ለቅዱሳን የተደረገ የገንዘብ መዋጮ እና የሐዋርያው ጳውሎስ ዕቅድ (1ኛ ቆሮ. 16፡1-24)

የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች አይተዋቸው ለማያውቋቸውና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ገንዘብ መስጠት ያለባቸው ለምንድን ነው? (1ኛ ቆሮ. 6፡1-4)

የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የጠየቁት የመጨረሻው ጉዳይ በኢየሩሳሌም ለሚገኙ አይሁዳውያን አማኞች ገንዘብ መዋጣትን የሚመለከት ነበር። ጳውሎስ በቅርቡ ክርስቲያኖች በድህነት ወደሚሠቃዩባት ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ለአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተናገረ ይመስላል። ስለሆነም የአሕዛብ ክርስቲያኖች ለአይሁድ ክርስቲያኖች ፍቅራቸውንና ወንጌሉን ለማካፈላቸው ምስጋናቸውን የሚገልጹበትን ዕድል ሰጣቸው። ጳውሎስ አሕዛብ ክርስቲያኖች በየሳምንቱ ምጽዋት እንዲሰበስቡና እርሱ በሚመጣበት ጊዜ በተወሰኑ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አማካኝነት ገንዘቡን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲልኩ መከራቸው። (ጳውሎስ እንደገና በ2ኛ ቆሮ. 8-9 ስለዚህ ጉዳይ ያነሣል።)

ከዚህ ክፍል አያሌ ጠቃሚ እውነቶችን ልንማር እንችላለን።

ሀ. ክርስቲያኖች ሁሉ ሁልጊዜም ለእግዚአብሔር ሥራና ለእግዚአብሔር ሕዝብ ገንዘባቸውን መስጠት አለባቸው። ጳውሎስ በየእሑዱ ምጽዋት እንዲሰበስቡ ነግሯቸዋል።

ለ. አማኞች ለራሳቸውና ለማኅበረ ምእመኖቻቸው ብቻ ሳይሆን በዓለም ሁሉ ለተበተኑት ወንድሞችና እኅቶች ፍላጎት ሊያስቡ ይገባል።

ሐ. ክርስቲያን መሪዎች ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ዝናቸው እንዳይጎድፍ መጠንቀቅ አለባቸው። ጳውሎስ ገንዘቡን ለማድረስ ሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች አብረውት እንዲሄዱ ጠይቋል። ጳውሎስ ይህን ያደረገው በራሱ ታማኝነት ላይ ጥርጣሬ ስላደረበት ሳይሆን፥ ታማኝነቱን የሚጠራጠሩ ሰዎች ወሬ እንዳያዛምቱበት ነበር። የመሪዎች ስም ከሚጎድፍባቸው ዐበይት መንገዶች አንዱ የተሳሳተ የገንዘብ አያያዝ ወይም ሌሎች ሰዎች የሚጠራጠሩበትን በር መክፈት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) የተሳሳተ የገንዘብ አጠቃቀም የአንድን ቤተ ክርስቲያን መሪ ስም ሲያጎድፍ ያየኸው እንዴት ነው? መሪዎች ስማቸውን ለመጠበቅ ምን የተለየ ነገር ማድረግ አለባቸው? ለ) ብዙ ክርስቲያኖች አሥራትን የሚሰጡ ይመስልሃል? ካልሆነ ለምን? ሐ) የአንድ ቤተ ክርስቲያን የገንዘብ አጠቃቀም፤ የራስን ጥቅም ከመፈለግና ከራስ ወዳድነት ወይም ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ክርስቲያን ያልሆኑትን ለመርዳት እንደዋለ የሚታወቀው እንዴት ነው?

መደምደሚያ (1ኛ ቆሮ. 16፡5-24)

ጳውሎስ ተጨማሪ ግላዊ መረጃ በመስጠት ይህን መልእክት ደምድሟል። በኤፌሶን ለጥቂት ወራት ከተቀመጠ በኋላ በመቄዶንያ በኩል ወደ ቆሮንቶስ ተጉዞ አያሌ ወራት እንደሚቆይ ይነግራቸዋል። ጢሞቴዎስ ሊጎበኛቸው ስለሚመጣ መልካም አቀባበል እንዲያደርጉለት ያሳስባቸዋል። በተጨማሪም፥ ጳውሎስ አጵሎስ ሄዶ እንዲያገለግላቸው መፈለጉንና አጵሎስ ግን በወቅቱ ይህንኑ ሊያደርግ አለመቻሉን ገልጾአል። አጵሎስ ከጳውሎስ የበለጠ የመናገር ስጦታ የነበረው ቢመስልም ጳውሎስ አልቀናበትም ነበር። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድጉ ስለሚፈልግ፥ አጵሎስ ከመንፈሳዊ ለጋነታቸውና ከችግሮቻቸው አልፈው እንዲሄዱ ይረዳቸው ዘንድ ወደደ፡፡

ጳውሎስ ለቆሮንቶስ አማኞች ሰላምታንና በሦስት ተወካዮቻቸው (እስጢፋኖስ፥ ፈርዶናጥስና አካይቆስ) አማካኝነት ስለላኩለት ስጦታ ምስጋና በማቅረብ መልእክቱን ደምድሟል። ከእስያ ክርስቲያኖች በተለይም ከአቂላና ከጵርስቅላ ሰላምታ አቅርቦላቸዋል። አቂላና ጵርስቅላ በቆሮንቶስ ከተማ ስለኖሩ የአገሪቱ ክርስቲያኖች ያውቋቸው ነበር።

ምሁራን ጳውሎስ የዓይን ሕመም ስለነበረበት መልእክቱን ራሱ ለመጻፍ ሳይሳነው እንዳልቀረ ያስባሉ። በመሆኑም፥ ለሮሜ መጽሐፍ እንዳደረገው በሌላ ጸሐፊ ተጠቅሟል (ሮሜ 16፡22)። ነገር ግን መልእክቱ የሌላ ሰው ሳይሆን የራሱ እንደሆነ ለማሳየት በደብዳቤው ላይ ፈርሞበታል።

ጳውሎስ ይህንን መልእክት የፈጸመው ክርስቶስን የማይወዱትን በማስጠንቀቅ ነበር። ጳውሎስ የክርስቶስን ምጽአት ቢናፍቅም፥ ምጽአቱ ክርስቶስን በሕይወታቸው ባላከበሩት ሰዎች ላይ ፍርድን እንደሚያስከትል አልዘነጋም። እኛም ልባችንን ሁልጊዜ ልንመረምር ይገባል። ልባችን «ማራናታ» ወይም «ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና» እያለ ቢጮህ፥ ለፍርዱ በፊቱ ለመቆም ልባችንን መመርመር አለብን። ለክርስቶስ ምጽአት ዝግጁዎች ነን?

የውይይት ጥያቄ፡- ከ1ኛ ቆሮንቶስ ጥናታችን የተማርሃቸው አንዳንድ ቁልፍ ትምህርቶች ምን ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

አማኝ ከሞተ በኋላ ሥጋው ምን ይሆናል? (1ኛ ቆሮ. 15፡1-58)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሞት የሰዎችን እምነት ጭምር የሚያናጋ አስፈሪ ነገር መሆኑን በተለያዩ መንገዶች አብራራ። ለ) ለክርስቲያኖች ከሞቱ በኋላ ስለሚደርስባቸው ነገር ግልጽ ግንዛቤ ማግኘት አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

በዓለም ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሁሉ ሞትን ይፈራሉ። ከሞት ለማምለጥ ያላቸውን ሀብት ሁሉ ለመሠዋት ፈቃደኞች ናቸው። ከሞት በኋላ የሚሆነውን ነገር በፍጹም አያውቁትም። አንድ መልካም ነገር ይመጣል ብለው ተስፋ ቢያደርጉም አያውቁትም። ስለሆነም፥ ሞት በተስፋ ቢስ ለቅሶና ፍርሃት የተሞላ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከሞት በኋላ በክርስቲያን ላይ ስለሚሆነው ነገር በግልጽ ያብራራል። ይህም እውቀት በሽታንና ሞትን ሳንፈራ በእርጋታ ክርስቶስን እንድንከተል ያደርገናል። ለክርስቲያን ሞት ሥቃይ፥ መከራ ወይም ሞት ወደሌለበት ስፍራ የሚመራን በር ማለት ነው። በዚያ ከክርስቶስ ጋር ለዘላለም እንኖራለን።

የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 15ን አንብብ። ሀ) ጳውሎስ ስለ ሙታን ትንሣኤ የገለጻቸውን እውነቶች ዘርዝር። ለ) እነዚህን እውነቶች ክርስቲያኖች ሁሉ በግልጽ ማወቃቸውና ማመናቸው ለምን ይጠቅማል?

ችግሩ፡- ብዙ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የሙታን ትንሣኤ መኖሩን የተጠራጠሩ ይመስላል። ግሪኮች በሥጋ ትንሣኤ አያምኑም ነበር። ለዚህ ነበር የአቴና ሰዎች ጳውሎስ ወንጌሉን ሲመሰክርላቸው የቀለዱበት። (የሐዋ. 17፡32 አንብብ።) እንደ ሰውነት ያሉ የተፈጠሩ ነገሮች ተራና በራሳቸው ክፉ ናቸው የሚል እምነት ነበር። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር ተራ የሆነውን ነገር ወደ መንግሥቱ እንዲገባ ስለማይፈቅድ መንፈስ እንጂ ሥጋ ከሞት እንዲነሣ አያደርግም የሚል አሳብ ነበራቸው። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችም ከሞት መነሣትን በተመለከተ ጳውሎስ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ደብዳቤ ጽፈው ጠየቁት። የጳውሎስ መልስ፡

፩. የክርስቶስ ትንሣኤ እኛም ከሞት እንደምንነሣ ያረጋግጣል (1ኛ ቆሮ. 15፡1-34)

ሀ. ወንጌሉ ክርስቶስ ለኃጢአት መሞቱን ብቻ ሳይሆን በሥጋ ከሞት መነሣቱንም ያስተምራል። የእርሱ ትንሣኤ መንፈሳዊ ብቻ አልነበረም። የክርስቶስ መነሣት በብዙ ሰዎች ተረጋግጧል። ራሱ ጳውሎስም ከሞት የተነሣውን ክርስቶስን አይቶታል። ጳውሎስ ከዕርገት በኋላ ከሞት የተነሣውን ጌታ ማየቱ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላም ቢሆን የትንሣኤ አካሉን ይዞ እንደሚገኝ ያመለክታል። ስለሆነም፥ የምናመልከው ክርስቶስ እንደ መንፈስ ብቻ ሳይሆን በትንሣኤ አካልም ይኖራል።

ለ. አካላዊ ትንሣኤን መካድ ማለት ክርስቶስ ራሱ ከሞት አልተነሣም እንደ ማለት ነበር። ይህ ማለት ደግሞ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ የሚያስተምረው ትምህርት ብቻ ሳይሆን ጠቅላላው ክርስትና ውሸት ነው እንደ ማለት ነበር። ቀደም ሲል የሞቱት ክርስቲያኖችም እንደ ዓለማውያን ሁሉ ያለ ተስፋ ጠፍተዋል እንደ ማለት ይሆናል። ለወደፊቱ የትንሣኤ ተስፋ ከሌላቸው ደግሞ ክርስቲያኖችም እንደ ዓለማውያን ሁሉ ያለ ተስፋ ጠፍተዋል ማለት ነበር። ለወደፊቱ የትንሣኤ ተስፋ ከሌላቸው ደግሞ ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር መኖራቸውን አቁመው ለራሳቸው መኖር ይኖርባቸዋል። ምቾትን በመከተል በሕይወት መደሰት አለብን። እንዲሁም፥ ከሞት በኋላ ሕይወት ከሌለ ፋይዳ ሊሰጥ ከማይችል ስደት መሽሽ አለብን ማለት ነው።

ሐ. ክርስቶስ ከሞት የተነሣ ሲሆን፥ ለተከታዮቹ የትንሣኤ ምሳሌ ነው። ጳውሎስ የክርስቶስ ትንሣኤ የሁሉም ክርስቲያኖች ትንሣኤ ምሳሌ መሆኑን ለማሳየት ሁለት ማብራሪያዎችን ተጠቅሟል። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ የሚሞቱት ክርስቲያኖች ሁሉ «በኩር» መሆኑን ገልጾአል። በብሉይ ኪዳን አዝመራ በሚደርስበት ጊዜ አይሁዶች ከእህል አነስተኛውን ክፍል ወደ ቤተ መቅደስ ወስደው ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ነበር (ዘሌ. 23፡10-11፥ 17፥20)። ይህንንም የሚያደርጉት እግዚአብሔር አዝመራውን እንደሰጣቸው ለመግለጽና ለስጦታውም ምስጋናቸውን ለማቅረብ ነበር። አንድ ሰው ከእህሉ የተወሰነውን ለእግዚአብሔር በሚሰጥበት ጊዜ የቀረውን ለእግዚአብሔር ክብር እንደሚያውል መግለጹ ነበር። ክርስቶስም እንዲሁ ከሞት የተነሡት ሰዎች ታላቅ አዝመራ በኩራት ነው። የክርስቶስ ተከታዮች እንደ ክርስቶስ ሁሉ ከሞት ይነሣሉ። ሁለተኛ፥ ኢየሱስ ሁለተኛው «አዳም» ነው። የመጀመሪያው አዳም በኃጢአቱ ምክንያት በሰዎች ሁሉ ላይ ሥጋዊና መንፈሳዊ ሞት አስከትሏል። ሁለተኛው አዳም ግን ከሞት በመነሣቱ ለክርስቲያኖች መንፈሳዊና ሥጋዊ ትንሣኤ ሕይወት አስገኝቶላቸዋል።

መ. የክርስቶስ ትንሣኤ በዘላለማዊነት የሚፈጸም የታላቅ ሂደት ጅማሬ ነው። ክርስቶስ «የትንሣኤዎች መከር» መጀመሪያ በመሆኑ፥ የትንሣኤን ሂደት በአዲስ አካል ጀምሯል። ሁለተኛ፥ የብሉይም ሆነ የአዲስ ኪዳን ቅዱሳን ትንሣኤ ይከተላል። ሦስተኛ፥ ክርስቶስ አገዛዙን በሰዎች ሁሉ ላይ ከመሠረተና ክፋትን ሁሉ ካወደመ በኋላ፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር አብ አሳልፎ ይሰጣል። ከሚጠፉት የመጨረሻ ክፋቶች አንዱ ሞት ነው።

፪. የትንሣኤው አካል አሁን ካለን አካል ጋር ቢመሳሰልም የተለየ ይሆናል (1ኛ ቆሮ. 15፡35-58)።

አሁን ያለን አካል በኃጢአት የተበላሸ ስለሆነ፥ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት የትንሣኤ አካል እንደሚኖራቸው እያሰቡ ነበር። ጳውሎስ ከትንሣኤ በኋላ ስለሚኖረው ሁኔታ የተለያዩ ገለጻዎችን ያቀርባል።

ሀ. ጳውሎስ የሰው ካልሆኑት ሦስት የተለያዩ አካላት ጋር በማነጻጸር ማብራሪያውን ይጀምራል። በመጀመሪያ፥ የትንሣኤ ሕይወት የተክልን ሕይወት ይመስላል። የስንዴ ዘር መሬት ውስጥ ተቀብሮ ከበሰበሰ በኋላ በእግዚአብሔር ኃይል አዲስ ተመሳሳይ ተክል ያስገኛል። ሁለተኛ፣ እግዚአብሔር ለተለያዩ እንስሳትና ዓሦች የተለያዩ አካላትን ይሰጣል። ሦስተኛ፥ ፀሐይ ከጨረቃ የበለጠ ክብር እንዳላት ሁሉ እግዚአብሔር የተለያዩ የክብር ደረጃ ዎችን ይሰጣል።

ጳውሎስ ከእነዚህ ማብራሪያዎች በመነሣት የሚከተለውን አስተምሯል።

 1. እንደ ተክል ሁሉ የትንሣኤ አካላችን ከቀድሞው አካላችን ጋር የሚመሳሰል ቢሆንም አዲስና የተለየ ይሆናል። ከእንግዲህ ሞትና መበስበስ የማይነካን ዘላለማውያን እንሆናለን። የትንሣኤው አካል ተፈጥሯዊ ብቻ ሳይሆን ለዘላለም ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር የሚያስችል መንፈሳዊ ብቃት ያለው አዲስ አካል ነው።
 2. እንደ ተለያዩ አካላት ሁሉ፥ የትንሣኤ ተጨባጭ ትንሣኤ ይሆናል። ነገር ግን የተለየ ዓይነት አካል ይኖረናል።
 3. የፀሐይና የጨረቃ ክብር የተለያየ እንደሆነ ሁሉ፥ አሁን ያሉን አካላት ብዙ ክብር የላቸውም። ከትንሣኤ በኋላ ግን አካላችን አዲስ ክብርና ኃይል ይኖረዋል።

ለ. ጳውሎስ አዳምንና ክርስቶስን (ሁለተኛ አዳም) ያነጻጽራል። አዳም የተፈጠረው ከምድር አፈር ነበር። የእኛም ቁሳዊና ኃጢአተኛ አካላት የእርሱን ይመስላሉ። ክርስቶስ ግን ከሰማይ ስለመጣ ከመጀመሪያው አዳም ይበልጣል። ክርስቶስ ከሞት ከተነሣ በኋላ አዲሱን «መንፈሳዊ» አካል መሥርቷል። ይህም ከሞት በተነሣን ጊዜ የምናገኘው ነው። ጳውሎስ መንፈሳዊ አካል የሚለው እንደ መላእክት ያለውን ዓይነት አይደለም። ነገር ግን በመንፈሳዊ ስፍራ ለመኖር የሚያስችል አካል ማለቱ ነው፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች ከትንሣኤው በኋላ ሊዳስሱትና ሊያዩት እንደቻሉት ዓይነት ተጨባጭ ይሆናል። ነገር ግን የትንሣኤ አካላችን የማይጠፋ፣ ኃጢአት እልባና ለዘላለም ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር የሚችል በመሆኑ ከምድራዊ አካል የተለየ ነው። ሰውነታችን የክርስቶስን የትንሣኤ አካል ይመስላል።

ሐ. የጳውሎስ ድምዳሜ፡- የትንሣኤ አካላችን ምን እንደሚመስል ሙሉ በሙሉ ግልጽ ባይሆንም፥ የክርስቶስን የትንሣኤ አካል እንደሚመስል አያጠራጥርም። ልናውቅ የምንችላቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ። በመጀመሪያ፥ ሥጋና ደም የሆነው የአሁኑ አካላችን በዘላለማዊ የእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ለመኖር ስለማይስማማ፥ የግድ ለውጥ መደረግ አለበት። የአሁኑ ሰውነታችን በሆነ መንገድ ተለውጦ የማይበሰብስ ይሆናል፡፡ ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር ለጳውሎስ በብሉይ ኪዳን ያልታወቀውን «ምሥጢር» ገልጦለታል። ያም ምሥጢር በመጨረሻው ዘመን የእግዚአብሔር ልጆች ምን እንደሚሆኑ የሚያሳይ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ነገሮች ከመቅጽበት ይለወጣሉ። ለውጡ የሚጀምረው «በክርስቶስ በሞቱት » ይሆናል። ይህም በሥጋ የሞቱትን ክርስቲያኖች የሚያሳይ ነው። ሥጋዊ ሰውነታቸው በትል ተበልቶ ቢጠፋም፥ የማይጠፋና የማይሞት የትንሣኤ አካል ከመቅጽበት ይቀበላሉ። ከዚያም በምድር ላይ በሕይወት ያሉት ሰዎች ሟች አካል በማይሞት፥ በማይጠፋና በትንሣኤ አካል ይተካል። ከዚያ በኋላ በእምነት ስንጠባበቅ በቆየነው በእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት ውስጥ ለመኖር ዝግጁዎች እንሆናለን።

ስለሆነም፥ ክርስቲያኖች ሞትን ወይም ከመቃብር በኋላ የሚመጣውን ያልታወቀ ክስተት መፍራት የለባቸውም። ምንም እንኳ የምንወዳቸው ሰዎች በሞት በሚለዩን ጊዜ ማዘናችን ባይቀርም፥ እንደ ሌሎች ሰዎች ተስፋ-ቢሶች አይደለንም። ምክንያቱም እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ልጅ አዲስን አካል እንደሚቀበል እናውቃለን። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲመለስና እኛም ዘላለማዊ አካላችንን ተቀብለን ከሌሎች አማኞች ጋር ለዘላለም በምንኖርበት ጊዜ የመለያየቱ ሥቃይ ሳይቀር ይወገዳል። ይህ እውነት ክርስቲያኖችን ሁልጊዜም ሊያጽናናቸው ይገባል። ከመቃብር በኋላ ለዘላለም ከክርስቶስ ጋር እንደምንኖር በመረዳት በልበሙሉነት እየተመላለስን እግዚአብሔርን ልናገለግል እንችላለን። ይህ ለማያምኑ ወይም እምነታቸውን ለተዉትም ማስጠንቀቂያ ነው። ሞተው በሚነሡበት ጊዜ ከሌሎች አማኞች ጋር አብሮ የመኖር ዕድል ሳያገኙ ወደ ዘላለማዊ ሲዖል ይወርዳሉ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ለጉባኤ አምልኮ የተሰጡ መሠረታዊ መመሪያዎች (1ኛ ቆሮ. 14፡26-40)።

ጳውሎስ ለጉባኤ አምልኮ አንዳንድ መመሪያዎችን በሚሰጥበት ጊዜ ለማስተላለፍ የሚፈልገውን መልእክት ለመረዳት ቤተ ክርስቲያኒቱ ምን ትመስል እንደነበረ ማስታወሱ አስፈላጊ ነው። ዛሬ እንደምናደርገው ቤተ ክርስቲያኒቱ በትልቅ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ አትሰባሰብም ነበር። አማኞች የሚሰባሰቡት በግለሰቦች ቤት ውስጥ በመሆኑ የሰዎቹ ቁጥር ከ50 ወይም 60 አይበልጥም ነበር። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያኒቷ የኅብረት ጸሎት ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚካሄድባት እንጂ በግዙፍ ሕንጻ ውስጥ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት የሚካሄድበት ዓይነት ቤተ ክርስቲያን አልነበረችም። የሰዎቹ ቁጥር ጥቂት ስለሆነ መዝሙር ለመምረጥ፥ ቃል ለማካፈል፥ በአስተርጓሚ አማካኝነት በልሳን ለመናገር፥ ወዘተ. ብዙ ነጻነት ነበራቸው። ጳውሎስ የሚከተሉትን መመሪያዎች ሰጥቷል።

 1. አምልኮ እንደ መሪዎች ወይም ኳዬርና ሰባኪ ያሉ ጥቂት ሰዎች ሁሉንም ተግባር የሚፈጽሙበትና ሌሎች በትዝብት የሚመለከቱበት ሳይሆን ምእመናን በሙሉ የሚሳተፉበት ነው። ጳውሎስም ሁሉም ትምህርት፥ ልሳን፥ ትንቢት፥ ወዘተ በማቅረብ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዳለ አመልክቷል። ጳውሎስ ይህን ሲል ሁሉም ሰው ሁሉንም ነገር ማድረግ አለበት ማለቱ ሳይሆን ሁሉም ሰው ለመሳተፍ እንደሚችል መግለጹ ነበር።
 2. አምልኮው ሁሉ ለምእመናን በሙሉ ጠቃሚ መሆን አለበት። አስተርጓሚ ሳይኖር በልሳን መናገሩ ለሌሎች መንፈሳዊ ጥቅም የማያስገኝ በመሆኑ ተከልክሏል። ሰዎች የሚነገረውን አሳብ ተረድተው «አሜን» (እስማማለሁ) ሊሉ አይችሉም ነበር። የጉባኤ አምልኮ የሁሉም ስለሆነ፥ የሁሉም መረዳት ወሳኝ ነው። መልእክቱ በሚገባቸው ቋንቋ ሊተላለፍና ፕሮግራሙም እምነታቸውን የሚያንጹትን ነገሮች ሊያካትት ይገባል። (ይህ አንድ ሰው ለቡድኑ እንዲጸልይ በሚጠየቅበት ጊዜ ለራሱ መጸለይ ወይም በልሳን መናገሩ ትክክል እንዳልሆነ የሚያመለክት ይመስላል። ሁሉም የግለሰቡን ጸሎት ካልሰሙ ጥያቄውን ማጽደቃቸውን ለማሳየት «አሜን» ሊሉ አይችሉም። የጉባኤ አምልኮ ዓላማ የግል ጸሎት፥ ጥያቄ ወይም በረከት ሳይሆን፥ የሁሉም በአንድነት መሳተፍ ነው።)
 3. ነገሮች በሥርዓትና በአግባቡ ሊከናወኑ ይገባል። ሰዎች በራስ ወዳድነት ስጦታዎቻቸውን ለማሳየት በመፈለጋቸው ምክንያት የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በሁከት ሳትሞላ አትቀርም። ጉባኤው ብዙ ሰዎች በአንድ ጊዜ በሚናገሯቸው የልሳንና የትንቢት መልእክቶች፥ እንዲሁም በሴቶች ጫጫታ ይታወክ ነበር። ነገር ግን አምልኮ ሥርዓትን የተከተለና አግባብነት ያለው ሊሆን ይገባል። በሌላ አገላለጽ፥ አምልኮ ለሕዝቡ ባሕል በሚስማማ፥ በሚጥም፥ ሕዝቡን ደስ በሚያሰኝ መንገድ መካሄድ አለበት። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ለቤተ ክርስቲያን አምልኮ የሚያገለግሉ መመሪያዎችን ሰጥቷል።

ሀ. ሰዎች በልሳን ለመናገር ከፈለጉ ሊፈቀድላቸው ይገባል። ነገር ግን ተራ በተራ መናገር ይኖርባቸዋል። በልሳን በሚናገሩበት ጊዜ ደግሞ መልእክቱ መተርጎም አለበት። ተርጓሚ ከሌለ ዝም ብለው በልባቸው መጸለይ አለባቸው። በአንድ የአምልኮ ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ብቻ በዚሁ መንገድ መናገር ይኖርባቸዋል።

ለ. ሰዎች ትንቢት መናገር ቢፈልጉ ተፈቅዶላቸው ነበር። ተራ በተራ ትንቢት መናገር ይቻላል። ትንቢትም ሆነ ልሳን በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር እንጂ ራስን በመሳት (in a trance) ሊነገር አይገባም። መንፈስ ቅዱስ እንደ ሰይጣን ሰዎች ከአእምሯቸው ውጭ እንዲሆኑ አያደርግም። ግለሰቡ አእምሮውን ሳይስት መንፈስ ቅዱስንና እርሱ የሚናገረውን ይሰማል። ትንቢት የሚነገርበት ዓላማ ግለሰቡ የተሰማውን እንዲናገርና ለሌሎች መልእክት የማካፈል ዕድል እንዲያገኝ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝቡ ለማስተላለፍ ነው። ስለሆነም፥ እርሱ እየተናገረ ሳለ እግዚአብሔር ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት በሌላ ሰው አማካኝነት የትንቢትን ቃል ከላከ፥ የመጀመሪያው ተናጋሪ ተራ ሊለቅለት ይገባል። በመጨረሻም፥ እንደ ልሳን ሁሉ በአንድ ጉባኤ ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ብቻ ትንቢትን እንዲናገሩ ተፈቅዷል።

ከቡሉይ ኪዳን በተለየ መልኩ፥ የአዲስ ኪዳን ትንቢት እግዚአብሔር ራሱ የሚናገረውን ያህል ጠንካራ ሥልጣን ያለው አይመስልም። አንድም የአዲስ ኪዳን ነቢይ፥ «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» እያለ ሲናገር አንመለከትም። ክርስቲያኖችም ትንቢትን በሁለት መንገዶች እንዲመረምሩ ተነግሯቸዋል። በመጀመሪያ፥ ቃላቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መስማማታቸውን ለመመርመር ትንቢትን እንፈትናለን። እግዚአብሔር ሊዋሽ ስለማይችል በአንድ በኩል (በሰው ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ) የተናገረውን መልእክት አይቃረንም። ስለሆነም የተነገረው ትንቢት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ከተጻፈው ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ ዐበይት መርሆች ጋር የሚጻረር ከሆነ ትንቢቱን መቀበል አያስፈልግም። ሁለተኛ፥ ትንቢቱ ለሁሉም ሰው የሚጠቅም መሆኑን መመርመር አለብን። ለሕዝቡ ሁሉ የማያገለግልና ቤተ ክርስቲያንን የማያንጽ ከሆነ፥ ትንቢቱን መቀበል አያስፈልግም። ወይም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ብቻ ማካፈል ያሻል።

ሐ. ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዝም ሊሉ ይገባል። ይህ ምንባብ በክርስቲያኖች መካከል ብዙ ውይይቶችንና የተለያዩ አመለካከቶችን አስከትሏል። በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ያልተደገፉ የሚመስሉ ሁለት የተራራቁ አመለካከቶች አሉ። በመጀመሪያ፥ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሴት በፍጹም በጉባኤ ላይ መናገር የለባትም ይላሉ። እነዚህ ወገኖች ሴቶች ማስተማር፥ መስበክ፥ ማካፈል፥ መጸለይ፥ ወዘተ… እንደማይችሉ ይናገራሉ። ሁለተኛ፥ ሌሎች ክርስቲያኖች እነዚህ የጳውሎስ ትእዛዛት ከእኛ ጋር እንደማይዛመዱ ያስረዳሉ። እነዚህ ትእዛዛት የተሰጡት ወንዶች ሴቶችን በሚንቁበት ዘመንና የሴት የቤተ ክርስቲያን ውስጥ መናገር የተሳሳተ ወይም የዓመፅ ምልክት ተደርጎ በሚወሰድበት ባሕል ውስጥ ለነበሩት ሰዎች እንደሆነ ያስረዳሉ። ጊዜው ስለተቀየረና ዘመናዊ ባሕሎች የሴቶችን እኩልነት ስለተገነዘቡ፥ ሴቶች የወንዶችን ያህል እኩል ድርሻና ሥልጣን ይይዛሉ። ተገቢው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከት የሚውለው በእነዚህ ሁለት የተራራቁ አመለካከቶች መሀል ይመስላል።

የትኛውንም አመለካከት ብንከተል፥ ጳውሎስ ቀደም ሲል በ1ኛ ቆሮንቶስ 11፡2-16 የተናገረውን ማስታወስ ይኖርብናል። በዚህ ክፍል ጳውሎስ ሴቶች የመጸለይና ትንቢት የመናገር ፈቃድ እንዳላቸው በማሰብ፥ ይህንኑ አገልግሎት በሚሰጡበት ጊዜ ከባሕላቸው ጋር ላለመቃረን ራሳቸውን መሸፈን እንዳለባቸው ገልጾአል። በኢዩኤል 2፡28-32 የተሰጠውና በሐዋርያት ሥራ 2፡17-21 የተጠቀሰው የመንፈስ ቅዱስ የተስፋ ቃል ወንዶችን ብቻ ሳይሆን ሴቶችንም ይጨምራል። ስለሆነም፥ የአዲስ ኪዳን ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊናገሩና ሊያገለግሉ እንደሚችሉ በግልጽ ያሳያል።

ክርስቲያኖች ከሚይዟቸው የተለያዩ አተረጓጎሞች አንዳንዶቹ ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል። እንደ እግዚአብሔር ቃል ተማሪ፥ አንተና ቤተ ክርስቲያንህ ይህን ክፍል በምታዛምዱበት ሁኔታ ላይ መንፈስ ቅዱስ እንዲመራችሁ በጸሎት ጠይቁ።

አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ እግዚአብሔር የአስተዳደርና የሥልጣን ደረጃ ዎችን ስለወሰነ ሴቶች በቤትም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለባሎቻቸው እንዲገዙ ለማስረዳት መፈለጉን ይገልጻሉ። ስለሆነም፥ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከመናገር ይልቅ ያልተገነዘቧቸውን ነገሮች ወደቤታቸው ከተመለሱ በኋላ ከባሎቻቸው በመጠየቅ አክብሮታቸውን ማሳየት ያስፈልጋቸው ነበር።

ሌሎች ምሁራን ጳውሎስ የተጋፈጠው ችግር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በቂ እውቀት ያልነበራቸውና በክርስትና እምነት ከወንዶች ጋር እኩል በመሆናቸው ምክንያት ባገኙት አዲስ ነጻነት የተደሰቱት ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የፈጠሩት ሁከት እንደነበረ ይናገራሉ። እነዚህ ሴቶች ስለ ትንቢት አተረጓጎም፥ ወዘተ. እየተንጫጩ ይከራከሩ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ እነዚህ ሴቶች ቤት ውስጥ ከባሎቻቸው ጋር እንዲወያዩና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መከራከራቸውን እንዲያቆሙ አዟል ይላሉ። ነገር ግን ጳውሎስ በክርክሩ ውስጥ ስለሚሳተፉት ወንዶች ምንም ሳይናገር ለምን ሴቶችን ብቻ እንደኮነነ መረዳቱ አስቸጋሪ ነው። ሴቶች መቼ መናገር እንዳለባቸው የሚያመለክት ተጨማሪ መመሪያ ሳይሰጥ በደፈናው ዝም እንዲሉ ያዘዛቸው ለምንድን ነው?

ሌሎች ደግሞ የጳውሎስ ትልቁ ግዳጅ አማኞች ለሌሎችና ለእግዚአብሔር አክብሮት በሚያሳይ መልኩ የጸጋ ስጦታዎቻቸውን በመጠቀም ቤተ ክርስቲያንን ማነጻቸው ነው ይላሉ። ለሌሎች ሰዎች አክብሮትን ማሳየት ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ ለሴቶች ተገቢ የሆነውን ባሕላዊ ግንዛቤ መጠበቅ ነበር። የጥንቱ ባሕል ሴቶች በሕዝብ ፊት እንዳይናገሩ ስለሚከለክል፥ ሴቶች ባሕሉን በማክበር በቤተ ክርስቲያንም ይህንኑ ተግባር ከመፈጸም መታቀብ ነበረባቸው። ጳውሎስ ሴቶች በሕዝብ ፊት ሊጸልዩና ትንቢትን ሊናገሩ የሚችሉባቸው ጊዜያት እንዳሉ ቢናገርም። ጉዳዩ ባሕላዊ ጫና እንዳለው ግልጽ ነው። በአጠቃላይ መልኩ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ተገቢው ነገር የሴቶች በጉባኤ ዝም ማለት ነበር። በዘመናችን ባሕሉ ተለውጦ የሴቶች በጉባኤ ላይ መናገር ግራ መጋባትንና ነውረኝነትን የማያስከትል ከሆነ፥ ሴቶች እንዲናገሩ ሊፈቅድላቸው ይገባል።

በመጨረሻም፥ ስለ ትንቢትና ልሳን በሚናገሩ አሳቦች ላይ በማተኮር አስተያየታቸውን የሚሰጡ ወገኖች አሉ። ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ትንቢቶችን በጥንቃቄ ስለምትመዝንበት ሁኔታ እያስተማረ ነበር። ሴቶችም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትንቢት ሊናገሩ እንደሚችሉ ተፈቅዶላቸው ነበር። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ትንቢቶችን መዝና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወይም ከእግዚአብሔር መሆን አለመሆናቸውን በምትወስንበት ሂደት ውስጥ ሴቶች ዝም ማለት ነበረባቸው፡፡ ወንዶች ስለ ትንቢት እንዲወያዩ በመፍቀድ በመጽሐፍ ቅዱስ መርሆ መሠረት ለወንዶች የተሰጠውን ሥልጣን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያንጸባርቁ ነበር። ሴቶች የተወሰነ አመለካከት ስለተወሰደበት ምክንያት ጥያቄ ቢኖራቸው በቤታቸው ውስጥ ባሎቻቸውን መጠየቅ ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እውቅና በተሰጠው የማስተማር ተግባር በወንዶች ላይ እንዲሠለጥኑ አይፈልግም ነበር። የትንቢት ግምገማ አንድ ነገር ከእግዚአብሔር መሆን አለመሆኑን ለመወሰን እንደሚያስችል ሥልጣን ይታይ ነበር። እግዚአብሔርም ይህንን ኃላፊነት የሰጠው ለወንዶች ነበር። ስለሆነም፥ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነውንና ያልሆነውን የመወሰን ሥልጣንን ለሴቶች መስጠቱ ባሕላቸውን ከመጻረሩም በላይ እግዚአብሔር በፍጥረት ጊዜ የወሰነውን የሥልጣን ሥርዓት የሚያፋልስ ነበር። 24ኛ ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ሰዎች ልሳንን የሚጠቀሙበትን ሁኔታ ጳውሎስ ካስተማረው ጋር አነጻጽር። ልዩነቱና ተመሳሳይነቱ ምንድን ነው? ለ) አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች ያለ አስተርጓሚ በጉባኤ ውስጥ በልሳን ይጸልያሉ። ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ጋር የሚጣጣም ይመስልሃል? መልስህን አብራራ። ሐ) የሚጣጣም ካልሆነ፥ አምልኳችሁ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ምን ማድረግ የሚገባቸው ይመስልሃል? መ) ስለ ሴቶች በጉባኤ ላይ መናገርን ከሚያስረዱት አመለካከቶች የትኛውን ታምናለህ? ለምን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመንፈሳዊ ስጦታዎች በተለይም በልሳን የመናገር ዓላማ ምንድን ነው? (1ኛ ቆሮ. 12፡1-14፡25)

«ደካማ የምንሆንበት ምክንያት በቂ መንፈሳዊ ስጦታዎች ስለሌሉን ነው። ሁሉም ክርስቲያኖች ሊያገኙት የሚገባው እጅግ ጠቃሚ ስጦታ በልሳን መናገር ነው። መንፈስ ቅዱስ በክርስቲያኑ ውስጥ እንዳለ የሚታወቀው በልሳን ሲናገር ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሰዎች በልሳን ስለሚናገሩና ብዙ ተአምራት ስለሚፈጸሙ መነቃቃትን እንዳገኘን እናውቃለን።» ይላሉ። ለመሆኑ እንዲህ ዓይነት አባባሎች እውነት ናቸው?

መንፈሳዊ ስጦታዎች ጠቃሚዎች ናቸው። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች እንዲያውቁ የፈለገውም ለዚህ ነው (1ኛ ቆሮ. 12፡1)። ነገር ግን መንፈሳዊ ስጦታዎች አንድ ግለሰብ ወይም ቤተ ክርስቲያን በሳል መሆናቸውን አያሳዩም። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ምንም የጸጋ ስጦታ እንዳልጎዳላቸው ቢናገርም፥ መንፈሳዊ ብስለት እንዳልነበራቸው ገልጾአል (1ኛ ቆሮ. 3፡1-4)። ክፍፍል፥ ቅንዓትና ሌሎችም ኃጢአቶች ቤተ ክርስቲያኒቱን አጨናንቀው ነበር። እንዲያውም ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች ይህን ረዥም ትምህርት ያቀረበው የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ስጦታዎች ላይ በነበሯቸው የተሳሳቱ ግዛቤዎች ሳቢያ ይከፋፈሉ ስለነበረ ነው። የተቀረውን የአዲስ ኪዳን ክፍል በጥንቃቄ ብንመረምር፥ መንፈሳዊ ስጦታዎች በሌሎች ጥቂት ስፍራዎች ብቻ እንደተዘረዘሩ እንረዳለን (ሮሜ 12፡4-7፤ ኤፌ. 4፡11-13፤ 1ኛ ጴጥ. 4፡10-11)። ይህም መንፈሳዊ ስጦታዎች የአዲስ ኪዳን ቀዳሚ ትኩረቶች እንዳልሆኑ ያስረዳናል። በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ ውስጥ በአጽንኦት የተገለጸው የመንፈስ ፍሬ ነው (ገላ. 5፡22-23)። ይህም ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ እንድነት፥ ተስፋ፥ ትዕግሥት፥ የመሳሰሉት የሚገኙበት ነው። ይህም እውነተኛ መንፈሳዊነት በቀዳሚነት ራሱን የሚገልጸው በመንፈሳዊ ስጦታዎች ሳይሆን በመንፈሳዊ ባሕርያት እንደሆነ ያሳያል።

የውይይት ጥያቄ፡- አንዳንድ ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ መንፈሳዊ መነቃቃት እንዳለ ይናገራሉ። አስደሳች አምልኮ፥ የልሳን ስጦታና አስደናቂ ተአምራት ከወትሮው በበለጠ እንደሚታዩ ያስረዳሉ። ሀ) ይህ ሰዎች ከበፊት ይልቅ መንፈሳዊ ብስለትን እንደተላበሱ የሚያሳይ ይመስልሃል? መልስህን አብራራ። ለ) የመንፈስ ፍሬ (ገላ. 5፡22-23ን አንብብ።) ከበፊት የበለጠ የሚታይ ይመስልሃል ? መልስህን አብራራ።

የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ 12ን አንብብ። ሀ) ጳውሎስ በዚህ ክፍል ያተኮረባቸውን የመንፈሳዊ ስጦታዎች መርሆዎች ዘርዝሩ። ለ) ከእነዚህ መርሆዎች ዛሬ አንዳንድ ሰዎች ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች ከሚያስቡት እሳብ ጋር የሚጋጩት የትኞቹ ናቸው?

ችግሩ፡- የቆሮንቶስ አማኞች በአንዳንድ የጸጋ ስጦታዎች፥ በተለይም በልሳን አጠቃቀም ላይ በአሳብ የተከፋፈሉ ይመስላል። አንዳንድ ክርስቲያኖች በልሳን መናገር እጅግ በጣም ጠቃሚ ስጦታ ነው ብለው አሰቡ። እንዳንድ ክርስቲያኖች፥ «እውነተኛ ሰዎች ሁሉ በልሳን ይናገራሉ። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ሰዎች በልሳን መናገራቸው የሌሎችን አምልኮ ቢረብሽም እንኳ የተሻለ ነው» ይሉ ነበር። እነዚህ ሰዎች ጳውሎስ ክርስቲያኖች ሁሉ በልሳን እንዲናገሩ ያበረታታላቸው ዘንድ ፈለጉ። ሌሎች ክርስቲያኖች ደግሞ ብዙ ሕዝብ በሚያመልክበት ስፍራ በልሳን መናገሩ አስፈላጊ እንዳልሆነ በመግለጽ እጥብቀው ተቃወሙ። በልሳን የሚናገሩ ሰዎች ጉባኤውን ከሚያውኩ በቀር ምንም ጥቅም እንደሌለው አስረዱ። ስለሆነም፥ ጳውሎስ በልሳን የሚናገሩትን ሰዎች እንዲከለክል ፈለጉ። «የመንፈሳዊ ስጦታዎች ዓላማ ምንድን ነው? ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት አምልኮ ውስጥ (በተለይ ልሳንን) እንዴት ልንጠቀም ይገባል?» ሲሉ ጠየቁት። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በሰጠው ምላሽ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች ብቻ ሳይሆን፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው ፍቅር፥ አንድነትና መተሳሰብ ጠቃሚ ትምህርት ሰጥቷል።

መፍትሔው፡- ምንም እንኳ ጳውሎስ ብዙ ሕዝብ በሚገኝበት አምልኮ ውስጥ ልሳንን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ዝርዝር መመሪያዎችን ባይሰጥም (1ኛ ቆሮ. 14)፥ መንፈሳዊ ስጦታዎችን መጠቀም ስለሚያስፈልግባቸው ምክንያቶችና ስጦታዎቹን በምንጠቀምበት ጊዜ ሊኖረን ስለሚገቡ አመለካከቶች አጽንኦት ሰጥቶ አብራርቷል። ቀጣዩ ጳውሎስ የሰጠው ትምህርት ጭማቂ ነው።

ሀ. በልሳን መናገር የአንድን ሰው መንፈሳዊነት አያረጋግጥም (1ኛ ቆሮ. 12፡1-3)። በዚህ ክፍል የጳውሎስን ምክንያት መረዳቱ አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ጳውሎስ በልሳን ከሚናገሩ ሰዎች አንዳንዶቹ አረማውያን በነበሩ ጊዜ (በተለይ ጠንቋዮቹ) በልሳን ይናገሩ እንደነበረ እያስታወሳቸው ይሆናል። ስለሆነም በልሳን መናገር በራሱ የመንፈሳዊነት ምልክት ሊሆን አይችልም። ክርስቲያን የሆኑትም ያልሆኑትም በልሳን ሊናገሩ ይችላሉ። እንግዲህ፥ የአንድ ሰው ልሳን ከእግዚአብሔር ወይም ከሰይጣን መሆኑን እንዴት እናውቃለን? ጳውሎስ የክርስቶስን ጌትነት በልቡ የሚያምንና በሕይወቱ የሚያረጋግጥ ማንኛውም ክርስቲያን በሰይጣን ቁጥጥር ሊናገር እንደማይችል ገልጾአል።

ይህን መፈተኛ ለመረዳት፥ የጳውሎስን ዘመን ባሕል መረዳት አለብን። ዛሬ ሰዎች ስለ ትርጉሙ ብዙም ሳያውቁ መስቀልን የውበት ትምህርት አድርገው ይጠቀማሉ። ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች ሳይቀሩ ኢየሱስ ጌታ ነው ሊሉ ይችላሉ። በጳውሎስ ዘመን ግን አንድ አይሁዳዊ የሆነ ሰው ኢየሱስ የብሉይ ኪዳን አምላክ የሆነው ያህዌ ነው ቢል፥ አይሁዶች ለፈጸመው የስድብ ኃጢአት በድንጋይ ወግረው ይገድሉት ነበር። አንድ አሕዛብ ኢየሱስ ጌታ ነው ቢል፥ ማኅበረሰቡ የተሰቀለው ኢየሱስ ጌታ ነው በማለቱ ከማኅበራቸው ያስወጡት ነበር። ዛሬ ለሙስሊሞች በክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነት ማመን የሚከብደውን ያህል ያን ጊዜ ለሰዎች በክርስቶስ ማመኑ አስቸጋሪ ነበር። ስለሆነም፥ በክርስቶስ ላይ ላላቸው እምነት ለመሞት የሚመርጡ ሰዎች እግዚአብሔር በልባቸው ውስጥ ለውጥ ያመጣባቸው ብቻ መሆናቸውን ገልጾአል። እንደነዚህ ዓይነት አማኞች በልሳን በሚናገሩበት ጊዜ የስጦታው ምንጭ መንፈስ ቅዱስ ለመሆኑ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ጳውሎስ አጽንኦት የሰጠው በሚናገራቸው ቃላት ላይ ሳይሆን፥ ግለሰቡ በሕይወቱ ክፍሎች ሁሉ በክርስቶስ አገዛዝ ሥር ስለመኖሩ ነው። ግለሰቡ ለክርስቶስ የማይገዛና ፍቅርን የማያሳይ ከሆነ፥ በልሳን የመናገርን ኃይል የሰጠው ሰይጣን ሊሆን እንደሚችል የመጠራጠር መብት አለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አኗኗራቸው ክርስቶስ የሕይወታቸው ጌታ መሆኑን የሚመሰክርላቸው ክርስቲያኖች በልሳን ሲናገሩ ሰምተሃል? ለክርስቶስ እንደሚገዙ በምን ታውቃለህ? የዚህ ዓይነቱ ልሳን ምንጭ ማን ነው? ለ) ለክርስቶስ ተገዝተውና ታዘው እንደሚኖሩ ሕይወታቸው የማይመሰክርላቸው ክርስቲያኖች በልሳን ሲናገሩ ሰምተሃል? ለክርስቶስ አለመገዛታቸውን እንዴት ታረጋግጣለህ? የልሳናቸው ምንጭ ማን ነው?

ለ. ከአንዱ አሀዱ–ሥሉስ አምላክ የሚመጡ የተለያዩ ስጦታዎች (አገልግሎቶችና አሠራሮችም ተብለዋል) አሉ (1ኛ ቆሮ. 12፡4-6)። ጳውሎስ እንዴት በሁለት ቃላቶች ላይ እንደሚያተኩር አጢን። ጳውሎስ «ልዩ ልዩ» በሚለው ሐረግ ላይ በማተኮር የተለያዩ ስጦታዎች መኖራቸውን ያሳያል። ይህም እንደ ልሳን ካለው አንድ ስጦታ ይልቅ እግዚአብሔር በሚሰጣቸው ስጦታዎች ሁሉ ላይ አጽንኦት መስጠት እንዳለብን ያመለክታል። እንዲሁም፥ እነዚህ የተለያዩ ስጦታዎች ከእግዚአብሔር (ከአንድ ምንጭ) እንደሚመጡ ለማሳየት «አንድ» በሚል ቃል ላይ ትኩረት አድርጓል። ስለሆነም፤ በልሳን የመናገር ስጦታ ያለው ሰው ሌላ ዓይነት ስጦታ ካለው ሰው ይልቅ መንፈስ ቅዱስ በበለጠ ሁኔታ ይኖርበታል ማለት አይደለም።

ሐ. እያንዳንዱ ክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ለጋራ ጥቅም ይሰጠዋል። ይህም በክርስቲያኑ ሕይወት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ያሳያል (1ኛ ቆሮ. 12፡7)። የእያንዳንዱ መንፈሳዊ ስጦታ ዓላማ የጋራ ጥቅም ነው። ስጦታው የሚሰጠው ለግለሰቡ የግል ጥቅም ሳይሆን፥ ለቤተ ክርስቲያን ነው። መንፈሳዊ ስጦታ መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዱ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲያገለግል የሚሰጠው ችሎታ ነው።

መ. መንፈስ ቅዱስ ለተለያዩ ሰዎች የተለያዩ ስጦታዎችን ይሰጣል (1ኛ ቆሮ. 12፡8-10)። አንዳንድ ክርስቲያኖች የተወሰኑ መንፈሳዊ ስጦታዎች ብቻ እንዳሉ ቢያስቡም፥ በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ የተገለጹት የመንፈሳዊ ስጦታዎች ዝርዝሮች አንድ ዓይነት አይደሉም። ይህም መንፈስ ቅዱስ ሊሰጥ የሚችላቸው የተለያዩ ስጦታዎች እንዳሉ ያሳያል። መንፈስ ቅዱስ በልሳን መናገርን ለሁሉም አማኞች አይሰጥም። ይህ አንድ ስጦታ ብቻ ሲሆን፥ መንፈስ ቅዱስ ለተለያዩ ሰዎች የሚሰጣቸው የተለያዩ ስጦታዎች አሉ።

ሠ. ማን የትኛውን ስጦታ እንደሚቀበል የሚወስነው መንፈስ ቅዱስ ነው (1ኛ ቆሮ. 12፡1)። መንፈሳዊ ስጦታን የሚሰጠን መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ፥ ሌሎች ከእኛ ይበልጥ አስደናቂ ስጦታ የተቀበሉ በሚመስልበት ጊዜ የመቅናት መብት የለንም። እንደ እኛ አስደናቂ የሆኑ ስጦታዎች የሌላቸውንም ቁልቁል ልንመለከትና ልንንቃቸው አይገባም። ስጦታውን የሚወስነው ተቀባዩ ሳይሆን፥ እንደ ዓላማውና እንደ ምርጫው የሚሰጠው መንፈስ ቅዱስ ነው።

ረ. ሰውነት አብረው ከሚሠሩ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች እንደተዋቀረ ሁሉ፥ ቤተ ክርስቲያንም ለክርስቶስ አካል ጥቅም በሚሠሩ የተለያዩ ስጦታዎች ባሏቸው ሰዎች ተዋቅራለች (1ኛ ቆሮ. 12፡12-26)። ይህ አሳብ ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶችን ያስተምራል። በመጀመሪያ፥ እያንዳንዱ ክርስቲያን ስጦታውን በሚገባ ካልተጠቀመ ቤተ ክርስቲያን ትዳከማለች። ሁለተኛ፥ እያንዳንዱ መንፈሳዊ ስጦታ ዋጋ ሊሰጠው እንደሚገባና አንዱ መንፈሳዊ ስጦታ ከሌላው እንደሚበልጥ ሁሉ ከፍ ከፍ መደረግ እንደሌለበት ያሳያል። ሦስተኛ፥ እጅግ አስደናቂ ያልሆኑ ወይም ጎልተው የማይታዩ ስጦታዎች መከበር እንዳለባቸው ያሳያል።

ሰ. የበለጠ ጠቀሜታ ያላቸው አንዳንድ መንፈሳዊ ስጦታዎች አሉ። ስለሆነም፥ ሐዋርያት፥ ነቢያት፥ አስተማሪዎች በቀዳሚነት ተዘርዝረዋል (1ኛ ቆር. 12፡27-28፥ 31)። ጳውሎስ በልሳን መናገር ከወሳኝ መንፈሳዊ ስጦታዎች አንዱ እንዳልሆነ ለማሳየት በዝርዝሩ ውስጥ ከወደ መጨረሻው አካባቢ ጠቅሶታል።

ሸ. ሁሉም ስጦታዎች ያሉት ክርስቲያን የለም (1ኛ ቆሮ. 12፡29-30)። ጳውሎስ ሰዎች ሁሉ ሐዋርያት ወይም ነቢያት እንዳልሆኑ ሁሉ፥ ሁሉም በልሳን እንደማይናገሩ ገልጾአል። የትኞቹም ስጦታዎች ለሁሉም ሰው አይሰጡም፤ ሁሉም ስጦታዎች ያሉትም ክርስቲያን የለም።

የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 13ን አንብብ። ሀ) ጳውሎስ ይህን ከሁሉም የሚሻል መንገድ ያለው ለምን ይመስልሃል? ለ) በልሳን እንደ መናገር ባሉት ጉዳዮች በአሳብ በምንለያይበት ጊዜ ጳውሎስ በዚህ ስፍራ የገለጻቸው መርሆዎች እንዴት ሊመሩን ይገባል?

ቀ. ከመንፈሳዊ ስጦታዎች «እጅግ የሚሻለው መንገድ» እርስ በርሳችን መዋደዳችን ነው (1ኛ ቆሮ. 12፡31-13፡13)። እንደ ልሳን፥ ትንቢት፥ እውቀት ወይም ተአምር የመሥራት እምነት ያሉ እጅግ አስደናቂ ስጦታዎችን እንኳ ለሌሎች የማሰብንና የማፍቀርን መርህ ሳንከተል በተሳሳተ አመለካከት ከሥራ ላይ ልናውላቸው እንችላለን። እነዚህን ስጦታዎች በራስ ወዳድነት፥ ለግል ክብር ወይም በሚያውክ መንገድ በምንጠቀምበት ጊዜ፥ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡት ጥቅም ካለመኖሩም በላይ የአጥፊነትን ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።

የፍቅር መንገድ ከሁሉም የሚሻለው ለምንድን ነው? ጳውሎስ ፍቅርን የገለጸው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚካሄዱ አለመስማማቶች አንጻር ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተለያዩ ክርስቲያኖች ስለ ልሳን የተለያዩ አመለካከቶችን ይዘው ሳሉ አንድነትን ልንጠብቅ የምንችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ ለዚህ ችግር መፍትሔው ፍቅር እንደሆነ አስረድቷል። የተለያዩ አመለካከቶች በሚኖሩበት ጊዜ አንዱ ወገን ሌላውን መታገሥ አለበት። አንደኛው ወገን ከሌላው የበለጠ መንፈሳዊ መሆኑን ለማሳየት ሊሞክር፥ ሊሳደብና አመለካከቱን በግድ ለመጫን ሊጥር አይገባም። ነገር ግን እርስ በርሳቸው ለመረዳዳት፥ ለመከባበርና አንድነትን ለመጠበቅ በልዩነቶቻቸው ላይ በእውነተኝነት ሊወያዩ ይገባል።

ፍቅር ዘላቂ ስለሆነ ከሁሉም ይልቃል። ለዘላለም የሚዘልቀው ፍቅር ብቻ ነው። ልሳን አንድ ቀን ያበቃል። ሁሉንም ነገር ልናውቅ ስለማንችል፥ ትንቢትና እውቀት ሁልጊዜም ከፊል ብቻ ናቸው። ከመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ የማንረዳቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ስለሆነም፥ የራሳቸውን መንገድ የሚሹትን ሕፃናት ሳንመስል ሁሉንም ነገር ለማወቅ አለመቻላችንን በትሕትና ተቀብለን ለሌሎች ፍቅርና አቀባበልን ልናሳይ ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የተከሰተውን የአሳብ እለመግባባት በምሳሌነት በመውሰድ፥ በ1ኛ ቆሮንቶስ 13 የተገለጸው ዓይነት ፍቅር ለችግሩ መፍትሔ በመስጠት ሰዎች እንዳይጎዱና የክርስቶስም ስም እንዳይሰደብ ሊያደርግ የሚችልበትን መንገድ አብራራ።

የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 14ን አንብብ። ሀ) ሦስት ዓምዶች ያሉት ሠንጠረዥ ሥራ። የመጀመሪያውን ዓምድ «በልሳን መናገር» ብለህ ሰይም። ሁለተኛውን «ትንቢትን መናገር» ብለህ ሰይምና በሦስተኛው ዓምድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ዘርዝር።

ይህን ክፍል በምታነብበት ጊዜ፥ ጳውሎስ ስለ ልሳን የገለጸውን በመጀመሪያው ዓምድ፥ ስለ ትንቢት የገለጻውን በሁለተኛው ዓምድ፥ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በሦስተኛው ዓምድ ጻፍ። ለ) ጳውሎስ ትንቢትን መናገር ከልሳን እንደሚሻል በመግለጽ ያቀረባቸውን ነጥቦች ጠቅለል አድርገህ ጻፍ። ሐ) ከዚህ ክፍል የምንመለከታቸው የጉባዔ አምልኮ አንዳንድ ጠቃሚ መርሆዎች ምን ምንድን ናቸው?

በ. ክርስቲያኖች የሚበልጡትን የጸጋ ስጦታዎች እንዲፈልጉ ተበረታተዋል (1ኛ ቆሮ. 14፡1-25)። አብዛኞቹ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በልሳን የመናገር ጉጉት ነበራቸው። ይህ የመንፈሳዊ ብስለትና በመንፈስ ቅዱስ የመሞላት ትልቅ ምልክት ነው ብለው ያስቡ ነበር። መንፈስ ቅዱስ በበዓለ ኀምሳ ዕለት ራሱን የገለጻው በዚህ መንገድ አይደለምን? የሚል ክርክር አንሥተው ነበር። ጳውሎስ ግን ልሳን መንፈሳዊ ስጦታ መሆኑን ሳይክድ ከአንዳንድ ስጦታዎች ጋር ሲነጻጸር ልሳን አነስተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጾአል።

የሚበልጠው ስጦታ የትኛው ነው? መንፈሳዊ ስጦታዎች የተሰጡት ጠቅላላዪቱን ቤተ ክርስቲያን ለመገንባት እንጂ ለግል ጥቅም ስላልሆነ፥ የሚበልጠው መንፈሳዊ ስጦታ ጠቅላላዪቱ ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ብስለት እንድታድግና ምሉዕ እንድትሆን የሚረዳት ነው። ስለሆነም፥ የሚበልጠው መንፈሳዊ ስጦታ ቤተ ክርስቲያንን ለክርስቶስ በምታቀርበው አምልኮ፥ ክርስቶስን በመምሰል፥ ክርስቲያኖችንና ዓለምን በማገልገሉ ረገድ የተሟላ ተግባር እንድታከናውን የሚረዳትና ዳሩ ግን አሁን የሚጎድላት ስጦታ ነው። በመሆኑም፥ ቤተ ክርስቲያን ጥሩ አስተማሪ እያላት ወንጌላዊ ከሌላት፥ የሚበልጠው ስጦታ የወንጌል ስርጭት ይሆናል። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን አስተማሪ ሳይኖራት ወንጌላዊ ካላት የሚበልጠው ስጦታ ማስተማር ይሆናል። ጳውሎስ ትንቢት ከሁሉም የሚበልጥ ስጦታ ነው ማለቱ አይደለም። ቀደም ብሎ ትንቢት ከሁሉም እንደሚበልጥ ገልጾአል።

ጳውሎስ የተወሰኑ ስጦታዎች ከልሳን በላይ ለቤተ ክርስቲያን አስፈላጊዎች መሆናቸውን ለማብራራት ትንቢትንና ልሳንን አነጻጽሯል። አብዛኞቻችን ትንቢት የወደፊቱን ክስተት መተንበይ ነው ብለን እናስባለን። የትንቢት ስጦታ መሠረታዊ አሳብ ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚስማማ መልእክት ከእግዚአብሔር ተቀብሎ ለቤተ ክርስቲያን ማስተማርን ያሳያል። አንዳንድ ጊዜ መልእክቱ ወደፊት ከሚከሰቱ ነገሮች ጋር ሊዛመድ ይችላል። ብዙውን ጊዜ ግን መልእክቱ በወቅቱ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች የሚያገለግል ነው።

የጳውሎስ ትኩረት ስጦታዎችን ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው የአምልኮ ስፍራዎች የመጠቀሙ ሁኔታ እንደሆነ ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። ሕዝባዊ አምልኮ መንፈሳዊነታችንን የምናሳይበት ወይም በግላዊ በረከቶቻችን ላይ የምናተኩርበት አይደለም። ሕዝባዊ አምልኮ ምእመናን በጋራ የሚያካሂዱት ሲሆን፥ ዓላማውም የሁሉም መታነጽና መካፈል ነው። ጳውሎስ ስለ ግል አምልኮ አላነሣም። ጳውሎስ በዚህ ክፍል ልሳንን ከትንቢት ጋር እንደሚከተለው ያነጻጽረዋል።

 1. አንድ ሰው በልሳን በሚናገርበት ጊዜ ለሰው ሳይሆን ለእግዚአብሔር ይናገራል። አንድ ሰው ትንቢት በሚናገርበት ጊዜ የእግዚአብሔርን መልእክት ለሰዎች ይናገራል።
 2. አንድ ሰው በልሳን በሚናገርበት ጊዜ አሳቡን የሚረዳው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ለሌሎች ሰዎች ግን ልሳን ካልተቃኘ የሙዚቃ መሣሪያ እንደሚወጣ ድምፅ ሁሉ የማይታወቅ ነው። አንድ ሰው ትንቢትን በሚናገርበት ጊዜ ግን ሰዎች የሚረዱትን ቋንቋ ይጠቀማል።
 3. አንድ ሰው በማይተረጎም ልሳን በሚናገርበት ጊዜ እርሱም ሆነ ጉባኤው የሚነገረውን ቃል ስለማይሰማ ሊታነጽ አይችልም። ሊባረክም ሆነ ሊማር አይችልም። ነገር ግን ትንቢትን በሚናገርበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ሌሎችን እንዲያበረታታና እንዲያጽናና ይጠቀምበታል።
 4. አንድ ሰው በልሳን በሚናገርበት ጊዜ በመንፈሱ ከእግዚአብሔር ጋር በመገናኘቱ ምክንያት ሊታነጽና ሊባረክ የሚችለው ራሱ ብቻ ነው። በትንቢት ሲናገር ግን ራሱም ጉባኤውም ይታነጻል።
 5. በልሳን መናገር መልካምና የተፈቀደ ጉዳይ ቢሆን ኖሮ እንኳን፥ ብዙ ሰዎችን ስለሚጠቅም ትንቢትን መናገሩ የተሻለ ነው።
 6. በልሳን መናገር ለአሕዛብ ምልክት ሲሆን፥ ትንቢትን መናገር ግን ለአማኞች ምልክት ነው። ይህን አሳብ መረዳቱ አስቸጋሪ ነው። ጳውሎስ እግዚአብሔር በአይሁዶች ላይ በመፍረድ ወደ ባቢሎንና አሦር እንደሚሰዳቸው የተናገረበትን የራእይ 28፡11-12 ክፍል ይጠቅሳል። አይሁዶች ተማርከው በሚሄዱበት ጊዜ ከዚህ በፊት የማያውቁትን የአሦርና የባቢሎንን ቋንቋዎች ይሰሙ ዘንድ ተገድደው ነበር። ነገር ግን ባዕድ ቋንቋዎችን መስማቱ እስራኤላውያን ከኃጢአታቸው ተጸጽተው ንስሐ እንዲገቡ አላደረጋቸውም ነበር። ይሁንና ይህ በሌሎች ቋንቋዎች የሚናገሩ አሕዛብ ስለ እግዚአብሔር እንዲሰሙ አድርጓል። በሐዋርያት ሥራ 2 ሐዋርያት በልሳን በተናገሩ ጊዜም ተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጽሟል። ሐዋርያት በልሳን የተናገሩት በቀዳሚነት ለሰሚዎቹ ጥቅም ይመስላል። ይህ ከዓለም ዙሪያ ለተሰባሰቡ የማያምኑ ሰዎች ወንጌሉ ለእነርሱ መምጣቱን የሚያሳይ ምልክት ነበር። ሌሎች ምሁራን ጳውሎስ ይህን ሲል በብሉይ ኪዳን ባዕድ ቋንቋዎችን መስማት ለአይሁዶች የፍርድ ምልክት እንደሆነ ሁሉ፥ ዛሬም የማያምኑ ሰዎች የማይረዱትን ልሳን በሚሰሙበት ጊዜ አምነው ካልዳኑ ፍርድ እንደሚጠብቃቸው እየተገነዘቡ መሆኑን ማመልከቱ እንደሆነ ይናገራሉ።

ትንቢት ግን አማኞችን በእግዚአብሔር ቃል ለማነጽ ያገለግላል። ነገር ግን የማያምኑ ሰዎች እንኳ ትንቢትን በሚሰሙበት ጊዜ የእግዚአብሔርን ሥራ በመመልከት ይወቀሳሉ። ጳውሎስ በጉባኤ ላይ በልሳን ካልተናገርን የሚሉ ሰዎች የሕፃናትን ዓይነት ተግባር እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጾአል። እነዚህ ሰዎች በቀዳሚነት ለራሳቸውና ለራሳቸው መንፈሳዊ በረከት ትኩረት በመስጠታቸው የተሳሳተ አነሣሽ ምክንያት ነበራቸው ወይም ደግሞ ስጦታቸውን ለማሳየት ይፈልጉ ነበር። ለሌሎች ጥቅምና ዕድገት አስተዋጽኦ ለማድረግ ወይም ለማያምኑ ሰዎች መልካም ምስክርነትን ለመስጠት ፍላጎት አልነበራቸውም።

 1. በልሳን መናገር ንግግሩን በማይሰሙ ክርስቲያኖችና እንደ ሰከሩ ወይም እንዳበዱ በሚያስቡ ዓለማውያን ጭምር ግራ መጋባትን ያስከትላል። ትንቢትን መናገር ለክርስቲያኖች ጠቃሚ ትምህርትን ሲሰጥ፥ ዓለማውያንን ወደ ንስሐ ይመራል።

የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) ብዙ ሰዎች በልሳን መናገር የሚፈልጉት ለምንድን ነው? ሰዎች በልሳን የሚናገሩባቸው መልካምና መልካም ያልሆኑ አነሣሽ ምክንያቶች ምን ምንድን ናቸው? ለ) በልሳን ላይ የሚያተኩሩ ሰዎች እንደ አስተዳደር፥ ልግስና፡ አገልግሎት፥ ትምህርት፥ ላሉት ለሌሎች የጸጋ ስጦታዎች አጽንኦት የማይሰጡት ለምንድን ነው? ሐ) ሰዎች በአስደናቂ የጸጋ ስጦታዎች ላይ እንዲያተኩሩ የሚያደርጋቸው አነሣሽ ምክንያት ምን ይመስልሃል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

በቅዱስ ቁርባን ጊዜ ትክክለኛው ባሕርይ ምንድን ነው? (1ኛ ቆሮ. 11፡17-34)።

«አሁን የጌታን እራት እንወስዳለን» ሲባል ጉባኤው በዝምታ ይዋጣል። ንግግርና ጭውውት አብቅቶ ጉባኤው ያረምማል። ይህ እጅግ የተቀደሰ የአምልኮ ጊዜ ነው። ብዙ አብያተ ክርስቲያናት የተጠመቁ አባሎቻቸው ብቻ ቅዱስ ቁርባንን እንዲወስዱ ያደርጋሉ። ንስሐ ስላልገቡባቸው ኃጢአቶች ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል። ዛሬ ስለ ቅዱስ ቁርባን በጥብቅ የሚያሳስበን ነገር አለ። ይኽውም የጌታን እራት አለአግባብ ልንጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? የሚል ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የጌታ እራት ለአንተ ልዩ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) 1ኛ ቆሮ. 11፡17-34 አንብብ። በጌታ እራት ጊዜ የተከሰተውንና ጳውሎስ የተቃወመውን ችግር ግለጽ። ሐ) ስለ ቅዱስ ቁርባን ሊያስተካክል የፈለገው የተሳሳተ አመለካከት ምን ነበር? መ) ጳውሎስ ስለ ጌታ እራት የሰጠውና ዛሬ ከእኛ ጋር የሚዛመደውን መመሪያ ዘርዝር።

ችግሩ፡- የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የተቸገሩበት ሁለተኛው የአምልኮ ክፍል በጌታ እራት ጊዜ ትክክለኛው ባሕርይ ምን ዓይነት ነው? የሚል ነበር፡፡ ችግሩን ለመረዳት እንችል ዘንድ የቀድሞዪቱ ቤተ ክርስቲያን የጌታን እራት ስለምትወስድበት ሁኔታ ማወቅ አለብን። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የጌታን እራት የምትወስድበት ሁኔታ በተለያዩ መንገዶች ከዛሬው ዘመን የተለየ ነበር። በመጀመሪያ፥ ክርስቲያኖች ሁሉ በጌታ እራት ተካፋይ ነበሩ። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ሰዎችን ወዲያውኑ እንዳመኑ ታጠምቃቸው ስለነበር፥ አንድ ሰው በሚያምንበትና የጌታን እራት በሚወስድበት መካከል ብዙ የጊዜ ርቀት አልነበረም። በአባሎችና እንዲሁ ለመካፈል በመጡት ሰዎች መካከልም ልዩነት አልነበረም። ሁለተኛ፥ ዛሬ በአብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት በወር አንድ ጊዜ እንደሚሰጠው ሳይሆን፥ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የጌታ እራት በየአምልኮ ፕሮግራሙ ላይ ይደረግ ነበር። ሦስተኛ፥ የጌታ እራት ሰዎች የዳቦ ቁራሽና አነስተኛ መጠጥ የሚጠጡበት ሥርዓት ብቻ አልነበረም። ነገር ግን ምእመናኑ በአምልኮው ሰዓት መጨረሻ ላይ አብረው የሚበሉት ምግብ ነበር። የቅዱስ ቁርባን ዳቦና መጠጥ የሚቀርበው ከምግቡ በኋላ ነበር።

በቆሮንቶስ እያንዳንዱ ቤተሰብ ምግቡን አምጥቶ በጋራ ይመገብ የነበረ ይመስላል። ምእመናኑ ያመጡትን ምግብ አብረው ከበሉ በኋላ የጌታን እራት ሥርዓት ያካሄዳሉ። ነገር ግን ሰይጣን ይህን መልካም ልማድ ወደ ራስ ወዳድነት ተግባር ለወጠው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሀብታምና ድሀ ክርስቲያኖች ነበሩ። ሀብታም ክርስቲያኖች ብዙ ጥሩ ጥሩ ምግቦች (እንደ እንጀራና ወጥ ያለ) ይዘው ሲመጡ፥ ድሆቹ ግን ምንም ወይም ደከም ያለ (እንደ ንፍሮ ዓይነት) ምግብ ያመጡ ነበር። ሀብታም ክርስቲያኖች ጥሩ ምግባቸውን በልተውና ወይናቸውን ጠጥተው ሲሰክሩ፥ ድሆቹ ጥሩ ምግብ ለመብላት አልቻሉም ነበር። ድሆቹ ሀብታሞቹ የሚበሉትን እየጓጉ ከመመልከት ያለፈ ሚና አልነበራቸውም። ወደ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ምግብ ይዘው ሊመጡ ስለማይችሉ ዝቅተኛነት ይሰማቸው ነበር። ስለሆነም፥ የጌታ እራት የፍቅርና የአንድነት መዘከሪያ ከመሆን ይልቅ የመከፋፈልና የራስ ወዳድነት መገለጫ ሆኖ ተገኘ። ጳውሎስ ክፍፍልና ራስ ወዳድነት እያሉ የጌታን እራት በአግባቡ ማካሄድ እንደማይቻል አመልክቷል። ጳውሎስ በዚህ ክፍል የተቃወመውም ይህንኑ ክፍፍልና ራስ ወዳድነትን ነው።

መርሁ፡- እግዚአብሔር የሚቀበለው አምልኮና የጌታ እራት በአንድነት፥ በፍቅርና ለሌሎች በማሰብ ሊካሄድ ይገባል። ራስ ወዳድነትና ከፍፍል ካሉ የአምልኮ፥ የዝማሬ፥ የአሥራት፥ የስብከትና የጌታ እራት ሥርዓት ማካሄዱ ለእኛም ሆነ ለሌሎች የሚያበረክተው ፋይዳ አይኖርም።

ትእዛዛት፡

 1. ጳውሎስ መፍትሔ መስጠት የጀመረው ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ስለ ቅዱስ ቁርባን ዓለማ በማስታወስ ነው። ትኩረት ሊሰጥ የሚገባው በሚበሉት ምግብ ላይ ሳይሆን፥ ስለ እነርሱ የሞተውን ክርስቶስን በማስታወሱ ላይ ነበር። ስለሆነም ከራባቸው በቤታቸው እንዲበሉና ሰይጣን የኢኮኖሚ ልዩነታቸውን ለማጉላት የሚጠቀምበትን ብዙ ምግብ ይዞ የመምጣት ተግባራቸውን እንዲያቆሙ መክሯቸዋል።
 2. የቅዱስ ቁርባን ዓላማ ሰዎች ክርስቶስ ስለ እኛ በመስቀል ላይ መሞቱን እንዲያስታውሱ ማገዝ ነው፡፡ ክርስቶስ ብዙውን ጊዜ በተለያዩ ነገሮች ስለምንጣደፍ ይህ የእምነታችን መሠረታዊ እውነት እንደሚዘነጋ ያውቅ ነበር። በመጀመሪያ፥ የጌታ እራት ከኃጢአት መዳናችንን፥ መንፈስ ቅዱስ መቀበላችንን፥ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን የዘላለም ሕይወት ማግኘታችንን ጨምሮ፥ ደስ የምንሰኝባቸውን በረከቶች ሁሉ እንድናስታውስ ይረዳናል። እነዚህ በረከቶች ሁሉ የተገኙት ክርስቶስ ለኃጢአታችን በመሞቱ ምክንያት ነው። ሁለተኛ፥ የጌታ እራት ክርስቲያኑ ማኅበረሰብ እምነቱና ተስፋው በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት እንዳረፈ የሚመሰክርበት ነው።
 3. በአማኞች ማኅበረሰብ የጌታ እራት በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊወስድ ይገባል። በግለሰብም ሆነ በአማኞች አካል ደረጃ ልባችንን በመመርመር ኃጢአታችንን ልንናዘዝ ይገባል። በመካከላችን ክፍፍልና ራስ ወዳድነት፥ እንዲሁም ሌሎች ያልተናዘዝናቸው ኃጢአቶች እያሉ የጌታን እራት መውሰድ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ላይ ማላገጥ ይሆናል። ክርስቶስ የሞተው ለኃጢአታችን ስለሆነ ንስሐ ሳንገባ የጌታ እራት የምንወስድ ከሆነ፥ ክርስቶስ ለኃጢአታችን እጅግ ተሠቃይቶ በደሙ እኛን ስለ መግዛቱ ግድ የለንም ማለት ነው። አሁንም በዓመፀኛነታችን እንቀጥላለን ማለት ነው። ጳውሎስ አንዳንድ ክርስቲያኖች ለጌታ እራት እንዲህ ዓይነት የግድየለሽነት አመለካከት በማሳየታቸው በሞት እንደተቀጡ ገልጾአል። አንዳንዶች በሕመም ሌሎች ደግሞ በሞት ተቀጥተዋል (አንቀላፍተዋል)። አሁንም ሆነ የኋላ ኋላ የእግዚአብሔርን ፍርድ ከመቀበል ይልቅ ሕይወታችንን መመርመር፥ ኃጢአታችንን መናዘዝና በኅብረት መብላቱ ጠቃሚ ይሆናል።
 4. የጌታ እራት ልዩነቶችንና የራስ ወዳድነትን ሁኔታ ከማሳየት ይልቅ ፍቅርንና አንድነትን ሊያንጸባርቅ ይገባል። አማኞች እርስ በርሳቸው ተጠባብቀው አንድ ላይ እንዲመገቡ ተነግሯቸዋል። የጌታ እራቱ በክርስቶስ ሞት እንጂ በምግባቸው ላይ ሊያተኩር አይገባም ነበር። የተራበ ሰው ቢኖር ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመምጣቱ በፊት መብላት አለበት።

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ብዙ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመከፋፈል ወይም ሌሎች ኃጢአቶች ቢኖሩም ክርስቲያኖች የጌታን እራት መውሰዳቸውን ይቀጥላሉ። ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ ምን የሚል ይመስልሃል? ለ) የጌታን እራት ፍች በትክክል ብንረዳ፥ ይህ ቤተ ክርስቲያንን ሊያነጻ የሚችለው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ሕዝብ በሚሰበሰብበት ይፋዊ አምልኮ ላይ የሴቶችና ወንዶች ትክክለኛ አለባበስ ምን ዓይነት መሆን አለበት? (1ኛ ቆሮ. 11፡2-16)።

1ኛ ቆሮንቶስ 11-14 ብዙ ሕዝብ ስለሚካፈልበት ይፋዊ አምልኮ ይናገራል። በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ በአምልኮ ጊዜ ተገቢውን የአለባበስና የባሕርይ ሥርዓት መከተል እንደሚያስፈልግ ያስረዳል (1ኛ ቆሮ. 11፡2-16)። ሁለተኛ፥ በጌታ እራት ላይ የሚከሰቱትን ችግሮች ለማረም ይፈልጋል (1ኛ ቆሮ. 11፡17-34)። ሦስተኛ ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች፥ በተለይም በልሳን ስለመናገር ክርስቲያኖች የነበሯቸውን የተሳሳቱ ግንዛቤዎች ለማረም ይፈልጋል (1ኛ ቆሮ. 12፡14)።

የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 11፡2-16 አንብብ፡፡ ሀ) እግዚአብሔር የመሠረተውን የሥልጣን ቅደም ተከተል ዘርዝር። ለ) ስለ ወንዶችና የአለባበስ ሥርዓት የተሰጠውን ድንጋጌ ግለጽ። ሐ) ስለ ሴቶችና የአለባበስ ሥርዓት የተሰጠውን ድንጋጌ ግለጽ።

1ኛ ቆሮንቶስ 11፡2-16 ዛሬ እንዴት ተግባራዊ ሊሆን ይገባል? የሚለው ጥያቄ በምሁራን መካከል ከፍተኛ ክርክሮችን አስከትሏል። ጳውሎስ ሴቶች ራሳቸውን እንዲሸፍኑና ወንዶች ጸጉራቸውን እንዲያሳጥሩ የሰጠው ሕግ ዛሬም ይሠራል? ወይስ ይህ በጳውሎስ ዘመን የነበረ ባሕላዊ ጉዳይ በመሆኑ ዛሬ ዝርዝር ደንቦቹን ሳይሆን መርሆዎቹን ብቻ ተግባራዊ የምናደርግበት ነው? ጳውሎስ ሴቶች ፀጉራቸውን እንዲሸፋፈኑ በማዘዝ የሰጠው ድንጋጌ እርሱ የነበረበትን ዘመን እንጂ የእኛን ዘመን የማይመለከት ከሆነ፥ ወንድ ከሴት የመብለጡም ጉዳይ ባሕላዊ መሠረት ያለውና ተመሳሳይ ግንዛቤ የሚያሻው ነው? ይህንን ምዕራፍ አስቸጋሪ የሚያደርገው ስለ ጥንት ሰዎች ባሕልና ጳውሎስ ይህን ጉዳይ ለማንሣት የተገደደበትን ምክንያት አለማወቃችን ነው። ጳውሎስ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደነበሩ የሰማቸውን ችግሮችና ቤተ ክርስቲያኒቱ ያነሣቻቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት በማድረግ ላይ ነበር። ስለሆነም፥ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በአምልኮ ወቅት ሊለበሱ ስለሚገባቸው ተገቢ ልብሶች የጠየቁት ይመስላል።

እንደ ሌሎች ምንባቦች ሁሉ፥ የዛሬውን ዘመን አለባበስ ሳይሆን የጥንቱን ዘመን ባሕላዊ ልምምዶች ለመረዳት መሞከር ይኖርብናል። በጥንት ጊዜ ሰዎች ቦላሌ ሱሪዎችን፥ ሸሚዞችን፥ ጫማዎችን፥ ቀሚሶችን፥ ወዘተ አይለብሱም ነበር። በጳውሎስ ዘመን ለሴቶች ተለምዷዊ አለባበስ ሁለት ባሕላዊ መመዘኛዎች ነበሩ። (በእስያና መካከለኛው ምሥራቅ) ሴቶች በአደባባይ ወይም ከእንግዶች ጋር በሚሆኑበት ጊዜ ፊታቸውን የመሸፋፈን ልማድ ነበራቸው (ዘፍጥ. 24፡65)። በግሪክ ግን ሴቶች የራስ መሸፋፈኛ አልነበራቸውም። ምሁራን በ1ኛ ቆሮንቶስ ውስጥ የተገለጸው የራስ መሸፈኛ ጭንብልን ወይም ረዥም ፀጉርን ስለማመልከቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪዎች ይከራከራሉ።

በተጨማሪም፥ ምሁራን የዚህ ምዕራፍ ዋነኛ ጉዳይ ሴቶች ራሳቸውን ሳይሸፋፈኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄዳቸው ይሆን? ወይስ ፀጉራቸውን ሸብ አድርገው ሳያስሩ ከትከሻቸው ላይ ማዘናፈላቸው ይሆን? በሚለውም አሳብ ላይ ይከራከራሉ። ጳውሎስ የሚናገረው ረዥም ፀጉር ስላላቸው ምዕራባውያን ሴቶች እንጂ ስለ አፍሪካውያን ሴቶች አልነበረም። ፀጉራቸውን ሳያስይዙ ማዘናፈል በጥንት ባሕል አንድም የአልቃሽነት ወይም የዘማዊነት ምልክት ነበር።

የትኛውንም አመለካከት ብንቀበል፥ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነጻነትና አክብሮት ያገኙት አንዳንድ የቆሮንቶስ ሴቶች ከባሕላቸው ያፈነገጡ ይመስላል። ቤተ ክርስቲያን ከእንግዲህ «ወንድ፥ ሴት፥ ባሪያ ወይም ነፃ ሰው» የለም፥ ሁሉም በክርስቶስ አንድ ሰው ናቸው ብላ ታስተምር ነበር (ገላ. 3፡28 አንብብ።) የራስ መሸፈኛ ማድረግን ወይም ፀጉራቸውን ማስያዝ አቆሙ። ይህ ደግሞ በዘመኑ ባሕል ተቀባይነት አልነበረውም። ስለሆነም ጳውሎስ ሴቶች አዲሱን ነጻነታቸውን ባሕላቸው በማይፈቅደው መንገድ መጠቀም እንደሌለባቸው ያስረዳል። ጳውሎስ ባሕላቸውን አክብረው ሊለብሱና በአደባባይ ከመናገር ሊቆጠቡ እንደሚገባቸው ገለጻ (1ኛ ቆሮ. 14፡34)።

ይህን ምንባብ በጥንቃቄ በምናጠናበት ጊዜ የሚከተሉትን ነገሮች እንረዳለን።

 1. እግዚአብሔር የሥልጣንን ቅደም ተከተልና አስተዳደር አዋቅሯል። ከሁሉም የሚበልጠው ባለሥልጣን እግዚአብሔር አብ ሲሆን፥ ከእርሱ ቀጥሎ ከርስቶስ ነው። (እዚህ ባይጠቀስም፥ ቀጣዩ መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንረዳለን።) ቀጣዩ ወንድ ሲሆን፥ ሴት የመጨረሻውን ስፍራ ትይዛለች። ጳውሎስ ይህን የሥልጣን ቅደም ተከተል «ራስ» ይለዋል። አንዳንድ ምሁራን «ራስ» ከበላይ ያለ አካልን ማክበርን የሚያመለክት ነው ይላሉ። ስለሆነም፥ ሴት ወንድን፥ ወንድ ክርስቶስን፥ ክርስቶስ ደግሞ እግዚአብሔር አብን ማክበር አለበት ይላሉ። ሌሎች ራስ የሚለው ቃል ሥልጣንን እንደሚያመለክት ይናገራሉ። ስለሆነም፥ የእግዚአብሔር የሥርዓት ቅደም ተከተል ከእግዚአብሔር አብ ወደ ክርስቶስ ከዚያ ወደ ወንድና ብሎም ወደ ሴት እንደሚተላለፍ ያስረዳሉ። ይህ የሥልጣን ቅደም ተከተል በአምልኮ ውስጥ በተለያዩ ባሕሎች ሊገለጥ የሚችለው እንዴት ነበር? ይህ ወንዶች ባርኔጣቸውን በማውለቅና ፀጉራቸውን በአጭሩ በመቆረጥ እግዚአብሔርን ማክበር እንደነበረባቸው ያመለክታል። ሴቶች በአምልኮ ሰዓት ራሳቸውን በሻሽ፥ መጎናጸፊያ አልያም በረጅም ፀጉር መሸፈን እንደነበረባቸው ያመለክታል።

ስለዚህ ምንባብ የትኛውንም እመለካከት ብንከተል፥ ጳውሎስ ሴቶች ከወንዶች ያንሳሉ ማለቱ እንዳልሆነ መገንዘብ ይኖርብናል። በተቃራኒው ግን ስለ እግዚአብሔር የአስተዳደር ሥርዓት መግለጹ ነበር። ክርስቶስ ከእግዚአብሔር አብ ጋር በባሕርይና በኃይል የሚስተካከል ፍጹም አምላክ ሆኖ እያለ በሥልጣን ተዋረድ ከእግዚአብሔር አብ በታች እንዳለ ሁሉ፥ ሴቶችም በባሕርይና በጠቀሜታቸው ከወንዶች እኩል ናቸው። ነገር ግን ሴቶች በወንዶች አስተዳደር ሥር ይኖራሉ። ጳውሎስ የወንዶችና የሴቶች ግንኙነት በእግዚአብሔር አብና በእግዚአብሔር ወልድ መካከል ባለው ግንኙነት ምሳሌነት የተዘጋጀ መሆኑን አመልክቷል።

 1. የቤተ ክርስቲያን አምልኮ የአካባቢውን ባሕል ያንጸባርቃል። ትክክለኛ ያልሆነ አለባበስና ባሕርይ ወንጌሉን በማሰደብ ሰዎች ስለ ክርስትና የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ስለሚያደርግ፥ ክርስቲያኖች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይቃረኑትን ባሕላዊ መመዘኛዎች መከተል ይኖርባቸዋል። ስለሆነም፥ አንድ ወንድ ራሱን ተሸፋፍኖ ትንቢት መናገሩ ባሕሉ ለወንድ ተገቢ እንደሆነ ከሚገልጸው ድርጊት ያፈነገጠ በመሆኑ ትክክል አይሆንም። በጳውሎስ ዘመን ወንዶች ለእግዚአብሔር ያላቸውን አክብሮት ለማሳየት ባርኔጣቸውን ማንሣትና ራሳቸውን አለመሸፈን የሚጠበቅባቸው ይመስላል። ከሴቶች ይልቅ ፀጉራቸውን ማሳጠር ይኖርባቸዋል። ይህንን ማድረግ ቢያቆሙ ግን በውጪ ባሉት ዘንድ ለእግዚአብሔር ተገቢውን ክብር እንደማይሰጡ ያስቆጥርባቸዋል። በሌላ በኩል፥ ሴት ራሷን ሳትሸፋፈን ትንቢት ብትናገር፥ ባሕሉ ትክክል ነው ብሎ ከሚያስበው ግንዛቤ መውጣቷ ነበር። የጠበቀ ሥነ ምግባራዊ አኗኗር የማይከተሉ ሴቶች ፀጉራቸውን አይሸፋፈኑም ነበርና። ይህ ለዝሙት ወይም ጋለሞታነት የሚሰጠውን ፀጉርን የመላጨት ተግባርን ያህል አሳፋሪ ነበር። በተጨማሪም፥ ይህ ሴቶች የባሎቻቸውን ሥልጣን ባለመቀበል ያሻቸውን እንደሚያደርጉ የሚያሳይ ድርጊት ነበር። (ጳውሎስ ሴት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትንቢት ልትናገር እንደምትችል ይናገራል።) ስለሆነም፥ ጳውሎስ ሴቶች በአምልኮ ወቅት ባሕላቸው በሚፈቅደው መሠረት ባሎቻቸውን ማክበራቸውን እንዲያሳዩ ይጠይቃል። በቆሮንቶስ ይህ ማለት የሴቶች በአምልኮ ሰዓት ራሳቸውን መሸፋፈን ነበር። ይህም ሚስት ባሏንና እግዚአብሔርን ማክበሯን የሚያሳይ ሲሆን፥ የእግዚአብሔር ልጆች የሚያከናውኑትን ተግባር ለሚመለከቱት መላእክት መልካም ምስክርነት ነው።
 2. በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ወንድና ሴት፥ ባሎችና ሚስቶች እኩልና አንዳቸው ያለ ሌላቸው ሊኖሩ የማይችሉ ናቸው። ጳውሎስ ይህ ትምህርት ከመጠን በላይ እንዲለጠጥና ወንዶች ሴቶችን የመቆጣጠር፥ የመግዛትና የመጨቆን ሥልጣን አለን ብለው እንዲያስቡ አይፈልግም። ወንዶች ለሴቶች እንደሚያስፈልጓቸው ሁሉ፥ ሴቶችም ለወንዶች ያስፈልጓቸዋል። እግዚአብሔር መጀመሪያ ሰውን ወንድና ሴት አድርጎ በአምሳሉ እንደፈጠረ አስታውስ (ዘፍጥ. 1፡27)።

ይህ ክፍል ከዛሬዪቱ ቤተ ክርስቲያን ጋር ስለሚዛመድበት ሁኔታ ክርስቲያኖች ቢያንስ ሦስት አመለካከቶች አሏቸው።

ሀ. እነዚህ በሁሉም ዘመን ለሚሠሩ ክርስቲያኖች ሁሉ የተሰጡ ትእዛዛት ናቸው። ይህን አመለካከት የሚቀበሉ ሰዎች ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ሁሉ በራሳቸው ላይ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ያስተምራሉ። መንፈስ ቅዱስ በታሪክ ሁሉ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ክርስቲያኖች እነዚህ ትእዛዛት ለሁሉም ባሕሎች የተሰጡ ናቸው ብለው እንዳያስቡ ያደረገው ባሕላዊ መሠረት ስላላቸው ሳይሆን አይቀርም።

ለ. በዛሬው ዘመን ትክክለኛ በሆነው ጉዳይ ላይ የተለያዩ ባሕላዊ ግንዛቤዎች ስላሉ፥ የጳውሎስን ዝርዝር ትእዛዛት መከተል አያስፈልግም። ነገር ግን ሚስቶች ለባሎቻቸው በመገዛት አክብሮታቸውን ማሳየት እንዳለባቸው የሚያመለክተው የጳውሎስ አስተምህሮ በሁሉም ዘመን በሁሉም ባሕሎች ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች የሚሠራ ዐቢይ መርሆ ነው። ዋናው ነገር የአለባበስ ጉዳይ ሳይሆን እግዚአብሔርን እየፈሩ በተገዢነት መኖር ነው። ከሕይወታችን ጋር ልናዛምደው የሚገባን መርህ በባሕላችን ውስጥ ዓመፀኝነትን ሳይሆን ለእግዚአብሔር ጨዋነትንና አክብሮትን በሚያሳይ መልኩ መልበስ እንዳለብን ነው።

ሐ. ጳውሎስ ወንዶች ፀጉራቸውን በአጭሩ እንዲቆረጡና እንዳይሸፋፈኑ ሴቶች ረዥም ፀጉር እንዳያሳድጉና እንዲሸፋፈኑ፥ ወንዶች በሴቶች ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸው ያዘዘው ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ብቻ ነው። በ1ኛ ቆሮ. 11፡11-12 ጳውሎስ የወንዶችንና የሴቶችን እኩልነትና አንዳቸው የሌላቸው ጥገኛ መሆናቸውን ገልጾአል። ይህ ዛሬ ተግባራዊ ልናደርገው የሚገባን እውነት ነው።

ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር አብና ወልድ የሥልጣን ደረጃ መናገሩ ባል በሚስቱ ላይ አስተዳደራዊ ሥልጣን እንዳለው ሊያመለክት ይችላል። ነገር ግን ይህ ወንዶችና ሴቶች አንዳቸው ለሌላቸው ስለሚገዙበት ሁኔታ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከሚናገሩት አሳብ ጋር መዛመድ አለበት (ኤፈ. 5፡21)። ክርስቶስ ለኃጢአታቸው በመሞት ክርስቲያኖችን እንደወደደ ሁሉ፥ ባሎችም የሚስቶቻቸውን ፍላጎት ከራሳቸው በማስቀደም በመሥዋዕትነት ማፍቀር አለባቸው (ኤፌ. 5፡25)። ወንዶች በሴቶች ላይ የሚኖራቸው ሥልጣን ሚስቶቻቸውን ለመበደል፥ እንደ ባሪያ ለማዘዝ፥ ዝቅ አድርጎ ለመመልከት፥ ወዘተ… መብትን አይሰጣቸውም። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን የሰይጣን አስተምህሮ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ ራስን ስለመሸፋፈን ላቀረበው ትምህርት ከተሰጡት ከእነዚህ ሦስት ግንዛቤዎች የትኛውን ታምናለህ? ለምን? ለ) የገጠርና የከተማ፥ እንዲሁም ወጣቶችና አዋቂዎች ስለ ትክክለኛ አለባበስ ያላቸውን ግንዛቤ አነጻጽር። ሰዎች ትክክለኛ አለባበስ ነው ብለው የሚያስቡት ከባሕል ባሕል የሚለያየው እንዴት ነው? ) ሚስቶች ለባሎቻቸው አክብሮታቸውን የሚያሳዩባቸው አንዳንድ ባሕላዊ መንገዶች ምን ምንድን ናቸው? መ) የባልና የሚስትን ተደጋጋፊነት፥ ተከባባሪነትና ተገዥነት፥ እንዲሁም ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን በወደደበት መንገድ ባል ሚስቱን መውደድ እንዳለበት የሚያስረዳውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለማንጸባረቅ ይቻል ዘንድ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊታረሙ የሚገባቸው የወንዶች የበላይነት የተሳሳቱ ገጽታዎች ምን ምንድን ናቸው? ሠ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ጋብቻዎች የእግዚአብሔርን ፍጹማዊ ግንኙነት የሚያንጸባርቁ ይመስልሃል? ለምን? ረ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ለሚገኙ ባለትዳሮች ስለ ትክክለኛው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ግንኙነት ምን ታስተምራለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ክርስቲያን ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ መብላት አለበት? (1ኛ ቆሮ. 8፡1-11፡1)

የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 8-10 አንብብ። ሀ) የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ያሳሰባቸው ጉዳይ ምን ነበር? ለ) ጳውሎስ ለጣዖት የተሠዋን ሥጋ ስለ መብላት ወይም ስላለመብላት የሰጣቸውን መርሆች ዘርዝር። ሐ) ዛሬ ክርስቲያኖች በአመለካከት የሚለያዩባቸውንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ያልተጠቀሱትን ልምምዶች ዘርዝር። የጳውሎስ መርሆች ከእነዚህ የተለያዩ ግንዛቤዎች ጋር የሚዛመዱት እንዴት ነው?

ሁልጊዜም ክርስቲያኖች በአመለካከት የሚለያዩባቸው የተለያዩ ልምምዶች አሉ። ክርስቲያኖች አልኮል ሊጠጡ፥ ከንፈራቸውንና ጥፍራቸውን ቀለም ሊቀቡ፥ የፋሽን ልብስ ሊለብሱ፥ ፊልም ሊያዩ፥ የዓሣማ ሥጋ ሊበሉ፥ ወዘተ.. ይችላሉ? ከኦርቶዶክስ እምነት የመጡ ክርስቲያኖች አንገታቸው ላይ የነበረውን ክር ሊበጥሱ ይገባል? ክርስቲያኖች በእነዚህ ጉዳዮች በአሳብ አይስማሙም። እንግዲህ፥ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ በማይከለክላቸው ጉዳዮች ላይ በአሳብ በሚለያዩበት ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል? በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ ልዩነቶችን አቻችሎ ስለመኖር ጠቃሚ መርሆዎች ቀርበዋል።

ሀ. በቆሮንቶስ የነበረው ሁኔታ፤ በቆሮንቶስ ከተማ ብዙ ጣዖታትና ጥቂት ክርስቲያኖች እንደነበሩ ቀደም ብለን ተመልክተናል። በቆሮንቶስ ከተማ ከጣዖት አምልኮ ጋር የሚዛመዱ ብዙ ነገሮች ነበሩ። የቆሮንቶስ ሰዎች በክርስቶስ ካመኑ በኋላ፥ «ከቀድሞ ሕይወታችን ልንተወውና ይዘን ልንቀጥል የሚገባን ምንድን ነው? እያሉ ይጠይቁ ነበር። ሁለተኛው ጥያቄ ደግሞ፥ «ቀደም ሲል ሃይማኖታዊ አስከትሎቶችን ያስተናገዱትንና በራሳቸው ክፉዎች ያልሆኑትን ነገሮች እንዴት ልናስተናግዳቸው ይገባል?» የሚል ነበር። በቆሮንቶስ ክርስቲያን በገበያ ላይ የሚሸጥ ሥጋ ሊበላ ይገባል ወይ? በሚለው ጥያቄ ዙሪያ የተጧጧፈ ክርክር ይካሄድ ነበር። አንድ ሰው ለጣዖት ለመሠዋት በሚፈልግበት ጊዜ እንስሳውን ወደ ቤተ ጣዖት ይወስዳል። እንስሳው ታርዶ ከፊሉ ለጣዖት ከተሠዋ በኋላ፥ ከቀረው ሥጋ የተወሰነውን ለካህኑ ሲሰጥ፥ የተወሰነውን ደግሞ ቤቱ ወስዶ ከወዳጆቹ ጋር ሊመገብ ወይም ገበያ ላይ ሊሸጥ ይችል ነበር። ገበያ ላይ የሚሸጠው ሥጋ በአብዛኛው ለጣዖት የተሠዋ ነበር። ስለሆነም፥ የቆሮንቶስ አማኞች፥ «ክርስቲያኖች ከገበያ ላይ ሥጋ ገዝተው ሊበሉ ይችላሉ? ከዓለማዊ ሰው ቤት ሲጋበዙስ የሚቀርብላቸውን ሥጋ ሊበሉ ይገባል? ይህ ሥጋ ለጣዖት የተሠዋ ሊሆን ይችላልና» የሚል ጥያቄ አነሡ። ይህ እንዳንድ ክርስቲያኖች ከሙስሊም ሉካንዳ ወይም በተገቢው የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ያልታረደ ሥጋ ለመብላት ከሚቸገሩበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ ለዚህ ጥያቄ «እንዲህ አድርጉ/ እንዲህ አታድርጉ» የሚል ቀላል ምላሽ አልሰጠም። እንደነዚህ ዓይነት ጥያቄዎች ሁልጊዜም ሥር የሰደዱ ጉዳዮችን እንደሚያካትቱ ተገንዝቦ ነበር።

መርሆዎች፡- ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከሰጣቸው መልሶች ለሁላችንም ጠቃሚ የሆኑትን መርሆዎች እናገኛለን። እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ሀ. አንድ ነገር ስሕተት አለመሆኑን ማወቃችን በፍቅርና ለሌሎች ከማሰባችን ጋር ሊጣጣም ይገባል (1ኛ ቆሮ. 8፡1-3)። ፍቅር ያልታከለበት እውቀት ኩሩና አጥፊ ነው። ለምሳሌ፥ ወደ ፊልም ቤት መሄድ ስሕተት አለመሆኑን ባውቅና ሌሎች ክርስቲያኖች ግን ስሕተት ነው ብለው ቢያስቡ፥ የእኔ ወደ ፊልም ቤት መሄድ የእነርሱን እምነት ከመጉዳትና የእኔን ምስክርነት ከማበላሸት የተሻለ ጥቅም አይኖረውም። ‹እውቀቴን ጉዳትን እንጂ ጥቅምን አላስከተለም። ሰዎች ተጨማሪ ትምህርት ከተከታተሉ በኋላ ተመልሰው የቤተ ክርስቲያናቸው መሪ በሚሆኑበት ጊዜ ይኩራራሉ። እውቀታቸው ከሌሎች ሰዎች የሚያስበልጣቸው ይመስላቸዋል። ይህ የኩራት እውቀት እነዚህ ሰዎች ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ብዙም እንደማያውቁ ያሳያል።

ለ. ከእውቀት አንጻር፥ ሰብአዊ ጣዖት (ወይም ሌላ ሃይማኖት) ሰው ሠራሽ እንጂ አምላክ እንዳልሆነ በሳል ክርስቲያኖች ያውቃሉ (1ኛ ቆሮ. 8፡4-7)። አንዱ እውነተኛ አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጠው ብቻ ነው። ብቸኛው አምላክና ጌታ በዓለም ውስጥ ሁሉንም ነገር የፈጠረው እግዚአብሔር አብ፥ የፍጥረት ሥራ ሁሉ ወኪል የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስና ሕይወት ሰጭ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ነው። ስለሆነም፥ ሕይወትና ኃይል ለሌላቸው ሰው ሠራሽና ሙት ጣዖታት የተሠዋን ሥጋ መብላት ምንም ማለት እንዳልሆነና ሊበላ እንደሚችል በሳል (ጠንካራ) ክርስቲያኖች ይገነዘባሉ።

ሒ. ሌሎች ቢያደርጉትም እንኳ ትክክል ነው ብለህ ያላመንኸውን ነገር ማድረጉ ኃጢአት ነው። ጣዖት ሲያመልኩ የኖሩና በእምነታቸው ያልበሰሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሥጋውን መብላት በጣዖት አምልኮ ውስጥ መሳተፍ ነው ከሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ። ይህም ድነትን (ደኅንነትን) ባገኙ ጊዜ የተዉት ልምምድ ነበር። ስለሆነም፥ ሌሎች ክርስቲያኖች ይህን ሥጋ ሲበሉ አይተው ከኃፍረት የተነሣ አብረው በሚበሉበት ጊዜ፥ ሕሊናቸው ስለሚቆሽሽ ኃጢአትን ይሠራሉ። የሚያደርጉት ነገር በእግዚአብሔር የተፈቀደ ነው ብለው እስካላመኑ ድረስ (ጳውሎስ «በእምነት ካልሆነ» እንዳለው)፥ ሌሎች የሚያደርጉትን መከተል አያስፈልጋቸውም ነበር።

መ. ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ መብላትም ሆነ አለመብላት ምንም ዓይነት መንፈሳዊ እሴት የለውም። አንድን ሰው ወደ እግዚአብሔር አያቀርበውም ወይም ከእግዚአብሔር አያርቀውም (1ኛ ቆሮ. 8፡8)። አዲስ ኪዳን ሁሉም ነገር በጸሎት የተባረከ ስለሆነ ልንበላ እንደምንችል ያስረዳል። በእምነት እስካደረግነው ድረስ በእግዚአብሔር የተፈቀደ ነው (ማር. 7፡14-19፤ የሐዋ 10፡9-16)።

ሠ. አንድ ተግባር በእግዚአብሔር የተፈቀደ ነው ብለን ብናምን እንኳ ፍቅር ከግለሰባዊ ነጻነት ይልቃል (1ኛ ቆሮ. 8፡9–9፡27)። ስለሆነም፥ ሥጋን መብላት ምንም ችግር የለውም የሚል እምነት ያላቸው (ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተከለከለውን ተግባር የሚፈጽሙ) ሰዎች የተለየ አመለካከት የሚከተሉትን ወገኖች ላለመጉዳት ሲሉ ነጻነታቸውን መገደብ አለባቸው። (ጳውሎስ «ደካማ» እና «ጠንካራ» ክርስቲያኖች እንዳሉ ገልጾአል። ጳውሎስ ይህን ሲል ስለ መንፈሳዊ ብስለት ወይም መንፈሳዊነት መናገሩ አይደለም። እርሱ ያተኮረው አንድ ሰው በያዘው የግንዛቤ ደረጃ ላይ ነው። ስለሆነም፥ አንድ ክርስቲያን የዓሣማ ሥጋ በመብላቱ በኩል «ጠንካራ» ሊሆንና የፋሽን ልብስ በመልበሱ ረገድ «ደካማ» ሊሆን ይችላል። ሌላው ክርስቲያን ደግሞ ሥጋ ለመብላት ሊቸገርና የፋሽን ልብስ ለመልበስ ሊደፍር ይችላል።) ጠንካራ ክርስቲያኖች ደካማ ክርስቲያኖችን ላለማሰናከል ሲሉ ተግባሮቻቸውንና ነጻነቶቻቸውን መገደብ አለባቸው። ከሁሉም የሚበልጠው ፍቅር ነው። ፍቅር ደግሞ ሥጋን መብላት ወይም የተወሰኑ ልብሶችን መልበስ ሌላውን ክርስቲያን የሚጎዳው ከሆነ፥ ከዚህ ተግባር መቆጠብ እንዳለብን ይመክረናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች የተለያዩ አመለካከቶችን ስለሚይዙባቸው ነገሮች ያቀረብኸውን ዝርዝር ከልስ። ወይም ሌሎች ምሳሌዎችን ጨምርበት። ጠንካራውና ደካማው የትኛው እርምጃ እንደሆነ ግለጽ። ለ) ፍቅር አልባ እውቀት ያለው ሰው በእነዚህ ልምምዶች ሁሉ ወቅት ምን እንደሚያደርግ ግለጽ። ሐ) ፍቅር ያለው ሰው በእነዚህ ልምምዶች ወቅት ምን እንደሚያደርግ ግለጽ።

ማብራሪያ፡ ለሌሎች ባለን ፍቅር የግል መብቶችንና ነጻነቶችን ስለመተው ጳውሎስ ከራሱ ሕይወት ምሳሌ ሰጥቷል (1ኛ ቆሮ. 9)። ጳውሎስ ሐዋርያ ቢሆንም፥ ለወንጌሉ ሲል ብዙ ጊዜ መብቶቹን ትቷል። ለምሳሌ፥

ሀ. ጳውሎስ የማግባት መብት ቢኖረውም ለወንጌሉ ሲል አላደረገውም።

ለ. ጳውሎስ ለሐዋርያዊ አገልግሎቱ ገንዘብ የመቀበል መብት ቢኖረውም፥ ሰዎች ለራስ ወዳድነት ምክንያቶች ያስተምረናል ብለው እንዳያስቡ ትቷል። ቆሮንቶሶችና አዳዲስ ክርስቲያኖች ለወንጌል ስርጭቱ ዓላማ ጥርጣሬ እንዳይኖራቸው በማሰብ፥ ጳውሎስ ክፍያ ላለመቀበል ወስኗል። ስለሆነም፥ ከበሳል አብያተ ክርስቲያናት በሚያገኘው ስጦታ ወይም ራሱ ሠርቶ በሚያገኘው ገንዘብ (በቆሮንቶስ ሳለ ድንኳን ይሰፋ እንደነበረ የሐዋ. 18፡3 አንብብ።) ራሱን ይደግፍ ነበር። በፊልጵስዩስ 1፡5 እና 4፡14–18 ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት አገልግሎቱን በገንዘብ እንደደገፈች ገልጾአል። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ከወንጌል ስብከት ገንዘብ ለማግኘት ካልፈለገ ምን ይሆን የፈለገው? ጳውሎስ ገንዘብ ቢከፈለውም ሳይከፈለውም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወንጌልን የመስበክ ግዴታ እንደተጣለበት ያውቅ ነበር። በግሉ የተሸላሚነት ስሜት የሚሰማው ገንዘብ ሳይጠይቅ ለጠፉት ወንጌልን በሚሰብክበት ጊዜ ነበር። (ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግሉ፥ በተለይም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ብለው የገቢ ማግኛቸውን የሚተዉ ሰዎች ደመወዝ ሊከፈላቸው እንደሚገባ የሚያስረዳውን የመጽሐፍ ቅዱስ መርህ አጽንዖት ሰጥቶ ገልጾአል። ለሚያገለግሏት ሰዎች የማትከፍል ወይም ነፃ የውጭ ወንጌላውያን ሥራዎቿን እንዲያካሄዱላት የምትፈልግ ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ፈቃድ እንዳፈነገጠች ግልጽ ነው።)

ሐ. ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እስካልወጣ ድረስ ጳውሎስ እንደፈለገ የመኖርና የመሥራት ነጻነት ነበረው። ነገር ግን በተቻለ መጠን ብዙዎችን ያድን ዘንድ ነጻነቱን ገድቦታል። አይሁዶችን በሚያገለግልበት ጊዜ ወንጌሉን ሊያካፍላቸው እንዲችል የተወሰኑ ምግቦችን የመመገብ፥ በተወሰኑ መንገዶች የመልበስና የማምለክ ነጻነቱን በመገደብ ባሕሉን ቀይሯል። አሕዛብን በሚያገለግልበት ጊዜ የቋንቋ አጠቃቀሙን፥ የአለባበስና የአምልኮ ሁኔታውን በመቀየር ከባሕላቸው ጋር ተግባብቶ ወንጌሉን ሰብኮላቸዋል። ጳውሎስ በእምነታቸው ደካሞች ሆነው እግዚአብሔር እንዳልከለከለ የሚያውቃቸውን ነገሮች ለማድረግ የማይፈልጉ ሰዎች በሚያጋጥሙት ጊዜ፥ እንደነርሱው «ደካማ» ሆኗል። ጳውሎስ ለግል ነጻነቱና መብቱ ብዙም ትኩረት አይሰጥም ነበር። ለጳውሎስ ዋናው የሰዎች መዳን ነበር። ስለሆነም፥ ሰዎች እንዳይድኑ የሚያደናቅፉትን ነገሮች ሁሉ ከማከናወን ይታቀብ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡– ) በኢትዮጵያ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትና ባሕሎች በሃሳብ የሚለያዩባቸውን አንዳንድ ነገሮች ዘርዝር። ለ) የተወሰኑ ሕዝቦች (ለምሳሌ፥ ኦርቶዶክሶች ወይም ሙስሊሞች) በሚበዙበት አካባቢ የምታገለግል ወንጌላዊ ብትሆን፥ ወንጌሉን ለመስማት የበለጠ ፈቃደኞች ይሆኑ ዘንድ ነጻነትህን የምትወስንባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

መ. ለጳውሎስ መንፈሳዊ ሩጫውን በሚገባ ሮጦ እግዚአብሔር የሰጠውን አገልግሎት በታማኝነት መፈጸምና መንግሥተ ሰማይ መድረስ ወሳኝ ነበር። ስለሆነም፥ የሚወዳቸውንና የሚጠላቸውን ነገሮች፥ አነሣሽ ምክንያቶቹን፥ ተግባራቱንና ሥጋዊ ፍላጎቶቹን በመቆጣጠር ራሱን ገዝቷል። (ጳውሎስ ይህንን ሥጋን መጎሰም ይለዋል።) ይህም የግል ነጻነቱን እየተወ ማንንም ሳያስቀይም ለሰዎች ሁሉ ወንጌልን እንዲሰብክና እግዚአብሔርን እንዲያገለግል ይረዳዋል። (ቆሮንቶስ ከጥንት የስፖርት ከተሞች አንዷ ነበረች። ለዚህ ነበር ጳውሎስ ስለ ክርስትና ለማስተማር ስፖርታዊ ምሳሌዎችን የጠቃቀሰው።)

ከብሉይ ኪዳን የተወሰደ ምሳሌ (1ኛ ቆሮ. 10፡1-13)፡- አንዳንድ ጊዜ በመንፈሳዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን ሳናድግ፥ ሁለንተናችንን ለእግዚአብሔር አሳልፈን ሳንሰጥና ሌሎችን በትሕትና ሳናገለግል በራስ ወዳድነት እየተሯሯጥን እንዋዥቃለን። ጳውሎስ ይህ አደገኛ አመለካከት መሆኑን ገልጾአል። ለእርሱ መንፈሳዊ ሕይወት እንደ ማራቶን ወይም እንደ ቦክስ ውድድር ነበር። ይህም ፍላጎታችንንና ሥጋችንን መቆጣጠርን የሚጠይቅ ከፍተኛ ራስን የመግዛት ተግባር ነው። ይህ ካልሆነ፥ ጳውሎስ ለመንፈሳዊ ሩጫው ብቁ እንደማይሆን አመልክቷል። ይህንንም እውነት ለማብራራት ብሉይ ኪዳንን፥ በተለይም የእስራኤላውያንን የምድረ በዳ ጉዞ በምሳሌነት ጠቅሷል። እነዚህ ታሪኮች ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ጠቃሚ ትምህርቶችን ከመስጠታቸውም በላይ፥ ለክርስቲያኖች ሁሉ ማስጠንቀቂያዎችን ያስተላልፋሉ።

ሀ. እስራኤላውያን በክብር ደመና እየተመሩ ይጓዙ ነበር። (ቀን ቀን የክብር ደመና፥ ማታ ማታ የእሳት ዓምድ ይመራቸው ነበር።)

ለ. እስራኤላውያን ሁሉ የእግዚአብሔርን ኃይል ተመልክተዋል፤ ቀይ ባሕር ተከፍሎ ተሻግረዋል።

ሒ ሁሉም “በሙሴ ተጠምቀዋል”። ጳውሎስ ይህን ሲል ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ከነበረው ግንኙነት በመነጩት መንፈሳዊ በረከቶች እየተደሰቱ በእርሱ አመራር ሥር ይኖሩ እንደነበር መግለጹ ነበር።

መ. ሁሉም መንፈሳዊውን የመና ምግብ በልተዋል። መናው ከእግዚአብሔር እንጂ ከምድር ስላልተገኘ መንፈሳዊ ተብሏል።

ሠ. ሁሉም አንድ ዓይነት መንፈሳዊ መጠጥ ጠጥተዋል። ይህም ከዓለቱ የፈለቀውን ውኃ ያመለክት ነበር። የብሉይ ኪዳን እስራኤላውያን በውኃውና በመናው እንደተደሰቱ ሁሉ፥ እኛም የሕይወት እንጀራችንና የሕይወት ውኃችን በሆነው በክርስቶስ ደስ እየተሰኘን ነው። (ዮሐ 6፡30-35፤ 7፥37-39 አንብብ።) መናውና የዓለቱ ውኃ ክርስቶስ ለተከታዮቹ የሚሰጣቸውን በረከት ያመለክታሉ።

ምንም እንኳ ሁሉም እስራኤላውያን ወደ ተስፋዪቱ ምድር ለመግባት በረሃውን እያቋረጡ መንፈሳዊ ሩጫ ቢሮጡም፥ ሩጫውን የጨረሱት ኢያሱና ካሌብ ብቻ ነበሩ። የተቀሩት የከነዓንን በረከት ሳይቀበሉ በምድረ በዳ ውስጥ ሞተዋል። በወሲብ ኃጢአት፥ በጣዖት አምልኮ፥ እንዲሁም በመሪዎቻቸውና በእግዚአብሔር ላይ በማመፃቸው ሩጫውን በሚገባ ሊሮጡ አልቻሉም። ስለሆነም፥ ጳውሎስ በመንፈሳዊ ሩጫቸው በመዘናጋት ላይ የነበሩት የቆሮንቶስ አማኞች ዋናው ሩጫውን መጀመር ወይም ለአጭር ጊዜ መሮጥ ሳይሆን ከፍጻሜ ላይ መድረስ እንደሆነ እንዲያስታውሱ አስጠንቅቋቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች እስከ መጨረሻው ለመሮጥ ይችሉ ዘንድ ሕይወታቸውን ለመቆጣጠር ከመጣር ይልቅ በድነታቸውና (በደኅንነታቸው) ጊዜያዊ በረከቶች ላይ የሚያተኩሩት እንዴት ነው? ለ) 2ኛ ጢሞ 4፡6-8 እንብብ። ጳውሎስ ለእምነቱ ሊሞት ሲል ስለዚህ ሩጫ ምን አለ?

ጳውሎስ እውነተኛውን የሕይወት አቅጣጫ የሚከተል ሰው ስለነበር፥ በሩጫ ውስጥ መንፈሳዊ ፈተናዎች መኖራቸውን ለክርስቲያኖች አስጠንቅቋል። ስለሆነም ጸንተው ለመቆም ሊቆርጡ ይገባል። ብዙ ክርስቲያኖች በ1ኛ ቆሮንቶስ 10፡13 የተገለጸውን አሳብ በተሳሳተ መንገድ ይረዳሉ። እግዚአብሔር ከፈተና እንደሚጠብቀን ወይም ፈተና ገጥሞን በምንጸልይበት ጊዜ እግዚአብሔር ከፈተና ያድነናል ብለው ያስባሉ። ጳውሎስ የሚለው ይህን አልነበረም። ጳውሎስ ስለ ፈተና የተለያየ እውነቶችን ገልጾአል።

በመጀመሪያ፥ ክርስቲያኖች ሁሉ ፈተና እንደሚገጥማቸው ገልጾአል። ብዙውን ጊዜ ፈተና በሚገጥመን ጊዜ እኛ ላይ ብቻ የደረሰ ይመስለናል። ጳውሎስ ግን ክርስቲያኖች ሁሉ በፈተና ውስጥ እንደሚያልፉ ገልጾአል።

ሁለተኛ፡ ጳውሎስ ታማኙ አምላካችን ከእኛ ጋር ስላለ ወደ ፈተና የምንገባው ብቻችንን እንዳልሆነ አስረድቷል።

ሦስተኛ፥ ታማኙ አምላካችን ከአቅማችን በላይ የሆነ ፈተና እንደማይገጥመን የተስፋ ቃል ገብቶልናል። እግዚአብሔር ምን ዓይነት ፈተናዎች እንደሚገጥሙን በመወሰን በመንፈሳዊ እድገት ደረጃችን የምንቋቋማቸውን ብቻ እንድንጋፈጥ ይፈቅዳል።

አራተኛ፥ ሁልጊዜም ፈተናን ለመቋቋምና ለመጽናት የሚያስችል መንገድ አለ። ለእግዚአብሔር የሚከብድ ባይሆንም፥ ጳውሎስ ያተኮረው ከፈተና ስለመትረፍ አልነበረም። ጳውሎስ አጽንኦት የሰጠው በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በመንፈሳዊ ጉዟችን ድል ነሺዎች ሆነን እስከ መጨረሻው በመጽናታችን ላይ ነው።

ጳውሎስ ስለ ሰዎች በፈተና መውደቅ ሰይጣንን እንደማይወቅስ አስተውል። ሰይጣን ዓለምንና ሥጋችንን ተጠቅሞ በኃጢአት ሊፈትነን ቢችልም፥ ኃጢአትን እንድንሠራ ለያስገድደን ግን አይችልም። እግዚአብሔር የማንችለውን ፈተና አመጣብን ብለንም ልናማርር አንችልም። ሌላ ሰው ለኃጢአት እንደገፋፋን በመግለጽም አንወቅሰውም። ሁልጊዜም ኃጢአትን የምንፈጽመው እግዚአብሔርን ከመታዘዝ ይልቅ የሥጋችንን ፍላጎት ለማሟላት ስለምንመርጥ ነው። ተግባሮቻችን የምርጫዎቻችን ውጤቶች በመሆናቸው ተጠያቂዎች ራሳችን ነን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች እውነተኛ ክርስቲያኖች ፈተና እንደማይገጥማቸው ወይም በመጸለይና ሰይጣንን በማሰር ፈተናው ትቷቸው እንዲሄድ እንደሚያደርጉ ሲናገሩ የሰማህበትን ሁኔታ አብራራ። ለ) አንዳንድ ክርስቲያኖች ራሳቸው ለፈጸሙት ኃጢአት ሰይጣንን ወይም ሌሎች ሰዎች ተጠያቂ የሚያደርጉት እንዴት ነው?

ስለ አምልኮተ ጣዖት የተሰጠ ማስጠንቀቂያ (1ኛ ቆሮ. 10፡14-22)። ጣዖታት አማልክት ላለመሆናቸው የነበራቸውን እውቀት በተሳሳተ መንገድ የተገነዘቡ አንዳንድ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ነበሩ። «ጣዖታት አማልክት እስካልሆኑ ድረስ ጎረቤቶቻችንን ለማክበር ስንል ሄደን መሥዋዕት ልናቀርብላቸው እንችላለን። ከጎረቤቶቻችን ጋር ያለን ግንኙነት አስፈላጊ ነው። እንደ ድንጋይ ጣዖት ላለ እውነተኛ ያልሆነ ነገር መሠዋቱ ሊጎዳን አይችልም» ብለው አሰቡ። ምናልባትም ጣዖትን በማምላካቸው ምንም ሊጎዱ እንደማይችሉ በማሰብ በዚሁ ተግባራቸው የቀጠሉ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ልጆች እንደ መሆናቸው ይህንኑ ተግባር ሊፈጽሙ የማችይሉባቸውን አያሌ ምክንያቶች ጳውሎስ ዘርዝሯል።

ሀ. ለጣዖት የተሠዋውን ምግብና መጠጥ እየበሉ እየጠጡ ከሌሎች ጋር ለጣዖት በሚሠዉበት ጊዜ የጣዖት አምልኮው ተካፋዮች መሆናቸውን እየገለጹ ነበር። አንድ ክርስቲያን ሙሉ ለሙሉ ከእግዚአብሔር ጋር የሚቃረን ተግባር ከሚፈጽሙ ሰዎች ጋር እንዴት በዚህ መንገድ ኅብረት ሊያደርግ ይችላል?

ለ. ጣዖታት በራሳቸው አማልክት ባይሆኑም፥ አጋንንት ከጣዖት ጋር ይሠሩ ነበር። ሰዎቹ አምልኮተ ጣዖትን በሚያካሂዱበት ጊዜ በትክክል አጋንንትን ማምለካቸው ነበር። ይህም ለሰይጣንና ለአጋንንት ሕይወታቸውን እንዲያጠቁ በር ይከፍታል። ክርስቲያኖች ደግሞ ከሰይጣን ጋር ለመዋጋት የሚያስችል ኃይል እንደሌላቸው ማወቅ አለባቸው። ማንም ሰው በቅዱስ ቁርባን ተምሳሌትነት እንደተገለጸው ክርስቶስን እያመለከ በጣዖት አምልኮ ውስጥ ሊካፈል አይችልም። ይህንን ማድረግ የእግዚአብሔርን ቅጣት ያስከትላል።

የውይይት ጥያቄ፡- ዛሬ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን እናመልካለን እያሉ ከሰይጣን ኃይል ሥር ያሉትን ነገሮች በማምለክ እግዚአብሔርን ሊያሳዝኑ የሚችሉባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

ለጣዖት ስለተሠዋ ምግብ የተሰጡ ዝርዝር ትእዛዛት (1ኛ ቆሮ. 10፡23-11፡1)

ሀ. ጳውሎስ ቀደም ሲል ስለ ዝሙት በሚያስተምርበት ጊዜ ወዳነሣው መሠረታዊ መርህ ይመለሳል (1ኛ ቆሮ. 6፡12)። (የምንፈልገውን የማድረግ ነጻነት አለን ብለን ልናስብ ብንችልም፥ ዋናው ጥያቄ፥ «ጠቃሚ ነው ወይ?» የሚለው ነው። ይህ ለግለሰቡ ጠቃሚ ነው? ከሁሉም በላይ፥ ይህ ለሌሎች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሰዎች ጠቃሚ ነው? ስለሆነም፥ በአንድ ልምምድ ላይ ሰዎች የተለያዩ አመለካከቶችን በሚያቀርቡበት ጊዜ፥ ልምምዱ ምንም ችግር ሊያስከትል እንደማይችል የሚያስበው ሰው ስለ ራሱ ነጻነት ብቻ ሳይሆን በሌሎች ላይ ስለሚያስከትለው ተጽዕኖም ማሰብ አለበት። ይህ ልምምድ በማያምኑ ሰዎች ፊት ምስክርነቱን ስለመጉዳቱና በሌሎች ክርስቲያኖች ላይ ስለሚያደርሰው ተጽዕኖ ማሰብ ይኖርበታል (1ኛ ቆሮ. 10፡23-24)።

ለ. ከገበያ የተገዛን ሥጋ መብላት። ለጣዖት ስለ መሠዋት አለመሠዋቱ አትጨነቅ። ለጣዖት ተሠውቷል ወይ? ብለህ የምትጠይቅ ከሆነ፥ ሕሊናህ እንዳትበላው እየነገርህ ነው ማለት ነው። ሥጋው መሠዋት አለመሠዋቱን አለማወቁ የተሻለ ነው። ሁሉም ነገር የእግዚአብሔር እንደሆነና እርሱም ደስ እንድንሰኝበት እንደሰጠን አስታውስ።

ሐ አንድ ዓለማዊ ምግብ ቢጋብዝህ፥ ለጣዖት ተሠውቶ ይሆን? ብለህ ሳትጠራጠር የቀረበልህን ብላ።

መ. አንድ ሰው (ዓለማዊውም ሆነ ጉዳዩ የሚያሳስበው ክርስቲያን) ለጣዖት የተሠዋ መሆኑን ከነገረህ አትብላው። ለምን? የማትበላው ሕይወት ለሌለው ጣዖት የተሠዋ ምግብ እንደማይጎዳህ እስካመንህ (እስካወቅህ) ድረስ መንፈሳዊ ችግር ስለሚያስከትልብህ አይደለም። የማትበላው ዓለማዊው የጣዖት አምልኮውን እየደገፍህለት እንደሆነ እንዳያስብ ነው። በደካማ ክርስቲያኖችም ፊት መብላት አይኖርብህም። ምክንያቱም ተግባርህ ሕሊናቸው የማይቀበለውን ነገር እንዲያደርጉ ያበረታታቸዋል። ሌሎች ሰዎች ምን ልናደርግ እንደምንችል ሊናገሩ አይችሉም። ሕሊናችን ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ይወሰናል። ነገር ግን ለሌሎችና ለወንጌሉ ባለን ፍቅር ምክንያት ተግባራችንን እንገድባለን።

ሠ. ተግባሮችህን የምትፈጽመው ስለፈለግህ ብቻ ሳይሆን ለእግዚአብሔር ክብርን ለማምጣት ጭምር እንደሆነ አረጋግጥ። ተግባሮችህ ለእግዚአብሔር የበለጠ ክብርን የሚያመጡት ክርስቲያናዊ ነጻነትህን እንዳሻህ ስትጠቀም ላይሆን ክርስቲያኖችንም ሆነ ዓለማውያንን ላለማሰናከል ጥረት ስታደርግ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ክርስቲያኖች ስለማይስማሙባቸው ልምምዶች የጻፍኸውን ዝርዝር ተመልከት። ጳውሎስ በዚህ ክፍል ውስጥ ያቀረባቸውን መርሆዎች በመመልከት ጠንካራ ክርስቲያን ብትሆን ምን ዓይነት ምላሽ እንደምትሰጥ ግለጽ።

ምንም እንኳን ጳውሎስ ባያትተውም፥ «ደካማ» ክርስቲያኖች የተባሉት በደካማነታቸው መጽናት የለባቸውም። የሚያስቀይማቸውን ወይም ከሌሎች የሚለያያቸውን ተግባር መመርመር ያስፈልጋቸዋል። ደካማ ክርስቲያን ያንን ተግባር ለመፈጸም ባይፈልግም እንኳ፥ ሌሎች ክርስቲያኖች ሌላ አቋም ሲይዙና ቀደም ሲል ይጠላው የነበረውን ተግባር ሲፈጽሙ በሚመለከትበት ጊዜ ለመታገሥ እንዲችል ወደ «ጠንካራ» ክርስቲያንነት መሸጋገር ይኖርበታል። ወደ ጠንካራ ክርስቲያንነት መሸጋገር እንጂ በደካማነቱ መጽናት የለብንም። (ማስታወሻ፡- የምንነጋገረው መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ስለጠቀሳቸው ኃጢአቶች ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ ስለማይናገርሳቸው ነገሮች መሆኑን አስተውል።)

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)