ዓለም-አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን

ዓለም-አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን፡- ክርስቶስ ራሷ የሆነ፥ ከበዓለ-አምሳ ዕለት ጀምሮ እስከ መነጠቅ ድረስ ያሉ አማኞች ሁሉ አባላት የሆኑባት መንፈሳዊት አካል ነች። የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ስለሆነች ቤተ ክርስቲያኔ ብሏታል (ማቴ. 16፡18)። የመጀመሪያ መሪዎቿን አስተምሯል (ዮሐንስ 14-16)፤ ሊጀምራትና ኃይል ሊሰጣት በበዓለ አምሳ ዕለት መንፈስ ቅዱስን ልኮላታል (ሐዋ. 2፡33)። በትንሣኤውና በዕርገቱ የቤተ ክርስቲያኑ ማለት የአካሉ ራስ ሆኗል (ኤፈ. 1፡20-23)። ስጦታ ሰጥቷታል (ኤፈ. 4፡8-11)፤ ያለ ነውርና ነቀፋ የሆነች ሙሽራ እንድትሆንለት ያዘጋጃታል (ኤፌ. 5፡26-27)። 

ክርስቶስ ስለ ቤተ ክርስቲያን በተናገረው ትንቢት ላይ የተለያዩ የትርጉም ችግሮች ተነስተዋል (ማቴ. 16፡18-19)። ከችግሮቹ አንዱ ቤተ ክርስቲያኑን የሚገነባበት አለት ምንድን ነው? (ቁ. 18) የሚል ነው። የሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጴጥሮስ ራሱ ነው ትላለች። ይህ ግን የማይታመን ነው። ምክንያቱም ጴጥሮስ የሚለው ቃል ተባዕታይ ሲሆን፥ አለት የሚለው ቃል (በግሪክኛው አጠቃቀም) አንስታይ ጾታ በመሆኑ ነው። ቤተ ክርስቲያን የምትመሠረትበት አለት ክርስቶስ እንጂ፥ እርሱ አለመሆኑን ጴጥሮስ ራሱ ያረጋግጣል (1ኛ ጴጥ. 2፡4-8)። ይህም አለቱ ኢየሱስ ነው ለሚለው ትርጉም ድጋፍ ይሰጣል (1ኛ ቆሮ. 3፡11ንም ይመልከቱ)። ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን የሚሠራበት ድንጋይ ማለት ጴጥሮስ ክርስቶስ የተተነበየለት መሢህ ስለመሆኑ የተናገረው ቃል ሊሆንም ይችላል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን አባል የሚሆን ሰው የክርስቶስን መሢህነት ተቀብሏል። 

ሌላው የትርጉም ችግር ደቀ መዛሙርቱ የተሰጣቸውን የማሠርና የመፍታት ሥልጣን ይመለከታል (ማቴ. 16፡19)። ደቀ መዛሙርቱ ሥልጣን የተሰጣቸው ነገሮች ላይ እንጂ በሰዎች ላይ እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ቃሉ “በምድር ያሠራችሁት ነገር በሰማያትም የታሠረ ነው” ይላል። ለመፍታትም እንዲሁ። በዮሐንስ 20፡23 ላይ ኃጢአትን ይቅር ስለማለትና ስላለማለት የተገለጠውን እንዲሁ በተመሳሳይ ሁኔታ ለመፍታት ይቻላል። በሁለቱም ጥቅሶች ውስጥ ያለው ቁም ነገር፥ ደቀ መዛሙርት ለማሠር ወይም ለመፍታት፥ ይቅር ለማለት ወይም ኃጢአትን ለመያዝ ሥልጣን አላቸው ማለት ሳይሆን፥ በሰማያት የሆነውንና የተከናወነውን ለማወጅ ወይም ለማረጋገጥ መቻላቸውን ለማሳየት ነው። እግዚአብሔር እነዚህን ነገሮች ይጀምራቸዋል፥ ሐዋርያት ደግሞ ለሰዎች ያውጇቸዋል። ምሳሌ ቢያስፈልግ፥ ሐዋርያቱ ቤተ ክርስቲያንን ስለማሠራቸው በሐዋርያት ሥራ 15 ላይ የተጠቀሰውን መመልከት ይቻላል። ኃጢአትን ይቅር ስለአለማለት ደግሞ ሐዋ. 5፡1-11 ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ምንም እንኳን የዛሬዎቹ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከቀድሞዎቹ ተመሳሳይ የሆነ ኀላፊነት ቢኖርባቸውም፥ ኀላፊነቶቹ ተሰጥተው የነበረው ለሐዋርያቶች ብቻ ነው። 

የዓለም-አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ምሳሌዎች 

በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያኑ መካከል ያለው ግንኙነት በአዲስ ኪዳን ውስጥ በአያሌ ምሳሌዎች ተገልጧል። ምሳሌዎቹ ዝርዝር ጥናት የሚያስፈልጋቸው ቢሆኑም፥ ጥቂቶቹን ብቻ ጠቅሰን እናልፋለን። 

1. ክርስቶስ እረኛ፥ እኛ ደግሞ በጎቹ ነን (ዮሐንስ 10)። እርሱ ለእኛ ያለው ጥንቃቄና፥ የእኛ በእርሱ መጠበቅ መልእክት በዚህ ምሳሌ ይተላለፋል። 

2. ከርስቶስ የወይን ግንድ ነው፥ እኛ ቅርንጫፎቹ ነን (ዮሐንስ 15)። ፍሬያማ የምንሆነው የሚያስፈልገንን ከግንዱ ስናገኝ ብቻ ነው። 

3. ክርስቶስ የማእዘን ድንጋይ፥ እኛ የሕንጻው ላይ ድንጋዮች ነን (ኤፌ. 2፡19-21)። የማእዘን ድንጋይ ለሕንጻው ቅርፅ ሲሰጥ፣ የሚቀመጠውም አንድ ጊዜ ብቻ ነው። 

4. ክርስቶስ ሊቀካህን ነው፥ እኛም የምንግሥቱ ካህናት ነን (1ኛ ጴጥ. 2)። እንደ ካህናት እኛነታችንን፣ ያለንንና፣ አገልግሎታችንን መሥዋዕት አድርገን መስጠት እንችላለን (ሮሜ 12፡፤ ዕብ. 13፡15-16)። 

5. ክርስቶስ ራስ፥ እኛም የአካሉ ብልቶች ነን (1ኛ ቆሮ. 12)። እንደ ራስ እርሱ ይመራል፥ እንደ ብልቶች ደግሞ ከሞት የተነሣው ራስ በሚሰጠን መንፈሳዊ ስጦታ እርስ በእርሳችን መገልገል እንችላለን። 

6. ክርስቶስ የመጨረሻው አዳም ነው፥ እኛ አዲስ ፍጥረታት ነን (1ኛ ቆሮ. 15፡45)። የትንሣኤውን ኃይልና ሕይወት እንካፈል ዘንድ የመጨረሻው አዳም በሆነው በክርስቶስ ውስጥ በእምነታችን አለን (ሮሜ3፡19)። 

7. ክርስቶስ ሙሽራ፥ እኛ የእርሱ ሙሽሪት ነን (ኤፌ. 5፡25-33፤ ራእይ 19፡7-8)። በሙሽራውና ሙሽራይቱ መካከል ያለው የማያቋርጥ ፍቅርና ውህደት የዚህ ምሳሌ ዋና ዋና ነጥቦች ናቸው። 

8. ክርስቶስ ወራሽ ነው፥ እኛም ከእርሱ ጋር ወራሾች ነን (ዕብ. 1፡23 ሮሜ 8፡17)። ዓለም እርሱነቱን በሚረዱበት ዕለት እኛም የክብሩ ተካፋዮች እንደምንሆን ይህ ቃል ዋስትናችን ነው። 

9. ክርስቶስ የመጀመሪያ ፍሬ፥ እኛ መከር ነን (1ኛ ቆሮ. 15፡23)። ትንሣኤው ለእኛ ትንሣኤ ዋስትና ነው። 

10. እርሱ ጌታ፣ እኛ ባሪያዎቹ ነን (ቁላ. 4፥ 1፤ 1ኛ ቆሮ. 7፡22)። ባሪያ የጌታውን ፈቃድ ይፈጽማል፤ በአንጻሩም ጌታ ለባሪያው የሚያስፈልገውን ያደርግለታል።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.