የእግዚአብሔር መለያዎች

የእግዚአብሔር መለያዎች በግልጥና በሥርዓት ሲተነተኑ፥ ባሕርያት [Attributes/አትርቢዩትስ] ተብለው በተለምዶ በሁለት ይከፈላሉ። እግዚአብሔር እንደ እኛ የሆነበት አንዳንድ ሁኔታዎች አሉ (ለምሳሌ እግዚአብሔር ትክክል ነው፥ ሰውም ትክክል ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ እግዚአብሔርን ልዩ የሚያደርጉት ሁኔታዎች አሉ (ዘላለማዊ ነው፥ ከእኛ አፈጣጠር ጋር ጨርሶ አይመሳሰልም። ይሁን እንጂ እነዚህ ክፍሎች ራሳቸውን የቻሉ አይደሉም። እያንዳንዱ የእግዚአብሔር ባሕርይ በየትኛው ክፍል መመደብ ይኖርበታል የሚለው ጥያቄ ክርክር ሊያስነሳ ይችላል። ባሕርያቱን የምናጠናበት ምክንያት፥ ስለ እግዚአብሔር የተገለጠውን ለማወቅ ብቻ ሳይሆን በሰው ሕይወትና አመለካከት ላይ የሚያስከትለውን ለውጥም ጭምር ለመረዳት ነው። 

(1.) አግዚአብሐር ሁሉን አዋቂ ነው። ይህ እውቀቱ ከዚህ በፊት የተከሰቱ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን ወደፊት ሊፈጸሙ የሚችሉትንም የሚጨምር ነው። ይህ ትምህርት ሳይሻ ራሱ ያለው እውቀት ነው። ጌታ ኢየሱስ ይህን መሰል አዋቂነት ሲያሳየን በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበርና። ብሏል (ማቴ. 11፡21)። ከዚህ ቀደም ሊከናወኑ ይችሉ የነበሩ ነገሮችን ስለማወቁ የሚጠቅሱ መረጃዎች እሆ። እግዚአብሔር “የከዋክብትንም ብዛት ይቆጥራል ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል” (መዝ. 147፡4)። እንዲሁም ከጥንት ጀምሮ ሥራው ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ነው…” (ሐዋ. 15፡18)። 

የእግዚአብሔር ሁሉን አዋቂነት የተገለጠባቸው አያሌ ተግባራዊ ውጤቶች አሉ። ለምሳሌ በአንድ አማኝና በሚደረግለት ዘላለማዊ ጥበቃ መካከል ያለውን ዝምድና እናስብ። እግዚአብሔር ሁሉን ስለሚያውቅ ሲያድነንም ስለ ደኅንነታችን የማያውቀው ጉዳይ አይኖርም፡፡ዘላለማዊውን ደኅንነት ሲሰጥ በእርሱ ዘንድ የተሰወረ አንዳች ነገር የለም። አሳዛኝና አስደንጋጭ ነገር ሲደርስብንም ከእርሱ እውቀት የተሰወረ አይሆንም። ሁሉን ከመነሻው ያውቃል። እንዲሁም ሁሉን ነገር ለከብሩና ለእኛ ሕይወት፥ ለመልካም ያደርገዋል። እስቲ የእግዚአብሔር ሁሉን አዋቂነት ከከርስትና ሕይወታችን ጋር ያለውን ዝምድና እናስብ። እርሱ ሁሉን ስለሚያውቅ አስቸጋሪዎቹንና ደሰ የምንሰኝባቸውን ሁኔታዎች የመለያ ጥብብ ይለግሰናል። የሚያዘንን ሁሉ ተግተን ከፈጸምን ከብዙ ችግሮች መዳን ብቻ ሳይሆን፥ ደስተኞችም እንሆናለን። 

(2.) እግዚአብሔር ቅዱስ ነው። ቅድስና የሚለውን ቃል መተርጎም እጅግ ያዳግታል። መዝገበ ቃላት፥ ቅድስና ክፋት የሌለበት ነገር ነው ብሎ፥ የሚመዘነውም እንደየግለሰቡ አመለካከት መሆኑን ብቻ ስለሚገልጥ እምብዛም አይረዳንም። በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ቅድስና ያለጥርጥር ከክፋት መራቅ ሲሆን፥ በጎ ምግባርንም ይጨምራል፡፡ቅድስና ብቸኛው የእግዚአብሔር መለያ ባሕርይ ባይሆንም፥ ከዋንኞቹ መለያዎቹ አንዱ ነው። በመሆኑም እግዚአብሔር ከቅዱስ ባሕሪው ጋር የማይጣጣምም ነገር አያደርግም፡፡ጴጥሮስም “የጠራችሁ ቅዱስ ነው” ሲል ይመሰክርና ይህ ባሕርይ በሕይወታችን የሚያመጣውን ለውጥ ሲገልጥ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ” ይላል (1ኛ ጴጥ. 1፡15)። 

ቅድስናን ለመግለጥ አንድ ምሳሌ መጠቀም ይረዳ ይሆናል። ጤናማ መሆን ማለት ምን ማለት ነው? ጤናማ መሆን ካለመታመም የተሻለ ነው። እንዲሁም ቅድስና ከኃጢአት መራቅ ከሚለው አሳብ በጣም ይስፋል። ቅድስና ቀጥተኛና ትክክለኛ መሆን ማለት ነው። ዮሐንስ እግዚአብሔር ብርሃን ነው ሲል ይህን ማለቱ ነው (1ኛ ዮሐ. 1፡5)። 

የዚህ ጥቅስ አባባል ግልጥ ነው። “በብርሃን ተመላለሱ” ማለት ነው። ሰለዚህ ለክርስቲያናዊ ሕይወት አስፈላጊ ስለሆነው ቅድስና በቂ ግንዛቤ ካለን አንድ ክርስቲያን ምን ማድረግ አለበት? ምንስ ማድረግ የለበትም? የሚለው ጥያቄ በአጭሩ ይቀጫል። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የምሠራው ሥራ ቅዱስ ነውን? ለሚለው ጥያቄ ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ፥ ከክርስቲያን ድርጅታቸውና ከቡድን አጋሮቻቸው ሳይርቁ፥ ወይም ሳይገለሉ፥ ምን ያህል ወደ ኃጢአት መቅረብ እንደሚችሉ ለማወቅ የሚጥሩ ይመስላል። እርስዎ ግን የቅድስና መሪ እንጂ፥ ወለም ዘለም የሚሉ ቡድኖች መሪም ተከታይም አይሁኑ። ይህ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል፤ ምከንያቱም ድርጊትዎ እርሱን ለመምሰል መጣርዎን ያሳያልና። 

(3.) እግዚአብሔር ቅን ፈራጅ ነው (ጻድቅ ነው)። ቅድስና በመሠረቱ የእግዚአብሔርን ባሕርይ ሲያመለክት፥ ቅን ፍርድና ጻድቅነት ግን ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ያተኩራል። ይህም ማለት እግዚአብሔር ሰዎችን በእኩልነት ያያል ወይም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስረዳን አድሏዊ አይደለም። ዳዊትም እንዲህ ብሏል፡- “የእግዚአብሔር ፍርድ እውነትና ቅንነት በአንድነት ነው” (መዝ. 19፡9፥ 116፡5፥ 145፡17፤ ኤር. 12፡1)። 

የእግዚአብሔር ትክክለኛነት የሚታየው ከፍርዱ ጋር ሲያያዝ ነው። ሰዎች ፍርድን ከእግዚአብሔር ለመቀበል ፊቱ ሲቆሙ፥ ያልተዛባ ብያኔ ያገኛሉ። ይህም በአንድ በኩል መጽናናት ሲሆን (በዚህኛው ሕይወት ለተጎዱት) ደግሞም ማስጠንቀቂያ ነው (ክፋት ቢሠሩም ቅጣት የማይደርሰባቸው ለሚመስላቸው)። ጳውሎስ ባልዳኑ ሰዎች ፊት በቆመ ጊዜ በማጠናከር የሰጠው ማስጠንቀቂያ፣ ስለሚመጣው የጻድቅ ፍርድ ነው፥ “በዚያን ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፥ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጧል” (ሐዋ. 17፡31)። 

ምናልባትም እግዚአብሔር ኃጢአተኛውን ካዳነ፣ ጻድቅ መሆን ይችላል ወይ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ይህ መልካም ጥያቄ ሲሆን መልሱንም ጳውሎስ በሮሜ 3፡21-26 ላይ በአዎንታ አስፍሮታል። ምክንያቱም (እርሱ እንደሚያስረዳው) እግዚአብሔር የሚሻውን የኃጢአት ዕዳ ኢየሱስ በሞቱ ስለከፈለልን ነው። ስለዚህ ዋጋ ከተከፈለ ዘንዳ እግዚአብሔር ትክክለኛ ሊሆን ይችላል (ቅድስናው ሳያወላውል)። በኢየሱስ የሚያምነውም የመዳን ጸጋ ያገኛል። 

(4.) እግዚአብሔር ፍቅር ነው (1ኛ ዮሐ. 4፡8)። ፍቅር ምንድነው? ይህ ቃል ብዙ ጊዜ የምንጠቀምበት ሲሆን በመዝገበ ቃላት ግን ትርጉሙ በትክክል አልተገለጠም፡፡የፍቅርን ትክክለኛ ፅንሰ አሳብ ለማግኘት አንድ መንገድ አለ። ወጣቶች ስለ ፍቅር ሲያስቡ በመጀመሪያ የሚሰላሰሉት ደስ ስለሚለው ስሜታዊ ልምድ ነው። ይህ ፍቅር ነው ቢባልም አሳቡን በሙላት አይገልጠውም። እነዚህ ወጣቶች ሲያድጉ፣ ሲያገቡና ሲወልዱ ልጆቻቸውን በሥነ-ሥርዓት መምራት እንዳለባቸው ይረዳሉ። እሹሩሩ የሚሉት ልጃቸው፥ የሚያቃጥል ነገር ለመንካት ሲሞከር ይገሥጹታል። ይህ የፍቅርን ሁለት ገጽታ ያሳየናል፤ የፍቅር ትርጉም ማፍቀርንና ማረምን የሚያጠቃልል መሆኑን። ከዚህ በመነሳት ለጊዜው የፍቅር ትርጉም ለተፈቃሪው መልካምን ሁሉ መሻት ነው እንል ይሆናል። ነገር ግን ወላጆች እንደሚያውቁት አንድን ሕፃን የሚንከባከቡት ብዙ አያቶችና አክስቶች የመኖራቸውን ያህል፥ ሕፃናትን በማሳደግ ሞያ የሰለጠኑ ሌሎች ሰዎችም አሉ። ለአንዱ መልካም መስሎ የታየው ነገር በሌላው አስተሳሰብ ተቃራኒው ይሆን ይሆናል። ክርስቲያን ግን መልካም የትኛው ነው? ለሚለው ጥያቄ መልሱን በቀላሉ ያገኛል፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ መልካም ነውና! ስለዚህ ከዚህ በፊት የሰጠነውን ትርጉም በማሻሻል ፍቅር ማለት የእግዚአብሔር ፈቃድ በምናፈቅረው ሰው ውስጥ መስረፁን መሻት ማለት ነው ልንል እንችላለን። ግን ይህ በግብር ሊረጋገጥ ይችላል? እስቲ እንፈትነው! እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ ማለትም የራሱን ፈቃድ ወይም ክብር ይሻል። ይህ የምናውቀው እውነት ነው። እግዚአብሔር ዓለምን ወዷል፥ ትርጕሙም በዓለም ያሉ ሁሉ ፈቃዱን እንዲከተሉ ይሻል ማለት ነው። እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን ይወዳል፤ ፈቃዱን እንዲፈጽሙና በአንድ ልጁ እንዲያምኑ ይፈልጋል። እርስ በርሳችን መዋደድ አለብን፥ ማለት የእግዚአብሔር ፈቃድ በሕይወታችን እንዲከናወን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። በዚህ አኳኋን ገለጣው የሚሠራ ይመስላል። 

እግዚአብሔር ፍቅሩ እጅግ የጠለቀ ከመሆኑ የተነሳ ማንም ከሚገምተው በላይ ለፍጥረቱ መልካምን ያስባል (1ኛ ዮሐ. 3፡16፤ ዮሐ. 3፡16)። እግዚአብሔር ፈቃዱ ከሰው ልጆች ጋር በስሜት መተሳሰሩ ከሰው አሳብ በላይ በሆነ አሠራር ፍቅሩን መግለጡ ነው። ከሁሉ የላቀ የፍቅሩ መግለጫ ግን ልጁን ለሰው ልጆች ደኅንነት ሲል ለመሥዋዕት መስጠቱ ነው (1ኛ ዮሐ. 4፡9-30)። መጽሐፍ ቅዱስም የእግዚአብሔር ፍቅር በእግዚአብሔር ልጆች ልብ ፈሷል ይላል (ሮሜ 5፡8)። 

ዛሬ ብዙ ተከታዮች ያሉት አንድ ትምህርት አለ፡- እግዚአብሔር ፍቅር ስለሆነና ፍጥረታቱን ስለሚወድ በሰዎች አይፈርድም፤ በመጨረሻ ሁሉም ይድናሉ የሚል። ይህ ትምህርት “ዩኒቨርሳሊዝም” [Universalism] ይባላል። የዚህ ትምህርት ችግር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኃጢአተኞች ለዘላለም ወደ ገሃነም እንደሚጣሉ የተጠቀሰውን (ማር. 9፡45-48)፣ መቃረኑ ብቻ ሳይሆን፥ ስለ ፍቅር ትርጉምና ከእግዚአብሔር ባሕርይ ጋር ስላለው ግንኙነት አለመረዳትም ጭምር ነው። ፍቅር ሊቀጣ ይችላል፥ የእግዚአብሔር ፍቅርም ከሌሎች ባሕርያቱ፥ በተለይም ከቅድስናና ከጽድቁ ተለይቶ አይሠራም። 

(5.) እግዚአብሔር እውነት ነው። እውነት፥ ለገለጣ አስቸጋሪ የሆነ ሌላ ፅንሰ አሳብ ሲሆን፥ መዝገበ ቃላት፥ በግንኙነት ላይ የተመሠረተ መግባባት ነው ይለዋል። መዝገበ ቃሉ እግዚአብሔርን በተመለከተ በሚሰጠው ትርጉም፥ እግዚአብሔር የማይለዋወጥ እንደመሆኑ የሚያደርገው ሁሉ እውነት ነው በማለት ያስረዳል (ሮሜ 3፡4)። ኢየሱስም ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር በማስተካከል እኔ እውነት ነኝ ብሏል (ዮሐ. 14፡6)። ይህ የእግዚአብሔር እውነተኛነት የሚያረጋግጠው፥ በሰጣቸው ቃል ኪዳናትና ተስፋዎች ተፈጻሚነት ነው። ይህም ተስፋ ለብዙሃን ወይም ለግለሰቦች ሊሆን ሲችል፥ ለእስራኤል የሰጠውንና በግልም ለአማኞች በየቀኑ የሚገባውን ቃል ያጠቃልላል። የእግዚአብሔር እውነት በራሱ መገለጥም ይንፀባረቃል፥ እርሱ የማይፈጽመውን ቃል ለእኛ አልገለጠምና። 

(6.) እግዚአብሔር ነጻ ነው። የፍጥረቱ ጥገኛ አይደለም። ይህ ግን ከራሱ ነጻ ነው ማለት አይደለም። ብዙ ጊዜ እግዚአብሔርን የሚወስነው የራሱ ባሕርይ ብቻ ነው ሲባል እንሰማለን፥ (ለምሳሌ ኃጢአት የማያደርገው ቅድስናው ስለሚያግደው ነው)። ምናልባት ነሩን እንደሚከተለው ለየት ባለ መልክ መመልከት ይሻል ይሆናል። እግዚአብሔርን የሚወስነው ፍጹምነቱ ነው። ፍጹምነት ደግሞ በተጨባጭ ሲታይ እገዳ ባለመሆኑ በእውነቱ እግዚአብሔር በምንም ነገር አይታገድም። ኢሳይያስ፥ እግዚአብሔርን ያማከረው፥ ያስተማረው ማነው? በማለት ሕዝቡን ሲጠይቅ (ኢሳ. 40፡13-14)፥ ማንም የሚል መልስ በመጠበቅ ነበር። ምክንያቱም እግዚአብሔር ነጻ ነውና (የፍጥረቱ ጥገኛ ያልሆነ ማለት ነው)። ይህ እውነት ከሆነ እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ያደረገው በጎ ነገር ሁሉ በፈቃደኝነት እንጂ ተገዶ የፈጸመው አለመሆኑን እንረዳለን። የሚያስገድደው ኃይልም ከቶ የለም። ያደረገልን ሁሉ ለእኛ ካለው ፍቅርና ርኅራኄ የተነሳ ብቻ ነው። 

(7.) እግዚአብሔር ሁሉን አድራጊ ነው። ይህ ሁሉን አድራጊነቱ በመጽሐፍ ቅዱስ አምሳ ስድስት ጊዜ ተገልጧል። (ይህ ቃል ከእግዚአብሔር በስተቀር ስለማንም አልተነገረም፥ ራእይ 19፡6ን ይመልከቱ።) ተማሪዎች ብዙ ጊዜ ስለ እግዚአብሔር ሁሉን አድራጊነት ሲወያዩ ሁለትና ሁለትን ስድስት ሊያደርግልን ይችላልን? በማለት ይቀልዳሉ። እንዲህ ያለው ፌዘኛ አስተሳሰብ የእግዚአብሔርን ሁሉን አድራጊነት በወጉ አያገናዝብም። አንድ ድማሚት ሁለትና ሁለትን ስድስት ያደርጋል ወይ? ብሉም ከመጠየቅ የተለየ አይሆንም። የሂሳብ ስሌቶች ሁሉን በመቻል ክልል ውስጥ የሚመደቡ አይደሉም። ነገር ግን የአማኞች የዘላለም ደኅንነት በዚህ በእግዚአብሔር ሁሉን አድራጊነት ጥላ ሥር በጽኑ የተጠበቀ ነው (1ኛ ጴጥ. 1፡5)። እርግጥ የደኅንነታችን ምንጩ የእግዚአብሔር የማዳን ኃይል የሆነው ወንጌል ነው (ሮሜ 1፡16)። ስለዚህ በርሱ የማዳን ኃይል የመዋጀታችን መሠረት ስለጸና እግዚአብሔርን እናመስግነው እንጂ፣ ጸጋውን አቃለን እንለፈው። የእግዚአብሔር ሁሉን አድራጊነት ከዚህም በላይ በመፍጠር ኃይሉ (ዘፍጥ. 1፡1)፥ ሁሉን በማጽናቱ (ዕብ. 1፡3) እና በሚያደርግልን ዘላለማዊ ጥንቃቄ ታይቷል። 

(8.) እግዚአብሔር የማይወሰንና ዘላለማዊ ነው። አለመወሰን የሚለውን ቃል ለመረዳት ቢቻልም ከሰው ደካማ ተፈጥሮ ሳቢያ እጅግ ከባድ ነው። እርግጥ ብዙ መዝገበ ቃላት ቃሉን በተቃራኒው በመግለጥ አማራጭ ሲጠቀሙ እናያለን። ማለቂያ፥ ማብቂያ፥ ማቆሚያ የሌለው እያሉ ይተረጉሙታል። ዘላለማዊነትም በጊዜ አንጻር ሲታይ ወሰን የሌለው ተብሉ ይተረጎማል። በዚህ መሠረት እግዚአብሔር በምንም የማይወሰን፥ በጊዜም መስፈርት የማይለካ መሆኑንና ከጊዜ በፊትና፥ ከጊዜም በኋላ የሚኖር መሆኑን እንረዳለን። ይህ ግን፥ ጊዜ በእግዚአብሔር ዘንድ አይታወቅም ማለት አይሆንም። ምንም እንኳን እግዚአብሔር ያለፉትንና የወደፊቱን ጊዜ ልክ እንደ አሁኑ በግልጥ ቢመለከታቸው፥ የሚያያቸው በየተራ እንደሚፈጸሙ እንጂ በሂደቶቹ የሚወሰን ሆኖ አይደለም። “ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘላለም እስከ ለዘላለም አንተ ነህ” (መዝ. 90፡2፤ ዘፍጥ. 21፡33፤ ሐዋ. 17፡24)። 

(9.) እግዚአብሔር አይለወጥም። ይህ አባባል እግዚአብሔር የማይለወጥና ሊለወጥ የማይችል መሆኑን ያሳያል። ስለ እግዚአብሔር ስናስብ የሚያድግና የሚሻሻል አካል እንደሆነ አድርገን መሆን የለበትም፡፡በእርሱ ዘንድ መለወጥ የሚባል ነገር የለም (ያዕ. 1፡17ን ከሚልክያስ 3፡6 እና ከኢሳይያስ 46፡9-10 ጋር ያነጻጽሩ)። 

የእግዚአብሔርን አለመለወጥ በሚመለከት አንድ የሚያጋጥመን ችግር አለ። ይህም እግዚአብሔር እንደተጸጸተ የሚገልጡትን ጥቅሶች በሚመለከት ነው (ዘፍጥ. 6፡6፤ ዮናስ 3፡10)። እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔር ዕቅዱን እንደለወጠ የሚያሳምኑ ከሆነ፥ የማይለወጥ አምላክነቱ ወይም ሉዓላዊነቱ ተሽሯል ማለት ነው። ነገር ግን እነዚህ ጥቅሶች መገለጥን ወይም የእግዚአብሔርን እቅድ ለሰዎች ማሳየትን ብቻ የሚያመለክቱ ከሆነ፥ ምንም እንኳን ዕቅዱ የማይለውጥ ቢሆን፥ ሰው ሲያየው ግን ለውጥን የያዘ ይመስላል። በሌላ ቃል የእግዚአብሔር “መጸጸት” በኛ ጠባብ ግንዛቤ ሲታይ እንጂ የእርሱ ዘላለማዊና የማይለወጥ ዕቅድ በታሪክ ውስጥ ተፈጻሚ ይሆናል። 

(10.) እግዚአብሔር በሁሉ ስፍራ አለ። ይህ አሳብ አስቸጋሪ አይደለም። ነገር ግን ከዚህ ጋር የተያያዙ ሌሎች ትምህርቶችን መቀበሉ ይከብዳል። ለምሳሌ የእግዚአብሔር በሁሉ ስፍራ መገኘቱና ሁሉ ነገር እግዚአብሔር ነው በሚለው “ፓንቲይዝም” [Pantheism] እምነት መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? በመሠረቱ እግዚአብሔር በሁሉ ስፍራ አለ ሲባል በማንነቱ ውስጥ ይኖራል ማለት ሲሆን፥ ፓንቲይዝም የተሰኘው ትምህርት ግን እግዚአብሔር በሁሉ ነገር ውስጥ አለ ይላል። እግዚአብሔር ሁሉ ስፍራ አለ ሲባል፥ እርሰዎ ይህን መጽሐፍ በሚያነቡበት ክፍል ውስጥ አለ ማለት ሲሆን፥ ፖንቲይዝም ግን በወንበሩ፥ በመስኮቱ … ውስጥ አለ ይላል። ሌላው ዋና ልዩነት ደግሞ የሚከተለው ነው። ምንም እንኳን እግዚአብሔር በሁሉም ቦታ ቢገኝ (ሁሉም ነገር ውስጥ አይደለም) በተለያዩ ቦታዎች በተለያየ ደረጃ መገኘቱ እውነትን የሚቃረን አይደለም። የእግዚአብሔር በክብር መገኘት ለአማኛች አንዳንድ ጊዜ በግልጥ የሚታይ ሲሆን፥ ባልዳኑት ሰዎች ዘንድ ግን መገኘቱ ተቀባይነት አይኖረውም። በተጨማሪ የእግዚአብሔር መገኘት በሚታይ አካል አይደለም። አንዳንዴ እግዚአብሔር ሲገልጥ ክብሩ ሲታይ፥ በሁሉ ስፍራ መኖሩ ግን መንፈሳዊ ክስተት ነው። መዝሙር 139 ስለ እግዚአብሔር በሁሉም ስፍራ መገኘት በግልጥ ያስተምራል። ትምህርቱ ማንም ከእግዚአብሔር ሊያመልጥ እንደማይችል የሚገልጥ ነው። ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ከእርሱ ለመሸሽ ቢጥሩም፣ በሞት ጊዜ ከእርሱ ሊያመልጡ አይችሉም፡፡በሌላ በኩል አማኝ የሆነ ሰው በማንኛውም ጊዜ ከእርሱ ጋር የመመላለስን በረከት ሲቀዳጅ በመከራና በችግሩም ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ሊያደርግ እንደሚችል ይታወቃል። 

(11.) እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ነው። ከሁሉ በላይ ነው ስንል የበላይ አለቃ፣ የመጨረሻው ባለሥልጣን፥ ብቸኛ የዓለማት ገዥ ማለታችን ነው። ይህ በእውነተኛ ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ቢረጋገጥም፥ ይህ ገዥ ግዛቱን እንዴት እንደሚመራ አይገልጥም። ቃሉ የሚያመለክተው በዓለም ሁሉ የበላይ ገዥ መሆንኑ ብቻ ነው። እርግጥ ገዥነት ሥልጣንን ያመለክታል። የእግዚአብሔር ሥልጣን ደግሞ አጠቃላይና ፍጹም ነው። ይህ ማለት ዓለምን እንደ አምባገነን ገዥ ይገዛል ማለት አይደለም። ምክንያቱም እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ብቻ ሳይን፥ ፍቅርና ቅዱስም ነው። ባሕርያቱን በተናጠል ሳይሆን በአንድ ጊዜ በኅብረት ይጠቀምባቸዋል። ከሁሉ በላይ መሆኑን የገለጠው የሥልጣት ስፋት አጠቃላይ ዕቅዱን ከዝርዝር ተግባራዊነቱ ያጠቃልለዋል። አንዳንድ ሁኔታዎች እርሱ በደነገገው ሕግ መሠረት በተፈጥሯዊ እቅጣጫቸው እንዲጓዙ ቢፈቅድም እንኳን፥ እርሱ ነው ድንቅ በሆነ ጥበቡ በነደፈላቸው ዕቅድ የሚያንቀሳቅሳቸው። 

መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር የሁሉም የበላይ መሆኑን እንደሚያስተምር ጥርጥር የለም። ኤፈሶን 1ን እና ሮሜ 9ን ያንብቡ (ስለ ዝርዝሩ አይጨነቁ)። የእግዚአብሔር ከሁሉ በላይ መሆን ለክርስቲያን መጽናኛ ነው። ምክንያቱም ምንም ነገር ከእግዚአብሔር ቁጥጥር ውጭ እንደማይፈጸምና ዕቅዱም አሸናፊ እንደሚሆን ያረጋግጥለታል። 

እነዚህ የእግዚአብሔር ዋና ዋና ባሕርያት ሲሆኑ፥ እውነተኛ አምላክም እርሱ ብቻ መሆኑን ያመለክታሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠው እግዚአብሔር፥ ሰው ሰአሳቡ የፈጠረው ወይም የመረጠው ሳይሆን፥ እሱነቱን በመግለጥ የታወቀው ራሱ ነው።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: