግበት ጊዜ ምን ያህል ኃጢአተኞች እንደሆንን ይገባናል። አሁንም የኃጢአት ! ተፈጥሮ ስላለን፣ አስተሳሰባችን የራስ ወዳድነት፣ ለሌሎች ሰዎች ያለን አመለካከት ኢየሱስ እንዲኖረን የሚፈልገው ዐይነት ፍቅር አይደለም። ስለሆነም ራሳችንን ከእግዚአብሔር ጋር በምናነጻጽርበት ጊዜ፣ ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከምንንቃቸው ጋለሞታዎች ጋር የሚቀራረብ ሕይወት እንዳለን እንገነዘባለን። ሁላችንም የእግዚአብሔር ምሕረት ያስፈልገናል። ልባችን በኃጢአታችን ሊሰበርና የእግዚአብሔርን ምሕረት ልንለምን ይገባል። ገና ከኃጢአት ጋር በመታገል ላይ ላሉትም ምሕረትን ልናደርግላቸው ይገባል። ለ40 ዓመት ክርስቲያን ሆኖ የኖረውና በቤተ ክርስቲያን መሪነት የሚያገለግለው የ60 ዓመቱ ሙላቱም እንደ ሌሎች ማንኛውም ሰዎች አሁንም ከኃጢአት ጋር እየታገለ ነው። ሁላችንም በመስቀሉ ፊት እኩል ነን። ሁላችንም የእግዚአብሔር ምሕረት የሚያስፈልገን ኃጢአተኞች ነን።

ኢየሱስ በይሁዳና በጴሪያ ሲያገለግል ቆይቷል፤ አሁን የምድር አገልግሎቱ በመጠናቀቅ ላይ ነው። ወደ ኢየሩሳሌም ሲቃረብ በቅርብ ቀን እንደሚሞት ያውቅ ነበር። በመጨረሻዎቹ ጥቂት ቀናት ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እርሱን መከተል ምን እንደሆነ በማስተማር፣ ስለሚገጥማቸውም ፈተና አስጠንቅቋቸዋል።

 1. ኢየሱስ በጸሎት ስለ መትጋት አስተማረ (ሉቃስ 18፡1-8)

እግዚአብሔር ሁልጊዜ ጸሎትን ይመልሳል? አዎን። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ የሚመልሰው እኛ በምንጠብቀው መንገድ ላይሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ በፍጥነት አዎንታዊ ምላሽ ሲሰጥ፣ ሌላ ጊዜ ግን «ጠብቅ» ይለናል። «የለም፣ እኔ ለአንተ የምፈልገው እንደዚህ ዐይነት ነገር አይደለም» የሚልበትም ጊዜ አለ። እኛ ግን ከእግዚአብሔር አፍ ለመስማት የምንፈልገው «እሺ፣ አደርግልሃለሁ» የሚለውን እንጂ፥ «አይሆንም» የሚለውን አይደለም። ነገር ግን ጳውሎስም እንኳ «መውጊያው» ከሥጋው እንዲነሣላት በጠየቀ ጊዜ የ«አይሆንም» መልስ ተሰጥቶታል (2ኛ ቆሮ. 12፡7-10)። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር «ጠብቅ» የሚል መልስ ይሰጠናል። ወይም ዝም ይላል። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ሳያቋርጡ ተግተው እንዲጸልዩ ነግሯቸዋል። ፍትሕ የማያውቀው ዳኛ በሴቲቱ ንዝነዛ ምክንያት ትክክል ከፈረደ፣ የሚወደንና ፍትሕን የሚወደው አምላካችን እግዚአብሔር ጸሎታችንን ምንኛ በጊዜ አሳምሮ ይመልስልን ይሆን? (ማስታወሻ፡ ኢየሱስ እግዚአብሔር አብ እንደ ዐመፀኛው ዳኛ ደጋግመን በጸሎት ልንጠይቀው የሚገባን መሆኑን እየተናገረ አይደለም። ይልቁንም በአፍቃሪ አባትና በዐመፀኛ ዳኛ መካከል ያለውን ልዩነት እያሳየ ነበር።)

የትምህርቱ አውድ የፍትሕ አስፈላጊነት ነው። ብዙውን ጊዜ የኢየሱስ ተከታዮች በኢ-ፍትሐዊ ዳኞች ይበደላሉ። እንዲያውም በዚህ ክፍለ ዘመን ብቻ ካለፉት ሌሎች ክፍለ ዘመናት ሁሉ በላይ ብዙ ክርስቲያኖች ለእምነታቸው ሞተዋል። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ክርስቲያኖች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? መበቀልና መዋጋት ያስፈልገናል? አያስፈልግም። እምነታችንን መተው አለብን? የለብንም። ልባችንን በእግዚአብሔር ፊት አፍስሰን ልንጸልይና ፍትሕን እንደሚያመጣ ልንተማመንበት ይገባል። አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ መልስ እስኪሰጠን ድረስ ደጋግመን መጸለይ አለብን። እግዚአብሔር በምንፈልገው መንገድ መልስ ሳይሰጠን ሲቀር እምነታችንን ለመተው ልንፈተን እንችላለን። ኢየሱስ ዳግም ሊመለስ ሲል ከበፊቱ የከፋ ስደት ይነሣል። ያን ጊዜ ብዙዎች ኢየሱስን በመከተል የሚከፈለውን ዋጋ ለመክፈል ፈቃደኛች አይሆኑም። ኢየሱስ በሚመለስበት ጊዜ እምነትን በምድር ላይ አገኝ ይሆን? በማለት የጠየቀው ለዚህ ነው። ጌታ በሚመለስበት ጊዜ በእምነት የሚመላለሱትን ሰዎች እንደሚያገኝ ባያጠራጥርም፣ በዚያን ጊዜ የኢየሱስ ተከታዮች በእርሱ ለመጽናት ከፍተኛ ዋጋ ይከፍላሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ኢየሱስ ጸሎትህን ወዲያውኑ የመለሰበትን ጊዜ አስታውሰህ ጻፍ። ለ) «አይሆንም» የሚል መልስ የሰጠህን ጊዜ ጻፍ። ሐ) «ጠብቅ» ካለህ በኋላ በራሱ ጊዜ የሚያስፈልግህን ነገር ስላደረገልህ ጊዜ ምሳሌ ስጥ። መ) ይህ ሳያቋርጡ ስለ መጸለይና ስለ ትሕትና ምን ያስተምረናል?

 1. ኢየሱስ እግዚአብሔር ምሕረትን ለሚፈልጉ ሰዎች እንደሚሰጣቸው አስተማረ (ሉቃስ 18፡9-14)

የሃይማኖት መሪዎች ራሳቸውን ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚያነጻጽሩበት ጊዜ መንፈሳዊ ኩራት ይሰማቸዋል። ይህ በፈሪሳውያን ሕይወት የታየ ሲሆን፣ በዚህም ዘመን የምንመለከተው ነው። ኢየሱስ በኃጢአቱ ተጸጽቶ በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ስለ ተደገፈ አንድ ቀራጭ እና እንደ ቀራጩ ባለመሆኑ በጽድቁ ስለተመካ ፈሪሳዊ የሚያስረዳ ታሪክ ተናግሯል። በዚህም ኢየሱስ ትሑትና የሚጸጸት ልብ ያላቸው ሰዎች ብቻ ኃጢአታቸውን እንደሚያውቁና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንደሚያገኙ አመልክቷል (መዝሙር 50፡16-17 አንብብ።] ከሌሎች የተሻልን በመሆናችን በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት እናገኛለን ከሚል አሳብ ልባችንን መጠበቅ አለብን። ባለማቋረጥ ኃጢአተኞች መሆናችንን በማስታወስ የእግዚአብሔርን ምሕረትና ጸጋ መማጸን አለብን!

 1. ልጆች እግዚአብሔርን የመከተል ምሳሌዎች ናቸው (ሉቃስ 18፡15-17)

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ሊያገኙ የሚችሉበትን መንገድ ለማስተማር ወደ ልጆች ማመልከቱ የሚደነቅ ነው። በምድር ላይ ልጆች ቸል ተደርገው የተተዉት ሰዎች አካል ናቸው። ለመብታቸው ለመከራከር የሚያስችል አካላዊ ብቃት ስለሌላቸው፣ ሰዎች በቀላሉ ይሰድቧቸዋል፤ ይጎዷቸዋል። ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ተጠግተው የሚኖሩ እንጂ፥ ለሌሎች ሰዎች ቁሳዊ በረከት የሚያስገኙ አይደሉም። ይሁንና ባይገባቸውም እንኳ በቶሎ የሚቀበሉና ከፍተኛ ፍቅር ያላቸው ናቸው። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የልጆች ጉዳይ እንደሚያሳስበው ገልጾላቸዋል። እኛም እንደ ልጆች ሁሉንም ነገር ባንረዳም እንኳ በፍጹም እምነትና ፍቅር ከእግዚአብሔር ጋር መዛመድ አለብን። ልጆች ያለ ብዙ ችግር ወንጌልን የሚቀበሉ የበሰሉ የመከር አዝመራዎች ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለልጆች ወንጌልን ለማካፈል ቤተ ክርስቲያንህ ምን እያደረገች ነው? ለ) የቤተ ክርስቲያንህ አገልጋዮች ልጆችን ከመናቅ ይልቅ እንደ ኢየሱስ የሚያከብሯቸው እንዴት ነው?

 1. ኢየሱስ ተከታዮቹ ከምንም ነገር በላይ እንዲወዱት ጠየቀ (ሉቃስ 18፡18-30)

ኢየሱስን በምንከተልበት ጊዜ ከሚያጋጥሙን ችግሮች አንዱ በልባችን ውስጥ የፍቅር ግጭት መኖሩና ኢየሱስ ደግሞ በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉም የላቀ ስፍራ መጠየቁ ነው። ለአንዳንዶች ፍቅር ማለት ቤተሰብ ነው። ለሌሎች ደግሞ ትምህርት ነው። እንደ ሀብታሙ ባለሥልጣን ላሉት ደግሞ ገንዘብና ሥልጣን፣ ብሎም ሥልጣን የሚያመጣው ምቾት ነው። ምንም እንኳ ሰውዬው በጣም ሃይማኖተኛና የብሉይ ኪዳንን ሕግ የሚጠብቅ ቢሆንም፣ ኢየሱስ በዚህ አልረካም። ወደ ወጣቱ ገዥ ሕይወት ዘልቆ በማየት መዋዕለ ንዋይ የልቡን ማዕከል እንደተቆጣጠረ ተገነዘበ። ለዚህ ወጣት ገዥ መድኃኒቱ በባርነት ከገዛውና የመጀመሪያውን ፍቅር ከወሰደበት ገንዘብ መራቅ ነበር። ስለሆነም ኢየሱስ የዘላለምን ሕይወት ከፈለገ ገንዘቡን ትቶ እንዲከተለው ጠየቀው። የሚያሳዝነው ወጣቱ ጊዜያዊ ጥቅም የሚያስገኝለትን ገንዘብ ትቶ የዘላለምን ሕይወት ለመቀበል አልፈለገም።

ኢየሱስ እርሱን ለመከተል ጥሪውን ቀላል እንዳልሆነ ገልጾአል። ገንዘብ ለማግኘት የተጠየቁትን ከማድረግ የማይመለሱትን ድሆችና ባላቸው የማይረኩትን ሀብታሞች ጨምሮ፣ ብዙ ሰዎች የገንዘብ ባሮች ናቸው። የኢየሱስ ተከታዮች ነን ከማለታችን በፊት ይህ መዳሰስ ያለበት አካባቢ ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር የምንወዳቸውን ነገሮች እንድንተው ካላስቻለን፣ ይህ የሚሞከር አይሆንም። ይህንን የሚያስችለው በሰውዬው ልብ ውስጥ ያለው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ብቻ ነው። ነገር ግን ልባችንን የሚቆጣጠሩትን ነገሮች አስወግደን ኢየሱስን ከሁሉም በበለጠ ስንወድ፣ ሕይወታችን ይለወጣል። በዚህ ጊዜ የዘላለምን ሕይወትና የወደፊት በረከቶችን ከማግኘታችንም በላይ፣ በዚህም ሕይወት ሽልማትን እናገኛለን። ያ ሽልማት ቁሳዊ ሀብት ሊሆን ወይም ላይሆን ይችላል፣ ኢየሱስ ከእኛ ጋር እንዳለና ሁሉም ነገር እንደሚበልጥ መገንዘቡ ከምንም ነገር የበለጠ ሀብት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ልብህን፡ ፍቅርህንና ሕይወትህን ለመቆጣጠር የሚፈልጉ ነገሮች የትኞቹ ናቸው? ለ) እነዚህን ነገሮች ከኢየሱስ በላይ የምትወድ መሆን አለመሆንህን እንዲያሳይህ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ጊዜ ውሰድ። ከዚያም ኢየሱስ በሕይወትህ ከሁሉም የሚበልጥ ፍቅር መሆኑን ለማረጋገጥ ምን ማድረግ እንዳለብህ ይገልጽልህ ዘንድ እግዚአብሔርን ጠይቀው።

 1. ኢየሱስ ሞቱንና ትንሣኤውን ተነበየ (ሉቃስ 18፡31-34) .

ጴጥሮስ ኢየሱስ መሢሕ መሆኑን ከመሰከረ በኋላ፣ ለደቀ መዛሙርቱ የመስቀል ላይ ሞት እንደሚጠብቀው ይነግራቸው ጀመር። ወደ መስቀሉ ይበልጥ በቀረበ ቁጥር፥ ደቀ መዛሙርቱን ስለ ሞቱ አብልጦ ያስጠነቅቃቸው ነበር። አሁን በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ሊሆን ስላለው ነገር በግልጽ ነግሯቸዋል። በአይሁዶች እጅ ለአሕዛብ አልፎ እንደሚሰጥ ነገራቸው። አሕዛብና አይሁዶች በእርሱ ላይ ከተሳለቁ፣ ሰደቡት፣ ከተፉበትና ከገረፉት በኋላ ገድለውታል። በዚህም ኢየሱስ እርሱን በመከተላቸው ምክንያት የመሳለቅ፣ የመሰደብ፣ የመገረፍ፣ የመተፋትና የሞት ስደት ለሚደርስባቸው ክርስቲያኖች ምሳሌ ሆኗል።) ከዚያም በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ በግልጽ ነገራቸው። በኢየሱስ ላይ ከደረሰው ነገር በድንገት የተከሰተ ምንም አልነበረም፡፡ ኢየሱስ የሚደርስበትን ሁኔታ እንዴት አወቀ? ይህንን ያወቀው አምላክ ስለሆነና ሁሉንም ነገር ስለሚንዘብ ብቻ ነውን? አይደለም። ሉቃስና ሌሎችም የወንጌል ጸሐፊዎች ካደረጓቸው ነገሮች አንዱ፥ የብሉይ ኪዳን ክፍል ሁሉ ወደ ኢየሱስ እንደሚያመለክት መግለጽ ነበር። ኢየሱስ ከመወለዱ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው ተንብየዋል።

 1. ኢየሱስ ዐይነ ስውሩን ለማኝ ፈወሰው (ሉቃስ 18፡35-43)

ሉቃስ ኢየስሱ ከመሞቱ በፊት እንዳደረገው በመግለጽ ያቀረበው የመጨረሻው ተአምር ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ላይ ሳለ ከኢያሪኮ ውጭ ተቀምጦ የነበረውን ለማኝ ዐይን መፈወሱ ነው። ምንም እንኳ አብዛኞቹ አይሁዶች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ዕውራን ቢሆኑም፣ ለማኙ ዐይነ ስውር ኢየሱስ መሢሕ መሆኑን ለመገንዘብ ችሎ ነበር። ስለሆነም ሥጋዊ ብርሃኑ በርቶለታል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ሉቃስ 17፡1-37

 1. እንደ ኢየሱስ ተከታዮች እንዴት መኖርና ማሰብ እንደሚገባ የሚያሳዩ ትምህርቶች (ሉቃስ 17፡1-10)

ሀ. ደቀ መዛሙርት የማሰናከያ ዓለት ሆነው ሰዎችን ለኃጢአት እንዳይዳርጉ መጠንቀቅ አለባቸው። የኢየሱስ ተከታዮች ኃጢአት መሥራታቸው የማይቀር ጉዳይ ነው። ኃጢአትን እንድናደርግ የሚፈትኑን ብዙ ፈተናዎች አሉ። ይህ ግን አንድ ሰው በተለይም የቤተ ክርስቲያን መሪ በግድየለሽነት እንዲኖርና ሌላውን ሰው ወደ ኃጢአት እንዲመራ ወይም ሌላውን ሰው በኃጢአት እንዲፈትን ማመኻኛ አይሆነውም። ኢየሱስ የዚህን ድርጊት ስሕተት ለማሳየት ሲል ደቀ መዛሙርቱ ፈሪሃ እግዚአብሔር እንዲያድርባቸውና ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ንጹሓን ይሆኑ ዘንድ እንዲያግዙ በብርቱ ቃል ያስጠነቅቃቸዋል።

ለ. ደቀ መዛሙርት ስለ ሌሎች አማኞች ግድ ሊላቸውና ኃጢአት በሚሠሩበት ጊዜ፥ ወቅሰው እግዚአብሔርን ወደ መታዘዝ ሊመልሷቸው ይገባል።

ሐ. ደቀ መዛሙርት ሁልጊዜ ፈጥነው ይቅር ማለት አለባቸው። ቂም መያዝ የለባቸውም። አንድ ሰው ደጋግሞ ቢበድላቸው ይቅር ከማለት ወደ ኋላ ማለት የለባቸውም።

መ. ዋናው ጉዳይ የኢየሱስ ተከታዮች ተጨማሪ እምነት ማግኘታቸው ሳይሆን፣ እምነታቸውን በሥራ ላይ ማዋላቸው ነው። ታላቁ አምላካችን ትንሹን እምነታችንን በመጠቀም ለእርሱ ክብር እንድናውለው መጠየቅ ይገባል። ኢየሱስ የሚፈልገው ዐይነት ደቀ መዝሙር ሆኖ ለመኖር ከባድ ነው። ነገር ግን የእምነት ዐይናችንን በእርሱ ላይ ካኖርን፣ ታላላቅ ነገሮችን እንድናደርግ ያስችለናል።

ሠ. ኢየሱስ ጌታ ሲሆን፣ ደቀ መዛሙርቱ ደግሞ ባሪያዎቹ ናቸው። ይህ ወደ ሁለት የተሳሳቱ አመለካከቶች ሊመራን ይችላል። አንደኛው፥ አንዳንድ ሰዎች በትዕቢት፣ «እኔ የኢየሱስ ተከታይ ነኝ። እናም ከአንተ እሻላለሁ። ለኢየሱስ ያደረግኋቸውን ነገሮች ተመልከት ሊሉ ይችላሉ። ሁለተኛው፣ ጥቅምን ለማግኘት ሆን ብሎ የመሥራት አደጋ ሊያጋጥም ይችላል። «ኢየሱስ የበለጠ ስለሚሰጠኝ ለድሆች መስጠት አለብኝ። ሽልማት ስለማገኝበት ኢየሱስን አገለግለዋለሁ።» ኢየሱስ ላደረግንለት አገልግሎት እንደሚሸልመን ጥርጥር የለውም። ይህ ማለት ግን ዋጋ ለማግኘት ስንል መሥራት አለብን ማለት አይደለም። በሥራ ሲጣደፍ የደከመ ባሪያ ጌታው ከመብላቱ በፊት ምግብ አይቀርብለትም። አንድ ጌታም ባሪያው ኃላፊነቱን ስለተወጣ ለማመስገን ኃላፊነት የለበትም። ልክ እንዲሁ፣ እኛም ለክርስቶስ ባደረግንለት ነገር ከመመካት ይልቅ፥ የባሪያን ትሕትና ልንላበስ ይገባል። የድርሻችንን ብቻ እንደተወጣን በትሕትና ልንገነዘብ ይገባል። እግዚአብሔርን የምናገለግለው ምስጋናውን ወይም ጥቅም በመፈለግ መሆን የለበትም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንዳንድ ጊዜ፣ «ለእግዚአብሔር ብትሰጥ እርሱ ብዙ ይሰጥሃል። እግዚአብሔር ያንተ ባለ ዕዳ አይደለም» የሚሉ አሳቦችን እንሰማለን። ሉቃስ 17፡1-10 ካነበብክ በኋላ ለዚህ አባባል ምን ዐይነት መልስ ትሰጣለህ? ለ) ኢየሱስን በምናገለግልበት ጊዜ ምን ዐይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? የራስ ወዳድነት አሳቦች የትኞቹ ናቸው? ኢየሱስን ለማክበር የልባችንን ምስጋና የሚያሳዩትስ የትኞቹ ናቸው?

 1. ኢየሱስን ያመሰገነው ለምጻም (ሉቃስ 17፡11-19)

ራስ ወዳድነት በሁላችንም ዘንድ የሚገኝ ችግር ነው። እግዚአብሔር አንድ መልካም ነገር ካደረገልን በኋላ እንኳ ለማመስገን ይከብደናል። ይህንን ለማረጋገጥ ጸሎታችን ምን እንደሚመስል ማጤኑ በቂ ነው። የተለያዩ ነገሮችን ለመጠየቅና ምስጋና ለማቅረብ ከምንጠቀምባቸው ቃላት የትኞቹ ይበዛሉ? ሉቃስ የኢየሱስ ተከታዮች የምስጋና ልብ ሊኖራቸው እንደሚገባ ያስተምራል። ይህንን አሳብ ለማስተማር ኢየሱስ 9 አይሁዶችና 1 ሳምራዊ ያለበትን የለምጻሞች ቡድን ስለፈወሰበት አጋጣሚ ተርኳል። የሚገርመው ከተፈወሰ በኋላ ወደ ኢየሱስ ተመልሶ ምስጋናውን ያቀረበው ሳምራዊው ብቻ ነበር። በእግዚአብሔር ቤት ረዥም ጊዜ የኖርን ሰዎች የአመስጋኝነት ልብ ሊኖረን እንደሚገባ መገንዘብ አለብን። ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔር እንደሚባርከን እያሰብን ለማመስገን ግን አንፈልግም። እንደ ጥንቶቹ እስራኤላውያን ነገሮች እንደጠበቅናቸው ሳይሆኑ ሲቀሩ፥ ፈጥነን እናጉረመርማለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ኢየሱስን እንድታመሰግን የሚያደርጉህን አሥር ነገሮች ዝርዝር። በጸሎትህ የተለያዩ ነገሮችን እንዲያደርግልህ ከመጠየቅ ይልቅ ያደረገልህን ነገር እየዘረዘርህ ማመስገንን ተለማመድ።

 1. ኢየሱስ ስለ መጭው የእግዚአብሔር መንግሥት ያቀረበው ትምህርት (ሉቃስ 17፡20-37)

አዲስ ኪዳን «የእግዚአብሔር መንግሥት» የሚለውን ሐረግ የሚጠቀመው በሁለት ዐበይት መንገዶች ነው። አንደኛው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ የጀመረው መንፈሳዊ መንግሥት አለ። ኢየሱስ እንደ ንጉሥ በሰዎች ሕይወት ወይም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚነግሥበት ጊዜ ሁሉ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በዚያ ይገኛል። ሁለተኛው፣ ይበልጥ ሙሉ የሆነና የሚታይ የእግዚአብሔር መንግሥት እንድ ቀን ይመጣል። ይህ የሚታይ መንግሥት የሚመጣው የኢየሱስ አገዛዝ በዓለም ሁሉና በሰዎች ሁሉ ላይ በሚገለጽበት ጊዜ ይሆናል።

ፈሪሳውያን ስለዚያ የሚታይ መንግሥት ኢየሱስን ጠይቀውታል። ኢየሱስ ግን ትኩረታቸውን በእርሱ መምጣት በተጀመረው መንፈሳዊ መንግሥት ላይ አድርጓል። ኢየሱስ በመካከላቸው ያለው መንግሥት በመጨረሻው ዘመን ስለሚመጣው መንግሥት ከማሰብ እንደሚበልጥ በመግለጽ አስጠንቅቋቸዋል። ንጉሡ ኢየሱስ በዚያ ነበር። እርሱን ምን ማድረግ ነበረባቸው? ፈሪሳውያን ታላቅና የሚታይ መንግሥት ከመጠባበቅ ይልቅ ኢየሱስ ላመጣው ስውር መንፈሳዊ መንግሥት ትኩረት መስጠት ነበረባቸው። ይሁንና ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ዘላለማዊና የሚታይ የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ እንደሚመጣ የሚለዩባቸውን አንዳንድ ምልክቶች ሰጥቷል።

ሀ. ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን እንደ ድል አድራጊ ንጉሥ ተመልሶ ሲመጣ ለመመልከት ፈልገው ነበር። ነገር ግን ይህ እነርሱ በፈለጉበት ጊዜ የሚሆን አልነበረም። ይህ ከመሆኑ በፊት ኢየሱስ መከራ መቀበልና መሞት ነበረበት።

ለ. የመብረቅ መምጫ እንደማይታወቅ ሁሉ የኢየሱስም መምጫ ቅጽበታዊና የማይጠበቅ ይሆናል። የኢየሱስ ተከታዮች መሢሕ ነን የሚሉትን ለመቀበል መጣደፍ አልነበረባቸውም።

ሐ. ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ ሰዎች በመብላት፣ በመጠጣትና በመጋባት የተለመደ የሕይወት ዘይቤ ይከተላሉ። የመምጫው ጊዜ በኖኅ ዘመን እንደተከሰተው ጎርፍ ወይም በሎጥ ዘመን በሰዶምና በገሞራ ላይ እንደተከሰተው አደጋ ቅጽበታው ይሆናል።

መ. የኢየሱስ መምጫ በጣም ቅጽበታዊ ስለሚሆን፣ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ቁሳዊ ሀብት መጨነቅ የለባቸውም። ሁሉንም ትተው መሸሽ ነበረባቸው። የኢየሱስ ተከታዮች ቁሳዊ ሀብቷን ለመመልከት ወደ ኋላ እንደተመለሰችው የሎጥ ሚስት መሆን የለባቸውም። (ማስታወሻ፡ የጥንት ቤቶች ጣሪያቸው ዝርግ ነበር፤ በሙቀት ጊዜ ሰዎች አየር ለማግኘት ወደዚያ ይወጡ ነበር። የመውጫ ደረጃዎቹ ከቤቱ ውጭ ስለነባር ኢየሱስ ንብረቶቻቸውን ለመውሰድ ወደ ቤቱ መግባት እንደሌለባቸው ይናገራል።) በምድራዊ ነገሮች ላይ የሙጥኝ የሚሉ ደቀ መዛሙርት ሕይወታቸውን ያጣሉ።

ሠ. የመጨረሻው ዘመን መከፋፈልን ያመጣል። የቅርብ ጓደኛሞች ወይም የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆን ብቻ በቂ አይደለም። እግዚአብሔርን የሚወዱ ሰዎች ወደ ዘላለማዊ ስፍራቸው ሲወሰዱ፣ የቀሩት – ግን የእግዚአብሔርን ቁጣ ይቀበላሉ።

ረ. ኢየሱስ የሚመለስበትን ስፍራ «አሞራዎች» ያመለክታሉ። ይህ ለመረዳት የሚያስቸግረን የኢየሱስ አባባል ምናልባትም አይሁዶች ሲጠቀሙበት የነበረ ምሳሌያዊ አነጋገር ሳይሆን አይቀርም። የአንድ አሞራ ማንዣበብ አንድ ነገር እንደ ሞተ ለማመልከት በቂ እንዳልሆነና በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ስለመመለሱ ከተነገሩት ምልክቶች አንዱ ብቻ መታየቱ በቂ እንዳልሆነ ለማመልከት የፈለገ ይመስላል። ነገር ግን ኢየሱስ የሰጣቸው ምልክቶች ሁሉ በሚፈጸሙበት ጊዜ የመምጫው ጊዜ እንደ ደረሰ እንገነዘባለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ብዙ ክርስቲያኖች ኢየሱስ በቶሎ ይመለሳል ብለው ያስባሉ። ሀ) በዘመናችን ኢየሱስ ከሰጣቸው ምልክቶች የትኞቹ በመፈጸም ላይ ናቸው? ለ) እስካሁን ያልታዩት ምልክቶች የትኞቹ ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ሉቃስ 16፡16-31

 1. ኢየሱስ በብሉይ ኪዳንና በፈሪሳያውን መካከል ስላለው ግንኙነት ያቀረበው ትምህርት (ሉቃስ 16፡16-18)

እዚህ ላይ ሉቃስ ኢየሱስ በተለያዩ ጊዜያት ያስተማራቸውን እውነቶች ጠቅለል አድርጎ የሚያቀርብ ይመስላል። አጠር ብለው ከመቅረባቸው የተነሣ አንዳንዶቹን ለመረዳት አስቸጋሪ ነው።

ሀ. ከሙሴ ዘመን ጀምሮ እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ አይሁዶች ዘወትር ብሉይ ኪዳንን ሲማሩ ቆይተዋል። አሁን ኢየሱስ በመካከላቸው ተገኝቶ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች እየነገራቸው ነበር። ነገር ግን ለመጥምቁ ዮሐንስም ሆነ ለኢየሱስ የተሰጡ ሁለት የተለያዩ ምላሾች ነበሩ። ፈሪሳውያን ብሉይ ኪዳንን እየታዘዝን ነው ብለው ቢያስቡም ይህንኑ እያደረጉ አልነበረም። (ለኢየሱስ ምን ዐይነት አመለካከት እንደ ነበራቸው በሉቃስ 16፡14 ላይ አንብብ።) መጥምቁ ዮሐንስም ሆነ ኢየሱስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ያስተማሩትን መልካም የምሥራች ለመቀበል አልፈለጉም። ስለሆነም የእግዚአብሔርን በረከት ሊቀበሉ አልቻሉም። በሌላ በኩል ደግሞ ተራ አይሁዶችና የተናቁ ኃጢአተኞች የእግዚአብሔር መንግሥት አካል ለመሆን ይሽቀዳደሙ ነበር። እነዚህ ሰዎች በእግዚአብሔር መንግሥት ላይ ስላተኮሩ፣ የዮሐንስንም ሆነ የኢየሱስን ትምህርቶች ሰምተው ለመታዘዝ ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር።

ለ. ምንም እንኳ ፈሪሳውያን ኢየሱስ የብሉይ ኪዳን ሕግ እንዳልጠበቀ በመግለጽ ቢከሱትም፣ እርሱ ግን ሕጉን እየጠበቀ ነበር። በኢየሱስ ምክንያት ከእግዚአብሔር ሕግ ውስጥ የሚፋቅ አንድም ሕግ የለም። አዲሱ ኪዳን አሮጌውን የብሉይ ኪዳን ሕግ ይፈጽመዋል እንጂ አይሽረውም።

ሐ. ፈሪሳውያን የብሉይ ኪዳን ሕግን እንዳላከበሩና ኢየሱስ ግን ይህንን ሕግ እንደፈጸመ ከምናስተውልበት መንገድ ውስጥ አንዱ በፍች ጉዳይ ላይ የቀረበው ትምህርት ነው። ፈሪሳውያኑ በሕጉ ዙሪያ ሰበብ በመፈለግ ፍችን ቀላል ለማድረግ ይጥሩ ነበር። ነገር ግን የእግዚአብሔርን ሕግ ለመፈጸም የፈለገው ኢየሱስ ፍችና ዳግም ጋብቻ በእግዚአብሔር ፊት ዝሙት መሆኑን በመግለጽ ተቃውሟል።

 1. የሀብታሙ ሰውዬና የአልዓዛር ታሪክ (ሉቃስ 16፡19-31)

ብዙውን ጊዜ ሕይወት በምድር ላይ ችግር የበዛበት ናት። ከእግዚአብሔር ልጆች አንዱ ለማኝ ሊሆንና ከሰይጣን ልጆች አንዱ ሀብታም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ከዚህ የሚበልጠው በዘላለማዊ መንግሥት የሚሆነው ነገር ነው። በዚያ ድሀ የነበረው የእግዚአብሔር ልጅ ሲያልፍለት፣ ሀብታም የነበረው የሰይጣን ልጅ የሥቃይ ሰው ይሆናል። በዚህ የሀብታሙ ሰውና የአልዓዛር ታሪክ፣ ኢየሱስ አይሁዶች አሁን የእግዚአብሔርን ቃል እንዲሰሙ ያስጠነቅቃቸዋል። ከሞት በኋላ ንስሐ ገብተው ሕይወታቸውን የሚለውጡበትን ዕድል አያገኙምና። ሉቃስ በተጨማሪም ስለ ገንዘብ ያለን አመለካከት መንፈሳዊ ሕይወታችን ምን እንደሚመስል ጥሩ አመልካች እንደሆነ እየገለጸ ነበር። በገንዘብ ጉዳይ ላይ ምሕረትን አለማሳየትና ንፉግ መሆን የእግዚአብሔር ተከታዮች አለመሆናችንን ያመለክታል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ይህ ምሳሌ ነው ወይስ እውነተኛ ታሪክ በሚለው አሳብ ላይ ይከራከራሉ። ታሪኩ ምላሌ ከሆነ፣ ኢየሱስ የባለታሪኮቹን ስም ስለጠቀሰ ምሳሌ ነው ለማለት የሚቻል አይመስልም። ስለሆነም፣ ብዙ ምሑራን ታሪኩ እውነተኛ እንደሆነና ከሞት በኋላ የሚሆነውን የሚያውቀው ኢየሱስ በሀብታሙ ሰውና በድሀው ላይ የደረሰውን ያውቅ እንደነበር ይስማማሉ። (ይህ ኢየሱስ ከሞት ያስነሣው የማርያምና ማርታ ወንድም ታሪክ እንዳልሆነ አስተውል።) ይህ ምሳሌ ይሁን እውነተኛ ታሪክ በትክክል ስለማናውቅ፣ ከሞት በኋላ ስለሚሆነው ነገር እንደ ማብራሪያ ከመጠቀም መጠንቀቅ አለብን።

ኢየሱስ የሁለቱን ሰዎች ሕይወት አነጻጽሯል። አንደኛው ሀብታም ሲሆን፣ በአለባበሱ (ሐምራዊና የተልባ እግር በጥንቱ ዘመን በአብዛኛው ነገሥታት የሚለብሱት እጅግ ውድ ልብስ ነበር)፥ በአኗኗሩና በገንዘቡ ይደሰት ነበር። ይህ ሰው ገንዘቡን ሁሉ የሚጠቀመው ለራሱ ነበር። ሌላኛው ደግሞ ምንም የሌለውና ከውሾች በቀር ሰው የማይቀርበው ምስኪን ነበር። ሁለቱም ሰዎች ሞቱ። በዚህ ጊዜ ስፍራቸውን ተለዋወጡ። አልዓዛር ለጻድቃን ወደ ተዘጋጀውና «የአብርሃም እቅፍ» ወደሚባለው ስፍራ ተወሰደ። ሀብታሙ ሰውዩ ግን ለኃጢአተኞች ወደ ተዘጋጀውና ሲኦል በመባል ወደሚታወቀው ስፍራ ተወሰደ። ስለ አብርሃም እቅፍ የተነገረ ብዙ ነገር ባይኖርም፣ የበረከት ስፍራ እንደሆነ እናምናለን። ሲኦል ግን የእሳትና የሥቃይ ስፍራ እንደሆነ ተገልጾአል።

ሀብታሙ ሰውዬ አብርሃምና አልዓዛር የደስታ ሕይወት ሲኖሩ ቢመለከተም፥ ወደዚያ ግን መሄድ አይችልም ነበር። ስለሆነም አልዓዛር መጥቶ የተቃጠለ ምላሱን በውኃ ያረጥብለት ዘንድ አብርሃምን ለመነ፡፡ ነገር ግን አሁን መከራ የመቀበል ተራው እንደ ደረሰና ከሞት በኋላ ሰዎች ከአንዱ ወገን ወደ ሌላው ሊዛወሩ እንደማይችሉ ተገለጸለት። በዚህ ጊዜ ሰውዬው አልዓዛር ወደ ወንድሞቹ ተልኮ የሲኦልን አስከፊነት እንዲነግራቸውና ሕይወታቸውን ለውጠው ወደ ሲኦል ከመውረድ እንዲተርፉ እንዲያደርግ ለመነ አብርሃም ግን ይህንኑ እውነት ከብሉይ ኪዳን ሊማሩ እንደሚችሉና ይህንን ለማድረግ ካልፈቀዱ የአልዓዛር መሄድ ለውጥ እንደማያመጣ ተናገረ።

ከዚህ ታሪክ ምን ያህሉን ለመተርጎም እንደምንችል ለመገንዘብ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ የሚከተሉትን እውነቶች መረዳቱ ተገቢ ይመስላል።

ሀ. ድሀ መሆን አንድን ሰው ወደ መንግሥተ ሰማይ እንደማያስገባው፣ ሀብታም መሆን ደግሞ አንድን ሰው ወደ ሲኦል እንደማያወርደው ከመጽሐፍ ቅዱስ እንገነዘባለን። መንግሥተ ሰማይ መግባትን አስመልክቶ፣ የአንድ ሰው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የመንፈሳዊ ሕይወቱን ያህል አስፈላጊ አይደለም። ነገር ግን ሕይወታችን፣ በተለይም የገንዘብ አጠቃቀማችንና ለድሆች ምሕረትን ማሳየታችን ጥሩ የመንፈሳዊ ሕይወት ምልክት ነው።

ለ. ከሞትን በኋላ እምነታችንንና ተግባራችንን ልንለውጥ አንችልም። ዘላለማዊ ሁኔታችን ተወስኖ አልቋል። ከሞት በኋላ የምንሄድበትን የሚወስነው ዛሬ በሕይወት ሳለን የእግዚአብሔርን ቃል እውነት ከሕይወታችን ጋር ማዛመዳችን ነው።

ሐ. ሙታን ሁሉ የሚሄዱበት ሁለት ዐበይት ስፍራዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንደኛው የበረከትና የክብር ስፍራ ሲሆን፣ ሌላኛው የቅጣትና የሥቃይ ስፍራ ነው። ሕይወት ከሞት በኋላ ምን እንደሚመስል ለመገንዘብ ይህን ምሳሌ ምን ያህል መጠቀም እንዳለብን አናውቅም። ወይም ደግሞ ምሳሌው የአዲስ ኪዳንን ሳይሆን የብሉይ ኪዳንን ዘመን ሁኔታ ብቻ የሚያመለክት እንደሆነም ግልጽ አይደለም። አንዳንድ ሰዎች ይህ ከኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በፊት የነበረውን የብሉይ ኪዳን ሁኔታ እንደሚያመለክት ይናገራሉ። በአንድ ሰፊ የሙታን ስፍራ ሁለት ክፍሎች ነበሩ። ከእነዚህም መካከል አንዱ የጻድቃን ነፍስ መኖሪያ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የኃጢአተኞች ነፍስ መኖሪያ ነው። እነዚህ ሰዎች እንደሚያስቡት፣ ከኢየሱስ ትንሣኤ በኋላ የጻድቃን ነፍስ ወደ መንግሥተ ሰማይ ተወስደዋል። ለዚህም ነው ጳውሎስ ከሥጋ ውጭ መሆን ማለት ከኢየሱስ ጋር በሰማይ መሆን ማለት ነው የሚለው ሲሉ ያስተምራሉ (2ኛ ቆሮ. 5፡6-9)። የዕብራውያን ጸሐፊ የጻድቃን ነፍሳት ስላሉበት ሰማይ ጽፎአል (ዕብ 12፡22-24)። በመጨረሻው ዘመን የጻድቃን ነፍስ ሥጋ ከመቃብር የሚነሡ ሲሆን፣ አዲሱ አካላቸው ከነፍሳቸው ጋር ተዋሕዶ ለዘላለም በእግዚአብሔር መንግሥት ደስ ይሰኛሉ። የኃጢአተኞችም ነፍስ ተነሥተው ከነፍሳቸው ጋር በመዋሐድ ለዘላለም የእግዚአብሔርን ፍርድ ይቀበላሉ (ራእይ 20፡11-15)።

መ. ታሪኩ አይሁዶች ለማመን አለመፈለጋቸውን በጽኑ የሚያመለክት ይመስላል። ፈሪሳውያን እንደ ሀብታሙ ሰውዬ ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ብሉይ ኪዳንን ለመረዳትና ለመታዘዝ ፈቃደኞች አልነበሩም። ኢየሱስ ቀደም ብሎ አንድ ሰው ከሞት አስነሥቷል። ከዚህ በኋላም አልዓዛር የተባለ ሌላ ሰው ከሞት ያስነሣ ነበር። ከዚያም ራሱ ኢየሱስ ከሞት ይነሣል። ነገር ግን ከእነዚህ ክስተቶች አንዱም የአብዛኞቹን አይሁዶች ልብ ሊለውጥና በኢየሱስ እንዲያምኑ ሊያደርግ አልቻለም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የሀብታሙ ሰውዬ ዕጣ እንዳይገጥመን፥ ሕይወታችንን እንድንመረምር ይህ ታሪክ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ የሚሰጠን እንዴት ነው? ለ) የገንዘብ አያያዛችንና ድሆችን የምናስተናግድበት መንገድ መንፈሳዊ ሁኔታችንን ደህና አድርገው የሚያሳዩት እንዴት ነው? ሐ) በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች ዙሪያ ሕይወትህን መርምር። በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች ላይ ለኢየሱስ ክርስቶስ ትታዘዝ እንደሆነ መንፈስ ቅዱስ እንዲያሳይህ ጠይቅ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)