የማቴዎስ ወንጌል ጥናት መምሪያ እና ማብራሪያ
ምልከታ እና ትርጓሜ
የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ሰባት የመጀመርያዎቹ ቁጥሮች በሕይወታችን ውስጥ ከሰዎች ጋር ስለሚኖረን ግንኙነትና ከእግዚአብሔር ጋር ስለሚኖረን የመጸለይ ሕይወት መሠረታዊ የሆኑ ትምህርቶችን ይሰጡናል። ጌታ ኢየሱስ ትምህርቱን የጀመረው “እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ” በሚል ታላቅ ማስጠንቀቂያ ነው። ይህ ማለት በሰዎች ላይ የምንሰጠው ፍርድና የምንጠቀምበት መስፈርት እኛም በምንመዘንበት ጊዜ ጥቅም ላይ እንደሚውል ማወቅ አለብን። ብዙ ጊዜ በሌላው ሰው ዓይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለማውጣት ስንጣጣር በገዛ ዓይናችን ውስጥ ያለውን ምሶሶ አንመለከትም። ይህ ግብዝነት በሰዎች መካከል ያለውን ሰላም የሚያጠፋና እኛንም ከእግዚአብሔር ጸጋ የሚለይ ነው።
ይህንን በምሳሌ ለመረዳት ያህል፦ አንድ ሰው በልብሱ ላይ ትልቅ ጭቃ ተለክፎ እያለ በሌላው ሰው ልብስ ላይ ያለችን አንዲት ጠብታ አቧራ ሊያጥብ እንደሚሞክር ግለሰብ ነው። መጀመሪያ የገዛ ልባችንን በንስሐና በትሕትና ካላጠብን የሌላውን ሰው ስህተት ለማረም የሞራል ብቃት አይኖረንም። ጌታ የሚፈልገው በሌሎች ላይ ፈራጅ እንድንሆን ሳይሆን በመጀመሪያ ራሳችንን መርምረን እንድንስተካከል ነው። ይሁን እንጂ ቅዱስ የሆነውን ለውሾች እንዳንሰጥና ዕንቁአችንን በዕሪያዎች ፊት እንዳንጥል ማሳሰቡ፣ በምናደርገው ነገር ሁሉ መንፈሳዊ ማስተዋልና ጥንቃቄ ሊኖረን እንደሚገባ ያሳያል። በመቀጠልም ጌታ በጸሎት ሕይወታችን ውስጥ ሊኖረን የሚገባውን ጽናትና እምነት ያስተምረናል። ለምኑ ይሰጣችኋል፣ ፈልጉ ታገኙማላችሁ፣ አንኳኩ ይከፈትላችኋል የሚሉት ቃላት የእግዚአብሔርን ዝግጁነትና የእኛን ጽናት ያሳያሉ። እግዚአብሔር የሚሰጠን አምላክ እንጂ የሚነሳ አምላክ አይደለም። ምድራዊ ወላጆች እንኳን ልጆቻቸው እንጀራ ቢለምኗቸው ድንጋይን እንደማይሰጡአቸው ሁሉ፣ በሰማያት ያለው አባታችን ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን አይሰጣቸውም? ይህ ትምህርት እግዚአብሔር ስለ እኛ የሚያስብና ለልጆቹ መልካሙን ሁሉ የሚመኝ አፍቃሪ አባት መሆኑን ያረጋግጥልናል።
የዚህ ሁሉ ትምህርት ማጠቃለያ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው የሚለው ወርቃማው ሕግ ነው። ይህ ሕግ የሕጉና የነቢያት ሁሉ ፍጻሜ ነው። እኛ ከሰዎች ፍቅርን፣ ክብርንና ምሕረትን የምንፈልግ ከሆነ እኛም እነዚህን ነገሮች ለሌሎች አስቀድመን መስጠት ይኖርብናል። ክርስትና ከራስ ወዳድነት ወጥቶ ለሌላው ማሰብና መኖር ነው። ይህንን መሠረታዊ መመሪያ በሕይወታችን ስንለማመድ የእግዚአብሔር መንግሥት በምድራዊ ኑሮአችን ውስጥ ትገለጣለች።
ተግባራዊ የውይይት ጥያቄዎች
👉”እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ” የሚለው ትእዛዝ ፍጹም የሆነ የፍርድ እቀባ ነው ወይስ ስለ ትክክለኛ ፍርድ?
👉የራስን ምሰሶ ማውጣት ለምን ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል?
👉”ዕንቁአችሁን በእሪያዎች ፊት አትጣሉ” የሚለው ትርጉሙ ምንድን ነው?
👉መለመን፣ መፈለግ እና ማንኳኳት በጸሎት ውስጥ ስላለን ትጋት ምን ያስተምረናል?
👉ምድራዊ አባቶች ለልጆቻቸው መልካም እንደሚሰጡ ሁሉ የሰማዩ አባት ለሚለምኑት ምን ይሰጣል?
👉ወርቃማው ሕግ (7፡12) ለምን የሕግና የነቢያት ሁሉ ፍጻሜ ተባለ?
👉ሌሎችን በምንፈርድበት መስፈርት እኛም እንደምንፈረድ ማወቅ በጠባያችን ላይ ምን ለውጥ ያመጣል?
👉እግዚአብሔር ለልጆቹ “መልካም ነገርን” ብቻ እንደሚሰጥ እንዴት እንረዳለን?
👉በወርቃማው ሕግ እና በሌሎች ሃይማኖቶች አስተምሮ (አታድርጉ በሚለው) መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?
👉ይህ ክፍል ስለ ሰው ግንኙነት እና ስለ እግዚአብሔር ግንኙነት ምን ዓይነት ሚዛን ይሰጠናል?