ኢሳይያስ 50-66

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያኖች በመከራ ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ስለ ዘላለማዊ መንግሥት መማር የሚያስፈልጋቸው ለምን ይመስልሃል? ለ) እግዚአብሔር ስለ መጨረሻው ዘመን ያለውን ዕቅድ የቤተ ክርስቲያንህ አባሎች ምን ያህል ተረድተውታል ብለህ ታስባለህ? ሐ) ስለ መጨረሻው ዘመን በተሻለ ሁኔታ ለማስተማር ምን ማድረግ ትችላለህ?

ክርስቲያኖች አስቸጋሪና አስጨናቂ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በሚገኙበት ጊዜ እግዚአብሔር ስለ መጨረሻው ዘመን ያለውን ዕቅድ መረዳት ይጠቅማቸዋል። የምንወዳቸው በሞት ሲለዩን፥ በስደት ጊዜ ወይም ድርቅና ራብ ሲኖር እግዚአብሔር በመጨረሻው ዘመን ምን ዕቅድ እንዳለው መረዳት አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ አንድ ቀን በጽድቅና በእውነተኛ ፍርድ በእኛ ላይ እንደሚነግሥ ማስታወስ አስፈላጊ ነው። በዚያ ድህነት፥ ሞት፣ ጦርነትና በሽታ አይኖርም። ክፉዎች ሁሉ ይደመሰሳሉ፤ የነገድና የጎሳ ጦርነትም ይቆማል። በመጀመሪያው ሰው በኃጢአት መውደቅ ምክንያት የተደመሰሰው ፍጥረት በአዲስ ሰማይና በአዲስ ምድር ይተካል። ዓይኖቻችንና አስተሳሰባችንን በእነዚህ ነገሮች ላይ ካደረግን፥ አስቸጋሪ በሆኑት በእነዚህ ጊዜያት እንኳ በታላቅ ደስታ ልንኖር እንችላለን። ጳውሎስ እንዳለው፡- «ስለዚህ አንታክትም፥ ነገር ግን የውጪው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል። የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው» (2ኛ ቆሮንቶስ 4፡ 16-18)።

ትንቢተ ኢሳይያስ ስለ መጨረሻው ዘመንና እግዚአብሔር ሊመሠርተው ስላቀደው ዘላለማዊ መንግሥት ብዙ የሚናገረው ነገር አለው። በእዚያ ስለሚኖረው ሰላምና ደስታ የሚናገሩ ብዙ ምሳሌዎችን ይጠቀማል። ከእነዚህ ምሳሌዎች አብዛኛዎቹ በዮሐንስ ራእይ ውስጥ ይገኛሉ። ክርስቲያኖች ስለ መጨረሻዎቹ ዘመናት የሚናገሩትን እነዚህን ምንባቦች በተለያየ መንገድ ቢተረጕሟቸውም እንኳ እግዚአብሔር አንድ ቀን በፍጹም በላይነት እንደሚነግሥና ኃዘንና ጦርነት፥ ኃጢአትም ፍጹም እንደሚደመሰሱ ይስማማሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ኢሳይያስ 50-66 አንብብ። ሀ) ስለ መጨረሻዎቹ ጊዜያት የሚናገሩ ናቸው ብለህ የምታስባቸውን በዚህ ክፍል የሚገኙ የተለያዩ ትንቢቶችን ጥቀስ። ለ) ስለዚያ ዘመን ለእስራኤል ሕዝብ በዚህ ክፍል የተሰጠው ቃል ኪዳን ምንድን ነው? ሐ) ክርስቲያን እንደመሆንህ መጠን በአስቸጋሪና በአስጨናቂ ጊዜ እነዚህ ትንቢቶች መጽናናት የሚሰጡህ እንዴት ነው? መ) «ስለ እግዚአብሔር አገልጋይ» በዚህ ክፍል የተነገሩ ትንቢቶች የትኞቹ ናቸው? 

በዚህኛው የኢሳይያስ መጽሐፍ ክፍል ውስጥ አራት ዋና ዋና ርእሶች ይገኛሉ፡-

1. ይህ ክፍል በዘመኑ መጨረሻ ስለሚሆኑ ነገሮች እግዚአብሔር በሰጣቸው ታላላቅ ተስፋዎች የተሞላ ነው። ስለ እስራኤል ሕዝብ መዳንና ስለ አይሁድ እግዚአብሔርን ማምለክ የተሰጡ ተስፋዎች አሉ፤ ስለ አሕዛብ መዳን የተሰጡ ተስፋዎችም አሉ። ስለ አዲስ ሰማይና ምድር የተሰጡ ተስፋዎች አሉ፤ ክፉዎች እንደሚፈረድባቸው የተነገረ የፍርድ ተስፋም አለ። 

2. የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት፥ በጽድቅ የሚኖረው ሊመጣ ያለው «የእግዚአብሔር አገልጋይ» ስለ ዓለም ኃጢአት ብሉ ማንም ያልተቀበለውን መከራ ይቀበላል (50፡4-9፤ 52፡13-53፡12)።

3. ለተጠሙና ኃጢአታቸው ይቅር እንዲባልላቸውና ከእግዚአብሔር ጋር እውነተኛ ግንኙነት ማድረግ ለሚፈልጉ ሁሉ የተደረገ የደኅንነት ጥሪ እናገኛለን (ኢሳይያስ 55)። 

4. ለእግዚአብሔር የሚቀርብ እውነተኛ አምልኮ ባሕርይና ከእግዚአብሔር እውነተኛ በረከትን የመቀበያ መንገድ (ኢሳይያስ 58)፡- እግዚአብሔርን ማምለክ በቅድሚያ በከንፈሮቻችን በመዘመርና በመጸለይ የምንፈጽመው ተግባር አይደለም፤ ወይም ደግሞ በየዕለተ እሑድ በቤተ ክርስቲያን በመገኘት የምንፈጽመው ሥርዓት አይደለም። ይልቁንም እውነተኛ አምልኮ በእግዚአብሔር ፊት ከሚደረጉ ትክክለኛ ተግባራት የሚፈልቅ ነገር ነው። እውነተኛ አምልኮ ለጎረቤቶቻችን ቅንና አድልዎ የሌለበትን ተግባር ስንፈጽምና በአካባቢያችን ለሚገኙ ድሆች ርኅራኄንና ልግሥናን ስናሳይ ነው። ሌሎችን ለማገልገል ራሳችንን ስንሰጥ እግዚአብሔር ደግሞ በተራው በመንፈሳዊ ብርሃን ይባርከናል፤ ይመራናል፤ የሚያስፈልጉንም ነገሮች ሁሉ ይሰጠናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔርን እያመለክህ የምትኖርባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) ለጎረቤቶችህ ቅን ፍርድን እንዴት እንደምታሳይ የሚያስረዱ መግለጫዎችን ስጥ። ሐ) ባለህበት ኅብረተሰብ ውስጥ የሚገኙትን ድሆች ለመርዳት የጣርህባቸውን መንገዶች ግለጽ። መ) የዚህ ዓይነቱ ሕይወት በረከትን ያመጣልህና ለእግዚአብሔር ያለህን አምልኮ በጥልቀት ያሳደገው እንዴት ነው? ሠ) እግዚአብሔርን በእውነተኛ አምልኮ ታከብረው ዘንድ በዚህ ረገድ መሻሻል የምትችልባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው?

የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔር ከእነርሱ ምን እንደሚፈልግ የቤተ ክርስቲያንህን ሰዎች ለማስተማር በትንቢተ ኢሳይያስ እውነቶች እንዴት ልትጠቀም ትችላለህ? 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ኢሳይያስ 40-49

የትንቢተ ኢሳይያስ ሁለተኛ ግማሽ ክፍል ለብዙ ክርስቲያኖች እጅግ ተወዳጅ ከሆኑት ቅዱሳት መጻሕፍት ክፍል መካከል የሚመደብ ነው። ስለ ፍርድ የሚናገሩት ባለፉት መልእክቶች አብቅተዋል። ኢየሩሳሌምን የሚያጠፋው የባቢሎን ፍርድ በእርግጥ የሚፈጸም መሆኑን ኢሳይያስ አውቋል፤ ስለዚህ ምርኮው እንደተፈጸመ አድርጎ በመቍጠር ይጽፋል። ራሳቸው በምርኮ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በሚያጽናና መንገድ ይጽፋል።

ኢሳይያስ ሕዝቡን በሦስት መንገዶች ለማበረታታት ይፈልጋል፡-

በመጀመሪያ፥ የእግዚአብሔርን ታላቅነትና እግዚአብሔር በአሕዛብ በምድር ነገሥታት፥ በአሕዛብ አማልክትና በሕዝቦቹ ሕይወት ውስጥ በሚፈጸሙ ድርጊቶች ሁሉ ላይ ያለውን ሉዓላዊ ሥልጣን ያለማቋረጥ በማመልከት ያበረታታቸዋል።

ሁለተኛ፡ ኢሳይያስ በምርኮ አገር ያሉ አይሁድ ወደገዛ ምድራቸው እንደሚመለሱ በማመልከት ያበረታታቸዋል። እግዚአብሔር ያኔም ቢሆን ለይሁዳ ሕዝብ ዓላማ ነበረው፤ ስለዚህ የአይሁድ ሕዝብ በሙሉ እንዲጠፉ አይፈቅድም። ሁልጊዜ ለእግዚአብሔር ታማኝ የሆኑ ቅሬታዎች ይኖራሉ። እግዚአብሔርም ከእነዚህ ቅሬታዎች ጋር ይሠራል፤ ይጠብቃቸዋል፤ እንዲሁም ወደ ምድራቸው ይመራቸዋል።

ሦስተኛ፥ ሊመጣ ወዳለው «የእግዚአብሔር አገልጋይ» በማመልከት ያበረታታቸዋል። በዚህ የትንቢተ ኢሳይያስ የመጨረሻ ክፍል ሊመጣ ወዳለው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያመለክቱ በርካታ ትንቢቶች ይገኛሉ። የእግዚአብሔር ሌላዋ አገልጋይ ከሆነችው ከእስራኤል በተቃራኒ፥ ይህ እውነተኛ አገልጋይ በእግዚአብሔር መንፈስ ኃይል ይመጣል፤ ጽድቅን ያደርጋል፤ ሕዝቡን ነፃ ያወጣል ስለ ኃጢአታቸውም ይሞታል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህ ከላይ የተመለከትናቸው ሦስት እውነቶች በዚህ ዘመን ላለን ክርስቲያኖች ማበረታቻ የሚሆኑት እንዴት ነው? ለ) ከእነዚህ ሦስት ርእሶች፥ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች ለማበረታታት መልእክት ልታቀርብ የምትችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር። 

የውይይት ጥያቄ፥ ኢሳይያስ 40-49 አንብብ። ሀ) በእነዚህ ቍጥሮች ውስጥ የእግዚአብሔር ታላቅነት የታየባቸውን የተለያዩ መንገዶች ዘርዝር። ለ) በእነዚህ ቍጥሮች ውስጥ እግዚአብሔር በምርኮ ላይ ላሉት ሕዝቡ የሰጣቸውን የተለያዩ የማበረታቻ ተስፋዎች ዘርዝር። ሐ) በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ስለሚመጣው «የእግዚአብሔር አገልጋይ» የተጠቀሱትን የተለያዩ እውነቶች ዘርዝር።

በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ያለማቋረጥ የምናያቸው ሁለት ዐበይት አሳቦች አሉ። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔርን ለማወቅ በሚመለከት ዋና አሳብ እናገኛለን። ዳንኤል 11፡32 እንዲህ ይላል፡- «…ነገር ግን አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ ይበረታሉ፥ ያደርጋሉም» (ሐሰተኛ ክርስቶስን ይቃወማሉ)። እኛ ክርስቲያኖች በታላቅ መከራና ችግር በተሞላችው በዚህች ዓለም ውስጥ በሙሉ ልብነትና በደስታ ልንመላለስ የምንችለው እግዚአብሔር ማን እንደሆነ፥ ምን እንደሚመስል፥ ምን እንደሚፈልግና የሰጠን ቃል ኪዳን ምን እንደሆነ በምናውቅበት ጊዜ ነው። ችግሩ ግን እግዚአብሔር ማን እንደሆነ፥ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነና ምን ያህል እንደሚወደን ግልጽ የሆነ መረዳት ያላቸው ጥቂት ክርስቲያኖች ብቻ መሆናቸው ነው። እነዚህ እውነቶች ይበልጥ ግልጽ በሆኑልን ቍጥር፥ የምንቀበለው መጽናናትና መበረታታትም እየጨመረ ይሄዳል። ኢሳይያስ በምርኮ የነበሩት እስራኤላውያን ዓይኖቻቸውን ወደ እግዚአብሔር እንዲመልሱ ያበረታታቸዋል። እግዚአብሔር በፍጥረታት፥ በአሕዛብ፥ በነገሥታት፥ በአሕዛብ የውሸት አማልክት ላይ እንኳ ታላቅ እንደሆነ ይነግራቸዋል። እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለውን ፍቅርና የወደፊት ዓላማ ይነግራቸዋል። ተስፋ በምንቈርጥበት በማንኛውም ጊዜ ወደ ትንቢተ ኢሳይያስ ሁለተኛ ክፍል ብንመለስና ትኩረታችንን በእግዚአብሔር ላይ ብናደርግ እንጽናናለን፤ ብርታትንም እናገኛለን።

ሁለተኛው ዋና አሳብ፥ «የእግዚአብሔር አገልጋይ» የሚለው ነው። በክፍሉ የተጠቀሱ ሁለት የተለያዩ አገልጋዮች አሉ፡-

1. የእግዚአብሔር አገልጋይ የሆነው የእስራኤል ሕዝብ (ኢሳይያስ 41:8-10)፡- የእግዚአብሔር አገልጋይ የሆነችው እስራኤል ብዙ ጊዜ ብትወድቅም፥ እግዚአብሔር ግን አልተዋትም። ይልቁንም እግዚአብሔር በምድር ላይ ከሚገኙ አሕዛብ ሁሉ መርጦ እስራኤልን ጠራት፤ ከእርሷ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ ምንጊዜም እንደማይተዋት ተስፋ ሰጣት። እግዚአብሔር እስራኤልን ይጠብቃታል፤ ይመራታል፤ የሚያስፈልጋትን ሁሉ ያደርግላታል። ወደ ቀድሞ ክብሯም ይመልሳታል። ቂሮስ የተባለ ሌላ አገልጋዩን በማስነሣት፥ ሕዝቡን ወደ ነፃነቱ ይመራዋል። እንደ ቤልና ኔቦ ያሉትን የባቢሎናውያን አማልክትና ባቢሎናውያንን ይደመስሳል። 

2. የእግዚአብሔር አገልጋይ የተባለው ሊመጣ ያለው የእስራኤል መሪ፡- ይህ አሳብ በቀሪው ኢሳይያስ ክፍል ውስጥ በሙሉ በመቀጠል የሚገኝ ነው (ኢሳይያስ 42፡1-7፤ 49፡1-7፤ 50፡4-9፤ 52፡13-53፡12)። ይህ እንደ ልቡ የሆነው የእግዚአብሔር አገልጋይ በመንፈስ ቅዱስ የሚሞላና በጽድቅ የሚነግሥ ነው። የዕውሮችን ዓይን በማብራትና ምርኮኞችን ነፃ በማውጣት፥ ለአሕዛብ ብርሃን ይሆናል። ከእግዚአብሔር የተማረና ሌሎችንም የሚያስተምር ይሆናል። በዚህም ዓይነት ለደከሙት ብርታትን ይሰጣቸዋል። ቤሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች ያሳድዱታል ይገድሉታልም። በዚህ መልኩ ደግሞ ለብዙዎች ደኅንነትን ያመጣል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ለእግዚአብሔር እንደ ልቡ ስልሆነው አገልጋይ የተነገሩትን እነዚህን እውነቶች ኢየሱስ ክርስቶስ የሚፈጽመው እንዴት ነው? ) እኛስ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር እንደ ልቡ አገልጋይ እንደሆነው እንዴት እንሆናለን? ሐ) እኛም የእግዚአብሔር አገልጋዮች መሆን አለብን (2ኛ ጢሞቴዎስ 2፡24 ተመልከት)። ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ይህ የዕለት እርምጃችንን የሚለውጠው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ኢሳይያስ 24-39

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚቀርቡ ስብከቶችና ትምህርቶች ውስጥ የሚተላለፉ መልእክቶችን ውጤታማ ከሚያደርጓቸው ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ መልእክቶቹ የጠፉትን የማዳንና ክርስቲያኖችን የማስተማር ሚዛናዊነታቸው የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ ነው። ስብከቶቻችን በሚያበረታታና ተስፋ በሚሞላ፥ እንዲሁም ስለ ፍርድ በሚናገር መልእክት መካከል ሚዛናዊ መሆን አለባቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16ን በቃልህ አጥና። ሀ) የእግዚአብሔር ቃል ለምን እንደሚጠቅም ዘርዝር። ለ) ለክርስቲያን የእግዚአብሔር ቃል የመጨረሻ ውጤት ምንድን ነው? ሐ) ባለፉት ሦስት ወራት በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የተሰበኩ ስብከቶችን ወይም አንተ ራስህ ባለፈው አንድ ዓመት የሰበከውን ስብከት አስታውስ። የእግዚአብሔር ቃል የሚጠቀምባቸውን የተለያዩ የሕይወት ክፍሎች (አቅጣጫዎች) በመጠቀም፥ የትኛው መልእክት ለየትኛው ዓይነት ጥቅም እንደታለመ ግለጽ። (ለምሳሌ፡- የደኅንነት መልእክትና ትምህርት)። መ) ብዙ ጊዜ ባለመሰበኩ ምክንያት ትምህርቱን ሚዛናዊ ያላደረገው የትኛው ዓይነት መልእክት ነው? ሠ) የሚሰጠው ትምህርት የበለጠ ሚዛናዊ ይሆን ዘንድ አንተ ወይም ቤተ ክርስቲያንህ ማቅረብ የሚገባችሁ አንዳንድ ርእሰ-ጉዳዮችን ጥቀስ።

ኢሳይያስ፥ እንደ ብዙዎቹ ነቢያት መልእክቱን ሚዛናዊ አደረገው። ነቢዩ አንዳንድ ጊዜ ሕዝቡን ለክፉና ኃጢአተኛ ለሆነው ሕይወታቸው በብርቱ ሲገሥጻቸው፥ በሌላ ጊዜ ደግሞ የሚያጽናናና የሚያበረታታ መልእክት ይነግራቸው ነበር። አንዳንድ ጊዜ ነቢያት በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ በቅርቡ ስለሚፈጸም ፍርድ ያመለክቱ ነበር። በሌላ ጊዜ ደግሞ ነቢያት በዓለም ላይ የሚገኝ ክፋት ሁሉ ስለሚደመሰስበትና እግዚአብሔር ስለሚነግሥበት የመጨረሻ ዘመን ይናገሩ ነበር። የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰብኩና የሚያስተምሩ ሰዎች በብሉይ ኪዳን የነበሩትን ነቢያት ምሳሌነትን ለመከተል በጣም ጠንቃቃዎች መሆን አለባቸው። ስለ መንፈሳዊ ስንፍናውና ስለ ቅድስና ጕድለት የእግዚአብሔርን ሕዝብ መገሠጽ የሚያስፈልግበት ጊዜ አለ። እንዲሁም ሕዝቡ እግዚአብሔርን በመከተሉ ሊመሰገንና ከዚያ በላቀ ሁኔታ ከእግዚአብሔር ጋር በቅርብ ተሳስሮ እንዲራመድ ሊበረታታ የሚገባውም ጊዜ መኖር አለበት።

ኢሳይያስ ከምዕራፍ 24 እስከ 39 ባለው የመጽሐፉ ክፍል የፍርድና የማጽናኛ ወይም የማበረታቻ መልእክቱን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ አቅርቦታል።

የውይይት ጥያቄ፥ ኢሳይያስ 24-39 አንብብ። ሀ) በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የፍርድ መልእክቶችን ዘርዝር። ፍርዶቹ ምንድን ናቸው? ለ) በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገኙትን የተለያዩ የማበረታቻ መልእክቶች ዘርዝር። የተሰጡት የተስፋ ቃሎች ምንድን ናቸው? ሐ) ከኢሳይያስ 36-39 የተገለጹ ታሪካዊ ድርጊቶች ምንድን ናቸው? እነዚህ ምዕራፎች በኢሳይያስ ትንቢት ላይ ተጨማሪ ነገሮችን የሚያክሉት እንዴት ነው?

የትንቢተ ኢሳይያስ አራተኛው ዐቢይ ክፍል ከምዕራፍ 24-35 ነው። እነዚህ ምዕራፎች እጅግ የተለያዩ መልእክቶችንና የወደፊቱን ሁኔታ የሚያመለክቱ ትንበያዎችን ይዘዋል። 

1. ኢሳይያስ 24፥ እግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥቱን ከመጀመሩ በፊት፥ በምድር ላይ ያለው ዘመን ስለሚያከትምበትና በሩቅ ስላለ የፍርድ ጊዜ የሚናገር መልእክት ነው። እግዚአብሔርን በመቃወም የሚቆሙ ሁሉ፥ ማለት መንግሥታት፥ ነገሥታት፥ አጋንንትም ሳይቀሩ (በከፍታ ያሉ ኃይላት ኢሳይያስ 24፡21) እንደሚደመሰሱ ይናገራል።

የውይይት ጥያቄ፡ ክፉ የሆኑ ሁሉ እንደሚደመሰሱ የተሰጠው ማረጋገጫ፥ ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕይወት ይኖሩ ዘንድ ማበረታቻ የሚሆነው እንዴት ነው?

2. ኢሳይያስ 25-27 የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚያጽናኑ መልእክቶች ናቸው። እግዚአብሔር የማጽናናት አምላክ ነው፤ ለድሆች መሸሸጊያ የሚሆን ታማኝም ነው። በችግር ጊዜ እግዚአብሔር ሕዝቡን ይረዳል። በችግርና በጥፋት ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ ሰላም የማግኘት ምሥጢሩ አእምሮአችንን በእግዚአብሔር ላይ ማድረግ ነው። እርሱ ውስጣዊ ሰላምና ዋስትናን ይሰጠናል (ኢሳይያስ 26፡3-4 ተመልከት)። አንድ ቀን ሞት ይደመሰሳል። የክፋት መጋረጃ ከምድር ላይ ይወገዳል።

3. ኢሳይያስ 28-31 የፍርድንና የተስፋን መልእክቶች አዋሕዶ ያቀርባል። ሦስት ዐበይት ፍርዶች ታውጀዋል፤ በመጀመሪያ፥ በኤፍሬም ላይ የተደነገገ ፍርድን እናያለን። ኤፍሬም የእስራኤል ሰሜናዊው መንግሥት ሌላ ስም ነው። (ኢሳይያስ 28) ኢሳይያስ እስራኤል ፈጥና እንደምትጠፋ ተነበየ። ኢሳይያስ ሕዝቡን ወደ ክፋት በመሩት በእስራኤል መሪዎች ላይ እንዴት ትኩረት እንዳደረገ አስተውል። ካህናትንና ነቢያትን ስለ ስካር ያወግዛል፤ ነገር ግን የጽዮን የመሠረት ድንጋይ ወደሆነውና ሊመጣ ወዳለው መሢሕ ዳግም ያመለከታል። ሁለተኛ፥ በዳዊት ከተማ ላይ ፍርድ ይመጣል። የዳዊት ከተማ የደቡቡ መንግሥት ዋና ከተማ የሆነችው የኢየሩሳሌም ሌላ ስም ነው (ኢሳይያስ 29-30)። ኢየሩሳሌም ትዋረዳለች እንጂ አትጠፋም፤ ዳሩ ግን ኢየሩሳሌም ልትጠፋ በተቃረበችበት ጊዜ ጠላቶችዋ ይደመሰሳሉ። ይህ የሚያመለክተው የአሦርን ጦር መደምሰስ እንደሆነ አያጠራጥርም (ኢሳይያስ 37)። ኢየሩሳሌም ፍርድ ልትቀበል የነበረችበት ምክንያት ሕዝቡ በከንፈራቸው እግዚአብሔርን እናከብራለን ቢሉ እንኳ እግዚአብሔርን የሚያመልኩት በባዶ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ብቻ ስለነበር ነው። እግዚአብሔርን ከልባቸው አያመልኩትም ነበር። የእግዚአብሔር ሕዝቦች እግዚአብሔርን በእውነት የሚያመልኩበት ጊዜ ግን ይመጣል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬም እኛ እግዚአብሔርን ከልባችን ሳይሆን በከንፈራችን ብቻ ማምለክ ቀላል የሚሆንልን እንዴት ነው? ምሳሌዎችን ጥቀስ። ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪ እንደ መሆንህ መጠን ሕዝቡ በከንፈሩ ብቻ ሳይሆን በልቡም ጭምር እግዚአብሔርን እንዲያመልክ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ሦስተኛ፥ ከጠላቶቻቸው ከአሦራውያን ያድኗቸው ዘንድ በእግዚአብሔር ላይ ከመታመን ይልቅ፥ በግብፅ ላይ በሚታመኑ ሰዎች ላይ ፍርድ ይመጣባቸዋል። አይሁድ የአሦር ጦር ኢየሩሳሌምን ለመውጋት በመጣ ጊዜ በጦርነቱ ይረዳቸው ዘንድ እጅግ ታላቅ ጦርና በርካታ ፈረሶች ያሉትን የግብፅን መንግሥት ለመጠየቅ በጣም ተፈትነው ነበር። እግዚአብሔር ግን ይህንን እንዳያደርጉ በኦሪት ዘዳግም አስጠንቅቆአቸው ነበር። ይልቁንም ነፃ እንዲያወጣቸው በእግዚአብሔር ላይ መታመን ነበረባቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬም እኛ በእግዚአብሔር ላይ ከመታመን ይልቅ በሌሎች ሰዎች፥ በመንግሥታት ወይም በውጭ ዜጎች እንዴት ልንታመን እንችላለን? ለ) ይህስ በእግዚአብሔር ላይ ስላለን እምነት ምን ይናገራል?

4. የሚመጣው የጽድቅ ንጉሥ (ኢሳይያስ 32)፡- የዓለም ተስፋ ሰብአዊ መንግሥት ወይም ሰብአዊ ንጉሥ አይደለም። እነዚህ ልክ እንደ እኛ ኃጢአተኞችና ደካሞች ስለሆኑ ሁልጊዜ ተስፋ ያስቈርጡናል። ከዚህ ይልቅ ተስፋችን ሊመጣ ባለው የጽድቅ ንጉሥ-በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ መሆን አለበት። በእርሱ የጽድቅ ዘመነ መንግሥት እውነተኛ ሰላም ይኖራል። 

5. ፍርድና በረከት (ኢሳይያስ 33-35)፡- ቀሪው የዚህ ክፍል ምንባብ ሊመጣ ያለውን ፍርድ፥ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ከተዘጋጁ የወደፊት አስደሳች የተስፋ ቃሉች ጋር አጣምረው የያዙትን ትንቢቶች ያካትታል። ፍርዱ በፍጥነት እንደሚሆን ይናገራል። ይህ የሚያመለክተው የአሦርንና የባቢሎንን ምርኮ ነው፤ ነገር ግን ነፃ የወጡት ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር በሰላምና በደኅንነት የሚኖሩበትንና ክፋት የሚደመሰስበትን የመጨረሻውን ጊዜ ደግሞ ያመለክታል።

የትንቢተ ኢሳያይስ የመጀመሪያ ዐቢይ ክፍል የሆነው ከምዕራፍ 1-39 ያለው አሳብ የሚጠቃለለው ታሪካዊ በሆነ አቀራረብ ነው። በዚህ ታሪክ ውስጥ ሁለት ዐበይት ታሪካዊ ድርጊቶች ይገኛሉ። በመጀመሪያ፥ አሦር ኢየሩሳለምን የወጋችበት ታሪካዊ ድርጊት አለ። ይህ ለሕዝቡ ሁሉ የኢሳይያስን መልእክት ትክክለኛነትና እውነተኛነት የሚያመለክት ስለሆነ በጣም ጠቃሚ ነበር። ኢሳይያስ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ላይ እንደሚፈርድና ዳሩ ግን ጨርሰው እንደማይጠፉ ተናገረ። አሦራውያን ይሁዳን ሊወጉ በወጡ ጊዜ ከኢየሩሳሌም በስተቀር ሁሉም ከተሞች ፈራረሱ። በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ሰዎች ወደ አሦር ተጓዙ። እግዚአብሔር ግን ከተማይቱ እንደማትወድቅ የገባውን ቃል አከበረ። ያለምንም የውጭ ጦር እርዳታ ጌታ ራሱ የአሦራውያንን ጦር ደመሰሰ። እርሱ ጠባቂያቸው እንደሆነና በእርሱ ብቻ ሊደገፉ እንደሚገባ እግዚአብሔር ለሕዝቡ አረጋገጠ።

ሁለተኛው ታሪካዊ ክሥተት የሕዝቅያስ ሕመም ሲሆን፥ እርሱም ከትንቢተ ኢሳይያስ ሁለተኛ ግማሽ ክፍል ጋር ያስተዋውቀናል። ሊመጣ ያለው የባቢሎን ምርኮ እርግጠኛ ነገር መሆኑን ያሳየናል። ሕዝቅያስ በታመመ ጊዜ እራስ ወዳድነቱ ዕድሜ እንዲጨመርለት እንዲጸልይ አደረገው። ሕዝቅያስ እስከዚህ ዘመኑ ድረስ እግዚአብሔርን የሚፈራ የመልካም ንጉሥ ሕይወት ምሳሌነት የሞላበት ኑሮ ስለኖረ በዚህ ሕመሙ ወቅት ቢሞት ይሻል ነበር። በስተ እርጅናው የታየው ራስ ወዳድነት ግን የሞኝነት ተግባር እንዲፈጽም አድርጎት ራሱንና ሕዝቡን አዋረደ።

የነበረውን ሀብት በሙሉ ለባቢሎናውያን በማሳየት፥ በሕዝቡ ላይ የወደፊት ጥፋት ጋበዘ። ያደረገው ነገር ቢኖር ስለ ራሱ በስስታምነት ማሰብ፥ እንደማይሞትና በዘመኑ ክፉ እንደማይመጣ በመመኘት መጽናናት ብቻ ነበር። አብዛኛውን የሕይወት ዘመናችንን እግዚአብሔርን ከተከተልን በኋላ እግዚአብሔርን፥ ራሳችንና ሕዝባችንን የማያስከብር ጥበብ የጐደለው ተግባር መፈጸም እጅግ ቀላል ነው።

ክፉው ንጉሥ ምናሴ የተወለደውም በዚህ ጊዜ ነበር። ከይሁዳ ነገሥታት ሁሉ የከፋ ሰው ነበር። ሕዝቅያስ በዚያን ጊዜ ሞቶ ቢሆን ኖሮ ይሁዳ ከዚህ ሁሉ ጥፋት ለማምለጥ በቻለች ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር በታማኝነት ሲጓዙ ቆይተው ድንገት የወደቁና እግዚአብሔርን ቤተሰባቸውንና የእግዚአብሔርን ሕዝብ ያሳደቡትን ሰዎች እንዴት አይተሃቸዋል? ለ) ይህ ነገር ለእኛ ማስጠንቀቂያ ሊሆን የሚገባው እንዴት ነው? 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ኢሳይያስ 12-23

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች ሌላ መንግሥት የተነሣባቸው በሚመስላቸው ጊዜ ወይም ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ጦርነት በሚካሄድበት ወቅት ተስፋ የሚቆርጡት ለምንድን ነው? ለ) ክርስቲያን እንዲህ ባሉ ወቅቶች ከተስፋ መቁረጥ ነፃ ይሆንና ይበረታታ ዘንድ ስለ እግዚአብሔር ማስታወስ ያለበት እውነቶች ምን ይመስሉሃል?

ክርስቲያኖች እንደመሆናችን፥ ብዙ የተዛቡ ፍርዶችን በምድር ላይ ደጋግመን በምንመለከትበት ወቅት እነዚህን ሁኔታዎች ሁሉ በእርግጥ እግዚአብሔር እየተቈጣጠረ ነውን? በማለት እንጠይቃለን። ምንም የማያውቁ ሰላማዊ ሕዝቦች ከጦር መኮንኖች ይልቅ የሚሠቃዩባቸው ጦርነቶች አሉ። እነዚህ ጦርነቶች ትክክለኞችና ፍትሐዊ አይደሉም። በአንድ ሕዝብ ላይ የሚደርሱና ሌላውን ሕዝብ የማይነኩ የሚመስሉ ድርቅና ራብ ወይም ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች በምድር ላይ ይታያሉ። የበለጠ ክፉና ኃጢአተኞች የሆኑ ሕዝቦች ከፍርድ እያመለጡ፥ በሌሎች ሕዝቦች ላይ ግን እጅግ ብዙ ችግር የሚደርስ በሚመስልበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር በምድር ላይ የሚፈጸሙ ድርጊቶችን በእርግጥ እየተቈጣጠረ ይሆንን!? በማለት በትዝብት ሳንጠይቅ አንቀርም።

የእስራኤል ሕዝብም በተመሳሳይ ሁኔታ አጠያያቂ እንደሆነባቸው ጥርጥር የለውም። የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ ነበሩ። እግዚአብሔር በዓለም ላይ ካለ ከማንኛውም ሕዝብ ይልቅ ታላቅ እንደሆነ ያውቃሉ። ይሁን እንጂ እስራኤል ያለማቋረጥ በሌሎች ሕዝቦች ጥቃት እየደረሰባት ትሸነፍ ነበር። ይህ የሆነው እግዚአብሔር ደካማና ሌሎችን ሕዝቦች ለመቈጣጠር የማይችል ስለሆነ ነውን? እግዚአብሔር ከአሕዛብ አማልክት ይልቅ ደካማ ነውን? እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ እንደሚፈርድ ተናግሯል። ይሁዳ ግን በሥነ- ምግባር ረገድ ከሌሎች አሕዛብ እጅግ የተሻለች ነበረች። እግዚአብሔር ታዲያ በይሁዳ ላይ የሚፈርደውና በሌሎች ሕዝቦች ላይ የማይፈርደው ለምንድን ነው? ኢሳይያስ እነዚህን ትንቢቶች በሚናገርበት ጊዜ በእርሱና እግዚአብሔርን በሚፈሩ ሌሎች አይሁድ አእምሮ ውስጥ እነዚህና ሌሎች ጥያቄዎች ተፈጥረው እንደነበር ጥርጥር የለውም።

እግዚአብሔር ጥያቄዎቻቸውን በጸጋ ተቀብሉ አስተናገደ። እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል የተፈጸሙትን ድርጊቶች እየተቈጣጠረ መሆኑን በኢሳይያስ በኩል ለአይሁድ አሳየ። አሕዛብንም በአይሁድ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሳይሆን፥ በራሱ ጊዜ በኃጢአታቸውና በክፋታቸው ይፈርድባቸዋል።

እግዚአብሔር በግለሰቦች ላይ በሕይወት አኗኗራቸው መሠረት እንደሚፈርድባቸው ብቻ ሳይሆን፥ መንግሥታትም በአጠቃላይ ቅን ፍርድን በማጕደልና የተለዩ ዜጎችን በመንከባከብ ስለፈጸሙት ድርጊት እንደሚፈርድ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። በተለይ የሚፈርድባቸው የራሱ ሕዝብ በሆኑት በአይሁድ ላይ በፈጸሙት ድርጊት ምክንያት ነው። አንዳንድ ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነትና ለሕዝባቸው የሚሆነውን የሥነ-ምግባር መሠረት የተዉ አገሮችን ካሉበት ሥልጣን ፈጥኖ ያወርዳቸዋል። በሌላ ጊዜ ይህ ፍርድ በመቶ የሚቈጠሩ ዓመታትን ሊወስድና በክርስቲያኖች የሕይወት ዘመን የማይታይ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በመጨረሻው ዘመን እግዚአብሔር በግለሰቦች ላይ ብቻ ሳይሆን፥ በመንግሥታትም ላይ እንደሚፈርድ እርግጠኞች ነን (ለምሳሌ ኢዩኤል 3)።

የውይይት ጥያቄ፥ መንግሥታትና መሪዎች ራሳቸውን እንዴት እንደሚመሩ፥ ሕግጋታቸው ምን ያህል ትክክለኞች እንደሆኑና ከመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ-ምግባር መመሪያዎች ጋር እንዴት እንደሚስማሙና በእግዚአብሔር ፊት መልስ እንደሚሰጡ ማወቃቸው ለምን ይጠቅማል?

ዛሬ የምናጠናው በይበልጥ እግዚአብሔር በሕዝቦች ላይ እንደሚፈርድ የሚያሳየውን የትንቢተ ኢሳይያስን ክፍል ነው። እነዚህ ሕዝቦች በኢሳይያስ ዘመን ገናና የነበሩ ናቸው። ስለ እግዚአብሔር የተነገሩት እነዚህ ትንቢቶች ስለተፈጸሙ፥ ዛሬ ከእነዚህ ሕዝቦች አብዛኛዎቹ ሙሉ በሙሉ ጠፍተዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ኢሳይያስ 13-23 አንብብ። በእነዚህ ምዕራፎች የተጠቀሱትን ልዩ ልዩ መንግሥታትና እግዚአብሔር የወሰናቸውን ፍርዶች ዘርዝር።

1. በባቢሎን ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 13-14፡1-23)

የመጀመሪያው ትንቢት የተነገረበት ሕዝብ የባቢሎን ሕዝብ ነው። ይህ ትንቢት በተነገረበት ወቅት ዓለምን ይገዛ የነበረው ታላቁ የአሦር የንጉሠ ነገሥት ግዛት ውስጥ ከነበሩት ዋና ዋና ከተሞች አንድዋ ባቢሎን ነበረች፤ ስለዚህ በአንድ በኩል፥ በባቢሎን ላይ የተነገረው ትንቢት በአሦር መንግሥት ላይ የተነገረ ነበር። ትኩረቱ በባቢሎን ላይ ስለሆነ ከዚህም የላቀ ትርጕም አለው። በኢሳይያስ ዘመን የነበረው ዓለምን የሚገዛ ዋና መንግሥት አሦር ሆኖ ሳለ ትንቢቱ በባቢሎን ላይ መነገሩ የሚያስደንቅ ነው። እግዚአብሔር ግን ከ150 ዓመታት በኋላ የይሁዳን ሕዝብ በምርኮ የሚያግዘው የባቢሎን መንግሥት እንደሆነ ያውቅ ነበር። ባቢሎን ርእሰ ከተማ ከመሆኗ በፊት እንኳ እግዚአብሔር ስለ ጥፋቷ ተናግሮ ነበር፡፡ ባቢሎንን የሚደመስሰው የሜዶን መንግሥት እንደሆነም አስቀድሞ ተናገረ።

ኢሳይያስ 14፡12-15 በምሁራን መካከል ከፍተኛ ውዝግብን ያስነሣ ክፍል ነው። ይህ ክፍል ማንን ነው የሚያመለክተው? የባቢሎንን ንጉሥ ብቻ ነው ወይስ ሰይጣንንም ጭምር?

ይህ ክፍል በመጀመሪያ የተጻፈው በሕዝብ ዘንድ እንደ አምላክ ይታይ ስለነበረው ስለ ባቢሎን ንጉሥ ሳይሆን አይቀርም። ይሁን እንጂ ይህ ክፍል በብዙ መንገድ ሰብአዊ ንጉሥን ብቻ የሚያመለክት አይመስልም። ስለ አንድ ልዩ ሕያው ፍጡር የሚያመለክት ይመስላል። በዘመናት ሁሉ የኖሩ ክርስቲያኖች ይህ ክፍል የሚናገረው ስለ ሰይጣን ውድቀት ነው ብለው የሚያምኑት በዚህ ምክንያት ነው። ሰይጣን «የአጥቢያ ኮከብ» ወይም «ሉሲፈር» ተብሎአል። ይህ ክፍል ስለ ሰይጣን የሚናገር ከሆነ፥ ሰይጣንን ለውድቀት የዳረገው ትዕቢት እንደነበረ መመልከት እንችላለን። ሰይጣን እንደ እግዚአብሔር ለመሆንና በነገሮች ሁሉ ላይ ለመግዛት ፈለገ፤ ስለዚህ ከሰማይ ተጣለ። በራእይ 13፡4 እና 17፡3 ይህ ክፍል በተምሳሌታዊነቱ በዘመናት መጨረሻ በሰይጣን ቍጥጥር ሥር ስለሚሠራው ክፉ መሪ ስለ አውሬው የተጠቀሰ ይመስላል።

የውይይት ጥያቄ፥ እነዚህ ጥቅሶች ትዕቢት በእግዚአብሔር አመለካከት ምን ያህል የከፋ ኃጢአት መሆኑን እንዴት ያሳያሉ?

ስለ ባቢሎን የተነገሩት እነዚህ ትንቢቶች ያለአንዳች ስሕተት እንዴት እንደተፈጸሙ ስናይ እንደነቃለን። ትንቢቱ እንዳመለከተው፥ ዛሬ ባቢሎን የሚባል ከተማ የለም፤ በረግረግ መካከል ያለ ፍርስራሽ ነው። እግዚአብሔር እስከወሰነ ትዕቢተኞች የሆኑ መንግሥታትንና መሪዎችን ለማዋረድ የሚያግደው ምንም ነገር የለም። 

2. በአሦር ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 14፡24-27)።

አሦር የመጀመሪያዋ የዓለም ታላቅ መንግሥት እንደነበረችና የሰሜኑን የእስራኤል መንግሥት የደመሰሰች መሆንዋን ታስታውሳለህ። እንዲሁም በኢሳይያስ ዘመን ከፍተኛ የዓለም መንግሥት በመሆን በይሁዳ ሕዝብ ላይ ታላቅ ጥፋትና መከራ አምጥታለች።

ይህ ትንቢት በተነገረ ጊዜ ታላቅ መንግሥት የነበረች ብትሆንም፥ በ150 ዓመታት ውስጥ እንደምትወድቅ እግዚአብሔር ያውቅ ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር የአሦርን መንግሥት መውደቅ ለማመልከት በትንቢተ ኢሳይያስ ውስጥ ልዩ ትኩረት አልሰጠውም። 

3. በፍልስጥኤም ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 14፡28-32)፡፡

ከይሁዳ መንግሥት የረጅም ጊዜ ጠላቶች አንዱ የፍልስጥኤም መንግሥት ነበር። ፍልስጥኤም በአይሁድ የተያዘችው በዳዊት ዘመነ መንግሥት ነበር። ሆኖም ዕድል ባገኘች ቍጥር፥ ፍልስጥኤም በአይሁድ ላይ በማመፅ፥ ይሁዳን ለማጥቃት ከይሁዳ ጠላቶች ጋር ብዙ ጊዜ ትተባበር ነበር። በዚህ ስፍራ እግዚአብሔር ፍልስጥኤም በአሦር ስለ መወረርዋና ስለመደምሰሷ ተነበየ። 

4. በሞዓብ ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 15-16)፡፡ 

ከጥንት የአይሁድ ጠላቶች አንድዋ ሞዓብ ነበረች። ከዳዊት ዘመን በኋላ በነበረው አብዛኛው ታሪኳ ሞዓብ በእስራኤል ወይም በይሁዳ ቍጥጥር ሥር ነበረች። አጋጣሚ ጊዜ ባገኘበት ጊዜ ሁሉ ግን ታምፅ ነበር። የይሁዳ ጠላቶች ኢየሩሳሌምን ለማጥቃት በተነሡበት ጊዜ ሁሉ ሞዓብ ትተባበር ነበርና እግዚአብሔር ሽንፈቷንና ጥፋቷን አስቀድሞ ተናገረ። ይህ ትንቢት ሞዓብ በባቢሎን መወጋቷንና መሸነፉን የሚያመለክት ቢሆንም እንኳ ዋናው አሳብ ግን በአሦር መንግሥት ስለሚደርስባት ጥፋት የተነገረ ሳይሆን አይቀርም። 

5. በደማስቆ ወይም በሶርያ ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 17)፡፡

ደማስቆ የአራም ወይም የሶርያ መንግሥት ዋና ከተማ እንደሆነች ታስታውሳለህ። ኢሳይያስ በኖረበት ዘመን፥ በተለይ ደግሞ በአካዝ ዘመነ መንግሥት የሶርያ መንግሥት ከእስራኤል ጋር በመተባበር ይሁዳን ለማጥቃት ውጊያ አካሂዶ ነበር። የሶርያ ሕዝብ የአይሁድ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላት ነበሩ (ለምሳሌ፡- 1ኛ ነገሥት 20)። እግዚአብሔር ሶርያ በተለይም ደግሞ ዋና ከተማዋ ደማስቆ በቅርቡ እንደምትደመሰስ ተናግሮ ነበር። ይህም በ732 ዓ.ዓ. አሦራውያን ከተማዋን ባጠፉትና ብዙ ሕዝብ ማርከው በወሰዱበት ወቅት ተፈጸመ። በዚህ ጊዜ የእስራኤል ሕዝብ ከሶርያ ጋር ተባብረው ነበር። ስለዚህ በዚህ ክፍል በተነገረው ትንቢት ውስጥ የሰሜኑ መንግሥት ተጨምሮ ነበርና እግዚአብሔር እስራኤልም ትደመሰሳለች በማለት ተናገረ። 

6. በኩሽ ወይም በኢትዮጵያ ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 18)፡፡

በጥንት ዘመን ኩሽ ተብሎ ይጠራ የነበረው ሕዝብ ከገናናው የግብፅ መንግሥት በስተደቡብ ይገኝ የነበረው ነው። ይህች አሁን አገራችን የምትጠራበት ያለችው በጥንታዊ ግሪክም «ኢትዮጵያ» በሚለው ስም ትጠራ ነበር። ይሁን እንጂ የጥንቱ የኩሽ ወይም የኢትዮጵያ ግዛት ከዛሬው የኢትዮጵያ ግዛት ጋር አንድ አይደለም።

የኩሽ ሕዝብ ከይሁዳ እጅግ ርቆ የሚገኝ ሕዝብ ነበር። ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር ፍርድ ሥር ወደቀ። ይህም ሊሆን የቻለው የኩሽ ምድር ሰዎች ከጠላቶቻቸው ጋር የሚዋጉት ብዙ ጊዜ ከግብፅ ጋር በመተባበር ስለነበረ ነው። እንዲያውም በ715 ዓ.ዓ. ከኩሽ የመጣ ሰው የግብፅ መሪ ሆኖ ነበር። የግብፅ ምድር መጀመሪያ በአሦር በኋላም በባቢሎን እንደተወረረች ሁሉ፥ የኩሽ ምድርም የእግዚአብሔርን ፍርድ የቀመሰችው በዚህ መንገድ ነበር፤ ነገር ግን አንድ ቀን የዚህ ምድር ሰዎች እግዚአብሔርን እንደሚያከብሩና ለእርሱ ስጦታን ይዘው ወደ ጽዮን እንደሚመጡ ኢሳይያስ ተንብዮአል። ይህ ትንቢት መሢሑ ሊገዛ በሚመጣበት በዘላለማዊው ጊዜ መንግሥት እንደሚፈጸም አያጠራጥም። 

7. በግብፅ ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 19-20)፡፡

የጥንቷ ግብፅ በጥበቧ፥ በኃይሏና በሥልጣኔዋ የምትታወቅ ነበረች። እግዚአብሔር ሊፈርድባት በወሰነ ጊዜ ግን እነዚህ ሁሉ ከንቱ ሆኑ። እግዚአብሔር አሦራውያንን በኋላም ደግሞ ባቢሎናውያንን በመጠቀም በግብፅ ትዕቢት ላይ ፈረደና አዋረዳት።

እንደገና እግዚአብሔር ወደ መጨረሻው ዘመን የሚያመለክተውን፥ የግብፅን ደኅንነት በሚመለከት አስቀድሞ ተናገረ። ግብፆች ወደ እስራኤል በመምጣትና እግዚአብሔርን በማምለክ ያከብሩታል። ጥንት ጠላቶች በነበሩት በአሦርና በግብፅ መካከልም ሰላም ይሆናል፤ ሁለቱም ከእስራኤል ጋር በመሆን የእግዚአብሔር ሕዝብ ተብለው ይጠራሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ወደፊት አሕዛብ በሙሉ እግዚአብሔርን እንደሚያከብሩና እግዚአብሔርም ከእስራኤል እኩል የተመረጡ ሕዝቦች አድርጎ እንደሚቈጥራቸው እነዚህ ቈጥሮች ምን ያስተምሩናል? ለ) ይህ ነገር ለእኛ ትልቅ ማበረታቻ የሚሆነንና በተስፋ ወደፊት እንድንጠብቀው የሚያደርገን እንዴት ነው?

በኢሳይያስ 20 አሦርን ለመውጋት ከግብፅ ጋር እንዳትተባበር ወይም ተስፋዋን በግብፅና በኩሽ ጦር ላይ እንዳታደርግ እግዚአብሔር ይሁዳን ይመክራታል ምክንያቱም የእነርሱም ጦር ስለሚደመሰስ ነው። ኢሳይያስ ለሦስት ዓመታት እንደ ባሪያ በመልበስና በባዶ እግሩ በመመላለስ ይህንን በተግባር አሳየ። 

8. በባቢሎን ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 21፡1-10)፡፡ 

ባቢሎን በሜዶን እንደምትደመሰስ እግዚአብሔር ለሁለተኛ ጊዜ ይናገራል። 

9. በኤዶም ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 21፡11-12)፡፡

ኤዶምም ከጥንት የእስራኤልና የይሁዳ ጠላቶች መካከል አንዷ ነበረች። እግዚአብሔር ምሳሌዎችን በመጠቀም፥ በኤዶም ምድር ላይ ጨለማ እንደሚሆን ተንብዮአል። ይህ ኤዶም በአሦርና በባቢሎን ስለ መደምሰሷ የሚናገር ነው። ገና ማለዳ በሚመስልበት ወቅት የአሦር ጥፋት ይመጣል፤ የባቢሎን ምርኮ ጨለማም በእነርሱ ላይ ይሆናል። 

10. በዐረብ ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 21፡13-17)፡፡

የዐረብ ምድር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሽንፈት እንደሚገጥመውና እንደሚመታ እግዚአብሔር አስቀድሞ ተናገረ። በ732 ዓ.ዓ. አሦራውያን፥ ዲዳናይቶች በመባል ይታወቁ የነበሩትን የዐረብ ነጋዴዎች መውጋት ጀመሩ፤ በኋላም ባቢሎናውያን ይህንኑ አደረጉ። 

11. በኢየሩሳሌም ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 22)፡፡

እግዚአብሔር በአሕዛብ ላይ ፍርድን በሚያመጣበት ጊዜ፥ በምርጥ ሕዝቦቹ በአይሁዳውያን ላይ ፍርድን አያመጣም ማለት አይደለም፡፡ ኢሳይያስ ወደ ይሁዳና ወደ ዋና ከተማዋ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ጥፋቷ እንደቀረበ በመተንበይ ይህንን አስታወሳቸው። እግዚአብሔር እንደ ኢሳይያስ ላሉ ነቢያት ራእይን የሚሰጠው በኢየሩሳሌም ስለነበር ኢየሩሳሌም «የራእይ ሸለቆ» በመባል ተጠርታለች። እግዚአብሔር አስቀድሞ እንደተናገረው ኢየሩሳሌም፥ አሦራውያን ከሚያመጡት ጥፋት ልታመልጥ ብትችልም፥ ባቢሎናውያን እነርሱን በምርኮ ለማጋዝ ከሚያመጡት ጥፋት ግን አታመልጥም።

12. በጢሮስ ላይ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 23)፡፡

የጢሮስና የሲዶና ትንንሽ የከተማ መንግሥታት በጥንት ዘመን የነበሩ ሁለት ትልልቅ ከተሞች ናቸው። የጢሮስና የሲዶና ሰዎች ፊንቄያውያን በመባል ይታወቁ ነበር። በመላው ሜዲተራኒያን ባሕር በመርከብ እየተዘዋወሩ በመነገድ ችሎታቸው የታወቁ ነበር። ጢሮስ ባለጠጋ አገር ሆነች። እንዲሁም ልትጠፋና ልትደመሰስ እንደማትችል ባሰበችው መንገድ የተገነባች ነበረች። የጢሮስ ከተማ አንዱ ክፍል በየብስ ላይ፥ ሌላው ክፍል ደግሞ በውጊያ አንሸነፍም ባሉበት በሜዲተራኒያን ባሕር ደሴት ላይ የተመሠረተች ነበረች። ይህም የጢሮስን ሰዎች በራሳቸው እጅግ እንዲታበዩ አደረጋቸው።

ብዙ ጊዜ ጢሮስና ይሁዳ በሰላም የቆዩ ነበሩ። እግዚአብሔር ግን ጢሮስን በከፍተኛ ትዕቢትና በክፉ የጣዖት አምልኮዋ ምክንያት ጠልቷት ነበር። የበዓል አምልኮ የተጀመረው በጢሮስ ነበር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ጢሮስን ሊያጠፋት ወሰነ። በየብስ ላይ ተገንብቶ የነበረው ዋናው የከተማዋ ክፍል በ572 ዓ.ዓ. በናቡከደነፆር ሲደመሰስ፥ በደሴት ላይ የነበረው የከተማዋ ክፍል ደግሞ በ332 ዓ.ዓ. በታላቁ እስክንድር ተደመሰሰ። ስለ ጢሮስ ጥፋት ሕዝቅኤል ከዚህ ይልቅ ዘርዘር ባለ ሁኔታ ይተነብያል (ሕዝቅኤል 26-28)።

ታላቅ የሆነው የእግዚአብሔር እጅ ማንም ሊያጠፋን አይችልም በማለት ይመካ የነበረውን ይህን ትዕቢተኛ ሕዝብና መሪዎቹን በማዋረድ ታሪክን እንደሚቈጣጠር እንደገና እንዳሳየ እናያለን።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ስለ እግዚአብሔር እንዲሁም ሕዝቦችንና መሪዎችን ስለ መቆጣጠሩ ከእነዚህ ምዕራፎች ምን እንማራለን? ለ) በመንግሥታትና በመሪዎች ቍጥጥር ሥር የሚኖሩትን ክርስቲያኖች ይህ እውነት የሚያበረታታቸው እንዴት ነው? ሐ) እግዚአብሔር ትዕቢትን የሚጠላው ለምን ይመስልሃል? መ) ዛሬ ሕዝቦች ወይም መንግሥታት ሊታበዩ የሚችሉባቸው መንገዶችን ጥቀስ። ሠ) ብዙ ክርስቲያኖች ሊታበዩ የሚችሉት እንዴት ነው? የሚታበዩትስ ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ኢሳይያስ 7-12

ብዙውን ጊዜ አንድ ክርስቲያን ችግር ሲያጋጥመው የሚወስደው የመጀመሪያ እርምጃ ከሌላ ክርስቲያን ወይም ከጎረቤት ወይም ከወዳጅ እርዳታ መፈለግ ነው፤ ወይም ደግሞ መንግሥት ነገሮችን እንዲያቃናለት ወይም እንዲያስተካክልለት ወደ መንግሥት ፊቱን ያዞራል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ችግር ኣጋጥሞህ የነበረበትን ጊዜ ዘርዝር። እርዳታ ፍለጋ የሄድከው ወደ ማን ነበር? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ ችግር አጋጥሟት የነበረበትን ጊዜ ዘርዝር። እርዳታ ፍለጋ የሄደችው ወደ ማን ነበር?

ብዙ ክርስቲያኖች ችግር በሚገጥማቸው ጊዜ ወዲያውኑ እርዳታ ፍለጋ ወደ ሌሎች ክርስቲያኖች ወይም ወደ ዘመዶቻቸው ይሄዳሉ። እነርሱ ወይም ቤተ ክርስቲያናቸው ወደ ሕግ ነክ ችግሮች ውስጥ ከገቡ ደግሞ መንግሥት (ፍርድ ቤት) ለእነርሱ እንደሚፈርድላቸው በማሰብ ወደሚመለከተው ክፍል ይሄዳሉ። በዚህ ተፈጥሮአዊ እንቅስቃሴ ውስጥ አንዳችም ስሕተት ባይኖርም እንኳ አደገኛ የሆነ መንፈሳዊ ችግርን የሚያስነሣ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። እኛ ወይም ቤተ ክርስቲያናችን ችግር በሚገጥመን ጊዜ ወደ እግዚአብሔር መመለስ አለብን። በችግራችን ጊዜ መጠጊያችንና ረድኤታችን እርሱ ብቻ ሊሆን ይገባል። ረድኤት የምንፈልገው ሁልጊዜ ከሰዎች ከሆነ በእግዚአብሔር ላይ ባለን እምነት ማደግን አንማርም፤ እግዚአብሔር ስለ እኛ ሆኖ ይሠራ ዘንድም አልፈቀድንለትም ማለት ነው።

ኢሳይያስ ከምዕራፍ 7-12 የተጻፈው የይሁዳ ሕዝብና ንጉሥ አካዝ በችግር ውስጥ በነበሩ ጊዜ ነው። የሶርያ ንጉሥ የነበረው ረአሶን የእስራኤል ንጉሥ ከነበረው ፋቁሔ ጋር በመተባበር የይሁዳን ሕዝብ ለመውጋት ዐቀዱ። ንጉሥ አካዝ ምርጫ ነበረው፤ ይኸውም፡- በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል የመጣለትን የእግዚአብሔርን ቃል በማመንና በእግዚአብሔር በመታመን ጠላቶቹን ማሸነፍና ዕቅዳቸውን ማክሸፍ ወይም ደግሞ እንደ አሦራውያን ወዳሉ ሌሎች መንግሥታት ዕርዳታ ፍለጋ መሄድ። ብዙዎቻችን ዛሬ እንደምናደርገው፥ በዚህ የችግር ጊዜ አካዝ በእግዚአብሔር ላይ ብቻ መታመን አቃተው፤ ነገር ግን ወደ አሦራውያን ሄዶ ጠላቶቹን በመውጋት እንዲረዱት ጠየቀ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ አሦራውያን የእርሱን መንግሥትና ሕዝብ ሙሉ በሙሉ እንደሚያጠፉ አልተገነዘበም ነበር። አካዝ በእግዚአብሔር መታመን ስላልቻለ በሕዝቡ ላይ ከፍ ያለ ችግር አመጣ።

የውይይት ጥያቄ፥ አንተ ወይም ሌላ የምታውቀው ሰው ወይም ቤተ ክርስቲያን በችግር ጊዜ ዕርዳታ ወይም መፍትሔ ፍለጋ ወደ አንድ ስፍራ ሄዳችሁ፥ አስቀድሞ ከነበረው ችግር የላቀ ከባድ ችግር ይዛችሁ የተመለሳችሁበትን ሁኔታ በምሳሌነት ጥቀስ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ኢሳይያስ 7-12 አንብብ። ሀ) የኢሳይያስ ልጆች ስሞችን ከነትርጕማቸው ተናገር። ለ) እግዚአብሔር ለንጉሥ አካዝ የሰጠው ምልክት ምን ነበር? ሐ) እግዚአብሔር ለእስራኤልስ ሕዝብ (ኤፍሬም) የሰጠው ተስፋ ምን ነበር? መ) የአሦር ሕዝብ ምን ያደርግ ነበር? ሀ) ንጉሥ ይሆን ዘንድ ላለው ሕፃን የተሰጡትን የተለያዩ ስሞች ዝርዝር (ኢሳይያስ 9፡6-7)። ረ) ከዳዊት ዘር ስለሚመጣው ቅርንጫፍ ወይም ቍጥቋጥ የተሰጡትን ተስፋዎች ዘርዝር (ኢሳይያስ 11)።

ኢሳይያይስ 7-12 የተጻፈው የይሁዳ ሕዝብ በብሔራዊ ችግር ውስጥ ሳለ ነበር። የይሁዳ ሕዝብ በሶርያ (አራም) እና በእስራኤል (ኤፍሬም) ሊደመሰስ የተቃረበበት ጊዜ ነበር። እግዚአብሔር ለኢሳይያስና ለይሁዳ ሕዝብ ስለ መሢሑ መምጣት የሚናገሩ በርካታ አስደናቂ ትንቢቶችን የሰጣቸው በዚህ ጊዜ ነበር።

በኢሳይያስ ምዕራፍ 7፥ እግዚአብሔር ኢሳይያስን ወደ አካዝ እንዲሄድና ብሔራዊ ሰቆቃ ባለበት በዚህ ጊዜ ውስጥ በጌታ ይታመን ዘንድ እንዲያበረታታው ነገረው። ኢሳይያስ የስሙ ትርጒም «ቅራታዎቹ ይመለሳሉ» የሚለውን ልጁን ሸር-ያሹብን አስከትሎ ወደ ንጉሡ ዘንድ ሄደ። ይህ የኢሳይያስ ልጅ ይህንን ስያሜ ያገኘው የይሁዳ ሕዝብ እንደሚጠፉ፥ ነገር ግን እግዚአብሔር አንድ ቀን ወደ ይሁዳ ምድር የሚመልሳቸው ቅሬታዎች እንደሚኖሩ የሚያመለክተውን የኢሳይያስን መልእክት ለማንጸባረቅ ነበር። እግዚአብሔር ለአካዝ የእስራኤልን (የኤፍሬምን) ጦር እንዳይፈራ ነገረው። (የእስራኤል ጦር ኤፍሪም በመባል የሚጠራው በእስራኤል ውስጥ ያለው ዋናው ነገድ የኤፍሪም ነገድ በመሆኑ ነው)። ይልቁንም የሶርያም ሆነ የእስራኤል መንግሥታት በ65 ዓመታት ውስጥ ሊደመሰሱ ነበር። ይህ ትንቢት የሶርያና የእስራኤል መንግሥታት በአሦራውያን ሙሉ በሙሉ በተደመሰሱባቸው በ732ና በ722 ዓ.ዓ. ተፈጽሟል።

እግዚአብሔር ይህ ትንቢት እንደሚፈጸም ለአካዝ ለማረጋገጥ ሲል እውነትነቱን የሚያሳይ ምልክት እንዲጠይቅ ፈቀደለት። ምልክት ብዙ ጊዜ ወደ ፊት የሚፈጸም ትንቢትን እርግጠኛነት ለማሳየት በቅርቡ የሚፈጸም ድርጊት ነው። አካዝ በአሦራውያን እንጂ በእግዚአብሔር መታመን ስላልፈለገ ምልክት ለመጠየቅ ሳይፈቅድ ቀረ፤ እግዚአብሔር ግን ለአካዝ ምልክትን ሰጠው። ምልክቱም አንዲት ድንግል አማኑኤል ተብሎ የሚሰየም ልጅ እንደምትወልድ ነበር።

ስለዚህ ምልክት ምሁራን የተለያየ አሳብ አላቸው። ከአዲስ ኪዳን በግልጥ እንደምንረዳው ይህ ትንቢት ልዩ በሆነ መንገድ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተፈጽሞአል። ይህም የሆነው ድንግል ማርያም አምላክ የሆነውን ልጅ በመውለዷ ነው (ማቴዎስ 1፡23)። ነገር ግን ትንቢተ የሚፈጸመው ወደፊት ስለነበረ ምልክቱ አካዝን የሚያበረታታ አልነበረም። ስለሆነም የዚህ ትንቢት አፈጻጸም በሁለት በኩል ሳይሆን አይቀርም። የመጀመሪያው፥ የተፈጸመው በኢሳይያስና በአካዝ ዘመነ መንግሥት ነው። የኢሳይያስ የመጀመሪያ ሚስት የሆነችው የሸአር-ያሹብ እናት ስለሞተች፥ ኢሳይያስ ሌላ ሴት የሚያገባበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። ስለሆነም ድንግል የሆነች ሴት በማግባትና የምትወልደው ልጅ «አማኑኤል» የሚል ስም እንዲሰጠው በማድረግ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ስለነበር የይሁዳ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ እንደማይጠፋ አመልክቷል። ልጁ ባደገ ጊዜ አሦራውያን ሶርያንና እስራኤልን ስላሸነፉ የሁለቱ አገሮች ዛቻ አክትሞ ነበር። ምሁራን፥ ይህ አማኑኤል የሚለው ስም «ምርኮ ፈጠነ ብዝበዛ ቸኮላ» የሚል ትርጓሜ የነበረው የኢሳይያስ ሁለተኛ ልጅ ሌላ ስም ስለመሆኑ ይሁን ወይም የሌላ ልጅ ስም የተለያየ አመለካከት አላቸው።

ኢሳይያስ ስለሚመጣው ስለ አሦር መንግሥት ተነበየ። የአሦር መንግሥት ከሶርያና ከእስራኤል ጥቃት የይሁዳን መንግሥት ለጊዜው ማሳረፍ ብቻ ሳይሆን፥ በመጨረሻ በይሁዳ ሕዝብና በዳዊት ቤት ላይ ከፍተኛ ጥፋት እንደሚያመጣ ኢሳይያስ ተንብዮ ነበር።

ኢሳይያስ ምዕራፍ 8 ወደፊት በይሁዳና በአሦር መካከል ስለሚደረገው ጦርነት መተንበዩን ይቀጥላል። አሦር የቅጣት መሣሪያ ትሆን ዘንድ በተለይ በእግዚአብሔር የተመረጠች መሆኑን ኢሳይያስ ተናግሮ ነበር። እርሷ «የእግዚአብሔር በትር» ሆና ነበር። ይህ እንደሚፈጸም ምልክት ይሆን ዘንድ ኢሳይያስ የስሙ ትርጕም «ምርኮ ፈጠነ ብዝበዛ ቸኮለ» የተባለ ሌላ ልጅ ወለደ። ይህ ልጅ፥ ይሁዳ በኃጢአት ምክንያት በአሦር መንግሥት የምትማረክና የምትበዘበዝ መሆንዋን የሚያመለክት ትንቢት ነበር። ይህ ትንቢት በሕዝቡ ዘንድ ባይወደድም፥ ሰውን ሳይሆን እርሱን እንዲፈራው እግዚአብሔር ኢሳይያስን አስጠንቅቆት ነበር (ኢሳይያስ 8፡12-13)። እጅግ አስጨናቂ በሆኑ ጊዜያት እንኳ ኢሳይያስ በእግዚአብሔር ለመታመንና ሕጉንና ምስክርነቱን ለመስማት ወሰነ (ኢሳይያስ 8፡17፥ 20)።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አካዝ በእግዚአብሔር ሳይሆን፥ በአሦር ለመታመን ሲወስን ምን ነገር ተፈጸመ? ለ) ከሰው ይልቅ እግዚአብሔርን መፍራት እንዳለበት እግዚአብሔር ለኢሳይያስ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች እጅግ ጠቃሚ ምክር የሚሆነው እንዴት ነው? ሐ) አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰውን ሊፈራ የሚችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

በኢሳይያስ 9-10 ስለ መሢሑ የተነገሩ ትንቢቶችን ቀጥለን እናያለን። የንፍታሌም ነገድና የገሊላ ምድር እንደሚከበሩ ኢሳይያስ ይተነብያል። የንፍታሌም ነገድና የገሊላ ምድር የሚገኙት በእስራኤል ሰሜናዊ ክፍል ሲሆን፥ ብዙ ጊዜ አሕዛብ ይወሩት ነበር። ብዙ ጊዜ በአሕዛብ ቍጥጥር ሥር የሚቆይ ምድር ነበር። ኢሳይያስ ይህን ትንቢት በሚናገርበት ጊዜ፥ ይህ ክፍል የአሦር ሕዝብ ግዛት እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። እግዚአብሔር ግን አንድ ቀን በገሊላ ልዩ የሆነ ብርሃን እንደሚበራ ተናገረ። ይህም ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ማቴዎስ 4፡15-16)። በይሁዳ ሕዝብ ዘንድ ገዥ የሚሆን ልዩ ልጅ እንደሚወለድ ተነገረ። መሢሕ ለሆነው ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጡትን ስሞች ተመልከት፡-

1. ድንቅ መካር፡- እነዚህ ሁለት ጣምራ ቃላት መሢሑ በንግሥናው ሕዝቦች የሚደነቁበትን ልዩ ተግባር እንደሚፈጽም የሚያሳዩ ናቸው።

2. ኃያል አምላክ፡- ይህ ሕፃን አምላክ ነው፤ ነገር ግን ጠላቶቹን ደምስሶ ለመግዛት የሚችል ኃያልም ነው። 

3. የዘላለም አባት፡- ገዝተው እንደሚሞቱ በጥንት ዘመን እንደነበሩ ነገሥታት ሳይሆን፥ መሢሑና መንግሥቱ ለዘላለም የሚኖሩ ናቸው። እንደ አባት የሕዝቡ ጠባቂና ተንከባካቢ ነው።

4. የሰላም አለቃ፡- በዚያን ጊዜ የይሁዳ ሕዝብ ይኖሩበት እንደነበረው መሢሑ በጦርነት ጊዜ ከመግዛት ይልቅ በምድር ላይ በግለሰቦች ሕይወት፥ በኅብረተሰብ፥ እንዲሁም በሀገሪቱም ሁሉ ዘንድ ሰላምን ስለሚያመጣ ግዛቱ የሰላም ይሆናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ እነዚህ የኢየሱስ ስሞች የሚያበረታቱን እንዴት ነው? ለ) የኢየሱስን ባሕርይ የሚወክሉት እነዚህ ስሞች በችግር ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ በእርሱ ብቻ እንድንታመን የሚያበረታቱን እንዴት ነው?

የመሢሑ መንግሥት የሚከተሉት ባሕርያት ይኖሩታል፡-

1. ዘላለማዊ ነው።

2. በዳዊት ዙፋን ላይ ይቀመጣል። 

3. መንግሥቱ የፍትሕና የጽድቅ መንግሥት ይሆናል።

የኢሳይያስ ምዕራፍ 9 የመጨረሻ ግማሽና የምዕራፍ 10 የመጀመሪያ ክፍል በይሁዳ ላይ በቅርብ ጊዜ ስለ ሚፈጸመው ጉዳይ በመመለስ፥ በእግዚአብሔርና በገቡት ቃል ኪዳን ላይ በማመፃቸው ስለሚመጣው ፍርድ ይናገራል።

ዳሩ ግን በኢሳይያስ ምዕራፍ 10 መጨረሻ እግዚአብሔር በአሦር ላይ ስለሚመጣው ቅጣትና ፍርድ አስቀድሞ ይናገራል። አሦር፥ ልዑል አምላክ ሕዝቡን ለመቅጣት የተጠቀመባት መሣሪያው ብትሆንም ስለ ጭካኔዋና ትዕቢትዋ በተራዋ እግዚአብሔር ይቀጣታል። ይህ ትንቢት የተፈጸመው ባቢሎን አሦርን በደመሰሰችበት ወቅት ነው፤ ነገር ግን በይሁዳ ቅሬታዎች ይኖራሉ።

ኢሳይያስ ምዕራፍ 11 ስለሚመጣው መሢሕ ወደ መተንበይ ይመለሳል። ይህ ትንቢት በእግዚአብሔር ታላቅነት ላይ ከማተኮር ይልቅ በንጉሥንት ባሕርዩ ላይ ወደማተኮር ያዘነብላል። ይህ መሢሕ ከእሴይ ግንድ የወጣ በትር ወይም ቍጥቋጥ ተብሏል። ይህም መሢሑ በእግዚአብሔር ፍርድ ምክንያት ሊጠፋ ምንም ያህል ካልቀረው ከዳዊት ዘር እንዴት እንደሚመጣ የሚያሳይ ነው። (ለምሳሌ፡- የባሕር ዛፍ ከተቆረጠ በኋላ እንደገና እንደሚያቈጠቍጥ ዓይነት ነው።) 

1. መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ ይሆናል። ያም መንፈስ፡-

ሀ) ለመሢሑ በአመራሩ ጥበብንና ማስተዋልን፥ ምክርንና ኃይልን፥ እንዲሁም እውቀትን ይሰጠዋል። 

ለ) እግዚአብሔርን በመፍራት እንዲመላለስ መሢሑን ይረዳዋል። 

2. በእኩልነት፥ በጽድቅና በፍርድ ይበይናል። 

3. ክፉዎችን (በብረት በትር) በኃይል ይቀጣል። 

4. የፍጥረተ ዓለምን ተፈጥሮአዊ ሥርዓት በመለወጥ፥ የእንስሳት ዓለም እንኳ በዔደን ገነት ጊዜ እንደነበረው ዓይነት እንዲሆን ያደርጋል። እንስሳት እርስ በርሳቸው ኣይገዳደሉም፤ እባብም አያስፈራም።

5. ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን ታውቃለች፤ ታከብረውማለች።

የአይሁድ ነባር ጠላቶች የሆኑ አሦራውያን፥ ግብፃውያን፥ ኢትዮጵያውያን፥ ባቢሎናውያን፥ እንዲሁም ታዋቂ ጠላቶችና እስከ

ምድር ዳር ድረስ ያሉ ሕዝቦች ሁሉ ሳይቀሩ መሢሑን ያከብራሉ።

6. የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ የሆኑት አይሁድ ከተበተኑበት ስፍራ ሁሉ ወደ እስራኤል ይሰበሰባሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ስለ መሢሑና ስለ መንግሥቱ የተሰጡ እነዚህ የተስፋ ቃሎች በዘመናት ሁሉ የሚኖሩትን ሰዎች ፍላጎት የሚያሟሉት እንዴት ነው? ለ) ክርስቲያኖች በመከራ ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ተስፋ የሚሆናቸው እንዴት ነው?

ኢሳይያስ ምዕራፍ 12 እግዚአብሔር በመሢሑ በኩል ሊሰጥ ስለገባው የበረከት ቃል ኪዳን የተሰጠ የምስጋና መዝሙር ነው። ኢሳይያስ የኖረበት ዘመን አሦራውያን ባመጡት ጥፋት ምክንያት የቱንም ያህል የጨለመ ቢሆን፥ አንድ ቀን እግዚአብሔር ፍጹም ጽድቅና ትክክለኛ ፍርድ የሞላበት ታላቅ የሆነ ዘላለማዊ መንግሥት በምድር ላይ እንደሚያመጣ በማወቁ ደስ ሊሰኝና ሐሴት ሊያደርግ ቻለ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በእግዚአብሔር ፊት ስለሚኖረን የመንግሥተ ሰማያትና የዘላለም ሕይወት በረከት የተሰጠውን ተስፋ ማወቅ በችግር ጊዜ ውስጥ እንዴት ያበረታታናል? ለ) በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ወደፊት ስለሚያመጣው መንግሥት አሁን ለትንሽ ጊዜ እግዚአብሔርን በምስጋና ስገድለት።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ኢሳይያስ 1-6

የምንሰብከው ወንጌል በረከትንና ፍርድን በአንድነት አጠቃልሉ የያዘ ነው። ለደኅንነታቸው በኢየሱስ ለሚታመኑና ለእርሱ በመታዘዝ ለሚኖሩ ሁሉ በረከት አላቸው። በኢየሱስ በማያምኑና እርሱን በማይታዘዙት ሁሉ ላይ ደግሞ ፍርድ አለ።

የውይይት ጥያቄ፥ ለማያምን ሰው በምትመሰክርበት ጊዜ በእነዚህ በሁለቱም የወንጌል ገጽታዎች እንዴት እንደምትጠቀም አብራራ።

ይህ ትምህርት በትንቢተ ኢሳይያስ ውስጥ ተንጸባርቋል። ትንቢተ ኢሳይያስ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ለሚኖሩ ሰዎች የበረከት ቃል ኪዳን የያዘ መጽሐፍ ነው። ደግሞም ከሕዝቡ ብዙዎቹ እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ፈቃደኞች ባለመሆናቸው በሰበቡ ስለሚቀበሉት አሳዛኝ የሆነ እውነታ የሚገልጽ መጽሐፍ ነው። እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል።

ትንቢተ ኢሳይያስ የሚጀምረው፥ የሚጠቃለለውም ፍርድን ዋና አሳቡ በማድረግ ነው። አይሁድ ሊመጣባቸው ስላለው የፍርድ ቅጣት በማስጠንቀቅ ይጀምራል። ክፉና ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎችን በማስሕንቀቅ ይደመደማል።

ኢሳይያስ ምዕራፍ 1 የሚጀምረው በፍርድ ቤት ችሎት ፊት እንዳለ ሆኖ ነው። ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር በይሁዳ ሕዝብ ላይ ክስ ይመሠርታል። የገባውን ቃል ኪዳን ባፈረሰው በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ሰማይና ምድር ጭምር ምስክር ሆነው ቀርበዋል (ዘዳግም 4፡26)። አይሁድ እግዚአብሔርን ለመታዘዝና ቃል ኪዳኑን ለመጠበቅ ፈቃደኞች ባለመሆናቸው፥ የእግዚአብሔርን ፍርድ መቅመስ ጀምረው ነበር። በመንግሥት ደረጃ በአሕዛብ መሸነፍ ጀምረው ስለነበር እንደ ሰዶምና ገሞራ ለመጥፋት ደርሰው ነበር።

እግዚአብሔር አይሁድን ወደ እርሱ እንዲመጡ፥ ከእርሱ ጋር እንዲነጋገሩና የኃጢአታቸውን ይቅርታ እንዲቀበሉ ጋብዞ ነበር። ይህ ይሆን ዘንድ ግን መንገዳቸውን መለወጥ ነበረባቸው። ሥነ-ሥርዓታዊ ኣምልኮአቸው ዋጋ አልነበረውም። እግዚአብሔርን በእውነት ለማምለክ፥ ከእነርሱ የሚያንስ ዕድል ከገጠማቸው ሰዎች ጋር በፍትሕ መኖር ነበረባቸው።

የእግዚአብሔርን ፍርድ መቅመሳቸው የማይቀር ቢሆንም እንኳ ክፋት የሚጠፋበትና የእግዚአብሔር ሕዝብ ከአምላካቸው ጋር ለገቡት ቃል ኪዳን በመታዘዝ የሚኖሩበት ጊዜ ይመጣል። በዚያን ጊዜ የይሁዳ መንግሥት ዋና ከተማ የሆነችው ኢየሩሳሌም በጽድቅና በፍትሕ ትሞላለች።

የውይይት ጥያቄ፥ የኢሳይያስ ምዕራፍ 1 ዋና ዋና ትምህርቶችን ዘርዝርና ለቤተ ክርስቲያንህ በማስጠንቀቂያነት እንዴት ሊጠቅሙ እንደሚችሉ አስረዳ።

ኢሳይያስ ምዕራፍ 2 የሚያተኩረው «በመጨረሻዎቹ ቀናት» ላይ ነው። በትንቢት ውስጥ ይህ ሐረግ በጣም ጠቃሚ ነው። ይህ ሐረግ እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ በሚሠራበት በማንኛውም ጊዜ ስለሚያመጣው ፍርድ ወይም በረከት የሚናገር ቢሆንም፥ ብዙ ጊዜ የሚያመለክተው ግን እግዚአብሔር ለዚች ምድር ያለውን ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ስለሚፈጽምበት የመጨረሻ ዘመን ነው። ኢሳይያስ ምዕራፍ 2 የሚጠቅሰው ስለዚሁ የመጨረሻ ዘመን ነው። ኢሳይያስ ምዕራፍ 2 በዚህ ጊዜ ስለሚፈጸሙ ሁለት ጉዳዮች ይናገራል፡

1. የታላቅ በረከት ጊዜ (ኢሳይያስ 2፡1-5)፡- ይህ የበረከት ጊዜ እግዚአብሔር በምድር መንግሥታታት ሁሉ ላይ በሚገዛበት ወቅት የሚፈጸም ነው። ሰዎች ሁሉ ከተለያዩ መንግሥታት እግዚአብሔርን ለማምለክ ይመጣሉ። እነርሱም ለእግዚኣብሔር ሕግ ታዛዦች ሆነው ይኖራሉ። እርሱ ደግሞ በመካከላቸው እውነተኛና ጻድቅ ፈራጅ ይሆናል። በሕዝቦች መካከልም ዘላቂ ሰላም ይሆናል።

2. የታላቅ ፍርድ ጊዜ (ኢሳይያስ 2፡6-22)፡- የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑት አይሁድ የእግዚአብሔርን ታላቅ በረከት ቀምሰውት ነበር። ብዙ ብር፥ ወርቅ፥ ፈረሶች፥ ወዘተ. ነበሯቸው። ነገር ግን ጣዖትን ማምለክና ትዕቢትን የመሰለ ከፍተኛ ክፋትም በመካከላቸው ነበረ። ስለዚህ የእግዚአብሔር የፍርድ ቀን ሲመጣ ክፉ ያደረጉትን ሁሉ ይቀጣል። የእግዚአብሔር ፍርድ የእርሱን ገናናነት በመግለጥ ሕዝቡ እንዲፈሩት ያደርጋል። ሰው መፍራት የሚገባው ከእግዚአብሔር ፍርድ ሊያስጥለው የማይችለውን ሰውን ሳይሆን፥ እግዚአብሔርን ነው። ኢሳይያስ ምዕራፍ 3 የሚያተኩረው በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ኃጢአት እንዲሁም እግዚአብሔር እነርሱን በሚቀጣበት ምክንያት ላይ ነው። እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ለመፍረድ በሚመጣ ጊዜ፥ የእግዚአብሔርን ፍርድ ከሁሉ በላይ የሚቀበሉት መሪዎች ነበሩ። በእስራኤል መሪዎች የማይኖሩበት ጊዜ ይመጣል። ለሕዝቡ መውደቅ እግዚአብሔር መሪዎችን እንዴት እንደሚወቅስ አስተውል (ኢሳይያስ 3፡12-15)። በተጨማሪም ይህ ምዕራፍ እግዚአብሔር በመታዘዝ ሳይኖሩ፥ ስለ ውጫዊ ውበታቸው ብቻ ስለሚያስቡና ስለሚታበዩ ሴቶች ኃጢአት አበክሮ ይናገራል። እግዚአብሔር በውበታቸው የታበዩትን እነዚህን ሴቶች ውበታቸው ወደሚረግፍበትና ወንዶቻቸው ወደሚገደሉበት ምርኮ በማፍለስ እንደሚያዋርዳቸው ይናገራል። 

ኢሳይያስ ምዕራፍ 4 እንደገና ተመልሶ የእግዚአብሔር ሕዝብ ቅሬታዎች ለወደፊት ስለሚያገኙት ክብር ይናገራል። በዚህ ክፍል የመሢሑ ወይም የኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ስም ከሆነው «ከእግዚአብሔር ቍጥቋጥ» ጋር እንድንተዋወቅ ተደርጓል። እስራኤል ወደ ቀድሞ ክብርዋ ትመለሳለች፤ ሕዝቡም የተቀደሱ ይሆናሉ። እግዚአብሔር በምድረ-በዳ እንዳደረገው (ዘጸአት 40፡34-38)፥ በመካከላቸው እንደ እሳት ዐምድና እንደ ክብር ደመና ይኖራል።

ኢሳይያስ ምዕራፍ 5 እንደገና በፍርድ መሪ አሳብ ላይ ተመሥርቶ፥ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ በሚፈርድባቸው ምክንያቶች ላይ ያተኩራል። ኢሳይያስ 5፡1-7 እስራኤል ከወይን ቦታ ጋር ተነጻጽራ የቀረበችበት የፍርድ መዝሙር ነው። በእስራኤል ውስጥ በጣም ከተለመዱና ከታወቁ የእርሻ ሥራዎች አንዱ የወይን ተክል ሥራ ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ለመግለጥ ወይንን በምሳሌነት ተጠቀመ። እግዚአብሔር የራሱን ወይን-እስራኤልን በከነዓን ምድር ተከለ፤ ጠበቃት፤ ተንከባከባትም። ነገር ግን እስራኤል የጽድቅ ፍሬ የሆነውን መታዘዝን በማፍራት ፈንታ ኮምጣጣ የሆነውን ያለመታዘዝንና የሐሰተኛ አምልኮን ፍሬ አፈራች። ስለዚህ እግዚአብሔር በወይኒቱ ላይ ይፈርዳል ያጠፋታልም።

በኢሳይያስ 5፡8-30 የእግዚአብሔርን ፍርድ ያመጡትንና በሕዝቡ መካከል ተስፋፍተው የነበሩትን ኃጢአቶች በዝርዝር እንመለከታለን። እነርሱም እያንዳንዳቸው የ «ወዮታ» ቃል የያዙ ስድስት ኃጢአቶች ነበሩ። በድሆች ጉልበት፥ ድካምና ጥረት ያለማቋረጥ ሀብት እያካበቱ የመኖር ፍላጎት የነበራቸው ሰዎች፥ ለእግዚአብሔርና ለሕዝቡ ባለባቸው ኃላፊነት ግድ የሌላቸውና ግብዣ በማድረግ የሚሰክሩ መሪዎች፥ በክፋትና በግፍ ደስ የሚሰኙና እግዚአብሔር በክፉዎች ላይ ስለሚያመጣው ፍርድ በተናገረው ቃል ላይ የሚሳለቁ፥ እግዚአብሔር መልካም ነው ያለውን ነገር ክፉ ነው የሚሉ ወይም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆኑትን ነገሮች መልካም ነው የሚሉ፥ በጥበባቸው የሚታበዩ፥ እንደዚሁም አዘውትረው የሚሰክሩና ፍርድን የሚያጣምሙ ሰዎች ነበሩ።

ኃጢአት ቅጣትን ያመጣል። በመሆኑም እግዚአብሔር ለእርሱ ባለመታዘዝ የሚኖሩትን ሰዎች እንደሚቀጣ ይናገራል። እግዚአብሔር ታላቅና ኃያል የሆነ ባዕድ ሕዝብን በይሁዳ ሕዝብ ላይ በማስነሣት ያጠፋቸዋል። ኢሳይያስ ምዕራፍ 6 ስለ ኢሳይያስ መጠራትና ለይሁዳ ሕዝብ የእግዚአብሔር ነቢይ እንዲሆን ስለ መመረጡ ይነግረናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እነዚህ ምዕራፎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለእግዚአብሔር ባለመታዘዝ የሚመላለሱ ከሆነ ስለሚያጋጥሟቸው ነገሮች የሚያስጠነቅቁት ምንድን ነው? ለ) ሀብታቸውንና ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ ስለሚጠቀሙ ሰዎች እነዚህ ምዕራፎች የሚያቀርቡት ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው? ሐ) እነዚህ ምዕራፎች [ በመከራና በሥቃይ ጊዜያት ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ማበረታቻ የሚሆን የወደፊት ተስፋ የሚናገሩት ነገር ምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

በትንቢተ ኢሳይያስ ውስጥ የሚገኙ ዋና ዋና አሳቦች

ትንቢተ ኢሳይያስን በምታነብበት ጊዜ፥ የሚከተሉትን ዋና ዋና አሳቦች መመልከት ጠቃሚ ነው። እነዚህ ዐበይት ዋና አሳቦች ሌሎች ትንቢቶችና ትምህርቶች የተመሠረቱባቸው የመጽሐፉ የጀርባ አጥንት ተደርገው የሚታዩ ናቸው።

1. የእግዚአብሔር ባሕርይ፡- ትንቢተ ኢሳይያስ ከሌሎቹ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ይልቅ የእግዚአብሔርን ታላቅነት፥ በተፈጥሮ፥ በሕዝቦችና በመንግሥታት ላይ ያለውን የበላይ ተቆጣጣሪነትን የሚገልጽ መጽሐፍ ነው። ይህ ባሕርይ ታላቅነትና ግርማን፥ ፍቅርና ምሕረትን፥ ፍርድና ቍጣን፥ ይቅርታና ተሐድሶን የሚጨምር ነው። እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንዴት እንደተገለጠ ተመልከት።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያኖች ስለ እግዚአብሔር ማንነት ግልጽና ትክክለኛ ግንዛቤ ሊኖራቸው የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ለ) ይህ ነገር እንዴት ሊያበረታታቸው ይችላል? ሐ) እግዚአብሔርን በትሕትና ለማገልገል ይህ ሊረዳቸው የሚችለው እንዴት ነው?

2. እግዚአብሔር የእስራኤል ቅዱስ ነው፡- ኢሳይያስ በመጽሐፉ እግዚአብሔርን ለመጥራት የተጠቀመባቸው የተለያዩ ስሞች ቢኖሩትም፥ አንድ ልዩ የሆነ ስም ግን ነበረው፤ ያም ስም «የእስራኤል ቅዱስ» የሚል ነው። በሌሉች ብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ አልፎ አልፎ ከመጠቀሱ በቀር፥ ይህ የእግዚአብሔር ስም የሚገኘው በትንቢተ ኢሳይያስ ውስጥ ብቻ ነው። ቅዱስ በሆነው በእግዚአብሔር ባሕርይ ላይ ያተኩራል፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ቅዱስ ብሉ ቢጠራቸውም እንኳ ከሕዝቡ ኃጢአተኝነት ጋር በንጽጽር የቀረበ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ጴጥ. 1፡15-16 አንብብ። ከእግዚአብሔር ቅድስና ጋር ሲነጻጸር የክርስቲያን ኃላፊነት ምንድን ነው?

3. እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ያዋርዳል (ኢሳይያስ 2፡11-17)፡

በእዚህ ስፍራ ትዕቢተኞች የተባሉት ሀ) ለእግዚአብሔርና ለሕዝቡ ተቃራኒ ሆነው የቆሙ ሕዝቦች፥ ለ) ራሳቸውን በእግዚአብሔር ፊት በማዋረድ ለእግዚአብሔር ለመታዘዝ ፈቃደኛ ያልሆኑ የይሁዳ ወይም የሌሎች ሕዝቦች ነገሥታት ወይም ሐ) በታዛዥነት ሕይወታቸውን እግዚአብሔርን ለመስጠት ፈቃደኞች ባለመሆን ትዕቢተኝነታቸውን የሚገልጡ ማንኛቸውም ተራ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። እግዚአብሔር ትዕቢትን ስለሚጠላ ይፈርድበታል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ትዕቢትን በእነዚህ ሦስት የሕይወት ክፍሎች ያየኸው እንዴት ነው? ለ) እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ሲያዋርድ ያየኸው እንዴት ነው? ሐ) ይህ በተለይ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንዳይታበዩ ማስጠንቀቂያ መሆን ያለበት እንዴት ነው?

4. እግዚአብሔር እስራኤልን የሚቤዥ ነው፡- እግዚአብሔር አይሁድን በኃጢአታቸው ምክንያት ተማርከው እንዲሄዱና ለአሕዛብ መንግሥት ባሪያዎች እንዲሆኑ ቢያደርግም፥ የሚቤዣቸውም ራሱ እግዚአብሔር ነው (ኢሳይያስ 41፡14፤ 43፡14፤44፡6 ተመልከት)። 

5. እግዚአብሔር ባዕዳን መንግሥታትን ይቆጣጠራል፡- በትንቢተ ኢሳይያስ ውስጥ ያለማቋረጥ የምናየው እግዚአብሔር በአጠቃላይ የአሕዛብ ሁሉ ተቆጣጣሪ መሆኑን ነው። ሕዝቡን ለመቅጣት አሦራውያንን ያስነሣው እግዚአብሔር ነው። የይሁዳን ሕዝብ ለማጥፋት ባቢሎንን ያስነሣው እግዚአብሔር ነበር። ባቢሎንን ለማጥፋትና የይሁዳን ሕዝብ ወደ እስራኤል ለመመለስ የእግዚአብሔር «አገልጋይ» የሆነውን ቂሮስን የተጠቀመበት እግዚአብሔር ነበር። እግዚአብሔር አንድን ሕዝብ ከፍ ያደርጋል፤ ሌላውን ያዋርዳል። እግዚአብሔር በእርሱ ላይ በሚያምፁት አሕዛብ ሁሉ ላይ ይፈርድባቸዋል።

6. የእስራኤል ቅሬታዎች፡- ትንቢተ ኢሳይያስ ካተኮረባቸው ነገሮች አንዱ ቅሬታዎችን የሚመለከት ነው። በኤልያስ ዘመን ለበኣል ያልሰገዱ 7000 ሰዎች እንደነበሩ ሁሉ (1ኛ ነገሥት 19፡18)። እግዚአብሔር ምንጊዜም ለእርሱ ታማኞች የሆኑ ቅሬታዎች አሉት። እግዚአብሔር እነዚህን ቅሬታዎች ነፃ ለማውጣትና ለማዳን ደግሞም ወደ ይሁዳ ምድር ለመመለስ ቃል ገብቶላቸው ነበር። ኢሳይያስ ለእነዚህ ቅሬታዎች የሚጽፍላቸው የማበረታቻ መልእክት ታላቅ ጥፋት በሚሆንበት ጊዜ እንኳ ለእግዚአብሔር ታማኞች እንዲሆኑ የሚያሳስብ ነበር። በእምነታቸው ጸንተው ቢቆዩና ለእግዚአብሔር ቢታዘዙ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሽልማትን ያገኛሉ።

7. ስለ እስራኤል ሕዝብ ተሐድሶ፡- እግዚአብሔር በእስራኤልና በይሁዳ ላይ ፍርድን እንደሚያመጣ አስቀድሞ የተናገረ ቢሆንም ከምርኮ እንደሚመልሳቸውም አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። እግዚአብሔር አሁንም ቢሆን ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም ዕቅድ ነበረው። 

8. በይሁዳ ላይ ገዥ የሚሆነው የመሚሑ መምጣት፡- በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙት መጻሕፍት ሁሉ በላቀ ሁኔታ ትንቢተ ኢሳይያስ በመሢሑ መምጣት ላይ ትኩረት ያደርጋል። መሢሑ ንጉሥ ሆኖ ሊገዛ ከዳዊት የዘር ግንድ ይመጣል። ከድንግል ይወለዳል፤ ነገር ግን አማኑኤል ይሆናል። በሰዎች መካከል በሥጋ የሚኖር በባሕሪው ግን እግዚአብሔር ማለት ነው። በቤተልሔም ተወልዶ፥ በገሊላ ያገለግላል። የገዛ ወገኖቹ ይገድሉታል፤ እርሱ ግን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል። እነዚህ ስለ መሢሑ ከተነገሩ ትንቢቶች ጥቂቶቹ ናቸው። አዲስ ኪዳን ከማንኛውም የትንቢት መጻሕፍት ይልቅ ከትንቢተ ኢሳይያስ ይጠቅሳል።

9. የእግዚአብሔር አገልጋይ፡- በትንቢተ ኢሳይያስ ሁለተኛ ግማሽ ክፍል ካሉት ልዩ አሳቦች አንዱ «የአገልጋይ መዝሙራት» ወይም ልዩ ስለሆነው የእግዚአብሔር አገልጋይ የሚናገረው መዝሙር ነው (ኢሳይያስ 42፡1-7፤ 49፡1-9፤ 52፡13-53፡12፤ 61፡1-3)። እስራኤል የእግዚአብሔር አገልጋይ እንደሆነች የተጠቀሰ ቢሆንም፥ እነዚህ ክፍሎች የሚናገሩት ግን ስለ አንድ ልዩ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው። እስራኤል ፈቃዱን የምትፈጽም አገልጋዩ እንድትሆን እግዚአብሔር የመረጣት ቢሆንም፥ እርስዋ ግን አልቻለችም። ሆኖም እግዚአብሔር ፈቃዱን ሙሉ በሙሉ የሚፈጽምና ታዛዥ የሆነ ልዩ አገልጋይ ነበረው፤ እርሱም መሢሑ ነበር። ስለ እስራኤል ሕዝብ ኃጢአት የሚሞትና የሚፈውሳቸው ይህ መሢሕ ነው። ከአዲስ ኪዳን በግልጽ እንደምንረዳው፥ ይህ መሢሕ የእግዚአብሔርና የሰው ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ኢየሱስ አምላክ ቢሆንም እንኳ ትሑት ሆኖ የእግዚአብሔርና የሰው ዘር አገልጋይ ሆነ (ማርቆስ 10፡45 ተመልከት)። በትሕትናና በመታዘዝ እስራኤልና ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ጋር፣ እንዲሁም እርስ በርሳቸው ሊኖራቸው የሚገባ ግንኙነት ምን መምሰል እንዳለበት ገለጠ።

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) አምላክ የሆነው ኢየሱስ፥ አገልጋይ መሆኑ የሚያስገርመው ለምንድን ነው? ለ) ኢየሱስ አገልጋያችን የሆነው በምን መንገድ ነው? ሐ) እንዴት የእግዚአብሔር አገልጋዮች መሆን እንደምንችል ግለጽ። መ) የሌሎች አገልጋዮች መሆን የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ምሳሌዎችን ስጥ። ሠ) የእግዚአብሔርና የሌሉች አገልጋዮች ለመሆን የሚፈቅዱ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ቁጥር ያነሰው ለምንድን ነው?

10. መሢሑ የሚመሠርተው መንግሥት፡- ትንቢተ ኢሳይያስ መሢሑ ስለሚመሠርተው ዘለዓለማዊ መንግሥት ብዙ ሥዕላዊ መግለጫዎችን ይሰጣል። የዚህ መንግሥት ማዕከል ኢየሩሳሌም ትሆናለች። በዚህም ሰዎች ሁሉ አሕዛብም ሳይቀሩ መጥተው ለማምለክ በሚችሉበት ሁኔታ ሰላምና ብልጽግና ይሆናል። እግዚአብሔር፥ በዚያ የዳዊት ዘር በሆነው በልጁ በኩል ይገዛል (ኢሳይያስ 24፡23፣ 33፡22፤ 43፡15፤ 44፡6 ተመልከት)። ምንም እንኳ ምሁራን ከእነዚህ ትንቢቶች መካከል ቀጥተኛ የሆኑትና ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ የቀረቡት ምን ያህሉ እንደሆኑና ስለ አፈጻጸማቸው የማይስማሙ ቢሆንም፥ እነዚህ ትንቢቶች እግዚአብሔር በዘመኑ ፍጻሜ ስለሚመሠርተው የተከበረ መንግሥት እጅግ ውብ የሆኑ መግለጫዎችን የሚሰጡ ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ 10 ትምህርቶች ምን እንደሚል መረዳት ለክርስቲያኖች የሚጠቅመው ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የትንቢተ ኢሳይያስ ዓላማ

የትንቢተ ኢሳይያስ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙ ጥልቅ የሥነ-መለኮት ትምህርቶች መካከል አንዳንዶቹን የያዘ ነው። መጽሐፉ የይሁዳ ሕዝብ በባቢሎን መንግሥት የሚማረክበትን ምክንያትና የይሁዳ ሕዝብ ቅሬታ ደግሞ በመጨረሻ ከምርኮ እንደሚመለስ ቢናገርም፥ የመጽሐፉ ተቀዳሚ ትኩረት ግን ይህ አይደለም። የኢሳይያስ ትኩረት በእግዚአብሔር ባሕርይ ላይ ነው። የቀሩት ትምህርቶች በሙሉ ኢሳይያስ ስለ እግዚአብሔር የነበረው ግንዛቤ ውጤቶች ናቸው። እግዚአብሔር በይሁዳ ሕዝብ ላይ እንደሚፈርድ ኢሳይያስ የሰጠው የማስጠንቀቂያ መልእክት የተመሠረተው በእግዚአብሔር ቅድስናና በሕዝቡ መካከል በሚከሠት ኃጢአት ላይ እንደሚፈርድ አስቀድሞ በሰጠው ቃል ኪዳን ላይ ነው። ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆነው የሚቆዩ ቅሬታዎች እንደሚኖሩ የተሰጠው ማረጋገጫ ወይም ዋስትና ደግሞ እግዚአብሔር ለገባው የተስፋ ቃል ያለውን ታማኝነት የሚያሳይ ነው። ስለ ሕዝቦች መሸነፍ የሚናገሩት ትንቢቶች ደግሞ እግዚአብሔር በምድር ላይ የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ሁሉ በበላይነት እንደሚቆጣጠርና ሉዓላዊ መሆኑን የሚያንጸባርቁ ናቸው። እግዚአብሔር ብቻውን በሚነግሥበት ጊዜ የሚኖረውን ወርቃማ ዘመንና ሰላም በምድር ላይ መስፈን የሚያሳየው፥ ንጉሥነቱንና በምድር ላይ ያለውን ዓላማ በመፈጸም መንግሥቱን እንደሚመሠርት ነው። በዚህ መንግሥት ጽድቅ ይኖራል፤ ደግሞም አይሁድም ሆኑ አሕዛብ እግዚአብሔርን ያመልኩታል።

የውይይት ጥያቄ፥ በኢትዮጵያ የሚገኙ ክርስቲያኖችም ይህን ዓላማ በሚገባ መረዳት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔር በነቢይ በኩል ዛሬ ለኢትዮጵያ ቢናገር ኖሮ የሚሰጠው መልእክት ምን ዓይነት የሚሆን ይመስልሃል? ለምን?

ነቢይ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ወይም ቃል አቀባይ መሆኑን ተመልክተናል። በዘመኑ ለነበሩ ሰዎች እንዲያደርስ እግዚአብሔር ግልጽ የሆነ መልእክት ይሰጠው ነበር። መልእክቱ ብዙ ጊዜ የሚያመለክተው ነቢዩ የነበረበትን ዘመን ነው። ይኸውም ሊመጣ ስላለው ፍርድ ማስጠንቀቂያ ወይም ተግሣጽ የሚሆን ወይም እግዚአብሔር ምን እንደሚያደርግላቸው የሚናገር የተስፋ መልእክት ነበር። አንዳንድ ጊዜ መልእክቱ ወደፊት የሚፈጸምን ነገር ያመለክት ነበር። በዚያን ዘመን ለነበሩ እስራኤላውያን በቅርቡ የተፈጸመ ሊሆን ይችላል፤ ወይም ደግሞ ገና ወደፊት በዘመናት መዉረሻ የሚፈጸም ትንቢት ሊሆን ይችላል።

ኢሳይያስ ከ740-680 ዓ.ዓ. ለይሁዳ ሕዝብ የእግዚአብሔር ቃል አቀባይ ነበር። ኢሳይያስ ታላቅ ነቢይ የነበረ ቢሆንም፥ መልእክቱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ለመመለስ እስከዚህም ስኬታማ አልነበረም። ትንቢተ ኢሳይያስን ለመረዳት ከምዕራፍ 6 መጀመር አለብን። ይህ ክፍል ኢሳይያስ የእግዚአብሔር ነቢይ እንዲሆን እንዴት እንደተጠራ የሚያሳይ ነው። ይህ ጥሪ በ740 ዓ.ዓ. ለኢሳይያስ ደረሰውና ሕይወቱን ለወጠው። አብዛኛዎቹ የትንቢተ ኢሳይያስ ኋለኛ መልእክቶች የሚያንጸባርቁት እርሱ በተጠራ ጊዜ ምን እንደተማረ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ኢሳይያስ 6 አንብብ። ሀ) ኢሳይያስ ያየው ራእይ ምን ነበር? በዚህ ራእይ ውስጥ የታዩት የእግዚአብሔር ዐበይት ባሕርያት ምንድን ናቸው? ለ) ኢሳይያስ ስለ ራሱና ስለ እስራኤላውያን ሕይወት ከዚህ ራእይ የተነዘበው ምንድን ነው? ሐ) የኢሳይያስ መልእክት ምን መሆን ነበረበት? መ) ለኢሳይያስ ሥራ የተሰጠው ምላሽ ምን ነበር? ሠ) በሕዝቡ ላይ ምን ሊደርስ ነበር? (ቍጥር 11-13)።

ኢሳይያስ 6 የሚያንጸባርቀው የትንቢተ ኢሳይያስን ዋና ዋና ትምህርቶችን ነው። በኢሳይያስ 6 የሚከተሉትን ዋና ዋና ትምህርቶችን መመልከት እንችላለን፡-

1. የእግዚአብሔር ታላቅነትና ቅድስና (6፡1-4)፡- እነዚህን ሁለት የእግዚአብሔር ባሕርያት በመጽሐፉ በአጠቃላይ ያለማቋረጥ በተደጋጋሚ የምናያቸው ናቸው። በመጀመሪያ፥ ኢሳይያስ የእግዚአብሔርን ታላቅነት «በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ» አየ። በዚህ ዓይነት ትንቢተ ኢሳይያስ እግዚአብሔርን የሰዎች ሁሉ ንጉሥ ወይም ገዥ አድርጎ ያለማቋረጥ ያቀርበዋል። እግዚአብሔር በሰማይ በዙፋኑ ላይ ሆኖ በምድር የሚፈጸሙ ድርጊቶችንና አካሄድን ይመራል። በሕዝቦች ላይ ይገዛል፤ ድርጊቶቻቸውንም ሁሉ ይቆጣጠራል። ኃይሉና ጥበቡ እጅግ ከፍተኛና የላቀ በመሆኑ፣ ሊቋቋመው የሚችል ማንም የለም።

ሁለተኛ፡ ኢሳይያስ እግዚአብሔርን ያየው በቅዱስነቱ ነው። ሱራፌልም ያለማቋረጥ ይህንን የእግዚአብሔርን ባሕርይ ያውጁ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ «ቅዱስ» ማለት ምን ማለት ነው? ይህንን ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ ተመልከት።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ «ቅዱስ» የሚለው ቃል መሠረታዊ ትርጕም «መለየት» ማለት ነው። «መለየት» የሚለው ቃል የሚያመለክተው ሁለት ነገሮችን ነው፤ በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር ከተፈጠሩ ነገሮች ሁሉ የተለየ መሆኑን ያመለክታል። እርሱ ከተፈጠሩ ነገሮች ሁሉ የተለየና የላቀ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፥ «ቅዱስ» የሚለው ቃል የሚያመለክተው፥ እግዚአብሔር ከኃጢአት የተገለለ መሆኑን ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ የሚፈርደው ቅዱስ ስለሆነ ነው።

በትንቢተ ኢሳይያስ፣ ነቢዩ እግዚአብሔርን የሚጠራበት የተለየ ስም አለው። ኢሳይያስ እግዚአብሔርን «የእስራኤል ቅዱስ» ብሎ ይጠራዋል፤ ይህም ስም 26 ጊዜ በመጽሐፉ ውስጥ ተጽፎ እናየዋለን። ስለሆነም፥ በትንቢተ ኢሳይያስ ውስጥ በአጠቃላይ በግልጽ እንደምናየው፥ የመጽሐፉ ትኩረት በእግዚአብሔር ቅድስና፥ በኃጢአት ላይ በሚገልጸው ቍጣና ኃጢአተኞችን ለመቅጣት ባለው ውሳኔ ላይ ነው። ይህም የራሱን ሕዝብ እስራኤልንና ይሁዳን፥ ደግሞም አሕዛብን በመቅጣቱ ታይቷል። 

2. የእግዚአብሔር ሕዝብ ኃጢአተኝነት (6፡5-7)፡- ኢሳይያስ የእግዚአብሔርን ቅድስና በተመለከተ ጊዜ ወዲያውኑ የተገነዘበው ነገር እርሱና ሕዝቡ ምን ያህል ኃጢአተኞች እንደሆኑ ነበር። የእግዚአብሔርን ቅድስና የሚያሳይ ራእይ ሁልጊዜ የሚያስገነዝበን የራሳችን ኃጢአት ከፍተኛነት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ የእግዚአብሔርን ቅድስና ይበልጥ በተረዳን ቍጥር የራሳችንን ኃጢአተኝነት በበለጠ በመገንዘብ ያዳነንንና የወደደንን እግዚአብሔርን እንዴት አብልጠን ልናደንቀውና ልናከብረው እንደሚገባን ግለጽ። 

የትንቢተ ኢሳይያስ አብዛኛው ክፍል የሚያተኩረው በፍርድ ላይ ነው። ይህ ፍርድ እግዚአብሔርን በካዱ ሕዝቦች ሁሉ ላይ ይመጣል። ነገር ግን ይህ ፍርድ በተለይ የሚመጣው የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ በሆኑት በአይሁድ ላይ ነው። ኢሳይያስ ይህ ፍርድ የሚመጣበትን ምክንያት ይናገራል። ይህ ፍርድ የሚመጣው በእግዚአብሔር ማንነት ምክንያት ነው። እርሱ ክፉዎችን የሚቀጣ ቅዱስና ጻድቅ ስለሆነ ነው። ፍርዱ የሚመጣው የእግዚአብሔር ሕዝብ ሕግጋቱን በግልጽ በመቃወማቸው፥ ለሰዎች ቅን ፍርድን በመንፈጋቸው፥ በመታበያቸው፥ ወዘተ. ነው።

የውይይት ጥያቄ.፥ እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ ክርስቲያኖች ሕይወታቸውና ሥራዎቻቸው ሁሉ እንደሚፈረዱና ፍርድ እንደሚሰጥ (እንደሚፈተኑ) በማወቅ መኖር ያለባቸው እንዴት ነው? (1ኛ ቆሮንቶስ 3፡10-15 ተመልከት)።

3. የኢሳይያስ መልእክት ተገቢውን ምላሽ ማጣቱ (6፡9-10)፡- ኢሳይያስ መልእክቱን ለማስተላለፍ ከተዘጋጀበት ከመጀመሪያው አንሥቶ ማንም እንደማይሰማው እግዚአብሔር ነግሮት ነበር። ሕዝቡ ንስሐ እንዲገቡና ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ኢሳይያስ ያለማቋረጥ ቢለምንም፥ ሕዝቡ ግን አልተቀበሉትም። ኃጢአታቸው የእግዚአብሔርን ድምፅ መስማት የማይሹ ልበ-ደንዳናዎች አድርጎአቸው ነበር። ዓለማዊ በሆነ ምርጫቸው ረክተው ነበርና የያዙትን ለመለወጥ አይፈልጉም ነበር። አይሁዶች ሃይማኖታውያንና እግዚአብሔርን ሥርዓታዊ በሆነ መንገድ ያመልኩ የነበሩ ሰዎች ቢሆኑም፥ እግዚአብሔርን ከልባቸው የሚያመልኩ ወይም ከእነርሱ ጋር በሲና ተራራ ላደረገው ቃል ኪዳን በመታዘዝ የሚኖሩ ሰዎች አልነበሩም።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ተመሳሳይ ነገር ዛሬም ቢሆን በክርስቲያኖች የሚፈጸመው እንዴት ነው? አንዳንድ መግለጫዎችን ስጥ።

4. የእግዚአብሔር ሕዝብ በንስሐ ስለማይመለስ እግዚአብሔር በሕዝቡና በከተማዋ ላይ ጥፋትን እንደሚያመጣ ተናግሯል (6፡11-13)። በትንቢተ ኢሳይያስ እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደሚቀጣ ተናግሯል። እስራኤል በሙሉ ተማርከው ወደ አሦር ተጋዙ። ኢሳይያስ፥ ይሁዳም ተማርካ ወደ ባቢሉን እንደምትሄድ ተናገረ። በኢሳይያስ የአገልግሎት ዘመን፥ ይህ የፍርድ ተስፋ ቃል አሦራውያን አብዛኛውን የይሁዳ ክፍል በመደምሰሳቸው ምክንያት በከፊል ተፈጽሟል። ሆኖም እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ታድጎአታል። 

5. እግዚአብሔር ይሁዳን የሚያጠፋው ሙሉ በሙሉ አልነበረም፤ ነገር ግን የቀረው ጉቶ «የተቀደሰ ዘር» ይሆናል (6፡13)። ይህ ሐረግ የሚገልጸው ኢሳይያስ ስለ ይሁዳ ቅሬታ የሚያስተምረውን ነገር ነው። አብዛኛው ሕዝብ ቢጠፋ ወይም በምርኮ ቢጓዝም፥ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ለእርሱ ታማኝ ሆነው የሚቀሩ «ቅሬታዎች» ይኖሩታል። እነዚህ ቅሬታዎች አንድ ቀን ወደ ይሁዳ ይመለሳሉ። እግዚአብሔር አንድ ቀን መንፈሱን የሚያፈስሰውና መንግሥቱንም የሚያመጣው በዚህ ቅሬታ ላይ ነው። በዚህ የኢሳይያስ ራእይ የተካተተው ሌላው ዐቢይ ትምህርት እግዚአብሔር በዘመናት መጨረሻ የሚያመጣው የዘላለም መንግሥት ነው። ትንቢተ ኢሳይያስ በብሉይ ኪዳን ከሚገኙ የትንቢት መጻሕፍት ሁሉ ይልቅ እግዚአብሔር ለዘላለም ስለሚነግሥበት ዘላለማዊ መንግሥት ይገልጻል። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የትንቢተ ኢሳይያስ አስተዋጽኦ

እንደ አብዛኛዎቹ የትንቢት መጻሕፍት ሁሉ የትንቢተ ኢሳይያስንም አስተዋጽኦ ማዘጋጀት አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም አብዛኛዎቹ የትንቢተ ኢሳይያስ ክፍሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ያላካተቱ ተከታታይ መልእክቶችና ትንቢተች ናቸው። ኢሳይያስ ከፍርድ መልእክት አጽናኝና ተስፋ ሰጭ ወደሆነ መልእክት፥ እንደገና ደግሞ ወደ ፍርድ መልእክት የሚመላለስ ይመስላል፡፡ ይህ ዑደት በመጽሐፉ ውስጥ በተደጋጋሚ ሲፈጸም የሚታይ ነው። ከዚህ ቀጥሉ ያለው ከመጽሐፉ አስተዋጽኦ ውስጥ አንዱ ሊሆን ይችላል።

የውይይት ጥያቄ፥ የሚከተለውን የትንቢተ ኢሳይያስ አስተዋጽኦ የመጽሐፉን ዋና ዋና ክፍሎችና በእያንዳንዱ ክፍል ውስጥ የሚገኙትን ዐበይት ትምህርቶች አጠቃላይ ገጽታ ለማግኘት በሚያስችል መንገድ አጥና።

ክፍል 1፡- በእስራኤል፥ በይሁዳና በአሕዛብ ሁሉ ላይ የመጣ የፍርድ መልእክት መጽሐፍ (ኢሳይያስ 1-39)

1. የትንቢተ ኢሳይያስ መግቢያ-እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ በሚደርሰው ነገርና በወደፊት ሁኔታቸው ሉዓላዊ ነው (ኢሳይያስ 1-6)፡-

ሀ. ይሁዳ ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገችውን ቃል ኪዳን በማፍረሷ እንደተወቀሰች (ኢሳይያስ 1)፥ 

ለ. እግዚአብሔር ወደፊት የሚመሠርተው መንግሥት (ኢሳይያስ 2፡1-5)። 

ሐ. እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ስለሚያመጣው ፍርድ (ኢሳይያስ 2፡6-4፡1)፥ 

መ. ስለ ይሁዳ የወደፊት ተሐድሶ (ኢሳይያስ 4፡2-6)፥ 

ሠ. እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ የሰጠው ፍርድና የሚመጣው ምርኮ (ኢሳይያስ 5)፥ 

ረ. የኢሳይያስ ራእይና ለነቢይነት መጠራቱ (ኢሳይያስ 6)። 

2. በአንድ ሕዝብ ላይ አገር አቀፍ የሆነ መከራና ችግር በሚደርስበት ጊዜ እግዚአብሔር ሉዓላዊ ነው-እስራኤልና ሶርያ ይሁዳን በወረሩበት ወቅት የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 7-12)፡-

ሀ. ይሁዳ በእስራኤልና በሶርያ እጅ እንደማትወድቅ በመግለጽ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 7)፡

ለ. ስለ ኢሳይያስ ወንድ ልጆችና የዳዊት ልጅ ስለሆነው ስለ መሢሑ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 8-9፡7)። 

ሐ. የእግዚአብሔር ፍርድ በእስራኤል ላይ (ኢሳይያስ 9፡8-10፡4)፥ 

መ. የእግዚአብሔር ፍርድ በአሦር ላይ (ኢሳይያስ 10፡5-34)።

ሠ. መሢሑና የወደፊት መንግሥቱ (ኢሳይያስ 11-12)።

3. እግዚአብሔር በሕዝቦች ሁሉ ላይ ሉዓላዊ ነው-በተለያዩ ሕዝቦች ላይ የተነገሩ ትንቢቶች (ኢሳይያስ 13-23)፡-

ሀ. በአሦር ላይ (ኢሳይያስ 13፡1-14፡27)፥ 

ለ. በፍልስጥኤም ላይ (ኢሳይያስ 14፡28-32)፥ 

ሐ. በሞዓብ ላይ (ኢሳይያስ 15-16)። 

መ. በደማስቆና በእስራኤል ላይ (ኢሳይያስ 17)፥ 

ሠ. በኢትዮጵያ ላይ (ኢሳይያስ 18)፥ 

ረ. በግብፅና በኢትዮጵያ ላይ (ኢሳይያስ 19-20)። 

ሰ. በባቢሎን ላይ (ኢሳይያስ 21፡1-10)። 

ሸ. በኤዶም ላይ (ኢሳይያስ 21፡11-12)። 

ቀ. በዐረብ ላይ (ኢሳይያስ 21፡13-17)። 

በ. በኢየሩሳሌም ላይ (ኢሳይያስ 22)፥ 

ተ. በጢሮስ ላይ (ኢሳይያስ 23)። 

4. እግዚአብሔር በይሁዳ ሕዝቡ ላይ ሉዓላዊ ነው-ስለ ፍርድና ስለሚመጣው መንግሥት የተተነበዩ የተስፋ ቃላት (ኢሳይያስ 24-27)። 

5. እግዚአብሔር በፍርድ ላይ ሉዓላዊ ነው-በእስራኤልና በአሦር ላይ የተነገሩ ስድስት የዋይታ ትንቢቶች (ኢሳይያስ 28-33)። 

6. እግዚአብሔር ሉዓላዊ ነው-የፍርድ መልእክቶችና የበረከት ተስፋዎች (ኢሳይያስ 34-35)። 

7. እግዚአብሔር በዓለም ላይ ባሉ ታላላቅ ኃያላን ላይ ሉዓላዊ ነው-እግዚአብሔር ነፃ እንደሚያወጣ የተነገረ ታሪክና ወደፊት ይሁዳ በባቢሎን እንደምትማረክ የተነገረ ትንቢት (ኢሳይያስ 36-39)። 

ክፍል 2፡- የማጽናናት መጽሐፍ (ኢሳይያስ 40-66) 

8. በአይሁድ ሕዝብ ነፃ መውጣትና መመለስ ላይ እግዚአብሔር ሉዓላዊ ነው (ኢሳይያስ 40-48)። 

9. አገልጋይን ወደ ሕዝቡ በመላክ እግዚአብሔር ሉዓላዊ ነው (ኢሳይያስ 49-57)።

10. በመጨረሻዎቹ ዘመናት ጉዳይ፥ ሕዝቡን ነፃ በማውጣት፥ በክፉዎችና በኃጢአተኞች ላይ በመፍረድና ሊመጣ ባለው ዘላለማዊ መንግሥት ጉዳይ እግዚአብሔር ሉዓላዊ ነው (ኢሳይያስ 58-66)

የውይይት ጥያቄ፥ ከላይ በተሰጠው አስተዋጽኦ ላይ የተንጸባረቁ ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚፈለጉባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ኢሳይያስ የኖረበት ዘመን ታሪካዊ ሥረ-መሥረት እና የነቢዪ ኢሳይያስ ሥረ-መሠረት

I. ኢሳይያስ የኖረበት ዘመን ታሪካዊ ሥረ-መሥረት፡-

የውይይት ጥያቄ፥ ኢሳይያስ 1፡1 እና 2ኛ ነገሥት 15-20 አንብብ። ሀ) ኢሳይያስ ባገለገለባቸው ዘመናት የነበሩትን ነገሥታት ስም ዘርዝር። ለ) የእነዚህ ነገሥታት ባሕርይ ምን ይመስል ነበር? ሐ) በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በእስራኤልና በይሁዳ የተከናወኑ ዋና ዋና ድርጊቶች ምን ነበሩ?

ነቢዪ ኢሳይያስ የኖረውና የሠራው ለብዙ ዓመታት ነበር። መቼ እንደተወለደ ባናውቅም እንኳ የነቢይነት አገልግሉቱን የጀመረው ንጉሥ ዖዝያን በሞተበት በ740 ዓ.ዓ. ይመስላል፤ የኖረውም እስከ 680 ዓ.ዓ. አካባቢ ይመስላል። ይህ ማለት በነቢይነት ያገለገለው ከ55 ዓመታት በላይ ነበረ ማለት ነው። ኢሳይያስ በዚህ ረጅም ዕድሜው በሕዝቡ መካከል የተካሄዱ የበርካታ ለውጦች ምስክር ነበር። ሕዝቡ በከፍተኛ ደረጃ እግዚአብሔርን የወደዱበትና ደግሞም በግልጽ በእግዚአብሔር ላይ ያመፁበትን ጊዜ ተመልክቷል። በሕዝብ መካከል ከፍተኛ ጥፋትና ደግሞም ከፍተኛ ብልጽግናና ሰላም የነበረበትን ወቅት ተመልክቷል። 

1. ዖዝያን፡- የዖዝያን ዘመነ መንግሥት የይሁዳ ሕዝብ ከዳዊትና ከሰሎሞን በኋላ ደርሶበት ወደማያውቀው ከፍተኛ ሥልጣን የደረሰበት ጊዜ ነበር። የግብፅና የአሦር መንግሥታት ደካሞች ስለነበሩ ይሁዳና እስራኤል ከውጭ መንግሥታት ተጽዕኖ ነፃ የሆኑበት ጊዜ ነበር፡፡ በሰሜን በኩል የእስራኤል መንግሥት በዳግማዊ ኢዮርብዓም አመራር ተከናውኖለት፥ ከይሁዳም ጋር በሰላም የሚኖርበት ጊዜ ነበር። በይሁዳ ሕዝብ መካከል ደግሞ መንፈሳዊ መነቃቃት የነበረበት ወቅት ነበር። ዖዝያን እግዚአብሔርን የሚፈራ ንጉሥ ስለነበረ ሕዝቡ እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ያበረታታ ነበር። ሕዝቡ ይህን ቢያደረጉም እንኳ ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸው ኅብረት ጥልቀት እንዳልነበረው ኢሳይያስ ያውቅ ነበር። ኢሳይያስ እርሱና ሕጉ በቅዱሱ በእግዚአብሔር ፊት ንጹሐን እንዳልነበሩ ባየው ራእይ ተገንዝቦአል። በዝያን ዘመነ መንግሥት መጨረሻ አካባቢ ነገሮች መለወጥ ጀመሩ። ዳግማዊ ኢዮርብዓም በ753 ዓ.ዓ. ሲሞት፣ በእስራኤል ዙፋን ላይ ለመቀመጥ ሽኩቻ ይካሄድ ነበር። እስራኤል በ722 ዓ.ዓ. ፈጽማ እስክትጠፋ ድረስ ሥልጣኗ ፈጥኖ እያሽቆለቆለ መሄድ ጀመረ። ዖዝያን በእግዚአብሔር ላይ በማመፁ በለምጽ ስለተመታ በ750 ዓ.ዓ. ዙፋኑን ለልጁ ለኢዮአታም ማስረከብ ነበረበት። 

ኢሳይያስ ያደገው በዖዝያን ዘመነ መንግሥት መጨረሻ አካባቢ ነበር፡፡ በ740 ዓ.ዓ. የሞተውን የታላቁን ንጉሥ የዖዝያንን ሞት ሲመሰክር ምናልባት ኢሳይያስ ወጣት ሳይሆን አይቀርም፤ ለነቢይነትም የተጠራው ዖዝያን በሞተበት ዓመት ነበር (ኢሳይያስ 6፡)። 

2. ኢዮአታም፡- የዖዝያን ልጅ የሆነው ኢዮአታም አብዛኛውን መንግሥቱን ያሳለፈው ከአባቱ ከዖዝያን ጋር ሲሆን፥ በኋለኛው መቶ ደግሞ ከልጁ ከአካዝ ጋር ነበር። በመሠረቱ ኢዮአታም የአባቱን የዖዝያንን መንገድ ቢከተልም፥ በዘመነ መግሥቱ መጨረሻ ገደማ ችግር ተጀመረ። በአሦር ሣልሳዊ ቴልጌልቴልፌሶር የተባለ ንጉሥ በ745 ዓ.ዓ. ሥልጣን ያዘ፤ መንግሥቱንም ወደ ምዕራብ ማስፋፋት ጀመረ። እስራኤልንና ይሁዳን በማጥቃት አሸነፋቸውና ነገሥታትን አስገበረ። የኢዮአታም ልጅ አካዝ በአቋሙ አሞራውያንን ይደግፍ ስለነበር ልጁ አካዝ አብሮት ይነግሥ ዘንድ ሕዝቡ ኢዮአታምን ግድ አሉት።

3. አካዝ፡- አካዝ በሥልጣን ላይ የነበረው ከ736-735 ዓ.ዓ. ነበር፤ እግዚአብሔርን አይፈራም ነበር፤ ይልቁንም የይሁዳን ሕዝብ ወደ ከፍተኛ ክፋት መራ። አካዝ ሥልጣን ላይ በተቈናጠጠ ጊዜ፥ ሕዝቡ ለአሦር መንግሥት ይገብር ነበር፤ ዳሩ ግን እስራኤልና ሶርያ በአሦር ላይ ለማመፅ ወስነው ነበር። በዚህ ዓመፅ የይሁዳ ሕዝብ እንዲተባበራቸው ፈለጉ፤ አካዝ ግን አሻፈረኝ አለ። በዚህ ምክንያት ሶርያና እስራኤል በይሁዳ ላይ ጥቃት ፈጸሙ። አካዝ እነዚህን አገሮች እንዳይፈራቸውና በእግዚአብሔር እንዲታመን ኢሳይያስ ቢነግረውም፥ መልእክት ወደ አሦር በመላክ እንድታድነው ጠየቀ። አሦር ሶርያን በማጥቃት በ732 ዓ.ዓ. ሙሉ ለሙሉ አጠፋቻት። የእስራኤልንም ምድር በአብዛኛው በመውሰድ መንግሥቱን አስገበረች፡፡ የአሦር ንጉሥ በሞተ ጊዜ ግን እስራኤል ከሌሉች ብዙ አሕዛብ ጋር በመሆን ለማመፅ ወሰነች። አሦር በ722 ዓ.ዓ. እስራኤልን በመደምሰስ አብዛኛውን ሕዝብ በምርኮ ወሰደች። ኢሳይያስ የእስራኤልን ጥፋት ያየው በከፍተኛ ኃዘን እንደነበር ጥርጥር የለውም። እስራኤል የእግዚአብሔር ሕዝብ አካል ቢሆኑም፥ ኃጢኣታቸው ጥፋትን አመጣባቸው። ኢሳይያስ ወደፊት ይሁዳም የሰሜኑ መንግሥት ያደረገውን ይህንኑ ኃጢአት በማድረግ ወደ ምርኮ እንደምትሄድ በተጨማሪ ያውቅ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለ ኃጢአታቸው ሲቀጣቸው ያየኸው በምን መንገድ ነው? ለ) ይህ ቅጣት እግዚአብሔርን በሚፈሩ ሰዎች ላይ ታላቅ ሥቃይ የሚያስከትለው እንዴት ነው? ሐ) እግዚአብሔር በኃጢአታቸው ምክንያት በራሱ ሕዝብ ላይ ፍርድን ሲያመጣ እርሱን የሚፈሩ ሰዎች ምላሽ ምን መሆን አለበት? 

አካዝ አሦር ባደረገችው ነገር በጣም ተደስቶ ነበር። የአምላካቸውን (የጣዖታቸው) ምስል ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ በማምጣት፥ ሕዝቡ የአሦራውያንን አምላክ እንዲያመልኩ አዘዘ። ሕዝቡ እውነተኛውን አምላክ እንዲያመልኩ አልፈቀደላቸውም። ኢሳይያስ ይህ ጉዳይ በእስራኤል ላይ ያመጣውን ዓይነት ፍርድ በይሁዳ ሕዝብም ላይ ሊያስከትል እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር። የትንቢተ ኢሳይያስ መጀመሪያ ክፍል አብዛኛው ምዕራፍ በአካዝ የክፋት ዘመነ መንግሥት የተጻፈ ነው ( ለምሳሌ፡- ኢሳይያስ 9)። 

4. ሕዝቅያስ፡- የአካዝ ልጅ ሕዝቅያስ እግዚአብሔርን የሚፈራና መንገዱን ከጌታ ጋር ያደረገ ንጉሥ ነበር። ኢሳይያስ ከሕዝቅያስ ጋር በቅርብ ሳይሠራ አልቀረም። እስራኤል ከወደቀችና ሕዝቅያስ ከነገሠ በኋላ ሕዝቡ በቤተ መቅደስ ውስጥ እውነተኛውን አምላክ ማምለክ እንዳለባቸው ወሰነ። በወደቀው የእስራኤል መንግሥትና በይሁዳ መንግሥት ይኖሩ የነበሩት ሕዝቦች ሁሉ እግዚአብሔርን በቤተ መቅደሱ ያመልኩ ዘንድ ጋበዘ። በይሁዳ መንግሥት ውስጥ በርካታ መንፈሳዊ ተሐድሶ ኣካሄደ። ይሁን እንጂ ከአሦር በኩል በይሁዳ ላይ እንደገና ችግር ተነሣ። ዳግማዊ ሳርጎን የተባለ አዲስ ንጉሥ (ከ722-705 ዓ.ዓ.) ሥልጣን ከያዘ በኋላ፥ ፍልስጥኤምንና (711 ዓ.ዓ.) በአሦር ላይ የተባበሩ ሌሎች ሕዝቦችን ሁሉ ወጋ። በዚህ ነገር እንዳይተባበር ኢሳይያስ ሕዝቅያስን አስጠንቅቆት ነበር። ኢሳይያስ ለሦስት ዓመታት እንደ ባሪያ ያለጫማ በመሄድና ቡቱቶ ለብሶ በመመላለስ ግብፅና ተባባሪዎችዋ እንዴት ለአሦር ባሪያዎች እንደሚሆኑ አሳይቷል። ሕዝቅያስ ለአሦር እንዲገብር ቢገደድም እንኳ ኢየሩሳሌም ጥቃት አልደረሰባትም። ሳርጎን በሞተ ጊዜ ግን ሕዝቅያስ የአሦርን የበላይ ጭቈና አሽቀንጥሮ ለመጣል ተፈተነ። የግብፅ ሕዝብ አሦርን ለመጣል የሚችል የኅብረ-ብሔር ጦር ለማቋቋም የሞከረው በዚህ ጊዜ ነበር። ኢሳይያስ፥ ሕዝቅያስን ወደዚህ ኅብረት በመግባት በግብፅ እንዳይታመን አስጠነቀቀው። ይልቁንም በእግዚአብሔር እንዲታመን አበረታታው። አሦር በሰናክሬም መሪነት ይሁዳን በመውጋት አብዛኛውን የይሁዳ ክፍል ደመሰሰ። ሆኖም ኢሳይያስ አስቀድሞ እንደተናገረው፥ እግዚአብሔር የአሦርን ጦር በመደምሰስ (በ701 ዓ.ዓ.) ኢየሩሳሌምን ከጥፋት ጠበቃት። 

5. ምናሴ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢሳይያስ አሟሟት ባይነግረንም እንኳ የአይሁድ አፈ-ታሪክ በምናሴ ዘመነ መንግሥት በመሥዋዕትነት መሞቱን ይናገራል። ምናሴ በአብዛኛው የሕይወት ዘመኑ እግዚአብሔርን እንደተወና የጣዖት አምልኮን ሥርዓት እንደገና ወደ ይሁዳ እንዳመጣ ታስታውሳለህ። ኢሳይያስ ይህን በሚመለከት እንደተቃወመው ጥርጥር የለውም። የአይሁድ አፈ ታሪክ እንደሚናገረው፥ ኢሳይያስ በአንድ ውስጠ ክፍት በሆነ የዛፍ ግንድ ውስጥ ከምናሴ በተሸሸገ ጊዜ፥ ምናሴ በመጋዝ ለሁለት እንደሰነጠቀው ይናገራል (ዕብራውያን 11፡37 ተመልከት።)

የውይይት ጥያቄ፥ ኢሳይያስ የኖረበትን ዘመን ፖለቲካዊና መንፈሳዊ ገጽታ በአንድ ዐረፍተ ነገር ግለጥ። (ኢሳይያስ ስለኖረበት ጊዜ ማወቅ አብዛኛውን ትንቢቶቹን ለመረዳት ይጠቅምሃል።)

እርግጠኛ ለመሆን ባንችልም እንኳ አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት፥ ትንቢተ ኢሳይያስ የተጻፈው ቀጥለው በተጠቀሱት ነገሥታት የግዛት ዘመን ቅደም ተከተል ነው፡-

1. ኢሳይያስ 1-6 የተጻፈው በዖዝያንና በኢዮአታም ዘመነ መንግሥት ነው (740-735) ዓ.ዓ.)፤ 

2. ኢሳይያስ 7-12 በአካዝ ዘመነ መንግሥት የተጻፈ ነው (735-715 ዓ.ዓ.) 

3. ኢሳይያስ 13-39 የተጻፈው ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት ከመነሣቱ በፊት፥ በሕዝቅያስ የመጀመሪያ ዘመነ-መንግሥት ነበር፤ (715-701 ዓ.ዓ.)፤ 

4. ኢሳይያስ 40-66 በሕዝቅያስ የኋለኛ ዘመነ መንግሥትና በምናሴ የመጀመሪያ ዘመነ መንግሥት የተጻፈ ነው (701-680 ዓ.ዓ.)።

II. የነቢዪ ኢሳይያስ ሥረ- መሠረት

የውይይት ጥያቄ፥ ኢሳይያስ የሚለውን ስም በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ተመልከትና ስለ ነቢዪ ኢሳይያስ የተጻፉ አንዳንድ እውነቶችን ጥቀስ።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢሳይያስ የግል ሕይወት የሚነግረን ብዙ ነገር የለም፤ ሆኖም ስለ እርሱ የሚከተሉትን መሠረታዊ እውነቶች እናውቃለን፡- 

1. ኢሳይያስ የአሞጽ ልጅ ነበር። የአይሁድ አፈ ታሪክ አሞጽ የንጉሥ ዖዝያን አባት የነበረው የንጉሥ አሜስያስ ወንድም ነው ይላል። ይህ ማለት ንጉሥ ዖዝያንና ኢሳይያስ የአጎት ልጆች ናቸው ማለት ነው፤ ስለዚህ ኢሳይያስ የዳዊት ንጉሣዊ ቤተሰብ አካል የነበረ፥ ብዙ መብትና ዕድል የነበረው ሰው ነው። ኢሳይያስ ለንጉሥ አካዝና ሕዝቅያስ በቀጥታ ይናገር የነበረበት ምክንያት ዘመዶቹ ስለነበሩ ይሆናል። ምናልባት በሃይማኖትም ሆነ በፖለቲካ ትምህርት የሠለጠነ ሰው ሳይሆን አይቀርም።

2. ኢሳይያስ እንደ እርሱ ነቢይት የሆነች ሴት አግብቶ ነበር (ኢሳይያስ 8፡3)። የኢሳይያስ ሚስት ነቢይት መሆኗን በሁለት የተለያዩ መንገዶች መገንዘብ እንችላለን፤ ይኸውም፡- አንድም ልክ እንደ ኢሳይያስ የእግዚአብሔርን ቃል በመናገር በእርግጥ የነቢይነትን ሥራ የምትሠራ ነበረች ማለት ሊሆን ይችላል፤ ወይም ነቢይ ስላገባች ነቢይት ተብላ ተጠርታ ሊሆን ይችላል። 

3. ለኢሳይያስ ቢያንስ ሁለት ልጆች እንደነበሩት እናውቃለን። እነዚህ ሁለት ልጆቹ የእርሱን የነቢይነት መልእክት የሚያንጸባርቁ ልዩ የሆኑ ስሞች ነበሯቸው። የአንዱ ልጅ ስም በዕብራይስጥ ማሃርሻላል-ሃሽ-ባዝ ሲሆን፥ ትርጕሙ «ምርኮ ፈጠነ፥ ብዝበዛ ቸኮለ» ማለት ነው። ይህ ስም እስራኤላውያን ከኃጢአታቸው ንስሐ ገብተው ካልተመለሱ እግዚአብሔር ለሚማርኩአቸው አሕዛብ አሳልፎ እንደሚሰጣቸው የሚናገር የማስጠንቀቂያ መልእክት ነበር (ኢሳይያስ 8:1-3)። የሁለተኛው ልጅ ስም በዕብራይስጥ ሸአር-ያሹብ ሲሆን ትርጕሙም «ቅሬታዎቹ ይመለሳሉ» ማለት ነው። ይህ ስም እስራኤላውያንን ለማጽናናትና ለማበረታታት የተሰጠ ስም ነበር። እግዚአብሔር እንደሚያስማርካቸው የተናገረ ቢሆንም፥ ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋቸው ግን ኣልነበረም። ሁልጊዜ ለእርሱ የሆኑ ቅሬታዎች ነበሩት፤ ስለዚህ አንድ ቀን እግዚአብሔር እነዚህን ቅሬታዎች በሕይወት ይኖሩ ዘንድ ወደ ይሁዳ ሊመልሳቸው ተስፋ ሰጠ (ኢሳይያስ 7፡3)።

አንዳንድ ምሁራን ኢሳይያስ ሌሎች ሁለት ተጨማሪ ልጆች ነበሩት ብለው ያምናሉ። የአንዱ ስም «አማኑኤል» ሲሆን የሌላኛው ስም ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም ይላሉ። [ኢሳይያስ 7፡14፤ 8፡8፥ 10፤ 9፡6]።

4. ኢሳይያስ አገልግሎት የሰጠው ብቻውን ሆኖ አልነበረም። ኢሳይያስ በሠራበት ዘመን ሆሴዕና አሞጽ በሰሜን እስራኤል ያገለግሉ ነበር። ሚክያስ ደግሞ በይሁዳ ገጠር ክፍል ያገለግል ነበር። የሚክያስና የኢሳይያስ መልእክቶች ምን ያህል ተመሳሳይ እንደሆኑ ማየት የሚያስደንቅ ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ መልእክቶቻቸው ፍጹም ተመሳሳይ ነበሩ (ለምሳሌ፡- ኢሳይያስ 2፡1-4ን ከሚክያስ 4፡1-3 ጋር አወዳድር)። መልእክቶቻቸው የተመሳሰሉት ኢሳይያስ ለይሁዳ መሪዎች የሰጠውን መልእክት ሚክያስ በገጠር ላሉ ሰዎች በድጋሚ ስለተናገረ ሳይሆን አይቀርም። 

5. ኢሳይያስ የተነበየው ስለ ሁለቱም ማለት ስለ ደቡቡና ሰሜኑ መንግሥታት ቢሆንም ዋናው መልእክቱ ስለ ይሁዳና እርሱ ስለኖረባት ስለ ኢየሩሳሌም ከተማ ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)