የሰው ተፈጥሮ፡- የሰው ባሕርይ

ሰው ምንድ ነው? የሚለው ጥያቄ ያለጥርጥር እጅግ መሠረታዊ የሆነ የፍልስፍናና የሥነ-መለኮት ተግባራዊ ጥያቄ ነው። ሰዎች መጀመሪያ ከየት መጣን? ለምንስ መጣን? መሄጃችንስ ወዴት ይሆናል? የሚሉና ሌሎችም ተመሳሳይ ጥያቄዎች ይሆናሉ። ፍልስፍና እዚህን ጥያቄዎች ለማጥናትና መልስ ለማግኘት በየዘመናቱ በተነሱ ፈላስፋዎቹ አካይነት የተለያዩ ሙከራዎችን አድርጓል። የብዙዎቹን ፍልስፍናዎች የአጠናን ዘዴና መልሶቻቸውን ስናይ፣ ሰዎች ለነዚህ ጥያቄዎች እርግጠኛ መልስ ለማግኘት አለመቻላቸውን እንረዳለን። ፍልስፍና ሰዎች ስለ ሰው ያሰቡትን ሊያስተምረን ሲከር፣ መጽሐፍ ቅዱስ ግን የሰውን አፈጣጠር በማስመልከት በሥልጣን የተደገፈና የተሟላ ትምህርት ይሰጠናል። ለሌሎች መሠረታዊ ጥያቄዎችም አጥጋቢ መልስ አለው። 

ሰው ፍጡር ነው 

አንድ ሰው፥ ስለ ሰው ዘር አመጣጥ ያለው አመለካከት ስለ ሰብአዊ ፍጡር የሚኖረውን እውቀትና አስተሳሰብ ይወስነዋል። ለምሳሌ ሰው በአዝጋሚ ለውጥ የመጣ ነው ብሎ ካመነ የኃጢአትን አስከፊነትና የአዳኝን አስፈላጊነት ሙሉ በመሉ ባይሰርዘው እንኳን እጅግ አቃሉ ይመለከተዋል። በሌላ በኩል ሰው በአምላክ የተፈጠረ ነው ብሎ የሚያምን ከሆነ ይህ ፅንሰ አሳብ ሰው ኅላፊነት አለበት የሚለውን የተያያዘ አሳብ ይይዛል። ሰው በእግዚአብሔር ከተጠረ፣ በፈጣሪና በፍጡሩ መካከል የበላይና የበታች ግንኙነት አለ ማለት ነው። ይህ ከሆነ እንግዲህ ሰው የራሱን ዕድል በራሱ የሚወስን አይሆንም፤ ወይም ለራሱ ተጠያቂ የሆነ የመጨረሻ ባለሥልጣንም ለመሆን አይችልም። ፍጡራን በፈጣሪያቸው ተገዢ መሆናቸውን ነው የሥነ-ፍጥረት ትምህርት የሚያመለክተው። ነገር ግን ሰው ከዝቅተኛ የሕይወት አካል በአዝጋሚ ለውጥ ከተገኘ፣ ፈጣሪ ሊጠየቅበት አይችልም ማለት ነው። 

የአዝጋሚ ለውጥ ትምህርት በየደረጃው በሰፊው የሚሰጥ ስለሆነ፣ በዚህ ክፍል፣ ስለዚህ ፅንሰ አሳብ ጥቂት አስተያየት መሰንዘሩ ብቻ በቂ ይሆናል። ይህ ፅንሰ አሳብ፥ ፍጥረት ሁሉ ከመጀመሪያይቱ “ሕዋስ” ቀስ በቀስ በተፈጥሮ ሂደት የተገኘ ነው ቢልም፣ የመጀመሪያዋ ሕዋስ ከየት እንደመጣች ግን አያመለክትም፡፡ በተወሰነ ደረጃ አንዳንድ ለውጦች መኖራቸውን ማንኛውም ክርሰቲያን አይክድም። ነገር ግን የአዝጋሚ ለውጥ ፅንሰ አሳብ ከዚህም የገዘፉ የለውጥ ትምህርቶችን ያካትታል። የቅርፅ፥ የዘርና፥ ሌሎች ውስጣዊና ረቂቅ ለውጦች ሁሉ ያለ ፈጣሪ ተሳትፎ ይፈጸማሉ ብሎ ያስተምራል። 

እንዴት ነው ይህ መሆን የሚችለው? እንደ አዝጋሚ ለውጥ እምነት አራማጆች [Evolutionists/ኢቮሉሽንስትስ] አባባል፥ ይህ የሚከናወነው በሚዩቴሽን [Mutation] ነው። [“ሚውቴሽን” ማለት በአንድ ድንገተኛ ሁኔታ የተነሳ በፍጥረታት ሕይወት መዋለድ ላይ የሚመጣ መላምታዊና ድንገታዊ ለውጥ ነው። በዚህም ረገድ ከወላጆቻቸው የተለ አዳዲስ ፍጡራን የሚፈጠሩ ሲሆን አዲስ የሆኑት ልጆችም እራሳቸውን እንጂ አያት ቅድመ አያቶቻቸውን የማይመስሉ ዘሮችን ይተካሉ።] ጠንካራ ጠንካራዎቹ በተፈጥሮ ምርጫ እየተጠበቁ በመቆየታቸው አዲስ የዘር ዓይነት ተገኘ እንደሚሉም ማስተዋል ይጠቅማል። በሂሳብ ጥበብ ቋንቋ ቀመሩ የሚከተለውን ይመስላል፡- ሚዩቴሽን + የተፈጥሮ ምርጫ + ጊዜ = አዝጋሚ ለውጥ። አንድ ጸሐፊ ሲጽፍ፡- «ሜንድል [Mende] በተባለ የለውጥ ተመራማሪ ለረዥም ጊዜ የታየው፣ የለውጥ ሙከራ የተመሠረተው ሕያው በሆኑት ባሕርያት ላይ ብቻ እንጂ፥ አዳዲስ ባሕርያት በመፍጠር እንዳልሆነ ነው። ፍጹም የሆኑ አዳዲስ አካላት ማግኘቱን ያረጋገጠ ሙከራም የለም። ይሁን እንጂ በአዝጋሚ ለውጥ ትምህርት የዋናዎቹን የለውጥ ደረጃዎች ክልል የሚያመለክተው በፍጥረታት ውስጥ የአዳዲስ ባሕርያት መከሰት ነው” ብሏል። 

ይህ መልስ ያላገኘ የአዝጋሚ ለውጥ እምነት አራማጆች መሠረታዊ ችግር ነው። እነዚህ አዳዲስ ነገሮች በምንም እኳኋን ይሁን በአዝጋሚ ለውጥ ተከስተዋል ብሎ ሜንድል ማመን አለበት። ለምሳሌ አንድ እውቅ የሰው ዘር አመጣጥ ተመራማሪ [Anthropologist/አንትሮፖሎጂስት] የጀርባ አጥንት ያላቸው ፍጥረታት፥ አጥንት ከሌላቸው በእድገት እንደተገኙ ሲጽፍ “ይህ በጣም ውስብስብ፥ ግልጥ ያልሆነና አሻሚ ጉዳይ ነው። ያም ሆነ ይህ አጥንት የሌላቸው እንስሳት በሆነ መንገድ የጀርባ አጥንት በማግኘት በኢቮሉሽን ተለውጠዋል” ብሏል፡፡ ይህ የግል እምነቱ ቢሆንም፥ የአስተሳሰብ ድክመት ይታይበታል። 

የቅሪት አካል ዘገባም ከዚህ በፊት ሆነዋል የሚባሉ ነገሮችን ያመለክታል። አዝጋሚ ለውጥ ትክክል ቢሆን ኖሮ ለውጡ ሳይቋረጥ ከቀላል ወደ ውስብስብ የተሸጋገረበትን ሂደት ሊያመለክት ይገባ ነበር። ነገር ግን በቢሊዮን ከሚቆጠሩት የታወቁ ቅሪት-አካላት ግኝቶችና ከፍተኛ የሕይወት ምድቦች መካከል ያለው ሽግግር ሆነ ተብሎ ተዘሏል! “አገናኞቹ ቀለበቶችም ከሚፈለጉበት ስፍራ ጠፍተዋል፤ ምናልባት ወደፊትም ብዙ አገናኝ ቀለበቶች ይጠፉ ይሆናል” በማለት አንድ ጸሐፊ ተናግረዋል። 

መጽሐፍ ቅዱስ የሰውን አፈጣጠር አስመልክቶ በዝርዝር ስላሰፈረው ጉዳይ የተለያዩ አስተሳሰቦች ቢኖሩም፥ እውነተኛዎቹ ማስረጃዎች ግን በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ ነው በግልጥ የሚገኙት። ዋና ዋናዎቹም ማስረጃዎች የሚከተሉት ናቸው። 

1. እግዚአብሔር ፈጣሪ ስለመሆኑ በዘፍጥረት ም. 1 ላይ ከአሥራ ሰባት ጊዜ በላይ ተገልጧል። እዚህ ላይ ትልቁ ጥያቄ የቱ እግዚአብሔር? የሚለው ነው። መልሱም ምዕራፉን የጻፈው ሰው፥ ሙሴ የሚያውቀው እግዚአብሔር፥ የሚል ይሆናል። ሙሴ በግሉ፥ ማንነቱን፥ ሕያውነቱን፥ ተአምራት አድራጊነቱን፥ የተረዳው አምላክ እግዚአብሔር ነው።  

2. በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ የሰፈረው ቃል እግዚአብሔር ፍጥረታትን የፈጠረበትን ሁኔታ ይነግረናል። በዘፍጥረት 1፡1፥ 21 እና 27 ላይ ያለው ግስ፥ ከባዶ ነገር እንደጀመረ ያስተምራል፤ ከዚያ በፊት ምንም አልነበረም። በዚህ ምዕራፍ እግዚአብሔር “ሠራ”፥ “ጠራ”፥ “አዘጋጀ”፥ “አበጀ “አደረገ”፥ “ወሰደ”፥ “ተከለ”…ወዘተ. የሚሉ ግሶች ይገኛሉ። በተጨማሪም ፍጥረታት “ቀን” “በቀን” ከመጀመሪያው (1፡1) እስከ መጨረሻው (2፡1) እንደተፈጠሩ ያመለክታል። 

3. የፍጥረታትን መፈጠሪያ ጊዜ በተመለከተም በዘፍጥረት የተጠቀሰ ማረጋገጫ አለ። የቀኖች ተራ በዘፍጥረት 1፡3 ይጀምራል። የነዚህን ቀኖች ትርጉም በተመለከተ አራት አመለካከቶች አሉ። በመጀመሪያ እነዚያ ቀኖች እግዚአብሔር ስለ አፈጣጠሩ ሁኔታ ለሙሴ የገለጠባቸው ናቸው የሚል ግንዛቤ አለ። እንግዲህ እነዚህ “የመግለጥ ቀናት” ናቸው እንጂ ከመፍጠር ጋር ግንኙነት የላቸውም። ሁለተኛ እነዚህ ቀናት ዘመናትን ነው የሚያመለክቱት (በብሉይ ኪዳን ቀን ረጅም ዘመንን ለማመልከት ተጽፏል፤ ኢዩ. 2፡31)። የምድር አፈጣጠር [Geologicalጂኦሎጂካል] ዘመናትም በቀላሉ በነዚህ ይካተታሉ። ሦስተኛዎቹ እውነተኛ ቀኖች ሲሆኑ (በ24 ሰዓት የሚለኩ) በመካከላቸው ሰፊ ክፍት ጊዜ አለ፥ ይህም የጂኦሎጂን ረጅም ዘመን ሊያጠቃልል ይችላል። አራተኛዎቹ የፀሐይ ቀኖች ይባላሉ። እነዚህ ክፍተት የሌላቸውና ተከታታይ ናቸው። ይህም አመለካከት “ምሽትና ማለዳ” በሚለው ሐረግ ይገለጣል። በብሉይ ኪዳን ውስጥ የቁጥር ቅጽል ከ“ቀን” ጋር ሲጠቀስ ሁልጊዜ የሚያመለክተው እውነተኛውን የፀሐይ ቀን ነው። በዚህ አመለካከት መሠረት መሬት የተፈጠረችው በቅርብ ጊዜ ነው። ሰውም እንደቀሩት ሦስት ግምቶች ሳይሆን፥ ከሌሎቹ ፍጥረታት በኋላ በቅርብ ጊዜ መፈጠሩን እንረዳለን። 

ዘፍጥረት 1፡1 ከሌላው የምዕራፉ ክፍሎች ጋር ያለው ግንኙነትም አከራካሪ ሆኗል። አንዳንዶች ይህ ለመንደርደሪያነት ብቻ የሚያገለግል አረፍተ ነገር ነው ሲሉ፥ የቀሩት ደግሞ ቀደም ሲል ስለነበረና በኋላ ባልታወቀ ምክንያት ድምጥማጡ ስለጠፋ ፍጡር ነው የሚያወራው ይላሉ። ለዚህም የሚያቀርቡት ማስረጃ ቁጥር 2 ላይ የተጠቀሰውን ቃል ነው። ይህ ድንገተኛ የጥፋት አደጋ የተከሰተው በሰይጣን ውድቀት ነው ይላሉ። ይህ ጉዳይ ከዚህ ጥናታችን ጋር ግንኙነት ያለው አይደለም። የውድቀትንም መነሻ መግለጡ ያዳግት ይሆናል። 

4. የጥፋት ውኃ ውጤት ያለጥርጥር ዛሬ የምናውቀውንም የዓለም ሁኔታ ለውጦታል፤ ስለዚህ ዓለም ከጥፋት ውኃ በፊት የነበራትን የተፈጥሮ ገጽታ ለመረዳት የጥፋት ውኃው ውጤት ሥእል በማንም አእምሮ ሊኖር ይገባል። ይህ የጥፋት ውኃ በእንድ አካባቢ የተወሰነ ቢሆን ኖሮ፥ በዚያው አካባቢ ብቻ ነበር ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው፤ መሬትን በሙሉ የሸፈነ ከነበረ ግን ውጤቱ እጅግ የተወሳሰበና ከግምታችን ላይ አስደንጋጭ ነበር ለማለት ይቻላል። እንዲህ ዓይነቱ ሁለንተናዊ ማጥለቅለቅ በጣም ብዙ ቅሪት-አካላትን ሊተው እንደሚችል ይገመታል። ይህ ደግሞ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚከናወን እንጂ፥ ጂኦሎጂያዊ ዘገባ እንደሚያመለክተው ረጅም ዓመታት የወሰደ ሂደት አይሆንም። ዓለም በሙሉ በውኃ ተጥለቅልቆ እንደነበር ማስረዳቱም ቀላል ነው። ስለ መርከቢቱም ግዝፈት በዘፍጥረት 7፡19-29 ላይ የተገለጠውን ልብ ይበሉ (ዘፍጥ. 6፡15)፤ መጥለቅለቁ የደረሰው በአንድ ክልል ብቻ ቢሆን ኖሮ፥ መርከብ አስፈላጊ ባልበረም። ይህን የጥፋት ውኃ በ2ኛ ጴጥሮስ 3፡3-7 ላይ ማጤን ጠቃሚ ነው። 

5. ፍጥረት ሁሉ በእግዚአብሔር ተፈጠረ እስከተባለ ድረስ፥ ከፍጥረታት አንዳንዶቹ ቀደም ሲል ረጅም ዕድሜ ያላቸው ይመስሉ እንደነበር መገንዘብ ያስፈልጋል። በዘፍጥረት ሂደት የአዳምና ሔዋን አፈጣጠር ሲታይ ጊዚ በሚጠይቅ የእድገት ሂደት ያለፉ ይምሰል እንጂ ገና ሲፈጠሩ ጎልማሳዎች ነበሩ። በኤደን የአትክልት ስፍራ ከነበሩት ዛፎች እንዳንዶቹ በጣም ትልልቆችና ረጅም ዕድሜ ያላቸው የሚመስሉ ነበሩ። ለምሳሌ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ የሠራው ወይን ጠጅ (ዮሐ. 2) ጣዕም የበሰለ ሲሆን፥ በእርግጥ ዝግጅቱ ጊዜ የፈጀ እንዳልነበረ እናውቃለን። 4000 እና 5000 ሰዎች የተመገቡት ምግብ ሁኔታም እንዲሁ ነው። ምግቡ ከደቂቃ በፊት የተሠራ ሲሆን፥ ሲበላ ግን ለብዙ ጊዜ የተሰናዳ መስሏል። እግዚአብሔር እነዚህን የመሳሰሉ ሁኔታዎች ስንት ጊዜ በፍጥረት ውስጥ እንዳከናወነ ባናውቅም፥ በአንዳንድ ሁኔታዎች ጎልተው መታየታቸው እውነት ነው። 

6. እንደ ታሪክ እውነታ ሁሉ የፍጥረት ታሪክም በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ተመዝግቦ እናገኛለን (ዘሌ. 20፡11፤ 1ኛ ዜና 1፡1፤ መዝ. 8፡3-6፤ ማቴ. 19፡4-5፤ ማር. 10፡6-7፤ ሉቃስ 3፡38፤ ሮሜ 5፡12-21፤ 1ኛ ቆሮ. 11፡9፤ 15፡22፣ 45፤ 2ኛ ቆሮ. 11፡3፤ 1ኛ ጢሞ. 2: 13-14ና ይሁዳ 14ን ይመልከቱ)። አንድ ሰው በአንዳንድ ምክንያቶች ሳቢያ በዘፍጥረት 1-11 ከተጻፈው እውነተኛ ታሪክ ለመሸሽ ቢሞክር እንኳን በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፉትን የፍጥረት ትምህርቶች (በተለይ የአዳምን ታሪክ ሊያስወግድ አይችልም። ብዙዎች በዘፍጥረት ከ1-11 የሰፈረውን ታሪክ የሰው ምናባዊ ገለጣ ነው ይላሉ። እንዲያ ከሆነ ሌሎችንስ ክፍሎች እንዴት ያብራሯቸው ይሆን? 

ሰው ባለ ብዙ ገጽ ፍጡር ነው 

በመሠረቱ ሰው፥ ቁሳዊ (አካል) እና ቁሳዊ ያልሆነ (መንፈስ ወይም ነፍስ ያለው) ፍጡር ነው። ሁለቱም አሠራሮች የእግዚአብሔር ቀጥተኛ የፈጣሪነት ሥራ ውጤቶች ናቸው (ዘፍጥ. 2፡7)። እግዚአብሔር ሰውን በመልኩና በምሳሌው ፈጠረ (ዘፍጥ. 1፡26፥ 5፡1)። ሰውን እጅግ ልዩ የሚያደርገው እግዚአብሔርን መምሰሉ ሲሆን፥ በኃጢአት ከወደቀ በኋላም ቢሆን ይህ አምሳያነቱ ሙሉ በሙሉ አልጠፋም። (1ኛ ቆሮ. 11፡7 እና ያዕ. 3፡9 ላይ የሰፈሩት ምክሮቹ ሰው የእግዚአብሔር አምሳያ መሆኑን ያረጋግጣሉ።) ያ አምሳያነት ምንድነው? 

ለዚህ ጥያቄ፥ ለዘመናት የተለያዩ መልሶች ሲሰጡ ኖረዋል። ከነዚህም መልሶች ውስጥ የሰው የእግዚአብሔር አምሳያነቱ ከተፈጥሯዊ አካሉ ነው፥ ወይም ለሥነ-ምግባርና ለመንፈሳዊ ጉዳይ ባለው ችሎታ ነው (ችሎታው አሁንም ይኖረው ወይም ፈጽሞ ያጣው ይሆናል) የሚሉት ይገኙበታል። ምናልባት እውነቱ የብዙ ነገሮች ስብስብ በመሆኑ ይሆን ይሆናል፡፡ ሰው የእግዚአብሐር አምሳል በመሆኑ ምድርን የመግዛት ሥልጣንና ሥነ-ምግባር የማስከበር ኃላፊነት ተሰጥቶታል፤ በኋላም ይህን ኀላፊነት በኃጢአት የተነሳ ተነጥቋል። ከዓለም ገዥነቱ ተሽሯል፥ በሥነ-ምግባሩም ተበላሽቷል። ያም ሆኖ ከፍጥረታት ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ እርሱ ብቻ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል። 

የሰው አካል (ቁሳዊው ክፍሉ) በጣም ብዙ ሥራ እንደሚያከናውን ግልጥ ነው። ማየት እንደ መስማት እይደለም። የስሜት ሥሮች አሠራር የተለያየና ራሱን የቻለ ቢሆንም፥ ከማየት፥ ከመስማትና ከሌሎችም ስሜቶች ጋር የሚያያዝበት መንገድ ይኖራል። 

ቁሳዊ ያልሆነውንም የሰው ክፍል በዚህ ሁኔታ ማየቱ ምናልባት አስፈላጊ ይሆናል። ነፍስ፥ መንፈሰ፥ ልብ፥ እእምሮ፥ ፈቃድና ሕሊና ቁሳዊ ያልሆኑ የሰው አካል ክፍሎች ሲሆኑ፥ በመካከላቸው ጥርት ያለ ልዩነት መፍጠሩ ያስቸግራል። ሰውን አካል፥ ነፍስና መንፈስ ነው ማለት በጣም ማቃለል ይመስላል። ምክንያቱም ነፍስና መንፈስ የሰውን ቁሳዊ ያልሆነ ክፍል በሙሉ ካለመግለጣቸውም በላይ ልዩነታቸው ሁልጊዜ ጉልህ ባለመሆን ነው። ለምሳሌ እግዚአብሔርን በፍጹም ነፍስህ ውደድ ተብሏል (ማቴ. 22፡37)። እንዲሁም “ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት” የሚል ሌላ ጥቅስ እናገኛለን (1ኛ ጴጥ. 2፡11)። መንፈስ ጌታን ሊያከብር ይችላል (ሉቃስ 1፡46-47)። እንዲሁም መንፈስ እንደ ሥጋ እንደሚረክስ (2ኛ ቆሮ. 3፡) ተጽፏል። በአንዳንድ ሁኔታዎች መንፈስ የሰውን ከፍተኛ አካል ያመላክታል (ሰዎች ሁሉ፥ ያልዳኑትንም ጨምሮ መንፈስ አላቸው፥ 1ኛ ቆሮ, 2፡11)። 

“ልብ” (ደም የሚረጨውን የውስጥ አካል ማለት አይደለም) እንዲሁ የሰውን ቁሳዊ ያልሆነ ክፍል ሁሉ የሚያጠቃልል ይመስላል። የሰው ሕይወት የእውቀት ማኅደር እንደሆነም ተገልጧል (ማቴ. 15፡19-20)፥ ስሜታዊውን ሕይወት (መዝ. 37፡4፤ ሮሜ 9፡2)፥ ፈቃዳዊውን ሕይወት (ዘዳግ. 7፡23፥ ዕብ. 4፡7)፥ መንፈሳዊውን ሕይወት (ሮሜ 10፡9-10፤ ኤፌ. 3፡17) ሁሉ ያጠቃልላል። 

ሕሊና በሰው ውድቀት የተጎዳ አካል ቢሆንም፥ አማኞችንም ሆነ የማያምኑትን ሰዎች ሊመራ የሚችል ውስጣዊ ምስክር ነው። ሮሜ 2፡15 እና 1ኛ ጢሞ. 4፡2ን በመመልከት በማያምኑት ሰዎች ውስጥ የሚታየውን ሕሊና ያስተውሉ። አማኙን በተመለከተ ግን ሕሊናው ከመንግሥት (ሮሜ 13፡5)፥ ከአሠሪው (1ኛ ጴጥ. 2፡19)፥ ከወንድሞቹ (1ኛ ቆሮ. 3፡7፥ 10፥ 12) ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖረው ይመራዋል። 

በጌታ ድነት (ደኅንነት) ያላገኘ ሰው አእምሮ፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ መልካም ያልሆነ ስም ተሰጥቶታል። የማይረባ (ሮሜ 1፡28)፣ ከንቱ (ኤፈ. 4፡17)፥ የረከሰ (ቲቶ 1፡15)፣ የጨለመ (ኤፈ. 4፡18)፥ በሰይጣን የታወረ (2ኛ ቆሮ. 4፡4) ተብሏል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ክርስቶስን አዳኝ አድርጎ ሲቀበል፥ ሕይወቱንም ለጌታ ሲሰጥቶ የአእምሮ መታደስን ያገኛል (ሮሜ 12፡2)። ከዚያ በኋላ እግዚአብሔርን መውደድ እንችላለን (ማቴ. 22፡37)፤ የጌታን ፈቃድ እንረዳለን (ኤፌ. 5፡17)፤ በማስተዋል እናመሰግነዋለን (1ኛ ቆሮ. 14፡15)። 

የሰው ፈቃድ ሌላው በጣም ጠቃሚ የሆነና ቁሳዊ ያልሆነው የተፈጥሮ ክፍል ነው። ያልዳነ ሰው ፈቃድ መልካም ውጤት ይኖረው ይሆናል (ሐዋ. 27፡43)፤ የአማኞችም እንዲሁ ሊሆን ይችላል (ቲቶ 3፡8)፤ የዚህ ተቃራኒም ይሆን ይሆናል (1ኛ ጢሞ. 6፡9፤ ያዕ. 4፡4)። 

እነዚህ ሁሉ ማብራሪያዎች፡ክርስቲያን ሁለት የተለያዩ ችሎታዎች ወይም ባሕርያት እንዳሉት ያመለክታሉ። ከመዳኑ በፊት ችሉታውን የሚጠቀምበት ራሱን ለማገልገልና ለማስደሰት ነው። ይህ አሮጌ፥ ወይም የኃጢአት ባሕርይ ክፉ ለማድረግ ከመቻል አንጻር ብቻ አይደለም የሚተረጐመው። ከዚያ የላቀ ሊሆን ይችላል። ከአሮጌው ባሕርይ የመነጩ፥ ግን ያልከፉ ነገሮች አሉ። የአሮጌው ባሕርይ ዋና መለያ በድርጊቱ ሁሉ ራሱን ማግለል ነው። በዳግም መወለድ ጊዜ እግዚአብሔርን ለማገልገል አዲስ ኃይል ወይም ባሕርይ ተሰጥቶናል (ሮሜ 6፡18-20፤ 2ኛ ጴጥ. 1፡4፤ ኤፌ. 4፡22-25ን ያጥኑ)። 

አንድ ሰው ያሉት የሁለት ተቃራኒ ባሕርያት ግንኙነት በዚህ ወጣት ክርስቲያን ተገልጧል፡- 

በልቤ ውስጥ ሁለት ትላልቅ ውሻዎች አሉ። አንደኛው ጥሩ ውሻ ነው፤ ይረዳኛል፣ እንክብካቤ ያደርግልኛል፣ ይጠብቀኛል። ሌላው ውሻ መጥፎና ከሃዲ ሲሆን ሁልጊዜ ችግር ውስጥ የሚጥለኝና የሚያሳዝነኝም ነው። እነዚህ ውሻዎች እርስ በእርሳቸው ይጠላላሉ። ሁሌም እየተጣሉ የበላይነትን ለማግኘት ይሞክራሉ። ነገር ግን ማናቸውም ቢሆኑ በመግደል ወይም አንዱ ሌላውን በማባረር ለማሸነፍ አይችሉም። ጥሩው ውሻ መጥፎውን አባርሮት ሰላም ለማግኘት ብችል እንዴት ደስ ባለኝ ነበር! ሕይወቴ በዚህ ቋሚ የሆነ ጦርነት በመሞላቱ የተረገምኩ ሆኛለሁ። 

አንድ ቀን መጋቢዩን ስለዚህ ጉዳይ ጠየቅሁትና በጣም ጥሩ ምክር ሰጠኝ፡- “አእምሮህ ውስጥ የምትጨምረው ነገር ሁሉ ለአንደኛው ውሻ የሚሆን ምግብ ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ያለማቋረጥ ብታነብ፣ መልካም ዘር ብታስብ እና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ብትሻ ጥሩውን ውሻ መገብክ ማለት ነው። ነገር ግን ስለ ክፉ ነገሮችና ስለ ራስህ ብቻ ብታስብ  ወይም ሰዎችን ለራስህ ጥቅም ለመጠጋት ብትሞክር የምትመግበው መጥፎውን ይሆናል” አለኝ። 

ቀጥሎም “አብልጠህ የመገብከው ውሻ ይበልጥ ጠንካራ ይሆናል፤ ድልም ያገኛል” አለ።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

One thought on “የሰው ተፈጥሮ፡- የሰው ባሕርይ

  1. Thank you so much for this preparation and sharing wonderful information. May God bless you in all your ministry!

    Like

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.