የሕይወት እንጀራ

2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች

መንፈሳዊ መሪ ለአዲሱ ኪዳንና ለእግዚአብሔር የማስቻል ኃይል አጽንኦት ይሰጣል (2ኛ ቆሮ. 2፡14-3፡18)።

ጳውሎስ ወደ በኋላ ቲቶን አግኝቶ ስለ ቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ንስሐና የአመለካከት ለውጥ ስለመስማቱ ይናገራል። ይህ የልብ ለውጥ የጳውሎስን ልብ በደስታ ሞላው (2ኛ ቆሮ. 7፡5-16)። ከቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጋር ስለነበረው ግንኙነት ማሰብ ሲጀምር አእምሮው እግዚአብሔርን ስለማገልገሉ አስደናቂ ምሥጢር ያስብ ጀመር። ስለሆነም፥ ከ2ኛ ቆሮ. 2፡14 እስከ 2ኛ ቆሮ. 7፡1 ድረስ ጳውሎስ ስለ አገልግሎቱና እግዚአብሔር በመሪዎች ሕይወት ውስጥ ስለሚያከናውናቸው ተግባራት የተለያዩ ነገሮችን ያብራራል። ሀ. በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የትኛውም ዓይነት ድልና ዕድገት ሊገኝ የሚችለው ከእግዚአብሔር ሥራ የተነሣ ነው (2ኛ ቆሮ. 2፡14-16)። ጳውሎስ ይህንኑ አሳብ ለማብራራት ስለ ሮም ጀኔራል የሚያስረዳ ምሳሌ ተጠቅሟል። ጀኔራሉ በጦርነት በሚያሸንፍበት ጊዜ በወታደሮቹና በምርኮኞቹ ታጅቦ ከጦር ሜዳ በፈረስ ይመለሳል። የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ጀኔራል የሆነው ክርስቶስ ሁልጊዜም ባሪያዎቹንና ቤተ ክርስቲያንን በድል ይመራል። ብዙውን ጊዜ ጄኔራሉ ወደ ከተማ በሚገባበት ጊዜ ዕጣን ያጥኑለት ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ የክርስቶስ ወታደሮች (ክርስቲያኖች) ለክርስቶስ በሚሠሩበት ጊዜ እንደ ዕጣን የሚያውድ መዓዛ ይረጫሉ። ወንጌሉን ሰምተው ለሚድኑ ሰዎች የዘላለምን ሕይወት መዓዛ እናውዳለን። ወንጌሉን ሰምተው ለማመን ለማይፈልጉ ሰዎች ግን የሞትን መዓዛ እናውዳለን። የሞት ምርኮኞች ብዙውን ጊዜ እንደሚገደሉ ሁሉ የማያምኑ ሰዎችም የዘላለምን ሞት ይጋፈጣሉና። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በማኅበረሰብህ ውስጥ የሕይወትና የሞት መዓዛ የምትሆንባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) ያ መዓዛ ሊበላሽ የሚችልባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ. ማንም ሰው የራሱን ጥበብና ችሎታ በመጠቀም ድል ሊነሣና ሌሎችን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊመራ አይችልም። ይህንን ሊያደርግ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው (2ኛ ቆሮ. 2፡16)፡፡ ሐ. በመንፈሳዊ ጦርነት ለክርስቶስ የሚዋጉ ሰዎች ንጹሕ ልብ ይዘው መዝለቃቸው በጣም አስፈላጊ ነው። የምንዋጋው ለራሳችን ሳይሆን ራሱ እግዚአብሔርን በመወከል ስለሆነ፥ ወንጌሉን በእውነትና በታማኝነት መስበክ እለብን (2ኛ ቆሮ.2፡17)። ምናልባትም ጳውሎስ ይህንን የተናገረው በቆሮንቶስ የተለየ የአገልግሎት እመለካከት የያዙ መሪዎች ወይም የሐሰት አስተማሪዎች እንደነበሩ ለማመልከት ይሆናል። እነዚህ ሰዎች ከወንጌል አገልግሎት የተነሣ በሚያገኙት ገንዘብና ክብር ላይ ያተኩሩ ነበር። ወንጌሉን እንዳሻቸው በመጠምዘዝ ከእግዚአብሔር መልእክት ይልቅ ለሰዎች ጆሮ እንደሚጥም አድርገው ያቀርቡ ነበር። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና ወንጌላውያን በሰይጣን ወጥመድ ተይዘው የተሳሳቱ ምክንያቶችን ሊያገለግሉ የሚችሉባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪ ከሆንህ በጸሎት መንፈስ ሆነህ የአገልግሎት መነሻ ምክንያትህን መርምር። ሰይጣን አነሣሽ ምክንያቶችህን አበላሽቶ እንደሆነ ለማወቅ ልብህን መርምር። እንደዚያ ከሆነ፥ በጸሎት የእግዚአብሔርን ይቅርታ ጠይቅ። ካልሆነ፥ እግዚአብሔርን ስለጠበቀህ አመስግነውና በሙሉ ልብህ እርሱን የምትከተልበትን ጥበብ እንዲሰጥህ ጠይቅ። መ. የጳውሎስ የሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ ምስክርነት ውጤት፥ አስፈላጊዎቹ የደብዳቤ ማስተዋወቂያዎች ራሳቸው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ነበሩ (2ኛ ቆሮ. 3፡1-3)። አንዳንድ የሐሰት አስተማሪዎች ከታዋቂ መሪዎች ወይም ከኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን የድጋፍ ደብዳቤ ይዘው በመምጣት እውነተኞቹ የቤተ ክርስቲያን ተወካዮች መሆናቸውን ሳይናገሩ አልቀሩም። (የኢየሩሳሌሟ ቤተ ክርስቲያን ቀደም ሲል ለጳውሎስ እንዲህ ዓይነት ደብዳቤ ሰጥታ ነበር- የሐዋ. 15፡23-29 አንብብ።) ነገር ግን ጳውሎስ በብጣሽ ወረቀት ወይም በሰዎች ድጋፍ ላይ አልተደገፈም ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በሕይወቱ ውስጥ በመሥራቱ ሰዎች በክርስቶስ አምነው ዳኑ። ጳውሎስ የፈለገው የእግዚአብሔር ተቀባይነትና ማረጋገጫ ይኸው ብቻ ነበር። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ማመን እግዚአብሔር ብዕር አንሥቶ በልባቸው ውስጥ ጳውሎስ አገልጋይ እንደሆነ የጻፈላቸው ያህል ነበር። ጳውሎስ ማንኛውንም ዘላቂ ተግባር ሊፈጽም የሚችለው እግዚአብሔር እንደሆነ ስለሚያውቅ፥ በራሱ ችሎታና ስሜት ላይ አልተደገፈም ነበር። እንደ ጳውሎስ ያሉትን ሰዎች በስጦታ ሞልቶ የተጠቀመባቸው ራሱ እግዚአብሔር ነበር። ሠ. ጳውሎስ ከብሉይ ኪዳን ሕግጋት ይልቅ እጅግ በሚልቀው በአዲስ ኪዳን ላይ ትኩረት ሰጥቷል (2ኛ ቆሮ. 3፡4-18)። አይሁዳውያን የነበሩት የሐሰት አስተማሪዎች በብሉይ ኪዳን ሕግጋት ላይ በማተኮር የቆሮንቶስን ክርስቲያኖች ግራ ሳያጋቡ አልቀሩም። ሙሴንና ብሉይ ኪዳንን በመጥቀስ ሰዎች በዚያ ዓይነት ሕይወት ሊመላለሱ እንደሚገባ አስተማሩ። ይህም ጳውሎስ አሮጌውንና አዲሱን ኪዳን እንዲያነጻጽር አነሣሣው። ሞትን ያስከተለው ብሉይ ኪዳን በድንጋይ ላይ ነበር የተጻፈው። ከእግዚአብሔር ዘንድ በሙሴ በኩል ስለተላለፈ በክብር ነበር የመጣው። ይህ ኪዳን በክብር ቢመጣም (ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር በተገናኘ ጊዜ ፊቱ እንዳንጸባረቀው)፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዘ መጥቷል። የተመለከቱት ክብር የሌሎቹን አይሁዶች ልብ ሊለውጥ አልቻለም ነበር። ይህን ክብር በመፍራታቸው ምክንያት ሙሴ ፊቱን እንዲሸፍን ጠየቁት። እግዚአብሔር በሙሴ በኩል የሰጣቸውን ሕግጋት ከመጠበቅ ይልቅ በልባቸው ውስጥ ያለማመንን መጋረጃ አኖሩ። ጳውሎስ አሁንም አብዛኞቹ አይሁዶች በዚህ መጋረጃ ተሸፍነው በክርስቶስ ከማመን እንደራቁ ገልጾአል። አዲስ ኪዳን የዘላለምን ሕይወት ያመጣል። ይህ ኪዳን በድንጋይ ላይ ሳይሆን በእያንዳንዱ ክርስቲያን ልብ ውስጥ ተጽፎአል። ክብሩም የሚደበዝዝ ሳይሆን እያደገ የሚሄድ ነው፡፡ ለደኅንነታቸው ወደ ክርስቶስ ለሚመለከቱ ሰዎች ያለማመን መጋረጃ ተወስዶላቸዋል። ራሳቸው የሚፈልጉትን ሳይሆን እግዚአብሔር የሚፈልግባቸውን እንዲሆኑ የሚረዳ መንፈስ ቅዱስ ተሰጥቷቸዋል። ከክርስቶስ ጋር ስንዛመድና ስለ እርሱ ባለን እውቀት ስናድግ፥ እኛም የክርስቶስን ክብር እናንጸባርቃለን። የእግዚአብሔር ክብር በእኛ ሕይወት ውስጥ አይደበዝዝም፤ ነገር ግን ክርስቶስን እንመስል ዘንድ ሕይወታችንን ይለውጠዋል። ምንም እንኳን ሁልጊዜ ኃጢአት መሥራታችን ባይቀርም ስንሞትና ከርስቶስን ስንመለከት፥ እርሱን እንደምንመስል ተነግሮናል (1ኛ ዮሐ 3፡2)። የውይይት ጥያቄ፡- ጳውሎስ ከውጫዊ ነገሮች ይልቅ በልባችን ውስጥ ስላለው ስለ ክርስቶስ ስውር ክብር ይናገራል። ሀ) ብዙውን ጊዜ እንደ ጳውሎስ እግዚአብሔር የሰዎችን ውስጣዊ ሕይወት በመለወጥ ከርስቶስን እንዲመስሉ ከሚያደርግበት ሁኔታ ይልቅ እንደ ሐሰት አስተማሪዎቹ በውጫዊ ነገሮች ላይ የምናተኩረው እንዴት ነው? ለ) ለእግዚአብሔር አስፈላጊ የሆኑና ክርስቶስን በመምሰል ማደጋችንን የሚያሳዩ አንዳንድ ውስጣዊና ድብቅ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

መንፈሳዊ መሪ ለአዲሱ ኪዳንና ለእግዚአብሔር የማስቻል ኃይል አጽንኦት ይሰጣል (2ኛ ቆሮ. 2፡14-3፡18)። Read More »

ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ስለ ራሱ ሁኔታ እብራራላቸው (2ኛ ቆሮ. 1፡12-2፡13)

ጳውሎስ በዕቅዱ መሠረት ለምን እንዳልጎበኛቸው ገለጸላቸው (2ኛ ቆሮ. 1፡12-2፡4) የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለሌሎች የገባኸውን ቃል መጠበቅ አስፈላጊ የሚሆነው ለምን ይመስልሃል? ለ) መሪዎች ለምእመናን የገቧቸውን የተስፋ ቃሎች በማይፈጽሙባቸው ጊዜያት ምን ይከሰታል? ሐ) ለመሪዎች በሚያክናውኗቸው ተግባራት ሁሉ በንጹሕ ሕሊና መመላለስ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? መ) ስለ ራስህ ሕይወት አስብ። ሰዎች ቢያውቋቸው የሚያሳፍሩህ አንዳንድ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? ይህ ስለ እውነተኛነትህና ስለ ሕሊናህ ምን ያሳያል? የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ጳውሎስን ስለተለያዩ ምክንያቶች የሚከሱት ይመስላል። በመጀመሪያ፥ አንዳንዶች ግልጽ ያልሆኑ ነገሮችን በመልእክቱ ውስጥ በማካተቱ ከሰሱት። ጳውሎስ በመልእክቶቹ ሊያታልላቸው የሚፈልግ መሰላቸው። ሁለተኛ፥ ሌሎች ቃሉን አይጠብቅም ብለው አሰቡ። ወደ መቄዶንያ ከመሄዱ በፊት እንደሚጎበኛቸው በቲቶ በኩል ሳይልክባቸው አልቀረም። ነገር ግን እነርሱ ዘንድ ሳይደርስ ወደ መቄዶንያ መሄዱን ሲሰሙ፥ «ቃሉን የማይጠብቅ ሰው እንዴት ሊታመን ይችላል?» ብለው ጠየቁ። ጳውሎስም በተሳሳተ መንገድ ስለተረዱት አዘነ። ከእነርሱ ጋር የሚያደርገው ግንኙነት ሁልጊዜም በግልጽነት፥ በቅድስናና በእውነተኛነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን እንዲረዱለት ፈለገ። በጻፈላቸው አሳብ ሊያታልላቸው ስላልፈለገ ሕሊናው ንጹሕ መሆኑን አብራራላቸው። እንዲሁም፥ ወደ ኢየሩሳሌም ከመሄዱ በፊት ሊጎበኛቸው ሁለት ጊዜ ስላቀደ ሕሊናው ንጹሕ ነበር። ጳውሎስ በሁኔታዎች ላይ ተመሥርቶ ቃሉን የማይለውጥ ሰው መሆኑን ገለጸላቸው። ጳውሎስ በቃሉ እንደ እግዚአብሔር ግልጽና እውነተኛ ለመሆን ይፈልግ ነበር። የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች በክርስቶስ በኩል እውነት (አሜን፥ አዎን) ናቸው። እግዚአብሔር ከሰጣቸው የተስፋ ቃሎች አንዱ ልጆቹ እስከ መጨረሻው ድረስ ጸንተው እንደሚቆሙ የሚያስረዳ ነው። ይህንኑ የተስፋ ቃል እውን ለማድረግ እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ክርስቲያን የባለቤትነት ማኅተም የሆነውን መንፈስ ቅዱስ ሰጥቷል። ይህም እግዚአብሔር ተስፋ የሰጠንን ውርስ እንደምንቀበል ዋስትና ይሰጠናል። ጳውሎስ ይህን ያለመተማመን መንፈስ ያሸነፈው እንዴት ነው? በመጀመሪያ፥ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በተሻለ ሁኔታ እንዲያውቁት ጠየቃቸው። አንድን ሰው በደንብ ስናውቅ ብዙም አንጠራጠረውም። ጳውሎስ በእርሱ ከማፈራቸው በፊት የበለጠ እንዲያውቁትና ከዚያ በኋላ እንዲተማመኑት፥ ብሎም እንዲመኩበት ጠየቃቸው። ጳውሎስ ይህን ሲል በተለይም የሁሉም ሥራና ልብ በሚመዘንበት የክርስቶስ ምጽአት ቀን በጳውሎስ ሥራ እንደሚኮሩ መግለጹ ነበር። ጳውሎስ በዚህ ሁሉ፥ ከእነርሱ ጋር ግልጽና እውነተኛ ግንኙነት እንደሚያደርግ ቃል ገባላቸው። ሁለተኛ፥ ጳውሎስ የጉብኝቱን ጊዜ የለወጠባቸውን ምክንያቶች ዘርዝሯል። ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ የሚያደርገውን ጉዞ ያዘገየበት ዋነኛው ምክንያቱ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ማሰቡ ነበር። እርሱንና እነርሱን የሚጎዱ የግንኙነት ችግሮች እያሉ ሊጎበኛቸው አልፈለገም ነበር። ቀደም ሲል ጳውሎስ ቆሮንቶስን በጎበኘ ጊዜ ጥሩ ሁኔታ አላጋጠመውም ነበር። ስለሆነም፥ እንደ ሐዋርያ እግዚአብሔር የሰጠውን ሥልጣን በመጠቀም ፍርድ የሚሰጥበትን ተጨማሪ ጉብኝት ለማድረግ አልፈለገም ነበር። ቀደም ሲል በጻፈላቸው ጠንካራ ደብዳቤ አሳዝኗቸው ነበር። ይህን ጠንካራ ደብዳቤ የጻፈው በቀላሉ ሳይሆን፥ በዕንባ፥ በጭንቀትና በሥቃይ ነበር። ጳውሎስ የቆሮንቶስን ክርስቲያኖች አጥብቆ ስለሚወድ በቀላሉ ሊያሳዝናቸው ወይም በተሳሳተ ሕይወታቸው እንዲቀጥሉ ዝም ብሎ ሊተዋቸው አይችልም ነበር። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ብዙውን ጊዜ ሰዎች መሪዎችን የሚጠራጠሩት እንዴት ነው? ለ) ጳውሎስ የወሰዳቸው ሁለት እርምጃዎች እንዲህ ዓይነት ጥርጣሬዎችን ለመፍታት የሚረዱት እንዴት ነው? ንስሐ የገባውን ኃጢአተኛ ይቅር ስለ ማለት (2ኛ ቆሮ. 2፡5-11) ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ለምን በዕቅዱ መሠረት እንዳልጎበኘ በ2ኛ ቆሮንቶስ 2፡12-13 እና በ2ኛ ቆሮንቶስ 7፡5-16 አብራርቷል። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ በዚህ መልእክቱ ውስጥ እንደሚያደርገው፥ ጳውሎስ ዋነኛ ርእሰ ጉዳዩን ከቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጋር ስለተፈጠረው የግንኙነት መበላሸት ያነሣል። አንድ ሰው ግልጽ ኃጢአት በሚሠራበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ብዙውን ጊዜ ከሁለት መንገዶች በአንዱ ምላሽ ትሰጣለች። አንዳንድ ጊዜ ኃጢአቱን ዝቅ አድርጋ በመመልከት ኃጢአተኛውን ከመቅጣት ወይም ንስሐ ለመግባት በማይፈልግበት ጊዜ የሥነ ሥርዓት እርምጃ ከመውሰድ ትታቀባለች። በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 5 ከክርስቲያኖቹ አንዱ ከአባቱ ሚስት ጋር እያመነዘረ ሳለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ምንም ዓይነት እርምጃ አለመውሰዱ ተገልጾአል። ጳውሎስ በዚያ ደብዳቤ ግለሰቡን ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት በማውጣት እንዲቀጡት ጠይቋል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚከሰተውን ኃጢአት በጥብቅ ካልተከታተልን በፍጥነት ሊስፋፋና የጠቅላላይቱን ቤተ ክርስቲያን ቅድስና ሊያጠፋ ይችላል። ይህ ደግሞ የክርስቶስን ስም ያሰድባል። ሁለተኛ፥ ቤተ ክርስቲያን በኃጢአተኛው ግለሰብ ላይ የመረረ ቅጣት ልትበይን ትችላለች። ቤተ ክርስቲያን ግለሰቡ ንስሐ ከገባ በኋላ እንኳ ይቅርታና ዕርቅ ለመስጠት ላትፈቅድ ትችላለች። ጳውሎስ የ2ኛ ቆሮንቶስን መልእክት በሚፈጽፍበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱ ይህንኑ ችግር እየተጋፈጠች ነበር። ምናልባትም ጳውሎስና የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መጀመሪያ ያልተስማሙት ኃጢአተኛውን ግለሰብ ስለ መቅጣት የተለያየ አሳብ በመያዛቸው ሳይሆን አይቀርም። (በዚህ ክፍል የተጠቀሰው ግለሰብ በ1ኛ ቆሮ. 5 የተጠቀሰው ሰው ስለመሆኑ እርግጠኞች አይደለንም። አንዳንድ ምሁራን ይህ ሰው ጳውሎስን በመቃወምና በመሳደብ አንዳንድ ክርስቲያኖች እንዲያምፁበት ያደረገ ነበር ይላሉ።) መጀመሪያ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በኃጢአት ውስጥ የነበረውን ግለሰብ ለመቅጣት አልፈለገችም ነበር። ጳውሎስ ግን የግድ መቀጣት እንዳለበት አሳሰባቸው። ምናልባትም የጠፋው መልእክት ስለዚሁ ጉዳይ የሚናገር ይሆናል (2ኛ ቆሮ. 2፡9)። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ከጳውሎስ አሳብ ጋር በመስማማት ግለሰቡን ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት አገለሉት። በኋላም ግለሰቡ ከልቡ ንስሐ እንደገባና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ግን ወደ ኅብረቱ እንዳይገባ እንደከለከሉት ሰማ። ጳውሎስ በዚህ ጊዜ ይቅር እንዲሉትና በፍቅር ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመልሱት ነገራቸው። የቤተ ክርስቲያን የሥነ ሥርዓት እርምጃ ዓላማ ንስሐ እንጂ ቅጣት አይደለም። ስለሆነም፥ ግለሰቡ ንስሐ በሚገባበት ወቅት ይቅር ለማለት መዘጋጀት አለብን። ጳውሎስ በሐዋርያዊ ሥልጣኑ ኃጢአተኛውን ይቅር ስላለ፥ እነርሱም ይህንኑ ማድረግ ነበረባቸው። ይቅር ለማለት አለመፈለግ ከሳሹ ሰይጣን በሁኔታው ውስጥ ድልን እንዲቀዳጅ ያደርጋል። ሰይጣን በኃጢአተኛው ሕይወት ውስጥ በመንገሥ እምነቱን ትቶ ወደ ዓለም እንዲመለስ ያደርገዋል። በጉዳዩ ላይ ክፍፍል እንዲፈጠር በማድረግ፥ በቤተ ክርስቲያንም ላይ ድል ይነሣል። በተጨማሪም፥ ቤተ ክርስቲያን ከምሕረት፥ ከይቅርታ፥ ከፍቅርና ከአንድነት ይልቅ የቤተ ክርስቲያን ደንብ በመሳሰሉት ውጫዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ትጀምራለች። የውይይት ጥያቄ፡- በቤተ ክርስቲያንህ የሥነ ሥርዓት እርምጃ የተወሰደበትን ሁኔታ ግለጽ። ሀ) ቅጣቱን እንዴት በቀላሉ ማካሄድ ይቻል እንደነበረ ግለጽ። ለ) ቅጣቱን እንዴት ጠንከር ባለ ሁኔታ ማካሄድ ይቻል እንደነበር ግለጽ። ሐ) ለዚህ የሥነ ሥርዓት እርምጃ የጳውሎስ ምክር ምን የሚሆን ይመስልሃል? እንደ ክርስቲያኖች ምሕረት የሌለንና ይቅር የማንል ሰዎች ሆነን እንዳንታወቅ መጠንቀቅ አለብን። ሁላችንም በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኞችና ቅጣት የሚገባን ሰዎች ነን። ማናችንም የመሪነት፥ የኳዬር፥ የጌታ እራት፥ ወዘተ. ተካፋይነት የሚገባን አይደለንም። ሰው ከልቡ ንስሐ በሚገባበት ጊዜ ይቅርታን እንደሚያገኝ መገንዘብ አለብን። የክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናልና (1ኛ ዮሐ 1፡9)። ጳውሎስ ለምን እንዳልጎበኛቸው ማብራራቱን ይቀጥላል (2ኛ ቆሮ. 2፡12-13) ምናልባትም በአካባቢው በተከሰተው ከፍተኛ ስደትና የሞት ዛቻ ሳቢያ ጳውሎስ ካሰበው ጊዜ ቀድሞ ኤፌሶንን ለቅቆ ሳይወጣ አልቀረም። ጳውሎስ ብዙ ክርስቲያኖች ለእርሱ መልካም አመለካከት እንዳልነበራቸው ከማወቁ በቀር ለጻፈው ደብዳቤ ስለሰጡት ምላሽ የሰማው ነገር ባለመኖሩ፥ ወደ ቆሮንቶስ ለመሄድ አልፈለገም ነበር። ስለሆነም፥ ወደ ጢሮአዳ ሄዶ ለጥቂት ጊዜ አገለገለ። ጳውሎስ በኋላ የጠፋውን መልእክት ወደ ቆሮንቶስ ያደረሰው ቲቶ በመቄዶንያ በኩል ወደ ጢሮአዳ እንዲመጣ የነገረው ይመስላል። ቲቶ ሳይመጣ ሲቀር ጳውሎስ ከአካይያ በስተሰሜን ወደምትገኘው መቄዶንያ ሄዶ ፈለገው። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ስለ ራሱ ሁኔታ እብራራላቸው (2ኛ ቆሮ. 1፡12-2፡13) Read More »

እግዚአብሔር የመጽናናት አምላክ (2ኛ ቆሮ. 1፡1-11)

ጌታሁን ከቦታ ቦታ እየተጓጓዘ ስለ ክርስቶስ የሚመሰክር ፍሬያማ ወንጌላዊ ነበር። በአገልግሎቱ ውጤታማ ነበር። አንድ ቀን ተሳፍሮ የሚጓዝበት አውቶቡስ ተገልብጦ ገደል በመግባቱ ጌታሁን ለሽባነት ተዳረገ። እየተጓዘ የሚያገለግለው አገልግሎቱ ተቋረጠ። ብዙ ክርስቲያኖች ወደ እርሱ መጥተው እንዲፈወስ ጸለዩለት። ምንም እንኳን በእግዚአብሔር ላይ ጠንካራ እምነት ቢኖረውም ሊፈወስ አልቻለም። ስለሆነም፥ «እግዚአብሔር ይህ በእኔ ላይ እንዲደርስ ለምን ፈቀደ? አንዳንድ ክርስቲያኖች በከፍተኛ ደረጃ የሚሠቃዩት ለምንድን ነው?» እያለ ይጠይቅ ጀመር። የጌታሁን ጥያቄ ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ የሚያነሡት ነው። መከራን ስንቀበል፥ ስንታመም፥ መጥፎ ነገር በቤተሰባችን ላይ ሲደርስ ሁላችንም ጥያቄዎችን እናነሣለን። እግዚአብሔር ልጆቹ እንዲሠቃዩ የሚፈልግባቸውን ምክንያቶች ሙሉ በሙሉ ባናውቅም፥ የ2ኛ ቆሮንቶስ መልእክት አንዳንድ ምክንያቶችን ይገልጽልናል። ሐዋርያው ጳውሎስ መከራ በሕይወቱ ውስጥ ስላበረከተው አስተዋጽኦ አብራርቷል። መከራ እግዚአብሔር ጳውሎስን ፍሬያማ የአሕዛብ ሐዋርያ አድርጎ የተጠቀመበት ዐብይ መሣሪያ ነበር። መከራ ርግማን ሳይሆን የእግዚአብሔር የሥልጠና መሣሪያ ነው። መከራ እግዚአብሔር መሪዎቹን የሚያሠለጥንበት ትምህርት ቤት ነው። አንድ አስተማሪ እንደተናገሩት፥ «እግዚአብሔር አንድን ሰው በከፍተኛ ደረጃ ከመጠቀሙ በፊት መጀመሪያ ክፉኛ ይሰብረዋል።» የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሮሜ 5፡3-5፤ ያዕ. 1፡2-4፤ 2ኛ ቆሮ. 1፡3-7 አንብብ። እነዚህ ጥቅሶች ስለ መከራ የተለያዩ ዓላማዎች ምን ያስተምሩናል? እግዚአብሔር በመከራ አማካኝነት ሊፈጽም የሚፈልገው ተግባር ምንድን ነው? ለ) እግዚአብሔር አንተን ወይም ሌላ ክርስቲያንን ላዘጋጀው ተግባር ብቁ ለማድረግ ሲል በመከራ ውስጥ ሲያሳልፍ ያየኸው እንዴት ነው? ሐ) መከራ በሰው ባሕርይ ወይም አመለካከት ላይ የሚያስከትለው ለውጥ ምንድን ነው? መ) መከራ እግዚአብሔር በመንፈሳዊ ሕይወታችን እናድግ ዘንድ ለማገዝ የሚጠቀምበት መሣሪያ መሆኑ በቤተ ክርስቲያን ሲሰበክ የማንሰማው ለምንድን ነው? ክርስቶስን ከመከተል በምናገኛቸው መልካም ነገሮች፥ ማለትም የጸጋ ስጦታዎች፥ ፈውስ፥ ደስታ፥ ወዘተ. ላይ ብቻ የምናተኩረው ለምንድን ነው? ከእግዚአብሔር ዘንድ በምናገኛቸው መልካም ነገሮች ላይ በምናተኩርበት በአሁኑ ዘመን፥ አስተምህሯችንን እግዚአብሔር ልጆቹን በመከራ መንገድ ወደ ብስለት ከሚመራበት ሁኔታ ጋር ሚዛናዊ ማድረግ አለብን። በአዲስ ኪዳን ውስጥ መከራ የምንሸሸው ሳይሆን የምንደሰትበትና የምንማርበት መንገድ ሆኖ ተጠቅሷል። መንፈሳዊ ባሕርይና ፍሬያማ አገልግሎት የሚገኙት በደስታና በምቾት ጊዜ ሳይሆን በመከራ ጊዜ ነው። ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ ውስጥ የተጠቀመው መግቢያ ከሌሎች መልእክቶቹ የተለየ ነው። ጳውሎስ በእግዚአብሔር መለኮታዊ ምርጫ ስላገኘው የሐዋርያነት ሥልጣን አጽንኦት ሰጥቶ ከገለጸ በኋላ፥ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሰላምታ አቀረበላቸው። ከእነዚህ ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶቹ ከጳውሎስ ጋር ኅብረት ያልነበራቸውና አገልግሎቱን የሚንቁ ነበሩ። ከጳውሎስ ጋር በአንዳንድ ጉዳዮች ባይሰማሙም እንኳን፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ መሆናቸውን ገልጾአል። ይሁንና፥ በሌሎች መልእክቶቹ እንደሚያደርገው ስለ ምንም ነገር አላመሰገናቸውም። (1ኛ ቆሮ. 1፡1-9ን ከ2ኛ ቆሮ. 1፡1-2 ጋር አነጻጽር።) ይህ ምናልባትም ለእነርሱ ግድ መሰኘቱንና ከአንዳንድ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጋር ሸካራ ግንኙነት እንደነበረው የሚያመለክት ይሆናል። ጳውሎስ 2ኛ ቆሮንቶስን የጻፈው ከእስያ አውራጃ ተነሥቶ ወደ መቄዶንያ እንደገባ ነበር። ምናልባትም ጳውሎስ ከእስያ የወጣው በተቀበለው ከባድ መከራ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፡፡ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ይህ መከራ ምንን እንዳካተተ አያብራራም። ነገር ግን ድሜጥሮስ በጳውሎስ ላይ ሁከትን እንዳስነሣ ይገልጻል። ጳውሎስም በዚያ ከአራዊት ጋር እንደታገለ አመልክቷል (1ኛ ቆሮ. 15፡32)። እነዚህ አራዊት እንደ አንበሳ ያሉ የዱር እንስሳት ወይም ከእግዚአብሔር እውነትና ከጳውሎስ ጋር የታገሉት ሰዎች ተምሳሌቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ጳውሎስ ስለ መከራ መናገሩ በ2ኛ ቆሮንቶስ ውስጥ በግልጽ ይታያል። የ2ኛ ቆሮንቶስ መልእክቱም በአብዛኛው በመከራ ላይ የተመሠረተ ነው። ከዚህ ክፍል ውስጥ የሚከተሉትን አጢን። ሀ. ጳውሎስ በመከራ ጊዜ እግዚአብሔር አብ እንዳጽናናውና ርኅራኄን እንዳሳየው ገልጾአል (2ኛ ቆሮ. 1፡3)። ርኅራኄ በሌሎች መከራ የመካፈል ስሜታዊ ተግባር ነው። ምንም እንኳ እግዚአብሔር ከመከራዎች ሁሉ የላቀ ቢሆንም፥ ይህ ግን ስለ እኛ ደንታ የለውም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን በመከራ ውስጥ ስናልፍ ኀዘናችንን ይካፈላል። እግዚአብሔር መከራን በግል ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው? በቀዳሚነት በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል እግዚአብሔር በምድር ላይ የምንጋፈጣቸውን የመከራ ዓይነቶች ሁሉ ተቀብሏል (ዕብ. 5፡7-9 አንብብ።) እግዚአብሔር በመከራችን ስለሚካፈል፥ መከራን በምንቀበልበት ጊዜ ወደ እኛ ተጠግቶ ያጽናናናል። በመከራ ውስጥ በምናልፍበት ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር እንደማይተወንና ዳሩ ግን ከእኛ ጋር እንደሚሠቃይ፥ ብሎም እንደሚያጽናናን መገንዘብ አለብን። ለ. እግዚአብሔር በመከራ ውስጥ እንድናልፍ የሚፈቅደው በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል እንድንችል ነው። መከራ እየተቀበልን ለክርስቶስ ታማኞች ሆነን በምንጸናበት ጊዜ በመከራ ውስጥ የሚገኙትን ሌሎች ክርስቲያኖች ልናበረታታ እንችላለን። እንደኛ ዓይነት መከራ ካልተቀበለ ክርስቲያን መጽናናትን ማግኘቱ ከባድ ነው። እንዲህ ዓይነት ሰዎች የአእምሮ እውቀት ሊኖራቸውና ትክክለኛ አሳቦችን ሊያካፍሉን ቢችሉም፥ ንግግራቸው ብዙም ትርጉም የሚሰጠን አይሆንም። ነገር ግን አንድ ሰው እንደኛው ዓይነት መካራ እንደተቀበለ ስናውቅ፥ በሚነግረን ቃል እንጽናናለን። በመከራ ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ እግዚአብሔር እኛን የሚያጽናናበት ዐቢይ መንገድ መከራ የተቀበሉትን ሌሎች ክርስቲያኖች በመጠቀም ነው። ስለሆነም፥ መከራ የተቀበልን ሰዎች ሌሎችን በመርዳት መከራችንን የበረከት መሣሪያ ልናደርግ ይገባል። መከራ አንድን ሰው መራር ወይም ርኅሩኅ ሊያደርግ ይችላል። መከራን ለመቀበል የማንፈልግ ከሆነ፥ እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ለመሥራት የሚጠቀምበትን መሣሪያ ተቃውመናል ማለት ነው። ነገር ግን የእግዚአብሔርን የመከራ መሣሪያ ብንቀበል፥ ብንጸናና ብንማርበት ርኅሩኆችና ሌሎችን ለማጽናናት የምናገለግል የእግዚአብሔር መሣሪያዎች እንሆናለን። ሐ. መከራ ለሰዎች ሁሉ የማይቀር ግዴታ ነው። ክርስቶስ በሞተ ጊዜ እግዚአብሔር ተሠቃይቷል። ክርስቶስም ሰዎች በተሣለቁበት፥ በገፉትና በሰቀሉት ጊዜ ተሠቃይቷል። ምንም እንኳ ሐዋርያ ቢሆንም ጳውሎስ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሆኖ በሚሠራበት ጊዜ መከራ ተቀብሏል። ጳውሎስ ከመከራ ጽናት የተነሣ በሕይወቱ ተስፋ ሊቆርጥ የደረሰበት ጊዜ እንደነበረ ገልጾአል። ጳውሎስ የቆሮንቶስም አማኞች በተመሳሳይ ሁኔታ መከራን እንደሚቀበሉ ተናግሯል። ስለሆነም፥ እያንዳንዱ ሰው የእኛን ማጽናናት ይፈልጋል። የምናጽናናቸው ወገኖች ደግሞ ሌሎችን ማጽናናት ይኖርባቸዋል። መከራ በክርስቶስ አካል ውስጥ የአገልግሎት በሮችን ይከፍታል። መ. በመከራ ጊዜ በትዕግሥት የመጽናት ባሕርይ ሊኖረን ይገባል። በትዕግሥት የመጽናትን ባሕርይ ለማግኘት ደግሞ እግዚአብሔር ሁኔታዎችን በመቆጣጠር ላይ መሆኑን ተረድተን ልንገዛለትና ልንታመንበት ይገባል። ሠ. እግዚአብሔር መከራ ውስጥ የሚከተን በራሳችን ሳይሆን ሙታንን በሚያስነሣ አምላክ እንድንደገፍ ለማስተማር ነው። በምቾት ጊዜ በችሎታችን፥ በብርታታችንና በጥበባችን ላይ ወደ መደገፍ እናዘነብላለን። ነገር ግን ሁኔታዎችና ችግሮች ከዓቅማችን በላይ በሚሆኑበት ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ ለመደገፍ እንገደዳለን። ረ. መከራን በምንቀበልበት ጊዜ የመጨረሻው ድፍረታችን ትንሣኤ ነው። ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ለክርስቲያን ዐቢይ ጠላት ስላልሆነ መፍራቱ አስፈላጊ አይደለም። በበሽታ ወይም በስደት ምክንያት ብንሞት እንኳ ከትንሣኤ የተነሣ ሁሉንም አሸንፈን ለዘላለም ከእግዚአብሔር ጋር እንኖራለን። ሰ. በስደት ጊዜ እርስ በርሳችን የምንረዳዳበት ትልቁ መሣሪያ ጸሎት ነው። እግዚአብሔር እኛ በማንረዳባቸው መንገዶች ጸሎታችንን ይጠቀማል። አንዳንድ ጊዜ በጸሎታችን አማካኝነት የክርስቲያኖችን መከራ ሲያቆም፥ በሌሎች ጊዜያት ደግሞ እግዚአብሔር ጸሎታችንን ተጠቅሞ ክርስቲያኖች በመከራ ውስጥ እርሱን የሚያስከብር ተግባር እንዲፈጽሙ ያደርጋቸዋል። አንዳንድ ጊዜም በሐዋርያት ሥራ 12፥19 በጴጥሮስ ሕይወት እንደተፈጸመው ጸሎት ክርስቲያኖችን ከመከራ ይታደጋቸዋል። በሌሎች ጊዜያት ግን (በሐዋርያት ሥራ 12፡1-2 በያዕቆብ ላይ እንደተፈጸመው) ተግተን እየጸለይን ሳለ እግዚአብሔር ክርስቲያኖች እንዲሞቱ ሊፈቅድ ይችላል። የውይይት ጥያቄ፡- በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ መከራ የሚቀበሉትን ሰዎች ስም ዘርዝር። እነዚህ እውነቶች በዚህ የመከራ ጊዜ ጸንተው እንዲቆሙ የሚያበረታቷቸው እንዴት ነው? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

እግዚአብሔር የመጽናናት አምላክ (2ኛ ቆሮ. 1፡1-11) Read More »

የ2ኛ ቆሮንቶስ መዋቅር እና አስተዋጽኦ

የ2ኛ ቆሮንቶስ መዋቅር የ2ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ከአንዱ ወደ ሌላው ርእሰ ጉዳይ ቢያመራም፥ በሦስት ክፍሎች ሊከፈል ይችላል። ጳውሎስ የሚደግፉትን አብዛኛዎቹን የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ያመሰግናቸዋል (2ኛ ቆሮ. 1-7)። ጳውሎስ በዕቅዱ መሠረት ለምን ወደ ቆሮንቶስ እንዳልመጣ ያብራራል። የክስተቶችን ቅደም ተከተል በመስጠት ቆሮንቶስን በቁጣ ለመጎብኘት ወይም በተቃወሙት ጊዜ ሐዋርያዊ ሥልጣኑን ለመጠቀም እንዳልፈለገ ያስረዳል። ንስሐ ገብተው የእርሱን ሐዋርያነት መቀበላቸው እንዳስደሰተውም ይገልጻል። ከኃጢአቱ ንስሐ የገባውን ወንድም ወደ ኅብረቱ እንዲቀበሉት ይጠይቃል። ጳውሎስ እግዚአብሔር ደካማ ሰዎችን የዕርቅ መሣሪያዎቹ አድርጎ የሚጠቀምበትን አስደናቂ ምሥጢር ያካፍላቸዋል። እግዚአብሔር የሚፈልገው የተማሩትንና ኃያላንን ሳይሆን እርሱን ለመታዘዝ ራሳቸውን የሰጡትን ተራ ሰዎች ነው። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ገንዘባቸውን አሰባስበው ለኢየሩሳሌም ድሆች እንዲልኩ ያበረታታቸዋል (2ኛ ቆሮ. 8-9)። ጳውሎስ እውነተኛ ሐዋርያ አይደለም ለሚሉት የሐሰት አስተማሪዎች ምላሽ ይሰጣል (2ኛ ቆሮ. 10-13)። ጳውሎስ በሐዋርያነቱ ስለከፈለው የስደት መሥዋዕት ገልጾአል። ዋናው ነገር ግን በጳውሎስ ድካም ውስጥ የተገለጸው የእግዚአብሔር ኃይል ነበር። ጳውሎስ ንስሐ ካልገቡ እንደ ሐዋርያ የእግዚአብሔርን ፍርድ እንደሚያመጣባቸው አመልክቷል። የ2ኛ ቆሮንቶስ አስተዋጽኦ መግቢያ (2ኛ ቆሮ. 1፡1-11) ጳውሎስ የቆሮንቶስን ክርስቲያኖች በዕቅዱ መሠረት ለምን እንዳልጎበኛቸው ያብራራል (2ኛ ቆሮ. 1፡12–2፡13)። ጳውሎስ የሐዋርያነት አገልግሎቱን በመከላከል ለመንፈሳዊ መሪዎች ምሳሌነትን ይሰጣል (2ኛ ቆሮ. 2፡14-7፡16)። ሀ. መንፈሳዊ መሪ በአዲሱ ኪዳንና በእግዚአብሔር የማስቻል ኃይል ላይ ያተኩራል (2ኛ ቆሮ. 2፡14–3፡18)። ለ. መንፈሳዊ መሪ የወንጌሉ መዝገብ የሚገኘው በእግዚአብሔር ኃይል በንጹሕ ልብ በሚያገለግሉ ደካሞች ውስጥ መሆኑን ይገነዘባል (2ኛ ቆሮ. 4፡1-12)። ሐ. መንፈሳዊ መሪ የወደፊቱን ዘላለማዊ ሽልማት እያሰበ በአገልግሎቱ ይጸናል (2ኛ ቆሮ. 4፡13-5፡10)። መ. መንፈሳዊ መሪ ሰዎችንና እግዚአብሔርን ለማስታረቅ የሚሻ የክርስቶስ አምባሳደር ነው (2ኛ ቆሮ. 5፡11-6፡2)። ሠ. መንፈሳዊ መሪ ከማያምኑ ሰዎች ጋር ባለመቀላቀል በንጽሕና ለመኖር ይወስናል (2ኛ ቆሮ. 6፡14-7፡1)፡፡ በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የአመለካከት ለውጥ የጳውሎስ መደሰት (2ኛ ቆሮ. 7፡2-26)፡፡ ጳውሎስ ለአይሁድ ክርስቲያኖች ስለሚሰጠው ምጽዋት ማብራሪያ ይሰጣል (2ኛ ቆሮ. 8-9)፡፡ ሀ. ጳውሎስ የስጦታውን ዓላማና እንዴት መሰብሰብ እንዳለበት ያብራራል (2ኛ ቆሮ. 8፡1-9፡5)፡፡ ለ. ጳውሎስ ለእግዚአብሔር በምንሰጥበት ጊዜ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባ ያስረዳል (2ኛ ቆሮ. 9፡6-15)፡፡ ጳውሎስ እውነተኛ ሐዋርያነቱን የሚያረጋግጡ ነጥቦችን በማቅረብ ይከራከራል (2ኛ ቆሮ. 10-13)፡፡ (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የ2ኛ ቆሮንቶስ መዋቅር እና አስተዋጽኦ Read More »

የ2ኛ ቆሮንቶስ ዓላማ እና ልዩ ባሕሪያት

የ2ኛ ቆሮንቶስ ዓላማ እንደዛሬው ሁሉ የቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያንም ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ጋር ታግላለች። ጳውሎስ አብያተ ክርስቲያናትን በተከለበት ስፍራ ሁሉ የሐሰት አስተማሪዎች ወንጌሉን ለመበረዝ ይጥሩ ነበር። ይህንን ያደርጉ የነበረው በሁለት ዐቢይ መንገዶች ነበር። አንደኛ፥ ሰዎች የእግዚአብሔርን መልእክተኛ እንዲጠራጠሩ ለማድረግ ይጥሩ ነበር። በዚህ መሠረት የሐሰት አስተማሪዎቹ የጳውሎስን እውነተኛነት በማጣጣል ሰዎች የጳውሎስን ትምህርት እንዲጠራጠሩ ያደርጉ ነበር። ሁለተኛ፥ የወንጌሉን መልእክት ተቃወሙ። ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት መሞቱን በሚያስረዳው መልእክት ላይ የተለያዩ አሳቦችን ጨምሩ። በቆሮንቶስ የነበሩት የሐሰት አስተማሪዎች ክርስቲያኖች የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን መከተል እንዳለባቸው አስተማሩ። ሌሎች ደግሞ ክርስቲያኖች እውነተኛ አማኞች ለመሆን ተጨማሪ እውቀትን ማግኘት እንዳለባቸው ገለጹ። ሌሎች የሐሰት አስተማሪዎች ክርስቶስ አምላክ ነው ወይስ ፍጹም ሰው? ሲሉ ጠየቁ። አንዳንዶች ደግሞ ድነት (ደኅንነት) የሚገናኘው ከግለሰቡ ነፍስ ጋር ብቻ ስለሆነ፥ አማኞች በሥጋ የሚያደርጉት ነገር በደኅንነታቸው ላይ ተጽዕኖ እንደማያስከትል አመለከቱ። ስለሆነም፥ ጳውሎስና የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚሰጡ መልእክቶችን ጻፉ። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንህን ከሚያውኩ የሐሰት ትምህርቶች አንዳንዶችን ዘርዝር። ለ) ብዙውን ጊዜ የሐሰት አስተማሪዎች የሚቃወሟቸውን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እውነተኛነት ለማሳጣት የሚጥሩበትን ሁኔታ ግለጽ። ሐ) እነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች የወንጌሉን ንጽሕና የሚያጠቁት እንዴት ነው? መ) የቤተ ክርስቲያንህ መሪዎች ምእመኖቻቸውን ከእነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች ለመጠበቅ ምን እያደረጉ ናቸው? 1ኛ ቆሮንቶስ ከተጻፈ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጠንካራ የሐሰት አስተማሪዎች በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሥራት ጀመሩ። በአመዛኙ እነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች ራሳቸውን ክርስቲያኖች ነን ብለው የሚጠሩ አይሁዶች ሳይሆኑ አይቀሩም። እነዚህ ሰዎች ከኢየሩሳሌም የ12ቱን ሐዋርያት ሥልጣን ይዘው መምጣታቸውን ይናገሩ ነበር። ቀደም ሲል የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በተዘፈቀችበት ግራ መጋባት ላይ ተጨማሪ ውዝግብ ለመፍጠር ሲሉ በጳውሎስ ላይ የተቃውሞ አሳቦችን ይሰነዝሩ ጀመር። የ2ኛ ቆሮንቶስን መልእክት በምንመረምርበት ጊዜ፥ እነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች ጳውሎስ የድጋፍ ደብዳቤ ስለሌለውና ከ12ቱ ይፋዊ ሐዋርያት አንዱ ስላልሆነ፥ እውነተኛ ሐዋርያ አይደለም ማለታቸውን እንገነዘባለን (2ኛ ቆሮ. 3፡1፤ 11፡5፤12፡11-12)። በተጨማሪም፥ ጳውሎስ አንደበተ ርቱዕ ያልሆነ ደካማ ሰው እንደሚመስል ገለጹ (2ኛ ቆሮ. 11፡6)። እንዲሁም ጳውሎስ በአካል ቀርቦ ለመነጋገር ሳይችል ጠንካራ ደብዳቤዎችን የሚጽፍ መሆኑን አስረዱ (2ኛ ቆሮ. 10፡10)። ከዚህም ሌላ በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ስም ለራሱ ገንዘብ እንደሚሰበስብም በመግለጹ ሳይከሱት አልቀሩም (2ኛ ቆሮ. 8፡20-23)። ጳውሎስ እንደሚጎበኛቸው ከተናገረ በኋላ በመቅረቱ ሊታመን እንደማይችል ጭምር ተናገሩ (2ኛ ቆሮ. 1፡15-2፡1)። እነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች የጳውሎስን አስተምህሮና ከብሉይ ኪዳን ጋር ያለውን ግንኙነት፥ እንዲሁም የድነትን (ደኅንነትን) መንገድ ተቃወሙ። ጳውሎስ ለዚህ ተቃውሞ ምላሽ በመስጠት ልቡንና ሕይወቱን ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከፈተ። ጳውሎስ ከደብዳቤ ይልቅ የግል ምስክርነት በሚመስለው መልእክቱ ስለ አገልግሎቱ፥ ሐዋርያነቱን ስለሚያረጋግጡት ነገሮችና መልእክቱ ተቀባይነት ሊያገኝ ስለሚገባቸው ምክንያቶች አብራርቷል። ጳውሎስ በመልእክቱ ውስጥ ካካተታቸው ነገሮች አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው። በዕቅዱ መሠረት ለምን ቆሮንቶስን እንዳልጎበኘ ለማብራራት (2ኛ ቆሮ. 1፡15-24)። ቀደም ሲል የጻፈላቸውን መልእክት ስለተቀበሉ ለመልእክቱና ለእርሱ የነበራቸውን አመለካከት ስለቀየሩ አማኞችን ለማመስገን (2ኛ ቆሮ. 7፡14-15) በቤተ ክርስቲያን የተቀጣውን ወንድም ወደ ኅብረቱ እንዲመልሱት ለማሳሰብ (2ኛ ቆሮ. 2፡6-9)። የሐሰት አስተማሪዎችን የሚከተሉትን ወገኖች ለማስጠንቀቅ (2ኛ ቆሮ 11፡3፥ 4፥ 13)። የክርስቶስ እውነተኛ ሐዋርያ እንደሆነና በእርሱ ሥልጣን የሚናገር እገልጋይ መሆኑን ለማረጋገጥ (2ኛ ቆሮ. 11፡1-12፡21)። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ለኢየሩሳሌም ድሆች በሚዋጣው ገንዘብ ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማሳሰብ (2ኛ ቆሮ. 8፡10-12)፡፡ ይህ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የተጻፈው መልእክት ንስሐን በማስከተሉና አማኞች ጳውሎስን እንዲቀበሉ በማድረጉ ረገድ ውጤታማ የነበረ ይመስላል። ይህንንም ጳውሎስ መልእክቱን ከጻፈ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ቆሮንቶስ ተጉዞ ለሦስት ወራት ካገለገለበት ሁኔታ መረዳት ይቻላል ( የሐዋ. 20፡2-3)። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥም ሉቃስ በጳውሎስና በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መካከል አለመግባባት ስለመኖሩ አልጠቀሰም። ጳውሎስ የሮሜን መልእክት የጻፈው በዚህ ጊዜ ሲሆን፥ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ችግር ስለመኖሩ አልገለጸም። በተጨማሪም፥ «ጠንካራው መልእክት» ጠፍቶ ሳለ ይኸኛው መልእክት ተጠብቆ መቆየቱም የቆሮንቶስን አማኞች የልብ ለውጥ ያሳያል። የ2ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ልዩ ባሕርያት የእግዚአብሔርን ሰው ታላቅ የሚያደርገው ምንድን ነው? የልቡ ፍላጎት ምን ሊሆን ይገባል? መረዳቱ ምን ሊሆን ይገባል? ከቤተ ክርስቲያን ጋር የሚኖረው ግንኙነት ምን ዓይነት መሆን አለበት? ስደቶችንና አሳዛኝ ሁኔታዎችን እንዴት ማስተናገድ አለበት? የ2ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል። ይህንን የሚያደርገው ግን ምን ልናደርግ እንደሚገባን የሚያስረዳ ስብከት በመጻፍ አይደለም። ነገር ግን ጳውሎስ እግዚአብሔር በሕይወቱ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በሚሠራበት ጊዜ ስለነበረው አኗኗሩ የግል ምስክርነቱን ይሰጣል። ጳውሎስ ሌሎች ሰዎች የእርሱን «ምሳሌነት» እንዲከተሉ ይፈልጋል። «እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ» ሲል ተናግሯል (1ኛ ቆሮ. 11፡1)። ጳውሎስ ከየትኞቹም መልእክቶቹ በላይ በ2ኛ ቆሮንቶስ ስለ ግል ሕይወቱ ይነግረናል። እንደ ጳውሎስ እግዚአብሔር እንዲጠቀምባቸው የሚፈልጉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና ወንጌላውያን ይህን መልእክት ሊያጠኑና ከሕይወታቸው ጋር ሊያዛምዱ ይችላሉ። ጳውሎስ ሰዎችን ወደ ታላቅነት የሚወስደው የመስቀሉ መንገድ ወይም የመከራ ጎዳና እንደሆነ አሳይቷል። እንደ ዛሬው ዘመን ሁሉ፥ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ክርስቲያን በመሆናቸው ምክንያት በሚያገኙት ጥቅም ላይ ያተኮሩ ይመስላል። የተሟላ ጤንነት፥ በተአምራት መመካት፥ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘት፥ ሰብአዊ ኃይል፥ ወዘተ. ይፈልጉ ነበር። በትምህርትና ሌሎችን በሚያስደስቱ ነገሮች ላይ ያተኩሩ ነበር። ክርስቶስን የሚከተሉት በራስ ወዳድነት ነበር። ጳውሎስ ግን ክርስቶስን መከተል የመስቀሉ ጎዳና እንደሆነና እግዚአብሔርም መከራን ለሚቀበሉት የመጽናናት አምላክ እንደሆነ ያስረዳል (2ኛ ቆሮ. 1፡3-7)። እንደ ሐዋርያና እንደ ክርስቲያኖች ሁልጊዜም ለክርስቶስ ሲሉ ሞትን መጋፈጥ ነበረባቸው (2ኛ ቆሮ. 4፡11)። ጳውሎስ ከድካም፥ ስድብ፥ መከራ፥ ስደትና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ከመሸሽ ይልቅ ይመካባቸው ነበር። ምክንያቱም በሚደክምበት ጊዜ የእግዚአብሔር ኃይል እንደሚያልፍበት ያውቅ ነበር (2ኛ ቆሮ. 11፡30፤ 12፡10)። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ምን ያህል ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ይልቅ ራሳቸውን ለማክበር በመፈለጋቸው ምክንያት ከክርስቶስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለራስ ወዳድነት ዓላማ እንዴት እንደሚጠቀሙ ግለጽ። ለ) ዛሬ ወጣት ክርስቲያኖች የመስቀሉን የመከራ መንገድ የሚፈሩት ለምንድን ነው? ሐ) ስንደክምና መከራን ስንቀበል እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ እንደሚያይል የሚያስረዳውን መንፈሳዊ መርሆ መረዳቱ ለምን ይጠቅማል? መ) ይህ በአንተ ወይም በሌላ ሰው ሕይወት ውስጥ እንዴት እንደተፈጸመ የሚያስረዱ ምሳሌዎችን ዘርዝር። ጳውሎስ ዓለም ከማይቀበለው የጎሳ ድንበር ባሻገር ዓለም አቀፋዊቷ ቤተ ክርስቲያን እርስ በርሷ መረዳዳት እንዳለባት ያሳያል። በጳውሎስ ዘመን በአይሁዶችና አሕዛብ መካከል ጠንካራ ጠላትነት ነበር። በአሕዛብ አገሮች አይሁዶች ለትንሽ ጉዳይ መከራ ይቀበሉና ይገደሉ ነበር። አይሁዶችም አሕዛብን አጥብቀው ከመጥላታቸው የተነሣ ድነትን (ደኅንነትን) ሊያገኙ እንደማይችሉና እግዚአብሔር ለፍርድ እንደፈጠራቸው ያምኑ ነበር። በጳውሎስ አገልግሎት አማካኝነት በቀዳሚነት አይሁዶች የሚበዙበት ቤተ ክርስቲያን በአሕዛብ እየተሞላች መጣች። ይህም በአይሁዶች መካከል ቁጣንና ጥላቻን አስከተለ። ጳውሎስ አይሁድና አሕዛብ ክርስቲያኖች አንድ ቤተሰብ መሆናቸውን ያውቅ ነበር። በተጨማሪም፥ ሰይጣን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቅንአትንና ጠላትነትን በቀላሉ ለማራባት እንደሚፈልግ ያውቅ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ የአሕዛብ ክርስቲያኖች የአይሁድ ክርስቲያኖችን እንዲቀበሉና እንዲረዱ፥ አይሁዶቹም ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ዕርዳታውን እንዲቀበሉ ለማግባባት ከፍተኛ ጥረት አደረገ። ጳውሎስ የአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት ለማያውቋቸው የኢየሩሳሌም ድሆች በልግስና እንዲሰጡ አበረታታቸው። በጎሳዊ ቡድኖች መካከል ጠላትነት በሚኖርበት ጊዜ ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያናቸው ያንኑ ጠላትነት እንዳታንጸባረቅ ማድረግ አለባቸው። ነገር ግን አንደኛው የጎሳ ቡድን ለሌላኛው ፍቅርንና አቀባበልን ማሳየት አለበት። በዚህ ዓይነት ሁላችንም የአንድ መንፈሳዊ ቤተሰብ አባላት መሆናችንንና ይህም ቤተሰብ ከምድራዊ ቤተሰብ ወይም የጎሳ ቡድን እንደሚበልጥ ልናሳይ እንችላለን። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በኢትዮጵያ ውስጥ ታሪካዊ የጠላትነትና የጥርጣሬ ግንኙነት ያላቸውን ሁለት ጎሳዎች ጥቅስ። ለ) ይኸው ተመሳሳይ ጥላቻና ጥርጣሬ እንዴት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊመጣ እንደሚችል ግለጽ። ሐ) የአንደኛው ጎሳ አባላት የሆኑ ክርስቲያኖች ሌላኛው የጎሳ አባላት የተወደዱ፥ ተቀባይነት ያገኙና የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን ለማሳየት ሊያደርጓቸው የሚችሏቸውን ነገሮች ዘርዝር። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን

የ2ኛ ቆሮንቶስ ዓላማ እና ልዩ ባሕሪያት Read More »

የ2ኛ ቆሮንቶስ መግቢያ

ስንታየሁ ከመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ በቅርቡ ተመርቆ አባል በነበረበት የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መጋቢ በመሆን ያገለግል ጀመር። መጀመሪያ ነገሮች በጥሩ ሁኔታ ይከናወኑ ጀመረ። እምነቱን ለዓለማውያን ከማካፈሉም በላይ፥ በየእሑዱ የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናትና መስበክ ያስደስተው ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ችግሮች መኖራቸውን ተገነዘበ። ሁለት ሽማግሌዎች ተጣልተው መነጋገር አቁመዋል። ሁለት የኳዬር መዘምራን ወሲባዊ ኃጢአት እየፈጸሙ ይመላለሱ ነበር። እነዚህ መዘምራን የታላላቅ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ልጆች ነበሩ። ጎሳዊ ውጥረቶች ቤተ ክርስቲያንን ይከፋፍሉ ነበር። እርሱ የአንድ ጎሳ አባል በመሆኑ ለዘሮቹ እንደሚያዳላ ይታማ ጀመር። ብዙውን ጊዜ ወዳጆቹና ቤተሰቦቹ ልዩ ችሮታ እንዲያደርግላቸው ይጠይቁታል። ሰዎች የትዳር፥ የሥራ ማጣት፥ የኤድስ በሽታና ሌሎችም ከባባድ ችግሮችን ይዘው በመምጣት የእርሱን እገዛ ይጠይቃሉ። እነዚህ የማያቋርጡ ችግሮች ስላዛሉት የቤተ ክርስቲያን አመራሩን ለመልቀቅ ተዘጋጀ። “ሁልጊዜም እነዚህን ችግሮች ከመስማት ይልቅ ነጋዴ መሆኑ በጣም ይቀላል” ሲል አሰበ። ነገር ግን የሙሉ ጊዜ አገልግሎቱን ለቅቆ ንግዱን ለመጀመር ባሰበ ቁጥር የጌታ መንፈስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባለው አገልግሎቱ እንዲቀጥል ሲገፋፋው ይሰማዋል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንተ ወይም አንተ የምታውቀው ሰው በቤተ ክርስቲያን የአመራር ችግሮች ሲታወክ ያየኽው እንዴት ነው? ለ) 2ኛ ቆሮ. 11፡28-29 አንብብ። 1) ጳውሎስ ተጨማሪ ችግር አመጣብኝ ያለው ምንን ነው? 2) ይህ በቤተ ከርስቲያንህ ውስጥ ለሚያገለግሉ መሪዎች እውነት የሆነው እንዴት ነው? 3) እነዚህ ጥቅሶች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚገባ የሚገልጹት እንዴት ነው? ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሰዎች ችግሮች ከመዛል የሚድኑት እንዴት ነው? ጳውሎስም ከዚህ የቤተ ክርስቲያን አመራር ጋር ታግሏል። ሊያገለግላቸው የሚፈልጋቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ ብቃት እንደሌለው፥ አምባገነን እንደሆነ፥ እንደ ሌሎቹ ጥሩ መሪ እንዳልሆነ፥ የተሳሳቱ አነሣሽ ምክንያቶች እንዳሉት፥ ወዘተ… በመግለጽ በተሳሳተ መንገድ ይረዱት ነበር። ጳውሎስ ስለ ወንጌሉ ከፍተኛ አካላዊ መከራ እንደተቀበለ በ2ኛ ቆሮ. 11 ውስጥ ገልጾአል። ከሁሉም በላይ የሚከብደው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቱ እንደሆነም አስረድቷል። ለክርስቲያኖች ችግሮች መፍትሔ መፈለጉ አድክሞት ነበር። የ2ኛ ቆሮንቶስ መጽሐፍ ስለ ቤተ ክርስቲያን መሪነት ከፍተኛ ትምህርት ይሰጣል። እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ለማገልገል ከፈለግን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ምን እንደሚመስል፥ ምን ዓይነት ኃዘንና ደስታን እንደሚያስከትል፥ ከሁሉም በላይ ችግሮች በሚኖሩበት ጊዜም እንኳ እግዚአብሔርን እንዴት በታማኝነት እንደምናገለግል ማወቅ አለብን። የውይይት ጥያቄ፡– ስለ 2ኛ ቆሮንቶስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብና ስለ ጸሐፊው፥ ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱና ስለ መጽሐፉ የተጻፈውን ሁሉ ጠቅለል አድርገህ ግለጽ። የ2ኛ ቆሮንቶስ ጸሐፊ የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) 2ኛ ቆሮንቶስ 1፡1 አንብብ። የ2ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ጸሐፊ ነኝ የሚለው ማን ነው? ለ) ከእርሱ ጋር ማን ነበር? ሐ) መልእክቱ የተጻፈው ለምንድን ነው? ጳውሎስ ሁልጊዜም እንደሚያደርገው፥ የ2ኛ ቆሮንቶስን መልእክት የጀመረው ስሙንና የጻፈበትን ሥልጣን በመግለጽ ነበር። እርሱ «የክርስቶስ ሐዋርያ» ነበር። ሐዋርያው እንደ መሆኑ፥ ጳውሎስ ክርስቶስን እንዲወክልና በሥልጣኑ እንዲናገር ክርስቶስ ወክሎት ነበር። ጳውሎስ የተናገረው የግል አሳብ ሳይሆን ክርስቶስን የሚወክል ነበር። ስለሆነም፥ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ክርስቶስን የሚሰሙትን ያህል ጳውሎስን መስማት ነበረባቸው። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ጠቅሶታል። ጢሞቴዎስ የወንጌል ስርጭት አጋሩ፥ የበፊቱን የ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ያደረሰና (1ኛ ቆሮ. 4፡17) የቆሮንቶስን ክርስቲያኖች በሚገባ የሚያውቅ ነበር። ጳውሎስ መልእክቱን ለማን ጻፈ? ጳውሎስ ይህን መልእክት የጻፈው «በአካይያ አገር ሁሉ ከሚኖሩ ቅዱሳን ሁሉ ጋር በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን» ነበር። ቆሮንቶስ ከግሪክ ዐበይት ከተሞች አንዷ እንደነበረች በ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክት መግቢያ ውስጥ ተጠቅሷል። ቆሮንቶስ ከግሪክ በስተደቡባዊ አካያን በሚባል አውራጃ ውስጥ ትገኝ ነበር። ጳውሎስ በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው በአብዛኛው በቆሮንቶስ ከተማ ኖሯል። በቆሮንቶስ ከተማ የተተከለችው ቤተ ክርስቲያን የኋላ ኋላ ወደ ሌሎች የአውራጃው ከተሞች ተሰራጨች። ቆሮንቶስ ሰፊ ከተማና የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት «እናት ቤተ ክርስቲያን» ስለነበረች፥ የቆሮንቶስ አማኞች ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በጳውሎስና እርሱ ለመፍታት በሚፈልጋቸው ነገሮች ላይ የነበራቸውን አመለካከት ሊጫኑ ይችሉ ነበር። ጳውሎስና በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መካከል የነበረው ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ ቢሻክርም፥ ጳውሎስ ሁለት ጠቃሚ ነገሮችን ተገንዝቧል። ይህ ግንዛቤም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋር በነበረው ግንኙነት ላይ ጠቃሚ አስተዋጽኦ አድርጓል። በመጀመሪያ፥ የክርስቲያኖች ማኅበረሰብ የእግዚአብሔር ንብረት ነበር። ምንም እንኳ ጳውሎስ ስጦታ ያለው ሐዋርያና የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መሥራች ቢሆንም፥ እያንዳንዱ ክርስቲያንና ጠቅላላው የክርስቲያኖች ማኅበረሰብ የእግዚአብሔር መሆናቸውን ተረድቷል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታየው ነገር ሁሉ አምልኮተ እግዚአብሔርን ማንጸባረቅ ነበረበት። ሁለተኛ፥ ምንም እንኳ ሁልጊዜም በተግባራዊ ቅድስና የማይመላለሱ ደካሞችና ራስ ወዳዶች ቢሆኑም፥ ጳውሎስ እነዚህን ክርስቲያኖች «ቅዱሳን» ብሎ ይጠራቸዋል። ቅዱስ የሚባለው ሰው ኃጢአት-አልባና ለእግዚአብሔር አንድ ታላቅ ተግባር የፈጸመ ሰው አይደለም። ሥጋዊ ክርስቲያኖችን ጨምሮ፥ እያንዳንዱ ክርስቲያን ቅዱስ ነው። ቅዱሳን የሆንነው በእግዚአብሔር ስለተመረጥን፥ ከማያምኑ ሰዎች ስለተለየንና የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካል ስለሆንን ነው። ጳውሎስ 2ኛ ቆሮንቶስን የጻፈበት ዘመንና ስፍራ ለአምስት ዓመታት ያህል ጳውሎስ ሦስተኛውን የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ ሲያካሂድ ነበር (ከ52-57 ዓ.ም.)። በዚህ ወቅት አብዛኛውን ጊዜ የኖረው በኤፌሶን ከተማ ነበር። ጳውሎስ በኤፌሶን ሳለ ከቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የተለያዩ መሪዎች እንደጎበኙት በ1ኛ ቆሮንቶስ ጥናታችን ተመልክተናል። እነዚህ ጎብኚዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ስለነበሩት ክፍፍሎችና ኃጢአቶች ለጳውሎስ ገለጻ አደረጉለት። በተጨማሪም፥ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች፥ ለኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ስለሚሰጠው ስጦታ፥ ስለ ጋብቻ፥ ወዘተ. የሚጠይቁ አሳቦች የተካተቱበትን ደብዳቤ ከቆሮንቶስ ክርስቲያኖች አመጡለት። በ55 ዓ.ም የተጻፈውን የ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ያደረሰው ጢሞቴዎስ ነበር። የውይይት ጥያቄ፡– 2ኛ ቆሮ. 2፡1-13፤ 7፡5-15፤ የሐዋ. 19፡21-41 አንብብ። እነዚህ ጥቅሶች በ1ኛና 2ኛ ቆሮንቶስ ጽሑፍ መካከል ስለተፈጸሙት አንዳንድ ነገሮች ምን የሚያመለክቱ ይመስላል? በ1ኛና 2ኛ ቆሮንቶስ መጻፍ መካከል የተፈጸሙትን ነገሮች ማወቁ አስቸጋሪ ነው። በ1ኛና 2ኛ ቆሮንቶስ ጽሑፍ መካከል በነበሩት ከአንድ ዓመት በሚበልጡ ጊዜያት የሚከተሉት ነገሮች የተከናወኑ ይመስላል። ሀ. ጢሞቴዎስ የአንደኛ ቆሮንቶስን መልእክት ይዞ ቆሮንቶስ ሊደርስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መልእክቱን የተቀበሉት በሁለት ቅይጥ ምላሾች ነበር። ስለ ጌታ እራትና ለጣዖት የተሠዋ ሥጋን ስለመብላት የሰጣቸው ምላሽ የጠቀማቸው ይመስላል። ነገር ግን የወሲብ ኃጢአት ስለፈጸመው ግለሰብ የሰጠው ፍርድ አንዳንድ ተቃውሞዎችን ያስከተለ ይመስላል (1ኛ ቆሮ. 5)። በተጨማሪም፥ አንዳንድ ሰዎች የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጳውሎስ ላይ እንዲያምጹና ሥልጣኑን እንዲጠራጠሩ የቀሰቀሱ ይመስላል። ይህም በጳውሎስና በቆሮንቶስ አማኞች መካከል የነበረውን ግንኙነት አቀዘቀዘው። ጢሞቴዎስ ወደ ጳውሎስ ተመልሶ ስለ አመለካከታቸው አብራራለት። ለ. ጳውሎስ ለአጭር ጊዜ ጉብኝት ወደ ቆሮንቶስ ሄደ። ጳውሎስ ይህንን «የኃዘን ጉብኝት» ይለዋል (2ኛ ቆሮ. 2፡1)። በዚህ ጊዜ ስለተፈጸመው ነገር ጳውሎስ ምንም አልጠቀሰም። ነገር ግን ግንኙነታቸው በመሻከሩ ጳውሎስ ለማስተካከል የፈለጋቸውን ነገሮች ሳያስተካክል ወደ ኤፌሶን የተመለሰ ይመስላል። ሐ. ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን ከተመለሰ በኋላ ሐዋርያዊ ሥልጣኑን ተጠቅሞ ጠንካራ የተግሣጽ ደብዳቤ ጻፈላቸው። ይህንንም ደብዳቤ ሌላኛው ረዳቱ ቲቶ አደረሰላት (2ኛ ቆሮ. 2፡3-9፤7፡5-7)። መ. የኤፌሶን አገልግሎቱ ሊፈጸም ሲል በጳውሎስ ላይ የነበረው ተቃውሞ ይበልጥ ተጠናከረ። ድሜጥሮስ በተባለ ግለሰብ መሪነት በኤፌሶን ጳውሎስን ለመግደል የሚፈልጉ ሰዎች ሁከት አስነሡ (የሐዋ. 19፡23-41)። ከአይሁዶች የተሰነዘረበት ተቃውሞም ቀላል አልነበረም። ከዚህ ሁከት በኋላ ብዙም ሳይቆይ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዘ ሳለ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትን ሊጎበኝ የወሰነ ይመስላል። ሠ. ጳውሎስ ከኤፌሶን ወደ ጢሮአዳ ሲሄድ የተሳካ አገልግሎትና የጠነከረ ተቃውሞ ገጠመው። ከዚያም ወደ መቄዶንያ (ሰሜን ግሪክ) በመጓዝ የፊልጵስዩስን፥ የተሰሎንቄንና የቤሪያን አብያተ ክርስቲያናት ሳይጎበኝ አልቀረም። በመቄዶንያ ሆኖ የቆሮንቶስ አብያተ ክርስቲያናትን ምላሽ ይጠባበቅ ነበር (2ኛ ቆሮ. 7፡5-7)። በዚህ ጊዜ የተመለሰው ቲቶ የቆሮንቶስ አማኞች ንስሐ ገብተው አመለካከታቸውን እንደለወጡ በመግለጽ ጳውሎስን ደስ አሰኘው። ረ. ጳውሎስ በ55 ዓ.ም. የመጨረሻዎቹ ወራት ወይም በ56 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ ወራት ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሌላ መልእክት ጻፈ። ይህ ሁለተኛ ቆሮንቶስ ብለን የምንጠራው መልእክት በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የአመለካከት ለውጥ ጳውሎስ ደስ መሰኘቱን ያሳያል። ነገር ግን ይህን የደስታ መልእክት እየጻፈ ሳለ የሐሰት አስተማሪዎች በቆሮንቶስ እየተስፋፉ መሆናቸውን በመስማቱ ጳውሎስ

የ2ኛ ቆሮንቶስ መግቢያ Read More »