የሳሙኤል መወለድና ጥሪ (1ኛ ሳሙ. 1-3)

1ኛ ሳሙኤል ስለ መሪነት የሚናገር መጽሐፍ ነው። እግዚአብሔር በአንዳንድ መሪዎች ለምን እንደሚጠቀምና ሌሎቹን ደግሞ ለምን እንደሚተው ይናገራል። መልካም ወይም ክፉ መሪ የሚያደርጉ ነገሮች ምን እንደሆነ ይናገራል። ይህም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሁሉ ይህን መጽሐፍ ማጥናታቸው አስፈላጊ እንደሆነ ያሳየናል። መጽሐፉን የምንመለከተው ታሪኮችን ለመረዳት ብቻ ሳይሆን፥ እግዚአብሔርን የሚፈራ መሪ ምን እንደሚመስልም ለመረዳት ነው።

የ1ኛ ሳሙኤል የመጀመሪያ ክፍል ዔሊና ሳሙኤል የተባሉ የሁለት ግለሰቦችን ታሪክ የምናገኝበት ነው። በአንጻንድ መንገዶች በጣም ተመሳሳይ ነበሩ። ለምሳሌ፡- ሁለቱም ሕዝቡን በአምልኮ የሚመሩ ካህናት ነበሩ። ደግሞም ሕዝቡን በምክር የሚረዱ መሳፍንት ነበሩ። ሁለቱም ተመሳሳይ የሆነ ደካማ ጎን ነበራቸው። ዔሊም ሆነ ሳሙኤል ልጆቻቸውን መቆጣጠር አልቻሉም ነበር።

ነገር ግን በዔሊና በሳሙኤል ሕይወት አንዳንድ ልዩነቶችን እንመለከታለን። ለምሳሌ፡- ዔሊ ለመንፈሳዊ ነገር ንቁ አልነበረም። የሐናን ጸሎት መገንዘብ ስላልቻለ፥ እንደሰከረች ቆጥሯት ነበር። ዔሊ የእግዚአብሔርን ድምፅ መለየት አልቻለም ነበር። በታቦቱ የተመሰለው የእግዚአብሔር ሕልውና ለሕዝቡ ነፃነትን ለማምጣት እግዚአብሔርን ለማስገደድ እንደማይጠቅም አልተገነዘበም ነበር።

ሳሙኤል መንፈሳዊ ንቃት ነበረው። የሚኖረው ከዔሊ ልጆች ጋር ቢሆንም እንኳ የእግዚአብሔርን አምልኮ ባበላሸው ክፉ ተግባራቸው ለመሳተፍ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። ለእግዚአብሔር ድምፅ ንቁ የነበረና የሚያዳምጥ ነበር። ሳኦልን ለንጉሥነት መቀባት ማለት የእስራኤልን ሕዝብ ለመምራት ሥራ አሳልፎ መስጠት ቢሆንም፥ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ሳኦልን ቀባው። እንደ መሪ ያልተቀበሉት ቢሆንም ለእስራኤል ለመጸለይ ቃል ገባ። ሌሎች ሰዎች እርሱን በመተው ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ኅብረት እንዲበላሽና ሕዝቡን ያገለግል ዘንድ ከእግዚአብሕር ለተቀበለው ጥሪ ታማኝ እንዳይሆን ተጽዕኖ ለማሳደር ያደረጉትን ሙከራ አከሸፈ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ለመንፈሳዊ መሪ መንፈሳዊ ንቃት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ለ) ዛሬ አንድ እግዚአብሔርን የሚፈራ መሪ በመንፈሳዊ ነገር ንቁ መሆን እንዴት እንደሚችል ምሳሌዎችን ዘርዝር ሐ) ዛሬም ሲሆን አንድ እግዚአብሔርን የሚፈራ መሪ መንፈሳዊ ንቃት እንዴት ሊጎድለው እንደሚችል የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

በእነዚህ ታሪኮች ውስጥ እግዚአብሔርን ስለሚፈራ መሪ የሚከተሉትን ነገሮች መመልከት እንችላለን፡-

  1. የእግዚአብሔርን ድምፅ ለመስማት ንቁና ፈጣን ነው።
  2. ለራሱም ሆነ ለቤተሰቡ ፍላጎት ምቹ በማይሆንበት ጊዜ እንኳ ለእግዚአብሔር ይታዘዛል። 
  3. የእግዚአብሔር ሕዝብ ባልተቀበሉት ጊዜ እንኳ ለእነርሱ የሚጸልይ የጸሎት ሰው ነው። 
  4. በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ቂም አይዝም። 
  5. ቤተሰቡን በመቆጣጠር፥ ከእግዚአብሔር ጋር ወዳለው ትክክለኛ ግንኙነት ይመራቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህ አምስት ነገሮች በዚህ ዘመን ለሚገኙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚያስፈልጓቸው ለምንድን ነው? ለ) እነዚህ አምስት ነገሮች በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሕይወት ውስጥ ሊታዩ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ ተጨባጭ ማስረጃዎችን ስጥ። ሐ) እነዚህ አምስት ነገሮች በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሕይወት ውስጥ ብዙ ጊዜ እንዴት እንደሚጎድሉ ተጨባጭ መግለጫዎችን ስጥ። ለምንስ ይጎድላሉ?

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ሳሙኤል 1-12 አንብብ። ሀ) የሳሙኤል እናት ማን ነበረች? ለ) ሳሙኤል ጡት በጣለ ጊዜ ለመኖር የሄደው ወደየት ነበር? ሐ) አንዳንዶቹን የዔሊ ልጆች ኃጢአት ዘርዝር። መ) እግዚአብሔር በዔሊ ላይ የፈረደው እንዴት ነበር? ሠ) ከጦርነቱ በኋላ ታቦቱ የተወሰደው ወዴት ነበር? ረ) እግዚአብሔር ኃይሉን ለፍልስጥኤማውያን ያሳየው እንዴት ነው? ሰ) እስራኤል ምድራዊ ንጉሥን የጠየቀችው ለምንድን ነው? ሰ) እስራኤላውያን ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው በጠየቁ ጊዜ እግዚአብሔር ምን እያደረጉ ናቸው አለ? ቀ) ሳኦል መጀመሪያ በተቀባ ጊዜ የነበረውን ባሕርይ አስረዳ። በ) በሕይወቱ የእግዚአብሔር ሕልውና እንዴት ተገለጠ?

  1. የሳሙኤል መወለድና ጥሪ (1ኛ ሳሙ. 1-3)

የ1ኛ ሳሙኤል ጸሐፊ በሳሙኤል ሕይወት ላይ ከፍተኛ ትኩረት አድርጓል፡ ይህ የሆነበት ምክንያት፥ ሳሙኤል በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ቁልፍ ሰው ስለነበር ነው። በእግዚአብሔር ትእዛዝ በእስራኤል ሕዝብ መካከል ንጉሣዊ አስተዳደር እንዲጀምር አደረገ። ደግሞም ከሙሴ ዘመን በኋላ በእስራኤል ሕዝብ መካከል የኖረ ታላቅ ነቢይ ነው። 

በሌላ አንጻር መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዳዊትና ስለ ሳኦል መወለድ አንዳችም ነገር ሳይናገር፥ አስደናቂው የሳሙኤል አወላለድን ገልጧል። ይህ ታሪክ የቀረበው ሳሙኤል በእስራኤል ታሪክ ውስጥ በሚጫወተው እጅግ ጠቃሚ ሚና ላይ ትኩረት ለመስጠት ነው። የሳሙኤል አገልግሉት በነገሥታት ዘመን የነበረው የነቢይነት አገልግሉት ምሳሌ ስለሆነ፥ በዚህም አንጻር እጅግ ጠቃሚ ነው። «የነቢያት ትምህርት ቤት ወይም ጉባኤ» በመባል (1ኛ ሳሙ. 10፡5፤ 19፡18-24) የሚታወቀውን ተቋም ለመቆርቆሩ አንዳችም ጥርጣሬ የለንም። ይህ የነቢያት ቡድን በአንድ ስፍራ አብሮ ለመኖር የተሰባሰበ የእግዚአብሔር ሰዎች ስብስብ ነበር። እነዚህ ሰዎች ልዩ በሆነ በእግዚአብሔር ኃይል የተሞሉ ነበሩ። በኋላ የምናያቸው እንደ ናታንና ጋድ ወዘተ. ያሉ ነቢያት ከዚህ የነቢያት ጉባኤ የወጡ ሳይሆኑ አይቀሩም፤ ስለዚህ የነቢያት ጉባኤ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ በኤልያስና በኤልሳዕ ጊዜም እንደነበረ እንመለከታለን (ምሳሌ፡- 2ኛ ነገሥት 2፡3-15)፤ ስለዚህ የነቢያት ጉባኤ የሚባለው በሳሙኤል መሪነት ነቢያት በአንድነት የሚሰባሰቡበት ኅብረት፥ ከሳሙኤል በኋላም ለብዙ መቶ ዓመታት ሳይቀጥል አልቀረም። ይህ ኅብረት እንዴት እንደተደራጀና ግለሰቦችም ወደዚህ ኅብረት የሚገቡት እንዴት እንደነበረ የምናውቀው ነገር የለም። 

ሳሙኤልን ልዩ የሚያደርገው ሌላው ተጨማሪ ነገር፥ ሦስት ዋና ዋና የመሪነት ተግባራትን አጣምሮ መያዙ ነው። እርሱ ካህን፥ ነቢይና የፖለቲካ ገዥ ወይም መስፍን ነበር። በኋላ እነዚህ ሦስት ዋና ዋና የመሪነት ተግባሮች ለሦስት የተለያዩ ሰዎች የሚሰጡ ሆነዋል። ካህናት ከአሮን ዝርያ የሚመጡ ሆኑ፤ ነቢያት የእግዚአብሔርን መልእክት ወደ ሕዝቡ ይዘው የሚመጡ ከየትኛውም ነገድ ልዩ በሆነ መንገድ በእግዚአብሔር የተመረጡ ሰዎች ሲሆኑ፥ በኋላ በነገሥታት የተቀየሩት መሳፍንት ደግሞ የፖለቲካ መሪዎች ነበሩ። እነዚህን ሦስት የመሪነት አገልግሎቶች እንደገና አጠቃሉ የያዘው ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው። እርሱ ካህን (ዕብ. 9፡11) ነቢይ (ሉቃ. 1፡76) እና ንጉሥ (ራእይ 17፡14፤ 19፡ 16) ነው። 

ሳሙኤል የተወለደው ለብዙ ዓመታት መካን ሆና ከኖረች ከአንዲት ሐና ከምትባል ሴት ነበር። ይህች ሴት ከብዙ ጸሎት በኋላ እግዚአብሔር የሰጣትን ልጅ መልሳ ለእርሱ ሰጠችው። ልጁ ባደገም ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ የአምልኮ ማእከል ወደ ሆነው በሴሉ ወደሚገኘው የመገናኛ ድንኳን ለአገልግሎት ተላከ። በዚያም በዔሊ እጅ አደገ። 

ሳሙኤል በመገናኛ ድንኳን ውስጥ በሚያገለግልበት ጊዜ፥ የዔሊ ልጆች ግን በእግዚአብሔር ላይ ዓመፁ። የካህንነት መብታቸውን እጅግ ተገቢ ባልሆነ መንገድ በመጠቀም፥ ለስስታምነት ዓላማቸው ተጠቀሙበት። መሥዋዕት በሚያቀርቡበትም ጊዜ እግዚአብሔርን አላከበሩትም። እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ሊያቀርቡ ከሚገባቸው መሥዋዕቶች አንዱ የድነት (ደኅንነት) መሥዋዕት ነበር። በዚህ መሥዋዕት የእንስሳው የተወሰነ ክፍል በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ይቃጠል ነበር። የቀረው የመሥዋዕት ክፍል ግን ይቀቀልና ከፊሉ ለካህናት፥ ከፊሉ ደግሞ አምልኮውን ለሚፈጽመው ሰው ቀርቦ በኅብረት ይበሉ ዘንድ የተፈቀደ ነበር። በእግዚአብሔር ፊት በኅብረት ይበሉት ነበር፤ የዔሊ ልጆች ግን በጣም ስስታም ስለነበሩ ለራሳቸው የሆነውን የመሥዋዕት ክፍል ብቻ አይወስዱም። አምልኮውን የሚፈጽመው ሰው የተወሰነውን ክፍል ለእግዚአብሔር እስኪሰጥ ድረስ እንኳ አይጠብቁም። የፈለጉትን የእንስሳውን ክፍል ይወስዳሉ። በሥነ ምግባር እጅግ የተበላሹ ስለነበሩም ወደ አምልኮው ስፍራ የሚመጡትን ሴቶች አስገድደው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ይፈጽሙ ነበር። ዔሊ ሊገሥጻቸው ቢሞክርም እንኳ አልሰሙትም። ልጆች በነበሩ ጊዜ በሚገባ በሥርዓት አላሳደጋቸውም። ስለዚህ በዕድሜ በገፉ ጊዜ እግዚአብሔርን ረሱ፤ ይከተሉትም ዘንድ እምቢ አሉ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ልጆቻቸውን በልጅነት ወራት በሚገባ ባለማሠልጠናቸው፥ ዕድሜያቸው በገፋ ጊዜ ከእግዚአብሔር ፊታቸውን የመመለስ ችግር በጣም የተለመደው እንዴት ነው? ለ) ልጆች ካሉህ አሁን፥ ከሌሉህ ወደፊትም ቢሆን፥ እግዚአብሔርን እንዲከተሉና እንዲታዘዙ እነርሱን ልታስተምርባቸው ያሰብካቸውን ዘዴዎች ግለጽ፤ (ምሳ. 22፡6)።

ልጆቹ የእግዚአብሔርን እውነተኛ አምልኮ በማበላሸታቸውና ለእርሱ ክብር ባለመስጠታቸው ምክንያት እንደሚያጠፋቸው እግዚአብሔር ዔሊን ባልታወቀ ነቢይ አስጠነቀቀው። የሊቀ ካህንነትን መብት ለሌላ፥ ማለት በእግዚአብሔር ፊት በታማኝነት ላለው ለሳሙኤል እንደሚሰጠው ቃል ገባ። 

ገና በልጅነቱ ወራት እግዚአብሔር ሳሙኤልን ይናገረው ጀመር። ሳሙኤል እየተናገረው ያለው እግዚአብሔር መሆኑን ለመረዳት ጥቂት ጊዜ ወስዶበታል። በቀረው ዘመኑ ግን እግዚአብሔር ሳሙኤልን ይናገረው ነበር። ወጣት ቢሆንም እንኳ ሰዎች እግዚአብሔር ሳሙኤልን እንደመረጠውና ለሕዝቡ የእግዚአብሔርን መልእክት የሚናገር ነቢይ እንደሆነ ለማወቅ ጊዜ አልወሰደባቸውም። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

2 thoughts on “የሳሙኤል መወለድና ጥሪ (1ኛ ሳሙ. 1-3)”

Leave a Reply

%d