ቃል ኪዳኖቹ

የሰው ልጅ ታሪክ ዘላለማዊው የእግዚአብሔር ዓላማ አፈጻጸም ታሪክ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጣል። የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅድ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጠ ሲሆን፥ እርሱም ክቡር የሆኑ ቃል ኪዳኖቹን መሠረት ያደረገ ነው። ቢያንስ ስምንት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ኪዳኖች በቃሉ ተመዝግበው ይገኛሉ። እነርሱም እግዚአብሔር ስለ ዓለም ካለው ዕቅድና ዓላማ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ዓበይት እውነታዎች ያካትታሉ። ከእነዚህ ቃል ኪዳኖች ብዙዎቹ መፈጸማቸው በማይቀርና በአዋጅ መልካ የቀረቡ መለኮታዊ ዓላማዎች ናቸው። የሥነ-መለኮት ጠበብት ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ኪዳኖች በተጨማሪ ከሰው ድነት ጋር የሚገናኙ ሦስት ሥነ-መለኮታዊ ቃል ኪዳኖችን አቅርበዋል። 

ሀ. ሥነ-መለኮታዊዎቹ ቃል ኪዳኖች 

የሥነ-መለኮት ሊቃውንት የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ዓላማ በሚገልጡበት ጊዜ፥ ዘላለማዊ ዓላማው የመረጣቸውን ማለት፥ ከዘላለም በፊት ለድነት የወሰናቸውን ማዳን ነው የሚል ፅንሰ አሳብ አቅርበዋል። ይህን ትምህርታቸውን ሲያስፋፉ መሠረታዊ የሆኑ ሦስት ሥነ-መለኮታዊ ቃል ኪዳኖችን ያብራራሉ። 

1. ከአዳም ጋር የተደረገው የሥራ ቃል ኪዳን። አዳም በቃል ኪዳኑ መሠረት እግዚአብሔርን ቢታዘዝ፥ ሰሙንፈሳዊ ሁኔታው የሚጠበቅ ከመሆኑም ባሻገር፥ ዘላለማዊ ሕይወትም ያገኝ ነበር። ቃል ኪዳኑ መልካምና ክፉ እውቀት ስለምትሰጠው ዛፍ በተነገረውና “ከእርሱ በላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና” (ዘፍጥ. 2:17) ተብሎ በተሰጠ ማስጠንቀቂያ የተደገፈ ነበር። ከዛፉ ባይበላ ኖሮ ባልሞተም ነበር፤ ደግሞም እንደ ቅዱሳን መላእክት ለእርሱም ተሰጥቶ የነበረው ሰፍራ ይጸናለት ነበር ተብሎ ይገመታል። ይህ ቃል ኪዳን ሙሉ በሙሉ የተመሠረተው በግምት ላይ በመሆኑና መጽሐፍ ቅዱስ በቃል ኪዳንነት ያልተጠቀሰ በመሆኝ፥ እንዲሁም በቂ መሠረት እንደሌለው ስለታወቀ ሰብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ዘንድ ተቀባይነት የለውም። 

2. ሌላው ቃል ኪዳን ማመቤዠት ቃል ኪዳን” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፥ እርሱም የሰውን ድነት የሚመለከት ሆኖ በእግዚአብሔር እብና በእግዚአብሔር ወልድ መካክል አላለም ጀምሮ ያተደረገ ቃል ኪዳን ነው ተብሏል። ይህ ቃል ኪዳን የእግዚአብሔር ልጅ ለሚያምኑበት የድነት ቤዛ እንደሚሆንና እግዚአብሔር አብም መሥዋዕቱን እንደሚቀበልለት ተስፋ የተሰጠበት ነው። 

ቃል ኪዳኑ ቀደም ሲል ከተጠቀሰው የሥራ ቃል ኪዳን ይበልጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ አለው። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ እንደሚያውጀው፥ የእግዚአብሔር የማዳን ዕቅድ ዘላለማዊ ነው። በዚህ ዕቅድ መሠረትም ክርስቶስ የኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ እንደሚሞትና እግዚአብሔርም በክርስቶስ የሚያምኑትን ለማዳን መሥዋዕቱን በቂ አድርጎ እንደሚቀበል በመታወቁ ነው። ይህም የዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን” (ኤፌ. 1፡4) ተብሎ በተጻፈው ቃል ተረጋግጧል። በክርስቶስ ያለንን ቦታ በማስመልከት ደግሞ፥ “እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ፥ አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን (ኤፌ. 4፡11) ተብሏል። 

ከእነዚህና ከሌሎችም ጥቅሶች በግልጥ የምንረዳው፥ በማዳን ረገድ የእግዚአብሔር ዓላማ ዘላለማዊ መሆኑን ነው። በእግዚአብሔር አብና እግዚአብሔር ወልድ መካከል የተደረገው ግልጥ ቃል ኪዳን የሚያመለክተው የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዓላማ ሰዎችን ማዳን መሆኑን ነው። 

3. ሌላው አቀራረብ የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ የማዳን ዓላማ እንደ የጸጋቃል ኪዳን” መመልከት ይገባል የሚለው ነው። በዚህ አመለካከት መሠረት ክርስቶስ የቃል ኪዳኑ መካከለኛና እምነታቸውን በእርሱ ለሚያደርጉ ሁሉ ወኪሳቸው እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል። ሰዎች ለዚህ ቃል ኪዳን ብቁ የሚሆኑት፥ ክርስቶስን አዳኛቸው አድርገው እምነታቸውን በእርሱ ላይ ሲያደርጉ ነው። ይህ ቃል ኪዳን ከዘላለማዊ የድነት ዕቅድ በተወሰደ ግምት ላይ የተመሠረተ ሲሆንዎ፥ የእግዚአብሔርን የማዳን ባለጠግነት ያጎላዋል። በመሆኑም የመቤዥት ቃል ኪዳንና የጸጋ ቃል ኪዳን የተወሰነ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት አላቸው። የሥራ ቃል ኪዳን የመጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ድጋፍ የሌለው ከመሆኑ የተነሣ፥ ሰብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። 

ነገር ግን ከፍተኛ ችግር የተነሣበት ሁኔታ አለ። ይኸውም የሥነ-መለኮታዊ ቃል ኪዳኖች ደጋፊ የሆኑ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ የእግዚአብሔርን የማዳን ዕቅድ እርሱ ለሰው ታሪክ ያለው የመጀመሪያ ዓላማ ያደርጉታል። ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ለእስራኤል፥ ለቤተ ክርስቲያንና ለአሕዛብ ያለውን ዕቅድ ልዩ ሁኔታዎች ቸል ወደ ማለት ያዘነብላሉ። የእግዚአብሔር የማዳን ዕቅድ የዘላለማዊ ዓላማው ዋና ክፍል ቢሆንም አጠቃላይ ዕቅዱ ግን አይደለም። የተሻለው አመለካከት እግዚአብሔር በታሪክ ያለው ዕቅድ ክብሩን መግለጥ ነው የሚለው ይሆናል። ይህን የሚያደርገው ሰዎችን በማዳን ብቻ ሳይሆን፥ ዓላማውን በማከናወንና ከእስራኤል፥ ከቤተ ክርስቲያንና ካሕዝቦች ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ራሱን በመግለጥ ጭምር ነው። በመሆኑም ታሪክን እግዚአብሔር በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ያለውን ዋና ዋና ዓላማዎች በሚገልጡትና የማዳን ዕቅዱን ባካተቱት ስምንት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ኪዳኖች በኩል መመልከቱ ይመረጣል። በሥነ-መለኮታዊ ቃል ኪዳኖች ላይ የሚያተኩሩ ወገኖች “የቃል ኪዳን ሥነ-መለኮታውያን” ተብለው ሲጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል ኪዳኖች የሚደግፉ ግን “ሥፍረ-ዘመናውያን” ይባላሉ፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ኪዳኖች በየሥፍረ-ዘመናቱ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በየደረጃው የታዩትን ልዩነቶች ስለሚገልጡ ነው። 

ለ. መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ኪዳኖች 

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቃለሉት የእግዚአብሔር ቃል ኪዳኖች በሁለት የሚመደቡ ሲሆን፥ እነርሱም ቅድመ ሁኔታዊና ከቅድመ ሁኔታ ነጻ የሆኑ ናቸው። ቅድመ ሁኔታዊ ቃል ኪዳን፥ ቃል ኪዳኑ ከሚመለከታቸው ሰዎች በኩል ለሚወሰድ እርምጃ እግዚአብሔር የሚሰጠው አጸፋ ነው። ቅድመ ሁኔታዊ ቃል ኪዳን፥ ሰዎች የሚጠበቅባቸውን ካደረጉ፥ እግዚአብሔር የራሱን ድርሻ እንደሚያደርግ ፍጹም እርግጠኛነት ዋስትና ይሰጣል። ሰው የሚጠበቅበትን ባያደርግ ግን፥ እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን ደፈጽም ዘንድ አይገደድም። 

ከቅድመ ሁኔታ ነጻ የሆነው ቃል ኪዳን ምናልባት አንዳንድ ከሰው የሚፈልጉ ሁኔታዎችን ጨምሮ የተወሰኑ የእግዚአብሔር ዓላማዎች አዋጅ ሲሆን፥ የዚህ ቃል ኪዳን ተስፋዎች ያለ ጥርጥር በእግዚአብሔር ጊዜና አሠራር ይፈጸማሉ። ከስምንቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ኪዳኖች፥ ኤደን ገነት ውስጥ የተደረገውና የሙሴ ቃል ኪዳኖች ነበሩ ቅድመ ሁኔታ የነበራቸው። ይሁን እንጂ ቅድመ ሁኔታዊ ሳልሆኑ ቃል ኪዳኖችም ሲሆን የተወሰኑ ግለሰቦችን ሰሚመለከት ቅድመ ሁኔታዊ ነገር አለ። ከቅድመ ሁኔታ ነፃ የሆነ ቃል ኪዳን ከቅድመ ሁኔታዊ ቃል ኪዳን የሚለየው፥ የመጨረሻ አፈጻጸሙ በእግዚአብሔር ተስፋ የተሰጠበት፥ እንዲሁም በርሱ ኃይልና ሉዓላዊነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው። 

1. ቅኤደን ቃል ኪዳን” እግዚአብሔር ከሰው ጋር የገባው የመጀመሪያ ቃል ኪዳን ነበር (ዘፍጥ. 1፡26-31፤ 2፡16-17)። ያም ቅድመ ሁኔታዊ ሆኖ በአዳም ታማኝ መሆን ወይም አለመሆን ምክንያት ሕይወትና በረከት ወይም ሞትና እርግማን የሚመጡ መሆናቸውን የሚገልጥ ነበር። የኤደን ቃል ኪዳን የሚያጠቃልለው፥ አዳም የሰው ዘር ሁሉ አባት የመሆኑን ኃላፊነት፥ ምድርን የመግዛት፥ እንስሳትን የማዘዝ፥ የአትክልቱን ስፍራ የመጠበቅና መልካሙንና ክፉውን ከምታስታውቀው ዛፍ ፍሬ አለመብላትን ነበር። አዳምና ሔዋን ከተከለከለው ዛፍ ፍሬ በመብላታቸው፥ ያለመታዘዝ ቅጣት የሆነው ሞት ተፈረደባቸው። ወዲያውኑ መንፈሳዊ ሞት ሞቱ፥ ከዚያ ለመዳን ዳግም ልደት አስፈለጋቸው። ቆይተውም አካላዊ ሞት ሞቱ። የእነርሱ ኃጢአት የሰውን ዘር ሁሉ ተመሳሳይ በሆነ ኃጢአትና ሞት ውስጥ ጣለው። 

2. ኅዳማዊው ቃል ኪዳን” ከውድቀት በኋላ ከሰው ጋር የተደረገ ነበር(ዘፍጥ. 3፡16-19)። ይህ ቃል ኪዳን ከቅድመ ሁኔታዎች ነጻ የሆነና ከኃጢአቱ የተነሣ የሰው ዕጣ በሕይወቱ ዘመን ምን መምሰል እንዳለበት እግዚአብሔር ያወጀበት ነው። ምንም ዓይነት ይግባኝ ወይም የሰው ኃላፊነት አልነበረበትም። 

ቃል ኪዳኑ በአጠቃላይ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የሰውን ሕይወት የሚለውጡ ጠቃሚ ሁኔታዎችን የሚያዘጋጅ ነበር። በዚህ ቃል ኪዳን የምንመለከተው ነገር፥ በእባብ የተመሰለው ሰይጣን መረገሙ (ዘፍጥ. 3፡14፤ ሮሜ 16፡20፤ 2ኛ ቆሮ. 11፡3፥ 14፤ ራእይ 12፡9)፤ እና አዳኝ የሚመጣ የመሆኑ ተስፋ (ዘፍጥ. 3፡15) ሲሆን፥ ተስፋው በመጨረሻ በክርስቶስ ተፈጽሟል። በዚያ ጊዜ ሴት በወሊድ ወቅት በብዙ ምጥና ጣር እንድትሠቃይ የተፈረደባት ከመሆኑም ባሻገር፥ ወንድ ራስ መሆኑን አውቃ እንድትገዛለት ተወስኖባታል (ዘፍጥ. 1፡26-27፤ 1ኛ ቆሮ. 11፡7-9፤ ኤፌ. 5፡22-25፤ 1ኛ ጢሞ. 2:11-14)። ከዚያ ወዲህ ሰው ሰፊቱ ወዝ እንጀራ እንዲበላ (ዘፍጥ. 2፡15፤ 3፡17-19)፥ በድካም እንዲኖርና በመጨረሻም እንዲሞት ተፈረደበት (ዘፍጥ. 3፡19፤ ኤፌ. 2፡5)። ከዚህ ጊዜ በኋላ ሰውም በአጠቃላይ በአዳማዊ ቃል ኪዳን ሥር መተዳደሩን ቀጠለ። 

3. ኖኀዊው ቃል ኪዳንስኖጎና ከልጆቹ ጋር ተደረገ(ዘፍጥ. 9፡1-18)። ይህ ቃል ኪዳን ከአዳማዊው ቃል ኪዳን የተወሰኑ ሁኔታዎችን የሚደግም ቢሆንም፥ ኃጢአትን ለመግታት ይቻል ዘንድ አዲስ የሰብአዊ መንግሥት ሥርዓትን አምጥቷል። እንደ አዳማዊው ቃል ኪዳን ከቅድመ ሁኔታዎች ነጻ ስለሆነም ከኖኅ ቀጥሎ ላለው የሰው ዘር የእግዚአብሔርን ዓላማ ገልጧል። 

የቃል ኪዳኑ ደንቦች ሰው የገደለ ይሙት የሚል ሕግ ያለውን ሰብአዊ መንግሥት አካተዋል። የተፈጥሮ ትክክለኛ ሥርዓትም ጸንቷል (ዘፍጥ. 8፡22፤ 9፡2)፥ ከጥፋት ውኃ በፊት አትክልት ብቻ ይመገብ የነበረው ሰው፥ የእንስሳት ሥጋም እንዲበላ ተፈቀደለት (ዘፍጥ. 9፡3-4)። 

የኖኅ ቃል ኪዳን ስለ ሦስቱ ልጆቹ ትውልድ የተነገረውን ትንቢት ያካትታል (ዘፍጥ. 9፡25-27)፤ ሴምም መሢሕ የሚመጣበት የትውልድ መስመር እንዲሆን ተሰይሟል። አሕዛብ በዓለም ታሪክ የበላይነት የሚኖራቸው መሆኑ ስለ ያፌት በተነገረው ትንቢት ተገልጧል። የሕሊና ሥፍረ-ዘመን በአዳም ቃል ኪዳን እንደተጀመረ ሁሉ፥ በኖኅ ቃል ኪዳንም የሰብአዊ መንግሥት ሥፍረ ዘመን ተጀመረ። 

4 . ብርሃማዊው ቃል ኪዳን” (ዘፍጥ. 12፡1-4፤ 13፡14-17፤ 15፡1-7፤ 17፡1-8)፥ የወደፊቱን ታሪክ በተመለከተ የቀረበና ከታላላቅ የእግዚአብሔር መገለጦች አንዱ ሲሆን፥ በውስጡም ስምስት አቅጣጫ ያተኮሩ ጥልቅ ተስፋዎች ተሰጥተዋል። ከሁሉም አስቀድሞ ለአብርሃም ዘሩ እጅግ እንደሚበዛ፥ (ዘፍጥ. 17፡16)፥ እንደሚባረከ (ዘፍጥ. 13፡14-15፥ 17፤ 15፡6፥ 18፤ 24፡34-35፤ ዮሐ.8፡56)፤ ስሙ ታላቅ እንደሚሆንና (ዘፍጥ. 12፡2)፥ ራሱም በረከት እንደሚሆን ተስፋ ተሰጥቶታል። 

ሁለተኛ፥ በአብርሃም በኩል ታላቅ ሕዝብ እንደሚመጣ ተስፋ ነበረ (ዘፍጥ 12፡2)። በእግዚአብሔር ዓላማ ውስጥ ይህ በዋናነት የሚመለከተው፥ እስራኤልንና አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች የመሠረቱትን የያዕቆብ ትውልድ ነው። ለዚህ ሕዝብ ምድርን የመውረስ ተስፋ ተሰጥቶት ነበር (ዘፍጥ. 12፡7፤ 13፡15፤ 15፡18-21፤ 17፡7-8)። 

ሦስተኛው ታሳቅ የአብርሃም ቃል ኪዳን ክፍል በአብርሃም አማካይነት መላው ዓለም እንደሚባረክ የተሰጠው ተስፋ ነው (ዘፍጥ, 12፡3)። ይህም እስራኤል የእግዚአብሔር ልዩ መለኮታዊ መገለጥ መተላለፊያ፥ እግዚአብሔርን የሚገልጡ ነቢያት ምንጭና የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችን አመንጭ በመሆኗ የሚከናወን ነበር። ከሁሉም የሚልቀው ተስፋ ለአሕዛብ የሚሆነው በረከት የሚመጣው፥ ከአብርሃም ዘር በሚወስደው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መሆኑ ነበር። እስራኤል ከእግዚአብሔር ጋር ባላት ልዩ ግንኙነት ምክንያት የሚረግሙአትን እርሱ እንደሚረግምና የሚባርኩትንም እንደሚባርካቸው ልዩና የማይሻር ቃል ኪዳን አደረገ (ዘፍጥ. 12፡3)። 

እንደ እዳማዊና ኖኀዊ ቃል ኪዳኖች ሁሉ የአብርሃማዊው ቃል ኪዳንም ከቅድመ ሁኔታ ነጻ ነው። የማንኛውም የእስራኤል ትውልድ አባላት ለእግዚአብሔር ቢታዘዙ የተዘጋጀላቸውን ሁሉ እንደሚያገኙና ባይታዘዙ ግን ለምርኮ አልፈው እንደሚሰጡ የታወቀ ነበር። እግዚአብሔር ለእስራኤል የነበረው የመጨረሻ ዓላማ መባረከ፥ ራሱን በእስራኤል በኩል መግለጥ፥ ቤዛነትን በርሷ በኩል ማዘጋጀትና እሰራኤልን ወደ ተስፋይቱ ምድር ማስገባት ነበር። ጉዳዩ በትክክል በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ኃይልና ፈቃድ እንጂ በሰው ኃይልና ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ስላልነበረ መከናወኑ ፍጹም እርግጥ ነበር። በብሉይ ኪዳን እስራኤላውያን ቢወድቁም፥ እግዚአብሔር በብዙ ሁኔታዎች ራሱን ገልጦላቸዋል፥ መጽሐፍ ቅዱስም እንዲጻፍ አድርጓል። እንዲሁም በመጨረሻ ክርስቶስ ተወለደ፥ ኖረ፥ ሞተ፤ የእግዚአብሔር ቃል እንደተናገረውም በትክክል ከሙታን ተነሣ። የሰው ውድቀት ያለ ቢሆንም የእግዚአብሔር ዓላማ መፈጸሙም የተረጋገጠ ነው። 

5, ሙሌያዊው ቃል ኪዳንለእስራኤል ልጆች በሙሴ አማካይነት የተተቸው፥ ከግብፅ ወጥተው ወደ ተስፋይቱ ምድር በሚጓዙበት ጊዜ ነበር (ዘጸ. 20፡1-31፡18)። በዘጸአት መጽሐፍ እንደተካተተውና በሌሎችም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንደተብራራው፥ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር የሚኖረውን የግንኙነት ሕግ ለሙሴ ሰጠው። እነዚህ ወደ ሰድሰት መቶ ይደርሳሉ ተብሎ የሚገመቱ ግልጥ ትእዛዞች በሦስት ዐበይት ክፍሎች ይመደባሉ። ሀ. ትእዛዛት፡- የእግዚአብሔርን የተለየ ፈቃድ የሚያጠቃልሉ (ዘፍጥ. 20፡1-26)፤ ለ. ፍርዶች፡- ከእስራኤል ማኅበራዊ ሕይወት ጋር የተዛመዱ (ዘጸ. 21፡1-24፡11) እና ሐ. ሥርዓቶች ናቸው (ዘጸ. 24 ፡12-31፡18)። 

የሙሴ ሕግ በቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፥ እስራኤል ሲታዘዝ እግዚአብሔር የሚባርከው መሆኑን፥ ባይታዘዝ ግን የሚረግመውና የሚቀባው መሆኑን የሚናገረ ሥርዓት በውስጡ እካቷል። ይህ በተለይ ዘዳግም 28 ውስጥ በግልጥ ይታያል። እስራኤል እንደማይታዘዝ የተነገረ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደማይተው ተስፋ ሰጥቷል (ኤር. 30፡1)። ሙሴያዊው ቃል ኪዳን ጊዜያዊና በክርስቶስ መሰቀል የሚያበቃ ነበር። ጸጋን የሚመዕከቱ ነጥቦች ቢኖሩትም፥ በመሠረቱ ግን የሥራ ቃል ኪዳን ነው። 

6. ስለ ከነዓን ምድር የተሰጠው ቃል ኪዳን (ዘዳ. 30፡1-10) ከቅድመ ሁኔታ ነጻ የኝ ቃል ኪዳን ሲሆን፥ እስራኤል በመጨረሻ ምድሩን የምትይዝ መሆንን ያስገነዝባል። ይህ ቃል ኪዳን የሚያስገነዝበን በመሠረቱ እንድ ከቅድመ ሁኔታዎች ነጻ የሆነ ቃል ኪዳን በርግጥ የሚፈጻም መሆኑን ነው። ሆኖም ይብዛም ይነስ ለማንኛውም የተለየ ትውልድ ቅድመ ሁኔታዊ ይዘት ይኖረዋል። ዘፍጥረት 12፡7 ላይ እና፥ ብሉይ ኪዳን ውስጥ ለአብርሃም እንደገና የተረጋገጠሰት ተስፋ፥ ዘሩ ምድሪቱን የሚወርስ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነበር። ይሁን እንጂ፥ ካለመታዘዝ ሳቢያ ያዕቆብና ትውልዱ ከስደት በፊት በመቶዎቹ ለሚቆጠሩ ዓመታት ግብፅ ውስጥ ኖሩ። ያም ሆኖ ከእግዚአብሔር ዓላማ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ተመልሰው ቢያንስ የምድሪቱን ከፈል ያህል ወርሰዋል። በኋላ ደግሞ ካለመታዘዝና የእግዚአብሔርን ሕግ ካለማክበር የተነሣ ለአሶርና ለባቢሎን ምርኮ ተዳረጉ። በባቢሎን ምርኮ ሰባ ዓመት ከቆዩ በኋላ በእግዚአብሔር ጸጋ እንደገና ተመልሰው፥ በ70 ዓ.ም. ኢየሩሳሌም እስከተደመሰሰች ድረስ ምድሪቱን ይዘው ነበር። ይሁን እንጂ፥ እስራኤል ዓመፀኛም ብትሆን በመጨረሻ ወደ ምድሯ እንደምትመለስ፥ በሠላምና በበረከት እንደምትኖር እንደገናም እንደማትበትን ተስፋ ተሰጥቷታል (ሕዝ. 39፡25-29፤ አሞፅ 9፡14-15)። 

ስለዚህ የአሁኑ የእስራኤል ወደ ምድሯ መመለስ ታላቅ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ለፍጻሜው ዘመን እስፈላጊ የሆነውን መድረክ ይህ የእስራኤል መመለስ ያከናውነዋል። 

የእስራኤል ወደ ምድሯ የመመለስ ዕቅድ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ መንግሥቱን ከመሠረተ በኋላ አንድ እስራኤላዊ እንኳ እስከማይቀር ድረስ ይጠናቀቃል (ሕዝ. 39፡25-29)። ማንኛውም ትውልድ ባለመታዘዙ ሳቢያ ከምድሩ እንዲሰደድ ሲደረግም፥ እግዚእብሔር ሕዝቡን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመመለስ ያለው የመጨረሻ ዓላማ፥ ቅድመ ሁኔታ የሌለውና በእርግጥ የሚፈጸም ነው። 

በመሆኑም ስለ ከነዓን ምድር የተሰጠው ቃል ኪዳን የእስራኤልን ባሰማመኗና ባለመታዘዟ መበታተንን (ዘፍጥ. 15፡13፤ ዘዳ. 28፡63-68)፥ የንስሐና የመታደስ ጊዜያትን (ዘዳ. 30፡2)፥ የእስራኤልን እንደገና መሰብሰብ (ዘዳ. 30፡3፤ ኤር. 23፡8፤ 30፡3፤ 31፡8፤ ሕዝ. 39፡25-29፤ አሞጽ 9፡9-15፤ ሐዋ. 15፡14-17)፥ የእስራኤልን በምድርዋ እንደገና መመሥረት (ኢሳ. 11፡11-12፤ ኤር. 23፡3-8፤ ሕዝ. 37:21-25፤ አሞጽ 9፡9-15)፥ የእስራኤል መንፈሳዊ መለወጥና ብሔራዊ መጠናከርን (ሆሴ. 2፡14-16፤ ሮሜ 11፡26-27)፥ በመንግሥትነት የመጨረሻውን ሠላምና ብልጥግና ማግኘቷን (አሞጽ 9፡11-15)፥ የጠላቶቿን ሰመለኮታዊ ፍርድ መቀጣት ያጠቃልላል (ኢሳ. 14፡1-2፤ ኢዩ. 3፡1-8፤ ማቴ. 25፡31-46)። 

1. “ዳዊታዊው ቃል ኪዳን” (2ኛ ሳሙ. 7፡4-16፤ 1ኛ ዜና. 17፡3-15)። ከቅድመ ሁኔታዎች ነጻ የሆነና እግዚአብሔር ፍጻሜ የሌለውን ንጉሣዊ ሐረግ፥ ዙፋንና መንግሥት ለዳዊት እንደሚሰጠው ተስፋ የገባበት ሲሆን፥ ተስፋዎቹ ሁሉ ዘላለማዊ ናቸው። ይህ ቃል ኪዳን ያህዌህ የዳዊትን ትውልድ ዘመነ መንግሥት አስፈላጊ ከሆነ በቅጣት ሊያቋርጥባቸው መብት እንዳለው የሚያረጋግጥ ቢሆንም (2ኛ ሳሙ. 7፡14-15፤ 

መዝ. 89፡20-37)፥ ቃል ኪዳኑ ግን የሚፈርስ ወይም የሚቀየር አይደለም። 

አብርሃማዊው ቃል ኪዳን ለእስራኤላውያን በሕዝብነታቸው የዘላለም ዋስትናን እንዳረጋገጠና (ኤር. 31፡36)፥ ምድሪቱንም ለዘላለም እንዳስጨበጣቸው ሁሉ (ዘፍጥ. 13፡15፤ 1ኛ ዜና. 16፡15-18፤ መዝ. 105 ፡9-11)፥ የዳዊት ቃል ኪዳንም እንዲሁ የዘላለም ዙፋንን (2ኛ ሳሙ. 7: 16፤ መዝ. 89፡36)፥ የዘላለም ንጉሥ (ኤር. 33፡21)፥ እና የዘላለም መንግሥትን ያረጋግጥላቸዋል (ዳን. 7፡14)። ይህ ቃል ኪዳን ከተደረገና በእግዚአብሔር መሐላ ከጸደቀበት ዕለት ጀምሮ (ሐዋ. 2፡30)፥ እስከ ክርስቶስ ልደት ድረስ ዳዊት በዙፋኑ የሚቀመጥሰትን ልጅ አላጣም (ኤር. 33፡21)። የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ልጅና የዳዊትም ልጅ የሆነው ክርስቶስ የዙፋኑ ባለመብት፥ ሰራሽና ገና በዙፋኑ ላይ የሚቀመጥ እንደመሆኑ (ሉቃስ 1፡31-33)፥ ከልጆቹ አንዱ ለዘላለም ይነግሣል የሚለውን ተስፋ ከፍጻሜ ያደርሰዋል። 

ዳዊታዊው ቃል ኪዳን ከሁሉም የሚልቀው፥ ክርስቶስ በምድር ላይ የሚነሥበትን የሺህ ዓመት መንግሥት በማረጋገጡ ነው። ከሙታን የሚነሣው ዳዊት፥ በንጉሡ ክርስቶስ ሥር ሆኖ በእስራኤል ላይ ይገዛል (ኤር. 23፡5-6፤ ሕዝ. 34፡23-24፤ 37፡24)። ዳዊታዊው ቃል ኪዳን ከርስቶስ በሰማይ ዙፋኑ በነገሠ ጊዜ የተፈጸመ አይደለም። ዳዊት መቼም ሰአብ ዙፋን ላይ አልተቀመጠም፤ ወደፊትም አይቀመጥም። የሚነግሠው በምድራዊው ዙፋን ነው (ማቴ. 25፡31)። ስለዚህ ዳዊታዊው ቃል ኪዳን ወደፊት ለሚፈጸመው የእግዚአብሔር ትንቢታዊ ዕቅድ ቁልፍ ነው። 

8. ብሉይ ኪዳን ውስጥ የተተነበየውና የመጀመሪያ ፍጻሜው በሺህ ዓመቱ መንግሥት የሚሆነው እዲስ ቃል ኪዳንከቅድመ ሁኔታ ነጻ ነው(ኤር. 31፡31-33)። እርሱም በኤርምያስ እንደተገለጠው እግዚአብሔር ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር” የሚገባው አዲስ ቃል ኪዳን ነው (ቁ. 31 )። ይህ ቃል ኪዳን በእስራኤል ከተጣሰው ሙሴያዊ ቃል ኪዳን ጋር ሲነጻጸር፥ አዲስ ቃል ኪዳን ነው (ቁ.32)። 

በቃል ኪዳኑም እግዚአብሔር “ከእነዚያ ወራት በኋላ …ሕጌን በልቦናቸው እኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፥ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ፥ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል” በማለት ተስፋ ይሰጣል (ቁ. 33)። እግዚአብሔር ራሱን በግል በመግለጡና ፈቃዱንም ለሕዝቡ በማሳወቁ እንዲህ ተብሏል፡- “እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን፥ እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል እግዚአብሔር። ሰደሳቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና” እያለ ያረጋግጣል (ኤር. 31፡34)። 

ይህ ምንባብ ክርስቶስ ስለሚነግሥበት የሺህ ዓመት መንግሥት ሁኔታዎችና ሰው ሁሉ ስለ ክርስቶስ የሚያውቅ ስለመሆኑ ይናገራል። በመሆኑም አንድም ሰው ባልንጀራውን ስለ ክርስቶስ ወንጌል ማስተማር እያስፈልገውም። ምክንያቱም ጌታን የሚመለከቱትን እውነታዎች ሁሉ መላው ዓለም ያውቃቸዋል። ደግሞም ዘመኑ እግዚአብሔር የእስራኤላውያንን ኃጢአት ይቅር የሚልበትና እጅግ የሚባረኩበት ዘመን ይሆናል። በኤርምያስ በኩል ከተሰጠው ከዚህ ቃል ኪዳን ግልጥ መሆን ያለበት ነገር፥ ቃል ኪዳኑ ዛሬ በመፈጸም ላይ አለመሆኑ ነው። ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያንም እውነትን ላልተረዳው ዓለም ወንጌሉን የማዳረሷ ትእዛዝ ገና በመከናወን ላይ ነው። 

አዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያንን ከአዲሱ ቃል ኪዳን ጋር ስለሚያገናኛት፥ አንዳንዶች ለእስራኤል የተሰጠውን ቃል ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ትፈጽመዋለች በማለት አስተምረዋል። በዚህ መሠረት የሺህ ዓመቱ መንግሥትና በእስራኤል መታደስ የማያምኑ ክፍሎች ይህ አዲስ ቃል ኪዳን ቤተ ክርስቲያን እንደሚፈጸም ያስተምራሉ። ይህን የሚያስተምሩበት ምክንያት በቃል ኪዳኑ የተገለጡ ተስፋዎችን ቃል በቃል ሳይሆን መንፈሳዊ ትርጉም በመስጠትና እስራኤልንና ቤተ ክርስቲያንን አንድና የማይለያዩ በማድረግ ነው። የእስራኤልን የወደፊት መታደሰና የሺህ ዓመቱን መንግሥት የሚቀበሉ ሌሎች ክፍሎች ደግሞ አዲስ ኪዳን አዲሱን ቃል ኪዳን ይመለከታል ይሳሉ። 

ይኸውም እስራኤል ካቤተ ክርስቲያን ጋር የሚኖራትን የወደፊት ቃል ኪዳን ወይም ሁለት እዲስ ቃል ኪዳኖችን ለመለየት (አንዱ በኤርምያስ የተገለጠውና ለእስራኤል የተሰጠው ሲሆን፥ ሌላው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት በአሁኑ የጸጋ ዘመን የተሰጠውና ለቤተ ክርስቲያን ድነት የሆነው አዲስ ቃል ኪዳን ነው) ነው በማለት ያስገነዝባሉ። እርግጥ አዲሱ ቃል ኪዳን የተሰጠው ለእስራኤልም ይሁን ለቤተ ክርስቲያን የሚገኘው በክርስቶስ ሞትና በፈሰሰው ደሙ ነው። 

እዲሱ ቃል ኪዳን እግዚአብሔር ከልጁ ደም የተነሣ ለሰዎች ሊያደርግ ያቀዳቸውን ነገሮች ሁሉ ያረጋግጣል። ይህም በሚከተሉት ሁለት መንገዶች ሊታይ ይችላል። 

(ሀ) በክርስቶስ የሚያምኑትን ሁሉ ያድናቸዋል፥ ይጠብቃቸዋል። ልጁን መስለው በመንግሥተ ሰማያት እንዲኖሩ ያስችላቸዋል። ለመዳን በኢየሱስ ክርስቶስ የማመኑ አስፈላጊነት እውነታ በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ እንደ ቅድመ ሁኔታ የተጠቃለለ ጉዳይ አይደለም። ማመን የቃል ኪዳኑ ክፍል ሳይሆን፥ ከዚያ ወደሚገኘው ዘላለማዊ በረከት ለመድረስ የሚያስችል መሠረት ነው። ቃል ኪዳኑም በቀጥታ የሚገናኘው ካልዳኑት ጋር ሳይሆን ከዳኑት ጋር ሆኖ ስለ እነርሱ የእግዚአብሔርን ታማኝነት ተስፋ ይሰጣል። ይህም፥ 

“በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ተረድቼአለሁና” ተብሎ በተጻፈው ቃል ተረጋግጧል (ፊልጵ. 1፡6)። የእግዚአብሔርን የማዳንና የመጠበቅ ኃይል የሚገልጠው ሌላ ተስፋ ሁሉ በጸጋ የዚሁ ቃል ኪዳን አካል ነው። 

በአሁኑ ዘመን በምድር ለሰው ፍጹም ጥበቃን የማያረጋግጥና በመጨረሻም የዳነውን በክብር የማያቀርብ ድነት ከቶ የለም። በአብና ክርስቲያን በሆነ ልጁ መካከል የየዕለት ሕይወትን የሚመለከት ጉዳይ ሊኖር ይችላል። ዳዊት ኃጢአት በሠራ ጊዜ እንደሆነው ሁሉ፥ የክርስቲያንም ኃጢአት ከእግዚአብሔር ቅጣትን ያስከትል ይሆናል። ነገር ግን በአማኝ ዕለታዊ ሕይወት ውስጥ የሚነሡ ጥያቄዎች እግዚአብሔር በጸጋ በተቀበላቸው ሰዎች የዘላለም ድነት ተስፋ ላይ ከቶ ምንም የቅድመ ሁኔታ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ አይችሉም። 

በሰው ፈቃድ፥ ኃይልና አስፈላጊነት ላይ ትኩረት የሚሰጡ ወገኖች አሉ። በዚህ አመለካከታቸው መሠረት የድነትና ሰላም መጠበቅ በሰው ፈቃድ ትብብር ቅድመ ሁኔታ መከናወን አለበት ይላሉ። አባባሳቸው በሰው አእምሮ ሲገመገም ትክክል ቢመስልም፥ መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው መገለጥ ላይ የተመሠረተ አይደለም። 

በማንኛውም ሁኔታ እምነታቸውን ሰርሱ ለሚያደርጉ ሁሉ እግዚአብሔር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚያደርግላቸውን አውጇል (ዮሐ. 5፡24፤ 6፡37፤ 10፡28)። ይህ የእያንዳዱኝ ሰው እሳብና ልብ ሙሉ በሙሉ ሊገዛ ይገባል። እግዚአብሔር ለኖኅ፥ ዘሩ የሰጠውን ትዕዛዛት በሙሉ እንደሚከተሉ ወይም ደግሞ ለአብርሃም ታላቅ ሕዝብ እንደሚያደርገው እና ከዘሩ ክርስቶስ እንደሚወለድ ያወጀውን እንዳለ አምኖ የመቀበልን ያህል ለሕሊና አስቸጋሪ አይሆንምና። 

በማንኛውም ረገድ ሲሆን ይህ ጉዳይ የሉዓላዊ ኃይልና ሥልጣን መግለጫ ነው። እግዚአብሔር ለሰው ፈቃድ ነጻነትን መስጠቱ ይታወቃል። እርሱ የሰዎችን ፈቃድ ይመለከታል። የዳኑ ሰዎችም ድነትና አገልግሎታቸው በምርጫቸው እንደሆነ እርግጠኞች ናቸው። እግዚአብሔር የሰዎችን ፈቃድ የሚቆጣጠር መሆኑ ተነግሮናል (ዮሐ. 6፡44፤ ፊል. 2፡13)። እንዲሁም የሰውን ፈቃድ የሚፈልግና በረከቱንም በዚያ ላይ እንደሚመሠረት እንረዳለን (ዮሐ. 5፡40፤ 7፡17፤ ሮሜ 12፡1፤ 1ኛ ዮሐ. 1፡9)። 

መጽሐፍ ቅዱስ ለእግዚአብሔር ሉዓላዊነት የማያወላውል ትኩረትን ይሰጣል። መሆን ያለበትን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር በትክክል ወስኗል፤ ያም መፈጸም አለበት። እርሱ ሰሚሆኑት ነገሮች ለመጸጸት ወይም ለመደነቅ አይችልም። እንዲሁም የእግዚአብሔር የማይለወጥ ታላቅነት ሁለት አቅጣጫዎች፥ ማለት ዘላለማዊ ዓላማና ትክክለኛ ተፈጻሚነቱ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እኩል ትኩረት ተሰጥቷቸዋል። ለሰብዓዊ ፈቃድ አንዳንድ ክንዋኔዎች በቂ ነጻነትን ቢሰጥም ዓላማው በምንም ሁኔታ አይሰናከልም። የዚህን እውነት አንድ ገጽታዎች ከሌሳው ለይቶ መመልከት፥ በአንድ በኩል ወደ ጸሎት ልምምድ ወደማያደርስ፥ የእግዚአብሔርን ፍቅር ለመግጠን ወደማይቻልበት፥ ለፍርድ የሚሆን መሠረት ወደሌለበት፥ ለወንጌል ሥራ አሳብን የሚስብ ፍሬ ወደማያፈራበትና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ፍቺም ትርጉም ወደማይሰጥበት ያደርሳል። በሌላ አባባል እግዚአብሔርን ከዙፋኑ ወደማውረድ አዝማሚያ ያመራል። የሰው ፈቃድ በእግዚአብሔር ቁጥጥር ሥር ሊሆን እንደሚችል ማመኑ ተገቢ ነው። የእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ከሰው ፈቃድ ጋር የተያያዘ ነው ብሎ ማመን ግን መሠረት የለሽ አሳብ ነው። ያመኑ ሁሉ የዳኑና ለዘላለም የማይጠፉ ናቸው፤ ምክንያቱም ድነታቸው ቅድመ ሁኔታ በሌለው የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ላይ ተመሥርቷል። 

(ለ) የእስራኤል የወደፊት ድነት ከቅድመ ሁኔታ ነጻ በሆነ አዲስ ኪዳን የተሰጠ ተስፋ ነው (ኢሳ. 27:9፤ ሕዝ. 37 ፡23፤ ሮሜ 11፡26-27 )። ድነቱ የሚፈጸመው በፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ብቻ ነው። ከክርስቶስ መሥዋዕትነት የተነሣ እግዚአብሔር ግለሰብን ለማዳን ፈቃዱ እንደሆነ ሁሉ፥ ሕዝብንም ለማዳን ይፈቅዳል። በክርስቶስ ትምህርት መሠረት እስራኤል በእርሻ ውስጥ የተሰወረች መዝገብን ትመሰላለች። እርሻው ዓሰም ነው። ያንን መዝገብ ለመግዛትና የራሱ ላማድረግ ያለውን ሁሉ የሸጠው ክርስቶስ እንደሆነ እናምናለን (ማቴ. 13፡44)። 

ስምንቱ ቃል ኪዳኖች በሚመረመሩበት ጊዜ፥ ከቅድመ ሁኔታ ነፃ የሆኑ ቃል ኪዳኖችን በተመለከተ በእግዚአብሔር ታላቅነት ላይ ብቻ ብዙ ማተኮር ይገባል። ይህ የሚሆነው፥ በቅድመ ሁኔታ ላይ ተመሠረቱና ሰውም ከቶ ከማይቻለው ቃል ኪዳኖች መፈጸም ጋር ሲነጻጸር ነው። እግዚአብሔር ከቅድመ ሁኔታ ነጻ አድርጎ የሚፈጽመው ማንኛውም ነገር የሚከናወነው፥ ከእርሱ ፍጹምነት የተነሣ ነው።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading