አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን

አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምንድን ናት? 

ዛሬ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምን ምን ማሟላት አለባት? በሚለው ጥያቄ ላይ ሰፊ ውይይት አለ። ቤተ ክርስቲያን ሁለት ወይም ሦስት አማኞች በኢየሱስ ስም የሚያደርጉት ስብሰባ ነው? ምን ያህል ድርጅት ያስፈልጋታል? ለቤተ ክርስቲያን አባልነት ጥምቀት አስፈላጊ ነው? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ይነሱ ይሆናል። አዲስ ኪዳን ስለ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚያስረዳው ግልጥ ማብራሪያ የሌለ መሆኑ ያሳዝናል። የጉባኤው እንቅስቃሴ እንዴት መካሄድ አለበት? ለሚለው ጥያቄ ነው መጽሐፉ መልስ የሚሰጠው። እኛም ከዚህ መንደርደሪያ አሳብ በመነሳት ስለ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ምንነት የሚከተለውን ማብራሪያ ለመስጠት ሞክረናል። በአዲስ ኪዳን እንደምናየው አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን የተቀበሉ አማኞች ጉባኤ ሲሆን አባላቱም የተጠመቁና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጁ መሆን አለባቸው። ማለት፡- 1. የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባል የሚሆነው ማመኑን የገለጠ ሰው ብቻ ነው፤ 2. አዲስ ኪዳን ያልተጠመቀ ሰው የቤተ ክርስቲያን አባል ስለመሆኑ የሚገልጠው ነገር የለም፤ 3. ቤተ ክርስቲያናት በተቻለ መጠን በፍጥነት ነበር የሚደራጁት (ሐዋ. 14፡23)። ሰለዚህ በአሁኑ ጊዜም ቢሆን ያልተደራጀ የአማኞች ኅብረት፥ ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ሊጠራ አይችልም፤ 4. ቤተ ክርስቲያን ዓላማ አላት። ይህም በተለያየ መንገድ የሚገለጠውን የእግዚአብሔር ፈቃድ መፈጸም ይሆናል (የተለያዩ ትእዛዞችንና ሥርዓቶችን መፈጸም፥ በየትኛውም የዕድሜ ክልል፥ በየትኛውም የዓለም ክፍል ላሉ ሰዎች አገልግሎት መስጠት ወዘተ.)። 

ይህ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ትርጉም በወጉ ቢገለጥም የሁለትና ሦስት ሰዎች ለኅብረት መሰብሰብ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አያሰኘውም። ምክንያቱም ይህ ዓይነቱ ጉባኤ፥ ቢያንስ በአካባቢው ላሉና በየዕድሜው ክልል የሚገኙ ሰዎችን ለማገልገል የተዘጋጀ አይሆንም። እንዲሁም የክርስቲያን ትምህርት ቤት፥ ወይም ከቤተ ክርስቲያን ውጭ የሆነ ክርስቲያናዊ ድርጅት ቤተ ክርስቲያን ሊሆን አይችልም። 

እርግጥ ይህ መግለጫ የሚለዋውጥበት ሁኔታ ይኖራል። አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የግድ ለሷ ተብሎ በተሠራ ሕንፃ ውስጥ ትሰብሰብ አይልም። ምን ዓይነት ወይም ስንት ስብስሳዎች መካሄድ እንዳለባቸው አያመለክትም። እንዲሁም ስለ ጥምቀት ዓይነትና ስለ መሪዎች አመራረጥ (ወደፊት በስፋት እናየዋለን) አይወሰንም። የመግለጫው ዋና ጥረት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ከሌሎች ቡድኖች፥ ከዚያም አልፎ ከቤተ ክርስቲያናት ጋር ከተዛመዱ ድርጅቶች የምትለይበትን ሁኔታ ለማመልከት ነው። 

እነማን ናቸው የቤተክርስቲያን መሪዎች? 

ቤተ ክርስቲያን አመራር ይኖራት ዘንድ መለኮታዊ ትእዛዝ ነው (ዕብ. 13፡7፥ 17)። መደራጀት ሥጋዊ ድርጊት፥ ወይም ስሕተት አይደለም። ሰዎች ግን ለዚህ ጉዳይ ከመጠን ያለፈ ትኩረት ይሰጡታል። አንዳንዶች ድርጅቱ እጅግ ሳይሰፋ አነስተኛ ቢሆን ይመረጣል ይላሉ፥ በተግባር ሲታይ ግን የበቂ ድርጅት አለመኖር የታሰበውን ሥራ ያደናቅፋል። በሌላ አቅጣጫ ስናየው ደግሞ አንዳንድ ቤተ ክርስቲያናት እጅግ ከመጠናከራቸው የተነሳ የቤተ ክርስቲያኑ መሪ (እግዚአብሔር) የሚሰጠው ምክርም ሆን ውሳኔ ተቀባይነት የሚያጣበት ጊዜ ይኖራል። ያም ሆነ ይህ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚያስፈልጓት ስለመሆኑ በአዲስ ኪዳን በየደረጃው ተገልጧል። 

1.ሽማግሌዎች። ያለጥርጥር ሽማግሌዎች የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ዋና መሪዎች ነበሩ። ብዙዎች ባይስማሙበት እንኳን፥ ሽማግሌዎችና ጳጳሳት በቤተ ክርስቲያን እኩል ሥልጣን እንዳላቸው ይገመታል። ሽማግሌ የሚለው ቃል ሥልጣንን ሲያመለክት፥ ጳጳስ የሚለው ደግሞ ሥራ አስፈጻሚነትን፥ አጠቃላይ ተቆጣጣሪነትንና ከበላይ ሆኖ መመልከትን ይገልጣል። ቢያንስ ቢያንስ በኤፈሶን ቤተ ክርስቲያን የሽማግሌና የጳጳስ ሥራ ተመሳሳይ ነበር (ሐዋ. 20፡17፥ 28)። በመሆኑም ሽማግሌዎች ከአጠቃላይ ሥራቸው በተጨማሪ በመሪነትም አገልግለዋል (1ኛ ጢሞ. 5፡17)፤ እውነትን ጠብቀዋል፥ አስተምረዋል (ቲቶ 1፡9)፣ የገንዘብ ገቢና ወጪም ተቆጣጥረዋል (ሐዋ. 11፡30)። በእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል ሽማግሌዎች ነበሩ የሚለው ጥያቄ አከራካሪ ሆኗል። ምንም እንኳን በግልጥ እንደሚታየው ቤተ ክርስቲያናት በነበሩባቸው ከተሞች ብዙ ሽማግሌዎች ነበሩ (ሐዋ. 14፡23፤ ፊልጵ. 1፡1)። ነገር ግን በየመኖሪያ ቤቱ በሚካሄዱት ስብሰባዎች ላይ ብዙ ሽግሌዎች፥ ወይም አንድ ሽማግሌ ብቻ እንደነበር የታወቀ ነገር የለም። በ1ኛ ጢሞቴዎስ 3 ጳጳስ የሚለው ቃል (በነጠላ) ከቁ. 1-7 ተጠቅሷል፤ ሰለ ዲያቆናት ግን (በብዙ) ከቁ. 8-13 ተገልጧል። ሽማግሌዎች ለተለየ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በተለየ መንገድ ይመረጡ እንደነበር ደግሞ ከሚከተለው ጥቅስ ለመረዳት እንችላለን (1ኛ ጢሞ. 4፡14፤ ቲቶ 1፡5)። 

የሽማግሌዎች መምረጫ ስለነበሩት መመዘኛ ነጥቦች በ1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡1-7 እና ቲቶ 1፡5-9 ተብራርቷል። የመጀመሪያውን ጥቅስ እንደሚከተለው ዘርዝሮታል፡- የማይነቀፍ (ለወቀሳ ያልተጋለጠ) የአንዲት ሚስት ባል፥ (ይህ ማለት አንዲት ሚስት ብቻ ያገባ ማለት ሲሆን ቃሉም በግሪክ 1ኛ ጢሞቴዎስ 5፡9 ከተጠቀሰው ጋር አንድ ነው፤ ብዙ ሚስት ማግባት በግሪኮችና በሮማውያኑ ዘንድ የሚታወቅ አልነበረም፤ ወይም ከተፋቱ በኋላ የሚያገቡትንም የሚከለክል ሊሆን ይችላል)፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሠራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብ የማይወድ፥ ቤቱን በመልካም የሚያስተዳድር (የቤቱን ጥቂት ሰዎች በመልካም ሁኔታ ማስተዳደሩ፥ ቤተ ክርስቲያንን ለማስተዳደር የሚችል መሆኑን ያመለክታል)፥ አዲስ ክርስቲያን ያልሆነ (የበሰለ)፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ መልካም ምስክርነት ያለው። በቲቶ መልእክት ውስጥ ያለው ክፍል ደግሞ በዚህ ላይ በመጨመር፥ የማይኮራ፥ የማይቆጣ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ (ሰዎችንም ሁኔታዎችንም)፥ ጻድቅና ቅዱስ (ንጹሕ) የሆነ የሚሉትን ያጠቃልላል። 

የዚህ ሁሉ ዝርዝር ገለጣ አስፈላጊነት ቤተ ክርስቲያን መመራት የሚኖርባት ብቃት ባላቸው ሰዎች መሆኑን ለማስገንዘብና መመዘኛውን ከማያሟሉ ብዙ ሰዎች ይልቅ፥ ብቃት ባላቸው ጥቂቶች መመራት እንደሚሻላት ለመጠቆም ነው። 

2. ከሽማግሌዎች በታች ያሉት ደግም ዲያቆናት ነበሩ። ዲያቆን የሚለው ቃል አገልጋይ ማለት ነው። ምንም እንኳን ክርስቲያኖች በሙሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ መሆን ቢችሉም፥ ዲያቆናት የታወቀ ልዩ አገልግሎት አላቸው። የሽማግሌዎች ረዳት ሲሆኑ (ሐዋ. 6፡1-6) በግልጥ የታወቀ የሥራ ድርሻም ነበራቸው (ፊልጵ. 1፡1)። የዲያቆናት ምርጫ መመዘኛ እንደ ሽማግሌዎች በጣም ዝርዝር ባይሆንም፥ አንዳንድ ተመሳሳይ መመዘኛዎችን ይጨምራል። በተለይ “በቃላቸው የሚታመኑ” (1ኛ ጢሞ. 3፡8) የሚል ቃል ታክሎበታል። ይህ የሚያስገነዝበን፣ ምናልባት ዲያቆናት ከምእመናን ጋር በየዕለቱ ፊት ለፊት የሚገናኙና ቤት ለቤት እየዞሩ እርዳታ የሚያደርጉ፥ የታመሙትን የሚጠይቁ በመሆናቸው፥ በዚህ አጋጣሚ ለአንድ ሰው አንድ ነገር፥ ለሌላው ሌላ እንዳይናገሩ ለማስጠንቀቅ ሲባል የተደረገ ይሆናል። በቲቶ መልእክት ዲያቆናት አለመጠቀሳቸው አሰፈላጊነታቸው ውሱን ነው ማለት አይደለም። ምናልባት የቀርጤስ ቤተ ክርስቲያን ትንሽ ከመሆኗ የተነሳ ዲያቆናት ሳያስፈልጓት፥ ወይም ዲያቆናት ኖረዋት ሽማግሌዎች ሳያስፈልጓት ቀርቶ ይሆናል። 

3. ሴቶች ዲያቆናት ሊሆኑ ይችላሉን? በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሁለት ጥቅሶች ብቻ ናቸው ሴት ዲያቆናት እንደነበሩ የሚያስረዱ (በሮሜ 16፡2)። ፌበን “አገልጋይ” ተብላ ተጠርታለች (ቃሉ “ዲያቆን” ማለት ነው)። ጥያቄው፣ የቃሉ አጠቃቀም የሚያስረዳው ይህች ሴት በድቁና የታወቀች (የሴት ዲያቆን) እንደነበረች ወይስ ተራ አገልጋይ? የሚል ይሆናል። ምናልባት (እንደ 1ኛ ቆሮንቶስ 16፡15 ገለጣ ከሆነ) አገልጋይ ብሎ መቀበሉ ይሻል ይሆናል። ሌላው ጥቅስ 1ኛ ጢሞ. 3፡11 ሲሆን እዚያም የተወሰኑ ሴቶች ስም ተጠቅሷል። እዚህም ላይ የሚነሳው ጥያቄ፥ እነዚህ ሴቶች የዲያቆናት ሚስቶች ናቸው? ወይስ ሴት ዲያቆናት? የሚል ይሆናል (ቃሉ በግሪክ “ሴቶች” ማለት ነው)። ሴት ዲያቆናት ቢሆኑ ኖሮ ስለ ዲያቆናት በሚገልጠው አንቀጽ መካከል ከሚሆን ይልቅ፥ ከቁጥር 13 በኋላ ሰለ ዲያቆናት የተሰጠው ማብራሪያ እንዳለቀ መጠቀስ ይኖርባቸው ነበር። ስለዚህ ምናልባት የዲያቆናት ሚስቶች ይሆናሉ የሚለውን አሳብ ያጠናክረዋል። በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን፥ በግልጥ የታወቁ የሴት ዲያቆናት መኖራቸው በጣም አጠራጣሪ ነው። 

4. በአዲስ ኪዳን ንብረት ጠባቂ የሚል የሥራ ድርሻ አልነበረም። ዛሬ ግን በማኅበሩ ስም የቤተ ክርስቲያንን ንብረት የሚጠብቁ ሰዎች አስፈላጊ ሆነዋል። የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያናት ስብሰባ የሚያደርጉት በየቤቱ ስለነበር ንብረት ጠባቂ አላሻቸውም። ዛሬ ግን ቤተ ክርስቲያናት የራሳቸው ሕንፃ ያላቸው ስለሆነ ንብረታቸው በግለሰቦች ሊያዝ አይገባም። በነገራችን ላይ በ2ኛ ቆሮንቶስ 8፡17-24 ገንዘብ ያዦችና የንብረት ባለ አደራዎች መኖራቸው ተገልጧል። እርግጥ ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ አቋም ባልነበራት በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የነዚህ ሰዎች አስፈላጊነት በአሁኑ ዘመን ካለው ሁኔታ እጅግ ይለያል፡፡

እስካሁን ስለ ቤተ ክርስቲያን አመራርና መሪዎቿ ተነጋግረናል። ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የተከናወነው በእነርሱ ብቻ እንዳልሆነ ማስታወስ ጠቃሚ ነው። እነርሱ ይመራሉ፥ ያስተዳድራሉ፥ ይጠብቃሉ፥ ያገለግላሉ። ነገር ግን ስጦታ ያላቸው ሌሎች ሰዎችም በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሊካፈሉ ይችሉ ነበር። ሽማግሌ ወይም ዲያቆን ያልሆኑ፥ ነገር ግን የማስረዳት ስጦታ ያላቸው ሰዎች ሊያስተምሩ ይችላሉ። እርዳታ፥ ምሕረት ማድረግ ገንዘብና ሌሎች ስጦታዎች ማበርከት፥ በማኅበረ ምእመናኑ ውስጥ የአመራር ቦታ በያዙት ሰዎች ብቻ የሚሰሩ አልነበሩም፡፡ መሪዎችም በመንፈሳዊ ስጦታዎቻቸው በመጠቀም በአገልግሎቱ ይሳተፉ ነበር። 

እዚህ ላይ በመደጋገም የሚነሳ አንድ ጥያቄ ይገጥመናል፡- ለመሆኑ የአዲስ ኪዳንን አመራር ዘይቤ ለመከተል ምን ያህል ግዴታ አለብን? የሚል። በግልጥ እንደሚታወቀው ብዙ ሰዎች በአመራሩ ትርጉምና አወቃቀር እንኳን አይስማሙም። ይህ ጉዳይ ለዘመናት ያከራከረ ሲሆን፥ አሁንም ቢሆን መልስ ይገኝለታል ማለት አይቻልም። ምናልባት የሚከተለው አሠራር የተሻለ ይሆን ይሆን? በመጀመሪያ በተቻለ መጠን የአዲሰ ኪዳንን አሠራር ፈለግ ይከተሉ፤ ከዚያም አሠራሩን ተከትለው ከግብ ለመድረስ ይጣሩ። ከአዲስ ኪዳን የአሠራር ስልት የሚያርቅ በቂ ምክንያት የለም፡፡ ይህም ሲባል እያንዳንዱን ዝርዝር መመሪያ በተግባር ማዋሉ ያስቸግር ይሆናል። 

ቤተ ክርስቲያን እንዴት ትተዳደር? 

ልክ የመሪዎቹ የሥራ ሁኔታ ጥያቄ እንደማስነሳቱ ሁሉ፥ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጥያቄም ያከራክራል። እንዲህ ባለው ትንሽ መጽሐፍ ሊገለጥ የሚችል መልካም ነገር፥ ዛሬ በተግባር ላይ ያሉ የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ዘዴዎችን መጥቀስ ብቻ ነው። 

የሥልጣን ተዋረድ ያለው አስተዳደር። በዚህ ዘዴ (የሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፥ ሉተራውያንና መቶዲስት [Methoodist] ቤተ ክርስቲያናት) በተለያየ መንገድ ይጠቀሙበታል። ጳጳሳት ቤተ ክርስቲያን ያስተዳድራሉ (ሽማግሌና ዲያቆናት ቢኖሩም)። ጳጳሳቱ ብቻ ናቸው ቅስናና ድቁና የመሳሰሉ ማዕረጎችን የመስጠት ሥልጣን ያላቸው። ይህ ዓይነት አስተዳደር በአዲስ ኪዳን ባይገኝም፥ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው ተግባር ላይ የዋለው። 

ፌደራላዊ አስተዳደር፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ አስተዳደር ቤተ ክርስቲያን (በ“ፕሬስቢቲሪያን” [Presbyterian] እና በአንዳንድ ነጻ ቤተ ክርስቲያናት እንደሚታየው) በማኅበረ ምእመናኑና ሥልጣን በተሰጣቸው ሽማግሌዎች ትተዳዳራለች። ይህ ሰዎች በቀጥታ ሳይሆን በወኪሎቻቸው አማካይነት (በሽማግሌዎች) የሚገዙበት የሕዝብ ውክልና አስተዳደር ነው። ብዙ ጊዜ በሚያስተዳድሩ ሽማግሌዎች (የሚያስተዳድሩ፥ ነገር ግን በማይሰብኩ፥ ሥርዓተ ቅዳሴ በማይፈጽሙ) እና በሚያስተምሩ ሽማግሌዎች (በሚሰብኩትና ሥርዓተ ቅዳሴ በሚፈጽሙ) መካከል ልዩነት አለ (1ኛ ጢሞ. 5፡17)። 

የፈዴራላዊ አስተዳደርን የሚደግፉ ሰዎች እንደ ድጋፍ የሚያቀርቡት ነጥብ፥ ሽማግሌዎች በሐዋርያት መመረጣቸውን (ሐዋ 14፡23፤ ቲቶ 1፡5) ከሐዋርያት ሌላ አስተዳዳሪዎች እንደነበሩ (ዕብ. 13፡7፥ 17)፣ እነሱም የሥነ-ሥርዓት መመሪያ መስጠታቸውን (1ኛ ቆሮ 5፤ 1ኛ ጢሞ. 5፡20) ያካትታል። ሹመትን በተመለከተ የቀረቡት ጥቅሶችም ይህንኑ ፊዴራላዊ ዘዴ ይከተሉ እንደነበር ያመለክታል። 

ማሕበረ-ምእመናዊ አስተዳደር [Congregational/ኮንግሪጌሽናል]። ይህን አስተዳደራዊ ዘይቤ በሚከተሉ ወገኖች እምነት ማንም ሰው ወይም ቡድን በአንድ አጥቢያ ኅብረት ላይ ኃይልና ሥልጣን ሊኖረው አይገባም፤ አስተዳደሩ በአባላቱ እጅ መሆን አለበት የሚል ነው። “ባፕቲስት” [Baptist]፣ “ኢቫንጀሊካል ፍሪ” [Evangelical Free]፥ “ዲሳይፕልስ” [Disciples] እና አንዳንድ ነጻ አብያተ ክርስቲያናት ይህን አሠራር ይከተላሉ። የእንዲህ ዓይነቱ ቤተ ክርስቲያናት መሪዎች፥ መጋቢዎችና ዲያቆናት ናቸው። መጋቢው (በእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን አንድ ሰው ነው) የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶችን የሚያስፈጽም ሲሆን፥ እንደ አዲስ ኪዳን ሽማግሌ ይመለከቱታል። ዲያቆናት (የብዙ ናቸው) የቤተ ክርስቲያኒቱን ደኅንነት በበላይነት ይመራሉ። አንዳንድ ማኅበሮች ዲያቆናትን ሲሾሙም፥ ሥርዓቶችን እንዲፈጽሙ ግን አይፈቅዱላቸውም። መጋቢውና ዲያቆናቱ በማኅበረ ምእመናኑ በድምጽ ብልጫ የሚመረጡ ሲሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን ደኅንነት በተመለከተ ውሳኔ የሚሰጠው በማኅበረም እመናኑ ነው። የውሳኔው እስፈጻሚዎች ግን መሪዎቹ ናቸው። 

ይህን የአስተዳደር ዘይቤ የሚከተሉ ወገኖች ስለአሠራራቸው ከሚያቀርቧቸው ጥቅሶች መካከል፡- 1. ሰለ መላው ቤተ ክርስቲያን አባላት ኀላፊነት የሚናገሩ (1ኛ ቆሮ. 1፡10፤ ፊልጵ. 1፡27)፥ 2. የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የሚፈጽሙትን አገልጋዮች የሚመርጡት መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ፥ አባላት ጭምር መሆናቸውን (ማቴ. 28፡19-20፤ 1ኛ ቆሮ. 11፡2፥ 20) 3. አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን አባላት መሪዎቻቸውን በመምረጥ መሳተፍን (ሐዋ. 6፡3፥ 5፤ 15፡29 30፤ 2ኛ ቆሮ. 8፡19) እና 4. ሥነ-ሥርዓትን በተመለከተ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት በሙሉ መሳተፋቸውን የሚያመለክቱት ይገኙበታል (ማቴ. 18፡17፤ 1ኛ ቆሮ. 51 2ኛ ተሰ. 3፡14) ። 

በዚህ ማኅበረ-ምእመናናዊ አስተዳደር፥ መጋቢ ብቸኛው የቤተ ክርስቲያኒቷ ሽማግሌ ይሆናል። በራእይ 2 እና 3 የተጠቀሱት ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት አንድ አንድ መሪ እንደነበራቸው መጠቀሱ (“መልአክ” ተብሎ የተጠራው ሰብአዊ መሪን ለማመልከት ነው) ይህን አሠራር የሚደግፍ እውነት ነው። እንዲሁም በ1ኛ ጢሞቴዎስ 3 በመጀመሪያው ክፍል አንድ ኤጲስ ቆጶስ (ሽማግሌ) ብቻ የተጠቀሰ ሲሆን የሚቀጥለው ክፍል (ቁ. 3-13) ደግሞ ዲያቆናትን ያመለከታል። ይህ የሚያስገነዝበው በአንድ ቤተ ክርስቲያን አንድ ሽማግሌና ብዙ ዲያቆናት መኖራቸውን ይመስላል። ነገር ግን በፊልጵዮስ 1፡1 ውስጥ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት በብዙ ቁጥር መጠቀሳቸው፥ በአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ሊኖሩ እንደሚችሉ ያስረዳል። ይህም ፌዴራላዊ አስተዳደርን ይደግፋል የሚሉ ክፍሎች አሉ። 

ብሔራዊ ቤተ ክርስቲያን። በአንዳንድ አገሮች፥ በተለይ አውሮፓ የአገሪቱ መሪ የቤተ ክርስቲያን መሪ ሲሆን ሌሎች የቤተ ክርሰቲያኒቱ መሪዎችም የሚመረጡት በአገሪቱ መሪ ነው። ይህ በእስካንዴኒቪያን አገሮች ባሉ ሉተራን (መካነ ኢየሱስ) እና በኢንግላንድ ቤተ ክርስቲያን የሚታይ እውነት ነው። 

አስተዳደር አልባ። ይህን ሁኔታ በተግባር የሚለማመድ ቤተ ክርስቲያን አለ ለማለት ባይቻልም፥ ጨርሶ ሰው አይገዛንም ክርስቶስ ብቻ ነው የቤተ ክርስቲያን ራስ የሚሉ ወገኖች አሉ። ከተግባራቸው የሚታየው ግን ሰብአዊ መሪዎች በጕባኤው አስተዳደርና በተለያዩ ውሳኔዎች ላይ ቁልፍ ሚና ሲጫወቱ ነው። 

የትኛው አሠራር ነው ትክክል? ይህ ጥያቄ ነው ከጥንት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያናትን ሲያከራከር የኖረው። አሁንም ለጥያቄው ትክክለኛ መልስ መስጠቱ ያስቸግራል። ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እንዳላት በቃሉ የተገለጠ ስለሆን “አስተዳደር አልባነት” የመጽሐፍ ቅዱስ አሠራር አይደለም። በአዲስ ኪዳን ዘመን የሮም መንግሥትና ቤተ ቤተ ክርስቲያን የተለያዩ መሆናቸው ግልጥ ነበር። የሥልጣን ተዋረድ አሠራርም ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በኋላ የመጣ መሆኑ ተረጋግጧል። ስለዚህ የፊዴራላዊ ወይም የማኅበረ ምእመናናዊ አስተዳደር ዘይቤዎች ናቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሊሆኑ የሚችሉት። እንዲያውም ፈዴራላዊ ወይም ማኅበረ ምእመናናዊ ብለን ከመለያየት ፈዴራላዊና ማኅበረ ምእመናናዊ ብሉ ማያያዙ ይሻላል። ምክንያቱም የሁለቱም አሳቦች በአዲስ ኪዳን በግልጥ የታዩ ናቸው። እርግጥ ቤተ ክርስቲያን ሙሉ በሙሉ የምትተዳደረው በማኅበረ ምእመናን ከሆነ፥ ጎን ለጎን ፈዴራላዊ ድርጅት መመሥረቱ ያስቸግራል። ቤተ ክርስቲያን ፈዴራላዊ መዋቅር ኖሯት አንዳንድ ውሳኔዎች በማኅበረ ምእመናን እንዲወሰኑ ማድረግ ግን ይቻላል።

የቤተ ክርስቲያን ዓላማ 

ክርስቶስ ከቤተ ክርስቲያን ምን ይጠብቃል? ይህን ጥያቄ በተለያዩ መንገዶች መመለስ ቢቻልም፥ የበኩላችንን ጥቂት አመለካከቶች እነሆ፡- 

1. አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ ለክርስቶስ ያላትን ፍቅር ማሳየት አለባት (ራእይ 2፡4)። 

2. ቤተ ክርስቲያን አባላቷን ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዲነቃቁና አርአያ እንዲሆኑ ማስተማር ይገባታል (ዕብ. 10፡24)። 

3. ቤተ ክርስቲያን ታላቁን ተልእኮ ለማከናወን ወኪል ናት። መመስከርና ማስተማር በእያንዳንዱ ክርስቲያን መከናወኑ ግልጥ ቢሆንም፥ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናትም ተግባር ነው። ላልዳኑ ሰዎች ወንጌል መስበክ አለባት (1ኛ ቆሮ. 14፡24)፤ የአጥቢያይቱ ማኅበረ ምእመናንም የማስተማር አገልግሎት ማበርከት ያለባቸው መሆኑን የአዲስ ኪዳን መልእክቶች ሁሉ ያሳስባሉ። 

4. ቤተ ክርስቲያን የራሷ የሆኑትን ማለት፥ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች፥ እጓለ-ማውታን እና ድሆችን መርዳት አለባት (ያዕ. 1፡27፤ 1ኛ ጢሞ. 5፡1-16፤ 2ኛ ቆሮ. 8-9)። 

5. ቤተ ከርስቲያን በዚህ ዓለም መልካም ማድረግ አለባት (ገላ. 6፡10)። 

6. የቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ዓላማ ግን የበሰሉና የጸኑ ቅዱሳን ክርስቲያኖችን ማፍራት ነው። ይህን ማድረግ አንዳንድ ጊዜ የግብረገብ ሥነ-ሥርዓት ማስያዝን (1ኛ ቆሮ. 5) እና የትምህርተ-መለኮት ጥራቷን መጠበቅን ያጠቃልላል (2ኛ ጢሞ. 2፡16-18)።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.