ለሽማግሌዎችና ለጎልማሶች የተሰጠ ምክር (1ኛ ጴጥ. 5፡1-14)

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መልካም ግንኙነት ሊኖር ይገባል። ጴጥሮስ ከሚያሳድዱን ዓለማውያን፥ ከቤተሰብ አባላትና ከሌሎች አማኞች ጋር ስለሚኖረን ግንኙነት አስተምሯል። አሁን ደግሞ የእግዚአብሔር ሕዝብ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖረው እንደሚገባ ያስተምራል።

 1. ጴጥሮስ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሆኑት ሽማግሌዎች ይጀምራል። በተለይ በስደት ጊዜ የሽማግሌዎች ቀዳማይ ኃላፊነት ምንድን ነው? ሽማግሌዎች የእግዚአብሔር መንጋ እረኞች እንደ መሆናቸው መጠን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን አማኞች ሁሉ በጥንቃቄ መጠበቅ ያስፈልጋቸዋል። ምንም እንኳን ይህ ተጨማሪ ሸክም ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ይህንን የአመራር ኃላፊነት ከሰጣቸው በደስታ ሊቀበሉት ይገባል። ነገር ግን መሪዎች ከዚሁ አገልግሎታቸው የተነሣ የሚጋፈጧቸውን የተለመዱ አደጋዎች መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። እንደ ገንዘብ ወይም የግል ሥልጣን (በኃይል መግዛት) ላሉት ጥቅሞች ሲሉ የመሪነትን አገልግሎት መቀበል የለባቸውም። መሪዎች የመጨረሻው ሽልማታቸው የእረኞቹ አለቃ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ ከጥሩ ደመወዝ ወይም ከሰዎች ከሚያገኙት ክብር እንደማይመጣ መረዳት ይኖርባቸዋል። በመንግሥተ ሰማይ፥ የክብርን አክሊል ይቀበላሉ። ይህም ከምድራዊው የገንዘብ ወይም የሥልጣን ሽልማት በተቃራኒ ከእነርሱ ሊወሰድ የማይችል ነው።

(ማስታወሻ፡ ጴጥሮስ ስለ መሪዎች ዐቢይ ኃላፊነት ጠቃሚ እውነትን ገልጾአል። ሽማግሌ የቤተ ክርስቲያን አባላት እረኛ ነው። ጴጥሮስ ይሄንን የጻፈው በጎቻቸውን በሚገባ የሚጠብቁትን አይሁዳውያን እረኞች በማስታወስ ነው (ለምሳሌ፥ መዝ. 23)። ሽማግሌዎች የቤተ ክርስቲያናቸውን አባላት ሁሉ በግል ማወቅ ይኖርባቸዋል። ይህም አማኞች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድጉና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፍሬያማ አገልግሎት እንዲያበረክቱ ለማበረታታትና ለማገዝ ያስችላቸዋል። በጴጥሮስ ዘመን አብያተ ክርስቲያናት በግለሰብ ቤቶች ውስጥ ይሰበሰቡ ነበር። በመሆኑም ሽማግሌዎች እያንዳንዱን አማኝ በግል ያውቁ ነበር። በዛሬዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ግን በመቶዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ስለሚገኙ፥ ሽማግሌዎች አባሎቻቸውን በግል ለማወቅ ይቸገራሉ። ይህ ግን እያንዳንዱን ክርስቲያን በአግባቡ በእረኝነት ለማገልገል እንዳይሞክሩ ያደርጋቸዋል ማለት አይደለም። አንድ ሽማግሌ ከ50 የሚበዙትን ክርስቲያኖች በበቂ ሁኔታ በእረኝነት ሊያገለግል አይችልም። በመሆኑም እያንዳንዱ ሽማግሌ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት የተወሰኑትን ሰዎች በእረኝነት እንዲያገለግል ሊመደብ ይገባል። እንዲሁም ሽማግሌዎች ከሥራቸው የሚያገለግሉትን ሰዎች መሾም ያስፈልጋቸዋል። ምናልባትም ብዙ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የማያድጉት፥ በሐሰት ትምህርት የሚወሰዱት ወይም ወደ ዓለም የሚመለሱት፥ ሽማግሌዎች ተገቢውን የእረኝነት አገልግሎት ስለማይሰጡ ይሆናል። እግዚአብሔር ሽማግሌዎች የእረኝነት አገልግሎት እንዲሰጡ ይጠብቃል። በእግዚአብሔር እርዳታ የእያንዳንዱ ክርስቲያን መንፈሳዊ ፍላጎቶች መሟላታቸውን ስለምናረጋግጥባቸው መንገዶች ማሰብ ይኖርብናል።)

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች አባሎቻቸውን የሚያውቁና ፍላጎቶቻቸውን በበቂ ሁኔታ የሚያሟሉ ይመስልሃል? ካልሆነ፥ ለምን? ለ) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያንዳንዱ ክርስቲያን በበቂ ሁኔታ ከሽማግሌዎች የእረኝነት አገልግሎት በሚያገኙበት መልኩ አመራርን ለማዋቀር ምን ማድረግ ያስፈልጋል?

 1. በመቀጠልም ጴጥሮስ ብዙውን ጊዜ ከሽማግሌዎች ጋር ለሚጋጩ ወጣቶች ምክርን ይሰጣል። ብዙውን ጊዜ ወጣቶች አሁኑኑ ለውጥ እንዲመጣ ይፈልጋሉ። በሥልጣን ላይ መቀመጥ ይሻሉ። ወጣቶች ብዙውን ጊዜ ከእነርሱ ያነሰ ትምህርት ያላቸውን ሽማግሌዎች ይንቃሉ። በእድሜ ገፋ ያሉ መሪዎች የእነርሱን ያህል መንፈሳዊ እንዳልሆኑ ያስባሉ። ጴጥሮስ ለውጥ በማምጣቱ አስፈላጊነት ላይ ሲያተኩር፥ እነዚህ ወጣቶች ለሽማግሌዎች እንዲገዙ ይመክራል። ሽማግሌዎች መንፈሳውያን ባይሆኑም እንኳን ወጣቶች በትሕትና ራሳቸውን ማስገዛት ይኖርባቸዋል። ወጣቶች እግዚአብሔር ሰውን ወደ ታላቅነት የሚያደርስበትን መንገድ ማስተዋል ይኖርባቸዋል። በመጀመሪያ አንድ ሰው ከሁኔታዎች ሁሉ ባሻገር ለእግዚአብሔርና ለሌሎችም መገዛት ይኖርበታል። ከዚያም እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ እና መንገድ የሥልጣንን ስፍራ ይሰጠዋል። የትሕትናን ትምህርት ሳይማሩ ወደ ሥልጣን ለመውጣት መቸኮሉ ለወጣቱ ብቻ ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያኒቱም አደገኛ ነው። የሕይወትን ጠቃሚ ነገሮች ለመማርና ለመብሰል ጊዜን ይጠይቃል፡፡ እነዚህ ትምህርቶች ደግሞ ከመጽሐፍ የሚገኙ አይደሉም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጴጥሮስ ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከሚሰጣቸው ምክሮች መካከል የዛሬዎቹ መሪዎች ለመፈጸም የሚሞክሩዋቸው የትኞቹ ናቸው? እግዚአብሔር የሚፈልገውን ዓይነት መሪ እንዳይሆኑ የሚከለክሏቸው ባሕርያት የትኞቹ ናቸው? ለ) ወጣቶች የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን እርምጃዎች በትዕግሥት ለመቀበል ባለመቻላቸው ወደ መሪነት ሥልጣን ለመውጣትና ቅጽበታዊ ለውጥ ለማምጣት ሲጥሩ የተመለከትክበትን ሁኔታ ግለጽ፡፡ ጴጥሮስ ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ስለሚሞክሩበት ሁኔታ ምን ምክር ሰጠ?

 1. በመጨረሻም፥ ጴጥሮስ አማኞች ሁሉ ሊያስታውሱ የሚገባቸውን አንዳንድ ጠቃሚ እውነቶች በፍጥነት ይዘረዝራል።

ሀ. «እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃቸውን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት»። አማኞችን የሚያስጨንቁ ብዙ ነገሮች አሉ። ከእነዚህም መካከል ስደት፥ የገንዘብ እጥረት፥ ሥራ አጥነት፥ በሽታና የመሳሰሉት ሊጠቀሱ ይችላሉ። አማኞች ለእነዚህ ችግሮች ምን ዓይነት ምላሽ ሊሰጡ ይገባል? እግዚአብሔር እንደሚያስብልንና በእርሱ አመለካከት ለእርሱ ጥሩ የሆነውን ብቻ ወደ ሕይወታችን እንደሚያመጣ በማመን፥ በጸሎትና በትሕትና ችግራችንን ለእርሱ ማሳወቅ ይኖርብናል።

ለ. በመጠን ኑሩ ንቁም። ጴጥሮስ ስለምን መንቃት እንዳለብን አልገለጸም። እየተናገረ ያለው ግን በመከራና ሥቃይ ዐውድ ውስጥ ሆኖ ነው። ሁልጊዜም፥ በተለይም በመከራና በሥቃይ ጊዜ አማኞች ልባቸውንና ሕይወታቸውን በጥንቃቄ መጠበቅ ይኖርባቸዋል። መራርነትና ቁጣ እንዳይሞላን መጠንቀቅ አለብን። አማኞች ሰዎችን ለመበቀል ማሰብ የለብንም። ከፍርሃት፥ እምነታችን ከመካድ ወይም ከመደበቅ መጠንቀቅ አለብን። ክርስቲያኖች ሁሉ የዓለም ወይም የኃጢአት ፍቅር ወደ ውስጣችን ዘልቆ እንዳይገባና ምስክርነታችን እንዳይጠፋ መጠንቀቅ አለብን። ሰይጣን እነዚህን ነገሮች ሁሉ እኛን ለማሸነፍ ቢጠቀምም ማወቅና መንቃት አለብን።

ሐ. ከምንጋፈጠው ትግል በስተጀርባ ያለውን መንፈሳዊ ጦርነት ማስታወስ አለብን። ጴጥሮስ፥ «ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት» ይላል። ጴጥሮስ ሰይጣንን እንዴት እንደምንቃወም አልገለጸም። በክርስቶስ ስም ከዚህ ሂድ ብለን በመገሠጽ ነው? ጴጥሮስ በዚህ ክፍል እንዲህ ዓይነት እርምጃ እንድንወስድ አልመከረንም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰይጣንን ስለመቃወም የሚያሳየን ምሳሌ ክርስቶስ በምድረ በዳ ውስጥ የሰይጣንን ፈተና የተቃወመበት ነው (ማቴ. 4፡1-11)። ክርስቶስ በቀዳሚነት የሰይጣንን ፈተና የተቃወመው የእግዚአብሔርን ቃል በመጥቀስ ነው። እንዲሁም ሰይጣን ከእርሱ ፈቀቅ እንዲል በማዘዝ ነው። የዚህ ትእዛዝ ዐውድ እንደሚያሳየው፥ በስደትና መከራ ጊዜ ሰይጣን በተለይ ተግቶ ይዋጋናል። ሰይጣን እምነታችንን ለማጥፋት፥ ሕይወታችንን በመራርነት ለመሙላት፥ እምነታችንን እንድንክድ ወይም እንድንደብቅ ለማድረግ የሚታገል መሆኑን በመገንዘብ፥ በእምነት ጸንተን ልንቃወመው ይገባል። ሰይጣንን የምንቃወመው ችግሮች ወደ ሕይወታችን የገቡት ኃጢአት በመሥራታችን፥ እግዚአብሔር እየቀጣን በመሆኑ ስለማይወደን ወደ ጥንቷ መንገዳችን በመመለስ ከስደት እንድናመልጥ በመግለጽ የሚያመጣቸውን ውሸቶች ባለመስማት ነው። ለክርስቶስ ያለንን መሰጠት በማደስና ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕይወት በመኖር ሰይጣንን እንቃወማለን። ይህንን የስደትና የመከራ ችግር የምንጋፈጠው ብቻችንን እንዳልሆነ በመገንዘብ ልንበረታታ ይገባል። ብዙ አማኞች እነዚህን ችግሮች እየተቀበሉ በእምነታቸው ጸንተው ቆመዋል።

ሰይጣን መከራ በምንቀበልበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይስማማ እርምጃ በመውሰድ በምንፈተንበት ጊዜም በሕይወታችን ውስጥ ተሳትፎ ለማድረግ መጣሩ የማይቀር ነው። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ድልንም የምንቀዳጀው እንዴት ነው?

 1. መጸለይ አለብን፡- በክርስቶስ ኃይል ሰይጣን ከአካባቢያችን እንዲርቅ የማዘዝ ሥልጣን አለን? (መጽሐፍ ቅዱስ በክርስቶስ ስም መጸለይ ሲል ይህን ማለቱ ነው።) (ነገር ግን አንዳንድ ክርስቲያኖች በተሳሳተ መንገድ እንደሚጸልዩት ሰይጣንን ወደ ጥልቁ የመላክ ሥልጣን የለንም።) በሰይጣን ላይ ድልን ለመቀዳጀት መጽሐፍ ቅዱስ ጸሎታችን ቢያንስ አራት ነገሮችን ሊያካትት እንደሚገባ ያስተምራል።
 2. በሕይወታችን ውስጥ ያለውን ማንኛውንም ኃጢአት ማስወገድ አለብን። ንስሐ ያልተገባበት ኃጢአት የሰይጣን ምሽግ ነው። ይህን ምሽግ ለማስለቀቅ ክርስቲያኖች ኃጢአታቸውን ለእግዚአብሔር መናዘዝ ያስፈልጋቸዋል። ኃጢአቱ የተፈጸመው በሌሎች ሰዎች ላይ ከሆነ ደግሞ፥ ለሰዎቹም መናዘዝ ያስፈልጋል። ሰይጣን ከአካባቢያችን እንዲርቅ መጸለዩ ብቻ በቂ አይደለም። ኃጢአታችንን ከተናዘዝን በኋላ፥ እግዚአብሔር ሰይጣን በእኛ ላይ ያለውን ምሽግ እንዲያፈርስ ልንጠይቅ እንችላለን። እግዚአብሔር ጸሎታችንን እንደ መለሰ በማመንና በክርስቶስ ስምና ሥልጣን የሚቀርበውን የጸሎት ሥልጣን በመጠቀም፥ ሰይጣን ምሽጉን እንዲለቅ ልናዘው እንችላለን።
 3. እግዚአብሔር ከሰይጣን እንዲጠብቀን የእግዚአብሔርን የጦር መሣሪያ መታጠቅ አለብን። (ኤፌ. 6፡10-18 አንብብ።) የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃ ሳንለብስ ሰይጣን ከአካባቢያችን እንዲርቅ በመጠየቃችን ብቻ ለቅቆ እንደሚሄድ ወይም እንደሚሸነፍ ማሰብ የለብንም።
 4. ክርስቶስ የእግዚአብሔርንም ቃል እንድንጠቀም ያስተምረናል። ሰይጣን በፈተነው ጊዜ ሁሉ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ቃል በመጥቀስ ነበር ምላሽ የሰጠው። ለምሳሌ ያህል፥ ስለ አንድ ሰው እንድንዋሽ በሚጠይቀን ጊዜ «በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር» (ዘጸ. 20፡16) የሚለውን ዓይነት ጥቅስ መጠቀም ይኖርብናል።
 5. ጴጥሮስ የሰይጣንን ውሸቶች ላለማመን ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ እንዳለብን ይነግረናል። የሰይጣንን ፈተና ሳንቀበል እግዚአብሔር እርሱን ለመታዘዝ እንዲያስችለን በእምነት ብንጠይቀው፥ እውነተኞች እና ንጹሖች ሆነን እግዚአብሔር የሚፈልገንን ዓይነት ሕይወት ልንኖር እንችላለን። ሰዎች በሚሳለቁብን ጊዜ ከመቆጣት ወይም ለመበቀል ከማሰብ ይልቅ፥ ሰይጣን እንድናደርግ የሚፈልገውን ከማድረግ ይልቅ እነዚህን ሰዎች ለመርዳት፡ ይቅር ለማለትና ስለ እነርሱ ለመጸለይ እንመርጣለን። ሰይጣንም በሚፈትነን ጊዜ ሁሉ የሚለንን ላለመስማት ቁርጥ ውሳኔ መወሰን አለብን።

በዚህ ዓይነት፥ ሀ) በጸሎት፥ ለ) ኃጢአትን በመናዘዝ፥ ሐ) የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃ በመጠቀም፥ መ) በቃሉ አማካኝነት፥ እንዲሁም ሠ) ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ፥ ሰይጣንን እናሸንፋለን። እነዚህ አምስቱ ነጥቦች አስፈላጊዎች ናቸው። ንጹሕ ሕይወት ለመምራት ሳንቆርጥ መጸለይ ሰይጣንን አያሸንፈውም። ሳንጸልይ እና እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ሳንወስን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ብንጠቅስ ሰይጣን አይሸነፍልንም? ጸሎት፥ የእግዚአብሔር ቃልና የእኛ ቅዱሳን ለመሆን መምረጥ አስፈላጊዎች ናቸው።

ጴጥሮስ ሰይጣንን በመቃወሙ እና በእምነታችን በመጽናቱ ረገድ ልንበረታ እንደሚገባ በማሳሰብ ይህንን ክፍል ይደመድማል። ጴጥሮስ እግዚአብሔር በስደት ውስጥ ጸጋን እንደሚሰጠን ይነግረናል። እርሱ በእምነታችን ጠንክረን እንድንጸና ያስችለናል። አንድ ቀን ደግሞ መከራው ያበቃና በክርስቶስ የምናገኘውን ዘላለማዊ ክብር እንቀዳጃ ለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አብዛኛዎቹ አማኞች ጴጥሮስ ዲያብሎስን ተቃወሙት ሲል ምን ማለቱ ነው ብለው ያስባሉ? ለ) ብዙ ክርስቲያኖች ሰይጣን ከአካባቢያቸው እንዲርቅ በተሟሟቀ ሁኔታ እየጸለዩ፥ ዳሩ ግን በግል ሕይወታቸው በቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ በኃጢአት ላይ ድል የማይቀዳጁበትን ሁኔታ ግለጽ። ይህ የሚሆነው ለምን ይመስልሃል? ሐ) እነዚህ ሰይጣንን የመቃወሚያ አምስት ነጥቦች አስፈላጊ ናቸው? ከሆነ በሕይወትህ ሰይጣንን ለመቃወም እንዴት እንደተጠቀምክባቸውና ሰይጣንን ከአካባቢህ እንዲርቅ እንዳደረገ ግለጽ?

ማጠቃለያ (1ኛ ጴጥ. 5፡12-14)፡፡ ጴጥሮስ ስልዋኖስ (ሲላስ) በዚህ ደብዳቤ ውስጥ አስተዋጽኦ እንዳደረገለት በመግለጽ መልእክቱን ይፈጽማል። ሲላስ እንዴት እንደረዳው አልተገለጸም። ምናልባት ደብዳቤውን ከጴጥሮስ ተቀብሎ ወደ ተከታዮቹ አድርሶ ይሆናል። ምናልባትም ደግሞ ሲላስ ጴጥሮስ የሚናገረውን ቃል እየሰማ በጽሑፍ አስፍሮት ይሆናል።

ጴጥሮስ በባቢሎን ካሉት ወገኖች ሰላምታ ያቀርባል። ምናልባትም ይህ ሮምን የሚያመለክት ተምሳሌት ሊሆን ይችላል። ጴጥሮስ ማርቆስን በስሙ ጠርቶታል። በመጀመሪያው የወንጌል መልእክተኝነት ወቅት ከጳውሎስና በርናባስ ጋር አብሮ የነበረው ዮሐንስ ማርቆስ ነው። ቀደምት የቤተ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ማርቆስ በኋላ የጴጥሮስ ረዳት ሊሆን እንደቻለና ከጴጥሮስ ጋር ካለው ቅርበት የተነሣ የማርቆስን ወንጌል ሊጽፍ እንደበቃ ይናገራል።

የውይይት ጥያቄ፡– ከአንደኛ ጴጥሮስ ጥናት የተረዳሃቸው ቁልፍ ትምህርቶች ምን ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ለእግዚአብሔር መኖር እና ክርስቲያን በመሆን የሚደርስ መከራ (1ኛ ጴጥ. 4፡1-19)

ክርስቲያኖች የተቀደሰ ሕይወት መምራት ይኖርባቸዋል (1ኛ ጴጥ. 4፡1-6)።

በመከራ ውስጥ በማለፍ ክርስቶስ ድልን ተቀዳጅቷል። እግዚአብሔር ክርስቶስን በማክበር ከሁሉም በላይ ሥልጣን ሰጥቶታል። ክርስቲያኖች መከራ በሚቀበሉበት ጊዜ የክርስቶስን ምሳሌነት ቢከተሉ ድል ነሺዎች ይሆናሉ። ብንሠቃይም፥ በኃጢአት ተፈጥሮአችን ላይ ድልን እንቀዳጃለን። መከራ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ላይ እንዲደገፉ ይረዳቸዋል። ከዘላለም ዘመን አንጻር አስፈላጊው ነገር ምን እንደሆነ ለይተው እንዲያውቁ ያግዛቸዋል። በሕይወታችን ውስጥ ያለውን ኃጢአት ተመልክተን እግዚአብሔርን ይቅርታ እንድንጠይቅ ያግዘናል። በስደት የሚሠቃዩት ሰዎች በአመዛኙ የዓለማውያንን ፈሪሃ እግዚአብሔር የጎደለበት ሕይወት አይጋሩም። እምነታቸውን ክደው ወይም ደብቀው ከዓለማውያን ጋር ይተባበራሉ ወይም መከራን ከሚቀበሉ አማኞች ጋር ሆነው የተቀደሰ ሕይወት ይመራሉ። ነገር ግን ክርስቲያኖች መከራ የሚያደርሱባቸው ሰዎች የሚቀጡበት ጊዜ እንደሚመጣ ማስታወስ ይኖርባቸዋል። በክርስቶስ ለሚያምኑ ክርስቲያኖች፥ የዘላለም ሕይወት ተዘጋጅቶላቸዋል። በክርስቶስ የማያምኑ ሰዎች ግን የዘላለም ሞት ይጠብቃቸዋል። ዛሬ እምነታችንን ክደን ጊዜያዊውን መከራ ልናመልጥ ብንችልም፥ ይህ ለዘላለማዊ ፍርድ የሚያጋልጠን በመሆኑ አደገኛ ነው። ይልቁንም ጊዜያዊውን መከራ ተጋፍጦ ወደ ዘላለማዊ ሕይወት መሻገሩ አስተዋይነት ነው።

የእግዚአብሔር ሕዝብ ሌሎች አማኞችን ከልባቸው መወደድ ይኖርባቸዋል (1ኛ ጴጥ. 4፡7-11)።

ጴጥሮስ ስለ ጸሎት በማካፈል ማብራሪያውን ይጀምራል። በሚያስገርም ሁኔታ እንደ ባለ አእምሮ ማሰብንና ራስን መቆጣጠርን ከጸሎት ጋር ያዛምደዋል። ጸሎት ስለ አንዳንድ ነገሮች ስናስብ የምናነበንበው ልማድ መሆን የለበትም። እንዲሁም ጸሎታችን በራስ ወዳድነት ወይም በፍርሃት ላይ መመሥረት የለበትም። ይልቁንም ጸሎታችን አስፈላጊና ዘላለማዊ በሆኑት ነገሮች ላይ መመሥረት ይኖርበታል። እነዚህም ነገሮች በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተገለጡና የእግዚአብሔርን ዓላማዎች የሚያንጸባርቁ ናቸው። ይህም የእግዚአብሔር ዓላማዎች በስደታችን ውስጥ ጭምር የሚገለጡ ናቸው። መከራ በምንቀበልበት ጊዜ፥ «ይህን መከራ ከእኔ አስወግድ» የሚለው ጸሎት ወደ ልባችን መምጣቱ የማይቀር ነው። ነገር ግን ጴጥሮስ በመከራ ውስጥ የሚገለጹትን አንዳንድ የእግዚአብሔር ዓላማዎችንና ክርስቶስም በቅርብ ጊዜ እንደሚመለስ ከተረዳን ጸሎታችን እንደሚቀየር ይናገራል። በመከራችን ውስጥ ክርስቶስን ለማስከበር የምንችልበትን ኃይል እንድናገኝ መጸለይ እንጀምራለን፡፡ ለሚያሳድዱን ሰዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት እንድንችል የእግዚአብሔርን ኃይል እንጠይቃለን። እግዚአብሔር ሕይወታችንን እንዲቀድሰው እንጠይቀዋለን። ደፍረን ለመመስከር እንድንችልም እንጸልያለን።

በስደት ጊዜ ልናደርጋቸው ከሚገቡን ጉዳዮች አንዱ አማኞች እርስ በርሳችን በጥልቅ ፍቅር መዋደዳችን ነው። በስደት ጊዜ የተሳሳተ ግንዛቤ መያዝና በኃጢአት መውደቅ ሊከሰት ይችላል። ነገር ግን ስለ አንድ ሰው መጥፎውን ከማሰብ ወይም እርስ በርስ ከመጋጨት ወይም ቤተሰባዊ መሥመሮችን ተከትሎ ከመከፋፈል ይልቅ፥ አማኞች እርስ በርሳቸው ለመዋደድ መቁረጥ አለባቸው። ለእርስ በርሳችን ፍቅር ልናሳይ የምንችልባቸው አያሌ መንገዶች አሉ።

ፍቅራችን ሌሎች ኃጢአት በሚሠሩበት ጊዜ ቁጣችንን በመሸፈን፥ በስሜት መጎዳትና መከፋፈል እንዳይከሰት ያደርጋል።

 1. ስደት የደረሰባቸው ክርስቲያኖች ለሌሎች ክርስቲያኖች ማበረታቻ መስጠት አለባቸው። መተጨማሪም በእንግድነት ሊቀበሏቸው ይገባል።
 2. እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ አማኝ የተለያዩ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ሰጥቷል። እነዚህን ስጦታዎች እርስ በርሳችን ለማገልገል እና ለእግዚአብሔር ክብር ለማዋል ልንጠቀምባቸው ይገባል። መንፈሳዊ ስጦታዎች የሥልጣን ስፍራ እንድናገኝ ወይም ከሰዎች ክብርን እንድንቀበል፥ እንዲሁም ለማንኛውም የግል ጥቅም የምንገለገልባቸው አይደሉም (ጴጥሮስ ከጸጋ ስጦታዎች መካከል መናገርንና ማገልገልን በምሳሌነት ገልጾአል።) መንፈስ ቅዱስ እነዚህን ስጦታዎች የሚሰጠን አንዳችን ሌላችንን ለማገልገል እንድንችል ነው። ቁልፉ ነገር ስጦታውን መጠቀማችን ሳይሆን፥ ስጦታውን ስንጠቀም ሊኖረን የሚገባው አስተሳሰባችን ነው። ዋናው ነገር መንፈሳዊ ስጦታዎችን መጠቀማችን ብቻ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር የሰጠንን ስጦታዎች የምንጠቀምበት ባህሪም ወሳኝ ነው። መንፈሳዊ ስጦታችን ታላቅ መሆኑ እግዚአብሔርን አያስደንቀውም። ምክንያቱም የመንፈሳዊ ስጦታውን ደረጃ የወሰነው እርሱ ነው። ነገር ግን እግዚአብሔርን በዋናነት የሚያሳስበው ስጦታችንን በታማኝነት መጠቀማችን ነው። ክርስቶስ ሽልማትን የሚሰጠን እርሱ የሰጠንን ስጦታ በታማኝነት መጠቀማችንን በመመርመር እንጂ እርሱ በሰጠን የስጦታ ደረጃ አይደለም።

ክርስቲያኖች ስደትን በደስታ መቀበል አለባቸው (1ኛ ጴጥ. 4፡12-19)።

ጴጥሮስ አሁንም ወደ መጽሐፉ ዋነኛው ጉዳይ ይመለሳል። ይኸውም በዘመኑ የነበሩት ክርስቲያኖች የሚጋፈጡት ስደትና መከራ ነው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ለስደት የሚያቀርበውን ትምህርት አንድ ደረጃ ወደፊት ያልቀዋል። ጴጥሮስ መከራን እንድንቀበል ብቻ ሳይሆን መከራን በምንቀበልበት ጊዜ አጸፋውን እንዳንመልስም ጭምር ነው የሚያስተምረን፡፡ ክርስቲያኖች መከራን መቀበል ወይም መከራ የሚያደርሱባቸውን ሰዎች አለመበቀል ብቻ ሳይሆን፥ ስደትን እንደ ዕድል መቁጠር ይኖርባቸዋል። ይህም ደስ እንድንሰኝ ያደርገናል። የምንደሰተው በመሰደዳችን ሳይሆን፥ የክርስቶስ መከራ የመቀበል ዕድል ስለገጠመን ነው። በምንሰደድበትም ጊዜ ስለ እኛ መከራ ከተቀበለው ክርስቶስ ጋር እንተባበራለን። ለክርስቶስ መከራ መቀበል ደግሞ እግዚአብሔር እንደሚተማመንበትና እንደሚያከብረን የሚያመለክት ማስረጃ ነው። መሰደድ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ መኖሩን ያሳያል። ክርስቶስ በክብሩ በሚመለስበት ጊዜ ሽልማትን እንደምናገኝ እናውቃለን።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የእግዚአብሔር ሕዝብ ቤተሰባዊ ግንኙነት እና መልካም በማድረግ መከራን መቀበል (1ኛ ጴጥ. 3፡1-22)

፩. የእግዚአብሔር ሕዝብ ቤተሰባዊ ግንኙነት (1ኛ ጴጥ. 3፡1-7)

እግዚአብሔር እንደሚፈልገን ለመኖር እና የሚደርስብንን ስደትና መከራ ለማሸነፍ የምንችለው ጤናማ ቤተሰባዊ ግንኙነት ካለን ብቻ ነው። ይህም ግንኙነት ከእግዚአብሔር አካል፥ ከወላጆች፥ ከልጆች፥ ከወንድሞችና ከእኅቶች ጋር የሚደረገውን ቤተሰባዊ ግንኙነት ይመለከታል።

 1. ሚስቶች ለባሎቻቸው መገዛት አለባቸው (1ኛ ጴጥ. 3፡1-6)። ጴጥሮስ ሚስቶች ለባሎቻቸው መገዛት እንዳለባቸው ያስተምራቸዋል። ባሎቻቸው ክርስቲያኖች ባይሆኑም እንኳን መታዘዝ አለባቸው፡፡ ሴቶች መንፈሳዊ ባሕርያትን እንዲያጎለብቱ ይመክራቸዋል። እግዚአብሔር ይህን መልካም ባህሪያቸውን በመጠቀም ባሎቻቸውን ወደ ክርስትና እምነት እንደሚያመጣ ያስተምራል። ክርስቲያን ሴቶች በውጫዊ ውበት ላይ ሳይሆን፥ በውስጣዊ ባህሪያቸው ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።
 2. ክርስቲያን ባሎች ደጎችና ከሚስቶቻቸው ጋር በማስተዋል አብረው የሚኖሩ መሆን አለባቸው (1ኛ ጴጥ. 3፡7)። ጴጥሮስ በዚህ ክፍል ውስጥ ሚስቶችን እንዴት እንደሚገልጽ ልብ ብለህ ተመልከት።

ሀ) ተካፋዮች ናቸው፡፡ ሚስቶች ባሪያዎች አይደሉም። ወንድ እንደፈለገ የሚጫወትባቸው ንብረቶች አይደሉም። ይልቁንም ትዳሩን የመሠረተውን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት አብረው በእኩልነት የሚሠሩ ተካፋዮች ናቸው።

ለ) ሚስቶች ከባሎቻቸው ጋር አብረው የሕይወትን ጸጋ የሚወርሱ ናቸው። ጴጥሮስ የሚናገረው ስለ ድነት (ደኅንነት) እና ዘላለማዊ በረከት ነው። በአገራችን ለወንዶች ልጆች ከሴቶች ልጆች የበለጠ ትኩረት ስለሚሰጣቸው፥ በአብዛኛው ንብረትን የሚወርሱት ወንዶች ናቸው። ሴቶች ግን ምንም አይደርሳቸውም ማለት ይቻላል። እግዚአብሔር ግን ወንዶችንና ሴቶች ልጆቹን የሚመለከተው በዚህ ዓይነት መንገድ አይደለም። እርሱ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ድነትን (ደኅንነትን) እና የዘላለም በረከቶችን እኩል እንዲወርሱ ያደርጋል።

ሐ) “ሴቶች ደካማ ፍጥረቶች ናቸው፡፡” ጴጥሮስ ይህንን ሲል ምን ማለቱ ነው? በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊነት ከወንዶች ያነሱ ናቸው ማለቱ ይሆን? ብዙውን ጊዜ ሴቶች ከወንዶች በላይ ለመንፈሳዊ ነገሮች ንቁ ስለሆኑና በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ በትጋት ስለሚሳተፉ፥ ጴጥሮስ ይህንን ማለቱ አይመስልም። በአእምሮአቸው ይሆን የደከሙት? አይደለም። ሴቶችም የወንዶችን ያህል የማሰብ ችሎታ ያላቸው ናቸው፡፡ ምናልባትም ጴጥሮስ ሴቶች ደካማ ፍጥረቶች ናቸው ያለው ሁለት ነገሮችን ለማመልከት ይሆናል። በመጀመሪያ፥ ሴቶች በአካላዊ ጥንካሬ ከወንዶች ያነሱ ናቸው። የወንዶችን ያህል ብዙ ጭነት ሊሸከሙ አይችሉም። ሁለተኛ፥ ከሁሉም በላይ በስሜታዊ ጥንካሬ ከወንዶች ያንሳሉ፤ ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ሴቶች ከወንዶች ያነሰ ስሜታዊ ጥንካሬ ይታይባቸዋል።

ይህንን ቤተሰባዊ ግንኙነት ጤናማ አድርጎ መጠበቅ የሚያስፈልገውና በተለይም ባሎች ሚስቶቻቸውን መውደድ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ጴጥሮስ በቤት ውስጥ ግንኙነታችን ትክክል ካልሆነ፥ ጸሎታችንን እግዚአብሔር እንደማይመልስ ይናገራል። እግዚአብሔር ጸሎታችንን የማይሰማ ከሆነ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ኃይልን እናጣለን። ይህም ስደትን እንዳንቋቋምና ለኃጢአት ፈተና በቀላሉ እጅ እንድንሰጥ ያደርገናል።

የውይይት ጥያቄ፡– ባለትዳር ከሆንክ፥ ከትዳር ጓደኛ ጋር ያለህን ግንኙነት መርምር፡፡ ትዳር ጴጥሮስ እንዳለው እግዚአብሔርን የሚያስከብር ነውን? ካልሆነ፥ ኩራትህንና ኃጢአትህን ለእግዚአብሔር ተናዘዝ፡፡ ከዚያም ትዕቢትህን ለትዳር ጓደኛህ ተናዘዝ። እግዚአብሔር ጸሎትህን እንዲሰማ የትዳር ችግርህን በፍጥነት አስተካክል።

፪. መልካም በማድረግ መከራን መቀበል (1ኛ ጴጥ. 3፡8-22)።

ስደት ወደ እግዚአብሔር ሕዝብ በሚመጣበት ጊዜ የተለያዩ ነገሮች ይፈትኗቸዋል። እነዚህን ፈተናዎች መቋቋሙ አስፈላጊ ነው። የሚጎዱንን ሰዎች የመጥላትና መበቀል ፈተና ይኖራል። ወይም ደግሞ የሚያሠቃዩንን ሰዎች ለመበቀል ፈተና ይሆንብናል። ከአለማውያን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ላለማድረግ መፈተንም ይኖራል። ጴጥሮስ ክርስቲያኖች ለእነዚህ ፈተናዎች እጃቸውን እንዳይሰጡ ያስጠነቅቃል። ስደትን ከሚያመጡብን ዓለማውያን ጋር በሚኖረን ግንኙነት የሚከተሉትን ነገሮች ልናደርግ እንደሚገባ ይመክረናል፡

 1. አማኞች ከጎረቤቶቻቸው ጋር በሰላም ለመኖር የሚችሉትን ጥረት ሁሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
 2. ክርስቲያኖች ለጎረቤቶቻቸው ትሕትናን፥ ርኅራኄንና ፍቅርን ማሳየት ይኖርባቸዋል።
 3. የእግዚአብሔር ልጆች ጎረቤቶቻቸው በሚያሳድዱአቸው ጊዜ ሊበቀሏቸው፥ ወይም ሊሰድቧቸው አይገባም። ይልቁንም ክርስቲያኖች እርዳታ መጠየቅ የሚኖርባቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው።
 4. ክርስቲያኖች በልባቸው ክርስቶስን ሊቀድሱት ይገባል። ዓለም ከምትጠብቀው የተለየ ሕይወት ለመምራት መቁረጥ ይኖርብናል። ይህንን ልናደርግ የምንችለው ክርስቶስን የሕይወታችን ጌታና ንጉሥ ስናደርገው ነው። እንዲሁም በባህላችን ወይም በደመ ነፍሳችን ተመርተን ለበቀል ከመነሣሣት ይልቅ በሁሉም ነገር ክርስቶስን ስንታዘዘው ነው።
 5. ክርስቲያኖች በእነርሱ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋቸው ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጁ ሊሆኑ ይገባል። ጴጥሮስ ይህን ሲል ዓለም ከሚጠብቀው በተለየ መንገድ ለሁኔታዎች ምላሽ በምንሰጥበት ጊዜ ሰዎች እንደሚደነቁ መግለጹ ነው። በዚህም ጊዜ ወደ አማኞች መጥተው ለምን ልንለይ እንደቻልን ይጠይቁናል። በዚህም ጊዜ ክርስቲያኖች ክርስቶስ ስለሰጣቸው ተስፋ ለመመስከር መዘጋጀት አለባቸው። ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ዓለማውያንን በቃላቸው ዝብዘባ ለማሳመን ይሞክራሉ። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ የክርስቲያንም የዓለማዊውም ተግባር ተመሳሳይ ነው። እኛ ክርስቲያኖቹ እንደ ዓለማውያኑ የተከፋፈልን፥ የምናጭበረብር፥ ጉቦ የምንሰጥ፥ እንዲሁም የሚጎዱንን ሰዎች የምንበቀል ሆነናል። በመሆኑም፥ ብዙ ዓለማውያን ሊሰሙን አይፈልጉም፥ ምክንያቱም የእነርሱም የእኛም ሕይወት ተመሳሳይ ነውና። ጴጥሮስ በፍቅር፥ በገርነትና በከበሬታ እየተመላለስን መንፈሳዊ ሕይወት የምንኖር ከሆነ፥ ብዙውን ጊዜ የሚያሳድዱን ዓለማውያን በሥራቸው እንደሚያፍሩ ይናገራል። ከዚያም በክርስቶስ አምነው የእኛን ደስታ፥ ሰላምና መንፈሳዊ ሕይወት ይጋራሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በአሁኑ ጊዜ ክርስቲያኖች ለስደት ምላሽ የሚሰጡት ጴጥሮስ ባስተማረው መንገድ ነውን? ለ) አንድ አማኝ በስደትና በመከራ በሰጠው መልካም ምላሽ ምክንያት እግዚአብሔር ብዙ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ያመጣበትን ሁኔታ ጥቀስ። ሐ) የአማኞች ትክከለኛ ያልሆነ ተግባርና አመለካከት ሰዎችን ከወንጌል ስላገለለበት ሁኔታ ምሳሌዎችን ስጥ።

ጴጥሮስ ክርስቶስ ስደትን ስለምንቀበልበት ሁኔታ መልካም ምሳሌአችን መሆኑን ይናገራል። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡17-22 በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለመረዳት ከሚያዳግቱን ምንባቦች አንዱ ነው። በዚህ ስፍራ ጴጥሮስ ለማስተላለፍ የሚፈልገውን መልእክት ለመረዳት ከመሞከራችን በፊት የዚህን ክፍል ዋነኛ ትምህርት መመልከቱ ጠቃሚ ይሆናል። በ1ኛ ጴጥሮስ 2፡18-25 ክርስቶስ ምንም ኃጢአት ሳይሠራ መከራ እንደ ተቀበለና እንደ ሞተ እኛም ኃጢአት ሳንሠራም እንኳን በክርስቶስ ላይ ላለን እምነት መከራን መቀበልና መሞት እንዳለብን አስረድቷል። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡17-22 በድጋሚ ወደ ክርስቶስ ምሳሌነት ይመለከታል። በዚህ ጊዜ ግን ጴጥሮስ ከክርስቶስ ሞት በኋላ ስለተፈጸመው ነገር ይናገራል። ክርስቶስ መከራ ተቀብሎ ቢሞትም፥ እንደ ሞተ አልቀረም። እግዚአብሔር ከሞት አስነሥቶ በክብርና በሥልጣን መቀመጫ በቀኙ አስቀምጦታል። እግዚአብሔር ለክርስቶስ ፍትሕ በመስጠቱ የማይታዘዙ መናፍስትን ጨምሮ ከሁሉም በላይ አክብሮታል።

በተመሳሳይ ሁኔታ አማኞች መከራ ተቀብለው ቢሞቱም፥ ይህ ግን ፍጻሜአቸው አይሆንም። ከሞት ተነሥተው ወደ ሰማይ ይገባሉ፡፡ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር ፍትሕን ይሰጣቸዋል። ምክንያቱም እግዚአብሔር በኖኅ ዘመን በዓለም ላይ ያመጣውን ፍርድ የሚመስል የፍርድ ቀን እየመጣ ነው፡፡ እግዚአብሔር በኖኅ ዘመን ሰዎችን በኃጢአታቸው አለመቅጣቱ ፍትሐዊ መስሎ እንዳልታየ ሁሉ፥ ዛሬም እግዚአብሔር ሰዎች ለእምነታቸው መከራ እንዲቀበሉ ማድረጉ ፍትሐዊ ላይመስል ይችላል። ነገር ግን እግዚአብሔር በኖኅ ዘመን ሰዎች ከኃጢአታቸው ንስሐ እንዲገቡና ከጥፋትም እንዲድኑ ለ120 ዓመታት በትዕግሥት ሲጠብቃቸው ቆይቷል። በመጨረሻም በምድር ላይ ከነበሩት በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች 8 የኖኅ ቤተሰቦች ብቻ ሊድኑ በቅተዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ እግዚአብሔር ለልጆቹ ፍትሕን በመስጠት በዓለም ውስጥ ያሉትን ክፉ ሰዎች የማያጠፋው ንስሐ ገብተው በክርስቶስ እንዲያምኑ ዕድል ለመስጠት ነው። አንድ ቀን ግን የእግዚአብሔር ትዕግሥት ያልቅና ለልጆቹ ፍትሕን ይሰጣል። የሚያሳዝነው እንደ ኖኅ ዘመን በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ዓላማውያን መካከል ድነት (ደኅንነት)ን የሚያገኙ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። እግዚአብሔር በስደት ውስጥ እያሉ ምላሽ ባለመስጠቱና ፍትሕን ባለማምጣቱ ተስፋ ቆርጠው በራሳቸው እጅ ለመበቀል ከሚነሣሱ፥ እንደ ኖኅ እግዚአብሔርን በመተማመን በትዕግሥት ሊጠብቁት ይገባል። እግዚአብሔር በጊዜው ፍትሕን ይሰጣቸዋል። ምክንያቱም ምሳሌአቸው የሆነው ክርስቶስ በሰዎችም ሆነ በመናፍስትም ላይ ሥልጣን አለው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር አንድ ቀን የሚያሳድዱን ሰዎች ንስሐ ገብተው የማያምኑ ከሆነ ወደ ፍርድ የሚያቀርባቸው የመሆኑ ሁኔታ ዛሬ ስደትን በትዕግሥት እንድንቀበል የሚያስችለን እንዴት ነው? ለ) ከዚህ ክፍል ስለ እግዚአብሔር ባህሪ እና ፍላጎት፥ እንዲሁም ስለ ክርስቶስ ኃይል ምን እንማራለን?

ጴጥሮስ ክርስቶስ ከሞተ በኋላ የተከሰቱትን አንዳንድ ነገሮች ጠቅለል አድርጎ ያቀርባል።

 1. ክርስቶስ ቢሞትም ተነሥቷል።
 2. ክርስቶስ ከረጅም ጊዜ በፊት ላልታዘዙት መናፍስት በወኅኒ ሰብኮላቸዋል። ይህ ለመረዳት የሚያስቸግር ምንባብ ነው። ከዚህ ክፍል፥ ሀ) ክርስቶስ መቼ እንደ ሰበከ መረዳቱ አስቸጋሪ ነው። ይህ የሆነው ክርስቶስ ከሞተ በኋላና ከመነሣቱ በፊት ነው? ከተነሣ በኋላ ነው? ወይስ ቀደም ሲል በኖኅ ዘመን ነበር? ለ) መናፍስት የተባሉት እነማን ናቸው? የወደቁ መላእክት ወይስ የሞቱ ሰዎች? ሐ) የቀረበው ስብከት ምን ነበር? ድነት (ደኅንነት)፥ ፍርድ ወይስ የድል አዋጅ?

ሰዎች ይህንን ክፍል በተለያዩ መንገዶች ተረድተዋል። ከእነዚህም መካከል ሦስቱ ዐበይት አተረጓጎሞች የሚከተሉት ናቸው።

 1. አንዳንድ ምሁራን ይህ ክፍል ክርስቶስ ከመሞቱ በፊት የነበረውን ሁኔታ ያመለክታል ይላሉ። ክርስቶስ በኖኅ ምስክርነት ውስጥ በኖኅ ዘመን የነበሩት ኃጢአተኞች ንስሐ ገብተው እንዲመለሱ ሰብኳል ሲሉ ያስተምራሉ። ይህ ለክፍሉ አሳብ የሚቀርብ አተረጓጎም አይመስልም።
 2. ሌሎች ምሁራን ደግሞ ክርስቶስ ከሞተ በኋላ እና ከመነሣቱ በፊት የሞቱ መናፍስት ወይም የሞቱ ሰዎች ወደሚኖሩበት ስፍራ እንደ ወረደ ይናገራሉ። በዚያም በጥፋት ውኃ ወቅት ለሞቱት ሰዎች ሰበከላቸው። ለእነዚህም ሰዎች ወንጌልን ወይም ደግሞ በአዳኝነት ያገኘውን ድል፥ እንዲሁም ባለማመናቸውና በአመፃቸው ምክንያት የጠፉ መሆናቸውን ገልጾአል።
 3. ሌሎች ምሁራን ደግሞ ጴጥሮስ በኖኅ ዘመን የእግዚአብሔር ልጆች የተባሉ መላእክት የሰዎች ሴቶች ልጆች ከተባሉት ሰብአዊ ፍጡራን ጋር የወሲብ ኃጢአት መፈጸማቸውን እንደሚያመለክት ይናገራሉ (ዘፍጥ. 6፡1-4)፥ መሳ. 6፤ 2ኛ ጴጥ. 2፡4)። እግዚአብሔር እነዚህን መላእክት በፍርድ ወደ ጥልቁ ጉድጓድ (ወኅኒ) ላካቸው፥ በዚያም በመጨረሻው ዘመን የሚመጣውን የፍጻሜ ፍርድ ይጠባበቃሉ። ይህን አሳብ የሚያቀርቡ ምሁራን ክርስቶስ ከሞተ በኋላና ከመነሣቱ በፊት ወደዚህ ጉድጓድ ወርዶ በሰይጣንና በክፉ መላእክት ሁሉ ላይ ድል መቀዳጀቱን እንዳወጀ ያስረዳሉ። (አንዳንድ ምሁራን እነዚህ የወደቁ መላእክት ሁሉንም ክፉ መናፍስት ወይም አጋንንት በተምሳሌትነት እንደሚያሳዩ ይናገራሉ)። በመሆኑም ክርስቶስ በትንሣኤው ወቅት በእነርሱ ላይ ድል መቀዳጀቱንና የተሸነፉ ጠላቶች መሆናቸውን ገልጾላቸዋል። (ቆላ. 2፡15 አንብብ።]

ጴጥሮስ እነዚህን በወኅኒ ያሉትን መናፍስት የጠቀሰው በእግዚአብሔር በቀል ከሞት የተነሣው ክርስቶስ ምን ያህል ታላቅ ኃይል እንዳለው ለማሳየት ሳይሆን አይቀርም። ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ በሰዎችና በመንፈሳውያን ፍጥረታት ሁሉ ላይ ሥልጣንና ኃይል አለው (ቆላ. 2፡15)። የክርስቶስ ኃይል እና ሥልጣን እጅግ ታላቅ በመሆኑ በኖኅ ዘመን በእግዚአብሔር ላይ ባመፁት በእነዚህ ክፉ መናፍስት እና መንፈሳዊ ፍጥረታት ላይ የተቀዳጀውን ሥልጣን ገልጾአል።

ጴጥሮስ የኖኅን ዘመን ክፋት በጠቀሰ ጊዜ፥ በዘመኑ የነበሩት አማኞች ሁኔታ ኖኅ ከነበረበት ጊዜ ጋር የሚመሳሰል መሆኑን አጢኗል። እንዲሁም በጥፋት ውኃና በጥምቀት ውኃ መካከል ያለውን አንድነት ተረድቷል። ጴጥሮስ በዚህ ስፍራ ለማስተላለፍ የሚፈልገውን መልእክት መረዳቱ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ይህን ክፍል በተሳሳተ መንገድ የተረዱ ክርስቲያኖች ሰውን የሚያድነው የውኃ ጥምቀት ነው የሚለውን አሳብ ስለሚጠቀሙበት ነው፡፡ (ማስታወሻ፡— በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጥምቀት ሰውን ሊያድን እንደሚችል የሚያሳይ ብቸኛው ጥቅስ ይሄ ብቻ ነው። ጥምቀት ሰውን የሚያድን ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር በሌሎች የአዲስ ኪዳን ምንባቦች ውስጥ በግልጽ ባሠፈረው ነበር።) የሚታየው የውኃ ጥምቀት ማንንም እንደማያድን አዲስ ኪዳን በግልጽ ይናገራል። አለዚያማ፥ ድነት (ደኅንነት) እኛ የምናደርገው ተግባር ይሆን ነበር። ጳውሎስ ግን በሮሜ፥ ገላትያ፥ እንዲሁም ኤፌሶን መልእክቶች ውስጥ ድነት (ደኅንነት) በክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ነፃ ስጦታ መሆኑን አመልክቷል። (ለምሳሌ፥ ኤፌ. 2፡8-9 አንብብ)። በሌሎች የአዲስ ኪዳን ክፍሎች ጥምቀት የሚጠቀሰው ከንስሐ ወይም ከእምነት ቀደም ብሎ ነው። (ለምሳሌ፥ የሐዋ. 2፡38)። ጴጥሮስ የውኃ ጥምቀት ድነትን ያስገኛል ማለቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ምክንያቱም ጥምቀት ከሰውነት ላይ እድፍን ማስወገድ ሳይሆን፥ ሕሊናን ማንጻት እንደሆነ ያስረዳል። ውኃ ኃጢአትን ሊያጥብ አይችልም። ይህን ሊያደርግ የሚችለው በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ያለን እምነት ብቻ ነው።

ጴጥሮስ ጥምቀት ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ለመረዳት የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ይህን ቃል እንዴት እንደ ተረዳች ማወቁ ጠቃሚ ነው። ለእኛ ጥምቀት ማለት አንድ እማኝ የሚያደርገው ተግባር ነው። ብዙውን ጊዜ አማኞች በክርስቶስ ካመኑ ከ3-6 ወራት መንፈሳዊ ትምህርት ከተከታተሉ በኋላ፥ ከክርስቶስ ላለመለየት እና የቤተ ክርስቲያን አባል ለመሆን የሚፈልጉ መሆናቸውን ለማሳየት የውኃ ጥምቀት ይወስዳሉ። አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ሕጻናትን ያጠምቃሉ። ይህም የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን ለማሳየት የሚወስዱት እርምጃ ነው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ግን ጥምቀት የተገለጸው ለየት ባለ ሁኔታ ነው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሰዎች የሚጠመቁት በክርስቶስ እንዳመኑ ወዲያውኑ ነው (የሐዋ. 8፡36-39፤ 16፡30-33 አንብብ)። ጆሲፈስ የተባለው አይሁዳዊ ጸሐፊ ከጴጥሮስ ዘመን ትንሽ ዘግየት ብሎ ሲጽፍ ሰዎች ወደ መጥምቁ ዮሐንስ ለመጠመቅ የሚመጡት የጽድቅ ኑሮ ለመምራት ሰዎችን በፍትሕ ለማስተናገድና በእግዚአብሔር ፊት የተቀደሰ ኑሮ ለመምራት፥ በዚሁም የጥምቀቱ ተካፋይ ለመሆን በመወሰን ነው ብሏል። የክርስትና ጥምቀት የመጥምቁ ዮሐንስን ጥምቀት ምሳሌነት የተከተለ ነው። በመሆኑም የቀድሞዎቹ አማኞች በሚጠመቁበት ጊዜ ውኃው እንደሚያድናቸው አያስቡም ነበር። ነገር ግን ይህ በልባቸው ውስጥ የተፈጸመውን ነገር በይፋ የሚገልጹበት መንገድ ነበር። ክርስቲያኖች ሲጠመቁ በክርስቶስ ማመናቸውን ያሳያሉ። ከዚህም በኋላ ክርስቶስን በጽድቅ፥ በተቀደሰ ሕይወትና ከሌሎች ጋር እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ግንኙነት በማድረግ ለመከተል ይወስናሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖችና የዛሬዎቹ ክርስቲያኖች ስለ ጥምቀት ያሉዋቸውን አመለካከቶች እነጻጽር። ልዩነቶቻቸውና አንድነቶቻቸው ምን ምንድን ናቸው?

ጴጥሮስ በዚህ ስፍራ ለማስተላለፍ የፈለገው መልእክት ምንድን ነው? ጴጥሮስ በኖኅ ዘመን የተፈጠረውን ሁኔታ ክርስቲያኖች ከሚያልፉበት ሁኔታ ጋር ያነጻጽረው ነበር። ሁለቱም የኖሩት በክፉ ዘመን ውስጥ ነበር። በሁለቱም ጊዜያት፥ እግዚአብሔር ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ እየተጠባበቀ ቅጣትን አዘግይቷል። በሁለቱም ጊዜያት፥ እግዚአብሔር የኋላ ኋላ ኃጢአተኞችን ቀጥቷል። በሁለቱም ጊዜያት፥ በአንጻራዊነት ጥቂት ሰዎች ብቻ ድነዋል። በሁለቱም ጊዜያት፥ እግዚአብሔር ሰዎችን ለማዳን ውኃን ተጠቅሟል።

በኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ በክፉ ሰዎች ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ ከማምጣቱም በላይ፥ ድነትንም (ደኅንነትም) እንዳስገኘ ጴጥሮስ ገልጾአል። እግዚአብሔር ውኃውን ተጠቅሞ መርከቢቱ ወደ ላይ ከፍ እያለች ያለ ስጋት እንድትሄድ አድርጓታል። ስለ ጥፋት ውኃው ማሰብ ጴጥሮስ የጥምቀት ውኃንም ጉዳይ እንዲያነሣ አድርጎታል። ጥምቀት በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ የተፈጸመውን ነገር ሁሉ በተምሳሌትነት ያሳያል። አማኞች በክርስቶስ በማመናቸው፥ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ለመኖር በመቁረጣቸውና በጥምቀት እምነታቸውን በይፋ በመግለጻቸው፥ እግዚአብሔር ከዚህ ክፉ ዓለም አድኗቸዋል።

መንፈስ ቅዱስ በልባችን ላይ ስላለው ኃጢአት በሚወቅሰን ጊዜ እንደ ኖኅ የእምነት ምላሽ መስጠት አለብን፡፡ እራሳችንን ለእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች ማስገዛት ይኖርብናል። ለኖኅ፥ ይህ መርከብ መሥራትንና ዝናብ ከመውረዱ በፊት ወደ መርከቢቱ መግባቱን ያጠቃልል ነበር። ለእኛ ደግሞ፥ ክርስቶስ በእኛ ፈንታ መሞቱ እንደሚያድነን ማመንንና በክርስቶስ የተስፋ ቃሎች መመላለስን ይጠይቃል። ጥምቀት ለድነታችን (ለደኅንነታችን) በክርስቶስ እንደምናምን የሚያሳይ ውጫዊ ተምሳሌት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች ድነት (ደኅንነት) ከመጠመቅ እንደሚገኝ ሲያስተምሩ ሰምተህ ታውቃለህ? ለ) እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ወንጌል ከእግዚአብሔር የምንቀበለው ስጦታ ሳይሆን ራሳችን የምናከናውነው ተግባር መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው? ሐ) እላይ የቀረበውን ማብራሪያ በመጠቀም፥ ጴጥሮስ ስለ ጥምቀትና ድነት (ደኅንነት) ያቀረበውን አሳብ እንዴት ትገልጻለህ?

ጴጥሮስ ውኃ ለኖኅና ለአማኞች ያስገኘውን ድነት (ደኅንነት) ካነጻጸረ በኋላ፥ አማኞች የክርስቶስን ምሳሌነት በመከተል ለሚደርስባቸው መከራ እንዴት መልስ ሊሰጡ እንደሚገባ ያስረዳል። የክርስቶስ ትንሣኤ አማኞች የኋላ ኋላ ከሞት እንደሚነሡና ድነት እንደሚቀዳጁ ዋስትና ይሰጣል። ክርስቶስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ከእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦአል። በዚያም ሰዎችም ሆኑ መላእክት ከሥልጣኑ ሥር ይሆናሉ። ክርስቶስ በሰይጣን ላይ ሥልጣን ስላለው በአማኞች ሕይወት ውስጥ ስደትንና መከራን በማምጣት ሊያከናውን የሚፈልጋቸውን ተግባራት ይገድባል። ክርስቶስ ብዙውን ጊዜ የእግዚአብሔርን ልጆች በሚያሳድዱበት የመንግሥታት መሪዎችና የማያምኑ ሰዎች ላይ ሥልጣን አለው። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ እግዚአብሔር ስደትን ለተቀበሉት ክርስቲያኖች ፍትሕን የሚሰጥበት ቀን ይመጣል። በጠላቶቻቸው ላይ ሥልጣን ተቀዳጅተው ከክርስቶስ ጋር ይነግሣሉ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ለአለቆችና ለጌቶች መታዘዝ (1ኛ ጴጥ. 2፡13-25)

የአንደኛ ጴጥሮስ መልእክት የመጨረሻው ዐቢይ ክፍል የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ መሆናችንን በሚያንጸባርቅ መልኩ ከዓለም የተለየ ሕይወት ልንኖር የምንችልባቸውን የተለያየ የሕይወት ክፍሎች ይመረምራል።

ሀ. ክርስቲያኖች ለመንግሥት መሪዎች መገዛት አለባቸው (1ኛ ጴጥ. 2፡13-17)። ሁሉም የመንግሥት ባለሥልጣናት እግዚአብሔርን ቢያከብሩም ባያከብሩም እግዚአብሔርን ቢያምኑም ባያምኑም፥ በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። ስለሆነም አማኞች መሪዎቻቸውን ማክበርና መታዘዝ ይኖርባቸዋል። ይህም ማለት ቀረጥን እንዲከፍሉ በሚጠየቁበት ጊዜ ከማጭበርበር ይልቅ መክፈል አለባቸው ማለት ነው። ወደ ማኅበራዊ ስብሰባዎች በመሄድ መሳተፍ አለባቸው ማለት ነው። ለከተማችንና ለሀገራችን ይበጀናል የምንላቸውን ሰዎች ለመመረጥ የሚያግዝ ድምጽ መስጠትንም ይጨምራል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች ለመንግሥት መሪዎች ሊገዙ የሚችሉባቸውን ሌሎች ምሳሌዎች ዘርዝር። ለ) ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ መንግሥት የመሠረታቸውን ግዴታዎች ላለማሟላት ጥረት የሚያደርጉባቸውን መንገዶች ዘርዝር። እግዚአብሔር ይህንን አመለካከት እንዴት እንደሚመለከት ግለጽ።

ለ. ክርስቲያን ባሪያዎች (ሠራተኞች) መከራ ቢቀበሉም እንኳን ለሰብአዊ ጌቶቻቸው መገዛት አለባቸው (1ኛ ጴጥ. 2፡18-25)። ጌቶቻቸው (አሠሪዎቻቸው) መልካም፥ አፍቃሪ ወይም ሰው የሚጠሉ መሆናቸው ለውጥ አያመጣም። አማኞች ምንም ኃጢአት ሳይሠራ መከራ የተቀበለውን የክርስቶስን ምሳሌነት መከተል ይኖርብናል። ይህም በባህሪያችንና በተግባራችን ሁሉ ሊገለጥ የሚገባው ነው። ክርስቶስ ምንም ኃጢአት ሳይሠራ ለእኛ ኃጢአት ሲል ሞቷል። ከዚህም የተነሣ፥ ይቅርታ ተደርጎልን የክርስቶስን ጽድቅ ሰጥቶናል። በተመሳሳይ መንገድ ባሪያዎች (ሠራተኞች) ምንም ዓይነት ጥፋት ሳይፈጽሙ መከራ መቀበላቸውን ማረጋገጥ አለባቸው። ክርስቲያን ባሪያዎች ለእምነታቸው ወይም ትክክለኛ የሆነውን ነገር በማድረጋቸው መከራን በሚቀበሉበት ጊዜ እንዴት የትሕትና መንፈስ ሊኖራቸው ይችላል? ጴጥሮስ ለዚህ ቁልፉ ለእግዚአብሔር ሥልጣን መገዛት እንደሆነ ይናገራል። እግዚአብሔር ይህን እውነት እንዳስከተለ መገንዘብ፥ ክርስቲያን ራሱን ለእግዚአብሔር አሳልፎ ይሰጣል። እግዚአብሔር አንድ ቀን ፍትሕን ይሰጠዋል። ከሁሉም በላይ ክርስቶስ ዛሬም እረኛችን በመሆኑ ነፍሳችንን ይጠብቃል። እንደ ባሪያዎች ስንሰደድ ወይም አለአግባብ ሥቃይ ሲደርስብን እርሱ ይታደገናል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሕያዋን ድንጋዮች ናቸው (1ኛ ጴጥ. 2፡4-12)።

በስደትና መከራ ጊዜ ክርስቲያኖች ከሚዘነጓቸው ነገሮች አንዱ ክርስቲያናዊ ማንነታቸውን ነው። ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ የተረገጡ፥ የተጨቆኑና ማኅበረሰቡ እንደ ከንቱ ነገር የሚቆጥራቸው ናቸው። «ደደቦች ናችሁ» የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ በክርስቲያኖች ጆሮ ያቃጭላል። ሰይጣን ብዙውን ጊዜ በዚህ ሰዓት ወደ እኛ በመቅረብ ክርስቶስን በመከተላችንና እንደ ሌሎች ሰዎች ባለመሆናችን የሞኝነት ውሳኔ እንደ ወሰንን እንድናስብ በማግባባት ይፈትነናል። እንዲሁም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር እንድንጠራጠር ይፈትነናል። ጴጥሮስ ለእነዚህ የሰይጣን ውሸቶች ምላሽ ሲሰጥ በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ማን እንደሆንን፥ እንዲሁም የእኛ ሁኔታ በክርስቶስ ላይ ከደረሰው ጋር እንዴት እንደሚመሳሰል ያስረዳል።

የአማኞች እውነተኛ ማንነት፡

ሀ) ሕያዋን ድንጋዮች፡ ጴጥሮስ የአማኞችን እምነት ለመግለጽ የራሱን ስም ተጠቅሟል። የጴጥሮስ የመጀመሪያው ስም ስምዖን እንደ ነበር ታስታውሳለህ። ነገር ግን ክርስቶስ ከጴጥሮስ ጋር በተገናኘበት ወቅት የጴጥሮስን ስም ወደ ድንጋይነት ለወጠው። (በአረማይክ ኬፋ፥ በግሪክ ደግሞ ጴጥሮስ ሁለቱም ድንጋይ ወይም ዓለት የሚል ፍቺ ይሰጣሉ።) [(ዮሐ. 1፡42)]። በኢየሩሳሌም ያለውን ዓይነት በክብር ያሸበረቀ ቤተ መቅደስ በማሰብ ጴጥሮስ እያንዳንዱን አማኝ በእግዚአብሔር ልዩ ቤት (የእግዚአብሔር ሕዝብ) በጥንቃቄ እንደ ተጠረበ ድንጋይ መሆኑን ይናገራል። የእግዚአብሔር ቤት ከድንጋይና ከስሚንቶ የተሠራ ሕይወት የሌለው ሕንጻ ሳይሆን፥ ሕያው ቤት ነው። አንድ ሰው በሚያምንበት ጊዜ በዚህ ዘወትር እያደገ በሚሄደው በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ሕያው ድንጋይ ይሆናል። ይህ ሕያው ቤት ዘላለማዊ እና ሰዎች ከሚያንጹአቸው የአምልኮ ሕንፃዎች የላቀ ነው። (ማስታወሻ፡ ይህ ለአምልኮ የምንገነባው ሕንፃ ለእግዚአብሔር እርሱ እየገነባ ካለው የቤተሰቡ መንፈሳዊ ቤት ጋር ሲነጻጸር እንደማይስተካከለው ያስታውሰናል። ለእግዚአብሔር ምንም ያህል ታላቅ የጸሎት ቤት ብንሠራም፥ አንድ ቀን መደምሰሱ አይቀርም። ነገር ግን እግዚአብሔር ለልጆቹ ሕይወት የሚሠራውን ቤት ማንም ሊያጠፋው አይችልም።)

ለ) ቅዱስ ካህናት፡- ክርስቲያኖች ባሪያዎች ወይም ጌቶች፥ የተማሩ ወይም ያልተማሩ፥ ብዙ ስጦታ ወይም አንድ ስጦታ ብቻ ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን እያንዳንዱ አማኝ ካህን ነው። ካህን እንደ መሆኑ መጠን እያንዳንዱ ክርስቲያን ለእግዚአብሔር መሥዋዕቶችን የማቅረብ ዕድል አለው። እነዚህም መሥዋዕቶች እግዚአብሔርን ደስ ያሰኙታል። ይህ በብሉይ ኪዳን ለሌዋውያን የተወሰኑ ልዩ የሕዝብ ቡድኖችን ብቻ እግዚአብሔርን በዚህ መልኩ ከሚያገለግሉበት መንገድ የተለየ ነው። ዛሬ በዘመናችን ከተቀሩት አማኞች የበለጡ ናቸው ተብለው የሚታመኑትን የተወሰኑ ሰዎች (ካህናት፥ ሽማግሌዎች ወይም መጋቢዎች) ለአገልግሎት በመለየትና እግዚአብሔርን የማገልገል በረከት እንዲያገኙ በማድረግ ልንሳሳት አይገባም። እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ሌሎች ምእመናን ቁጭ ብለው እንዲመለከቱ የሚያደርግ በመሆኑ ተገቢነት ሊኖረው አይችልም። ጴጥሮስ አማኞች ሁሉ ካህናት የመሆንና እግዚአብሔርን የማገልገል መብትና ዕድል እንዳላቸው ይመለከታል። ለእግዚአብሔር የምናቀርባቸው መሥዋዕቶች ምን ምን ናቸው? ጴጥሮስ የምሥጋናን መሥዋዕት ማቅረብ እንዳለብን ይገልጻል። ይህን ሲል ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምሥጋና መዝሙር መዘመሩን ብቻ ማለቱ አይደለም። ነገር ግን ለእግዚአብሔር የምናቀርበው ምሥጋና እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ የምንኖረው ሕይወት ነው። ሰውነታችን (ሮሜ 12፡1-2)፥ ገንዘባችን (ፊልጵ. 4፡18)፥ ምሥጋናችን (ዕብ. 13፡15)፥ እንዲሁም መልካም ተግባራችን (ዕብ. 1፡16) ሁሉ ለእግዚአብሔር የምንሠዋው መሥዋዕቶቻችን ናቸው። እንዲሁም በአኗኗራችን፥ ለሌሎች በመማለድ፥ በጠፋው ዓለም ውስጥ እግዚአብሔርን በመወከል የእግዚአብሔርን ቅድስና እያንጸባረቅን የክህነት አገልግሎት ልናበረክት እንችላለን።

ሐ) የተመረጠ ሕዝብ፡ በብሉይ ኪዳን የነበሩት አይሁዶች ከዓለም ሕዝብ ሁሉ ተመርጠው የእግዚአብሔር ልዩ ሕዝቦች (ዘጸ. 19፡5-6) ሆነዋል። ጴጥሮስ ብዙውን ጊዜ አይሁዶች ከእግዚአብሔር ጋር ስላላቸው ልዩ ግንኙነት ሲናገሩ ሲሰሙ የኖሩት አሕዛብም የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝቦች መሆናቸውን ይናገራል። እግዚአብሔር በምድር ላይ ላሉት ሰዎች ሁሉ እነዚህ የቤተሰቡ አባላት እንዲሆኑ መርጧቸዋል። ጠላቶቹ የነበርነውን ሰዎች የቤተሰቡ አባላት በማድረጉ እግዚአብሔር ታላቅ ምሕረቱን ገልጾአል።

መ) የንጉሥ ካህናት፡ ይህ የንጉሥን ስፍራ ከካህናት ለይተው ለሚመለከቱ አይሁዶች የሚቻል አልነበረም። ነገር ግን ጴጥሮስ ክርስቲያኖች እንደ ሌዊ ዝርያዎች ካህናት ብቻ ሳይሆኑ፥ እንደ ዳዊት ነገድ የንጉሥ ልጆች መሆናችንን ያስረዳል። በምድር ላይ ሰዎች የዝነኛ ሰው ወይም የመንግሥት ባለሥልጣን ልጆች በመሆናቸው ይኩራራሉ። ጴጥሮስ ክርስቲያኖች የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ ልጆች በመሆናቸው ሊመኩ እንደሚችሉ ይናገራል። ይህ በምድር ላይ ለሰዎች፥ በግልጽ ላይታይ ቢችልም።

ሠ) እንግዶችና መጻተኞች፡ ጴጥሮስ አሁን ከማንነታችን ውስጥ በጣም አስቸጋሪ የሆነውን ክፍል ያብራራል። የተመረጥን፥ ካህናትና የንጉሥ ቤተሰብ መሆናችንን እናውቃለን። ዓለም ግን የዚህ ዓይነቱን ክብር አትሰጠንም። ይልቁንም ከዓለም ተቃውሞ ይሰነዘርብናል። ስለሆነም፥ ጴጥሮስ በክርስቶስ ያገኘነው ማንነት ተፈጻሚነትን የሚያገኘው በመንግሥተ ሰማይ ውስጥ መሆኑን በድጋሚ ያስገነዝበናል። አሁን ግን በምድር ላይ ጊዜያዊ ጎብኚዎች የሆንን ያህል ልንመላለስ ይገባል። ይህ በሁለት መንገዶች ተጽዕኖ ያሳድርብናል። በመጀመሪያ፥ የዓለም የኃጢአት ፍላጎቶች ሕይወታችንን እንዲበክሉ መፍቀድ የለብንም። በኃጢአት በተጨማለቀው ዓለም ውስጥ በመኖራችን ኃጢአት ወደ ሕይወታችን እንዲገባ መፍቀድ የለብንም። ሁለተኛ፥ ሌሎች በክርስቶስ አምነው ይድኑ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጆች እንዴት እንደሚኖሩ ልናሳያቸው ይገባ ነበር። ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ (በሚጎበኝበት ቀን) ዛሬ ወደ ክርስቶስ እንዲመጡ መልካም ተጽዕኖ ያሳደርንባቸው ሰዎች እግዚአብሔር ባለበት በዚያ ያከብሩናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ለክርስቲያኖች ሰይጣንና ዓለም የሚሰጡንን ስም ከመስማት ይልቅ በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ማን መሆናችንን መገንዘቡ ለምን ያስፈልጋል? ለ) አማኞች እነዚህን እውነቶች ቢያስታውሱ፥ ስደትና መከራን እንዴት በተሻለ ሁኔታ ሊቀበሉ ይችላሉ?

ጴጥሮስ የእውነተኛ ማንነታችንን ከመግለጹም በላይ፥ በክርስቶስ የታየውን የእግዚአብሔር መንገድ ምሥጢርነት ጭምር ያብራራል። ልክ እንደኛው ክርስቶስም ሕያው ድንጋይ ነበር። ነገር ግን እርሱ ከእኛ የበለጠ እና የላቀ ድንጋይ ነው። እርሱ የማእዘን ድንጋይ ነው። የማእዘን ድንጋይ የጥንት ዘመን ጠቅላላው ሕንጻ የሚያርፍበት ወሳኙ ድንጋይ ነበር። ወይም ደግሞ ውብ ሆኖ የተቀረጸ እና ቤቱን አያይዞ የሚያቆም ዋነኛው ድንጋይ ነው፡፡ አዲስ ሕንጻ የሆነችው ቤተ ክርስቲያን የቆመችው በእኛ፥ በወንጌላውያን ወይም ሽማግሌዎች ሳይሆን በክርስቶስ ላይ ነው።

እግዚአብሔር የመረጠው ይህ ልዩ ድንጋይ ምን ሆነ? በዓለም እንደ ከንቱ ነገር በመቆጠሩ የክርስቶስ ኢየሱስ ድንጋይ ተጣለ፥ ያውም ክርስቶስ ተገደለ። እግዚአብሔር ግን ሰዎች የናቁትን ድንጋይ ወስዶ ክርስቶስን የአዲስ ሕዝብ ራስ አደረገው። በተጨማሪም ይህ ድንጋይ በእርሱ ለማመን የማይፈልጉትን ሁሉ ለፍርድ አሳልፎ የሚሰጥ ዳኛ ሆነ። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ዓለም ሊጥለንና ከንቱዎች አድርጎ ሊቆጥረን ይችላል። እግዚአብሔር ግን ዓለም የናቀውን በመውሰድ ልዩ እና ዘላለማዊ የሆነው ሕንጻ አካል ያደርገናል። ስለሆነም ስደትና ታላቅ መከራ በሚያጋጥመን ጊዜ ተስፋ መቁረጥ የለብንም። ሰዎች በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ቤት ውስጥ ምን ያህል አስፈላጊዎች እንደሆንን አያውቁም።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ድነት (ደኅንነት) ወደ ተቀደሰ አኗኗር ሊመራን ይገባል (1ኛ ጴጥ. 1፡13-2፡3)

ብዙውን ጊዜ በመጀመሪያ የድነት (ደኅንነት) ተግባር ላይ አጽንኦት እንሰጣለን። አንድ ሰው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በክርስቶስ በሚያምንበት ጊዜ ደስ እንሰኛለን። በመሠረቱ ይህ ትክከለኛ እርምጃ ነው። ይህ ታላቅ መዳን በመሆኑ፥ ሰማያት ሁሉ ከእኛ ጋር ይደሰታሉ (ሉቃ. 15፡10)። ነገር ግን ጴጥሮስ ድነት (ደኅንነት) ከዘላለማዊ ፍርድ ብቻ መዳን ሳይሆን፥ የአዲስ ሕይወት መነሻ እንደሆነ ይናገራል። አሁንም ጴጥሮስ በደኅንነታችን ታላቅነት ላይ ትኩረት ያደርጋል። ይህ እግዚአብሔር በልጁ እንዲጨክን ያደረገው ጉዳይ ነው። ውጤቱም ጊዜያዊ አይደለም። ሰዎች ሥጋዊ ፈውስ ማግኘታቸው እንደ ሣር መጠውለጋችውን (መሞታቸውን) አያስቀረውም። ድነት (ደኅንነት) ግን ዘላለማዊ በረከቶችን ያስገኛል። እግዚአብሔር በዘላለማዊ ቃሉ ይህን ስለተናገረ፥ አምነን ልንቀበለው ይገባል።

ጴጥሮስ ለእነዚህ በመከራ ውስጥ ላሉት ክርስቲያኖች አሁን እንደ እግዚአብሔር ልጆች የሚኖሩበት ሁኔታ እግዚአብሔርን የሚያሳስበው መሆኑን ይናገራል። እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ፥ ልጆቹም እንደ እርሱ ቅዱስ እንዲሆኑ ይፈልጋል። ብዙውን ጊዜ ቅዱስ የሚለው ቃል ከኃጢአትና ከክፉ አኗኗር መነጠል እንደሆነ እናስባለን። በእርግጥ ይህ የቅድስና አካል ነው። ጴጥሮስ እንደ ሰው፥ ሌሎች ክርስቲያኖችን ወይም ስደት የሚያመጡብንን ሰዎች እንደ መጥላት፥ ማታለል ወይም ለራሳችን መጠቀሚያ ማድረግ፥ ግብዝነት (ለሌሎች መንፈሳዊ መስሎ ለመታየት መጣር)፥ ከእኛ በተሻለ ሁኔታ ላይ በሚገኙ ሰዎች መቅናት እንዲሁም ስለ ባህሪያቸውና ተግባራቸው ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ሰዎችን ማማት የመሳሰሉትን ሕይወቶች ማስወገድ አለብን።)

ነገር ግን ቅድስና ለእግዚአብሔር ክብር የመኖርን አዎንታዊ ገጽታን ያመለክታል። ጴጥሮስ ራስን መግዛት፥ ተስፋችንን በሰማይና እግዚአብሔር በሰጠን ሰማያዊ በረከት ላይ ማሳረፍ በዓለም ውስጥ የሰዎች መለያ ከሆነና ክፉ ምኞቶችን (ራስ ወዳድነት፥ የግል ወይም የቤተሰብ ኩራት) አለመከተል፥ የመጻተኝነት ሕይወት መምራት (ቤታችን በምድር ላይ ላፈራናቸው ተግባራት) ከእግዚአብሔር ፍርድን የምንቀበልበት ጊዜ እንዳለ ማወቅ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት መጠበቅ፥ ለሌሎች አማኞች እውነተኛ ፍቅር በማሳየት፥ የእናትን ወተት ከመጥባት በስተቀር ስለሌላ ነገር እንደማያስበው አዲስ እንደ ተወለደ ሕፃን የእግዚአብሔርን ቃል ወተት በመጠጣት በመንፈሳዊ ብስለት ለማደግ መሻት ያሉትን ነገሮች ይጠቅሳል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጴጥሮስ አማኞች እንዲያደርጉ የማይፈልጋቸውን አሉታዊ ነገሮች የዘረዘረው ለምን ይመስልሃል? በተለይ ስደትን ለሚጋፈጡ ክርስቲያኖች እነዚህ ነገሮች የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው? ጴጥሮስ በአማኞች ሕይወት ውስጥ እንዲታዩ የሚፈልጋቸውን ነገሮች የዘረዘረው ለምንድን ነው? እነዚህ ነገሮች በተለይ በስደት ውስጥ ለሚያልፉ አማኞች የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው? ሐ) አንተና የቤተ ክርስቲያንህ ምእመናን ከእነዚህ ነገሮች መካከል ለመፈጸም የተቸገራችሁባቸው የትኞቹ ናቸው? መ) ሕይወትህ እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ቅዱስ አለመሆኑን በመግለጽ አሁኑኑ ንስሐ ግባ። እግዚአብሔር ለእርሱ እንድትኖር እንዲረዳህ ጠይቀው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ከስደት ባሻገር ድነታችን (ደኅንነታችን) ትልቅ ሽልማት ያስገኝልናል (1ኛ ጴጥ. 1፡1-12)

ወርቅነሽ ተወልዳ ያደገችው በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን፥ ቤተሰቦቿ ጠንካራ የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ነበሩ። አንድ ቀን አንድ ወንጌላዊ ወደ አካባቢያቸው መጥቶ ወርቅነሽ ከክርስቶስ ጋር የግል ግንኙነት ሊኖራት እንደሚገባ ነገራት። ከወንጌላዊው ጋር በምትወያይበት ጊዜ በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ መወለዱ ወይም ክርስቶስ እንደ ሞተ ማመኗ ብቻ በቂ እንዳልሆነና ዳሩ ግን ክርስቶስ ድነትን (ደኅንነትን) የምታገኝበት ብቸኛው መንገድ እንደሆነ በማመን ልትከተለው እንደሚገባው ስለተገነዘበች፥ ክርስቶስን የግል አዳኝዋ አድርጋ አመነች። ወላጆቿ ስለ አዲሱ እምነቷ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቆጡ። «እንዲህ ዓይነት ሃይማኖት ለመከተል ምን መብት አለሽ? አዲሱ እምነትሽን ክደሽ ወደ ቀድሞው እምነትሽ ካልተመለስሽ አንድ አደገኛ ነገር ይደርስብሻል» ሲሉ አስፈራሯት። እምነቷን ለመካድ ባልፈለገች ጊዜ አባቷ ዱላ አንሥተው ይደበድቧት ጀመር። እራሷን ስታ እስክትወድቅ ድረስ ይህንኑ ድብደባቸውን ቀጠሉ። በየቀኑ ወንድሞቿ፥ እኅቶቿና ሌሎችም ዘመዶቿ ስሟን በመጥራት ይሳለቁባት ጀመር። ወላጆቿ ልብስ ሊገዙላት ወይም የትምህርት ቤት ክፍያ ሊከፍሉላት ፈቃደኞች ሳይሆኑ ቀሩ። የኋላ ኋላ በክርስቶስ ላይ ያላትን እምነት ለመካድ እንደማትፈልግ ሲገነዘቡ፥ ከቤታቸው አባረሯት። በዚህ ጊዜ ከኢኮኖሚያዊ ችግር ባሻገር፥ ከቤተሰቦቿ በመለየቷ ልቧ ቆሰለ። «ለመሆኑ ይህ ለእኔ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውን? እኔ ትክክል ከሆንኩ፥ ለምንድን ነው በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የምሠቃየው?» ስትል ታስባለች።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቶስን ለመከተል በመወሰናቸው ከፍተኛ ሥቃይ የደረሰባቸውና በግል የምታውቃቸው ሰዎች ሁኔታ ምን እንደሚመስል ግለጽ። ለ) ወርቅነሽ ወደ አንተ መጥታ እግዚአብሔር ለምን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ እንድትሠቃይ እንደሚፈቅድ ብትጠይቀህ፥ ምን መልስ ትሰጣታለህ?

እንደ ወርቅነሽ ሁሉ ከመቶዎች በሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በትንሿ እስያ ውስጥ ተበትነው ይኖሩ የነበሩ አማኞች በክርስቶስ በማመናቸው ምክንያት ስደትን ይጋፈጡ ነበር። «እምነታችን እውነት ከሆነ፥ ትክክለኛ ምርጫ በመውሰዳችን የምንሠቃየው ለምንድን ነው? ከዚህ ስደት ለማምለጥ ስንል ወደ ጥንቱ የአምልኮ ሥርዓታችን መመለስ አለብን? በዚህ ዓይነት ሥቃይን እየተቀበልን ሳለ እግዚአብሔር ከእኛ ምን ይጠብቃል?» የሚሉ ጥያቄዎች በእነዚህ አማኞች አእምሮ ውስጥ ይጉላሉ እንደነበር አይጠረጠርም። የ1ኛ ጴጥሮስ መልእክት ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። ጴጥሮስ ለእነዚህ ለተበተኑ አማኞች ሲጽፍ፥ ስደት በሚመጣባቸው ጊዜ በእምነታቸው ጸንተው እንዲቆሙ ያበረታታቸዋል። ስደት ለጴጥሮስ አዲስ ነገር አልነበረም። ብዙ ጊዜ የታሰረና የተደበደበ ሲሆን፥ በቅርቡም ለእምነቱ ሲል የሞት ቅጣት ይፈጸምበት ነበር።

ብዙዎቻችን በተለያዩ መንገዶች ስደትን እንጋፈጣለን። የ1ኛ ጴጥሮስ መልእክት ስደትን ለመቋቋም በሚያስችል መልኩ ብቻ ሳይሆን፥ በስደት ውስጥ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ መኖር እንዳለብን ያስነዝበናል።

ሰይጣን በስደት ጊዜ ተስፋ ሊያስቆርጠን ከሚፈልግባቸው መንገዶች አንዱ ከክርስቶስና እርሱ ካዘጋጀልን ዘላለማዊ በረከቶች ላይ ዓይኖቻችንን እንድናርቅ ማድረግ ነው። ሰይጣን በስደት ላይ በማተኮር በራሳችን እንድናዝን ይፈልጋል። በመከራ ጊዜ ተስፋ ሊያስቆርጠን ሲሞክር ሰይጣንን ልንቃወም ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ በእግዚአብሔር እና ከእርሱ ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ትኩረታችንን መልሶ ማሳረፍ ነው። ጴጥሮስም ያደረገው ይሄንኑ ነበር። በመግቢያው ላይ፥ ጴጥሮስ ወዲያውኑ የአማኞቹን ቀልብ ከእግዚአብሔር ጋር ወዳላቸው ግንኙነት ሲመልስ እንመለከተዋለን። ጴጥሮስ አማኞችን ምን ብሎ እንደሚጠራቸው አጢን፡-

 1. የእግዚአብሔር ምርጦች፡ እግዚአብሔር አብርሃምን፥ ሙሴን ዳዊትንና ሌሎችንም ሰዎች እንደ መረጠ ሁሉ፥ እያንዳንዱ አማኝ የእርሱ ልጅ እንዲሆን መርጦታል። ዓለም ከንቱዎችና ሞኞች አድርጋ ብትቆጥረንም፥ በዓለም ውስጥ ካሉት ሰዎች ሁሉ መካከል እግዚአብሔር እንደ መረጠን ልናስታውስ ይገባል። እርሱ ከልቡ ይወደናል።
 2. መጻተኞች፡- ስደት የሰውን ልብ ከሚያቆስልባቸው መንገዶች አንዱ ከምንፈልጋቸው ነገሮች የሚያራርቀን በመሆኑ ነው። ብዙውን ጊዜ ከቤተሰቦቻችን፥ ከዘመዶቻችን፥ ከማኅበረሰቡ፥ ወዘተ… ይለየናል። በዚህን ጊዜ ብቸኝነት ይሰማናል። ስደት አንዳንድ ጊዜም ከጥሩ አኗኗር፥ ከትምህርት፥ እንዲሁም ከሥራ ይለየናል። ጴጥሮስ ይህንን ብቸኝነት በመገንዘብ፥ ብቸኛ የሆንንበት እውነተኛ ምክንያት ገና ከቤታችን ስላልደረስን መሆኑን ይናገራል። ቤታችን በሰማይ ነው፡፡ እውነተኛ ቤተሰባችን ያለው እዚያው ነው። በስደት ውስጥ የሚያልፉ ክርስቲያኖች በዚህን ጊዜያዊ ሕይወት ውስጥ እያለፍን ወደ ዘላለማዊው ቤታችን እየሄድን መሆናችንን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ይህንን ካስታወስን፥ ስደትን መቀበሉ ቀላል ይሆንልናል።
 3. እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ እንዳወቃቸው፡ ጴጥሮስ እያንዳንዱ የሥላሴ አካል በደኅንነታችን ውስጥ እንዴት እንደ ተሳተፈ ያሳያል። እግዚአብሔር አብ ልጆቹ እንድንሆን መረጠን። የእግዚአብሔር ልጆች የሆንነው በአጋጣሚ ወይም በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ በመወለዳችን አይደለም። ነገር ግን እግዚአብሔር አብ ከፍቅሩ የተነሣ እኔንና እንተን መርጦ ልጆቹ አድርጎናል። ይህም የሚያስደንቅ ነገር ነው!
 4. በመንፈስ የመቀደስ ሥራ፡ የእግዚአብሔርን ጥሪ እንድንሰማና እንድናምን የሚያደርገን መንፈስ ቅዱስ ነው። እርሱ ይቀድሰናል ወይም ይለየናል። ይህም ማለት፡- ሀ) እኛን የእግዚአብሔር ልጆች ለማድረግ በዓለም ውስጥ ካሉት ሌሎች ሰዎች ይለየናል። ለ) በተቀደሰው አምላክ ፊት ቅዱሳንና ተቀባይነት ያለን ሰዎች ያደርገናል።
 5. ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ፡ እግዚአብሔር ያዳነን ከሲዖል እንድናመልጥ ብቻ አይደለም። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስን በመታዘዝ እንድናስከብረው አድኖናል። ክርስቶስ ባዳነን ጊዜ፥ ይህንን ያደረገው እንዳሻን እንሆን ዘንድ ሕይወታችንን ቀላል ለማድረግ አልነበረም። ይልቁንም የክርስቶስ ተከታዮች እንድንሆንና ለእግዚአብሔር እየታዘዝን እንድንኖር ነው። ብዙውን ጊዜ ይህ የታዛዥነት ጎዳና ወደ ስደት ይመራናል። ክርስቶስ ከሥቃዩ ባሻገር ለእርሱ ታማኞች ሆነን እንድንቀጥል ይጠይቀናል።

የውይይት ጥያቄ፡- በስደት ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች እነዚህን አምስት እውነቶች ማወቃቸው አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

በስደትና መከራ ጊዜ ሊያበረታታን የሚገባ ሌላው ነገር ደግሞ እግዚአብሔር የሰጠንን ታላቅ ድነት (ደኅንነት) ማስታወስ ነው። ጴጥሮስ እግዚአብሔርን ስለዚሁ ታላቅ ተስፋ ያመሰግነዋል። ይህ ድነት (ደኅንነት) የተገኘው ከምርጫችን ወይም ካደረግነው አንዳች ተግባር ሳይሆን፥ ከታላቅ ምሕረቱ የተነሣ ነው። ይህም ድነት (ደኅንነት) አዲስ ልደትን ያስገኝልናል (የእግዚአብሔር ልጆች ያደርገናል)። እንዲሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ምክንያት እኛም ከሞት እንደምንነሣ ያረጋግጥልናል። የእኛም ድነት (ደኅንነት) ማንም ሊነጥቅብን ወደማይችለው የዘላለም በረከቶች ውርስ ይመለከታል። ምንም እንኳን መከራዎች በአሁን ሰዓት ከፍተኛ ስጋት ቢያስከትሉብንም፥ እነዚህ በረከቶች በምድር ላይ የምንጋፈጣቸው መከራዎች ቀለል ብለው እንዲታዩን ያደርጋሉ። (2ኛ ቆሮ. 4፡16-18 አንብብ)።

ጴጥሮስ ለእነዚህ አማኞች ይህ ድነት (ደኅንነት) ምን ያህል ታላቅና ልዩ እንደሆነ ይናገራል። የብሉይ ኪዳን ነቢያት ስለዚሁ ልዩ መዳን የተነበዩ ሲሆን (ለምሳሌ፥ ኤር. 31-34)፥ እግዚአብሔር ይህንን ተግባር ከፍጻሜ የሚያደስበትን ሁኔታ ለመረዳት ናፍቀው ነበር። እነዚህ ነቢያት ስለ ክርስቶስ ሞት በመተንበይ ለአዲሱ ኪዳን ዘመን አማኞች እያገለገሉ ነበር። ታላላቅ የሰማይ መላእክት እንኳን እግዚአብሔር ለኃጢአተኛ ሰዎች የሰጠውን ድነት (ደኅንነት)፥ የሰጠውን ስጦታና የሰጠውን ፍቅር በመመልከት ተደንቀዋል። ይህም ሙሉ በሙሉ ሊረዱት የማይችሉት ነው።

እንደ እግዚአብሔር ልጆች በሰማይ ርስት አለን፥ ይህም ማንም የማይወስደው ነው። ከዚህም በላይ፥ እግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥቱ እስኪመጣ ድረስ ይጠብቀናል። ይህ ጥበቃ ምንን እንደሚያካትት መገንዘቡ ጠቃሚ ነው። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ልጆቹን በዚህ ምድር ላይ ከስደትና መከራ ይጠብቃቸዋል። ለምሳሌ ያህል፥ እግዚአብሔር የዳንኤልን 3 ጓደኞች ከእሳት አድኗቸዋል (ዳን. 3)። ብዙውን ጊዜ ግን እግዚአብሔር በመከራ ውስጥ ሆነን ይጠብቀናል። ለእምነታችን ጸንተን የምንቆምበትን ኃይል ይሰጠናል። በታማኝነት እንድንቆም የሚያደርገን እርሱ ነው። ወደ ዘላለማዊ ቤታችን እንድንደርስ ይጠብቀናል።

ነገር ግን እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ መከራ እንድንቀበል የሚፈቅደው ለምንድን ነው? (ጴጥሮስ ልዩ ልዩ መከራ፥ ስደትን ብቻ ሳይሆን፥ እንደ በሽታ፥ ድህነት፥ ሥራ ማጣት፥ የቤተሰብ አባላት ሞት፥ የተፈጥሮ አደጋ የመሳሰሉትን ነገሮች እንደሚያመለክት ለማሳየት ልዩ ልዩ ፈተና የሚለውን ሐረግ ይጠቀማል። እነዚህም መከራን የሚያመጡና እነዚህም በሕይወታችን ውስጥ ሥቃይን የሚያስከትሉና እግዚአብሔር በመሣሪያነት የሚጠቀምባቸው ናቸው።) መጽሐፍ ቅዱስ ለምን መከራ በሕይወታችን እንደሚመጣ ለማመልከት የሚያቀርባቸው አያሌ ምክንያቶች አሉ።

 1. ጴጥሮስ እሳት ወርቅ እንደሚያጠራ ሁሉ መከራም ሕይወታችንን እንደሚያጠራ ይናገራል። መከራ እምነታችንን በማጥራት በሂደቱ ውስጥ እየበሰለ እንዲሄድ ያደርጋል። በተጨማሪም መከራ እግዚአብሔር ኩራትን፥ ራስ ወዳድነትን፥ የዓለምን ፍቅር፥ ወዘተ… በማቃጠል ባህሪያችንን ለመቅረጽ የሚጠቀምበት ዐቢይ መሣሪያ ነው።
 2. የእግዚአብሔር ልጆች በመከራ ጊዜ ጸንተው መቆማቸው እግዚአብሔርን ያስከብራል። በክርስቶስ ላለን እምነት እጅግ ጠንካራ ምስክርነቶች ከሚሆኑት ነገሮች ሁሉም ነገር አልሳካ እያለን በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት አለመተዋችን ነው። ሰይጣን በኢዮብ ላይ ያቀረበውን ክስ ታስተውላለህ። ሰይጣን ለእግዚአብሔር ባቀረበው ክስ የኢዮብ እምነት ከእግዚአብሔር ላይ በሚያገኛቸው በረከቶች ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ገልጾአል። ሰይጣን፥ «በረከቶቹን ብትወስድበት ኢዮብ በፊትህ ይሰድብሃል» ብሎ ነበር። ነገር ግን በረከቶቹ ሁሉ ከተወሰዱበት በኋላ፥ ኢዮብ፥ «እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሳ የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን» (ኢዮብ 1፡20-22) ብሏል። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ በታላቅ መከራ ውስጥ ሆነን በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት መጠበቃችን እግዚአብሔርን ለሰጠን በረከቶች ሳይሆን ለማንነቱ ብለን እንደምናምን ማረጋገጣችን ነው።
 3. መከራ ለእግዚአብሔር ፍቅር እንዳለን ያሳያል። እንደ ጴጥሮስ ክርስቶስን ባናየውም፥ እንወደዋለን፤ ከእርሱም ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለን። ነገሮች መልካም በማይሆኑበት ጊዜ ሳይቀር በክርስቶስ ያለንን እምነት ስንጠብቅ፥ ይኸው ፍቅር ይበልጥ እየጠራ ይሄዳል።
 4. ጳውሎስ በመከራ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ለማገልገል እንድንችል እግዚአብሔር የሚጠቀምበት መሣሪያ እንደሆነ ገልጾአል (2ኛ ቆሮ. 1:3-7)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንድን መከራ የተጋፈጥክበትን ሁኔታ ግለጽ። ይህ መከራ ከላይ ከተጠቀሱት አራት ነገሮች ወይም ሌሎች ምክንያቶች በሕይወትህ ውስጥ የትኛውን የፈጸመ ይመስልሃል? ለ) ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ከወደደንና እምነት ካለን፥ መከራ፥ እንደማይደርስብን ይናገራሉ። ይህ እውነት ይመስልሃል? በአማኞች ላይ ስለሚደርስ መከራ ያለህን ግንዛቤ ለማስደገፍ የሚያግዙህ ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የ1ኛ ጴጥሮስ መልእክት ዓላማ፣ ባሕሪያት፣ መዋቅር እና አስተዋጽኦ

የ1ኛ ጴጥሮስ መልእክት ዓላማ

የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ጴጥ. 5፡12 አንብብ። ጴጥሮስ የመልእክቱ ዓላማ ምንድን ነው ይላል?

የ1ኛ ጴጥሮስ መልእክት የተጻፈው ለተለያዩ ዓላማዎች ነበር።

የመጀመሪያው ዓላማ፡ አማኞች ምንም ዓይነት ስደት ወይም መከራ ቢደርስባቸው በእምነታቸው ጸንተው ይቆዩ ዘንድ ለማበረታታት (1ኛ ጴጥ. 1፡6፤ 2፡20፣ 4፡13፥ 19)። በክርስቲያኖች ላይ ስደት እየተጠናከረ መምጣቱን በመመልከቱ፥ ጴጥሮስ አዝማሚያው እየከፋ እንደሚሄድና ብዙ አማኞች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የተገነዘበ ይመስላል። ጴጥሮስ በስደቱ ከመረበሽ ይልቅ ክርስቲያኖች ስደትን የክርስትና ሕይወት አካላቸው አድርገው እንዲቀበሉትና ክርስቶስ እንዳደረገው እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ መከራ መቀበላቸውን መቀበልን እንዲማሩ ያበረታታቸዋል። እንዲያውም ጴጥሮስ እግዚአብሔር ልጆቹ በመንግሥተ ሰማይ ሽልማታቸውን ከመቀበላቸው በፊት በምድር ላይ መከራን እንዲጋፈጡ የሚፈቅድ መሆኑን ይናገራል።

በዘመናችን ከጴጥሮስ የሚቃረን ትምህርት የሚያስተምሩ አንዳንድ አማኞች አሉ። እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔር መከራን እንድንቀበል (እንድንደኸይ፥ የምንወዳቸውን ሰዎች እንድናጣ፥ እና እንድንታመም) አይፈልግም ይላሉ። እነዚህ ነገሮች ከሰይጣን የሚመጡ በመሆናቸው፥ ሰይጣንን በመቃወም ልናሸንፋቸው እንደምንችል ያስተምራሉ። ወይም ደግሞ እነዚህ ችግሮች በሕይወታችን ውስጥ ኃጢአት ከመኖሩ የተነሣ የሚመጡ ናቸው ይላሉ። እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ እንደ መሆኑ መጠን ከእነዚህ ጊዜያት ይሰውረናል ብለው ያስተምራሉ። ነገር ግን አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያንና የብሉይ ኪዳን ታሪክ ጸሐፊዎች ይህ እውነት እንዳልሆነ ያስተምራሉ። እግዚአብሔር ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል እንደ ፈቀደ ሁሉ፥ ክርስቲያኖችም መከራን እንዲቀበሉ ይፈቅዳል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ክርስቲያኖች ላይ መከራንና ስደትን ያመጣባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር ወደ ሕይወትህ መከራና ስደትን ያመጣው እንዴት ነው። ሐ) በስደትና መከራ ውስጥ ስለ እግዚአብሔርና ክርስትና ሕይወት ምን እንደተማርክ ግለጽ።

ሁለተኛ ዓላማ፡ አማኞች ከምድር ላይ ምቹና የተቃለለ ሕይወት ከመሻት ይልቅ ዓይኖቻቸውን በዘላለማዊ ቤታቸው ላይ እንዲተክሉ ለማበረታታት። ጴጥሮስ አማኞችን መጻተኞች ወይም ወደ ዘላለማዊ የመንግሥተ ሰማይ ቤታቸው እስኪደርሱ ድረስ በምድር ላይ የሚቅበዘበዙ ሰዎች አድርጎ ይገልጻል። ጳውሎስ ሰዎች ፈጥነው እንደሚጠወልግ አበባ መሆናቸውን ይናገራል (1ኛ ጴጥ. 1፡24)። ነገር ግን ክርስቲያኖች ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ቃል ዘመን የማይሽረውን የመንግሥተ ሰማይ ርስት ተስፋ እንደሚገባልን መገንዘብ ይኖርብናል (1ኛ ጴጥ. 1፡3-6)።

ሦስተኛ ዓላማ፡ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ለክርስቲያኖች ምክር ለመስጠት። ዋናው ነገር በሰላም ወደ መንግሥተ ሰማይ መድረስ ብቻ አይደለም። በዚህም ምድራዊ የእምነት ጉዞአችን የምንመላለስበት ሁኔታ ወሳኝ ነው። ስለሆነም ጴጥሮስ፥ ለባሎችና ሚስቶች (1ኛ ጴጥ. 3፡1-7)፥ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች (1ኛ ጴጥ. 5፡1-4)፥ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚገኙ ወጣቶች (1ኛ ጴጥ. 5፡5) ምክሮችን ይሰጣል። በተለይም ጴጥሮስ ቅድስናና ትሕትና አስፈላጊዎች መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥቶ ያስተምራል። ቅድስና እንድ ሰው ከኃጢአት ሕይወት ተመልሶ ለእግዚአብሔር ክብር መኖሩን ያሳያል። ትሕትና በዋናነት አማኞች እርስ በርሳቸው ምን ዓይነት ዝምድና ሊኖራቸው እንደሚገባና በተለይም ለሚያሳድዷቸው ሰዎች መልካም ባህሪ ማሳየት እንዳለባቸው ያሳያል።

የ1ኛ ጴጥሮስ መልእክት ልዩ ባሕርያት

 1. ጴጥሮስ ከክርስቶስ ጋር ከነበረው ግንኙነት የወሰዳቸውን ምሳሌዎች ይጠቀማል። ጴጥሮስ የሚለውን ስም የሰጠው ክርስቶስ ነበር። የስሙም ትርጓሜ ዓለት ማለት ነው። ነገር ግን ይህ ስም የተሰጠው ለእርሱ ብቻ አልነበረም። ክርስቲያኖች ሁሉ እግዚአብሔር እየገነባ ባለው መንፈሳዊ ቤት ውስጥ ሕያዋን ድንጋዮች ናቸው (1ኛ ጴጥ. 2፡5-9)። ክርስቶስ በመጨረሻ አካባቢ ከጴጥሮስ ጋር ሲነጋገር በጎቼን አሠማራ ብሎት ነበር (ዮሐ 21፡15-18)። አሁን ግን ጴጥሮስ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የእግዚአብሔርን በጎች ሊንከባከቡ እንደሚገባ ያመለክታል (1ኛ ጴጥ. 2፡25፣ 5፡2፥ 4)።
 2. ከመልእክቱ አጭርነት በተቃራኒ ጴጥሮስ ከብሉይ ኪዳን የወሰዳቸው ምንባቦች በየትኛውም የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ ከሚገኙ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች በልጠው ይገኛሉ። ጴጥሮስ የማይለወጥ ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ቃል ጠቃሚ በመሆኑ ላይ አጽንኦት ይሰጣል (1ኛ ጴጥ. 1፡23-25)።
 3. ጴጥሮስ ክርስቲያኖች ለተወሰኑ ነገሮች መጠራታቸውን በመግለጽ፥ የክርስትናን ሕይወት ቁልፍ ነገሮች ይዘረዝራል (1ኛ ጴጥ. 1፡15፤ 2፡9፣ 3፡9፤ 5፡10 አንብቡ)። ጴጥሮስ በቅድስና፥ የእግዚአብሔርን ምስጋና ለማወጅ፥ ስደት የሚያመጡብንን ሰዎች ከመርገም ይልቅ ለመባረክ፥ እንዲሁም በሰማይ ወደሚጠብቀን ዘላለማዊ ክብር እስክንገባ ድረስ ለእምነታችን መከራ ለመቀበል የተዘጋጀን እንድንሆን ያብራራል።

የ1ኛ ጴጥሮስ መልእክት መዋቅር

ብዙውን ጊዜ ጳውሎስ መልእክቶችን በሁለት ዐበይት ክፍሎች ይከፍላል። የመጀመሪያው ክፍል በዋናነት ስለ ነገረ መለኮታዊ እውነታችን ሲያስተምር፥ ሁለተኛው ክፍል የክርስቶስ ተከታዮች እንደ መሆናችን እንዴት መመላለስ እንዳለብን የሚያሳዩትን ተግባራዊ እውነቶች ያቀርባል። ጴጥሮስ ግን ሥነ መለኮታዊ እውነቶችን እግዚአብሔርን በሚያስከብርና የአማኞችን እምነት በሚያሳይ መልኩ መመላለስን ከሚያመለክቱ ተግባራዊ አንደምታዎች መካከል ይቀላቅላል።

በሁሉም ምዕራፍ ማለት ይቻላል እንደ ክርስቲያን መከራ የመቀበሉን ጉዳይ ያነሣል። የስደት ጭብጥ ደብዳቤው የተመሠረተበት አቋም ሆኖ እናገኘዋለን።

የ1ኛ ጴጥሮስ መልእክት አስተዋጽኦ

 1. መግቢያ (1ኛ ጴጥ. 1፡1-2)
 2. ድነታችን (ደኅንነታችን) ከመከራ ባሻገር ታላቅ ሽልማቶችን ያስገኛል (1ኛ ጴጥ. 1፡3-12)
 3. ድነት (ደኅንነት) ወደ ተቀደሰ ዓላማ ሊመራን ይችላል (1ኛ ጴጥ. 1፡13-2፡3)።
 4. የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ በመንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ውስጥ ሕያዋን ድንጋዮች ናቸው (1ኛ ጴጥ. 2፡4-12)።
 5. የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ እንዴት ሊመላለስ ይገባል (1ኛ ጴጥ. 2፡13-5፡11)።

ሀ. አማኞች ለመንግሥት መሪዎች መገዛት አለባቸው (1ኛ ጴጥ. 2፡13-17)

ለ. ክርስቲያን ባሪያዎች መከራ ሲደርስባቸውም እንኳን ለሰብአዊ ጌቶቻቸው መገዛት አለባቸው (1ኛ ጴጥ. 2፡18-25)።

ሐ. የእግዚአብሔር ሕዝብ ቤተሰባዊ ግንኙነቶች (1ኛ ጴጥ. 3፡1-7)

 1. ሚስቶች ለባሎቻቸው መገዛት አለባቸው (1ኛ ጴጥ. 3፡1-6)
 2. ባሎች ከሚስቶቻቸው ጋር በማስተዋል መኖር አለባቸው (1ኛ ጴጥ. 3፡7)

መ. የእግዚአብሔር ሰዎች አላግባብ በሚሰደዱበት ጊዜ ሳይቀር ከሰዎች ሁሉ ጋር በሰላም መኖር አለባቸው (1ኛ ጴጥ. 3፡8-22)።

ሠ. አማኞች የተቀደሰ ሕይወት መምራት ይገባቸዋል (1ኛ ጴጥ. 4፡1-6)

ረ. የእግዚአብሔር ሕዝብ ለሌሎች አማኞች ጥልቅ ፍቅር ሊኖራቸው ይገባል (1ኛ ጴጥ. 4፡7-11)።

ሰ. ክርስቲያኖች ስደትን በደስታ መቀበል አለባቸው (1ኛ ጴጥ. 4፡12-19)

ሸ. በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ ሊኖር የሚገባው ግንኙነት (1ኛ ጴጥ. 5፡1-1)

 1. ማጠቃለያ (1ኛ ጴጥ. 5፡12-14)

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ጴጥሮስ መልእክቱን የጻፈው ለማን ነው፣ መቼ እና የት ተጻፈ?

ጴጥሮስ መልእክቱን የጻፈው ለማን ነው?

ጴጥሮስ በመግቢያው ላይ፥ «ለጳንጦስና፥ ለገላትያ፥ በቀጰዶቂያም፥ በእስያም፥ በቢታንያም ለተበተኑት መጻተኞች» ይላል። እነዚህ አውራጃዎች የሚገኙት ከትንሹ እስያ (የአሁኗ ቱርክ) በስተ ሰሜን ነበር። መንፈስ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ እነዚህ አካባቢዎች እንዳይገባ ነግሮት ነበር (የሐዋ. 16፡6-8)። ምሁራን መንፈስ ቅዱስ ጳውሎስ ወደዚህ አካባቢ እንዳያገለግል የከለከለው ጴጥሮስ ቀደም ሲል ወይም ወደ በኋላ በዚህ አካባቢ የወንጌል አገልግሎት ይሰጥ እንደነበረ ስለሚያውቅ ነው ይላሉ። ጴጥሮስ በእነዚህ አውራጃ ዎች ውስጥ መቼ እንዳገለገለ ባናውቅም፥ ብዙ ጊዜ እያገለገለ በመቆየቱ ምክንያት በአማኞች ዘንድ ሊታወቅ የቻለ ይመስላል።

ጴጥሮስ በእነዚህ አካባቢዎች ስለነበሩት አማኞች አስገራሚ ገለጻ ያደርጋል። በመጀመሪያ፥ በእግዚአብሔር የተመረጡ ይላቸዋል። ጴጥሮስ ልክ እንደ ጳውሎስ እግዚአብሔር በምሕረቱ እያንዳንዱን አማኝ እንደ መረጠው ያውቅ ነበር። ድነትን (ደኅንነትን) አስመልክቶ የጴጥሮስ ትኩረት እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ያደረገው ተግባር እንጂ የእኛ ክርስቶስን መምረጥ አይደለም። ጴጥሮስ ይህንን የጻፈው በመከራ ውስጥ የሚያልፉትን ክርስቲያኖች ለማበረታታት ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ከመረጣቸው፥ እያንዳንዳቸውን እንደ ውድ ልጆቹ ስለሚመለከት እንደሚጠብቃቸው ግልጽ ነው። ሁለተኛ መጻተኞች ይላቸዋል። ጴጥሮስ እነዚህ ስደት የበዛባቸው አማኞች ገና ከቤታቸው እንዳልደረሱ ያሳስባቸዋል። እንደ አብርሃም፥ በምድር ላይ በጉዞ ይኖሩ ነበር። እማኞች ወደ እውነተኛይቱ ቤታቸው የሚደርሱት መንግሥተ ሰማይ ሲደርሱ ብቻ ነው። በመሆኑም፥ ከእምነታቸው የተነሣ ቤቶቻቸውንና ሥራቸውን በሚያጡበት ጊዜ ተስፋ ሊቆርጡ አይገባም። ምክንያቱም ማንም ከእነርሱ የማይወስደው ዘላለማዊ ቤት በሰማይ አላቸውና።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር እኛን ለይቶ መምረጡ መከራን በምንቀበልበት ጊዜ እንዴት ያበረታታናል ለ) በዓለም ውስጥ የምንኖር መጻተኝነታችንን መገንዘብ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

አንዳንድ ምሁራን ጴጥሮስ የአይሁዶች ሐዋርያ እንደ መሆኑ መጠን «የተበተኑ» የሚለውን ሐረግ እንደ ተጠቀመ ይናገራሉ። ይህም በሮም ግዛቶች ሁሉ ውስጥ የተበተኑትን አይሁዶች የሚያመለክት ቃል ነው። ጴጥሮስ መልእክቱን በቀዳሚነት የጻፈው በሰሜን ቱርክ የሚገኙ ጥቂት አይሁዳውያን አማኞች ለመሠረቷቸው አብያተ ክርስቲያናት ነበር። ነገር ግን የአንደኛ ጴጥሮስ መልእክት የተጻፈው በሰሜኑ የትንሹ እስያ ክፍል በተለያዩ ከተሞች ይሰበሰቡ ለነበሩ አይሁዳውያንና አሕዛብ አማኞች ይመስላል። በመሆኑም ይህ በስብሰባ ጊዜ በአንዱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከተነበበ በኋላ ወደ ሌላው ቤተ ክርስቲያን እየተላከ አብያተ ክርስቲያኑን በሞላ እንዲያዳርስ የታሰበ ተዘዋዋሪ ደብዳቤ ሳይሆን አይቀርም። እንዲያውም ጴጥሮስ የሮምን አውራጃ ዎች የጠቀሰበት ቅደም ተከተል መልእክቱን ለየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚያዳርሰው መልእክተኛ የሚሄድባቸውን ከተሞች ቅደም ተከተል የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ደብዳቤውን ገልብጠው ለራሳቸው ያስቀሩና ቀስ በቀስ እነዚሁ ቅጂዎች በክርስትናው ዓለም ውስጥ የተሰራጩ ይመስላል።

አንደኛ ጴጥሮስ የተጻፈበት ጊዜና ስፍራ

የውይይት ጥያቄ፡– 1ኛ ጴጥሮስ 5፡13 አንብብ። ይህ ጥቅስ 1ኛ ጴጥሮስ የት እንደ ተጻፈ ያሳያል? ጴጥሮስ ይህን መልእክት በጻፈ ጊዜ ከእርሱ ጋር ማን ነበር?

ይህ መልእክት በትክክል መቼ እንደ ተጻፈ አናውቅም። በ95 ዓ.ም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በጽሑፋቸው ውስጥ መልእክቱን ስለጠቀሱ፥ ከዚሁ ጊዜ ቀደም ብሎ እንደ ተጻፈ ለመረዳት ይቻላል። ጴጥሮስ በ68 ዓመተ ምሕረት በተጠናቀቀው የኔሮ ክርስቲያኖችን የማሳደድ ዘመቻ ውስጥ እንደ ሞተ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ስለሚያመለክት፥ ይህ መልእክት ከዚሁ ጊዜ ቀደም ብሎ የተጻፈ ይመስላል። ይህ መልእክት ኔሮ ክርስቲያኖችን ማሳደድ ከጀመረ በኋላ ከ64-65 ዓመተ ምሕረት ባለው ጊዜ ውስጥ የተጻፈ ይመስላል።

ጴጥሮስ በመልእክቱ በመጨረሻ ላይ ከባቢሎን ለሆኑት አማኞች ሰላምታ ይልካል። በአዲስ ኪዳን ዘመን፥ የብሉይ ኪዳን ዘመኗ ባቢሎን ፈራርሳ ነበር። በዚህ ጊዜ ባቢሎን ተብላ ትታወቅ የነበረችው አነስተኛ መንደር ነበረች። ምንም እንኳን ጳውሎስ በዚህች አነስተኛ መንደር ውስጥ ሊኖር ቢችልም፥ የባቢሎንን ከተማ ማመልከቱ አልነበረም። በመጀመሪያው ምእተ ዓመት መጨረሻ ላይ አይሁዳውያንም ሆኑ ክርስቲያን ጸሐፊዎች የሮምን ከተማ ባቢሎን በሚባል ተምሳሌታዊ ስም ይጠሩ ነበር። ይህንንም ያደረጉት ቀደም ሲል ባቢሎን አይሁዶችን በምርኮኛነት ማጋዟን በማስታወስ አሁንም ሮም አይሁዶችንና ክርስቲያኖችን እያሳደደች መሆኗን በመገንዘባቸው ነበር። ስለሆነም፥ ጴጥሮስ ይህን መልእክት የጻፈው ከሮም ከተማ ይመስላል። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በኔሮ የስደት ጊዜ ጴጥሮስና ጳውሎስ በሮም ከተማ እንደ ነበሩና ጴጥሮስ መልእክቶቹን ከሮም ከተማ ሆኖ እንደ ጻፈው ያረጋግጣል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የአንደኛ ጴጥሮስ ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ጴጥሮስ 1፡1 አንብብ። ሀ) የዚህ መልእክት ጸሐፊ ማን ነው? ለ) እራሱን እንዴት ይገልጸዋል? ይህ ጳውሎስ ሁልጊዜ ራሱን ከሚገልጽበት ሁኔታ የሚለየው ወይም የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ሐ) የዚህ መልእክት ተቀባዮች እነማን ናቸው። በዚህ መልእክት ውስጥ የተገለጸበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

የአንደኛ ጴጥሮስ መልእክት ጥንታዊ የደብዳቤ አጻጻፍ ስልት በመከተል የጸሐፊውን ማንነት በማስተዋወቅ ይጀምራል። እርሱም ጴጥሮስ መሆኑን ይነግረናል። ጴጥሮስ ልክ እንደ ጳውሎስ ራሱን ሐዋርያ ብሎ ይጠራዋል። ይህን ያደረገው በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሌሎች ጴጥሮስ ተብለው የሚጠሩ ሰዎች ስለነበሩ፥ የመልእክቱ ጸሐፊ ማን እንደሆነ ለይቶ ለማሳወቅ ብቻ ሳይሆን፥ ከዚህ በበለጠ ግን መልእክቱን ለመጻፍ ምን ሥልጣንና ስፍራ እንዳለው ለሕዝቡ ለማሳወቅ ይፈልጋል። መልእክቱን የሚጽፈው እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ነው።

ሐዋርያው ጴጥሮስ ምናልባትም በቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እጅግ የታወቀ የቤተ ክርስቲያን መሪ ሳይሆን አይቀርም። የጴጥሮስ አይሁዳዊ ስሙ ስምዖን ሲሆን፥ በገሊላ የተወለደ አይሁዳዊ ነበር። ይህች ስፍራ በፓለስታይን ምድር ውስጥ ብዙም ያላደገች ነበረች። በገሊላ አካባቢ አይሁዶችም አሕዛብም ይኖሩ ነበር። ጴጥሮስ ያደገው ምናልባትም የግሪክና የአረማይክ ቋንቋዎችን እየተናገረ ይሆናል። አባቱ ዓሣ አጥማጅ ነበር። ከዚህም የተነሣ ከወንድሙ እንድርያስ ጋር ዓሣ አጥማጆች ሆኑ። የጴጥሮስ መንፈሳዊ እድገት የጀመረው መጥምቁ ዮሐንስን ባገኘው ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። ወንድሙ እንድርያስ የመጥምቁ ዮሐንስ ተከታይ ስለነበር፥ ጴጥሮስም እንዲሁ የዮሐንስ ደቀ መዝሙር የነበረ ይመስላል (ዮሐ 1፡40-42)።

ክርስቶስ ከተጠመቀ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ እንድርያስ ጴጥሮስን ከክርስቶስ ጋር አስተዋወቀው። ከዚያም በኋላ ጴጥሮስ ቀሪ ዘመኑን ሁሉ ክርስቶስን ይከተልና ያገለግል ጀመር። ክርስቶስ መጀመሪያ አገልግሎቱን በገሊላ በጀመረ ጊዜ ጴጥሮስ አብሮት ጥቂት ጊዜ ካሳለፈ በኋላ (ዮሐ. 2)፥ ቤተሰቡ ወደሚተዳደርበት ዓሣ የማጥመድ ተግባር የተመለሰ ይመስላል። ኢየሱስ ይፋዊ አገልግሎቱን በጀመረ ጊዜ፥ ካከናወናቸው ተግባራት አንዱ ጴጥሮስ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ እንዲሆን መጥራት ነበር። ጴጥርስ አንድ ቀን በዓለም ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚያሰራጭ ተማሪ ነበር (ማቴ. 4፡18-20)።

ለቀጣይ ሦስት ተኩል ዓመታት፥ ጴጥሮስ ከኢየሱስ ጋር በመሆን ተአምራቱን ሲመለከት፥ ስብከቶቹን ሲሰማና በክርስቶስ ለአገልግሎት ሲላክ እንመለከታለን። በዚህም አገልግሎቱ ተአምራትን የማድረግና በእሥራኤል ምድር ሁሉ ለመስበክ ተልኮአል። ጴጥሮስ የመሪነት፥ የድፍረትና የችኩልነት ባሕርያት ያሉት ይመስላል። ብዙም ሳይቆይ የደቀ መዛሙርቱ ቃል አቀባይ ሆነ ክርስቶስ ጴጥሮስን ከብዙ ተከታዮቹ መካከል ለይቶ ብዙ ጊዜውን አብሯቸው ከሚያጠፋው ከ12ቱ ደቀ መዛሙርቱ ውስጥ አካተተው። በተጨማሪም፥ ክርስቶስ ለወደፊት የቤተ ክርስቲያን መሪነት ይጠቅሙ ዘንድ ተጨማሪ ጊዜ ወሰደ። ከሚያሠለጥናቸው ሦስት ደቀ መዛሙርት (ከያዕቆብና ዮሐንስ ጋር) አንዱ ጴጥሮስ ነበር።

ጴጥሮስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ መሢሕ እንደሆነ በድፍረት ባወጀ ጊዜ (ማቴ. 16፡16-20)፥ ክርስቶስ ስሙን ከስምዖን ወደ ኬፋ (አረማይክ) ወይም ጴጥሮስ (ግሪክ) ለወጠው። ይህም ዓለት የሚል ፍቺ ይስጣል። ይህ የስም ለውጥ ለጴጥሮስ የሚሰጠውን ልዩ ኃላፊነት እና ሥልጣን ያመለክታል። ጴጥሮስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን የሚመሠርትበት ዓለት ይሆን ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን የጴጥሮስ ድፍረትና እምነት ግን ይከስማል። ክርስቶስ ከመሰቀሉ በፊት በአይሁድ አለቆች በሚመረመርበት ወቅት፥ ጴጥሮስ ኢየሱስን ሦስት ጊዜ ካደው። ጴጥሮስ በዚያን ሌሊት ክርስቶስን መካዱን በፍጹም ሊረሳው አልቻለም። በአንደኛ ጴጥሮስ ውስጥ እንኳን ሳይቀር ስለዚሁ ጉዳይ ይጠቅሳል። ሥቃይ ልቡን እየናጠው ጴጥሮስ በምሬት አለቀሰ። ከትንሣኤ በኋላ ግን፥ ኢየሱስ ፍቅሩንና ይቅርታውን በሚያሳይ መልኩ ጴጥሮስን አነጋገረው። በዚህም ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ዋና መሪ ወደ መሆኑ ኃላፊነት እንደገና መልሶ አስቀመጠው።

ጴጥሮስ በቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዋና መሪ መሆኑ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የመጀመሪያዎቹ ገጾች ውስጥ ተመልክቷል። መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ በወረደ ጊዜ፥ የመጀመሪያውን ስብከት ያቀረበውና አይሁዶች በኢየሱስ አምነው የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ እንዲቀበሉ የጋበዛቸው ጴጥሮስ ነበር (የሐዋ. 2)። እግዚአብሔር ጴጥሮስ ለማኙን የመፈወስ የመጀመሪያውን ተአምር እንዲሠራ ተጠቅሞበታል (የሐዋ. 3)። ለእምነቱ በቀዳሚነት ስደትንና መከራን የተቀበለው ጴጥሮስ ነው። ወደ በኋላም ጴጥሮስ በዚሁ ርእሰ ጉዳይ ላይ ጽፎአል (የሐዋ. 4)። የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ለሰማርያውያን ወንጌልን በሰበከች ጊዜ የሰማርያውያንን እምነት እንዲገመግሙና ለሰማርያውያን አማኞች ሁሉ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ እንዲያስተላልፉ ቤተ ክርስቲያን ጴጥሮስና ዮሐንስን ነበር የላከቻቸው (የሐዋ. 8፡14-17)። (ሰማርያውያን ከፊል አይሁዶችን ከፊል አሕዛብ ነበሩ።) እግዚአብሔር አሕዛብን ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚያመጣበት ጊዜ ሲደርስ፥ ጴጥሮስ ከቆርኔሌዎስ ጋር እንዲገናኝ አደረገ። ጴጥሮስ እየመሰከረ ሳለ መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያዎቹ አሕዛብ አማኞች ላይ ወረደ (የሐዋ. 10)። አሕዛብ ተጠምቀው ወደ አይሁዳዊነት ሳይለወጡ መንፈስ ቅዱስን ከእግዚአብሔር መቀበላቸው የጴጥሮስን አስተሳሰብ ለወጠው። በመሆኑም ወደ በኋላ ጴጥሮስ እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያምኑትን አሕዛብ እንደሚቀበል አጥብቆ ሲከራከር እንመለከታለን (የሐዋ. 15፡7-11)።

እግዚአብሔር ወንጌልን ወደ አሕዛብ ሁሉ ለማድረስ ጳውሎስ የተባለ ሌላ ሰው አስነሣ። ለጊዜው የአይሁዶች ሐዋርያ የተባለው ጴጥሮስ (ገላ. 2፡8) በኢየሩሳሌም ተቀምጦ በፍልስጥኤም ምድር ላሉ አይሁዶች ሁሉ ሲሰብክ ኖረ። ጴጥሮስ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ የሚያገለግል ሰባኪ በመሆኑ ምክንያት ይመስላል፥ በኢየሩሳሌም የነበረችው የእናት ቤተ ክርስቲያን አመራር የክርስቶስ ወንድም ለነበረው ለያዕቆብ ተሰጠ (ገላ. 1፡19)። ጴጥሮስ እስከሚሞትበት ጊዜ ድረስ በመጨረሻዎቹ 20 ዓመታት ምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደነበር የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ በግልጽ አይነግረንም። ጳውሎስ ጴጥሮስ በአንጾኪያ እንደነበረ ይናገራል (ገላ. 2፡1-14)። ምናልባትም ወደ ቆሮንቶስ ተጉዞ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች እንዲከተሉት ሳይጠይቃቸው አልቀረም (1ኛ ቆሮ. 1፡12)። የበለጠ ትክክለኛ የሚመስለው ኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ከተጠናከረበት ጊዜ በኋላ፥ ጴጥሮስ በምሥራቃዊ የሮም ግዛት ውስጥ እየተዘዋወረ የወንጌል መልእክተኝነት አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር የሚያሳየው ይሆናል። ጴጥሮስ በጳንጦስና በገላትያ፥ በቀጰዶቅያም፥ በእስያም፥ በቢታንያ ለተበተኑ መጻተኞች መልእክት ለማስተላለፍ በመፈለጉ ምናልባትም በእነዚህ አካባቢዎች ወንጌልን እንደ ሰበክ ሊያመለክት ይችላል። ጴጥሮስ የኋላ ኋላ ወደ ሮም እንደ ሄደ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያመለክታል። በዚያ ምን ያህል ጊዜ እንደ ሠራ አልተጠቀሰም። አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ በሮም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩትን አንዳንድ ክፍፍሎች ለማስተካከል ጴጥሮስን ጋብዞት ነበር ይላሉ። ነገር ግን በኔሮ ዘመነ መንግሥት ክርስቲያኖች ላይ ስደት በተነሣ ጊዜ ጴጥሮስ በምርኮኛነት ተወሰደ። አንድ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚያሳየው፥ ሮማውያን ጴጥሮስን ለመግደል በመጡ ጊዜ እንደ ጌታ ኢየሱስ ለመሰቀል ባለመፈለጉ፥ ራሴን ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ ብሏል። ይህ እውነት ይሁን እውነት አይሁን የሚታወቅ ነገር የለም። ምናልባትም ጴጥሮስ የሞተው ጳውሎስ በሞተበት ጊዜ አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። ይህም በ67 ዓመተ ምሕረት አካባቢ መሆኑ ነው።

የአንደኛ ጴጥሮስ መልእክት የተጻፈው በጴጥሮስ ነው። ጴጥሮስ ይህንን መልእክት የጻፈው በሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ ነው። ይህ መልእክት የተጻፈበት የግሪክ ቋንቋ ከፍተኛ ጥራት ስላለው ምናልባትም መልእክቱን የጻፈው ስልዋኖስ (ሲላስ) ሳይሆን አይቀርም። ሲላስ ግሪክን በሚገባ ያውቅ የነበረ ሲሆን፥ ጴጥሮስ የሚናገረውን አሳብ በዚሁ መልእክት ውስጥ ሳያሰፍር አልቀረም። ጴጥሮስ በእርጅናው ዘመን ይህን መልእክት ሲጽፍ ከክርስቶስ ጋር ለረጅም ጊዜ የኖረ በመሆኑ መከራን መቀበል ምን እንደሆነ ያውቅ ነበር። በወጣትነቱ ጊዜ እርሱ እንዳደረገው ክርስቶስን እንዳይክዱና በመከራ ታግሰው እግዚአብሔር ያዘጋጀላቸውን ሽልማት እንዲቀበሉ ያበረታታቸዋል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)