ከኃጢአት ቅጣት መዳን

ሀ. የድነት ትርጉም 

ድነትን የሚመለከተው መለኮታዊ መገለጥ፥ በእምነት የእግዚአብሔር ልጅ በሆነ ሰው ሁሉ በሚገባ መታወቅ አለበት። ምክንያቱም፡- (1) የግል ድነት የሚመሠረተው በርሱ ላይ ስለሆነ፥ (2) አማኝ ለዓለሙ ሁሉ እንዲያውጀው እግዚአብሔር የሰጠው ዋነኛ መልእክት ስለሆነና፥ (3) የእግዚአብሔርን ፍቅር በሙላት የሚገልጠው መለኪያ ይኸው ብቻ ስለሆነ ነው። 

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጠው ሰፊ ትርጉም መሠረት፥ “ድነት” የሚለው ቃል እግዚአብሔር ሰውን ከዘላለም የኃጢአት ጥፋትና ፍርድ ያዳነበትን አጠቃላይ ሥራ ያመለክታል። የጸጋውን ባለጠግነት፥ ዘላለማዊ ሕይወትና ዘላለማዊ ክብርን በሰማይ ለኃጢአተኛው የተሰጠ መሆኑንም ያስገነዝባል። “ድነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” (ዮናስ 2፡9)። ስለዚህ ድነት በሁሉም መልኩ በሰው ፈንታ እግዚአብሔር የሠራው እንጂ፥ በምንም ሁኔታ ሰው በእግዚአብሔር ፈንታ የሠራው አይደለም። 

የዚህ መለኮታዊ ሥራ አንዳንድ ዝርዝር ሁኔታዎች ከዘመን ዘመን የተለያዩ ናቸው። ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ በነበረው ዘመን እምነታቸውን በእግዚአብሔር ላይ የጣሉ ሰዎች በመንፈስ እንደገና ተወልደው የሰማያዊ ክብር ወራሾች መሆናቸው ተረጋግጦላቸዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ የእስራኤል መንግሥት ጌታ በሚመለስበት ጊዜ በአንድ ቀን በመንፈስ ትወለዳለች (ኢሳ. 66፡8)። 

ደግሞም በሚመጣው መንግሥት የሚኖሩ ከአይሁድና ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሁሉ ከትንሹ እስከ ትልቁ ጌታን ያውቁታል ተብሏል (ኤር. 31፡34)። ይሁን እንጂ፥ በአሁኑ ዘመን ለሰዎች የተሰጠው ድነት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዝርዝር መስፈሩ ብቻ ሳይሆን፥ በሚሠራቸው አስደናቂ ነገሮች ከሌሎች የእግዚአብሔር የማዳን ሥራዎች ሁሉ ይልቃል። የድነት ትምህርት፥ የመንፈስ ቅዱስን በአማኞች ውስጥ ማደር፥ ማተምና የመንፈስ ጥምቀት የመሳሰሉትን የእግዚአብሔር የጸጋ ሥራዎች ይጨምራል። 

ለ. ድነት፥ ለኃጢአት እግዚአብሔር ያዘጋጀው መፍትሔ 

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኃጢአት በሚያቀርባቸው ትምህርቶች አንዳንድ ልዩነቶች ቢኖሩም፥ የሚከተሉት ሁለት አጠቃላይ እውነታዎች በቅድሚያ መታወቅ ይኖርባቸዋል። 

1. ኃጢአት ባልሰለጠነ ወይም በሰለጠነ ሰው፥ ዳግም በተወለደ (በክርስቲያን) ወይም ባላመነ ሰው ሲሠራ፥ ሁሉንም እኩል ነው ኃጢአተኛ የሚያደርጋቸው። በፍርድ ወቅት ኃጢአተኛ ለበደሉ ብዙ ወይም መለስተኛ ቅጣት የሚቀበል መሆኑ ግልጥ ነው (ሉቃስ 12፡47-48)። ይሁን እንጂ፥ ኃጢአት ሁሉ ቅዱስ በሆነው በእግዚአብሔር ፊት ልዩነት የለውም። ምክንያቱም፥ ኃጢአት ከጌታ ቅዱስ ባሕርይ ጋር በፍጹም የሚሄድ አይደለም። 

ኃጢአት ሊፈወስ የሚችለው በፈሰሰው የእግዚአብሔር ልጅ ደም ብቻ ነው። ይህ ፈውስ የእንስሳት መሥዋዕት በማቅረብ በትንቢታቸው የክርስቶስን ሞት ለተነበዩም ሆነ ያን የክርስቶስ ሞት ወደኋላ በእምነት ለሚመለከቱ ሁሉ ይሠራል። የኃጢአትን ቅጣት በተመለከተ፥ መለኮታዊው ይቅርታ ቅጣትን የማሳሳት ድርጊት አይደለም። ኃጢአት ይቅር የተባለው በኃጢአተኛው ፈንታ ቅጣትን የሚቀበል ምትክ ስለቀረበ ነው። በአሮጌው ሥርዓት ኃጢአተኛው ይቅርታ የሚያገኘው፥ ሕጉ እንደሚያዘው የኃጢአት ማስተሥረያ የሆነውን የደም መሥዋዕት ካህኑ ካቀረበ በኋላ ነው። ይህ ሁኔታ ኃጢአተኞች ይቅርታ ያገኙበትን የክርስቶስ ሞት አስቀድሞ የሚያመለክት ነበር (ዘሌ. 4፡20፥ 26፥ 31፥ 35፤ 5፡10፥ 13፥ 16፥ 18፤ 6፡7፥ 19፡20፤ ዘኁ. 15፡25፥ 26፥ 28)። ከክርስቶስ ሞት በኋላ በቃሉ፥ “በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን፥ እርሱም የበደላችን ሥርየት” (ኤፌ. 1፡7፤ ቆላ. 1፡14) ተብሎ እንደተጻፈ ይሄው እውነት ተፈጽሟል። 

ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ያከናወነው የምትክነት ሥራ ፍጹም ብቃትና ሙላት ያለው ነው። ስለሆነም በክርስቶስ የሚያምን ኃጢአተኛ ሁሉ ይቅርታ የሚያገኝ ብቻ ሳይሆን፥ ለዘላለም የሚጸድቅ ነው (ሮሜ 3፡24)። እግዚአብሔር ምንጊዜም ቢሆን ኃጢአትን በዋዛ እልፎ አያውቅም። የኃጢአት ይቅርታ በኃጢአተኛ ላይ ምንም ዓይነት ሸክም እይጭንበትም። ምክንያቱም ከባዱ መለኮታዊው የኃጢአት ቅጣት ክርስቶስ ላይ ስላረፈ ይቅርታ አግኝቷል፥ ጸድቋልም (1ኛ ጴጥ. 2፡24፤ 3፡18)። 

ሐ. ድነት፥ ከመሰቀሉ በፊትና በኋላ 

1. ከክርስቶስ የመስቀል ሞት በፊት የኃጢአት ይቅርታ የሚያስገኘው መለኮታዊ አሠራር የማስተሥረያ መሥዋዕት ነበር። ማስተሥረይ የሚለው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ትርጉሙ “መሸፈን” ማለት ነው። የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን ሊያስወግድ አልቻለም፥ አይችልምም (ዕብ. 10፡4)። የደም መሥዋዕት በኃጢአተኛው በኩል የሚያመለክተው፥ የእግዚእብሔርን ጻድቅ ፍርድ ወይም ቅጣት መቀበልን ነው (ዘሌዋ. 1፡4)። በእግዚአብሔር በኩል ደግሞ መሥዋዕቱ ያመለክት የነበረው፥ ሊመጣ ያለውንና አጥጋቢ ወይም ብቁ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነበር። በመሥዋዕትነት ይቀርብ የነበረው የማስተሥረያ ደም፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ምሳሌ በመሆን ኃጢአትን ይሸፍን ነበር። ይህ ይሆን የነበረው ክርስቶስ የዓለምን ኃጢአት ለዘላለም እስከሚያስወግድበት ዕለት ነበር። “ማስተሥረይ” ወይም “መሽፈን” የሚለው የብሉይ ኪዳን ቃል፥ ማሳለፍ የሚል አሳብን ይዟል። 

1. ለምሳሌ ሮሜ 3፡25 ውስጥ “ማስተሥረይ” የሚለው ቃል “ማሳለፍ” የሚል ትርጉም አለው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ክርስቶስ በሞተ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ከመስቀሉ በፊት የተሠሩ ኃጢአቶችን በማሳለፍ ጻድቅነቱን አሳይቷል። እነዚያ ኃጢአቶች ለማስተሥረያ የደም መሥዋዕት የቀረበባቸው ነበሩ። እግዚአብሔር ብቁ የመሥዋዕት በግ እንደሚሰጥ እና፥ በብርቱ ተስፋው መሠረትም ኃጢአትን ይቅር እንደሚል ተናግሮ ነበር። በመሆኑም በክርስቶስ ሞት አማካይነት በሰጣቸው ተስፋዎቹ ሁሉ ጻድቅ መሆኑን እረጋገጠ። 

2. ኢየሱስ በመስቀሉ ላይ ከሞተ ወዲህ እግዚአብሔር ኃጢአትን የሚመለከትበት ሁኔታ ሮሜ 3:26 ውስጥ ተገልጧል። ክርስቶስ ሞቷል። ይህ መሥዋዕትነት ከእንግዲህ ገና እንደሚፈጸም ተስፋና በእንስሳት ደም ተምሳሌትነት የሚታይ አይደለም። አሁን ማንኛውም ሰው፥ የቱንም ያህል ኃጢአተኛ ቢሆን፥ እንዲያደርግ የሚጠየቀው፥ ፍጹም በሆነ ጸጋ እማካይነት ለርሱ በተከናወነው ማዳን እንዲያምን ነው። እግዚአብሔር በእያንዳንዱ ኃጢአተኛ ላይ ያለውን መለኮታዊ ፍርድ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ከፍሏል። ይህን በማድረግም ጽድቁን፥ ወይም ቅድስናውን የማይፃረር መሆኑንና በአንጻሩም ከቅጣቱ ባሻገር በኢየሱስ የሚያምን ኃጢአተኛን የሚያጸድቅ መሆኑን አረጋግጧል። 

“ሥርየት” የሚለውና በብሉይ ኪዳን ብቻ በሚገባ ይከናወን የነበረው ቃል ኃጢአትን ለጊዜው ማሳለፍን”፥ “ይቅር ማለትን” እና “መሸፈንን” ያመለክት ነበር። ክርስቶስ መስቀሉ ላይ ኃጢአትን በቀላሉ አላሳለፈም፥ ወይም አልሸፈነም። ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ተሸከመው። ለሁሉ ስለሚበቃው መሥዋዕትነቱም፥ “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” ተብሎ ተመስክሮለታል (ዮሐ. 1፡29፤ ቆላ. 2፡14፤ ዕብ. 10፡4፤ 1ኛ ዮሐ. 3፡5)። ደግሞም “እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ” (1ኛ ጴጥ. 2፡24) ተብሏል። መስቀሉ ላይ ኃጢአትን ለጊዜው ወይም በከፊል የማየት ጉዳይ አልነበረም። ይህ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለ ታላቅ ጉዳይ የእግዚአብሔርን ፍጹም ቅድስና በሚያረካ ሁኔታ ተከናውኗል። ቀሪው ጥያቄ በዚህ እግዚአብሔርን ባረካ መሥዋዕት ሰውስ ረክቷል ወይ? የሚለው ነው። ለኛ የክርስቶስን ሥራ መቀበል ማለት፥ ነፍስን በሚያድነው አዳኝ ማመን ማለት ነው። 

መ. የድነት ሦስቱ ጊዜያት 

1. በሰዋስዋዊ አገላለጥ የድነት ኃላፊ ጊዜ በአንዳንድ የቅዱሳት መጻሕፉት ክፍል ተመልክቷል። እነዚህ የመጻሕፍት ክፍሎች ስለ ድነት በሚናገሩበት ጊዜ፥ ለአማኙ ሙሉ በሙሉ ያለፉ ወይም የተፈጸሙ የሚሆኑ ናቸው (ሉቃስ 7፡50፤ 1ኛ ቆሮ. 1፡18፤ 2ኛ ቆሮ. 2፡15፤ ኤፌ. 2፡5፡8)። ይህ መለኮታዊ ሥራ ፍጹም ስለሆነ፥ አማኝ የዘላለም ድነት ዋስትና አለው (ዮሐ. 5፡24፤ 10፡28፥ 29፤ ሮሜ 8፡1)። 

2. ድነት የአሁን ጊዜ መሆኑን የሚያመለክተውና፥ በሚቀጥለው ምዕራፍ የሚብራራው ጉዳይ፥ በዚህ ዘመን በዓለም ነግሦ ከሚገኘው የኃጢአት ኃይል መዳንን ያስገነዝባል (ሮሜ 6፡14፤ 8፡2፤ 2ኛ ቆሮ. 3፡18፤ ገላ. 2፡19-20፤ ፊሊ. 1፡19፤ 2፡12-13፤ 2ኛ ተሰ. 2፡13)። 

3. ድነት የወደፊት ጊዜ ሆኖ በቀረበበት ክፍል የሚገልጠው ደግሞ አማኝ በእምነት ሙሉ በሙሉ ክርስቶስን እስከ መምሰል ድረስ የሚድን በመሆኑ ላይ ያተኩራል (ሮሜ 8፡29፤ 13፡11፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡5፤ 1ኛ ዮሐ. 3፡2)። የድነት አንዳንድ ሁኔታዎች ለአማኙ የሚፈጸሙለት ወደፊት ነው የሚለው አባባል እውነትነት፥ ስለ መጨረሻው ፍጻሜ ጥርጥር አለ ማለት አይደለም። ምክንያቱም የድነት የወደፊት ሁኔታ በአማኙ ታማኝነት ላይ ይመሠረታል፥ የሚል ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም። እግዚአብሔር ታማኝ ነው፥ የጀመረውን መልካም ሥራ እስከ ኢየሱስ ቀን ድረስ ይፈጽመዋል (ፊልጵ. 1፡6)። 

ሠ. ድነት፥ በክርስቶስ የተፈጸመ ሥራ 

እግዚአብሔር ለጠፉ ሰዎች ያከናወነው ሥራ በሚታሰብበት ጊዜ፥ ክርስቶስ ለሁሉ ባከናወነው ፍጹም ሥራና፥ አማኝ በክርስቶስ በሚያምንበት ጊዜ እግዚአብሔር በሚፈጽመው የድነት ሥራ መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘቡ ጠቃሚ ነው። 

ኢየሱስ ነፍሱን ከመስጠቱ በፊት “ተፈጸመ” የሚል የመጨረሻ ቃል እንደተናገረ ተጽፏል (ዮሐ. 19፡30)። ይህን በተናገረ ጊዜ ያመለከተው ስለ ራሱ ሕይወት፥ ስለ አገልግሎቱ ወይም ስለ ሥቃዩ ሳይሆን፥ አብ የሰጠው ልዩ ሥራ መፈጸሙን ለማመልከት ነበር። ይህ ሥራ ኢየሱስ እስከተሰቀለበት ጊዜ ድረስ አልተፈጸመም ነበር። ፍጻሜ ያገኘውም በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ ነው። ለዓለም ሁሉ የተከናወነ ሥራ ነበር (ዮሐ. 3፡16፤ ዕብ. 2፡9)። ሥራው የቤዛነት (1ኛ ጢሞ. 2፡6)፥ የማስታረቅ (2ኛ ቆሮ. 5፡19)። እንዲሁም ለእያንዳንዱ ሰው የኃጢአት ማስተሥረያ (1ኛ ዮሐ. 2፡2) ነው። 

እግዚአብሔር ከቅድስናው ጋር በሚስማማ ሁኔታ ከኃጢአተኞች ክፉውን እንኳን ያድን ዘንድ መሠረት ይሆናል እንጂ፥ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞቱ ብቻውን ሰዎችን አያድንም። ይህ ነው ክርስቲያን ለዓለም ሁሉ ያውጅ ዘንድ የተሾመበት የምሥራች። የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ደም በጌታ ፊት እጅግ ክቡር ቢሆንም፥ ኃጢአተኞችን ለመዋጀት ተከፍሏል። ኃጢአት ኃጢአተኛውን ከእግዚአብሔር ለይቶት ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ራሱ ያን ኃጢአት ለዘላለም ለማስወገድ የመሥዋዕቱን በግ ሰጠ።

ይህ ሁሉ አስቀድሞ የተፈጸመ በመሆኑ ኃጢአተኛው መልእክቱን እንደ እግዚእብሔር ምስክርነት በእምነት እንዲቀበለው ይጠየቃል። ሰው ይህን መልእክት ሰምቶ ለኃጢአቱ ይቅርታ እንዳገኘና፥ የኃጢአት ችግር ተወግዶለት እፎይ ማለቱን ተገንዝቦ፥ እግዚአብሔርን ስለ ታላቅ በረከቱ ካላመሰገነ አምኗል ለማለት ያስቸግራል። 

ረ. ድነት፥ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ 

በአንድ ሰው መዳን ጊዜ የሚከናወነው የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ የተለያዩ የጸጋ ሥራ ደረጃዎችን ያጠቃልላል። እነርሱም ከኃጢአት ነፃነት፥ እርቅ፥ ማስተሰረይ፥ ይቅርታ፥ ዳግም ልደት፥ ውርስ፥ ጽድቅ፥ ቅድስና፥ ፍጹምነት፥ ክብር ናቸው። በዚህ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ አማካይነት ከቅዱሳን ጋር ወራሾች ለመሆን በቅተናል (ቆላ. 1፡12)፥ በውድ ልጁ ተቀባይነትን አግኝተናል (ኤፌ. 1፡6)፥ የእግዚአብሔር ጽድቅ ሆነናል (2ኛ ቆሮ. 5፡21)፥ ወደ እግዚአብሔር ቀርበናል (ኤፌ. 2፡13)፥ የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናል (ዮሐ. 1፡12)፥ የሰማዩ መንግሥት ዜጎች ሆነናል (ፊሊ. 3፡20)፥ አዲስ ፍጥረት ሆነናል (2ኛ ቆሮ. 5፡17)፥ የእግዚአብሔር ቤተሰብ ሆነናል (ኤፌ. 2፡19፤ 3፡15)፥ እና በክርስቶስ ፍጹም ሆነናል (ቆላ. 2፡10)። ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጅነትን ያገኘ ሰው፥ ከጨለማው ሥልጣን ድኖ ወደ ልጁ የዘላለም መንግሥት ተሸጋግሯል (ቆላ. 1፡13)። ከዚህም የተነሣ አሁን መንፈሳዊ በረከትን ሁሉ እግኝቷል (ኤፌ. 1፡3)። 

ከላይ ከተጠቀሱት አስደናቂ የእግዚአብሔር ሥራዎች ለመረዳት እንደሚቻለው፥ በክርስቶስ አምኖ የዳነ ሰው፥ ለበደሉ ይቅርታ አግኝቶ ለዘላለም ጸድቋል ስለተባለ የኃጢአት በደለኛነትና ቅጣት ተወግዶለታል። እግዚአብሔር ከክርስቶስ መስቀል ውጪ ማንንም ይቅር አይልም። ከክርስቶስ ሞት ወዲህ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚመጡትን ሁሉ ሊያድናቸው ይችላል። 

ሰ. ድነት፥ የዳነ ሰው ከኃጢአት ጋር ያለው ግንኙነት 

1. አንድ ሰው በክርስቶስ በሚያምንበት ጊዜ፥ ወዲያውኑ የድነቱ እንድ ክፍል የሆነውን የኃጢአት ይቅርታ ያገኛል። ለድነት የሚያበቁ ብዙ ነገሮችም በእግዚአብሔር ይሠሩለታል። በጸጋ አጠቃላይ ሥራ ከሚገኝ ድነትና በክርስቶስ አዳኝነት ከማመን ውጪ ግን ይቅርታ አይገኝም። 

2. ክርስቲያን በሚሠራው ኃጢአት ላይ የሚመጣውን መለኮታዊ ቅጣት በተመለከተ፥ የሚታየው ኃጢአቱ ብቻ ነው። በዚህ መሠረት የክርስቲያኑ ኃጢአት ይቅር የሚባለው፥ ለድነት በማመን ሳይሆን፥ ለሠራው ኃጢአቱ ንስሐ በመግባቱ ነው (1ኛ ዮሐ. 1፡9)። 

ኃጢአት በአማኝ ላይ የሚያስከትለው፥ ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ ከአብና ከወልድ ጋር ያለውን አንድነት ማጣት፥ እንዲሁም በራሱ ውስጥ ያለውን መንፈስ ቅዱስ ማሳዘን ነው። ያም ሆኖ ኃጢአት የሠራ ክርስቲያን ኃጢአቱን ሲናዘዝ አንድነቱ፥ ደስታው፥ በረከቱና ኃይሉ ይመለስለታል። 

ኃጢአት በአማኝ ላይ የሚያስከትለው ነገር በረከትን ማጣት ቢሆንም በንስሐ ይታደሳል። አማኝ የሚሠራው ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት የከፋ ውጤት አለው። የፈሰሰው የክርስቶስ ደምና እርሱ በሰማያት የሚያከናውነው ጥብቅና (ሮሜ 8፡34፤ ዕብ. 9፡24፤ 1ኛ ዮሐ. 3፡1-2) ባይኖር ኑሮ፥ ኃጢአት ክርስቲያንን ከእግዚአብሔር ለዘላለም ይለየው ነበር። ሆኖም ደሙ የሚያስተሰረይ (1ኛ ዮሐ. 2፡2) እና የጥበቃውም ዓላማ ጽድቅ በመሆኑ (1ኛ ዮሐ. 2፡1) ዋስትና አለን። ኃጢአት የሚያደርግ ክርስቲያን በአብ ዘንድ ጠበቃ ስላለው፥ ኃጢአት ቢያደርግ እንኳን ከኃጢአቱ የተነሣ ድነቱን አያጣም። ሆኖም ይህ እውነት ክርስቲያን ኃጢያትን ይሠራ ዘንድ ነፃነት የሚሰጠው አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ኃጢአትን አታድርጉ” የሚለው ይህ እውነት (1ኛ ዮሐ. 2፡1) በግልጥ ተጽፏል። አዳኛችን ስለ እኛ በሰማይ ጠበቃ መሆኑን መረዳቱ፥ ለማንኛውም ኃጢአት በቀላሉ እንዳንጋለጥ ሊያደርገን ይገባል እንጂ ኃጢአትን ለመሥራት አያበረታታንም። 

ሽ. በእምነት ብቻ የሚገኝ ድነት 

አዲስ ኪዳን ውስጥ 150 በሚሆኑ ስፍራዎች፥ ኃጢአተኛ ድነት የሚያገኘው በእምነት ብቻ መሆኑ ተገልጧል። አንድ ሰው ሲያምን በፈቃደኝነት በክርስቶስ ለመደገፍ ውሳኔን ያደርጋል። እምነት በሁለንተና የሚገለጥ እንጂ፥ የአእምሮ ወይም የስሜት ሥራ ብቻ አይደለም። የአእምሮ መስማማትና፥ የስሜት መነሣሣት ስላለ ብቻውን እውነተኛ እምነት አለ እያሰኝም። እምነት ግለሰብ ክርስቶስን ለመቀበል በፈቃዱ የሚፈጽመው ግልጥ እርምጃ ነው። 

መጽሐፍ ቅዱስ ከነዚህ ዋና ዋና እውነቶች ጋር ይስማማል። ነፍስን ማዳን የሚቻለው እግዚአብሔር ብቻ ሲሆን፥ ይህን የሚያደርገውም በልጁ መሥዋዕትነት በኩል ነው። ሰው ሌላ መዳኛ ሊኖረው እንደማይችል ተገንዝቦ፥ ለድነቱ ከራሱ ሥራ ይልቅ እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል ባከናወነው ሥራና በመልእክቱ ማመን አለበት። እምነት ሥራ ሳይሆን ጌታ በሠራው ላይ መደገፍ ነው። ስለዚህ ድነት ከእምነት በቀር በሌላ ነገር ላይ ከተመሠረተ፥ የድነት ትምህርት ባጠቃላይ ይዛባል። መለኮታዊው መልእክት “እመንና ጸልይ”፥ “እመንና ኃጢአትህን ተናዘዝ”፥ “እመንና የኢየሱስን ጌትነት መስክር”፥ “እመንና ተጠመቅ”፥ “እመንና ተለወጥ”፥ “እመንና ካሣ ክፈል” የሚል አይደለም። እነዚህ ስድስት ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰዋል። ቢሆንም ለድነታችን መሠረት ሆነው አይደለም። የድነት መሠረት እምነት ብቻ ነው። እነዚህ ነገሮች የማመንን ያህል ለድነት አስፈላጊ ቢሆኑ ኑሮ፥ የመዳን መንገድ በተጠቀሰባቸው ጥቅሶች ሁሉ ውስጥ በተገኙ ነበር (ዮሐ. 1፡12፤ 3፡16፥ 36፤ 5፡24፤ 6፡29፤ 20፡31፤ ሐዋ. 16፡31፤ ሮሜ 1፡16፤ 3፡22፤ 4፡5፥ 24፤ 5፡1፤ 10፡4፤ ገላ. 3፡22)። ድነት የሚገኘው በክርስቶስ ብቻ ነው፤ ሰዎች የሚድኑት እርሱን የግል አዳኛቸው እድርገው የተቀበሉት እንደሆነ ብቻ ይሆናል።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: