የሕይወት እንጀራ

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች

የሐዋርያትን ምሳሌነት በመከተል መከፋፈልን ማስወገድ (1ኛ ቆሮንቶስ 4፡1-21)

ተመስገን በቅርቡ ከሥነ መለኮት ኮሌጅ የተመረቀ ክርስቲያን ነው። ወደ አካባቢው ሲመለስ የቤተ ክርስቲያኒቱ የአውራጃው መንፈሳዊ አገልግሎቶች ኃላፊ ሆኖ ይሠራ ጀመር። የአውራጃው ቤተ ክርስቲያን፥ መንፈሳዊነት እንዲያድግ ይፈልግ ነበር። «እኔ ዲግሪ ያለኝ ሊቅ ነኝ። ኃላፊነቱም በእጄ ውስጥ ስላለ ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ልነግራቸው እችላለሁ። እንዲህ ዓይነት ጠቃሚ ዲግሪና እንዲህ ዓይነት አገልግሎት ስላለኝ፥ ሊያከብሩኝና ጥሩ ደመወዝ ሊከፍሉኝ ይገባል። በተጨማሪም፥ በተለይ በወጣቱ ዘንድ ታዋቂ መሆን ስላለብኝ ምንም እንኳ ፕሮግራሞቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ባይመሠረቱም እነርሱ የሚወዷቸውን ፕሮግራሞች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጀመር አለብኝ» ሲል አሰበ። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንዳንድ ጊዜ የተመስገን አስተሳሰብ በሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚታየው እንዴት ነው? ለ) የዚህ ዓይነቱ አመላካከት በቤተ ክርስቲያን ላይ ምን ዓይነት ለውጥ ያመጣል? ሐ) 1ኛ ቆሮ. 4ን አንብብ። ጳውሎስና ተመስገን ለአገልግሎት ያላቸውን አመለካከት አነጻጽር። ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሪነትን በተመለከተ የተመስገንን ዓይነት አመለካከት ላላቸው መሪዎች ምን የሚል ይመስልሃል? ክርስቲያኖች በቀላሉ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስላለ አመራር የተሳሳተ መረዳት ሊኖራቸው ይችላል። በተሳሳተ መንገድ ሊረዱ ይችላሉ። ስለ መሪዎች የተሳሳቱ ሃሳቦችን ይዘው ከእገሌ ይልቅ እገሌን እከተላለሁ በሚሉ ምእመናን ምክንያት አንዳንድ ክፍፍሎች ተከስተዋል። አንዳንድ ጊዜም መሪዎቹ ራሳቸው ስለ ክርስቲያናዊ አመራር የተሳሳተ አመለካከት በመያዝ፥ ምእመኖቻቸው እንዲያከብሯቸውና እንዲከተሏቸው ይሻሉ። ይህ ሰይጣን ክርስቲያኖች እንደ እግዚአብሔር ጥበብ ሳይሆን እንደ «ዓለም ጥበብ» እንዲያስቡ ለማድረግ የሚጠቀምበት አንድ አቅጣጫ ነው። ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያንን መሪዎች ራሳቸውን እንደ ባሪያዎች እንዲመለከቱ በግልጽ አሳስቧል (ማቴ. 20፡24-28 አንብብ።) ነገር ግን ብዙውን ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የዓለምን ምሳሌነት በመከተል ራሳቸውን እንደ አለቆች ይቆጥራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን የሚያተኩረው በአገልጋይ መሪዎች አገልግሎት ላይ ነው። ሰይጣን ግን ብዙውን ጊዜ መሪዎች በሥልጣንና ክብር ላይ እንዲያተኩሩ ያደርጋል። መሪዎቿ ወይም ምእመናኖቿ ስለ አመራር ተገቢውን ግንዛቤ ካልጨበጡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለትልቅ አደጋ ትጋለጣለች። ለዚህ ነው ጳውሎስ አመራር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምን እንደሚመስል የጻፈው። የቤተ ክርስቲያን አመራር ከዓለማዊ አመራር ሙሉ በሙሉ የሚቃረን ስለሆነ፥ ይህንን ትምህርት መገንዘቡ ጠቃሚ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን እንጂ በአስተዳደር ዘዴዎች፥ በትምህርትና በሥልጠና ላይ የሚያተኩረውን የዛሬውን ዘመን የዓለም የአመራር ጥበብ እንዳንከተል መጠንቀቅ አለብን። ጳውሎስ ስለ መሪነት የሚከተሉትን እውነቶች አመልክቷል። ሀ. መሪዎች እንደ ጳውሎስና አጵሎስ የክርስቶስ ባሪያዎች ሲሆኑ፥ የእግዚአብሔርን እውነት በአደራ የተረከቡ ናቸው። መሪዎች ማንን የማክበር ኃላፊነት እንዳለባቸው ማወቃቸው በጣም ጠቃሚ ነው። የመሪዎቹ ጌታ የሽማግሌዎች ቦርድ ወይም አውራጃ ሳይሆን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ለአመራር ተግባራቸውም በኃላፊነት የሚጠይቃቸው ክርስቶስ ነው። ሽማግሌዎችን ለማስደሰት የሚሠራ መሪ የሽማግሌዎች ባሪያ ነው። ምእመናኑን ለማስደሰት የሚሠራ መሪ የቤተ ክርስቲያኒቱ ባሪያ ነው። ዋነኛው ፍላጎታችን ክርስቶስን ማስከበር በሚሆንበት ጊዜ የእርሱ ባሪያዎች እንሆናለን (ገላ. 1፡10ን አንብብ።)። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አንድ ዐቢይ አገልግሎት አላቸው። የእግዚአብሔር እውነት ተሰጥቷቸዋል። ይህንን እውነት ሊያውቁ፥ ሊኖሩትና ሊሰብኩት ይገባል። ጳውሎስ ብዙ ክርስቲያኖችና የማያምኑት ስለማያውቁት «የእግዚአብሔር ምሥጢር» የሚለውን ይህንኑ የእግዚአብሔርን ቃል እውነት መሪዎች በአግባቡ መጠቀማቸው ወሳኝ ነው። እግዚአብሔር በኃላፊነት የሚጠይቃቸው በዚህ ተግባራቸው ነውና። መሪዎች እንደ ጥሩ አኗኗር፥ ተጨማሪ እውቀት፥ ጥሩ ደመወዝ፥ የፈውስ አገልግሎት፥ የማኅበረሰቡን ተወዳጅነት በመሻት፥ ወዘተ… ከኃላፊነታቸው ሊዘናጉ ይችላሉ። እነዚህ ነገሮች የእግዚአብሔርን ቃል ምሥጢራት ከማካፈል ካደናቀፉአቸው የመሪነት ተግባራቸውን ሊወጡ አልቻሉም ማለት ነው። ሰዎችን የሚያስደንቅ የጸጋ ስጦታ ያላቸውም ሆኑ ተራ የሚመስሉ መሪዎች በእኩል ደረጃ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው። ስለሆነም አንዱን በመውደድና ሌላውን በመጥላት መሪዎችን የማወዳደር መብት የለንም። ለ. እግዚአብሔር ከመሪዎች የሚፈልገው ዋናው በሕርይ ታማኝነት ነው። የአንድ መልካም መሪ ዋነኛ ባሕርይ ጥበብ፥ የባሕርይ ጽናት፥ ጥሩ የጊዜ አጠቃቀም ወይም የአመራርና አስተዳዳር ችሎታ አይደለም። ጳውሎስ ታማኝነት ከሁሉም እንደሚበልጥ ያስረዳል። ለቤተ ክርስቲያን፥ ለሽማግሌዎች ታማኝ መሆኑ አስፈላጊ ነው። ከሁሉም በላይ ግን እግዚአብሔር የወንጌሉን እውነት እንዲሰብኩ የሰጣቸውን «አደራ» በመወጣት መሪዎች ታማኝነታቸውን ማረጋገጣቸው ወሳኝ ነው። ሐ. ዋናው ነገር የመሪው ታዋቂነት አይደለም። ጳውሎስ ውጤታማነቱን የለካው የቆሮንቶስ አማኞች ታላቅ መሪ ነው ብለው በማሰባቸው ላይ ተመሥርቶ አልነበረም። ነገር ግን እግዚአብሔር በሰጠው ችሎታና ስጦታ አማካኝነት ጥሪውን በትክክል ለመፈጸሙ ሕሊናው ይመሰክርለት ነበር። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ምስጋናም ሆነ ወቀሳ አገልግሎትን ለመመዘን የሚጠቅም ዋነኛ ጉዳይ ነው የሚል ግምት አልነበረውም። ይህ ዘላለማዊ ሁኔታውን ሊለውጥ አይችልም ነበር። ነገር ግን ጳውሎስ የወንጌሉን እውነት በመስበኩ በኩል ምን ያህል የታማኝነት ተግባር እንዳከናወነ በዘላለም ፈራጅ ፊት የሚመዘን መሆኑን ያውቅ ነበር። ዋናው ነገር ደግሞ ይሄ ነበር። እግዚአብሔር ሰዎች የሚመለከታቸውን ውጫዊ ነገሮች (ርቱዕ አንደበት፥ የሰዎችን ስሜት ማስደሰት፥ ታዋቂነት፥ ትምህርት) አልፎ ልብን ያያል። ከመሪዎች ተግባር በስተጀርባ ያለውን የተነሣሽነት ምክንያት ያያል። እግዚአብሔር እንዲያከብረን የማያደርጉት ወይም የሚያደርጉት እነዚህ የተነሣሽነት ምክንያቶች እንጂ ሰዎች የሚመለከቷቸው ውጫዊ ተግባራት አይደሉም። መ. ለሁሉም ክርስቲያኖችና መሪዎች ስጦታዎችን የሚሰጣቸው እግዚአብሔር ነው። ችሎታውን ያገኙት የበለጠ ስለተማሩ፥ የበለጠ መንፈሳውያን ስለሆኑ፥ ተግተው ስለሚሠሩ ወይም ከሌላው ሰው የተለዩ ስለሆኑ አይደለም። ስለሆነም በችሎታቸው ወይም በታዋቂነታቸው ሊመኩ አይገባም። ከእነርሱ ያነሰ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች መናቅ የለባቸውም። ከእነርሱ የበለጠ ችሎታ ባላቸው ሰዎችም ላይ ሊቀኑ አይገባም። ሀ. የቤተ ክርስቲያን መሪነት መንገድ ብዙውን ጊዜ ብዙ ጥቅሞችን ሳይሆን ብዙ ሥቃዮችን ያስከትላል። ጳውሎስ የራሱን ሕይወት ከቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሕይወት ጋር አነጻጽሯል። ጳውሎስ ከአሥራ ሦስቱ እጅግ ወሳኝ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች አንዱ የሆነ ሐዋርያ ነበር። ነገር ግን በጦርነት ከተማረኩ በኋላ ሕዝብ እንዲያያቸውና በኋላም እንዲገደሉ ወደ ስታድዬም እንደሚወሰዱ የዘመኑ ወታደሮች ፥ እርሱም ለመሳለቂያነት መዳረጉን ያስረዳል። ጳውሎስም ሆነ ሌሎች ሐዋርያትና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የመከራ ሕይወት ከመግፋት አልፈው እንደ ጠቢብና ባለጸጋ ሊከበሩ አልቻሉም ነበር። ሰዎች እንደሚያሳድዷቸውና እንደሚቀልዱባቸው ለማኞች ነበሩ። በአንጻሩ፣ የቆሮንቶስ አማኞች ቀላልና ምቹ ሕይወት ይመሩ ነበር። ብዙ ገንዘብ ነበራቸው። ልጆቻቸው የተሻለ የትምህርት ዕድል ያገኙ ነበር። የተሻለ ቤት፥ የተሻለ ገቢ፥ ወዘተ… ነበራቸው። ጳውሎስ ይህ ትክክክል አይደለም እላለም። እርሱ የሚለው መሪዎችና መእመናን አብረው ሊያድጉ ይገባል ነው። የቤተ ክርስቲያን ምእመናን ለመሪዎቻቸው በቂ ደመወዝ እለመክፈላቸውና እነርሱ እየበለጸጉ መሪዎች በኑሮ ሲቸገሩ ይሄ ለእግዚአብሔር ነገሮች ብዙም ትኩረት አለመስጠታቸውን ያሳያል። በሌላ በኩል፥ መሪዎቹ ከምእመናን የበለጠ ደመወዝ ማግኘታቸውና ምእመኖቻቸው የገንዘብ ችግር እያጋጠማቸው እነርሱ እየከበሩ መሄዳቸው ይሄም በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ትክክል አይደለም። ነገር ግን የመሪነት ወይም የወንጌላዊነት ሕይወት ተጨማሪ በረከትን ሳይሆን ተጨማሪ ሥቃይን እንደሚያስከትል ጳውሎስ ከራሱ ሕይወት ጠቅሶ አስረድቷል። ይህም ሙሉ ለሙሉ መጥፎ አይደለም። ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያን አመራር ከከባድ ሥቃይ ይልቅ ብዙ ጥቅም የሚያስገኝ ቢሆን ኖሮ ሰዎች የተሳሳቱ ምክንያቶች እያቀረቡ መሪዎች ለመሆን ይፈልጉ ነበር። ረ. አብያተ ክርስቲያናት ለመሪዎች፥ በተለይም እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ለመትከል ለሚጠቀምባቸው አገልጋዮች ልዩ ክብር መስጠት አለባቸው። የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የበለጠ ስጦታ ያለው ሰባኪ በሚመጣበት ጊዜ በእርሱ ላይ ከመሳለቅ ይልቅ ጳውሎስን ማክበር ነበረባት። ሰ. መሪነት በቀዳሚነት ተግባራዊ የሚሆነው ከቃላት ይልቅ በሕይወት ምሳሌነት ነው። ብዙውን ጊዜ የተማሩ ወጣቶች ለመሪነት ይሾማሉ። ነገር ግን የክርስቶስ አርአያ ለመሆን የሚያበቃ ብስለት የላቸውም። ስለሆነም፥ ስለ መሪነት የተሳሳቱ አመለካከቶችን በሚያንጸባርቁበት ጊዜ ልንፈርድባቸው አይገባም። ለመሪነት ወሳኙ ቅድመ ሁኔታ መንፈሳዊ ብስለት ሲሆን፥ ይህም ብዙ ጊዜ የሚወስድ ሂደት ነው። ጳውሎስ ልቡም ሆነ ተግባራቱ ትክክል መሆናቸውን ስለሚያውቅ፥ «እኔን ምሰሉ» ለማለት ችሏል (1ኛ ቆሮ. 4፡16)። ምእመኖቻችን መንፈሳውያን እንዲሆኑ፥ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድጉ፥ እንዲቀደሱና ስለ አመራር ተገቢውን ግንዛቤ እንዲያገኙ ከፈለግን እኛ መሪዎች ይህንን እንዴት እንደሚያከናውኑ ማሳየት አለብን። በራስ ወዳድነትም ይሁን ለእግዚአብሔር ክብር አመራር በምንሰጥበት ጊዜ የእኛን ምሳሌ ይከተላሉ። ሸ. ጳውሎስ ሐዋርያ እንደ መሆኑ «በትር» ሲል የገለጸው ልዩ ሥልጣን ነበረው። ጳውሎስ ይህን ሥልጣኑን በዓመፀኞች የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ላይ ፍርድን ለማምጣት ሊጠቀም እንደሚችል ገልጾአል። ነገር ግን

የሐዋርያትን ምሳሌነት በመከተል መከፋፈልን ማስወገድ (1ኛ ቆሮንቶስ 4፡1-21) Read More »

ክፍፍል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ (1ኛ ቆሮ. 1፡10-4፡21)

ጳውሎስ በመልእክቱ ውስጥ ያነሣው የመጀመሪያው ዐቢይ ጉዳይ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለተከሰተው ክፍፍል ነበር (1ኛ ቆሮ. 1-4)። ጳውሎስ ክፍፍል፥ በተለይም የተወሰኑ መሪዎችን በመከተል የሚፈጠር ክፍፍል የዓለምን ጥበብ እንደሚያሳይ፥ የአማኞችን አለመብሰል እንደሚያመለክትና የመሪነትን ጽንሰ አሳብ በተሳሳተ መንገድ መረዳታቸውን እንደሚያስረዳ ገልጾአል። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መከፋፈል መኖሩን ገለጸ (1ኛ ቆሮ. 1፡10-17)። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበው የመጨረሻው የክርስቶስ ጸሎት ስለ አማኞች አንድነት የቀረበ ነው (ዮሐ 17)። ጳውሎስ ጠንካራ እገላለጾችን በመጠቀም የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በሃሳብና በተግባር አንድነት በመመሥረት ይህንኑ ጸሎት እውን እንዲያደርጉ ጠይቋል። ይህ ግን ጳውሎስ ሰዎች ሁሉ በሁሉም ነገር ተመሳሳይ አሳብ እንዲይዙ መፈለጉን አያሳይም። ነገር ግን ጠቃሚ በሆነው ጉዳይ ላይ እንዲያተኩሩ፥ ማለትም አንድነትን ለመፍጠር እንዲቆርጡና አብረው እንዲሠሩ ይፈልጋል። ክርስቲያኖች በተለያዩ ነገሮች ላይ ይከፋፈላሉ። አንዳንድ ጊዜ በአነስተኛ የአስተምህሮ ጉዳዮች፥ ሌላ ጊዜ ደግሞ በዘርና በጎሳ፥ ወይም አንዱ ቡድን ሌላውን በሆነ መንገድ በመጉዳቱ ምክንያት እንከፋፈላለን። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የተከፋፈሉበት ምክንያት የተለያዩ ታዋቂ መሪዎችን በሞዴልነት ለመከተል በመፈለጋቸው ነበር። (ይህም ሰዎች እንደ ሮናልዶ ዓይነቱን ስፖርተኛ ወይም እንደ ቦንኬ ዓይነቱን ሰባኪ ወይም የፈውስ አገልጋይ በቲፎዞነት ከሚከተሉበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው።) እነዚህ ክርስቲያኖች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ታላቁ መሪ ማን እንደሆነና ማንን ለመከተል እንደሚፈልጉ ይከራከሩ ነበር። አንዳንዶች የቤተ ክርስቲያኖቻቸው መሥራችና ታላቅ የአሕዛብ ሐዋርያ የነበረውን ጳውሎስን ተከተሉ። ሌሎች ጳውሎስ በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው መጨረሻ ከቆሮንቶስ ከወጣ በኋላ መጥቶ ሲያገለግል የነበረውንና በአንደበተ ርቱዕነት የሚታወቀውን አጵሎስን ተከተሉት። የአይሁድ ክርስቲያኖች የቤተ ክርስቲያን መሥራችና የአይሁዶች ሐዋርያ የነበረውን ኬፋን (የጴጥሮስ አይሁዳዊ ስም) ተከተሉት። አንዳንድ ምሁራን ይህ ጴጥሮስ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለማገልገል እንደመጣ ያሳያል ይላሉ። በመጨረሻም፥ በጣም መንፈሳውያን ነን የሚሉት ደግሞ የክርስቶስ ተከታዮች መሆናቸውን ገለጹ። የውይይት ጥያቄ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከከርስቶስ ይልቅ በሰብአዊ መሪ ላይ ሲያተኩሩ የተመለከትከው እንዴት ነው? ጳውሎስ የትኛውንም ሰብአዊ መሪ መከተሉ ትክክል እንዳልሆነ ገልጾአል። የበለጠ የስብከት ስጦታ አለው የሚባለውን አገልጋይ ለማግኘት ከቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን መዟዟሩ ትክክል አይደለም። ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ የሚያመጣ ይመስል ታላቅ የፈውስ አገልጋይ በሄደበት ሁሉ መዞሩም ተገቢ አይሆንም። ይህንን በምናደርግበት ጊዜ ሰይጣን ዓይኖቻችንን ከክርስቶስ ላይ አንሥተን ኃጢአተኛ፥ ደካማና ፍጹም ባልሆነ የሰው ልጅ ላይ እንድናሳርፍ አድርጓል ማለት ነው። ጳውሎስ አሉታዊ ምላሽ የሚያስገኙ ጥያቄዎችን በማንሣት እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ትክክል አለመሆኑን ያሳያል። ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካልና አንድ ክፍል ነች። የክርስቶስ አካል እንዴት ሊከፋፈል ይችላል? ጳውሎስ ለኃጢአታቸው አልተሰቀለም ነበር። በእርሱ ስምም አልተጠመቁም ነበር (ጳውሎስ ሰዎች በእርሱ ስለመጠመቃቸው በትምክሕት እየተናገሩ ከክርስቶስ ይልቅ እርሱን እንዳይከተሉት በማሰብ ብዙዎችን ከማጥመቅ እንደ ተቆጠበ ገልጾአል። ይህም ዛሬ አንዳንድ ክርስቲያኖች በተሳሳተ መልኩ ከሚያስተምሩት በተቃራኒ ጳውሎስ የውኃ ጥምቀት ለድነት (ደኅንነት) አስፈላጊ ነው ብሎ እንዳላሰበ ያሳያል። እንደዚያ ዓይነት አመለካከት ቢኖረው ኖሮ፥ ወደ ክርስቶስ የመለሳቸውን ሰዎች በሙሉ ራሱ ባጠመቃቸው ነበር።) መንፈሳዊ ስጦታ ባለው መሪ ላይ ትኩረት በምናደርግበት ጊዜ ሁሉ የሰውን ጥበብ ተከትለናል ማለት ነው። በዓለም የሚታየው ይኸው ነውና። በሰዎች ላይ በምናተኩርበት ጊዜ ደግሞ ከክርስቶስ መስቀል ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ ከመሻት እንታቀባለን። ስለ ዓለማዊ ጥበብና በክርስቶስ መስቀል በተገለጠው መንፈሳዊ ጥበብ መካከል ያለውን ልዩነት ጥርት አድርጎ አለማወቅ ክፍፍልን ያስከትላል (1ኛ ቆሮ. 1፡18-2፡16)። ስሕተት የሆነው ነገር እንደ አስፈላጊ ነገር አጽንኦት ሲሰጠው ዓለማዊ ጥበብ ይንጸባረቃል። ሀ. ዓለማዊ ጥበብ በሰው አንደበተ ርቱዕነት ምክንያት፥ በማቅረብ ችሎታውና ሰዎችን የሚያስደስቱ ጥበቦችን በመጠቀም ብቃቱ ላይ ያተኩራል። ጳውሎስ ይህን «የሰው የቃል ጥበብ» ይለዋል (1ኛ ቆሮ. 1፡17)። ይህ ጥበብ በእውነት፥ በሚነገረው መልእክት፥ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በመስማማቱ ወይም እግዚአብሔር የሚፈልገውን በማብራራቱ ላይ እያተኩርም። ይህ ጥበብ የሚያተኩረው በንግግር ችሎታው፥ ሰዎችን ለመሳብና ስሜቶችን ለማነሣሣት በመቻሉ ላይ ነው። ለ. ዓለማዊ ጥበብ የተማሩ ሰዎች በሚወዷቸው ነገሮች ላይ ያተኩራል፡፡ የተማሩትና የሠለጠኑት ግሪኮች እውቀታቸውን በሚያሳዩበት ጥበብ ላይ አጽንኦት ያደርጉ ነበር። ዛሬ ብዙ ሰዎች፥ «ምን ያህል እንደተማርህ አሳየን፤ አስደናቂ ቃላትን ተጠቀም፣ እንግሊዝኛም እየቀላቀልህ ተናገር፤ አሳቦችን ውስብስብ አድርግ» ሲሉ የዓለማዊ ጥበብን ዝንባሌ ያሳያሉ። ጳውሎስ አብዛኛው የዓለም የፍልስፍና ትምህርት ወንጌሉን እንደሚቃወምና የእግዚአብሔርን ጥበብ እንደማይቀበል አስረድቷል። ሐ. ዓለማዊ ጥበብ ሰዎችን ለሚያስደንቁ ነገሮች ትኩረት ይሰጣል። አይሁዶች የታላቅነት ዐቢይ ማረጋገጫው ተአምር ማድረግ ነው ብለው ያስቡ ስለነበረ ሁልጊዜም ተአምራዊ ምልክቶችን ይፈልጉ ነበር። «ተአምር እሳየንና እንከተልሃለን። ተአምር አድርግና ወደ ስብሰባህ እንመጣለን።» ስለሆነም፥ ተአምራትን እንደሚያሳዩ ቃል የሚገቡና ሥጋዊ ጥቅም የሚሰጡ ሰዎች በአይሁዶች ዘንድ እጅግ ተወዳጆች ነበሩ። ይህ ከዛሬው ዘመን ጋር ይመሳሰላል? የውይይት ጥያቄ፡- ዛሬ ክርስቲያኖች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በዚሁ ዓለማዊ ወጥመድ የሚጠመዱት እንዴት ነው? የእግዚአብሔር ጥበብ ከዓለም የጥበብ ትምህርት ተቃራኒ ነው። ሀ. የእግዚአብሔር ጥበብ በመስቀሉ ስብከት ላይ ያተኩራል። ዋናው ነገር የሰባኪው ማንነት ሳይሆን፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ መምጣቱና እውነት መሆኑ ነው። ለ. መለኮታዊ ጥበብ ሰዎች እንደ ታላቅ ነገር ከሚመለከቱት ጋር ይቃረናል። ዓለም መስቀል የሽንፈት ስፍራ እንደሆነ ታስባለች። የነፍሰ ገዳዮች መቀጫ የሆነው መስቀል ለሰው ልጆች ችግሮች መፍትሔ የሚሆነው እንዴት ነው? እግዚአብሔር ግን በጥበቡ የሞትን መሣሪያ ወደ ሕይወት መሣሪያነት በመለወጥ የሰውን ልጆች የኃጢአት ዋጋ በከፈለበት ቦታ የእርሱ ልጆች የሚሆኑበትን መንገድ ከፍቷል። ሐ የእግዚአብሔርን ጥበብ የሚረዳው ትሑቱ እንጂ ኩሩው አይደለም። ስለሆነም፥ ዝቅ ያሉ፥ ብዙ ትምህርት፥ ሀብት ወይም የዓለም ክብር የሌላቸው ሰዎች ናቸው ወንጌሉን ተረድተው የሚቀበሉት። የእግዚአብሔር መንግሥት በቀዳሚነት የተገነባው ዓለም በምትንቃቸው ሲሆን፥ ዓለም የምታከብራቸው ሰዎች የእግዚአብሔርን የድነት (ደኅንነት) መንገድ ለመቀበል ይቸገራሉ። መ. የእግዚአብሔር ጥበብ ከሰዎች፥ በተለይም የፖለቲካ፥ የትምህርትና የኢኮኖሚ መሪዎች ከሆኑት ወገኖች የተሰወረ ነው። ብዙውን ጊዜ ወንጌሉ ትሕትናን እንዴት እንደሚጠይቅ ለመረዳት የሚቸገሩ ሲሆኑ፥ ያላቸውን በረከት ትተው ሙሉ ለሙሉ ወደ እግዚአብሔር ድነት (ደኅንነት) ለመመለስ ይፈተናሉ። ይህ ለመሪዎች ከባድ ነው። የፖለቲካና የሃይማኖት መሪዎች ክርስቶስ እንዲሰቀል የጠየቁት ለዚህ ነበር። ሠ. በክርስቲያኖች ውስጥ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ፍላጎት፥ አሳብና አመለካከት ያውቃል። እውነተኛ መንፈሳዊነት ያላቸው ሰዎች ራሳቸውን ለመንፈስ ቅዱስ የሚሰጡና እርሱም በሰዎች፥ በትምህርት ወይም በኃይልና በመሳሰሉት ላይ ሳይሆን በድነትና እግዚአብሔርን በማስከበር ላይ የሚያተኩረውን ጥበብ እንዲገልጥላቸው የሚፈቅዱት ብቻ ናቸው። ረ. የእግዚአብሔር ጥበብ የመንፈሳዊ ጥበብ መለያ ነው። ክርስቲያኖች በሚጣሉበት ጊዜ ወይም ከክርስቶስ ይልቅ ሰዎችን በሚከተሉበት ወቅት የእግዚአብሔር ጥበብ እንደሌላቸው ያሳያል። መንፈሳዊ ብስለት ቢኖራቸው ዓለማዊ ጥበብ (ዓለም ዋጋ የምትሰጣቸው ነገሮች) ለዘላለማዊ መንግሥትና ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር የሚስማማ ሕይወት እንዲመሩ ለማድረግ እንደማይጠቅም ባወቁ ነበር። ሰ. የእግዚአብሔር ጥበብ ከትምህርት አይገኝም። ይህ እግዚአብሔር ለሰዎች የሚገልጠው ነው። ጳውሎስ ድነትን (ደኅንነትን) ያላገኙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ሊረዱ አይችሉም ማለቱ አይደለም። ያልዳነ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን እንብቦ ቃላቱን ሊረዳ ቢችልም፥ እውነቱ ከሕይወቱ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ግን አያውቅም። የእግዚአብሔር ጥበብ፥ ትሑቱን ሲሸልም ኩሩውን ግን ይፈርድበታል፥ በእግዚአብሔር የሚታመነውን ሲያድን በራሱ የሚታመነውን ይኮንነዋል። መስቀሉ ድነትን (ደኅንነትን) እንዲያመጣ ሲያደርግ የሰው ፍልስፍናን አታላይነት ያሳያል፥ ሌሎችን ማገልገል እንደሚያስከብርና ራስን ማገልገል እንደሚያዋርድ ያሳያል። ሸ. ዓለም ሞኝነትና ጥበብ የሆነውን እንደምታውቅ ብታስብም፥ ትክክል የሆነውንና ያልሆነውን፥ ዘላለማዊውንና በዚህ ዓለም ብቻ የተወሰነውን፥ እንዲሁም እውነተኛውንና እውነተኛ ያልሆነውን ጥበብ በግልጽ ሊረዱ የሚችሉት የእግዚአብሔር ጥበብ ያላቸው ብቻ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያውቁና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለመከተል የወሰኑ ሰዎች «የክርስቶስ ልብ» ስላላቸው፥ ጠቢባን ብቻ ሳይሆኑ ጠቅላላ ሕይወታቸውን እግዚአብሔርን ለማስከበርና ለዘላለማዊ ሕይወት በሚያዘጋጃቸው መልኩ የሚኖሩ ናቸው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከምታውቃቸው ሰዎች መካከል በዓለም ጠቢባን ላይባሉ ቢችሉም፥ በአኗኗራቸው መለኮታዊ ጥበብን የሚገልጹትን ሰዎች ዘርዝር። ለ) ሕይወታቸው በሌሎች ሰዎች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምንድን ነው? ጳውሎስ ዘላለማዊ መፍትሔዎች የሚገኙት በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት የተገለጠውን የእግዚአብሔርን

ክፍፍል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ (1ኛ ቆሮ. 1፡10-4፡21) Read More »

መግቢያ፡- (1ኛ ቆሮ. 1፡1-9)

ጳውሎስ የመጽሐፉ ጸሐፊ መሆኑን ይናገራል (1ኛ ቆሮ. 1፡1)። ሰላምታው በእግዚአብሔር የተመረጠ ሐዋርያ መሆኑን ያመለክታል። ጳውሎስ የክርስቶስ ወኪል ሆኖ ስለሚናገር፥ የቆሮንቶስ አማኞች በጥንቃቄ ሊሰሙት ይገባ ነበር። ምሁራን የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ይህንን መልእክት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ማካተቷ ጳውሎስ የእግዚአብሔር ቃል አቀባይ ሆኖ መናገሩን እንደሚያሳይ ያስረዳሉ። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መጻፉን ገልጾአል (1ኛ ቆሮ. 1፡2-3)። ብዙውን ጊዜ የጳውሎስ መግቢያ የደብዳቤውን ትኩረት ያሳያል። ለዚህም ነው በሮሜ መልእክቱ ወንጌል ላይ ያተኮረው። በዚህ ክፍል ጳውሎስ የመልእክቱ ዓላማ ስለ ቅድስና ማብራራት እንደሆነ ገልጾአል። እግዚአብሔር በክርስቶስ የሚያምኑትን ሁሉ ቅዱሳን ብሎአቸዋል። ይሁንና፥ በአኗኗራችን ይህንኑ ቅድስና ማሳየት አለብን። ጳውሎስ የቆሮንቶስን አማኞች ያመሰግናቸዋል (1ኛ ቆሮ. 1፡4-9)። አብዛኛዎቹ ጥንታዊ ደብዳቤዎች የሚጀምሩት በምስጋና ወይም ጸሐፊው ስለ አንባቢዎቹ እንደሚያስብ በሚያሳዪ ቃላት ነበር። በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ችግሮች ቢኖሩም ጳውሎስ ተስፋ አልቆረጠም ነበር። በአንጻሩ ጳውሎስ እግዚአብሔርን በቆሮንቶስ አማኞች ሕይወት ውስጥ ስለሚሠራው ሥራ ያመሰግነዋል። እግዚአብሔርን ያመሰገነባቸው ምክንያቶችም የሚከተሉት ናቸው። ሀ. ለቆሮንቶስ ቤተ ክርቲያን ስለ ሰጠው ብዙ በረከት። ምንም እንኳ አማኞቹ ከእነዚህ ስጦታዎች ብዙዎቹን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ቢጠቀሙም፥ ስጦታዎቹ ያው የእግዚአብሔር በረከቶች ነበሩ። ከስጦታዎቹ አንዱ የንግግርና የእውቀት ችሎታ ነበር። ችግሩ እማኞቹ ትክክል ባልሆነ እውቀት (ጥበብ) እና በመንፈሳዊ ኩራት ላይ ማተኮራቸው ነበር። ሌላው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታዩ መንፈሳዊ ስጦታዎች ነበሩ። ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ ሊሰጣቸው ከፈለገው ስጦታዎች እንድም እንዳልጎደለባቸው ገልጾአል። አሁንም ችግራቸው ለተወሰኑ መንፈሳዊ ስጦታዎች የነበራቸው አመለካከትና ለሰዎች ሁሉ ከማገልገል ይልቅ ለራስ ወዳድነት ዓላማ ለማዋል መፈለጋቸው ነበር። ለ. የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን መመለስ ይጠባበቁ ነበር። የሚያስቡትም በዚህ ዓለም ውስጥ እንዴት እንደሚኖሩ፥ እንዴት ብዙ ሀብት፥ ብዙ መሬት የተሻለ ሥራ ወይም ትምህርት እንደሚያገኙ አልነበረም። ዓይኖቻቸውና ልባቸው በኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት ላይ ነበር። ነገር ግን የዚያን መጭ መንግሥት አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮች በተለይም የሙታንን ትንሣኤና በምድር ላይ እያሉ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት አካል ሆነው የሚኖሩበትን ሁኔታ በተሳሳተ መልኩ ነበር የተረዱት። ሐ. ጳውሎስ እግዚአብሔር በልጆቹ ሕይወት ውስጥ ለሚያከናውነው በትዕግሥት የተሞላና ዳሩ ግን ጥብቅ የሆነ ተግባር ልበ ሙሉነት ይሰማው ነበር። እኛ በኃጢአትና በራስ ወዳድነት የተሞላን፥ መንፈሳዊ ብስለትም የጎደለን ልንሆን እንችላለን። ጳውሎስ ግን በእግዚአብሔር ባሕርይ ምክንያት ልበ ሙሉነት ይሰማዋል። እግዚአብሔር ታማኝ ነው። እያንዳንዱን አማኝ ስለመረጠ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት በምንቆምበት ጊዜ እንከን የለሽ እንሆን ዘንድ በሕይወታችን ውስጥ ይሠራል። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደ መሆናችን፥ ይህንን ማስታወስ አለብን። ብዙውን ጊዜ ዓይኖቻችን የሚያርፉት በአብያተ ክርስቲያኖቻችን ድክመቶችና በክርስቲያኖች ችግሮች ላይ ነው። ጳውሎስ በእግዚአብሔር ላይ ስላተኮረና በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ በሚያከናውነው ተግባር ላይ ልበ ሙሉነት ስለተሰማው፥ ዐበይት የቤተ ክርስቲያን ችግሮች በሚታዩበት ጊዜ ሳይቀር በመተማመን ይመላለስ ነበር። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉትን ችግሮች ዘርዝር። ለ) በእነዚህ ችግሮች ላይ ማተኮር ተስፋ መቁረጥን ወይም ፍራቻን እንዴት ሊያስከትል እንደሚችል ግለጽ። ሐ) እግዚአብሔር በግለሰቦችና አብያተ ክርስቲያናት ሕይወት በመሥራት ስሙን ሊያስከብር በመቻሉ ላይ ብናተኩር አመለካከታችን እንዴት ይቀየራል? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

መግቢያ፡- (1ኛ ቆሮ. 1፡1-9) Read More »

የ1ኛ ቆሮንቶስ ልዩ ባሕርያት፣ መዋቅር እና ርእሰ ጉዳዮች

፩. የ1ኛ ቆሮንቶስ ልዩ ባሕርያት አብዛኛው የ1ኛ ቆሮንቶስ ክፍል የተለመደው ዓይነት ደብዳቤ ሳይሆን ችግሮችን የሚያንጸባርቅ ሆኖ እናገኘዋለን። ስለሆነም፥ ከዳር እስከ ዳር ጎልቶ የሚታይ ጭብጥ ከመያዝ ይልቅ (የሮሜ መልእክት በድነት ላይ እንደሚያተኩር)፥ የቆሮንቶስ መጽሐፍ በቤተ ክርስቲያኒቱ ችግሮችና ጥያቄዎች ላይ ያተኩራል። 1ኛ ቆሮንቶስን ማንበብ አንድ ሰው በስልክ ሲነጋገር እንደ መስማት ነው። ከአጠገባችን ያለው ሰውዬ የሚናገረውን ልንሰማ ብንችልም፥ ከሌላኛው የስልኩ ጫፍ ያለው ግለሰብ የሚያነሣቸውን ጥያቄዎች ወይም ሃሳቦች ልንሰማ አንችልም። ስለሆነም፥ የዚያ ሰውዬ ጥያቄዎችና የነበረበት ሁኔታ ምን ዓይነት እንደሆኑ መገመት ይኖርብናል። በ1ኛ ቆሮንቶስ፥ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ችግሮች የሰጣቸውን መልሶች ብንመለከትም፥ ችግሮቹ የተነሡባቸውን ዝርዝር ሁኔታዎች ግን አናውቅም። ለምሳሌ፥ ጳውሎስ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን እንዳይናገሩ ወይም ራሶቻቸውን እንዲከናነቡ ያዘዘው ለምን ነበር? ይህ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ አንድ ችግር እንደነበረ ቢያሳይም፥ በትክክል ምን እንደሆነ አናውቅም። ጳውሎስ ምላሽ የሚሰጠው ለእንደነዚህ ዓይነት በጊዜው ለተከናወኑ ዝርዝር ጉዳዮች በመሆኑ፥ ይህን ክፍል በምንተረጉምበትና ከቤተ ክርስቲያናችን ጋር በምናዛምድበት ሁኔታ ላይ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል። ዛሬ የምንጋፈጣቸው ችግሮች ከቆሮንቶስ የተለዩ ሊሆኑ ስለሚችሉ፥ የጳውሎስ ዝርዝር ትምህርቶች ከዛሬው ሁኔታችን ጋር እንደሚስማሙ ከመገመት ይልቅ መርሆችን መፈለግ ይኖርብናል። ለምሳሌ፥ ዛሬ ሴቶች ጸጉራቸውን መሸፈናቸው የተለየ ዓላማ ካለውና በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የተከሰተውን ዓይነት ሁኔታ የማያስከትል ከሆነ፥ ዛሬም ይህንኑ ደንብ መከተል አለብን? ብዙ ክርስቲያኖች የለብንም ይላሉ። ፪. የ1ኛ ቆሮንቶስ መዋቅር የ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክት በሁለት ዐበይት ክፍሎች ይከፈላል። በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ ከቆሮንቶስ ሊጎበኙት ከመጡት ሰዎች የሰማቸውን ጉዳዮች በማስመልከት ከምዕራፍ 1-6 ያለውን አሳብ ጽፎአል። ጳውሎስ ከዚህ ቃላዊ ዘገባ ተነሥቶ ስለ ክፍፍል፥ በጥበብ ላይ ስለሚደረግ የተጋነነ ትኩረት፣ ስለ ራሱ ሐዋሪያዊ ሥልጣን፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሚታይ ወሲባዊ እርኩሰትና ስለ አማኞች መካሰስ ምላሽ ሰጥቷል። የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 1፡11፥ 19፤ 5፡1፤ 6፡1፤ 7፡1፤ 8፡1፤ 11፡3፤ 12፡1፤ 15፡1፤ 16፡1 አንብብ፡ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የዘገባና የደብዳቤ ምላሽ በመስጠት ያነሣቸውን ጉዳዮች ዘርዝር። ሁለተኛ፥ 1ኛ ቆሮንቶስ 7-16 የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ለጳውሎስ ባቀረቧቸው የተወሰኑ ጥያቄዎች ላይ ያተኩራል። (1ኛ ቆሮ 7፡1 አንብብ።) ጳውሎስ አዲስ ጉዳይ በሚጀምርበት ጊዜ «ስለ . . .» የሚል መስተዋድድ ስለሚጠቅም (1ኛ ቆሮ. 7፡1፥ 25፤ 11፡3፤ 12፡1፤ 16፡1)፥ የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥያቄዎችና መልሶች በቀላሉ መለየት ይቻላል። ጳውሎስ በምላሹ ስለ ጋብቻ፥ ለጣዖት የተሠዋን ሥጋ ስለ መብላት፥ ስለ ሴቶች አለባበስ፥ ስለ ቅዱስ ቁርባን፥ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች፥ ስለ አማኞች ትንሣኤና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ድሆች ስለሚሰጠው እርዳታ አብራርቷል። ፫. የ1ኛ ቆሮንቶስ ርእሰ ጉዳዮች I. መግቢያ (1ኛ ቆሮ. 1፡1-9) II. ክፍል አንድ፤ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዳሉ የተገለጹ ችግሮች (1ኛ ቆሮ. 1፡10-6፡20) የመጀመሪያው ችግር፤ የቤተ ክርስቲያን ክፍፍል (1ኛ ቆሮ. 1፡10-4፡21) ሀ. ጳውሎስ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ክፍፍል የመኖሩን እውነታ ያስተዋውቃል (1ኛ ቆሮ. 1፡10-17) ለ. ስለ ዓለማዊ ጥበብና በክርስቶስ መስቀል በተገለጠው የመንፈሳዊ ጥበብ መካከል ያለውን ልዩነት ጥርት አድርጎ አለማወቅ ክፍፍልን ያስከትላል (1ኛ ቆሮ. 1፡18-2፡14) ሐ. የተለያዩ ሰዎችን ከመከተል የሚመጣው ክፍፍል መሪዎችን እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች የሚያበረክቱትን ድርሻ በተሳሳተ መንገድ እንድንረዳ ያደርጋል (1ኛ ቆሮ. 3) መ. የሐዋርያነትን ምሳሌነት በመከተል ክፍፍልን ማሸነፍ (1ኛ ቆሮ. 4) ሁለተኛው ችግር፤ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሰተ የሥነ ምግባር ብልሹነት (1ኛ ቆሮ. 5፡1-12) ሦስተኛው ችግር፤ የአማኞች በችሎት ፊት መካሰስ (1ኛ ቆሮ. 6፡1-8) ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሚከሰት ወሲባዊ ኃጢአት ያቀረበው ተጨማሪ ትምህርት (1ኛ ቆሮ. 6፡9-20)። III. ክፍል ሁለት፤ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጥያቄዎች የሰጣቸው መልሶች (1ኛ ቆሮ. 7፡1-16፡4)። 1ኛ ጥያቄ፡- ክርስቲያን ሊያገባ ወይስ ብቻውን ሊኖር ይገባል? (1ኛ ቆሮ 7) ሁለተኛ ጥያቄ፡- ክርስቲያን ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ ሊበላ ይገባል? (1ኛ ቆሮ. 8-11፡1) ሀ. የመብላት ነጻነት ለሌሎች ክርስቲያኖች ባለን ፍቅር መወሰን አለበት (1ኛ ቆሮ. 8) ለ. ጳውሎስ ነጻነትን ስለ መገደብ ከራሱ ሕይወት የሰጠው ምሳሌ (1ኛ ቆሮ. 9) ሐ. ከብሉይ ኪዳን እስራኤላውያን ታሪክ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ (1ኛ ቆሮ. 10፡1-13) መ. በምግብ አማካኝነት የጣዖት አምልኮ ተካፋይ እንዳይሆኑ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ (1ኛ ቆሮ. 10፡14-22)። ሠ. ክርስቲያን ለሌላው ክርስቲያን ካለው ፍቅር የተነሣ ከምግብ ለመታቀብ ወይም ምግብ ለመብላት ስለሚኖረው ነጻነት ጳውሎስ የሰጣቸው ዝርዝር መመሪያዎች (1ኛ ቆሮ. 10፡23-11፡1)። ሦስተኛ ጥያቄ፡- ወንዶችና ሴቶች በአምልኮ ስብሰባ ላይ ምን ዓይነት ልብስ መልበስ ይኖርባቸዋል? (1ኛ ቆሮ. 11-14) አራተኛ ጥያቄ፡- በቅዱስ ቁርባን ላይ ሊኖር የሚገባው ትክክለኛ አመለካከት ምንድን ነው? (1ኛ ቆሮ. 11፡17-34)። አምስተኛ ጥያቄ፡- የመንፈሳዊ ስጦታዎች፥ በተለይም የልሳን ዓላማ ምንድን ነው? (1ኛ ቆሮ. 12-14)። ሀ. ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ይውሉ ዘንድ ለእያንዳንዱ ክርስቲያን የሚሰጡ የተለያዩ ስጦታዎች አሉ (1ኛ ቆሮ. 12)። ለ. መንፈሳዊ ስጦታዎችን የምንጠቀምበት ዓላማ ፍቅርና ለሌሎች ክርስቲያኖች ማሰብ ሊሆን ይገባዋል (1ኛ ቆሮ. 13)። ሐ. ትንቢት በልሳን ከመናገር ለምን እንደሚሻል (1ኛ ቆሮ. 14፡1-12)። መ. ስለ ልሳን፥ ትንቢትና በጉባዔ ውስጥ ስለሚደረግ የሴቶች ንግግር የተሰጠ መመሪያ (1ኛ ቆሮ. 14፡13-40)። ስድስተኛ ጥያቄ፡- አንድ አማኝ ከሞተ በኋላ ሥጋው ምን ይሆናል?(1ኛ ቆሮ. 15) ሰባተኛ ጥያቄ፡- የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች አይተዋቸው ለማያውቋቸው የአይሁድ ክርስቲያኖች ገንዘብ መስጠት ያለባቸው ለምንድን ነው? (1ኛ ቆሮ. 16፡1-4) IV. መደምደሚያ፡- (1ኛ ቆሮ. 16፡5-21) (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የ1ኛ ቆሮንቶስ ልዩ ባሕርያት፣ መዋቅር እና ርእሰ ጉዳዮች Read More »

የ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ዓላማ

ጳውሎስ በአብዛኞቹ ሌሎች መልእክቶቹ ውስጥ እንደሚያደርገው፥ በ1ኛ ቆሮንቶስ ውስጥ ለሥነ መለኮታዊ እውነቶች ትኩረት እልሰጠም። በመሆኑም፥ መጽሐፉን በሥነ መለኮታዊና ተግባራዊ ክፍሎች አልከፈለም። (ይህም ከሮሜና ከኤፌሶን መልእክቶች የተለየ ነው።) በ1ኛ ቆሮንቶስ ውስጥ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሚያጋጥሟት ችግሮች መፍትሔ በመጠቆሙ ሂደት ላይ ሁሉንም ሥነ መለኮታዊና ተግባራዊ እውነቶች ይዳስሳል። ጳውሎስ በንድፈ አሳባዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር የሥነ መለኮት ምሁር ሳይሆን፥ አማኞች እንደ ክርስቶስ ተከታዮች በእውነት ላይ ተመሥርተው እንዲኖሩ የሚሻ አገልጋይ ነበር። ጳውሎስ 1ኛ ቆሮንቶስን ከጻፈባቸው ምክንያቶች አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው። የመንፈሳዊ ብስለትን ምንነት ለማስረዳት። መንፈሳዊ ትኩሳት ወይም የጸጋ ስጦታዎች አንድ ክርስቲያን ወይም ቤተ ክርስቲያን በሳልና መንፈሳዊ ጤንነቱ የተሟላ መሆኑን በትክክል አያመለክቱም። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከፍተኛ የጸጋ ስጦታዎች እንደነበሯቸው መስክሯል። (1ኛ ቆሮ. 1፡5-7 አንብብ።) ነገር ግን ከሌሎች ጥንታዊያን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የባሰ መንፈሳዊ ትግል አድርገዋል። ስለዚህ ጳውሎስ ለእነዚህ ላልበሰሉና መንፈሳዊያን ላልሆኑ ክርስቲያኖች እንደ ክርስቶስ እንዴት ሊኖሩ እንደሚገባቸው በደብዳቤው ገለጾላቸው (1ኛ ቆሮ. 3፡1-4)። የአንድ ሰው ችሎታ ወይም መንፈሳዊ ስጦታዎች መንፈሳዊነቱን ሊገልጹ እንደማይችሉ ጳውሎስ አካፍሎአል። ይልቁን የአንድ ሰው መንፈሳዊ ብስለት ምልክቱ አንድነት፥ ፍቅርና ለሌሎች ክርስቲያኖች ግድ የሚለው ሲሆን ነው። ጳውሎስ የተወሰኑ ችግሮችን ማለትም እንደ መከፋፈልና ልቅ የግብረ ሥጋ ግንኙነት በተመለከተ ከቤተ ክርስቲያን በደረሰው መረጃ መሠረት መንፈሳዊ ብስለት ምን እንደሆነና መንፈሳዊ ብስለት ያላቸው ሰዎች እንዴት መመላለስ እንደሚገባቸው ለማስረዳት ይጥር ነበር። የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ዛሬ ምን ያህል ክርስቲያኖች እንደ ልሳንን የመሳሰሉትን መንፈሳዊ ስጦታዎች እንዴት እንደ ዋነኛ የመንፈሳዊ ብስለት ምልክቶች አድርገው እንደሚወስዱና አንድነት፥ ፍቅር፥ ንጽሕና በመሳሰሉት መንፈሳዊ ባሕርያት ላይ እንደማያተኩሩ ግለጽ። ለ) በተወሰኑ መንፈሳዊ ስጦታዎች ላይ ትኩረት ማድረጉ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድነት፥ ፍቅር፥ መንፈሳዊነትና ቅድስና እንዲጨምር አስተዋጽኦ ያደርገ ይመስልሃል? ለምን? በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታዩትን ትክክለኛ ያልሆኑ አስተምህሮዎችና ተግባራት ለማረም። ጳውሎስ በኤፌሶን በሚያገለግልበት ጊዜ የተለያዩ ክርስቲያኖች ሊጎበኙት ከቆሮንቶስ መጥተው ነበር። የቀሎዔ ቤተ ሰዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ስለነበረው ክፍፍል ነግረውታል (1ኛ ቆሮ. 1፡11)። ሦስት ቁልፍ የቆሮንቶስ መሪዎች ለጳውሎስ የተወሰነ ገንዘብና ደብዳቤ አምጥተውለታል። ምናልባትም በቆሮንቶስ ስለነበረው ሁኔታ ዘርዘር ያለ መረጃ ሳይሰጡት አልቀሩም። ስሞቻቸውም እስጢፋኖስ፥ ፈርዶናጥስና አካይቆስ ይባል ነበር (1ኛ ቆሮ. 16፡17)። (ምሁራን እነዚህ ሦስት ሰዎች የቀሎዔ ቤተ ሰዎች ይሁኑ ወይም ሌሎች በርግጠኝነት አያውቁም። አብዛኛዎቹ ግን ከሌላ ወገን ናቸው ይላሉ።) ኤፌሶን ከቆሮንቶስ በጀልባ ለመሄድ ከ300 ኪሎ ሜትሮች በላይ ስለሚርቅና ጳውሎስም በኤፌሶን የጀመረውን እገልግሎት ለማቋረጥ ባለመቻሉ፥ የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን ችግሮች ለመፍታት ይህን ጠቃሚ መልእክት ጽፎላቸዋል። ጳውሎስ በዚህ መልእክቱ ያነሣቸው ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው። ሀ. ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚከፋፍሉ ዐበይት ችግሮች ነበሩ። ክርስቲያኖች በክርስቶስ የነበራቸውን አንድነት ዘንግተው በሕይወታቸው ላይ ለውጥ ያመጡትን ወይም ጠቃሚዎች ናቸው ብለው ያሰቧቸውን የተለያዩ መሪዎች ይከተሉ ነበር (1ኛ ቆሮ. 1፡11-12)። ለ. የጳውሎስን የሐዋርያነት ሥልጣን የሚጠራጠሩ ሰዎች ነበሩ። ስለሆነም፥ ጳውሎስ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን የሚናገር ሐዋርያ መሆኑን ገልጾላቸዋል። ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ መልእክቱ ስለዚህ ጉዳይ የበለጠ ያስተምራል። ሐ. ጳውሎስ ምእመናን ግልጽ ወሲባዊ ርኩሰት እንደሚፈጽሙና መሪዎችም በኃጢአት ላይ አቋም ከመውሰድ ይልቅ የግልጽነትና የቸርነት ምልክት ነው በሚል የተሳሳተ ግምት ኃጢአት ሳይቀጣ እንዲቀር ያደርጉ እንደነበር ሰማ። መ. በተጨማሪም፥ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር በሚጋጩበት ጊዜ ወደ ፍርድ ቤት ይወስዷቸው እንደነበር ሰምቶ ነበር። ሠ. በጌታ እራት ጊዜ ሰዎች የሚበሉት የሌሏቸውን ድሆች ቸል እያሉ በራስ ወዳድነት ይበሉና ይጠጡ ነበር። ረ. ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጥያቄዎች መልስ ሰጥቷል። እነዚህም ጥያቄዎች፥ 1) ክርስቲያን ማግባት አለበት ወይስ በላጤነት መኖር አለበት? 2) ክርስቲያን ለጣዖት የተሠዋውን ሥጋ ከገበያ ገዝቶ መብላት ይችላል? 3) ሴቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጡ አለባበሳቸው ምን ዓይነት መሆን አለበት? 4) በልሳን መናገር ክርስቲያኖች ሁሉ ሊፈልጉት የሚገባ እጅግ አስፈላጊ ስጦታ ነው ወይስ ሊከለከል ይገባል? 5) ክርስቲያኖች ከሞት ሊነሡ ይችላሉ? 6) ለኢየሩሳሌም ክርስቲያኖች የሚወሰደው ገንዘብ እንዴት መሰብሰብ አለበት? የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከእነዚህ ጉዳዮች ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ችግር እየፈጠረ ያለው የትኛው ነው? ለ) ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች የጳውሎስን መልስ መረዳቱ ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው? ምሁራን 1ኛ ቆሮንቶስ የጥንቱ ቤተ ክርስቲያን ላጋጠማት ችግር ጥሩ ምሳሌ እንደሆነች ያምናሉ። ምንም ወይም ጥቂት የብሉይ ኪዳን ግንዛቤ የነበራቸው አሕዛብ ወደ ቤተ ክርስቲያን በሚመጡበት ጊዜ፥ የራሳቸውን ባሕላዊ ግንዛቤ ይዘው ነበር የመጡት። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በሁሉም ባሕሎች ላይ በመፍረድ ወደ ራሱ ይመልሳቸዋል እንጂ ራሱን ከየትኛውም ባሕል ጋር እያስማማም። ጳውሎስ ምእመናን እንደ ዓለም አባላት ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር መንግሥት አባላት መመላለስ እንዳለባቸው በመግለጽ ያስተላለፈው ትምህርት ከቆሮንቶስ ሰዎች ባሕል ያፈነገጠ ነበር። ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለነበሩት ጉዳዮችና ችግሮች እንዴት መልስ እንደሰጠ አጢን። ለጳውሎስ «እንዲህ አድርጉ አታድርጉ» የሚሉ የትእዛዛት ዝርዝር መስጠት ይቀለው ነበር። ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ችግሮችን የሚያስተናግዱት በዚህ መንገድ ነው። ትልቁን ግንዛቤያቸውን በመጠቀም፥ ሰዎች እንዲከተሉ የሚፈልጓቸውን ዝርዝር ደንቦች ያወጣሉ። (ወደ ሲኒማ ቤት አትሂዱ፤ ጫት አትቃሙ፤ ፋሽን ልብስ አትልበሱ፤ የከንፈር ቀለም አትቀቡ) የሚሉትን ዓይነት ትእዛዛት ይሰጣሉ። ምንም እንኳ ብዙ ሰዎች የዚህ ዓይነቱን ክርስትና ቢመርጡም፥ ይህ አደገኛ ልምምድ ነው። ሰይጣን እንደዚህ ዓይነት ሰው ሠራሽ ደንቦችን በመጠቀም ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ሳያደርጉና ውስጣዊ ለውጥ ሳያካሂዱ በውጫዊ ደንቦች ላይ እንዲያተኩሩ ይገፋፋቸዋል። ጳውሎስ ግን ለችግሮቹ ምላሽ የሰጠው በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ሊያገለግሉ የሚችሉትን መርሆች በማቅረብ ነበር። ክርስቲያኖች በፍርድ ቤት የማይካሰሱት ለምንድን ነው? አንድ ክርስቲያን ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ መብላት ያለበት ወይም የሌለበት ለምንድን ነው? በልሳን መናገር የሚከለከለውና የሚፈቀደው ለምንድን ነው? የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የፈለጉት ዝርዝር ትእዛዛትን ነበር። ጳውሎስ ግን በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ሊያገለግሉ የሚችሉትን አመለካከቶች ሰጥቷቸዋል። ለክርስቲያኖች የሚያስፈልጉት ፍቅርና አንድነት መሆናቸውን አመልክቷል። ራስ ወዳድነት፥ ሌሎችን ከመረዳት ይልቅ የራስን መብት ለማስከበር የሚደረግ ጥረት ሁሉ ትክክል አይደለም። ከእግዚአብሔርና ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት የማያደናቅፍ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ነጻነት አለን። የውይይት ጥያቄ፡– በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚገኝ አንድ ችግር ግለጽ። ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ደንቦችን በማውጣት ለችግሩ እልባት ሊሰጡ የሚችሉበትን ሁኔታ በምሳሌ ግለጽ። ለ) መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርህ በመፈለግ ችግሩን መፍታት የሚቻለው እንዴት ነው? ሐ) ችግሩን ለመፍታት የትኛው መንገድ ይሻላል? ለምን? ሌላው በሕግጋትና በደንቦች ላይ ተመሥርቶ ችግሮችን መፍታት ከሁሉም የተሻለ አማራጭ የማይሆንበት ምክንያት፥ ችግሮች ሁልጊዜም የሚለዋወጡ በመሆናቸው ነው። በአንድ ዘመን ተቀባይነት ያልነበራቸው ነገሮች በሌላው ዘመን ተቀባይነት ያገኛሉ (ለምሳሌ፥ ዘመናዊ የሙዞቃ መሣሪያዎችን ለአምልኮ ዝማሬ መጠቀም)። በአንድ ባሕል ተቀባይነት የሌለው ነገር በሌላው ባሕል ተቀባይነት ይኖረዋል (ለምሳሌ፥ የአሳማ ሥጋ መብላት)። ነገር ግን ሁልጊዜም የምንጋፈጣቸው ችግሮች አሉ። ብዙ ዓይነት ችግሮችን ለመፍታት የሚያገለግሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሆችን በማቅረብ ለአንድ ጉዳይ መፍትሔ በምንሰጥበት ጊዜ መፍትሔው ወደፊት ለሚከሰቱት ሌሎች ችግሮችም የሚሠራ ሆኖ እናገኘዋለን። ወንጌልን የተቃወሙትን ወይም በተሳሳተ መንገድ የተረዱትን ለማረም። እግዚአብሔር አንድን ክርስቲያን መሪ በከፍተኛ ደረጃ በሚጠቀምበት ጊዜ ብዙውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚቃወሙት ሰዎች ይነሣሉ። ይህ እውነት በሐዋርያው ጳውሎስ ላይ ደርሷል። በሚሄድበት ስፍራ ሁሉ ከማያምኑ አይሁዶች ተቃውሞ ይደርስበት ነበር። ስለ ክርስትና ከጳውሎስ የተለየ አመለካከት የነበራቸው የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ሰዎችም ተቃውመውታል። ለምሳሌ ያህል፥ አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች አሕዛብ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት መገረዝና የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን መጠበቅ እንደሚገባቸው በመግለጽ የጳውሎስን ትምህርት እንደተቃወሙ ከመልእክቶቹ እንረዳለን። 1ኛ ቆሮንቶስ በተጨማሪም የጳውሎስን ትምህርቶች ስለሚቃወሙት ወይም ከራሳቸው አሳብ ጋር እንዲሄድላቸው ስለሚያጣምሙ የተለያዩ ቡድኖች ያስረዳል። በመጀመሪያ፥ አንድ ሰው የፈለገውን (ኃጢአትንም ጨምሮ) ሊያደርግ እንደሚችል በመግለጽ በክርስቲያኑ ነጻነት ላይ የሚያተኩሩ ነበሩ። በሥጋችን ላይ የምናደርገው ነገር በነፍሳችን

የ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ዓላማ Read More »

ጳውሎስ 1ኛ ቆሮንቶስን የጻፈበት ዘመንና ስፍራ

ምንም እንኳ ብዙዎቹ የጳውሎስ መልእክቶች የተጻፉባቸውን ቁርጥ ጊዜያት መናገሩ አስቸጋሪ ቢሆንም፥ 1ኛ ቆሮንቶስን የጻፈው በሦስተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ ኤፌሶን ውስጥ እያገለገለ ሳለ መሆኑ ግልጽ ነው። ጳውሎስ እስከ በዓለ ኀምሳ ድረስ በኤፌሶን እንደሚቆይና ከዚያ በኋላ ቆሮንቶሶችን እንደሚጎበኝ ተናግሯል (1ኛ ቆሮ. 16፡8፥19፣ በተጨማሪም የሐዋ. 19፡10ን አንብቡ።) ይህም የ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክት የተጻፈው ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከተከለ ከ5 ዓመታት በኋላ በ55 ዓ.ም መሆኑን ያሳያል። ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ የጻፋቸው መልእክቶችና ያደረጋቸው ጉብኝቶች ቅደም ተከተል ምሁራን ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ባደረጋቸው ጉብኝቶችና በተለይም በጻፋቸው የተለያዩ መልእክቶች ቅደም ተከተል ላይ ይከራከራሉ። ጳውሎስ በኤፌሶን ላይ ባተኮረበት በሦስተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ወቅት አራት የተለያዩ መልእክቶችን የጻፈ ይመስላል። በመጀመሪያ፥ ጳውሎስ በኤፌሶን ሳለ አንድ መሠረታዊ የመጀመሪያ መልእክት ሳይጽፍ እንዳልቀረ ብዙ ምሁራን ያምናሉ (1ኛ ቆሮ. 5፡9)። ይህ መልእክት ጠፍቷል። ጳውሎስ በዚህ የመጀመሪያ መልእክቱ ስለ ግብረገባዊ ንጽሕና ላያስተምር አልቀረም። የቆሮንቶስ ሰዎች ንጹሕ ግብረገባዊ ሕይወት ከሌላቸው ሰዎች ጋር ኅብረት እንዳያደረጉ አሳስቧቸዋል (1ኛ ቆሮ. 5፡9)። ክርስቲያኖቹ የጳውሎስን አሳብ በተሳሳተ መንገድ በመረዳት ይህ ማለት አምልኮተ ጣዖት ከሚያካሂዱና ግብረገባዊነት የጎደለው የወሲብ ግንኙነት ከሚፈጽሙ ዓለማውያን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አለማድረግን ያሳያል ብለው አሰቡ። የክርስቲያኖች ከዓለማውያን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አለማድረግ መልካም ውጤት የሚያስገኝ ነገር አልነበረም። እንደዚያ ከሆነ፥ ለማያምኑ ሰዎች መስክረው ወደ ክርስቶስ የሚመልሷቸው እንዴት ነው? ጳውሎስ የሚናገረው ለክርስቶስ ለመገዛትና የእግዚአብሔርን ሕግጋት ለመከተል ከማይፈልጉ ክርስቲያኖች ጋር ኅብረትን ስላለማድረግ ነበር። ጳውሎስ አማኞችን ወደ ንስሐ ለመምራትና ለመቅጣት በማሰብ እነዚህ ግብረ ገባዊነት የጎደላቸው ክርስቲያኖች ከክርስቲያናዊ ኅብረት እንዲገለሉ ነበር የተናገረው። የዚህም ቅጣት ዓላማ አማኞቹ አፍረው በኃጢአት ከተሞላው አኗኗራቸው እንዲመለሱ ለመርዳት ነበር። እንደ ቆሮንቶስ ሰዎች ሁሉ፥ ዛሬም ብዙ ክርስቲያኖች በግልጽ ኃጢአት ከሚመላለሱ ሰዎች ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት እንደሚያደርጉ ይቸገራሉ። ኃጢአትን እየፈጸሙ የሚኖሩትን ክርስቲያኖች ወደ መታገሡ እናዘነብላለን። ክርስቲያኖች ካልሆኑና በክርስቲያናዊ ማኅበረሰብ ውስጥ ለመኖር ከሚፈልጉት ክርስቲያኖች ደግሞ ራሳችንን እናገኛለን። ብዙውን ጊዜ ምስክርነታችን ደካማ የሚሆነውና ብዙ ዓለማውያን ወደ ክርስቶስ የማይመጡት ለዚህ ነው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቀዳሚነት ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ብቻ ኅብረት ለማድረግ ክርስቲያኖች (በተለይም የክርስቲያኖች ልጆች) ዝንባሌ ማሳየታቸውን እንዴት እንደታዘብህ ግለጽ። ለ) ይህ በቤተ ከርስቲያን ላይ ያስከተለው አሉታዊ ውጤት ምንድን ነው? ሁለተኛ፥ ጳውሎስ ሊጎበኙት ከመጡት የቆሮንቶስ አማኞች በመካከላቸው ስለነበረው ክፍፍል ከሰማና ቤተ ክርስቲያኒቱ የተወሰኑ ጥያቄዎችን በማንሣት የላከችለትን ደብዳቤ ካነበበ በኋላ፥ ሁለተኛውን መልእክት ጻፈ። ይህም በአዲስ ኪዳን ውስጥ ተካትቶ የምናገኘው የ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ነው። ጳውሎስ አጵሎስ ወደ ቆርንቶስ ተመልሶ ችግሮችን እንዲፈታ ቢጠይቀውም ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለም (1ኛ ቆሮ. 16፡12)። ስለሆነም፥ ጳውሎስ በሌሎች ሰዎች፥ ምናልባትም ሊጎበኙት በመጡት የቀሎዔ ቤተ ሰዎች አማካኝነት ደብዳቤውን ላከላቸው። ሦስተኛ፥ ጳውሎስ መልእክቱን ከጻፈ በኋላ አንዳንድ ችግሮች እርሱ በፈለገበት መንገድ ሳይሄዱለት የቀሩ ይመስላል። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ለአጭር ጊዜ ጉብኝት ወደ ቆሮንቶስ ሄደ። ጳውሎስ ይህንን ጉብኝት «የሥቃይ ጉብኝት» ብሎታል (2ኛ ቆሮ. 2፡1)። ወደ ኤፌሶን ከተመለሰ በኋላ፥ «የኃዘን ደብዳቤ» የተባለ ሌላ መልእክት ጽፎ በቲቶ በኩል ሰደደ (2ኛ ቆሮ. 2፡4፤ 7፡8-9)። (አንዳንድ ምሁራን ይህ የ1ኛ ቆሮንቶስን መልእክት ያመለክታል ይላሉ። ሌሎች ግን በዚህ መልእክት ውስጥ ብዙ ኃዘን እንደሌለ በመግለጽ፥ ጳውሎስ አሁን በእጃችን ስለሌለ መልእክት እየተናገረ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ።) አራተኛ፥ ጳውሎስ የኤፌሶን አገልግሎቱን ከፈጸመ በኋላ ወደ ቆሮንቶስና ኢየሩሳሌም አመራ። ይህንንም ያደረገው በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው የመሠረታቸውን አብያተ ክርስቲያናት በእግር እየተጓዘ በመጎብኘት በመቄዶንያ በኩል በማለፍ ነበር። በተጨማሪም፥ አብያተ ክርስቲያናት በኢየሩሳሌም ለሚገኙ ድሆች ክርስቲያኖች እንዲሰጥ ያዋጡትን ገንዘብ ሰብስቧል። ጳውሎስ በመቄዶንያ ሳለ፥ ቲቶ ከቆሮንቶስ ተመልሶ ስለ ቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መለወጥ ገለጸለት (2ኛ ቆሮ. 7፡5-7)። ጳውሎስም በአመስጋኝነት በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ የሚገኘውን የሁለተኛ ቆሮንቶስን መልእክት ጻፈ። ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ደርሶ በጋውን (3 ወራት ያህል) እዚያው አሳለፈ። ከዚያም የአሕዛብ ክርስቲያኖች ለአይሁድ ክርስቲያኖች ያዋጡትን ገንዘብ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ጳውሎስ 1ኛ ቆሮንቶስን የጻፈበት ዘመንና ስፍራ Read More »

ጳውሎስ መልእክቱን ለማን ጻፈ?

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) 1ኛ ቆሮ. 1፡2 እንብብ። ጳውሎስ ይህንን መልእክት የጻፈው ለማን ነበር? ለ) ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንዴት ነው የገለጻት? ሐ) ይህንን ከሮሜ 1፡7 ጋር አነጻጽር። ይህ ጳውሎስ የሮሜን ቤተ ክርስቲያን ከገለጸበት ሁኔታ ጋር እንዴት እንደሚመሳሰልና እንደሚለያይ አብራራ። መ) የሐዋ. 18፡1-11ን አንብብና ቤተ ክርስቲያኒቱ መጀመሪያ እንዴት እንደተመሠረተች ጠቅለል አድርገህ ግለጽ። ጳውሎስ የጥንታዊ ደብዳቤዎችን አጻጻፍ በመከተል ጸሐፊነቱን ከገለጻ በኋላ ደብዳቤውን ለማን እንደሚጽፍ ጠቅሷል። ጳውሎስ፥ «በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት» ብሏል። ከዚህ ገለጻ አራት ነገሮችን ልንመለከት እንችላለን። ደብዳቤው የተጻፈው ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ነበር። ቤተ ክርስቲያን የሚለውን ቃል ስንሰማ ሰዎች ስለሚያመልኩበት ሕንፃ እናስባለን። ለዚህም ነው በአማርኛ ቋንቋ «ቤተ ክርስቲያን» (የክርስቲያን ቤት) የሚባለው። ሌሎች ደግሞ «የጸሎት ቤት» ይሉታል። በባሕላችን፥ የቤተ ክርስቲያኑ አስፈላጊነት የሚለካው በቤቱ ትልቅነት ነው። ለዚህም ነው የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች የቤተ ክርስቲያን ሕንፃዎቻቸውን ሁሉም ሰው ሊያይ በሚችልባቸው ደብሮች ላይ የሚሠሩት። የሕንጻዎቹ ማማርም የቤተ ክርስቲያኑን አስፈላጊነት ያጎላዋል ብለው ያስባሉ። ወንጌላውያን ክርስቲያኖችም በሕንፃ ላይ ያተኩራሉ። በቤት ወይም ከቤት ውጭ በመጠለያ ውስጥ ተሰባስቦ ማምለኩ የትንሽነት ስሜት የሚያሳድር ይመስላቸዋል። ይህ ደግሞ መሬት አግኝተው የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ እስኪገነቡ ድረስ ለጊዜው ብቻ የሚጠቀሙበት አማራጭ ነው። የሣር ቤት ካለን ወደ ቆርቆሮ ቤት ለመለወጥ ጥረት እናደርጋለን። ሕንፃው ትልቅ በሚሆንበት ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑም የበለጠ አስፈላጊ ይመስለናል። እንደዚህ ሲሆን ሰዎች ለአምልኮ ይመጣሉ ብለን እናስባለን። በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ግን እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ አልነበረም። «ቤተ ክርስቲያን» ተብሎ የተተረጎመው የግሪኩ ቃል የትኛውንም ዓይነት የሰዎች ስብስብ ያመለክታል። መንግሥት ሕዝቡን በሚሰበስብበት ጊዜ ስብሰባው «ቤተ ክርስቲያን» ተብሎ ይጠራ ነበር። ስለሆነም፥ እንደ ጳውሎስ ያሉ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ይህን ቃል የሚጠቀሙት የክርስቶስን ተከታዮች ለማመልከት ነበር። የቤተ ክርስቲያን ሕንጻዎች የተሠሩት ክርስቶስ ከሞተና ከተነሣ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ በመሆኑ፥ የጥንት ክርስቲያኖች የሚሰባሰቡት በግለሰብ ቤቶች ውስጥ ነበር። በአዲስ ኪዳን ውስጥ «ቤተ ክርስቲያን» የሚለው ቃል በሦስት ዐበይት መንገዶች ይተረጎማል። በመጀመሪያ፥ የአንድ አካባቢ አማኞች በግለሰቦች ቤት ውስጥ ይሰባሰቡ ነበር። በሮሜ 16፡5 ጳውሎስ በጵርስቅላና አቂላ ቤት ውስጥ ስለምትሰባሰብ ቤተ ክርስቲያን ጽፎአል። ሁለተኛ፥ በአንድ አካባቢ የሚገኙ ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያን ይባሉ ነበር። ምንም እንኳ በቆሮንቶስ የሚገኙ ክርስቲያኖች በተለያዩ ቤቶች እየተሰባሰቡ ያመልኩ የነበረ ቢሆንም፥ ጳውሎስ ለሁሉም ባስተላለፈው መልእክት «ለቆሮንቶስ» ሰዎች የሚል አገላለጽ ተጠቅሟል። ሦስተኛ በዓለም ውስጥ የሚገኙትን አማኞች በሙሉ ያመለክታል። ይህም አንዳንድ ጊዜ «ዓለም አቀፋዊው ቤተ ክርስቲያን» የሚባለው ነው (ኤፌ. 1፡22)። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ ኢትዮጵያውያን ለአምልኮ ጥሩ ሕንፃ ያስፈልጋል ብለው የሚያስቡት ለምንድን ነው? ለ) ይህንን አመለካከት ከአዲስ ኪዳን ዘመን ሁኔታ ጋር አነጻጽር። ሐ) ትልቅ የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ መፈለጋችን ጥሩ ይመስልሃል ወይስ መጥፎ? መልስህን አብራራ። የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን። ለጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን የግለሰብ፥ የክርስቲያኖች ቡድን ወይም የቤተ እምነት ሳትሆን የእግዚአብሔር ናት። ቤተ ክርስቲያንን በክርስቶስ ደም የገዛት እግዚአብሔር ነው። ክርስቲያኖችን የሚጠራቸው እግዚአብሔር ሲሆን፥ መንፈስ ቅዱስ ወደ አማኞች ኅብረት ውስጥ ይጨምራቸዋል። ዛሬ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ቤተ ክርስቲያን የእነርሱ ንብረት እንደሆነች ያስባሉ። «ቤተ ክርስቲያኒቱ በእኔ መሬት ላይ ነው የቆመችው። ለቤተ ክርስቲያን ብዙ ገንዘብ ሰጥቻለሁ» ይላሉ። መሪዎች አንዳንድ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን የእነርሱ እንደሆነችና ያሻቸውን ሊያደርጉባት የሚችሉ ይመስላቸዋል። ባለቤቷ ለሆነው ለክርስቶስ የሚሠሩ መጋቢያን ብቻ የመሆናቸውን እውነታ ይዘነጋሉ። እርሱም ቤተ ክርስቲያኑን ስላስተዳደሩበት ሁኔታ አንድ ቀን ይጠይቃቸዋል። መሪዎች ቤተ እምነታቸው ብዙ ክብር እንዲያገኝ ይጥራሉ። ቤተ እምነታቸው የፈለጉትን ያህል ክብር ሳያገኝ ሲቀር ወይም አባሎቻቸው የሌላ ቤተ ክርስቲያን አባላት በሚሆኑበት ጊዜ ይቀናሉ። ጳውሎስ ግን የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን ሲመሠርታትም እንኳ የእርሱ ንብረት እንዳልሆነች ያውቅ ነበር። ቤተ ክርስቲያኒቱ ሙሉ ለሙሉ የእግዚአብሔር ንብረት ስለሆነች፥ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የሚያደርጉት ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን ሊያስከብር ይገባል። ለግል ወይም ለቤተ እምነት ክብር መሥራት አያስፈልጋቸውም ነበር። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙውን ጊዜ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ሳትሆን የእኛ ናት ብለን የምናስበው ለምንድን ነው? ለ) የየትኛውም ቤተ እምነት ተከታይ የሆነ ቤተ ክርስቲያን ሁሉ የእግዚአብሔር እንደሆነ ብናስብ አመለካከታችን እንዴት ይቀየራል? በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በክርስቶስ ተቀድሰዋል። ጳውሎስ በኃላፊ ጊዜ ግስ እየተናገረ መሆኑን አጢን። ጳውሎስ ወደፊት እንደሚቀደሱ ሳይሆን ቀደም ሲል እንደተቀደሱ ገልጾአል። ጳውሎስ የሚጽፍላቸው እነዚህ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ሕይወት ይኖሩ ነበር? ትክክለኛውን የቅድስና ፍች የሚያንጸባርቅ ሕይወት ይመሩ ነበር? አልነበረም። የወሲብ ኃጢአት፥ ክፍፍል፥ የጌታን እራት አግባብነት በጎደለው ሁኔታ የመመገብ ኃጢአቶች ነበሩባቸው። እንዲያውም አንዳንዶች በጌታ እራት አወሳሰድ ላይ በፈጸሙት ጥፋት የሞትና የሕመም ቅጣት ደርሶባቸው ነበር። ቤተ ክርስቲያኒቱ በራስ ወዳድነት ተሞልታ ነበር። ይህም ሆኖ፥ ጳውሎስ «ተቀድሰዋል» ብሏል። ለምን? ምክንያቱም መቀደስ ማለት መለየት ማለት ነው። እግዚአብሔር በቆሮንቶስ ከተማ ውስጥ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ መካከል ልጆቹ እንዲሆኑለት መርጧቸዋል። እንደ ልጆቹ ተመላለሱም አልተመላለሱ፥ በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት በክርስቶስ በማመናቸው ምክንያት ከዓለም የተለዩ ልጆቹ ናቸው። ቅዱሳን ለመሆን ተጠርተዋል። ምንም እንኳ እነዚህ ሰዎች ከብዙ ችግሮች ጋር ቢታገሉም፥ እግዚአብሔር በሕይወታቸው ለመሥራት የሚፈልግበት ዓላማ ነበረው። ጳውሎስ እግዚአብሔር ከሁሉም በላይ በቅድስና እንዲኖሩ የሚፈልግ መሆኑን ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ገልጾላቸዋል። ቢቀደሱ ኖሮ ክፍፍላቸው፥ የወሲብ እርኩሰታቸው፥ ራስ ወዳድነታቸው፥ ወዘተ… ይለወጥ ነበር። ጴጥሮስ እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ፥ እኛም በቅድስና እርሱን እንድንመስል ጠይቆናል (1ኛ ጴጥ. 1፡15–16)። መቀደስ ማለት ኃጢአትን አለመሥራት ማለት ብቻ አይደለም። መቀደስ ማለት መለየትና ልዩ መሆን ማለት ነው። ይህም በአመለካከታችን፥ በዓላማችን፥ በባሕሪያችንና በተግባራችን ከዓለም መለየታችንን ያሳያል። ይህ ክርስቶስን የምንመስልበትና እንደ እርሱ የምንመላለስበት ሕይወት ነው። እግዚአብሔር ከልጆቹ ሁሉ የሚፈልገው ይህንን ነው። አንድ ሰው አማኝ ነኝ እያለ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳያሳይ በተከታይ በኃጢአት ውስጥ የሚመላለስ ከሆነ፥ ድነቱን (ደኅንነቱን) ልንጠራጠር እንችላለን። የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር አንተን ከጠራባቸው ምክንያቶች አንዱ እርሱን እንድትመስልና እንድትቀደስ ነው። ሀ) ክርስቲያን ከሆንህ በኋላ ክርስቶስን ለመምሰልና ለመቀደስ የለወጥሃቸውን ነገሮች ዘርዝር። ለ) በተግባርህና በአስተሳሰብህ አሁንም ክርስቶስን እንዳትመስል የሚከራከሩህ ያልተቀደሱ ነገሮችህ ምንድን ናቸው? አሁን ጊዜ ወስደህ እነዚህን ኃጢአቶች ተናዘዝና መንፈስ ቅዱስ ክርስቶስን ትመስል ዘንድ እንዲለውጥህ ጠይቀው። የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ተመሠረተች? ጥንታዊቷ የቆሮንቶስ ከተማ ምን ትመስል ነበር? በሐዋርያት ሥራ 18 እንደተገለጸው፥ ጳውሎስ በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኛነት (ሚሲዮናዊ) ጉዞው ወደ ቆሮንቶስ ከተማ ሄደ። በዚያም ለ18 ወራት ሲሰብክና ቤተ ክርስቲያን ሲተክል ቆየ። ቆሮንቶስ ጳውሎስ በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኛነት ጉዞው ወቅት የቆየባት ዐቢይ ከተማ ነበረች። በዚህ ጊዜ ነበር እግዚአብሔር ጳውሎስ ብዙ አይሁዶችንና አሕዛብን፥ በተለይም ግሪኮችን ወደ ክርስቶስ እንዲመልስ የተጠቀመበት። አብዛኞቹ ግሪኮች በግሪክ ፍልስፍናና ትምህርት ይደነቁ ስለነበር፥ ጳውሎስ ከእግዚአብሔር ጥበብ ጋር ሲነጻጸር የዓለም ጥበብ ሞኝነት እንደሆነ ገለጸላቸው (1ኛ ቆሮ. 1፡18–2፡16)። ነገር ግን አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ከሀብታሞች ወይም ከተማሩት ወገን የመጡ ሳይሆኑ፥ ድሆች፥ ያልተማሩና ምናልባትም ባሮች ነበሩ (1ኛ ቆሮ. 1፡26-28)። በሦስተኛው የወንጌል መልእክተኛነት ጉዞው ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ተመልሶ 3 ወራት በዚያ አሳልፎአል። ጳውሎስ ወንጌልን በሰበከበት ወቅት የወንጌሉ ንጹሕነት ከሰዎች የክፋት ሥራ ጋር ግጭት ሊፈጥር ችሏል። ቆሮንቶስ በሮሜ የእካይያ ክፍለ ሐገር ዋና ከተማ ነበረች። ቆሮንቶስ በአያሌ ነገሮች የታወቀች ከተማ ነበረች። ሀ. ትልቅ ከተማ ነበረች። በከተማዪቱ ውስጥ 250,000 ነፃ ሰዎችና 400,000 ባሪያዎች ይኖሩ እንደነበረ ይገመታል። ለ. ዋነኛ የንግድ ከተማ ነበረች። ቆሮንቶስ ሁለት ውኃማ አካላትን በምትከፍል አነስተኛ ሰርጥ ውስጥ የተመሠረተች ከተማ ነበረች። በስተምሥራቅ ወደ እስያና መካከለኛው ምሥራቅ የሚወስድ የኤጂያን ባሕር ነበር። በስተምዕራብ የአድሪያቲክ ባሕርና ወደ ሮም የሚወስድ መንገድ ነበር። ይህም የሮም ግዛት እምብርት ነበር። ከሮም ወደ ምሥራቅና እስያ የሚሄዱ ነጋዴዎች ሁሉ በቆሮንቶስ ከተማ ውስጥ ይገናኙ ነበር። ብዙውን ጊዜ ባለመርኮበች አደገኛ በሆነው

ጳውሎስ መልእክቱን ለማን ጻፈ? Read More »

1ኛ ቆሮንቶስ ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) 1ኛ ቆሮንቶስ 1፡1ን አንብብ። ጸሐፊው ማን እንደሆነና ራሱን እንዴት እንደሚገልጽ ተናገር። ) ይህን መግቢያ ከሮሜ 1፡1 ጋር አነጻጽርና ጸሐፊው ስለ ራሱ አጽንኦት ሰጥቶ በጠቀሳቸው ነገሮች መካከል ያሉትን ልዩነቶች ግለጽ። ጳውሎስ በመልእክቶቹ ሁሉ መጀመሪያ ራሱን፥ «በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ ጳውሎስ» ብሎ በማስተዋወቅ ጥንታዊ የደብዳቤ አጀማመር ይከተላል። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከሚከፋፈሉባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የጳውሎስ ሥልጣን በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሐዋርያት ጋር እኩል የመሆኑ ወይም ያለመሆኑ ጉዳይ ነበር። ለዚህም ነበር ሐዋርያው ጴጥሮስ የበለጠ ሥልጣን አለው ብለው ያሰቡት ወገኖች «እኛ የጴጥሮስ ነን» ያሉት። ከ2ኛ ቆሮንቶስ መልእክት አብዛኛው ጳውሎስ ከሌሎች ሐዋርያት ጋር እኩል መሆኑን በመግለጽ የተከራከረበት ነው። ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ መግቢያው የኢየሱስ ክርስቶስ «ሐዋርያ» መሆኑን በአጽንኦት ገልጾአል። ኢየሱስ ክርስቶስን ወክሎ ለዓለም ሁሉ እንዲያገለግል እግዚአብሔር ነበር ለይቶ የመረጠው። ጳውሎስ ራሱ ሐዋርያ ለመሆን እንዳልመረጠና ራሱን በሚያስደንቀው ሁኔታ እግዚአብሔር እንደመረጠው ገልጾአል። ስለሆነም፥ ጳውሎስ የሚናገረውን አለመስማት ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገረውን አለመስማት እንደ ማለት ነበር። ይህ ልናስታውሰው የሚገባን ጠቃሚ እውነት ነው። አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ወይም እንደ ጳውሎስ ያሉ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰጧቸውን ትእዛዛት በማይፈጽምበት ጊዜ ሁሉ፥ በእግዚአብሔር ላይ እያመፀ ነው ማለት ነው። እግዚአብሔር የሚናገረውን ለመስማት አይፈልግም ማለት ነው። ዛሬ የምንኖረው፥ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ ጋር ወደማይጣጣሙ አስደናቂ ነገሮችና ልምምዶች በሚሳቡበት ዘመን ውስጥ ነው። እነዚህ ልምምዶች ስለሚያስደንቋቸውና መልካም ስለሚመስሏቸው ብዙ ክርስቲያኖች ይከተሏቸዋል። «ይህ ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ ጋር ይስማማል?» የሚል ጥያቄ በሚያነሡበት ጊዜም ስድብ ይሰነዘርባቸዋል። «ለእኛ ጥሩ ስሜት እንዲሰጠን ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆን አለመሆኑን ልትጠይቀን ምን መብት አለህ? ልምምዳችንን እያበላሸህብን ነው።» የሚል ምላሽ ይሰጣሉ። በዚህ ዓይነት በእግዚአብሔር ትእዛዝና ሥልጣን የጻፉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊያን ከመታዘዝ እንቆጠባለን። ራሳችንንና ሌሎች ሰዎችን ለልምምዶቻችን መመዘኛዎች አድርገን እንወስዳለን። ጳውሎስ የጻፈው መልእክት የግል አሳብ ላይሆን የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችና እኛም እንድንገነዘብ ይፈልጋል። ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች አለመገዛት ማለት ለእግዚአብሔር አለመገዛት ነው። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ቃል ከመገዛት ይልቅ ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ ጋር በማይስማሙ አስደናቂ ነገሮች ሲወሰዱ የተመለከትህበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) ይህ ለቤተ ክርስቲያን አደገኛ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) አንዳንድ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ የሚያቀርበውን ግልጽ ትምህርት እየጣሱ የሚያከናውኗቸውና ሌሎችን ወደ ጥፋት የሚመሩባቸው ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? መ) ለብዙ ክርስቲያኖች የአንዳንድ ነገር እውነት መሆን ወይም አለመሆን አሳሳቢ የማይሆነው ለምን ይመስልሃል? ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ራሱን ያስተዋወቀበት ሁኔታ ከሮሜ ቤተ ክርስቲያን ይልቅ አጠር ያለው ለምንድን ነው? ምናልባትም ይህ የሆነው ጳውሎስ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መሥራች በመሆኑና በዚያ የነበሩት ክርስቲያኖች በሚገባ ስለሚያውቁት ይሆናል። ነገር ግን የሮሜ ክርስቲያኖች ጳውሎስን ስለማያውቁት ማንነቱንና የሮሜን መልእክት የጻፈበትን ሥልጣን በጥንቃቄ አብራርቶላቸዋል። ጳውሎስ የ1ኛ ቆሮንቶስን መልእክት እንደጻፈ የሚጠራጠሩ ምሁራን ጥቂት ናቸው። 1ኛ ቆሮንቶስ ከተጻፈ ከ40 ዓመታት በኋላ (በ95 ዓ.ም) የሮሜው ክሌመንት የተባለው እውቅ ግለሰብ ይህን መልእክት ጠቅሶታል። በዚያን ጊዜ መልእክቱ እንደ ሮም ባሉት የአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት እየተገለበጠ ተሰራጭቶ ነበር። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1ኛ ቆሮንቶስ ጸሐፊ Read More »

የ1ኛ ቆሮንቶስ መግቢያ

አንዳንድ ክርስቲያኖች «እንደ ጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ብንሆን መልካም ነበር። ክርስቲያኖች ታላቅ ፍቅርና አንድነት፥ እንዲሁም መንፈሳዊ ሕይወት ነበራቸው፥ አስደናቂ ተአምራት ይደረጉ ነበር። ወደ ጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ዘመን መመለስ ይኖርብናል። ያኔ እግዚአብሔር ያለ ጥርጥር ይባርከናል ይላሉ። እውን እነዚያ ጊዜያት ከእኛ ዘመን የተሻሉ ነበሩ? አዲስ ኪዳንን በጥንቃቄ በምናጠናበት ጊዜ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችንን የሚያውኩ ችግሮች በቀድሞዪቱም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደነበሩ እንገነዘባለን። ግብዝነት፥ ክፍፍል፥ ዝሙት፥ የሐሰት ትምህርትና እግዚአብሔርን ለማስደሰት ከነበራቸው ፍላጎት የሚመነጩ የሕግ አጥባቂነት አመለካከቶች ይታዩ ነበር። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን በመሰልን እያሉ ሲመኙ የሰማኸው መቼ ነው? ለ) ከላይ የተጠቀሱትን የጥንት ቤተ ክርስቲያን ችግሮች ተመልከትና፥ ዛሬ ከእነዚህ መካከል የትኞቹ ችግሮች ቤተ ክርስቲያኖቻችንን እንደሚያውኩ ግለጽ። ለእነዚህ ለእያንዳንዳቸው ችግሮች ምሳሌዎችን ስጥ። የሮሜ መልእክት ከጳውሎስ መጻሕፍት ሁሉ ረዥም በመሆኑ፥ ከሐዋርያት ሥራ ቀጥሎ በቀዳሚነት ቀርቧል። ይህ መጽሐፍ ሰው እንዴት እንደሚድን፥ እንደዳነ፥ ሰው ኃጢአትን እንዴት እንደሚያሸንፍና የእግዚአብሔር ልጆች ስለሚወርሱት ተስፋ በመግለጽ ሥነ መለኮታዊ የድነት (ደኅንነት) ጉዳዮችን ያብራራል። ከጳውሎስ መልእክቶች በርዝመቱ የሁለተኛነቱን ደረጃ የያዘው የቆሮንቶስ መልእክት ነው። 1ኛ ቆሮንቶስ የተጻፈው በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩትን የተወሰኑ ችግሮች ለመቅረፍ ነበር። በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ችግሮች ዛሬ በየቤተ ክርስቲያኖቻችን ውስጥ ይገኛሉ። ስለሆነም፥ ለክርስቲያኖች የ1ኛ ቆሮንቶስን ትምህርት በግልጽ መረዳት ጠቃሚ ነው። የውይይት ጥያቄ፡- ስለ 1ኛ ቆሮንቶስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደ ተመሠረተች፥ የቆሮንቶስ ከተማ ምን እንደምትመስል፥ የመጽሐፉ ደራሲ ማን እንደሆነ፥ የመጽሐፉ ዓላማ ምን እንደሆነ ወዘተ. ጠቅለል አድርገህ ጻፍ። ለ) ይህ መጽሐፍ ከዛሬዪቱ ቤተ ክርስቲያን ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን እውነቶች ይይዛል ብለህ የምታስብባቸውን ምክንያቶች ዘርዝር። የ1ኛ ቆሮንቶስ መግቢያ ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ 11፡28-29 በሐዋርያነት አገልግሎቱ ያጋጠማቸውን ችግሮች ሲገልጽ፥ «የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው፡፡ የሚደክም ማን ነው? እኔም አልደክምምን? የሚሰናክል ማን ነው? እኔም አልናደድምን?» ብሏል። እግዚአብሔር በሮም ግዛት ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ለመመሥረት በጳውሎስ ተጠቅሟል። ጳውሎስ ግን ቤተ ክርስቲያን በመመሥረቱና የተወሰኑ ሰዎች ለጸሎትና አምልኮ ሲሰባሰቡ በማየቱ ብቻ የሚረካ ሰው አልነበረም። እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ሕይወቷ እንድትበስል ይፈልግ ነበር። በጳውሎስ መልእክቶች ውስጥ የሚገኙትን የተለያዩ ጸሎቶች ብንመለከት፥ ጳውሎስ አማኞች በእውቀት፥ በአንድነትና በብስለት እንዲያድጉ ከልብ መሻቱን እናያለን። (ለምሳሌ፥ ኤፌ. 1፡14-21፤ 3፡14-21)። ጳውሎስ እጅግ አጥብቆ ለሚወደው ለክርስቶስ አማኞችን እንደ ንጽሕት ሙሽራ አድርጎ ለማቅረብ ይፈልግ ነበር (2ኛ ቆሮ. 11፡2)። ክርስቲያኖች እንደ እግዚአብሔር ልጆች የሚገባቸውን ዓይነት ሕይወት ሳይኖሩ በሚቀሩበት ጊዜ ጳውሎስ በፍቅርና አንዳንዴም በቁጣ ወደ ትክክለኛው ስፍራ ሊመልሳቸው ይተጋል። ከእግዚአብሔር መንገድ ሾልከው የሚወጡ ልጆች በሥጋ የወለዷቸውን ሰዎች ስሜት በእጅጉ እንደሚጎዱ ሁሉ፥ ጳውሎስም መንፈሳዊ ልጆቹ ከእውነት ፈቀቅ በሚሉበት ጊዜ በጽኑ ይቆስል ነበር። ጳውሎስ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ለመመለስ ብቻ ሳይሆን በእምነታቸው እንዲያድጉ ለመርዳት ጭምር የተሰጠውን ሐዋርያዊ ሥልጣኑን ተመለከተ። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለቤተ ክርስቲያንህ በማሰብ ምን ያህል በጽኑ እንደተጎዳህ ግለጽ። ለ) አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለቤተ ክርስቲያናቸው ምእመናን መንፈሳዊ ዕድገት አጥብቀው በማሰባቸው ምክንያት እንደ ጳውሎስ የሚጎዱ ይመስልሃል? መልስህን አብራራ። ሐ) ብዙ ሰዎች እየዳኑ ቢሆኑም፥ ብዙዎች ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን እየወጡ ናቸው። ይህ አማኞች ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱና በእምነታቸው እንዲያድጉ መሪዎች የሆንን ሰዎች ተግተን አለመሥራታችንን የሚያሳየው እንዴት ነው? ምናልባትም የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በጳውሎስ ላይ ከፍተኛ ሥቃይና ሕመም ሳታስከትል አልቀረችም። በመሆኑም ከሌሎች ሁሉ በላይ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ብዙ መልእክት ጽፎአል። ጳውሎስ እነዚህ ክርስቲያኖች ችግሮቻቸውን ተቋቁመው በእምነታቸው እንዲያድጉ በማበረታታት 1ኛና 2ኛ ቆሮንቶስን ጽፎላቸዋል። ጳውሎስ ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ቢያንስ ሁለት ተጨማሪ መልእክቶችን የጻፈ ቢሆንም፥ ጠፍተዋል። ጳውሎስ በቆሮንቶስ 18 ወራትን ስላሳለፈ፥ ቤተ ክርስቲያኒቱንና ክርስቲያኖቹን በደንብ ያውቃቸው ነበር። ስለሆነም፥ እንደ ሮሜ መልእክት አጠቃላይ እውነቶችን ከማብራራት ይልቅ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያኒቱ ባጋጠማት የተወሰኑ ጉዳዮች ላይ አተኩሯል። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የ1ኛ ቆሮንቶስ መግቢያ Read More »