የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በድነት (ደኅንነት) ውስጥ

ዛሬ በጣም ጠቃሚውና ታላቁ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ድነት (ደኅንነት)ን የሚመለከት መሆኑ አያጠያይቅም። እርግጥ ከሕሊና ወቀሳ አንስቶ ሰውን መንግሥተ ሰማይ እስከ ማስገባት ድረስ የእርሱ ሥራ ነው። 

የሕሊና ወቀሳ ዮሐ 6፡8-11) 

“የሕሊና ወቀሳ” የሚለው አሳብ ውስብስብ ነው። የሚያጠቃልላቸው አሳቦች ሥልጣናዊ ምርመራን፥ የማያከራክር ማስረጃን፣ የማያወላውል ፍርድን፣ ቅጣትን ያካትታል። የጉዳዩ ማብቂያ ምንም ይሁን ምን በሌላው ላይ “የሚፈርድ” እውነትን በማያሻማ ሁኔታ ወደ ብርሃን በማውጣት ማሳየትና እንዲታመንበት ማድረግ ይኖርበታል። ይህን ዓይነቱን ተዓማኒ ፍርድና ውሳኔ የሚቃወም፥ እውነትን ካየም በኋላ በጭፍን የሚክድ መጥፊያውን ያከብዳል። እውነት እንደ እውነት ካልታየና ተቀባይነት ካላገኘ ፍርድን ያስከትላል።” 

በዚህ መንፈስ ቅዱስ የወንጌልን ብርሃን ላልዳነ ሰው በማብራት ሰውየው ኢየሱስን እንደ ግል አዳኙ ተቀበለም አልተቀበለ፥ እውነቱን እንዲያውቅ ያደርጋል። ወቀሳው መልእክቱን ግልጥ ማድረግ እንጂ፥ የመዳን (የመውለድ) ተግባር አይደለም። ማዳን ዳግመኛ ልደት መስጠት ነው። በሌላ አነጋገር ስለ እግዚአብሔር የማዳን ጸጋ የሚመሰክር ሰው ምስክርነቱ ግልጥ እንዲሆን በመንፈስ ቅዱስ መደገፍ አለበት። 

የትኛውን እውነት ነው መንፈስ ቅዱስ ግልጥ የሚያደርገው? እውነቱ ስለ ኃጢአት፥ ስለ ጽድቅ፥ ስለ ፍርድ ማሳወቅ ነው (ዮሐ. 16፡8 እና ተከታዮቹ ቁጥሮች)። ሰዎች በኃጢአት ውስጥ ለመኖራቸው ማረጋገጫ ቃሉ “በእኔ ስላላመኑ ነው” ይላል። የክርስቶስ ጽድቅ ከሞት በመነሣቱና ወደ አብ በማረጉ ተረጋግጧል። ጻድቅነቱ ወደ ሰማይ በተመለሰ ጊዜ ይፋ ሆኗል። መጪው ፍርድ የሚመሠረተውም ጥንት በሰይጣን ላይ በተፈረደው ዓይነት ይሆናል። የክርስቶስ ዋነኛ ጠላት ሰይጣን ከተፈረደበት (ዮሐ. 12፡31)፥ የእግዚአብሔርን ጸጋ የማይቀበል ሰውስ ከፍርድ ለማምለጥ ምን ተስፋ ይኖረዋል? 

የመንፈስ ቅዱስ የሕሊና ወቀሳ በቅደም ተከተል የሚካሄድ ነው። ሰው በቅድሚያ ኃጢአተኛነቱን ሊያጤን ይገባል። ከዚያም ከኃጢአቱ ሊያነጻው በሚችለው ጻድቅ አዳኝ ማመን ይኖርበታል። ይህን አዳኝና ጸጋውን ካልተቀበለ ግን፥ የዘላለም ፍርድ እንደሚጠብቀው መረዳት አለበት። 

ዳግም ልደት (ቲቶ 3፡5) 

ምንም እንኳ “ዳግም መወለድ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱሳችን የተጠቀሰው ሁለት ጊዜ ብቻ ቢሆን (ከቲቶ 3፡5 ላይ ዳግም ልደትን የሚያሳየውና ማቴ. 19፡28 ላይ የሺህ ዓመት ግዛትን የሚያመለክተው)፥ ዳግም የመወለድ አሳብ ዮሐንስ 3ን ጨምሮ በሌሎችም ክፍሎችም ይገኛል። በክርስቶስ ለሚያምን ሁሉ ዘላለማዊ ሕይወትን የመስጠት የእግዚአብሔር ተግባር ነው። እምነትና ዳግም ልደት የተቀራረቡ ቢሆኑም፥ የተለያዩም ናቸው። እምነት የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ጸጋ ይቀበል ዘንድ ሊከተለው የሚገባውን መንገድና ኃላፊነት ሲያመለክት፥ ዳግም ልደት ዘላለማዊው ሕይወትን የሚያስገኝ የእግዚአብሔር ልዩ ኃይል ነው። ሁለቱም በአንድ ላይ የሚከናወኑ ስለሆኑ፥ አንዱን ከአንዱ ለማስቀደም መሞከር ፍሬ ቢስና የአእምሮ ሥራ ዓይነት ሆኖ ይቀራል። አንዳንዶች፥ ሰው በኃጢአቱና ሕግ በመጣሱ የሞተ ስለሆነ ማመን አይችልም፤ ያምን ዘንድ እግዚአብሔር በቅድሚያ ዳግም ልደት ሊሰጠው ይገባል ይላሉ። ይህ እውነት ከሆነ፥ ማለት ዳግም ልደት ከተቀበለና የዘላለምን ሕይወት ካገኘ ማመኑ ለምን ያስፈልገዋል? ሁለቱ ክንውኖች በአንድ ጊዜ የሚፈጸሙና የማይለያዩ ናቸው። እንዲሁም የእግዚአብሔር ቃል ከዳግም ልደት ጋር በቅርብ የተያያዘ ሲሆን፥ ይህም ተገቢውን የትምህርት ይዘት ለሰው ልጅ እምነት ለመስጠት አስፈላጊ መገለጥ ነው (1ኛ ጴጥ. 1፡23፤ ያዕ. 1፡18)። 

ምንም እንኳን ለዳግም ልደት የቅድመ ሁኔታዎች መስተካከል አስፈላጊና ጊዜ የሚፈጅ ሂደት ቢሆንም፥ ያ ታላቅ ለውጥ ያንድ አፍታ ክንውን ነው። አንድ ሰው በዚያን ቅፅበት ዳግም ይወለዳል ወይም አይወለድም። ሰውየው የሚድንበትን ትክክለኛ ጊዜ አያውቅ ይሆናል፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ዓይን ወይ በኃጢአቱ ሙት የሆነ ወይም በአምላክ ቤተሰብነት የተወለደ ይሆናል። ዳግም ልደት አዲስ ፍጡር ያደርጋል (2ኛ ቆሮ. 5፡17)። በጽድቅ ለማገልገል አዲስ ጉልበት ይሰጣል። ሆኖም አሮጌው ባሕርይ ሙሉ በሙሉ ይጠፋል ማለት አይደለም። ምክንያቱም ሰው እስኪሞት ድረስ ራሱን የማገልገል ፍላጎት ይኖረዋል። ዳግም ልደት ሰውን በእግዚአብሔር ቤተሰብነት እንዲኖርና በክርስቶስ አምሳል እያደገ፥ አብን ለማስደሰት አዲስ ችሉታ እንዲኖረው ያደርገዋል እንጂ ፍጹም አያደርገውም። ከአዲሱ ባሕርይ የሚታየው ፍሬም ዳግም ልደት ለመከናወኑ እርግጠኛ ማረጋገጫ ይሆናል(1ኛ ዮሐ. 2፡29)። 

የመንፈስ ቅዱስ በሰው ውስጥ መኖር (1ኛቆሮ. 6፡19) 

ዛሬ የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ልዩ የሚያደርገው የሰውየው መንፈሳዊ ሁኔታ ምንም ይምሰል ምን፥ በእያንዳንዱ አማኝ ውስጥ መኖሩ ነው። ለዚህ ቀላል መመዘኛ የሚሆነን፥ ኃጢአት የሚያደርጉ ከርስቲያኖች እንኳን መንፈስ እንደሚኖርባቸው በአዲስ ኪዳን መገለጡ ነው። የቆሮንቶስ ሰዎች ትዝ ይሉዎታል? ሥጋዊ የሆኑ አማኞች ነበሩ (1ኛ ቆሮ. 3፡3)። አንድ ወንድም (1ኛ ቆሮ. 5፡5) በከፋ ኃጢአት ተዘፍቆ ይኖር ነበር። ብዙዎቹም እርስ በርሳቸው ይካሰሱ ነበር (1ኛ ቆሮ. 6)። ይሁን እንጂ ጳውሎስ እንዳች ልዩነት ሳያደርግ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ እንደሚኖርባቸው ጠቅሷል (1ኛ ቆሮ. 6፡19)። ይህን በመንተራስ ነው ሰውነታቸውን እንዳያረክሱ የመከራቸው። ሮሜ 8፡9 የመንፈሰ ቅዱስ በአንድ ሰው ውስጥ አለመኖር ያለመዳን ምልክት ነው ይላል። ስለዚህ መንፈስ በሰው ሕይወት የሚሄድና የሚመጣ ከሆነ ሰው ድነት (ደኅንነት) የማግኘቱና የማጣቱ ጉዳይ ይደጋገማል ማለት ነው። 

እንዴት ነው አንድ አማኝ የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጡ መኖሩን የሚያውቀው? ሁለት ማረጋገጫዎች አሉ። አንዱ የእግዚአብሔር ቃል የሚናገረውን እውነት ማመን ይሆናል። ሌላው ወደ ክርስቲያናዊ ልምምዶች ተመልክቶ የመንፈስን መኖርና አንድ ሰው ሕይወት ውስጥ የሠራውን መረዳት ነው። ይሁን እንጂ ኃጢአት የመንፈስን ሥራ ሊያግደው ይችላልና፥ ልምምድ ሁልጊዜ የመንፈስን መኖር እያረጋግጥ ይሆናል። እናም ጤናም በሆነ የክርስትና ሕይወት የአንድ ሰው እድገት አዝጋሚና የማይቋረጥ፥ ብሎም ልዩ የሆን የእግዚአብሔር ኃይል የማይከሰትበት ሊሆን ይችላል። ቢሆንም ይህ ዓይነቱ እድገት የመንፈስን በአንድ ሰው ውስጥ አለምኖር የሚያሳይ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። መንፈስ ቅዱስ በእያንዳንዱ አማኝ ሕይወት ውስጥ ለዘላለም ይኖራል (ዮሐ. 14፡16-17)። 

ማጥመቅ (1ኛቆሮ. 12፡13) 

ጥምቀት ሲባል ብዙዎች የሚታያቸው የውኃ ምስል ወይም ልዩ የሆነ ኃይል መገለጥ ነው። ይህ ግን የመንፈስን የማጥመቅ ሥራ በትክክል አይገልጠውም፡፡ ጥምቀት የሚለው ቃል ከውኃ ጥምቀት የተለየ ነው። ይህም ለክርስቲያን በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ቦታን፥ በሁለተኛ ደረጃ ኃይልን ይሰጠዋል። ብዙ ጊዜ ሰዎች በውኃ ጥምቀትና በመንፈስ ቅዱስ ሙላት መካከል ባለው ልዩነት ግር ይሰኛሉ። ሁለቱ የተለዩ የመንፈስ አገልግሎቶች ናቸው። ከመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት መለያዎች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል። 

1. የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ያለ ምንም ልዩነት ለአማኝ ሁሉ የሚፈጸም ነው። ጳውሎስ ሥጋዊ ለሆነችው የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሲጽፍ ነበር ሁሉም በመንፈስ ተጠምቀዋል ያለው (1ኛ ቆሮንቶስ 12፡13)። ከሥጋዊነት ለመዳን ተጠመቁ ብሎ እንዳልመከራቸው ያስተውሉ። 

2. የመንፈስ ጥምቀት በመጀመሪያ የተከናወነው በበዓለ አምሳ ዕለት ነበር (ጌታ በሐዋርያት ሥራ 1፡5 የሰፈረውን ቃል የተናገረው ገና ወደፊት እንደሚፈጻም አድርጎ ሲሆን፥ ጴጥሮስም በሐዋርያት ሥራ 11፡13-16 ላይ መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያ በበዓለ አምሳ ዕለት እንደወረደ አስታውቋል)። ስለዚህ የመንፈስ ጥምቀት ለአሁኑ ስፍረ-ዘመን ልዩ የሆነ ነገር ነው። 

3. አማኝ የሚጠመቀው አንዴ ብቻ ነው (በ1ኛ ቆሮንቶስ 12፡13 ያለውና ድርጊቱ የተፈጸመበትን ጊዜ የሚያሳየው የግሥ ዓይነት [Aorist/ ኤሪስት] ጥምቀት የማይደገም መሆኑን ያሳያል። 

4. ጥምቀት አማኙን የብዙ ኃይል ምንጭ ከሆነው ክርስቶስ አካል ጋር ያዋህደዋል (ሮሜ 6፡1-10)። ይሁን እንጂ ከተለመደው ውጭ ለየት ባለ የሕይወት ልምምድ አለመኖር በመንፈስ አለመጠመቅን አያመለክትም (ይህ ከሆነማ አንድ ሰው አማኝ ቢሆንም በክርስቶስ አካል ውስጥ አልኖረም ማለት ይሆናል)። ሥጋውያኑ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀው ነበር። የገላትያ ሰዎችም በመንፈስ ቅዱስ የተጠቁ ሆነው ከእውነተኛው ወንጌል ዞር ብለው ነበር (ገላ. 1፡6፥ 3፡27)። በልሳን ያልተናገሩ ብዙዎች ተጠምቀው ነበር (1ኛ ቆሮ. 12፡13፣ 30)፡፡ በመጠመቅ የሚገኘውን ይሆን አዲስ ደረጃ ከነበረከቱ ለመለማመድ በመንፈስ ቅዱስ መሞላትን ይጠይቃል። ጥምቀቱ ለክርስትና እድገትና ልምምድ መሠረት ነውና። 

ማተም (ኤፌ. 4፡30) 

የአማኙ የዘላለም ድነት (ደኅንነት) ዋስትና ትልቁ ማረጋገጫ፥ አብ ማንኛውንም አማኝ በመንፈስ ቅዱስ ማተሙ ነው (2ኛ ቆሮ. 1፡22፤ ኤፌ. 1፡13፥ 4፡30)። ሁላችንም ታትመናል (ሥጋውያኑን የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጨምሮ)፤ ይህም የሚሆነው ባመንን ጊዜ ነው (ኤፈ. 1፡13)። 

ማተም የሚለው አሳብ ባለቤትነትን፥ ሥልጣንና ጥበቃን ያካትታል። እግዚአብሔር ስላተመን ንብረቱ ነን፤ እስከ ቤዛ ቀን ድረስ እንጠበቃለን (ከእርሱ በላይ ኃይለኛ እስከሌለ ድረስ)። ስለ ማኅተም የሚያስረዳን ጥሩ ምሳሌ የአደራ ደብዳቤ ነው። አንድ የአደራ ደብዳቤ ፖስታ ቤት ሲመዘገብ ይታተማል። ያን የታተመ ፖስታ ሊከፍቱ የሚችሉት ላኪው፥ ወይም ተቀባዩ ብቻ ናቸው። በእኛም ሁኔታ እግዚአብሔር ላኪም ተቀባይም ነው። እርሱ ብቻ ነው ማኅተውን ሊከፍት የሚችል። ወደ መንግሥተ ሰማያትም ሊያስገባን ቃል ገብቷል። እንግዲህ ዘላለማዊ ድነት (ደኅንነት) በአጭሩ ይህን ይመስላል። ነገር ግን የኤፌሶን 4፡30ን የጥቅስ አገባብ ያስተውሉ። መታተም መንፈስን ኃጢአት በመሥራት (በተለይም በአንደበታችን) እንዳናሳዝን ላቀረበው ወቀሳ መሠረት ነው። ስለ ዋስትና ተገቢ ግንዛቤ ማግኘት ለኃጢአት ፈቃድ ከመገዛት ይጠብቃል።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.