እግዚአብሔር ወልድ፡ መለኮታዊነቱና ዘላለማዊነቱ

መጽሐፍ ቅዱስ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም ሰውና ፍጹም መለኮት አድርጎ ያቀርበዋል። በዚህ መሠረት እንደ ማንኛውም ሰው ነው፥ አይደለም። በዮሐንስ 1፡14፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡ 16 እና ዕብራውያን 2፡14-17 መሠረት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰው የተወለደ፥ በሰዎች መካከል የኖረ፥ የተሠቃየ እና የሞተ መሆኑ ተገልጧል። ኢየሱስ ክርስቶስ ከዘላለም በፊት የነበረ በመሆኑ፥ እንደ ሰው አለመሆኑን፥ በሰብአዊነቱ ኃጢአትን የማያውቅ መሆኑን፥ ሞቱ ለዓለም ሁሉ ኃጢአት መሥዋዕት መሆኑን፥ ከሙታን ተለይቶ በመነሣትና ወደ ሰማይ በማረግ መለኮታዊ ኃይሉን የገለጠ መሆኑን በማስገንዘብ ረገድም መጽሐፍ ቅዱስ ግልጥ ነው። 

በሰብአዊነቱ ጅማሬ ነበረው፤ ከመንፈስ ቅዱስ ተፀንሶ ከድንግል ማርያም ተወልዷል። በመለኮታዊነቱ ግን ከዘላለም በፊት የነበረ በመሆኑ ጅማሬ የለውም። ኢሳይያስ 9፡6 ውስጥ “ሕፃን ተወልዶልናል፤ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል” የሚል ትንቢት ተነግሮ ነበር። በተወለደ ሕፃንና በተሰጠ ልጅ መካከል ያለው ልዩነት ግልጥ ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ ገላትያ 4፡4 ውስጥ እንዲህ ተብሏል፡- “… የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን፥ ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ”። ዘላለማዊው የእግዚአብሔር ልጅ ሥጋ በመልበስ “ ከሴት ተወሰደ። 

ክርስቶስ ከመወለዱ በፊት ነባሪ ነው፥ የሚለው ገለጣ ከመወለዱ በፊት መኖሩን በቀላሉ ያረጋግጣል። የፍጥረታት ሁሉ በኩር ሆኖ ብቻ ይኖር ነበር፥ የሚለው አስተሳሰብ (በአራተኛው ክፍለ ዘመን የነበረ አርዮሳዊ ኑፋቄን፥ የጊዜያችን ትምህርት አይደለም። ስለዚህ የቀዳሚ ነባሪነቱና የዘላለማዊነቱ ማረጋገጫዎች ጣምራ ናቸው። ክርስቶስ እግዚአብሔር ከሆን ዘላለማዊ መሆኑ፥ ዘላለማዊ ከሆነ እግዚአብሔርነቱ እርግጥ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ መለኮትነትና ዘላለማዊነት የሚደጋገፉ ናቸው። 

የኢየሱስ ዘላለማዊነትና መለኮትነት በሁለት መንገድ ተገልጧል፡- (1) ቀጥተኛ ገለጣ (2) በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠ። 

ሀ. የእግዚአብሔርን ልጅ ዘላለማዊነትና መለኮትነት ቀጥተኛ ገለጣ 

የኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊነትና መለኮትነት እጅግ ሰፊ በሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በተመዘገበው ቃል ተረጋግጧል። ይህም ከሴሳው የሥላሴ አካል ከአብ ጋር አቻነቱን፥ ፍጹምነቱንና ዘላለማዊነቱን ያረጋግጣል። ይህ እውነት ክርስቶስ ሥጋ በመልበሱ ሳቢያ አልተዛባም። 

መጽሐፍ ቅዱስ ዮሐንስ 1፡ 1-2 ውስጥ የመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። “ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነው አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም” ይላል። በትንቢተ ሚክያስ 5፡2 ሲገለጥ ደግሞ 

“አንቺ ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ! አንቺ ከይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፥ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤል ላይ ገዢ የሚሆን ይወጣልኛል” ተብሏል። ኢሳይያስ 7፡ 14 ውስጥ ደግሞ፥ ከድንግል መወለዱን አረጋግጦ እማኑኤል የሚል ስም ይሰጠዋል፤ ትርጉሙም “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” ማለት ነው። በኢሳይያስ 9፡6-7 መሠረት፥ ኢየሱስ እንደ ሕፃን ቢወለድም፥ እንደ ወንድ ልጅም የተሰጠ ነው። ይህ ብቻም አይደለም፥ “ኃያል አምላክ” ተብሏል። ክርስቶስ ራሱ ዮሐንስ 8፡58 ውስጥ ሲገልጥ፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ” ብሏል። 

ይህ አገላለጥ፥ መለኮታዊነትንና ዘላለማዊነትን እንደሚያመለክት አይሁድ ተገንዝበዋል (ዘጸ. 3፡ 14፤ ኢሳ. 43፡13)። ዮሐንስ 17፡5 ውስጥ እንደተጠቀሰው ደግሞ፥ ክርስቶስ በጸሎቱ፥ “አሁንም አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አክብረኝ” ብሏል (ይህን ቃል ከዮሐ. 13፡3 ጋር ያነጻጽሩት)። ፊልጵስዩስ 2፡6-7 ውስጥ ክርስቶስ ሥጋ ከመልበሱ በፊት “በእግዚአብሔር መልክ” እንደነበር ተገልጧል። 

ከሁሉም ግልጥ የሆነው ማስገንዘቢያ የሚገኘው፥ ቆላስይስ 1፡15-19 ውስጥ ነው። በዚያ ስፍራ ክርስቶስ ከፍጥረት በፊት እንደነበር፥ ራሱ ፈጣሪ እንደሆነ እናየማይታየው አምላክ ምሳሌ እንደሆነ ተገልጧል። 1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡ 16 ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ “በሥጋ የተገለጠ አምላክ” ተብሏል። ዕብራውያን 1፡2-3 ውስጥም ወልድ ፈጣሪ እና የተገለጠ የእግዚአብሔር አምሳል መሆኑ እንደገና ተገልጧል። ዘላለማዊነቱም ዕብራውያን 13፡ 8 ውስጥ ተረጋግጧል (ይህን ማረጋገጫ ከኤፌሶን 1፡4፤ ራእይ 1፡8 ጋር ያነጻጽሩት)። ክርስቶስ ዘላለማዊ እና አምላክ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ አበክሮ ይገልጣል። ጥቂት ከሃዲ የአምልኮ ክፍሎች ሲቀሩ፥ መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ ሥልጣን ያለው መሆኑን የሚቀበሉ የጊዜያችን ምሁራን ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊና መለኮታዊ መሆኑን ያረጋግጣሉ። 

ለ. የእግዚአብሔርን ልጅ ዘላለማዊነት የሚያመለክቱ ሁኔታዎች 

የእግዚአብሔር ቃል፥ የኢየሱስ ክርስቶስን ከዘላለም በፊት ኗሪነትና ዘላለማዊነት በተከታታይና ባለማቋረጥ ያመለክታል። የዚህ እውነት ግልጥ ማረጋገጫ ከሆኑት አንዳንዶቹን ለመጥቀስ ይቻላል። 

1. ተፈጥሮ በክርስቶስ እንደተከናወነ ተገልጧል(ዮሐ. 1፡ 3፤ ቆላ. 1፡16፤ ዕብ. 1፡ 10)። ስለዚህ ከፍጥረታት ሁሉ ይቀድማል። 

2. የእግዚአብሔር መልአክ መታየቱ ብሉይ ኪዳን ውስጥ ተመዝግቧል፤ የያዌ መልእክ ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ሊሆን አይቻልም። አንዳንድ ጊዜ እንደ መልአክ ከዚያም አልፎ እንደ ሰው ቢታይም፥ የማያሳስት የመለኮትነት መገለጫ አለው። ለአጋር ተገልጧል፥ (ዘፍጥ. 16፡7)፥ ለአብርሃም (ዘፍጥ. 18፡ 1፤ 22 ፡ 11-12፤ በተጨማሪ ዮሐ. 8፡58ን ልብ ይብሉ)፥ ለያዕቆብ (ዘፍጥ. 48፡ 15-16፥ እንዲሁም ዘፍጥ. 31፡11-13፤ 32፡24-32)፥ ለሙሴ፥ (ዘጸ. 3፡2፥14)፥ ለኢያሱ፥ (ኢያ. 5፡13-14)፥ እና ለማኑሄ፥ (መሳ. 13፡ 19-22)። የራሱ ለሆኑ የሚዋጋና የሚጠብቃቸው እርሱ ነው (2ኛ ነገሥት 19፡35፤ 1ኛ ዜና 21፡ 15-16፤ መዝ. 34፡7፤ ዘካ. 14፡ 1-4)። 

3. የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መጠሪያዎችና ማዕረጎች ዘላለማዊነቱን ያመለክታሉ። እርሱ በትክክል እንደ ስሙ ነው። “የእግዚአብሔር ልጅ”፥ “አንድያ ልጅ”፥ “የመጀመሪያውና የመጨረሻው ፥ “አልፋና ኦሜጋ”፥ “ጌታ”፡ (“የሁሉ ጌታ”፥ “የክብር ጌታ”፥ “ክርስቶስ”፥ “ድንቅ”፥ “መካር”፥ “ኃያል አምላክ”፥ “የዘላለም | አባት”፥ “እግዚአብሔር ከኛ ጋር”፥ “ታላቅ አምላካችን” እና “ለዘላለም የተባረከ አምላክ። 

እነዚህ መጠሪያዎች ኢየሱስን በብሉይ ኪዳን ከተገለጠው ያህዌ- አምላክ ጋር ያዛምዱታል (ማቴ. 1፡23፥ ይህን ካኢሳ. 7፡ 14 ጋር ያነጻጽሩት፥ ማቴ. 4፡7ትን ደግሞ ከዘዳ. 6፡ 16 ጋር፥ ማር. 5፡ 19ን ከመዝ. 66፡ 16 ጋር እና ማቴ. 22፡42-45ትን ከመዝ. 110፡1 ጋር ያነጻጽሩ)። 

አዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሱት የእግዚአብሔር ልጅ ስሞች ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ መጠሪያዎች ጋር ተዛምደዋል። ይህም ከአካላቱ ጋር ያለውን አቻነት ያመለክታል (ማቴ. 28፡19፤ ዮሐ. 14፡1፤ 17፡3፤ ሐዋ. 2፡ 38፤ 1ኛ ቆሮ. 1፡3፤ 2ኛ ቆሮ 13፡ 14፤ ኤፌ. 6፡23፤ ራዕ. 20፡6፤ 22፡3)። በማያሻማ ሁኔታም እግዚአብሔር ተብሏል (ዮሐ. 1፡ 1፤ ሮሜ. 9፡5፤ ቲቶ 2፡ 13፤ ዕብ. 1፡8)። 

4. የእግዚአብሔር ልጅ ከዘላለም በፊት ኗሪነቱና ዘላለማዊነቱ፥ የእግዚአብሔር ባሕርያት ያሉት መሆኑን በሚያስገነዝቡት እውነቶች ውስጥ ተመልክቷል። ሕይወት (ዮሐ. 1፡4)። ኗሪ (ዮሐ. 5፡26)፥ የማይለወጥ ወይም የማይሻር (ዕብ. 13፡8)፥ እውነት (ዮሐ. 14፡6)፥ ፍቅር (1ኛ ዮሐ. 3፡ 16)፥ ቅድስና (ዕብ. 7፡26)፥ ዘላለማዊነት (ቆላ. 1፡17፤ ዕብ. 1፡ 1 1 )፥ በሁሉም ስፍራ መገኘት (ማቴ. 28፡20)፥ ሁሉን አዋቂነት (1ኛ ቆሮ. 4 ፡ 5፤ ቆላ. 2፡3) እና ሁሉን ቻይነት(ማቴ. 28፡ 18፤ ራእይ 1፡8)። 

5. በተመሳሳይ ሁኔታ ከዘላለም በፊት ኗሪነቱና ዘላለማዊነቱ፥ እንደ እግዚአብሔር በመመሰኩ እውነት ውስጥ ተገልጧል (ዮሐ. 20፡28፤ ሐዋ. 7:59-60፤ ዕብ. 1፡6)። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር እንደመሆኑ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ኗሪ ነው። 

የእግዚአብሔር ልጅ መለኮትነትና ዘላለማዊነት ጉዳይ፥ ከክርስቶስ ከሰብአዊ ልደት ወይም ሥጋ መልበስ ጋር በቅርብ መያያዝ አለበት። ይህ ነው የሚቀጥለው ምዕራፍ መነጋገሪያችን።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: