በቤትና በሥራ ቦታ መንፈሳዊ ግንኙነቶችን መጠበቅ (ቆላ. 3፡18-4፡18)

ክርስትና የግለሰብ ወይም የቤት ውስጥ እምነት ብቻ አይደለም። የአንድ ግለሰብ መላ ሁለንተና ሌላውን ይገነባል። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ሰዎች እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ይመላለሱ ዘንድ ከማኅበራዊ ነገሮች አንዳንድ ማብራሪያዎችን ይሰጣል።

ሀ. በቤት ውስጥ፥ ሚስቶች ተገዥዎች፥ ባሎች አፍቃሪዎች፥ እንዲሁም ልጆች ታዛዦች ሊሆኑ ይገባል።

ለ. በሥራ ቦታ፥ ባሪያዎች (ሠራተኞች) እግዚአብሔርን ለማስደሰት በማሰብ በትጋት መሥራት ይኖርባቸዋል። ለሰብአዊ ጌቶቻቸው የሚሠሩ ቢመስልም፥ ለመለኮታዊ ጌታቸው ለኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚሠሩ መረዳት አለባቸው። አሁን ባሪያዎች ቢሆኑም፥ እግዚአብሔርን ካከበሩ እርሱም እነርሱን በማክበር በመንግሥቱ ውስጥ ርስትን ይሰጣቸዋል። ይህም የክብር ስፍራ ነው። ክርስቲያን ጌቶች (አሠሪዎች) ደግሞ ለባሪያዎቻቸው (ለሠራተኞቻቸው) ትክክለኛውንና ፍትሐዊውን ነገር ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከእነርሱ የሚበልጥ ጌታ እንዳለና በሰማይ ያለው ክርስቶስ ሠራተኞቻቸውን ለሚያስተናግዱበት መንገድ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው ሊያውቁ ይገባል።

ጳውሎስ አያሌ ጠቃሚ እውነቶችን በማቅረብ ስለ አማኞች አኗኗር ያቀረበውን ትምህርት ያጠቃልላል። በመጀመሪያ የጸሎት ሰዎች ልንሆን ይገባል። አንዱ አማኝ ለሌላው መጸለይ አለበት። «እግዚአብሔር ይባርከን» ከሚለው አጠቃላይ ጸሎት ባሻገር፥ ዘርዘር ያሉ ጸሎቶችን ልንጸልይ ይገባል። በእኛና በሌሎች ሕይወት ውስጥ ላከናወነው ዝርዝር ተግባር እግዚአብሔርን ማመስገን እለብን። ጸሎታችን ከግል የራስ ወዳድነት ምኞቶች በላይ በእውነተኛ ፍላጎቶች ላይ ይመሠረት ዘንድ ማስተዋል የታከለበትን ጸሎት ማቅረብ አለብን። ለዚህ ዓይነቱ ጸሎት ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ምሳሌ ሰጥቷቸዋል። ይኸውም የቆላስይስ አማኞች ጳውሎስ ካለበት እሥራት ባሻገር ለክርስቶስ የመመስከርን ዕድሎችና ተጨማሪ ሥቃይና ስደት የሚደርስበት ቢሆንም እንኳን ለመመስከር የሚችልበትን ድፍረት እንዲያገኝ ይጸልዩለት ዘንድ ጠይቋቸዋል።

ሁለተኛ፥ አማኞች ከማያምኑ ሰዎች (በውጭ ካሉት) መለየት የለባቸውም። እግዚአብሔር ስለ ክርስቶስ የሚመሰክሩበትን ዕድል ይሰጣቸው ዘንድ አማኞች ከማያምኑ ሰዎች ጋር ግንኙነት ማድረጋቸውን መቀጠል አለባቸው። ወንጌሉን በግድየለሽነትና ለሌሎች ባለማሰብ ማካፈል የለብንም። ጳውሎስ እግዚአብሔር ትክክለኛውን የመመስከሪያ ጊዜ ይሰጠን ዘንድ በገርነትና በቸርነት ልንጠይቀው እንደሚገባን ያስረዳል። እነዚህን መልካም የመመስከሪያ አጋጣሚዎች የሚያመጣልህ ምን ይሆን? ከሰዎች ጋር የምትነጋገርበት ሁኔታ ሊሆን ይችላል። ስለሆነም ንግግራችን በጸጋ የተሞላና በጨው እንደ ተቀመመ ሁሉ ጣፋጭ ሊሆን ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አማኞች በግድየለሽነትና ለሌሎች ባለማሰብ ወንጌሉን የሚሰብኩባቸውን መንገዶች በምሳሌ አብራራ። ይህ ከሚያምኑ ሰዎች የሚያስገኘው ምላሽ ምንድን ነው? ለ) እምነታችንን በጨው እንደ ተቀመመ ሁሉ በጸጋ ልናቀርብ ስለምንችልባቸው መንገዶች ምሳሌ ስጥ። ይህ በግድየለሽነት ከሚቀርበው የወንጌል ምስክርነት የተለየ ምላሽ የሚያስከትለው እንዴት ነው?

በማጠቃለያ ክፍሉ ውስጥ ጳውሎስ ከእርሱ ጋር በሮም ከነበሩት ቁልፍ መሪዎች አንዳንዶቹን ይጠቅሳል። አብዛኞቹ እሥረኞቹ ያልነበሩና ጳውሎስን ለመጎብኘት የተፈቀደላቸው ነበሩ። ከእነዚህ ቁልፍ መሪዎች መካከል የሚከተሉትን እናገኛለን።

ሀ) የጳውሎስን ደብዳቤ ለቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን የሚያደርሰው ቲኪቆስ (ኤፌ. 6፡21) እንደሚነግረን፥ ይህ አገልጋይ ደብዳቤውን ለኤፌሶንም ያደርሳል።)

ለ) የበርናባስ የአክስቱ ልጅ የሆነው ማርቆስ። ከ11 ዓመት በፊት ዮሐንስ ማርቆስን በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ ላይ በማሳተፉ ጉዳይ ላይ ጳውሎስና በርናባስ አለመግባባትን ፈጥረው ነበር። ለዚህም ምክንያቱ ማርቆስ በመጀመሪያው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ ላይ ከእነርሱ ተለይቶ መሄዱ ነበር (የሐዋ. 15፡36-41 አንብብ።) ጳውሎስ ከማርቆስ ጋር ላለመሥራት ወሰነ። ማርቆስ ግን በእምነት ጠንክሮ በመገኘቱ ጳውሎስ ይቅርታ አድርጎለታል። በመሆኑም አብረው በመሥራት ላይ ነበሩ።

ሐ. ኤጳፍራ – ይህ ሰው ምናልባትም የቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን መሥራች የነበረና ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ እንዲጽፍ ያነሣሣውን ሪፖርት ያመጣው አገልጋይ ሳይሆን አይቀርም። ኤጳፍራ በሮም ከጳውሎስ ጋር አብሮ በመሥራት ላይ ነበር። ጳውሎስ ኤጳፍራ ለቆላስይስ አማኞች መንፈሳዊ ብስለት የሚጸልይ ትጉ የጸሎት ተጋዳይ እንደሆነ ገልጾአል።

መ. ሉቃስ – የሐዋርያት ሥራ ጸሐፊ። በሁለተኛውና በሦስተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ ወቅት ከጳውሎስ ጋር የነበረ ከመሆኑም በላይ፥ ጳውሎስ በታሰረ ጊዜ ወደ ሮም ሄዷል።

ሠ. ዴማስ – የጳውሎስ የቅርብ የሥራ ጓደኛ የነበረ ሲሆን፥ የኋላ ኋላ ይህን ዓለም ወይም ቁሳቁሶችን በመውደድ ከጳውሎስ ተለይቷል (2ኛ ጢሞ. 4፡10)።

ረ. አክሪጳ – የቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን መሪ ሽማግሌ ወይም መጋቢ የነበረ ይመስላል።

ጳውሎስ የቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን ይህን መልእክት ለሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን እንዲሰጡ በመጠየቅ ደብዳቤውን ይፈጽማል። ለሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን የተላከውንም መልእክት ተቀብለው እንዲያነቡት ነግሯቸዋል። አያሌ ምሁራን ይህ የሎዶቅያ መልእክት ለብዙ አብያተ ክርስቲያናት የተጻፈውን የኤፌሶን መልእክት ብለን የምንጠራው እንደሆነ ያስባሉ። ወይም በኋላ የጠፋ ሌላ መልእክት ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ ለጸሐፊው እየተናገረ ያጻፈው ይህ መልእክት የራሱ መሆኑን ለማመልከት ከመጨረሻው ላይ ስሙን ይጽፋል።

የውይይት ጥያቄ፡– ከቆላስይስ የተማርሃቸውን አንዳንድ እጅግ አስፈላጊ እውነቶች ዘርዝር። አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የተቀደሰ አኗኗር (ቆላ. 3፡1-17)

አንድ ጊዜ አንድ መምህር ለስኬታማ ክርስቲያናዊ ሕይወት ምሥጢሩ በሕይወታችን እውነቶችን ሚዛናዊ ማድረግ ነው ብሎ ነበር። ብዙውን ጊዜ የተሳሳተ ልምምድና ትምህርት የሚከሠተው አንድን እውነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች እውነቶች ጋር ሚዛናዊ ከማድረግ ይልቅ እንደ ዋነኛ እውነት አድርገን ስንወስደው ነው። ይህንን በብዙ መንገዶች መመልከት ይቻላል። በልሣን መናገር መንፈሳዊ ስጦታ መሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመልክቷል። ነገር ግን በልሳን መናገር የችግሮች ሁሉ መፍትሔ ወይም የመንፈሳዊነት ምልክት ነው ብሎ ማሰቡ ሚዛናዊነት የጎደለው አስተሳሰብ ነው። የእግዚአብሔር ቃል ሌሎች ብዙ መንፈሳዊ ስጦታዎችና ተግባራት ለመንፈሳዊነት እኩል ጠቀሜታ እንዳላቸው ያስተምራል። መዘመርና ማምለክ አስፈላጊዎች ናቸው። ነገር ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጋር መመጣጠን አለባቸው። የሰው ወይም የቤተ ክርስቲያን ደንቦች ሕጋዊ ቢሆኑም ቀዳማዊ አጽንኦት ሊሰጣቸው አይገባም። ይልቁንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለንን ግንኙነት እናንጸባርቅ ዘንድ በልባችን፥ በአመለካከታችንና በተግባራችን ላይ ልናተኩር ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰዎች የሚያተኩሩባቸውንና የእምነት ወይም የተግባር አለመመጣጠን የሚያስከትሉትን ነገሮች ግለጽ። ለ) አዲስ ኪዳን ለመንፈሳዊ ሕይወታችን በጣም ጠቃሚዎች መሆናቸውን እየገለጸ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙውን ጊዜ የማይነገሩትን አንዳንድ እውነቶች ዘርዝር። አገልጋዮች እነዚህን እውነቶች የሚያስተምሩት ለምንድን ነው?

በቆላስይስ የነበሩ አስተማሪዎች በብዙ ሰው ሠራሽ ደንቦች ላይ ትኩረት ያደርጉ ነበር። አይሁዶችም የራሳቸው ደንቦች ነበሩዋቸው። ግሪኮችም እንዲሁ። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ላይ የሚያስከትሉት አዎንታዊ ተጽዕኖ አልነበራቸውም። ጳውሎስ የቆላስይስ ክርስቲያኖች እነዚህን ከመከተል እንዲቆጠቡ አስጠንቅቋቸዋል። ይህ ማለት ክርስቲያኖች የሚከተሉት ሕግ ወይም ትእዛዝ የለም ማለት አይደለም። የምንፈልገውን የማድረግ «ነጻነት» የለንም።

ነገር ግን እግዚአብሔር እንድንሆን የሚፈልገውን የመሆን፥ እርሱ በፈጠረን ዓላማ የመኖርና ክርስቶስ ባዳነን መንገድ የመመላለስ ነጻነት አለን። ይህ የቆላስይስ መልእክት የመጨረሻው ክፍል (ቆላ. 3-4) እንዴት ላመንንበት ወንጌል እንደሚገባ መኖር እንዳለብን ያሳያል።

ሁላችንም ከምንጋፈጣቸው ችግሮች አንዱ የምናምነውን ከአኗኗራችን ጋር ማስማማት ነው። ባኗኗራችን ክርስቶስን እንደምናስከብር መናገር ወይም ኢየሱስ ጌታ ነው ማለቱ ቀላል ነው። ነገር ግን በሥራ ቦታ፥ በቤት፥ በማኅበረሰቡ መካከል ወይም በትምህርት ቤት የምናከናውነው ተግባር ክርስቶስን እንደሚያስከብር የምንገመግመው ጥቂቶች ነን። በቀዳማዊነት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በምናከናውነው ተግባር በአምልኮአችን ወይም እንደ ዝሙት ያሉትን ታላላቅ ኃጢአቶች ባለመፈጸም ክርስቶስን እንደምናስከብር እናስባለን። ለወንጌሉ እንደሚገባ መመላለስ ማለት ግን የሕይወታችንን ክፍሎች በሙሉ ለክርስቶስ አሳልፎ መስጠት ማለት ነው። ተግባራችን ክርስቶስን እንደሚያስከብር ወይም እንደማያስከብር ከምንገመግምባቸው መንገዶች አንዱ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለራሳችን ማቅረብ ነው። ክርስቶስ ቢሆን ምን ያደርግ ነበር? ክርስቶስ ነጋዴ ቢሆን ኖሮ ምን ያደርግ ነበር? ጉቦ ይሰጥ ነበር? ተገቢ ያልሆነ ዋጋ ያስከፍል ነበር? የውጪ አገር ዜጎችን ያጭበረብር ነበር? ክርስቶስ ተማሪ ቢሆን ምን ያደርግ ነበር? ከተማሪዎች መልስ ይኮርጅ ነበር? ፈተናውን ለመስረቅ ይሞክር ነበር? በቤትስ ምን ያደርግ ነበር? ልጆቹና ሚስቱ እንደ ባሮች ያገለግሉት ዘንድ ስማቸውን እየጠራ ያዋክባቸው ነበር? ክርስቶስ በቤተ ክርስቲያን አመራር ውስጥ ቢኖር ምን ያደርግ ነበር? ከሕዝቡ ጋር ሳይቀላቀል እርሱ የሚፈልገውን ብቻ እንዲያደርጉ በሥልጣን ያዛቸው ነበር? ክርስቶስ ራሱን ለማስከበር፥ ኃይሉን ለማሳየት፥ ከመሪነት እንዲወርድ በሚጠየቅበት ጊዜ ፈቃደኛ ባለመሆን፥ የአመራር ጥቅማ ጥቅሞችን ከሕዝቡ ይልቅ ወደ ራሱና ወደ ቤተሰቦቹ እንዲግበሰበሱ በማድረግ ሰዎችን ይበድል ነበር? ክርስቶስ ለመንግሥት ቢሮ ቢሠራ ኖሮ ምን ያደርግ ነበር? ሰዓቱን እክብሮ ይሠራ ነበር? ወይስ አርፍዶ መጥቶ ሰዓቱ ሳይደርስ ይሄድ ነበር? ጉቦ በመቀበል አድልዎ ይፈጽም ነበር? ወይስ ሰዎችን በእኩልነት ያስተናግድ ነበር? በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስብከት እንዲያቀርብ ቢጠየቅ ምን ያደርግ ነበር? ብዙም ሳያጠና የሰበከው ጥሩ እንደሚሆን ተስፋ ያደርግ ነበር? ወይስ በሚገባ በማጥናት፥ መልእክቱን በግልጽ ለማቅረብ በመዘጋጀትና እግዚአብሔር መልእክቱን እንዲባርክ በጸሎት በመጠየቅ የድርሻውን ይወጣ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ከላይ የቀረቡትን ጥያቄዎች ተመልከት። ሀ) ከላይ በቀረቡት ሁኔታዎች ሁሉ ውስጥ ክርስቶስ ምን የሚያደርግ ይመስልሃል? ይህንን ብዙዎች ክርስቲያኖች ክሚያደርጉት ጋር በማነጻጸር መልስ። ለ) ይህ ክርስቶስን እያስከበሩ ስለ መኖርና ዛሬ በተቃራኒው ብዙ ክርስቲያኖች ስለሚኖሩበት ሁኔታ ምን ያሳያል?

ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ ለወንጌሉ እንደሚገባ መኖር አለመኖርህን ያሳያል። ዓለምን የምንኮርጅ ከሆነ በተገቢው መንገድ እየኖርን አለመሆናችንን እናውቃለን። እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ የማንኖር ከሆነ ደግሞ እግዚአብሔር ኃጢአትን ምን ያህል እንደሚጠላ አልተገነዘብንም ማለት ነው። እንዲሁም አማኞች እንደ መሆናችን ለኃጢአት የሞትንና ለእግዚአብሔር ሕያዋን የሆንን አዳዲስ ፍጥረታት መሆናችንን አልተገነዘብንም ማለት ነው። ዛሬ ከምንጋፈጣቸው ዐበይት ችግሮች አንዱ አብዛኞቹ ምእመናን ክርስቶስን በሚያስከብር መንገድ የማይኖሩ መሆናቸው ነው። ክርስቶስን የማናስከብር ከሆነ ደግሞ የሚገባንን ያህል አንወደውም ማለት ነው።

ትክክለኛ ነገሮችን ማመኑ ብቻ በቂ አይደለም። እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ መኖር አለብን። በዚህ የቆላስይስ መልእክት የመጨረሻ ክፍል ጳውሎስ አንዳንድ ነጥቦችን ጠቅለል ባለ መልኩ ያቀርባል። እነዚህም ነጥቦች እምነታችንን ለማንጸባረቅና በወንጌሉ እንደሚገባ ለመመላለስ በሕይወታችን ውስጥ ሊለወጡ የሚገባቸውን ነገሮች ያሳያሉ።

ሀ. እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ለመኖር የሚያግዙ ሁለት መሠረታዊ መርሆዎች፥ በቆላስይስ 3፡1፥ ጳውሎስ የቆላስይስ ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ጋር መተባበራቸውን ያስገነዝባቸዋል። ከዚህም የተነሣ ለኃጢአት ባሕርያቸው ሞተው እግዚአብሔርን ለማገልገል ከክርስቶስ ጋር ሕያዋን ሆነዋል። አንድ ቀን ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ከእርሱ ጋር አብረው ይከብራሉ። ጳውሎስ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መልኩ ለመኖር ልናደርጋቸው የሚገቡ ሁለት መሠረታዊ መርሆዎች እንዳሉ ያስረዳል።

በመጀመሪያ፥ «በላይ ያለውን እሹ»። ጳውሎስ ያስፈልጉናል ስለምንላቸው ነገሮች ነው የሚናገረው። ዓይኖቻችንን በሰማይ ላይ እንድናሳርፍ ይናገራል። ዋናው ነገር የዘላለም ሕይወት፥ ከክርስቶስ ጋር መንገሥ፥ በእርሱ መሸለምና እርሱ እንደሚፈልገው መኖር ነው። ዘላለማዊ እሴት ላላቸው ነገሮች ቅድሚያ መስጠት አለብን። ይህም የምንወደውንና ለኃጢአታችን የሞተውን ክርስቶስን ለማስደሰት መሻታችንን ያሳያል። የዓለምን ነገሮች (ክብር፥ ሀብት፥ ትምህርት፥ ጥሩ አኗኗር፥ ወዘተ…) በመሻት ቀዳማይ ትኩረት ልንሰጣቸው አይገባም።

ሁለተኛ፥ «በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም።» ቀኑን ሁሉ የምናስበው ነገር ለሕይወታችን ወሳኝ ጉዳይ ነው። ዓለም ስፍራ ስለሚሰጣቸው ነገሮች የምናስብ ከሆነ፥ ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ የሚያመለክት ሕይወት ልንኖር አንችልም። ነገር ግን እግዚአብሔር አስፈላጊ ናቸው ስለሚላቸው ነገሮች የምናስብ ከሆነ፥ ሕይወታችን ይለወጥና እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንኖራለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከሰማይ ያልሆኑትንና ክርስቲያኖች ልባችንን ልናሳርፍ የምንችልባቸውን ነገሮች ዘርዝር። ለ) ክርስቲያኖች አእምሮአችንን ልናሳርፍባቸውና እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ከመኖር የሚመልሱንን ነገሮች ዘርዝር። ሐ) እግዚአብሔርን በሚያስከብሩና በሚያስደስቱ ነገሮች ላይ እናተኩር ዘንድ ልባችንንና አእምሯችንን ልናሠለጥን የምንችልባቸው መንገዶች ምን ምንድን ናቸው?

ለ. ጳውሎስ ክርስቲያኖች ሊያደርጓቸው የማይገቧቸውን «አሉታዊ» ነገሮች ይዘረዝራል። እነዚህ ነገሮች በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ጥሩዎች ባለመሆናቸው ልንገድላቸው ወይም ልናስወግዳቸው የሚገቡ ናቸው።

 1. ልንቆጠብባቸው የሚገቡን የተለያዩ ኃጢአቶች። ከእነዚህ ኃጢአቶች አንዳንዶቹ ታላላቅ ኃጢአቶች ናቸው የምንላቸው ናቸው። እነዚህም እንደ አመንዝራነትና ዝሙት ያሉ ናቸው። እጅግም መጥፎዎች አይደሉም የምንላቸው ሌሎች ኃጢአቶች ደግሞ ምኞት፥ ክፉ አሳብና ስግብግብነት ናቸው። አንድ የቤተ ክርስቲያን አባል ዝሙት ከፈጸመ ቤተ ክርስቲያን ልትቀጣው ትችላለች። የስግብግብነትን ኃጢአት ግን እምብዛም ከቁም ነገር አንቆጥረውም። እግዚአብሔር ግን ኃጢአትን ትንሽና ትልቅ ብሎ አይከፋፍልም። ሁሉም ኃጢአት በእግዚአብሔር ላይ የሚፈጸም ዓመፅ በመሆኑ ትክክል ሊሆን አይችልም። እንዲያውም ጳውሎስ ስግብግብነት ጣዖትን እንደ ማምለክ ነው ብሏል። ይህ በየጠዋቱ የምንሰግድለት ቁሳዊ ጣዖት ላይሆን ይችላል። በእግዚአብሔር ፊት ግን ጣዖት ከእግዚአብሔር አስበልጠን የምንወደው ማንኛውም ነገር ነው። ስግብግብነት ገንዘብን ከእግዚአብሔር በላይ መውደድ ነው። ንግዳችንን ለማስፋፋት ብለን ጉቦ ስንሰጥ በልባችን ውስጥ ስግብግብነትና አምልኮተ ጣዖት አቆጥቁጠዋል ማለት ነው።
 2. የቆላስይስ አማኞች ግንኙነቶችን የሚያወድሙትንና እግዚአብሔርን የማያስከብሩትን ባሕርያትና ተግባራት ማስወገድ ያስፈልጋቸው ነበር። ጳውሎስ እንደ ቁጣ፥ ንዴት፥ ክፋት፥ ስድብ፥ ጸያፍ ንግግር፥ ውሸት ያሉትን ዘርዝሯል። ጳውሎስ እነዚህ ከወሲባዊ ኃጢአቶች እንደሚያንሱ አልገለጸም። ሁሉም ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነው። ይህም ሆኖ፥ ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ሌሎችን በመጥላትና በማማት እግዚአብሔርን ይበድላሉ። በዚህም ሁሉ ኃጢአት መፈጸማቸው ትዝ አይላቸውም። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚከሠቱት ክፍፍሎች የአብዛኞቹ መንሥኤዎች ክፋት፥ ስድብና ውሸት ናቸው። እግዚአብሔር እነዚህን ኃጢአቶች ምን ያህል እንደሚጠላቸው የምንገነዘበው መቼ ይሆን?
 3. አማኞች የክርስቶስ አካል በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን አንድነት ማስታወስ ነበረባቸው። ጳውሎስ በዘመኑ የነበሩትን አንዳንድ ክፍፍሎች ዘርዝሯል። በአይሁድ (በተገረዙ) እና በግሪኮች (አሕዛብና ያልተገረዙ)፥ ባልተማሩ (አረማዊ) እና በተማሩ፥ እስኩቴስ (በአገራችን ቆላማ አካባቢዎች የሚገኙትን ዘላኖች የሚመስሉ)፥ በባሪያና በጨዋ (ነፃ) ሰዎች መካከል ልዩነቶች ነበሩ። የጎላ ልዩነቶች አስፈላጊ ነገሮች አይደሉም። ትምህርት፥ የአኗኗር ዘይቤ (ዘላኖችና ገበሬዎች)፥ እንዲሁም የኢኮኖሚ ደረጃዎች (ነፃ ወይም ባሪያ) አስፈላጊዎች አይደሉም። በክርስቶስ ካመንን እርሱ በሁላችንም ውስጥ በእኩል ደረጃ ይኖራል።

ሐ. የቆላስይስ አማኞች እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኙትን ተግባራትና ባሕርያት እንዲለብሱ ተጠይቀዋል። እግዚአብሔር የሚፈልገው ኃጢአት መሥራታችንን እንድናቆም ብቻ ሳይሆን፥ አዎንታዊ ለውጦችንም እንድናሳይ ጭምር ነው። ጳውሎስ በክርስቶስ አካል ውስጥ አንድነትንና ኅብረትን በሚያመጡት ነገሮች ላይ ያተኩራል። አንድነትን የሚያመጡት እነዚህ ባሕርያት ምን ምንድን ናቸው? እነዚህም «ምሕረት፥ ርኅራኄ፥ ቸርነት፥ ትሕትና፥ የዋህነት፥ ትዕግሥት» ናቸው። በአሳብ የመለያየት ሁኔታ መከሠቱ የማይቀር ነው። ነገር ግን ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው ይቅር እንዲባባሉ ጳውሎስ ጥሪ አቅርቧል። እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ ሌሎችን ይቅር እንድንል በሚጠይቅበት ጊዜ እርሱ እኛን ይቅር እንዳለ ይናገራል። ቅዱስ የሆነው አምላክ በእርሱ ላይ አስከፊ ኃጢአት የሠራነውን ሰዎች ይቅር ብሎናል። እኛም እኛ እግዚአብሔርን ከበደልነው ኃጢአት ጋር ሲነጻጸሩ በጥቂቱ የበደሉንን ሰዎች ይቅር ልንል ይገባል። ብዙውን ጊዜ ሌሎችን ይቅር ለማለት በማንፈልግበት ጊዜ ምን ያህል ኃጢአተኞች እንደነበርን ወይም እግዚአብሔር ምን ያህል ይቅር እንዳለን አልተገነዘብንም ማለት ነው። ጳውሎስ እነዚህን ሁሉ ባሕርያትና ተግባራት የሚያቅፈውን ፍቅርን በአጽንኦት ገልጾአል።

መ. አማኞች በእግዚአብሔር ቃል ሥር መስደድ ያስፈልጋቸው ነበር። ብዙ ሰዎች ሀብታም ለመሆን እንደሚፈልጉ ሁሉ፥ የእግዚአብሔርም ሕዝብ ቃሉን በመረዳት መበልጸግ አለባቸው። የእግዚአብሔርን ቃል በግል ደረጃ ማወቁ ለሁለት ዐበይት አገልግሎቶች ጠቃሚ ነው።

 1. ሌሎችን ማስተማር። በኮሚኒዝም ዘመን «የተማረ ሁሉ ያስተምር» የሚል መፈክር ይነገር ነበር። ይህ ከእኛ ከሚጠበቀው ነገር ጋር ይመሳሰላል። ሁላችንም በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ አስተማሪዎች ነን። ወላጆች ከሆንን ልጆቻችንን፥ በሳል ክርስቲያኖች ከሆንን አዳዲስ አማኞችን እናስተምራለን። የእግዚአብሔርን ቃል አውቀን ለሌሎች ማስተላለፍ አለብን።
 2. አምልኮ። ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል ማወቅ ከአምልኮ ጋር ማያያዙ አስገራሚ ነው። ከዚህም እግዚአብሔርን ልናከብር የምንችለው መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምረው መንገድ ያመለክን እንደሆነ መሆኑን እንረዳለን። ክርስቶስ እንዳለው፥ እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኘው መንገድ ለማምለክ በእውነትና በመንፈስ ልናመልከው ይገባል (ዮሐ. 4፡23-24)። ወጣቶች ብዙውን ጊዜ «መንፈስን»  ወይም ጮክ ብሎ መዘመር፥ እጅን ማጨብጨብ፥ ማሸብሸብና መደነስ የሚታይበትን ስሜታዊ የአምልኮ ክፍል ይወዳሉ። አንዳንድ አማኞች አምልኮን የሚገልጹት በስሜታዊነት ደረጃው ነው። ጳውሎስ ግን ሁሉም አምልኮ በእግዚአብሔር ቃል ግልጽ እውቀት ሊካሄድ፥ በእውነት ላይ ሊመሠረትና ከአመስጋኝ ልብ ሊመነጭ እንደሚገባ ያስተምራል። ጳውሎስ ይህንን አሳብ ያመጣው ቀደም ሲል አማኞች ሊያደርጓቸው የሚገባቸውንና የማይገቧቸውን ነገሮች ካብራራ በኋላ መሆኑን አጢን። ይህም እግዚአብሔርን ለማስከበር እርሱ በሚፈልገው መንገድ መመላለስ እንዳለብን ያሳያል።

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) የቤተ ክርስቲያን አባላት እግዚአብሔርን በእውነት ከማምለካቸው በፊት ሊያደርጓቸው ስለሚገቧቸውና ስለማይገቧቸው ነገሮች ምን ሊያውቁ ይገባል? ለ) ብዙ አማኞች በእግዚአብሔር ቃል ከማደግ ይልቅ በመዝሙር ላይ የሚያተኩሩት ለምንድን ነው? ሐ) አምልኮ እውነትንና መንፈስን እንዲይዝና በእግዚአብሔር ቃል ላይ እንዲመሠረት በቤተ ክርስቲያንህ ምን ሊለወጥ ይገባል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

አማኞች ከንቱ ሰብአዊ ትምህርቶችን ከመከተል ይልቅ በክርስቶስ ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል (ቆላ. 2፡6-23)

አሁን ደግሞ ጳውሎስ በሐሰተኛ ትምህርቶች ላይ ያተኩራል። እነዚህንም ትምህርቶች ጳውሎስ፥ እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ያለ ፍልስፍናን ከንቱ መታለል» ሲል ይገልጻል። አማኞች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድጉ ያበረታታቸዋል። ሥር እንደሌላቸውና ማዕበል በተነሣ ጊዜ እንደሚወድቁ ዛፎች ከመሆን ይልቅ ከክርስቶስ ጋር ጥልቅ የእውቀትና የግንኙነት ሥሮች ልንይዝ ይገባል። መጀመሪያ ባመንን ጊዜ ባገኘነው እውነት ላይ እየጨመርን መሄድ አለብን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቅርቡ የተማርሃቸውና መንፈሳዊ ሥሮችህ ወደ ክርስቶስ ጠልቀው እንዲሄዱ ያደረጉህ እውነቶች ምን ምንድን ናቸው? ለ) ብዙ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የሚያድጉትና ባላቸው እውቀት የሚረኩት ለምንድን ነው? ሐ) ሰዎች ከክርስቶስ ጋር የጠለቀ ግንኙነት እንዲመሠርቱና ስለ እርሱም የበለጠ እንዲያውቁ ቤተ ክርስቲያንህ ምን ልታደርግ ትችላላች?

ጳውሎስ አጽንኦት የሰጠባቸው አንዳንድ እውነቶች፡-

ሀ. ኖስቲኮች ክፉ ሰብአዊ ሰውነት ሊለብስ እንደማይችል ያስተምሩ ነበር። ይህም ክፉ ያደርገዋል ብለው ያስቡ ነበር። ጳውሎስ ግን ክርስቶስ ሙሉ በሙሉ አምላክና ሰው እንደሆነ ያስረዳል።

ለ. ኖስቲኮች የቆላስይስ አማኞች ከክፉ ቁሳዊ ተፈጥሮ ነፃ የሚያደርጋቸውን ምሥጢራዊ ነገሮች ስለማያውቁ ምሉዓን እንዳልሆኑ ገልጸው ነበር። ጳውሎስ ግን በክርስቶስ ምልዓት እንደተሰጣቸው ያስረዳል። የሚያስፈልጋቸው ክርስቶስ ብቻ እንጂ ሌላ ልዩ ነገር አልነበረም። እርሱ በቂ የሆነው ለምንድን ነው?

 1. ክርስቶስ አማኞች ለኃጢአት ተፈጥሮ የታሠሩበትን ሁኔታ በማስወገድ ልባቸውን ገርዟል። ከክርስቶስ ጋር በሞቱ፥ በቀብሩና በትንሣኤው ስለተባበርን፥ በሕይወታችን ላይ የነበረው የኃጢአት ቁጥጥር ተወግዷል። በመሆኑም ኖስቲኮች የሚፈልጉትን አዲስ ሕይወት አግኝተናል።
 2. የአማኞች ኃጢአቶች በሙሉ ይቅርታን አግኝተዋል። «በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው።» በጥንት ጊዜ አንድ ሰው ገንዘብ በሚበደርበት ጊዜ መበደሩን የሚያመለክት ፊርማ ያሰፍር ነበር። የተበደረውን ገንዘብ ባይከፍል አበዳሪው ፊርማው ያረፈበትን ማስታወሻ ከዳኛ ዘንድ በመውሰድ በፍርድ ቤት ገንዘቡን ያስከፍል ነበር። ገንዘቡን በሚከፍልበት ጊዜ ሕዝብ በሚያልፍበት ስፍራ «በሙሉ ተከፍሏል» የሚል ማስታወቂያ ይለጠፋል። ጳውሎስ ስለ ኃጢአታችንም ተመሳሳይ ማብራሪያ ይሰጣል። እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሰጣቸውን ትእዛዛት ስላልጠበቅን፥ በደለኛነታችንን የሚያመለክት የዕዳ ጽሕፈት ነበረብን። ክርስቶስ ስለ እኛ በሞተ ጊዜ ግን ኃጢአታችን ወይም የዕዳ ጽሕፈታችን በሙሉ በመስቀል ላይ ተጠረቁ። ሰይጣን የሚከስሰን ስለ እነዚሁ ኃጢአቶቻችን ነበር። ክርስቶስ በሞተ ጊዜ ለእነዚህ ዕዳዎቻችን ተገቢውን ዋጋ ከፈለ። ስለሆነም፥ በእግዚአብሔር ዐይኖች ፊት በዚያው የዕዳ ጽሕፈት ላይ «በሙሉ ተከፍሏል» ተብሎ ይጻፋል። ስለሆነም ሰይጣን ከእንግዲህ ወዲህ ሊከስሰን አይችልም። እግዚአብሔር ራሱ ስለከፈለልን ዕዳችንን መክፈል አያስፈልገንም።
 3. ክርስቶስ ክፉ ኃይላት (ሰይጣንና አጋንንቱ) በእኛ ላይ የነበራቸውን ይዞታ አስወግዷል። አንድ ድል አድራጊ ጄኔራል በጦርነት የማረካቸውን እሥረኞች በሰንሰለት አሥሮ እንደሚነዳ ሁሉ፥ ክርስቶስ ሰይጣንና አጋንንትን በመስቀል ላይ አሸንፎ በሰንሰለት ጠፍሯቸዋል። ሰይጣን ዛሬም በዓለማችን ውስጥ ኃይል ስላለው ኃጢአትን እንድንሠራ ሊፈትነን ይችላል። ነገር ግን ሕይወታችንን የመቆጣጠር አቅም ስለሌለው፥ እግዚአብሔር እንዲቀጣን የማዘዝ ችሎታ የለውም። በክርስቶስ ደም የኃጢአታችን ዋጋ ተከፍሏል።

እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ስለተቀበለን የሐሰት አስተማሪዎችን ትምህርት የምንከታተልበት ምክንያት አይኖርም። ክርስቲያኖች የተወሰኑ ምግቦችን እንዲመገቡ፥ የብሉይ ኪዳን ሃይማኖታዊ በዓላትን እንዲከተሉ ወይም በሰንበት ቀን እንዲያመልኩ የሚጠይቀውን የአይሁዶች ትምህርት የሚከተሉበት ምክንያት አይኖርም። በተጨማሪም ክርስቲያኖች በምሥጢራዊ ዕውቀት ወይም ሰውነትን በመቅጣት የኃጢአትን ቁጥጥር ለማሳነስ በሚሞከሩ ሕጎች ላይ ማተኮር የለባቸውም። በእነዚህ ሰው ሠራሽ ደንቦች ላይ ብዙ አጽንኦት መስጠቱ ጠቃሚ የማይሆንባቸው አያሌ ምክንያቶች አሉ።

በእነዚህ ነገሮች ላይ ማተኮሩ ክርስቶስ ለኃጢአቶቻችን መሞቱን ሙሉ በሙሉ እንደማናምን ያሳያል። እምነታችን ለጋ መሆኑን ያሳያል። ይህም በአብዛኛው ወደ ትዕቢት ይመራል። በውጫዊ ሕጎችና ልምምዶች ላይ ማተኮራችን ዓይናችንን በክርስቶስ ላይ ተክለን ከእርሱ ጋር ኅብረት እያደረግን እንደማንመላለስ ያሳያል። እነዚህ ነገሮች ዘለቄታዊ እሴት የሌላቸውና በመንግሥተ ሰማይ የማናገኛቸው ናቸው። ሕግጋቱ እውነተኛ አምልኮን አያስከትሉም። እግዚአብሔር እንዲኖረን የሚፈልገውን ጥበብ አያሳዩም። ራሳችንን እንድንጎዳ የሚያዙንን እነዚህን ሕግጋት መጠበቁ የመንፈሳዊነት ምልክት ቢመስልም ግን አይደለም። ዋናው ክርስቶስ እንጂ ሕግጋት አይደሉም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ጋር የተሟሟቀ ግንኙነት ከመመሥረት ይልቅ ቤተ ክርስቲያናቸው በፈጠረቻቸው ውጫዊ ደንቦችና ሕግጋት ላይ እንዴት አጽንኦት እንደሚሰጡ ግለጽ። ለ) ከመንፈሳዊነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ሳይኖራቸው ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች የሚጠብቋቸውን ነገሮች፥ ሕጎችና ደንቦች ዘርዝር። (ለምሳሌ፥ ክርስቲያኖች ሊከተሉ የሚገባቸው አለባበስ፥ ወዘተ) እነዚህ ነገሮች የሚመጡት ከየት ነው? እነዚህ ሕጎች ለጋዎችና መንፈሳዊ ብስለትን የማያሳዩ የሆኑበትን ምክንያት አብራራ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ክርስቶስ ጳውሎስ የሚያስተምረው የወንጌል መልእክት እምብርት ነው (ቆላ. 1፡24-2፡5)

ኖስቲኮች ሰው ከክፉ ዓለም ለማምለጥ ሊያከናውናቸው ይገባል ከሚሏቸው ምሥጢራዊ እውነቶች በተቃራኒ፥ ጳውሎስ ግልጽ የወንጌል እውነቶችን ሰብኳል። ለመሆኑ የዚህ ወንጌል መሠረቱ ምንድን ነው?

የወንጌል ትኩረቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ጳውሎስ በዚህ ክፍል ውስጥ በሚከተሉት ነገሮች ላይ አጽንኦት ይሰጣል።

ሀ. ጳውሎስ ወንጌሉን የመስበክ ቀዳማዊ ተልዕኮ ያለው የክርስቶስ አገልጋይ ነው። ይህ ተልዕኮ መከራ መቀበልን ይጨምር ነበር። ጳውሎስ በዚህ ጊዜ ለዚሁ ወንጌል ወኅኒ ቤት ታሥሮ ነበር። በማፈር ፈንታ ጳውሎስ፥ በዚህ መከራ ደስ ይለኛል ይላል። ጳውሎስ «በሥጋዬ በክርስቶስ መከራ የጎደለውን እፈጽማለሁ» ብሏል። ይህ ለመረዳት የሚያስቸግር አገላለጽ ነው። ይህ የክርስቶስ ሞት አማኞችን ለማዳን እንደማይበቃና ሞቱ ለኃጢአታችን በቂ ይሆን ዘንድ እኛም መከራ መቀበል አለብን ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ጳውሎስ ቀደም ሲል የክርስቶስ ሞት ነገሮችን ከእግዚአብሔር ጋር እንዴት እንደሚያስታርቅ ገልጾአል። ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ስለመሆኗ የሚያስብ ይመስላል። ስለሆነም፥ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርስ ነገር ሁሉ በክርስቶስ ላይ ይደርሳል። ለዚህ ነው ክርስቶስ በሐዋርያት ሥራ 9፡4-5 ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ማሳደዱ እርሱን ማሳደድ መሆኑን የገለጸው። ይህም ማለት በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ፥ በምድር ላይ በክርስቶስ ላይ የደረሰው ዓይነት መከራ (ፈተና፥ ስደት፥ ሞት) በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ ይቀጥላል ማለት ነው። የምስራቹ ቃል ስብከት በመከራ ውስጥ ያድጋል። የክርስቶስ አካል ክፍል የሆኑ ክርስቲያኖች መከራን በሚቀበሉበት ጊዜ፥ ክርስቶስም ከእነርሱ ጋር ይሠቃያል። የጳውሎስ መታሠር በክርስቶስ ላይ ሥቃይን አስከትሏል። እኛም ለወንጌሉ በምንሠቃይበት ጊዜ ክርስቶስ አብሮን ይሠቃያል። ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ መከራችን በሙሉ ይጠናቀቃል። የእርሱም መከራ ፍጻሜን ያገኛል። በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር በልጆቹና ከዚህም የተነሣ በራሱ ላይ እንዲደርስ የፈቀደው መከራ ሁሉ ያከትማል። በዘላለሙ መንግሥት በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይም ሆነ በክርስቶስ ላይ የሚደርስ መከራ አይኖርም።

ለ. ወንጌሉ ምሥጢርን አካቷል። ሐሰተኛ አስተማሪዎች ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን የሚያስገኝ ምሥጢር እንዳላቸው ተናግረው ነበር። ጥልቅ መንፈሳዊነት የሚገኘው እነርሱ ዘንድ ብቻ እንደሆነና ልዩውን ቃል ወይም ሐረግ ሊያውቁ የሚችሉት ከእነርሱ ቡድን ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ይናገሩ ነበር። ልዩው ቃል ወይም ሐረግ የእግዚአብሔርን ተጨማሪ ሞገስ ያስገኝላቸዋል ሲሉ አስተምረዋል። ጳውሎስ ግን አንድ ጠቃሚ ምሥጢር ብቻ እንዳለ ያስረዳል። ይኸውም የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ነው። ይህ ወንጌል ለጥቂቶች ብቻ የተሰጠ ምሥጢር ሳይሆን ለሰዎች ሁሉ እየተሰበከ ያለው ነበር። ምሥጢሩ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ዘመን ያልገለጠውና አሁን ግን ለሕዝቡ ሁሉ ያስታወቀው ነበር። ይህ ምሥጢር ምን ነበር? ምሥጢሩ አሕዛብ በክርስቶስ በማመን በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ሙሉ ተቀባይነት ማግኘታቸው ነበር። ይህ ወንጌል በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያተኩራል። እርሱም በሕዝቡ ልብ ውስጥ የሚያድር አምላክ ነው።

ሐ. ለሰዎች የሚያስፈልገው ብቸኛ ‹ጥበብ› ይኼ ወንጌል ብቻ ነው። የዓለም ጥበብ ወይም የኖስቲኮች ስውር ፍልስፍናዎች አያስፈልጉንም። ሁሉም ሰው ወንጌሉን ተረድቶ በሚቀበልበት ጊዜ ምሉዕ ይሆናል። («ፍጹም» የሚለው ቃል ምሉዕነትን እንጂ ኃጢአት አልባነትን አያመለክትም።)

መ. ይህ ወንጌል ጠቃሚ በመሆኑ ጳውሎስ በሙሉ ኃይሉ አሰራጭቶታል። ለዚሁ ወንጌል እስከ መታሠርም ደርሷል። ጳውሎስ መከራን የተቀበለው ለራሱ ወይም ለሚያውቃቸው አብያተ ክርስቲያናት ብቻ አልነበረም። ምንም እንኳ ለቆላስይስ የቅርብ ከተማ የነበረችውን ሎዶቅያን ጎብኝቶ ባያውቅም፥ መከራው ለእነርሱ ጥቅም ነበር። የጳውሎስ መከራን መቀበል ዛሬ ላለን ሰዎች ጥቅም አለው። ምክንያቱም በጳውሎስ መከራና በሰበከው ወንጌል አማካኝነት አሕዛብ የሆንን ሰዎች ድነት (ደኅንነትን) አግኝተናል። ጳውሎስ እሥር ቤት ውስጥ ሆኖ የጻፋቸው መልእክቶችም እጅግ ጠቅመውናል።

ምንም እንኳን ጳውሎስ ውጤታማ ወንጌላዊና ሐዋርያ ቢሆንም፥ ስለምንም ነገር መመካት እንደሌለበት ያውቅ ነበር። ያገኛቸው ውጤቶችና ክንውኖች ክርስቶስ በእርሱ በኩል የመሥራቱ ውጤቶች እንደነበሩ ያውቅ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ሁላችንም ለወንጌሉ መከራን እንድንቀበል እንዳቀደ ተገልጾአል። ሀ) ለወንጌሉ መከራ እየተቀበልህ ያለኸው እንዴት ነው? ለ) አንዳንድ ክርስቲያኖች ከመከራ ለመሸሽና ለወንጌሉ መከራን ላለመቀበል የሚፈተኑት እንዴት ነው? ሐ) የክርስቶስ መከራ ተካፋይ መሆን ክብር የሚሆነው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ክርስቶስ ከተፈጠሩት ነገሮች ሁሉ የበለጠና እንደ እግዚአብሔር አብ ያለ አምላክ ነው (ቆላ. 1፡15-23)

ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች እንደ ፈውስ፥ በልሳን መናገር፥ ቁሳዊ ሀብት፥ መንፈሳዊ ያደርጉናል ብለው በሚያስቧቸው መንፈሳዊ ነገሮች ላይ ሲያተኩሩ፥ ወይም በሐሰት ትምህርት ሲወሰዱ ምን ይከሰታል? በዚህ ጊዜ ክርስቶስን ሳይሆን ሰዎችን (ራሳቸውን ወይም ሌሎች)፥ ወይም የዓለምን ነገሮች ይመለከታሉ። የቆላስይስ ክርስቲያኖች አንዳንድ ስዎች ጠቃሚዎች ናቸው ያሏቸውን ነገሮች ይመለከቱ ነበር። አንዳንዶች የተወሰኑ ሕግጋትን ወይም ደንቦችን መጠበቃቸው ወሳኝ እንደሆነ ይነግሯቸዋል። ሌሎች ደግሞ ሊያውቁት የሚገባቸው ልዩ መንፈሳዊ ምሥጢር እንዳለ ይነግሯቸዋል። የቆላስይስ አማኞች እነዚህን ሁሉ የሐሰት ትምህርቶች እያደመጡ ክርስቶስን ከመመልከት ታቀቡ። የመንፈሳዊ ሕይወታችን ሚዛን የሚጠበቀው እርሱን ብቻ ለመምሰልና ለማስከበር በማሰብ ወደ ክርስቶስ የተመለከትን እንደሆነ ነው። የቆላስይስ ክርስቲያኖች በቀጥታ ከሐሰተኛ መምህራን ስለተማሩና በተዘዋዋሪ ደግሞ ጠቃሚ ባልሆኑ ነገሮች ላይ ማተኮር ስለጀመሩ፥ ክርስቶስን እንደሚገባቸው ሊያከብሩት አልቻሉም ነበር። ስለሆነም ጳውሎስ በሕይወታቸው ዋናው ነገር ክርስቶስ እንደሆነ ያስተምራቸዋል።

ክርስቶስ ምን ያህል ታላቅ ነው? ኖስቲኮች ወይም የይሖዋ ምስክሮች እንደሚያስተምሩት ከእግዚአብሔር ያነሰ አምላክ ነውን? ወይስ ከእግዚአብሔር አብ የተለየና እኩል የሆነ የሥላሴ አካል ነው? ጳውሎስ ክርስቶስ ከአብ ጋር እኩል እንጂ የማይተናነስ መሆኑን ያስረዳል።

ጳውሎስ የሚገልጻቸውን ነገሮች ቀጥለን እንመልከት።

ሀ. ክርስቶስ የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው። ጳውሎስ በዚህ ዐረፍተ ነገር ሁለት ዐበይት እውነቶችን ያስተላልፋል። በመጀመሪያ፥ ወልድ ከአብ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ያስረዳል። ከእግዚአብሔር አብ ጋር የመንትያ ዓይነት ተመሳሳይነት አለው ልንል እንችላለን። (ከዕብራውያን 1፡3 ተመሳሳይ አገላለጽ መመልከት ይቻላል።) ኢየሱስን ማየት እግዚአብሔር አብን እንደ ማየት ነው ( ዮሐ 14፡9)። ሁለቱም በባሕርይ፥ በኃይል፥ በአሳብ፥ በስልጣን ተመሳሳይ ናቸው። ሁለተኛ፥ ጳውሎስ ምንም እንኳን አብ ለሰዎች ባይታይም ወልድ የሚታይ መሆኑን ያስረዳል። ስለሆነም የሚታየውን ክርስቶስን መመልከት የማይታየውን እግዚአብሔርን እንደ ማየት ነው። ከውስን ሰብአዊ እይታችን የተነሣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ክርስቶስ በምናነብበት ጊዜ የቀድሞዎቹ ሐዋርያትም በተመለከቱት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል በግልጽ እንረዳለን (ዮሐ. 1፡18፥ 14፡9)።

ለ. ኢየሱስ የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው። «በኩር» የሚለውን ቃል መረዳት ያለብን ዛሬ ቃሉን በምንገነዘብበት መልኩ ሳይሆን አይሁዶች በሚረዱበት መንገድ ሊሆን ይገባል። የይሖዋ ምስክሮች ይህን ጥቅስ በመጠቀም ኢየሱስ የመጀመሪያው የእግዚአብሔር ፍጥረት እንደሆነና በዚህም ምክንያት ከአብ እንደሚያንስ ያስተምራሉ። ነገር ግን ይሄ ቃል የመጣው ከብሉይ ኪዳን ነው። በአይሁድ ባሕል በኩር የሚለው ቃል ልዩ የክብር ስፍራ ማግኘትን ያሳያል። በቤተሰብ ውስጥ ልዩ ክብር የሚያገኘው መጀመሪያ የተወለደው ልጅ ነበር። እስራኤል የእግዚአብሔር በኩር ተብላ ትጠራ ነበር። ይህም ከሌሎች የዓለም አገሮች የተለየ ስፍራ እንደነበራት ያመለክታል (ዘጸ. 4፡22)። የእሰይ የመጀመሪያ ልጅ ያልነበረው ዳዊት ከሌሎቹ አይሁዶች የተለየ የክብር ስፍራ ስለነበረው በኩር ተብሏል (መዝ 89፡27)። ጳውሎስ ኢየሱስ የፍጥረት ሁሉ ገዢና የበላይ መሆኑን ለማሳየት ይፈልጋል። እርሱ ከፍጥረት ሁሉ የቀደመ ስፍራ አለው። ታላቅነቱም የፍጥረት ሁሉ ጀማሪ በመሆኑ ተረጋግጧል።

ሐ. ክርስቶስ የተፈጠረው ነገር ሁሉ ምንጭ ነው፡፡ በሰማይ የመላዕክት በምድር ደግሞ የእንስሳት፥ የዕፅዋትና የሰዎች ምንጭ ነው። እርሱ ሰዎች የሚያዩዋቸውንና የማያይዋቸውን ነገሮች የፈጠረ አምላክ ነው። እዚህ ላይ አንዳንድ ክርስቲያኖች ጳውሎስ የኖስቲኮችን አስተሳሰብ በመሠረታዊነት እየተጠቀመ ነው ይላሉ። ኖስቲኮች ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ስለ አማላጆች ወይም ትናንሽ አማልእክት ያስተምር ነበር። እነዚህንም አማልእክት «ጌትነት፥ አለቅነት፥ ሥልጣናት» ሲሉ ይገልጻሉ። ጳውሎስ እንደዚህ ዓይነት ትናንሽ አማልእክት አሉ ብሎ አያምንም። ቢኖሩ እንኳ በክርስቶስ የተፈጠሩ ስለሚሆኑ ከክርስቶስ ማነሳቸው አይቀርም። ነገር ግን ጳውሎስ እነዚህን ቃላት የተጠቀመው ስለ መላዕክት ለመናገር ይመስላል። ሰብአዊ ሠራዊቶች የሥልጣን ደረጃ (ኮሎኔል፥ ጄኔራል፥ ወዘተ.) እንዳላቸው ሁሉ፥ የእግዚአብሔር መላዕክትም የሥልጣን ደረጃዎች አሉዋቸው። እነዚህንም ጳውሎስ ዙፋናት፥ ኃይላት፥ ጌትነትና ሥልጣናት ሲል ይገልጻል። ነገር ግን መላዕክት ምንም ያህል ታላቅ ቢሆኑም ክርስቶስ ፈጣሪያቸው በመሆኑ ይበልጣቸዋል።

መ. ክርስቶስ ከፍጥረት ሁሉ ቀዳሚ ነው። ዮሐንስ 1፡1 ክርስቶስ ሁልጊዜም ከእግዚአብሔር ጋር የኖረ ዘላለማዊ አምላክ እንደሆነ ተገልጾአል። ስለሆነም ከማንኛውም ነገር በፊት እርሱ ነበር።

ሠ. ፍጥረታትን ሁሉ ያያያዘው ክርስቶስ ነው። ክርስቶስ ሁሉን ነገር መፍጠር ብቻ ሳይሆን እንዳይጠፋም ይጠብቃል። አንድ መካኒክ መኪና አገልግሎት መስጠቷን እንድትቀጥል እንደሚያደርግ ሁሉ ክርስቶስ ዓለም ጉዞዋን እንድትቀጥል ያስችላታል።

ረ. ክርስቶስ አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው። እርሱ የቤተ ክርስቲያን መሪና ጠባቂ ነው። ክርስቶስ በቤተ ክርስቲያን ላይ ሙሉ ሥልጣን አለው።

ሰ. ክርስቶስ ከሙታን በኩር ነው። መጀመሪያ በአዲስ የትንሣኤ አካል ከሞት የተነሣው እርሱ ነው። በሙታንም ላይ ሥልጣን ያለው እርሱ ነው። ሙታንን ከሞት የሚያስነሣቸውም እርሱ ነው።

ሽ. ክርስቶስ የእግዚአብሔር ሙላት ሁሉ አለው። ጳውሎስ ይህን ሲል ክርስቶስ የእግዚአብሔር ባሕሪያት፥ ኃይላት፥ ሥልጣን፥ ችሎታ፥ ወዘተ… እንዳሉት መግለጹ ነው። እግዚአብሔር ያለው ሁሉ ክርስቶስም አለው። አንዳንድ ኖስቲኮች ያስተምሩ እንደነበረው እርሱ ከትናንሽ አማልእክት አንዱ አልነበረም።

ቀ. ክርስቶስ የእግዚአብሔር ዕቅዶች ፍጻሜ ነው። ጳውሎስ እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል የሚፈጽማቸው ሁለት ዓላማዎች እንደ ነበሩት ይናገራል። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ የበላይ ይሆናል። ይህም ክርስቶስ የነገሮች ሁሉ ገዢና ጌታ እንደሚሆን ያሳያል። በፊልጵስዩስ 2፡10-11 አንድ ቀን በሰማይና በምድር የሚኖሩ ፍጥረታት ሁሉ በክርስቶስ ፊት ተንበርክከው እንደሚሰግዱና እንደሚያከብሩት እንመለከታለን። ሁለተኛ፥ ክርስቶስ በሰማይና በምድር ያሉትን ነገሮች ለማስታረቅ የእግዚአብሔር መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። ሰይጣንና የሰው ልጆች በኃጢአት መውደቃቸው በሰማይና በምድር ላይ ተጽዕኖ አስከትሏል። እግዚአብሔር በኃጢአት ምክንያት በፍጥረታት ላይ የደረሰውን ይህንኑ መለያየት ለማስወገድ ክርስቶስን ለመሣሪያነት ተጠቅሟል። በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት ምክንያት ዕርቅ በመርሕ ደረጃ ተከናውኗል። ኖስቲኮች እንደሚያስተምሩት የክርስቶስ ሰብአዊ አካል ክፉ ሳይሆን ስረከት ነበር። እግዚአብሔር የነገሮችን የመጨረሻ ዕርቅ ተግባራዊ ለማድረግ ክርስቶስን ይጠቀማል።

ከዚያም ጳውሎስ ይህ የዕርቅ ሥራ በቆላስይስ ክርስቲያኖች ላይ እንዴት ተጽዕኖ እንደሚያስከትል ያብራራል። የተመረጠው የእግዚአብሔር ሕዝብ አካል ባለመሆናቸው ምክንያት አሕዛብ፥ ከእግዚአብሔር መንፈሳዊ በረከቶች ሁሉ የራቁ ነበሩ። አሕዛብ በአስተሳሰባቸውና በተግባራቸው በእግዚአብሔር ላይ ያምፁ ነበር። ነገር ግን ከክርስቶስ አካላዊ ሰውነትና በመስቀል ላይ ከመሞቱ የተነሣ የሚያምኑ አሕዛብ በእግዚአብሔር ፊት ቅዱሳን፥ እንከን የሌላቸውና ከክስ የነፁ ነበሩ። ነገር ግን ጳውሎስ የቆላስይስ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ፍርድ በሚያስከትሉ የስሕተት ትምህርቶችና ተግባራት እንዳይጠመዱ ያስጠነቅቃቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቶስ ማን እንደሆነና ምን እንዳደረገልን በግልጽ መረዳቱ ጠቃሚ የሚሆንባቸውን ምክንያቶች ዘርዝር። ለ) ስለ ክርስቶስ የተገለጹ ዘጠኝ ነጥቦች እያንዳንዳቸው ዛሬ በሕይወታችን ላይ እንዴት ተጽዕኖ እንደሚያስከትሉ ግለጽ። ለእያንዳንዱ ነጥብ አንድ ምሳሌ ልጥ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ጳውሎስ ስለ ቆላስይስ ክርስቲያኖች ያቀረበው ምስጋናና ጸሎት (ቆላ. 1፡1-14)

«ይህ ታላቅ ጀማ ስብከት ወንጌል እንዳያመልጥዎ። በጉባኤው ላይ ታላቅ የፈውስ አገልጋይ ይጋበዛል። ማንኛውም ዓይነት በሽታ ያለበት ሰው ከበሽታው ይፈወሳል»። «ይህ ከአያት ቅድማያቶቻችን ያገኘነው ሃይማኖት ነው። ስለሆነም እንከተለዋለን።» «ዶ/ር እገሌ ሦስት ዲግሪዎች ያሉት ዝነኛ የዩኒቨርስቲ ሌክቸረር ነው። ትምህርቱን መስማት አለብን።»

ዓለም ቀልባችንን በሚስቡ ድምፆች የተሞላች ነች። ሁሉም እንድንሰማቸው ይፈልጋሉ። «እኛ ምሥጢር አለንና። እኛ ጥሩውንና ትክክለኛውን እናውቃለን» ይሉናል። ከላይ የተጠቀሱት ሕይወታችንን ለመለወጥና ችግሮቻችንን ለመፍታት ያስችላሉ ስለተባሉ መረጃዎች የሚናገሩ የዓለም ድምፆች ምሳሌዎች ናቸው። ኮሚኒዝም፥ ካፒታሊዝም፥ ዲሞክራሲ፥ ዝግመተ ለውጥ (ኢቮሉሽን)፥ እንዴት ሀብታም መሆን እንደሚቻል፥ እያለ ዝርዝሩ ይቀጥላል ። በእግዚአብሔር ቃል ሥር ላልሰደደ ክርስቲያን እነዚህ የዓለም ድምፆች ብዙ ግራ መጋባትን ሊፈጥሩ ይችላሉ። ብዙ ክርስቲያኖች ወደ ዩኒቨርስቲ ገብተው እግዚአብሔርን ከማያውቁ ፕሮፌሰሮች ጋር በሚፋጠጡበት ጊዜ እምነታቸውን ያጣሉ። ትምህርታቸው መልካምና ትክክለኛ ይመስላል። በመጨረሻ ግን ባአቸውን ይቀራሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ክርስቲያኖች መልካም በሚመስሉ ፍልስፍናዎችና ትምህርቶች ሲወሰዱ የተመለከትኸው እንዴት ነው?

የቆላስይስ ክርስቲያኖች በአካባቢያቸው የነበሩትን የአንዳንድ ታላላቅ መምህራን ትምህርቶች ይሰሙ ነበር። የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን ለማስከበር የሚጥሩ አይሁዶችና ክፉ ቁሳዊ ባሕርያችንን ለማሸነፍ የሚያስችል ልዩ ምሥጢራዊ እውቀት አለን የሚሉ ግሪኮች ድምፆቻቸውን ከፍ አድርገው ይጮኹ ነበር። ይህ ክርስቲያኖቹን ግራ አጋባቸው። ለዚህ ችግር መፍትሔው ምን ነበር? እነዚህን ከዓለም የሚመጡ ተቃራኒ ድምፆች እንዴት መከላከል ይቻላል? ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ግልጽ ግንዛቤ በመጨበጥ እነዚህኑ ትምህርቶች መከላከል እንደሚቻል ያምናል። ክርስቶስ ማን ነው? ክርስቶስ በፊት፥ አሁንና ወደፊት በሕይወቴ ላይ ለውጥን የሚያስከትለው እንዴ ነው? ጳውሎስ አስፈላጊ ናቸው ብሎ ያመነባቸው ጥያቄዎች እነዚህ ብቻ ነበሩ። ሌሎች ትምህርቶች ሁሉ በክርስቶስና በክርስቶስ ላይ ባለን እምነት ላይ ተመሥርተን የምንገመግማቸው ናቸው። ጳውሎስ የቆላስይስን እማኞች ለሳቡት አወዛጋቢ ፍልስፍናዎች የሰጠው ምላሽ ክርስቶስን ማመልከትና እርሱ ብቻ የእውነት እስኳል የሆነበትን ምክንያት በዝርዝር ማብራራት ነበር።

የፈውስ አገልጋይ ወይም የአባቶቻችን እምነት የእምነታችን መሠረት ሊሆን አይችልም። ብዙ ዲግሪዎችን መሰብሰብ አንድን ሰው ከመሳሳት ነጻ አያደርገውም። እውነትን የምንገመግመው በክርስቶስና ከእርሱ ጋር ባለን ግንኙነት ላይ ተመሥርተን ነው። እግዚአብሔርም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሕተት የሌለው እውቀት ሰጥቶናል። ይህም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያስተላለፈው መልእክት ነው።

 1. ጳውሎስ ስለ ቆላስይስ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን ያመሰግናል (ቆላ.1፡1-8)።

የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሕይወታቸው ውስጥ ስለሚታይ መንፈሳዊ እድገትና ደህና አድርገው ለሚያከናውኗቸው ተግባራት ምእመኖቻቸውን ማመስገን ይኖርባቸዋል። ይህ ሰዎችን በማበረታታት በእድገታቸው እንዲገፉ ያግዛቸዋል። ብዙውን ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ምእመኖቻቸውን በመውቀስ ነው። በመንፈሳዊ ሕይወታችሁ አልተነቃቃችሁም፤ ከጸሎት ስብሰባ ቀርታችኋል ሲሉ ያማርራሉ። አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባላት ወደ ቤተ ክርስቲያን በሚመጡበት ጊዜ መሪዎች የሚሰነዝሩት ትችትና ጩኸት ያሰለቻቸዋል። ጳውሎስ እንደ ገላትያ ቤተ ክርስቲያንን ሊያወድም የደረሰ ሁኔታ እስካላጋጠመው ድረስ ብዙውን ጊዜ መልእክቱን የሚጀምረው ጠንካራ ጎኖቻቸውን በማመስገን ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ብዙውን ጊዜ ለምእመኖቻቸው አሉታዊ አመለካከት ስለሚይዙበት ሁኔታ አብራራ። ምእመናን ሁልጊዜም መሳሳታቸው ብቻ ሲነገራቸውና ለምንም ነገር ምስጋና ሳይቀርብላቸው ሲቀር ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጣሉ? ለ) ስለ ቤተ ክርስቲያንህና ስለ ቤተ ክርስቲያንህ መሪዎች እግዚአብሔርን የምታመሰግንባቸውን አሥር ነገሮች ዝርዝር። አሁን ስለ እነዚህ ነገሮች እግዚአብሔርን በማመስገን ጸልይ። በዚህ ሳምንት ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምስጋናህን የምታቀርብበትን አጋጣሚ ፈልግ።

ራሱን ሐዋርያው ጳውሎስ ነኝ ሲል ካስተዋወቀና ለቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ ካቀረበ በኋላ፥ ጳውሎስ ስለ ቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን የሰጣቸውን ሦስት ነገሮች ይዘረዝራል። ጳውሎስ የቆላስይስን ቤተ ክርስቲያን ጎብኝቶ ስለማያውቅ እነዚህን ነገሮች የሰማው ከሥራ አጋሩና ምናልባትም በቆላስይስ ካገለገለው ከኤጳፍራ ሳይሆን አይቀርም።

ሀ. ጳውሎስ በክርስቶስ ላይ ስላላቸው እምነት እግዚአብሔርን ያመሰግናል። ይህም ድነት (ደኅንነትን) ያገኙበት እምነት ብቻ ሳይሆን፥ ክርስቶስ ለችግሮቻቸው መፍትሔ እንደሆነ በማመን የሕይወታቸው ቀዳሚ አጀንዳ አድርገው እንዲከተሉት አስችሏቸዋል።

ለ. ጳውሎስ ለቅዱሳን ሁሉ ስላላቸው ፍቅር ያመሰግናቸዋል። የሚገባትን ያህል ፍቅርና አንድነት ልታሳይ ካልቻለችው የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን በተቃራኒ የቆላስይስ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ይዋደዱ ነበር። ፍቅራቸውም ራስን በመንከባከብና በመርዳት ላይ የተመሠረተ የራስ ወዳድነትን ፍቅር አልነበረም። ጳውሎስ ፍቅራቸው አይተው ለማያውቋቸው ክርስቲያኖች ጭምር እንደደረሰ ይነግራቸዋል።

ሐ. ጳውሎስ በሰማይ ስለተዘጋጀላቸው ተስፋ እግዚአብሔርን ያመሰግናል። የቆላስይስ ክርስቲያኖች ዓይኖቻቸውንና ልቦቻቸውን ያሳረፉት በሰማይ እንጂ በምድራዊ ሁኔታዎች ላይ አልነበረም። እነዚህ ሰዎች የክርስቶስን ምጽአት ይናፍቁ ነበር። ለክብሩ ከኖሩ እንደሚሸልማቸው በመገንዘብ ለክርስቶስ ይሠሩ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡– እምነት፥ ተስፋና ፍቅር የሚሉ ሦስት ቃላት በዓለም ውስጥ የሚሰበከውን ወንጌል ጠቅለል አድርገው ይገልጻሉ። ሀ) እነዚህ ሦስት ቃላት ወንጌሉን፥ ከእግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር የሚኖረንን ግንኙነትና ሕይወታችንን የምንመራበትን ሁኔታ ጠቅለል አድርገው የሚገልጹት እንዴት ነው? ለ) እነዚህ ሦስቱ ቃላት በሕይወትህ ውስጥ እንዴት እየተገለጡ እንደሆነ አብራራ።

 1. ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ይጸልያል (ቆላ. 1፡9-14)።

ብዙውን ጊዜ የምንጸልየው በአካል ለምናውቃቸው ሰዎች ነው። ጳውሎስ ግን በአካል ላልተገናኛቸውም ሰዎች መጸለዩ ተገቢ እንደሆነ ተገንዝቧል። በዚህ መንገድ በመንፈሳዊ እድገታቸውና አገልግሎታቸው ውስጥ ሊሳተፍ ይችል ነበር። ጳውሎስ በአካል ለሚያውቋቸው ለእነዚህ ክርስቲያኖች ስለምን ለመጸለይ እንደ ፈለገ መመልከቱ ጠቃሚ ነው።

ሀ. እግዚአብሔር ጥበብንና መንፈሳዊ ማስተዋልን በመስጠት በፈቃዱ እውቀት እንዲሞላቸው ይጸልያል። እነዚህ ክርስቲያኖች ከክርስቶስ በሚያርቋቸው እርባና ቢስ ፍልስፍናዎች ግራ ተጋብተው ነበር። ስለሆነም ጳውሎስ እግዚአብሔር በትክክለኛ እውቀት እንዲሞላቸው ይጸልያል። ጳውሎስ እግዚአብሔር ለእነዚህ ክርስቲያኖች ምን ማመን፥ እንዴት መኖር እንዳለባቸው እንዲያውቁ ከእግዚአብሔር የሆነውንና ከከንቱ ፍልስፍና መለየት፥ ጊዜያዊውንና ዘላለማዊውን ማገናዘብ እንዲችሉ እንዲያግዛቸው ይፈልጋል።

ለ. ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በማወቃቸው፥ አማኞቹ ለጌታ እንደሚገባ እንዲኖሩና በሁሉም ነገር እንዲያስከብሩት ይጠይቃቸዋል። እውነቱን ማወቅ ብቻ አይበቃም። እውነት የተሰጠው አኗኗራችንን ለመለወጥ ነው። ትክክለኛ ነገሮችን ስናስብና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ስናውቅ እግዚአብሔር እንደሚፈልገው እንኖር ዘንድ ሕይወታችንን እናስተካክላለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሳናውቅ በእግዚአብሔር መንገድ ላይ ልንመላለስ አንችልም። ነገር ግን አእምሯችን ዓለም መልካም ናቸው በምትላቸው ነገሮች ተሞልቶ ከእውነት ያርቀናል።

ሐ. ጳውሎስ ኃይልን ሁሉ ይሞሉ ዘንድ ይጸልያል። እውነቱን ብናውቅም ይህንኑ ሕይወት የምንኖርበትን ኃይል ልናጣ እንችላለን። የውስጡ ሰውነታችን ደካማ በመሆኑ ለራስ ወዳድነትና ኃጢአት ያዘነበለ ነው። ስለሆነም ጳውሎስ የቆላስይስ ክርስቲያኖች እንደሚገባቸው ለመኖር የእግዚአብሔርን ኃይል ይላበሱ ዘንድ ይጸልይላቸዋል። ይህ ኃይል ትዕግሥትን፥ ጽናትንና ደስታን ይሰጣቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህን ጸሎት ለራስህ፥ ለቤተ ከርስቲያንህ ምእመናንና ለቤተ እምነትህ አባላት ብትጸልይ፥ ምን ለውጥ የሚከሠት ይመስልሃል? ለ) የጳውሎስን ጸሎት ብዙውን ጊዜ ለራሳችንና ለሌሎች ከምንጸልየው ጸሎት ጋር አነጻጽር። የጳውሎስ የጸሎት ጥያቄዎች እኛ ብዙውን ጊዜ ከምንጸልይባቸው ጉዳዮች እንዴት እንደሚሻሉ እብራራ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የቆላስይስ መጽሐፍ ዓላማ፣ ልዩ ባሕሪያት፣ መዋቅርና አስተዋጽኦ

፩. የቆላስይስ መጽሐፍ ዓላማ

የመጀመሪያው ዓላማ፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የተነሣውን የሐሰት ትምህርት መመከት። ጳውሎስ በኤፌሶን ካገለገለ ስምንት ዓመታት ያህል አልፈዋል። በዚህ ጊዜ በቆላስይስ ክርስቲያኖች እምነት ውስጥ መጠነኛ ለውጥ ተከስቷል። በክርስቶስ ላይ የነበራቸውን እምነት ባይክዱም፥ የይሁዲና በትንሹ እስያ የተለመዱ ፍልስፍናዎችን የቀየጡበት ይመስላል። ይህ የሌሎችን እምነቶች የመጨመር ተግባር ወንጌሉን ስለሚለውጥ አደገኛ ነው። ይህም የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የይሁዲነት እምነቶችን ከእምነቷ ላይ ከጨመረችበትና ብዙ የአፍሪካ ሃይማኖቶች በክርስትና እምነታቸው ላይ የአያት ቅድማያት ወይም የጥንቆላ ትምህርቶችን ከሚጨምሩበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው። የቆላስይስ አማኞች በእነዚህ ትምህርቶች ባይወሰዱም፥ ለቤተ ክርስቲያን አደገኛ ሊሆኑ የሚችሉትን ትምህርቶች መቀበል ጀምረው ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ የብዙ ሰዎች እምነት ከመበከሉ በፊት ይህንን የሐሰት ትምህርት መከላከሉ አስፈላጊ መሆኑን ተገነዘበ።

ጳውሎስ፥ ኤፌሶንን ከለቀቀ በኋላ ለሚከተሉት ስምንት ዓመታት፥ ሁለት ዓባይት የሐሰት ትምህርት ቡድኖች ቆላስይስን ሲያውኩ ነበር። ይህም የቆላስይስን ክርስቲያኖች ግራ አጋባቸው። የሐሰት አሰተማሪዎቹ የሚናገሩት ቀደም ሲል ጳውሎስ ያስተማረውን ዓይነት ትምህርት እንዳልሆነ ቢያውቁም እውነተኛው የትኛው እንደሆነ ለመረዳት አልቻሉም። በመሆኑም፥ አማኞቹ ስለዚህ ጉዳይ ከጳውሎስ ጋር እንዲነጋገር መሪያቸው የነበረውን ኤጳፍራን ወደ ሮም የሰደዱት ይመስላል። ጳውሎስም ሆነ ኤጳፍራ ወደ ቆላስይስ ተመልሰው የሐሰት ትምህርቱን በአካል ሊከላከሉ ስላልቻሉ፥ ጳውሎስ ይህንን መልእክት ለመጻፍ ተገደደ።

የቆላስይስን ቤተ ክርስቲያን ያውኩ የነበሩ የሐሰት ትምህርቶች ምን ምን ነበሩ? ጳውሎስ እነዚህን ትምህርቶች በስማቸው ባይጠቅስም አንዳንድ ትምህርቶቻቸውን ግን ገልጾአል። ጳውሎስ በዚህ መልእክቱ ሁለት ዓይነት የሐሰት ትምህርቶችን የሚጠቅስ ይመስላል። .

 1. ክርስቲያኖች የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን እንዲከተሉ የፈለጉ አይሁዶች። ጳውሎስ እነዚህ አይሁዶች እንደ ምግብ፥ መጠጥ፥ የበዓል ቀናትን በመሳሰሉ ውጫዊ ደንቦች ላይ ያተኩሩ እንደነበረ ገልጾአል (ቆላ. 2፡16-17)። በግርዘት ላይም እንዲሁ አጽንኦት ይሰጡ ነበር (ቆላ. 2፡11)።
 2. የቀድሞውን የኖስቲሲዝም ትምህርት ይከተሉ የነበሩ አሕዛብ። ጳውሎስ የገለጻቸው የዚህ ፍልስፍና ትምህርቶች የሚከተሉትን ነገሮች ያካትታሉ።

ሀ. ከዓለም ነገሮች መራቅ (ቆላ. 2፡21-23)

ለ. መላእክትን ማምለክ (ቆላ. 2፡18)

ሐ. ክርስቶስ ፍጹም አምላክ እንዳልሆነ መገንዘብ (ቆላ. 1፡15-20፥2፡2-3፥ 9)

መ. መንፈሳዊ ሕይወት በሆነ ምሥጢራዊ እውቀት እንደሚገኝ የሚያስረዱ ትምህርቶች (ቆላ. 2፡18)

ሠ. በሰብአዊ ጥበብና ልማድ ላይ ማተኮር (ቆላ. 2፡4፥8)

ምሁራን የቆላስይስና የ1ኛ ዮሐንስ መልእክቶች ምን ያህል ኖስቲሲዝም ከተባለ የሐሰት ትምህርት ጋር እንደሚዛመዱ ይከራከራሉ። ኖስቲሲዝም ሐሰተኛ ትምህርት መሆኑ የታወቀው ከጳውሎስ ዘመን ከ100 ዓመታት በኋላ ነበር። ነገር ግን የኖስቲሲዝም መሠረታዊ ገጽታዎች የሆኑ አንዳንድ ነገሮች በጳውሎስና በዮሐንስ ዘመንም የነበሩ ይመስላል።

ኖስቲሲዝም የሚለው የግሪክ ቃል እውቀትን ያመለክታል። ይህም ለድነት (ደኅንነት) ልዩ እውቀት አስፈላጊ መሆኑን ያስተምራል። ይህ የሐሰት ትምህርት ሦስት ዐበይት ነገሮችን ያካትታል። እነዚህም፥ ሀ) የተፈጠረው ነገር ሁሉ ክፉ ነው። ለ) በክፉው ዓለምና በተቀደሰው አምላክ መሀል ምልጃን የሚያካሂዱ እንደ መላእክት ያሉ ልዩ ፍጥረታት አሉ። ሐ) ሰው የሚድነው በራሱ ልዩ እውቀት ነው የሚሉ ነበሩ።

ኖስቲኮች በእግዚአብሔርና በተፈጠረው ቁሳዊ ዓለም መካከል ብዙ ርቀት እንዳለ ያምናሉ። እግዚአብሔር ይህን ክፉ ዓለም አልፈጠረውም ይላሉ። ከዓለም ጋርም ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ግንኙነት እያደርግም ሲሉ ያስተምራሉ። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ሥራ ብዙ የመንፈሳዊ ፍጥረታት (መላእክት ወይም ትናንሽ አማልክት) ደረጃዎች እንዳሉና ከሁሉም አነስተኛ የሆነው መለኮታዊ አካል ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ ዓለምን እንደፈጠረ ያምናሉ። ስለሆነም ዓለምና በውስጧ ያለው ሁሉ ክፉ እንደሆኑ ያስባሉ። ሰው የዚህ ክፉ ዓለም አካል ነው። አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ «ዙፋናት፥ ጌትነት፥ አለቅነት፥ ሥልጣናት» ሲል እነዚህኑ መለኮታዊ አካላትን ማመልከቱ ነው ይላሉ (ቆላ. 1፡16፥ 2፡9፥ 15)።

ስለሆነም ኖስቲኮች ዓለምን ለሁለት ይከፍሏታል። የሚታየው የተፈጠረ ዓለም ክፉ ነው ይላሉ። መልካም የሆነው የመናፍስት ዓለም እንደሆነ ያምናሉ። የሰው ልጅ ከዚህ ክፉ የተፈጠረ ዓለም ወጥቶ ወደ መናፍስት ዓለም ሊገባ የሚችለው የግለሰቡ ነፍስ የመለኮታዊ ሕይወትን ብልጭታ ካገኘች ነው ይላሉ። ይህም የሚሆነው ሰውየው ልዩ ምሥጢራዊ እውቀት ሲያገኝ ነው። ይህ ምሁራዊ እውቀት አልነበረም። ነገር ግን ይህ አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ለማድረግ በሚሞክርበት ጊዜ የሚማረው እንደ ልዩ ስም ወይም ዜማ ያለ ነገር ነው። እንዲህ ዓይነት ልዩ እውቀት ያላቸው ሰዎች የምሥጢራዊ ማኅበራት አካል ነበሩ።

ኖስቲሲዝም በክርስትና ላይ በተጨመረ ጊዜ ትምህርቶቹ የወንጌልን እምነት በብዙ መንገዶች ጎድተዋል።

በመጀመሪያ፥ የክርስቶስን ደረጃ ዝቅ በማድረግ ሰዎች ከዚህ ክፉ ዓለም እንዲላቀቁ መንገድ እንደከፈተ አነስተኛ አምላክ ገልጾታል። ኖስቲኮች ክርስቶስ ከእግዚአብሔር አብና ከሌሎች ታላላቅ መንፈሳዊ አካላት ጋር እኩል እንዳልሆነ ያምናሉ። በእነርሱ ግምት እርሱ ከታናናሾቹ መለኮታዊ አካላት አንዱ ነው። ነገር ግን ክርስቶስ ዓለምን የፈጠሯት አነስተኛ አማልእክት የነበሯቸውን ዓይነት ክፉ ባሕርይ እንዳልያዘ ያስተምራሉ። ኖስቲኮች ክርስቶስ እውነተኛ ሰው ሆኖ እንደማያውቅ ይናገራሉ። ይህ ክፉ ያደርገው ነበር ይላሉ። ልክ እንደ መንፈስ ሰው መስሎ ታየ እንጂ እውነተኛ ሰው አልሆነም ይላሉ። አንዳንድ ኖስቲኮች ደግሞ የመለኮታዊ ክርስቶስ መንፈስ በጥምቀቱ ጊዜ ኢየሱስ በተባለው ሰው ላይ እንዳረፈና ከእምነቱ በፊት እንደተለየው ያስተምራሉ። ጳውሎስ ለዚህ ምላሽ ሲሰጥ ክርስቶስ ፍጹም አምላክና ከእግዚአብሔር አብ ጋር እኩል እንደሆነ አስረድቷል። ክርስቶስ ፍጹም ሰው እንደሆነም ገልጾአል (ቆላ. 1፡15፥ 19)።

ሁለተኛ፥ ኖስቲሲዝም በኃጢአትና በክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት አልሰጠም። ስለሆነም፥ የክርስቶስ ሞተ፥ መቀበርና መነሣት ጠቃሚ እውነቶች እንደሆኑ አይገነዘብም። የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር የመለኮታዊ ሕይወት መሰጠትና ሰዎችን ከእስራት ያስለቀቀ «ምሥጢራዊ» እውቀት ብቻ ነበር። ጳውሎስ ግን ያዳነን የክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት እንጂ ልዩ እውቀት እንዳልሆነ አስረድቷል (ቆላ. 1፡13-14፥ 21-22፥ 2፡13-15)።

ሦስተኛ፥ አንዳንድ ኖስቲኮች የተፈጠረው ነገር ሁሉ ክፉ እስከሆነ ድረስ ከማኅበራዊ ሕይወት መራቅ እንደሚሻል ያስተምሩ ነበር። ስለሆነም ወደ ገዳማት መግባት፥ ብዙ አለመመገብ፥ በወለል ላይ መተኛት እና የመሳሰሉት ጠቃሚ እንደሆኑ ያስተምሩ ነበር። ይህም አንድ ሰው የክፉ ዓለምን ተጽዕኖ እንዲገድብ ይረዳዋል ተብሎ ይታሰባል። ሰውነታቸውን በመቅጣት ነፍሳቸውን ለማፋፋት ፈለጉ። ይህ ትምህርት በቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ተጽዕኖ እያደረሰ ነበር። ጳውሎስ እነዚህ ነገሮች የሰውን የኃጢአት ተፈጥሮ ሊያሸንፉ እንደማይችሉና ምንም ዓይነት ጠቀሜታ እንደሌላቸው አስረድቷል (ቆላ. 2፡20-23)።

አራተኛ፥ ሌሎች የኖስቲክ አስተማሪዎች እንደ ሰዎች በምናከናውናቸውና በመንፈሳዊ ባሕሪያት መካከል ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለ ያስተምሩ ነበር። ክርስቲያኖች እንዳሻቸው ሊኖሩ እንደሚችሉ ይናገሩ ነበር። ወሲባዊ ኃጢአት ውስጣዊ ሕይወታችውን ስለማይነካ ስሕተት እንዳልሆነ ያስተምሩ ነበር። የ1ኛ ዮሐንስ መልእክት ይህንን ትምህርት ያፋልሰዋል። በቆላስይስ 3፡5ም ስላለው ጉዳይ ፍንጭ ተሰጥቷል። ጳውሎስ ለዚህ ለአሮጌው ሕይወት እንደሞትንና አዲስ ባሕርይ እንደ ለበስን ገልጾአል። ይህም አዲስ ባሕርይ ወደ አዳዲስ ተግባራት የሚመራ ነው (ቆላ. 3፡1-17)።

አምስተኛ፥ በልዩ እውቀት ላይ የተደረገው አጽንኦት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመደብ ደረጃ አስከተለ። ልዩ እውቀት (ይህን ምሥጢራዊ ቃል ወይም ሐረግ) ያላቸው ሰዎች ከሌሎች የተሻልን ነን ብለው አሰቡ። ጳውሎስ ዋናው ምሥጢር አንድ ብቻ መሆኑን ያስረዳል። ይህም እግዚአብሔር ሰዎች በክርስቶስ በማመን ሊድኑ እንደሚችሉ በጳውሎስ በኩል ማስታወቁ ነበር። ምንም ተጨማሪ እውቀት አያስፈልግም። አንድ ሰው ለወንጌል ምላሽ መስጠቱ ብቻ ይበቃዋል። ሁሉም «ጥበብና እውቀት» የሚገኘው ከክርስቶስና ስለ እርሱ ከሚናገሩ ትምህርቶች ብቻ ነው (ቆላ. 1፡25-2፡4)።

ዛሬም የኖስቲኮች ዓይነት አስተሳሰብ በአንዳንድ ክርስቲያኖች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ለምሳሌ፥ በአንዳንድ ክርስቲያናዊ ቡድኖች ጋብቻ እንደ ክፉ ነገር ይታያል። አንዳንዶች ደግሞ ከማኅበረሰቡ ተነጥለው በዋሻዎች ውስጥ ይኖራሉ። በቅርቡ ደግሞ ክርስቲያን በሥጋው የሚያደርገው ነገር ምንም ችግር እንደማያስከትል እየተነገረ ነው። አንድ ሰው ልቡን በአምልኮ እስካነጻ ድረስ የወሲብ፥ የስርቆት ወይም ሌላም ዓይነት ኃጢአት ቢፈጽም ምንም እንዳልሆነ ይናገራል። የይሖዋ ምስክሮች ስለ ክርስቶስ የሚያምኑትም ከኖስቲሲዝም ጋር ተመሳሳይነት አለው። ሕልሞችን፥ ራእዮችን ወይም በልሳን መናገርን አጥብቀው የሚከተሉ ሰዎችም «ልዩ እውቀት» ወይም «ልዩ ልምምድ» የመፈለግና የእነርሱ ዓይነት ልምምዶች የሌሏቸውን ሰዎች ዝቅ አድርጎ የመመልከት ዝንባሌ ይታይባቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡– ከኖስቲክ የመነጩትንና ዛሬ ተጽዕኖ እያደረሱ ያሉትን ሌሎች ትምህርቶች በምሳሌነት ጥቀስ።

የውይይት ጥያቄ፡- ቆላስይስ 1፡14-22 እንብብ። ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የተነገሩትን ነገሮች በሙሉ ዘርዝር። እነዚህ እውነቶች በሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት እንዴት ነው?

ሁለተኛው ዓላማ፡- የቆላስይስ መጽሐፍ ክርስቶስ ማን እንደሆነ ያብራራል። የኖስቲክን የሐሰት ትምህርት ፉርሽ ለማድረግ የሚቻለው ስለ ክርስቶስ ማንነት ግልጽ ትምህርት በማቅረብ ነበር። ጳውሎስ ክርስቶስ ከአነስተኛ አምላክ በላይ መሆኑን ያስረዳል። እርሱ ፍጹም አምላክና ከአብ ጋር እኩል ነው። ጳውሎስ የክርስቶስን የከበረ ስፍራ በብዙ መንገዶች ያብራራል።

ሀ. ክርስቶስ የማይታይ አምላክ አምሳል ነው። ክርስቶስ በሁሉም ነገር ከእግዚአብሔር አብ ጋር አንድ ዓይነት ነው። እርሱ ከማይታየው አምላክ ጋር እኩል ነው (ቆላ. 2፡9)።

ለ. ክርስቶስ የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው። ክርስቶስን ከፍጥረት ሁሉ በኩር ብሎ በመጥራቱ ጳውሎስ የክርስቶስን ሥጋዊ ልደት ሳይሆን ከማንኛውም ፍጡር የላቀውን የከበረ ስፍራውን እያመለከተ ነበር። እንዲያውም ጳውሎስ ክርስቶስ ሁሉንም ነገር እንደ ፈጠረና ፍጥረታት በሙሉ ሊያከብሩት እንደሚገባ አስረድቷል (ቆላ. 1፡15-16)።

ሐ. ክርስቶስ ሁሉንም እንዳያያዘም ተገልጾአል (ቆላ. 1፡17)። ክርስቶስ የአጽናፈ ዓለሙ ማጣበቂያ ነው። አጽናፈ ዓለሙ ጉዞውን እንዲቀጥል፥ ሕይወት ወደፊት እንዲገሠግሥ፥ ታሪክ ወደፊት እንዲሄድ፥ ፀሐይ ሁሌም እንድትወጣ፥ ወዘተ… የሚያደርገው እርሱ ነው።

መ. ክርስቶስ ለጠፋው ሰብአዊነት መፍትሔ ነው። ከጨለማችንና ከኃጢአታችን አውጥቶ በብርሃን መንግሥት ውስጥ የሚያስቀምጠን እርሱ ነው (ቆላ. 1፡13-14)።

ሠ. ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው። የኤፌሶን መልእክት በክርስቶስ ራስነት ሥር ስለምትተዳደረው ቤተ ክርስቲያን ሲያስተምር፥ የቆላስይስ መልእክት ግን የቤተ ክርስቲያን ራስ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያተኩራል።

ረ. ክርስቶስ በዩኒቨርስ ውስጥ ያለው ኃይልና ሥልጣን ሁሉ የበላይ ገዥ ነው (ቆላ. 2፡10)

ሰ. ክርስቶስ የጥበብና የእውቀት ሁሉ ምንጭ ነው (ቆላ. 2፡3)

ሸ. ክርስቶስ ክፉ ኃይላትን ሁሉ አሸንፎአል (ቆላ. 2፡15)።

ቀ. ክርስቶስ በአብ ቀኝ እየገዛ ነው (ቆላ. 3፡1)።

ሦስተኛ ዓላማ፡ ጳውሎስ ክርስቲያኖች ወደ ቀድሞው የአረማዊነት አኗኗራቸው እንዳይመለሱ (ቆላ. 3፡5) እና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት በሚያንጸባርቅ መልኩ እንዲመላለሱ ያስጠነቅቃቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡– ዛሬ ክርስቲያኖች እነዚህን ትምህርቶች ማወቅና ከሕይወታችን ጋር ማዛመድ ያለብን ለምንድን ነው?

፪. የቆላስይስ ልዩ ባሕርያት

 1. ቆላስይስ ከኤፌሶን ጋር በጣም ይመሳሰላል። በቆላስይስ መልእክት ውስጥ ከሚገኙት ጥቅሶች ከግማሽ የሚበዙት ከኤፌሶን ጋር ተመሳሳይ ናቸው። ሁለቱንም መልእክቶች ያደረሳቸው ቲኪቆስ ነው (ኤፌ. 6፡21፤ ቆላ. 4፡7)። ሁለቱም እንደ ምሥጢር፥ ጥበብ፥ እውቀትና አለቅነት ዓይነት ቃላትን ይጠቀማሉ። ሁለቱም በክርስቶስ ማንነትና ከቤተ ክርስቲያን ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ያተኩራሉ። ኤፌሶን ስለ ቤተ ክርስቲያንና ከክርስቶስ ጋር ስለተዛመደችበት ሁኔታ ሲያስተምር፥ ቆላስይስ ግን በክርስቶስና ከቤተ ክርስቲያን ጋር ስለተዛመደበት ሁኔታ ያብራራል። ሁለቱም መልእክቶች ከክርስቶስ ጋር ያለን ግንኙነት በማኅበረሰቡ ውስጥ ባለን ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ያስተምራሉ።
 2. ቆላስይስ ብዙውን ጊዜ ከእግዚአብሔር ጥበብ ጋር በሚጋጩ የሰው ፍልስፍናዎችና ጥበብ ላይ እንዳናተኩር ያስጠነቅቃል (ቆላ. 2፡8)። ክርስቲያኖች ሁልጊዜም በትምህርት ቤት ውስጥ የሚማሩትን በእግዚአብሔር ቃል መገምገም አለባቸው። ግጭት በሚኖርበት ጊዜም የእግዚአብሔር ቃል የሚለውን እንጂ ትምህርት ወይም ባሕል የሚለውን ማመንና መከተል የለባቸውም።

፫. የቆላስይስ መዋቅር

እንደ ሌሎች የጳውሎስ መልእክቶች ሁሉ ቆላስይስ በሁለት ዐበይት ክፍሎች ተካፍሏል። የመጀመሪያው ክፍል (ቆላ. 1-2) አስተምህሯዊ ሲሆን፥ ስለ ክርስቶስ ማንነት ይናገራል። ጳውሎስ የክርስቶስን ታላቅነት ካሳየ በኋላ (ቆላ. 1፡13-27)፥ ስለ ክርስቶስና እርሱን ስለ መከተል የሚያወሳውን እውነት ስለሚያጣምሙ የሐሰት አስተማሪዎች ይናገራል (ቆላ. 2፡8-23)።

ሁለተኛው ክፍል (ቆላ. 3-4)። የክርስቶስ ተከታዮች እንዴት እግዚአብሔርን በሚያስከብር መልኩ ሊኖሩ እንደሚገባቸው ያስተምራል። በግለሰብ ደረጃም ሆነ እንደ ክርስቶስ አካላት ከኃጢአት መለየት አለብን። እንዲሁም፥ ክርስቶስ ራሳችን መሆኑን በሚያሳይ መልኩ በቤታችንና በማኅበረሰቡ ውስጥ እርስ በርሳችን መዛመድ አለብን።

፬. የቆላስይስ አስተዋጽኦ

 1. መግቢያ (ቆላ. 1፡1-14)
 2. ጳውሎስ ለክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ያስተምራል (ቆላ. 1፡15-2፡23)።

ሀ. ክርስቶስ እንደ አብ ሁሉ ከተፈጠሩት ነገሮች የበለጠ ነው (ቆላ.1፡15-23)

ለ. ክርስቶስ ጳውሎስ ያስተማረው የወንጌል እምብርት ነው (ቆላ. 1፡24-2፡5)።

ሐ. አማኞች ከንቱ የሆነውን የሰው ትምህርት ከመከተል ይልቅ በክርስቶስ ላይ ማተኮር አለባቸው (ቆላ. 2፡6-23)።

 1. ጳውሎስ ክርስቲያኖች እንዴት ለክርስቶስ ሊኖሩ እንደሚገባቸው ያስተምራል (ቆላ. 3፡1-4፡6)።

ሀ. እንዴት የተቀደሰ ሕይወት እንደሚኖሩ (ቆላ. 3፡1-17)

ለ. በቤትና በሥራ ቦታ እንዴት መንፈሳዊ ግንኙነቶችን እንደሚያደርጉ (ቆላ. 3፡18–4፡1)

ሐ. እግዚአብሔርን እንዴት ማስደሰት እንደሚቻል የሚያስረዳ የመጨረሻ ትእዛዝ (ቆላ. 4፡2-6)

 1. ማጠቃላያ (ቆላ. 4፡7-18)

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የቆላስይስ መልእክት በማን ተጻፈ፣ ለማን ተጻፈ፣ የተጻፈበት ዘመንና ቦታ

፩. የቆላስይስ መልእክት ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፡- ቆላ. 1፡1-2 አንብብ። ሀ) ጸሐፊው ማን ነው? ለ) ጸሐፊው ራሱን የሚገልጸው እንዴት ነው? ይህ ከፊልጵ. 1፡1 የሚለየው እንዴት ነው? ሐ) መልእክቱን የጻፈው ለማን ነው?

የውይይት ጥያቄ፡- ስለ ቆላስይስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። ስለ መጽሐፉ ጸሐፊ፥ ስለ ከተማይቱ፥ ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱና ስለ መጽሐፉ የተሰጠውን ትምህርት ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።

ጳውሎስ የጻፈው ሦስተኛው «የእሥር ቤት መልእክት» የቆላስይስ መልእክት ነው። ጳውሎስ በዚህ መልእክት ውስጥ ስለ ራሱ ልማዳዊ ገለጻ አድርጓል። ለቆላስይስ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ሊሆን መብቃቱን ያስረዳል። የቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን ከጳውሎስ ጋር የቅርብ ግንኙነት ካላቸውና የጳውሎስን የሐዋርያነት ሥልጣን ከማይጠራጠሩ የፊልጵስዩስ አማኞች የተለየች ነበረች። ጳውሎስ ጎብኝቶ በማያውቃት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰርጎ በመግባት ላይ ያለውን የሐሰት ትምህርት ለመከላከል በመጣር ላይ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ስለ ሐሰት ትምህርቱ ለማስተማርና እውነትን ከሐሰት ለይቶ ለማሳየት እግዚአብሔር በሰጠው የሐዋርያነት ሥልጣኑ ላይ አጽንኦት አደረገ።

ጢሞቴዎስ አብሮት ስለነበረ ጳውሎስ የእርሱንም ስም ጠቅሷል። የመልእክቱ ጸሐፊ ግን ጳውሎስ እንጂ ጢሞቴዎስ አይደለም። አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ የጢሞቴዎስን ስም የጠቀሰው በዚያች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሆነ ወቅት ስላገለገለ ሊሆን ይችላል ይላሉ።

፪. መልእክቱ ለማን ተጻፈ?

ጳውሎስ በቆላስይስ ለሚገኙ ቅዱሳንና የታመኑ አማኞች እንደ ጻፈ ገልጾአል። ይህም መልእክቱ ሰቆላስይስ ከተማ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች እንደ ተጻፈ ያስረዳል።

የቆላስይስ ከተማ ከኤፌሶን በስተምሥራቅ 50 ኪሎ ሜትሮች ያህል ርቃ በእስያ ውስጥ ከሚያልፉ ዐበይት ጎዳናዎች በአንደኛው ላይ ትገኝ ነበር። (ከመጽሐፉ መጨረሻ ላይ ያለውን ካርታውን ተመልከት።) ቆላስይስ በፍርጊያ ግዛት ውስጥ እጅግ ከታወቁ ከተሞች አንዷ እንደነበረች ቢታወቅም፥ ጳውሎስ በኤፌሶን ውስጥ በሚሠራበት ወቅት ትንሽ ከተማ ነበረች። መጠኗ የቀነሰው በአካባቢዋ በስፋት ከሚከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ ሊሆን ይችላል። ከቆላስይስ በስተሰሜን ሰፊዋ የሎዶቅያ ከተማ ነበረች።

የቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደ ተመሠረተች አይታወቅም። ምናልባትም ይህ የሆነው ጳውሎስ ለሦስት ዓመታት ኤፌሶን ውስጥ ባገለገለበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም። በዚህ ጊዜ በእስያ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሁሉ ወንጌልን መስማታቸው ተገልጾአል (የሐዋ. 19፡10)። ጳውሎስ የቆላስይስንም ሆነ የሎዶቅያን ቤተ ክርስቲያን እንዳልጎበኘ ይናገራል (ቆላ. 2፡1)። ነገር ግን እነዚህ አብያተ ክርስቲያን የጳውሎስ አገልግሎት ተዘዋዋሪ ውጤቶች ነበሩ። ምናልባትም የቆላስይስ ሰዎች ለንግድ ወደ ኤፌሶን በመጡ ጊዜ የጳውሎስን ስብከት ሰምተው በክርስቶስ አምነው ይሆናል። ወደ አገራቸው ተመልሰው ለሌሎች በመመስከር ቤተ ክርስቲያን ሊመሠርቱ ችለው ይሆናል። ወይም ጳውሎስ ኤጳፍራ ወንጌሉን እንዳመጣላቸው ስለሚናገር (ቆላ. 1፡7)፤ ጳውሎስ ኤፌሶን ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሠርት ልኮት ይሆናል። ሌላው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ወደ ቆላስይስ ከተማ እንደ ላከውና እርሱም ኤጳፍራን ወደ ክርስቶስ እንደ መራው የሚያስረዳ ነው። ጳውሎስ የጢሞቴዎስን ስም ከመግቢያው ላይ የጠቀሰው በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

ጳውሎስ በአካል ወደዚያ ባይሄድም፥ በቆላስይስ የሚኖሩትን ቁልፍ ክርስቲያኖች ያውቅ ነበር። ከመልእክቱ መጨረሻ ላይ ለተወሰኑ የቤተ ክርስቲያን አባላት ሰላምታ ያቀርባል (ቆላ. 4፡14-17)። ምናልባትም በኤፌሶን ውስጥ በነበረው እገልግሎቱ ሳቢያ ድነት (ደኅንነትን) በማግኘታቸው የቆላስይስና የሎዶቅያ አማኞች ጳውሎስን እንደ መንፈሳዊ አባታቸው ሳይመለከቱት አልቀሩም። ጳውሎስ አማኞቹ ያልተገረዙ መሆናቸውን ስለሚናገር (ቆላ. 2፡13)። አብዛኞቹ የቆላስይስ ምእመናን አሕዛብ ሳይሆኑ አይቀሩም።

፫. ቆላስይስ የተጻፈበት ዘመንና ቦታ

በቆላስይስና ኤፌሶን መካከል ካለው ተመሳሳይነት የተነሣ፥ ሁለቱም መልእክቶች በተመሳሳይ ጊዜ የተጻፉ መሆናቸውን መናገር ይቻላል። ጳውሎስ ይህን መልእክት በጻፈ ጊዜ በሮምና ቂሣርያ ወይም ኤፌሶን መታሠሩ ምሁራኑን ቢያከራክራቸውም፥ ትክክለኛ የሚመስለው ሮም ነበረ የሚለው ነው። (መልእክቱ ስለተጻፈበት ስፍራ በኤፌሶን ወይም በፊልጵስዩስ ውስጥ ከተሰጠው ማብራሪያ አንብብ።) የተጻፈበት ዘመን ምናልባትም ከ60-61 ዓ.ም. ይሆናል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የቆላስይስ መልእክት መግቢያ

አንድ ሳይንቲስት በእንቁራሪት ላይ ምርምር አደረገ። መጀመሪያ ውኃ አፈላና እንቁራሪቷን እዚያው ውስጥ ጨመራት። ውኃው በነካት ጊዜ እንቁራሪቷ ትዘል ጀመር። የፈላው ውኃ ሲያቃጥላትም አልሞተችም። ሌላዋን እንቁራሪት ደግሞ በቀዝቃዛ ውኃ ውስጥ ጨመራት። የውኃውና የእንቁራሪቱ የሙቀት መጠን ተመጣጣኝ ስለነበር ይህችኛዋ እንቁራሪት ሳትዘል ዝም ብላ ተቀመጠች። ከዚያም ላይንቲስቱ ቀዝቃዛውን ውኃ እዚያው ውስጥ ካለችው እንቁራሪት ጋር አነስተኛ ሙቀት ባለው ምድጃ ላይ ጣደ። ውኃው ቀስ በቀስ እየፈላ ሄደ። የሚገርመው እንቁራሪቷ ምንም ዓይነት የመንፈራገጥ ምልክት ሳታሳይ በውኃ ሙቀት ተጠብሳ እስክትሞት ድረስ ዝም አለች።

እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ከዓለም እሴቶችና የአኗኗር ስልቶች እንድትለይ ጠርቷታል። በዓለም ውስጥ እንደ ጨውና ብርሃን እንድንኖር ታዝዘናል። ብዙውን ጊዜ አማኞች የስደት «ግለት» ወይም ሌሎች ሃይማኖቶች በሚያጋጥሟቸው ጊዜ፥ ልዩ ማንነታችንን ለመጠበቅ እንጥራለን። ስደትና ሌሎች ሃይማኖቶች እምብዛም ለቤተ ክርስቲያን አስጊዎች አይደሉም። ነገር ግን ሰይጣን በተዘዋዋሪ መንገድ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ሲፈልግ ዓለምን እንድትመስል ያደርጋታል። ሰይጣን ክርስቲያኖች ከሚያምኗቸው ትምህርቶችና እምነቶች በመጠኑ ለየት ያለ አስተሳሰብ በማቅረብ ቀስ በቀስ ወንጌሉንና ክርስቲያኖች በዓለም ውስጥ የሚኖሩበትን ሁኔታ ይለውጣል። በቤተ ክርስቲያን ላይ ትልቁ አደጋ የሚመጣው የክርስቲያኖችን እምነትና አኗኗር ቀስ በቀስ ከሚቀይሩ አነስተኛ ማመቻመቾች ወይም ከዓለም እንዳንለይ ከሚያደርጉ አነስተኛ የአኗኗር ስልት ለውጦች ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰይጣን ቀስ በቀስ የሐሰት ትምህርቶችንና ዓለማዊነትን በማምጣት ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ሲሞክር ያየህበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለዚህ ዓይነቱ ዝንባሌ ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል? ሐ) የሐዋ. 20፡28-31 አንብብ። ጳውሎስ የኤፌሶንን ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ያስጠነቀቀው ስለ ምንድን ነው?

ለቤተ ክርስቲያን እጅግ አደገኛ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ዓለማዊነት ነው። ዓለማዊነት ከሁለት ገጽታዎች የሚመጣ ነው። የመጀመሪያው፥ እምነትን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኝ ንጹሕ ወንጌል የመለወጥ ዓለማዊነት ነው። በዚህ ፋንታ የሐሰት አስተማሪዎች ሌላ ወንጌል ያቀርቡልናል። አንዳንዶች በክርስቶስ ከማመን ላይ ሰናይ ምግባራትን ይጨምራሉ። (ለምሳሌ፥ ሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት።) ሌሎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለ የተስፋ ቃል ይጨምራሉ። (ለምሳሌ፥ እግዚአብሔር ክርስቲያኖችን ሀብታም ያደርጋል የሚሉ የብልጽግና ሰባኪዎች።) ሌሎች ደግሞ የክርስቲያኖችን የሚመስል አምልኮ እያካሄዱ አንድ-በሦስት የሆነውን (ሥሉሠ ዋሕድ) እግዚአብሔርን ይክዳሉ። (ለምሳሌ፥ «ኢየሱስ ብቻ» ቤተ ክርስቲያን) ይህ ሁሉ በእውነት ላይ የተመሠረተ አምልኮ የሚፈልገውን አምላክ ደስ እንዳናሰኝ ለማደናቀፍና እምነታችንን ለመለወጥ ሰይጣን የሚያደርገው ጥረት ነው። በሐዋ. 20፥ ጳውሎስ ብዙም ሳይቆይ አባሎቻቸው ሐሰተኛ ትምህርቶችን እንደሚቀበሉ በመግለጽ የኤፌሶንን ቤተ ክርስቲያን መሪዎች አስጠንቅቋቸዋል።

ሁለተኛው ዓይነት ዓለማዊነት የሚመጣው ክርስቲያኖች የዓለማውያንን እሴቶች ተቀብለው እንደ ዓለማውያን ሲኖሩ ነው። ዓለም ወሲባዊ ኃጢአትን ታደፋፍራለች። ብዙውን ጊዜ ይህ ችግር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይታያል። ዓለም ትምህርት፥ ሀብት፥ እንዲሁም ቁሳዊ ቅርስ ወሳኝ ነገሮች እንደሆኑ ታስተምራለች። ብዙ ምእመናንም ይህንኑ አስተሳሰብ ይጋራሉ።

ጳውሎስ የቆላስይስን ቤተ ክርስቲያን ጎብኝቶ አያውቅም ነበር። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ አንዳንድ ዓለማዊ እምነቶችን እየተቀበለች መሆኗን በሰማ ጊዜ፥ ደብዳቤ ጻፈላት። ብዙውን ጊዜ መናፍስትን ለመለየትና (1ኛ ቆሮ. 12፡10) ዓለም የምታስተምራቸውን አሳቦችና እነዚህ አሳቦች በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያደርሱትን ጥፋት ለመመልከት ትልቅ ጥበብን ይጠይቃል። ብዙውን ጊዜ የሐሰት ትምህርትና የዓለማዊ አኗኗር ጥፋቶች ቀስ በቀስ ወደ ሕይወታችን ውስጥ ስለሚዘልቁ ሳትንፈራገጥ ተጠብሳ እንደሞተችው እንቁራሪት ችግሩን ለይተን ለማወቅ እንቸገራለን። ጳውሎስ የሐሰት ትምህርት እሳት እየጎዳቸው እንደሆነና ወደ ጥፋትም እንደሚወስዳቸው ይነግራቸዋል። ጳውሎስ በክርስቶስ ወንድሞቹና እኅቶቹ የሆኑት ክርስቲያኖች በስሕተት ሕይወት እንዲመላለሱ አልፈለገም። ጳውሎስ የሐሰት ትምህርቶች ሊጋለጡና ሐሰትን የሚከተሉ ሰዎች ግልጽ ውሳኔ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተረድቶ ነበር።

በዘመናችንም ክርስቲያኖች ነን እያሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሾልከው የሚገቡ ብዙ የሐሰት ትምህርቶች አሉ። የብልጽግና ወንጌል ክርስቶስ ካመንን ሀብታሞች እንደምንሆን ይናገራል። ሌሎች ደግሞ ብናምን ከሁሉም ዓይነት በሽታ እንደምንፈወስ ያስተምራሉ። እንደ ኢየሱስ ብቻ፥ የይሖዋ ምስክሮች፥ ሞርሞኖች፥ የአዲሱ ዘመን እንቅስቃሴና የመሳሰሉት ሃይማኖቶች ክርስቲያኖች ነን የሚሉትን ሰዎች እያወኩ ናቸው። ለረዥም ጊዜያት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሰዎች ቤተ ክርስቲያናቶቻቸውን ለቅቀው በመሄዳቸው ሲማረሩ ቆይተዋል።

የሰይጣንን የውሸት እውነቶች በማጋለጥ በስሕተት ውስጥ የሚወድቁ ምእመኖቻችንን ለማስጠንቀቅ ጊዜው አይደለምን? መሪዎች ዛሬ ለዚህ ችግር ምላሽ የሚሰጡበትን መንገድ ለማወቅ ጳውሎስ በቆላስይሳ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረውን የሐሰት ትምህርት ካስተናገደበት ሁኔታ የምንቀስመው እውቀት ይኖራል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)