ሥላሴ ማለት ምን ማለት ነው?

ሥላሴ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም አንዳንዶችም፤ አንዳንዶችም ሥላሴ የሚለው ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ትምህርት የሚያስተምረንን ለመግለጥ በቂ አይደለም ይላሉ። እርግጥ ቀጥለን እንደምናየው ግማሹን ብቻ ነው የሚገልጥልን። ብዙ ሳንቆይ ምክንያቱን እንረዳለን። 

እርስዎ እንዲህ ዓይነቱን መጽሐፍ ሲያነቡ ጸሐፊው ወይም ቤተ ክርስቲያን፥ ወይም አንድ የሆነ ሰው “ትምህርቶቹ እነሆ ቀርበውልሀል እመንባቸው!” የሚል ይመስልዎ ይሆናል። እንዲያ የሚሰማዎ ከሆነ ትኩረትዎ በትምህርቱ ሂደት ላይ ሳይሆን፥ በሰውየው የጥናት ውጤት ላይ ሆኗል ማለት ነው። እኛ የምንለው፥ “ቢወዱም ባይወዱም ይህን ትምህርት ይቀበሉ” ሳይሆን “እውነቱ ይኸውና ቀርቦልዎታል፥ እንዴት አድርገው ያቀናጁታል?” የሚል ይሆናል። 

የሥላሴ ትምህርት ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። ምናልባት አንድ አምላክ በሦስት አካላት ውስጥ እንደሚኖር የሚገልጠውን የሥላሴ ትምህርት ብቻ ተምረው ይሆናል። ከዚያም አስረጂ ምሳሌዎችን ጠይቀው የሚያረካ መልስ አላገኙ ይሆናል። ስለዚህ ምንም ይሁን ምን ትምህርቱን ማመን አለብኝ ብለው ደምድመዋል እንበል። እንዲያ መሆን የለበትም፤ ልንከተለው የሚገባ አቅጣጫ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ፥ የሚያጋጥሙንን እውነቶች በጥልቀት መመልከት ነው። መጽሐፉ በተለይ አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ በግልጥ ይናገራል። እንዲሁም በእኩል ግልጥነት ደረጃ ኢየሱስ ክርስቶስ የተባለ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር እኩል እንደሆነ መናገሩንና፥ ሌላውም አካል መንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል እንደሆነ ተመልክተናል። ታዲያ እነዚህን እውነቶች እንዴት ያዋህዷቸዋል? ሃይማኖታዊ ወግ አጥባቂዎች እነዚህን እውነቶች አንድ ላይ ያስማሙበት መንገድ፥ የሥላሴን ትምህርት አስገኘ። ሌሎቹም እነዚህን እውነቶች አያይዘው ሌላ መንገድ በመከተል ስለ ሥላሴ የተለየ አሳብ ሰነዘሩ (እያንዳንዱ አካል የራሱ የሆነ የግል ማንነት ያለው ሳይሆን፥ እግዚአብሔር መለኮታዊነቱን የሚገልጥበት የተለያየ መልክ ነው የሚል)፤ ሌሎችም ኢየሱስና መንፈስ ቅዱስ አምላክ ናቸው የሚለውን የሥላሴ ትምህርት አንቀበልም አሉ። እነዚህ “ዩኒተሪያን” [Unitarian] በሚል ስያሜ ይጠራሉ። ነገር ግን የሥላሴ እውነትነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገባ ተገልጧል። በዚህ ክፍል ይህን አሳብ እናጠናለን። 

ማንኛውም የሥላሴ ትምህርት በጥንቃቄ መመዘን አለበት። ምክንያቱም ትምህርቱ በአንድ በኩል የእግዚአብሔርን አንድነት የሚያረጋግጥ ሲሆን፥ በሌላው ደግሞ በመለኮት አንድ የሆኑ ሦስት ፍጹማን አካላት እንዳሉ የሚያስረዳ ነው። ሥላሴ የሚለውን ቃል ብቻውን ወስደን ከተመለከትን ግን የሚያስተላልፍልን የትምህርቱን ግማሽ ብቻ ይሆናል። ስለዚህ ይህ ቃል ሦስትነት እንጂ አንድነትን ስለማያሳይ ምናልባት “ሥሉስ አሐዱ” በሚል ሌላ ቃል ቢተካ፣ ሦስትነትንና (ሥሉስ) አንድነትን (አሐዱ) ስለሚገልጥ የተሻለ ሊሆን ይችላል። 

ለአንድነቱ ማስረጃ 

ዘዳግም 6፡4 በብዙ መንገድ ሊተረጎም ይችላል (ለምሳሌ “ያህዌ አምላካችን አንድ ያህዌ ነው” ወይም “ያህዌ አምላካችን ነው፥ ያህዌ ብቻ ነው”፤ ይህ በማንኛውም መንገድ የአምላክን አንድነት እጠንክሮ ያውጃል። ዘዳግም 4፡35ና 32፡39 እንዲሁም ኢሳይያስ 45፡14 እና 46፡9 ይህንኑ ያስረዳሉ። ከአሥርቱ ቃላት የመጀመሪያው ትእዛዝ እስራኤል ሊያመልከው የሚገባ አንድ እውነተኛ አምላክ ብቻ መኖሩን ያሳያል (ዘጸ. 20፡3፤ ዘዳግ 5፡7)። በአዲስ ኪዳንም በ1ኛ ቆሮንቶስ 8፡4-6፤ ኤፌ. 4፡3-6 እና ያዕ. 2፡19 ያሉት ክፍሎች ሁሉ በጥብቅ የሚገልጡት አንድና እውነተኛ አምላክ እንዳለ ነው። ስለዚህ የሥላሴ ትምህርት ስንል ሦስት አምላኮች እንዳሉ ለመግለጥ አለመሆኑ በግልጥ ሊታወቅ ይገባል። እግዚአብሔር ልዩና ብቻውን ያለ ነው፤ ሌላ ተወዳዳሪ ስለማይኖረው፥ በምንም እኳኋን ሦስት አምላክ ነው የሚል ፍንጭ አናገኝም። 

ለሦስትነቱ ማስረጃ 

አዲስ ኪዳን በየትም ቦታ ስለ “አሐዱ ሥሉስ” ትምህርት በግልጥ አያስረዳም፤ ለምን ቢባል ስለዚህ ጉዳይ የሚያነሳው 1ኛ ዮሐ. 5፡7 ከመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት አንዱ ነው ተብሎ እምብዛም ስለማይታመን ነው። ይሁን እንጂ አሳቡን የሚያረጋግጡ አያሌ ማስረጃዎች እናገኛለን። 

(1.) አብ እንደ አምላክ ተገልጧል። ከብዙዎቹ ጥቅሶች መካከል ለማስረጃ በተለይ ዮሐንስ 6፡27 እና 1ኛ ጴጥሮስ 1፡2ን ይመልከቱ። ይህ ብዙ ጊዜ የማያከራክር ነጥብ ነው። 

(2.) የኢየሱስ አምላክነት ታውቋል። ተጠራጣሪው ተማሪም ይሆን ይመሰክራል (ዮሐ. 20፡28)፥ ኢየሱስ ራሱም አምላክ ብቻ ሊኖረው የሚችል ባሕርያት እንዳሉት ገልጧል፥ ለምሳሌ ሁሉን ማወቅ (ማቴ. 9፡4) ሁሉን ቻይነት (ማቴ. 28፡18)፥ በሁሉ ቦታ መሆን (ማቴ. 28፡20)። በተጨማሪም አምላክ ብቻ ሊያደርገው የሚችለውን ተአምር ፈጽሟል (ሰዎችም ይህን ተረድተዋል) (ማር. 2፡1-12)። ሽባውን በፈወሰበት ወቅት ኃጢአትን ይቅር ለማለት ሥልጣን እንዳለው አረጋግጧል። ይህ አምላክ ብቻ የሚችለው ተግባር ነው ተብሎ ይታመን ነበር። 

(3.) መንፈስ ቅዱስ እንደ አምላክ ተገልጧል። ስለ አምላክነቱም ሲመሰከርለት (ሐዋ. 5፡3-4) ለመንፈስ መዋሸት ለአምላክ የመዋሸትን ያህል ነው ተብሏል። የአምላክ ብቻ የሆነና፥ በአምላክ ያለ ባሕርይ አለው (ሁሉን ማወቅ፥ 1ኛ ቆሮ. 2፡10፤ በሁሉም ስፍራ መገኘት፥ መዝ. 139፡7)። ሰውን ለዳግም ልደት የሚያበቃ መንፈስ ነው (ዮሐ. 3፡5-6፥ 8)። 

ይህ የአዲስ ኪዳን ማስረጃ በጣም ግልጥና ጥርት ያለ ነው። ግን በብሉይ ኪዳን እንዲህ ዓይነቱ ማስረጃ ይኖራልን? መልሱ የለም ነው። ብሉይ ኪዳን ስለ ሥላሴ የሚገልጠው በተዘዋዋሪ ነው። እንዲያ ባይሆንም፥ ብሉይ ኪዳን በአዲስ ኪዳን ለሚገለጠው እውነት መነሻ ነበር ማለት ይቻላል። በብዙ ቁጥር የተገለጠውን ኤሎሂምን የመሰለ የአምላክ ስምና ሌሎቹም ይህን የኋላ መገለጥ ይጠቁማሉ (ዘፍጥ. 1፡1፥26)። የያህዌ መልአክ እንደ እግዚአብሔር ተቆጥሯል። ይሁን እንጂ፥ ከእግዚአብሔር የተለየ ነው (ዘፍጥ. 22፡15-16)። ይህ ሁኔታ ሁለት እኩል አካላትን ያመለክታል። መሢሁ ኃያል አምላክ ተብሉ ተጠርቷል (ኢሳ. 9፡6)። እንዲሁም ዘላለማዊነት እንደተሰጠው ሚክ. 5፡2ን ይመልከቱ። ምናልባት ኢሳይያስ 48፡16 ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ስለ ሥላሴ የሚናገር የብሉይ ኪዳን ክፍል ነው። ምክንያቱም “እኔ” አምላክህ የሚለው ቃል እግዚአብሔርንና መንፈስ ቅዱስን ለመግለጥ በእኩልነት ጥቅም ላይ ውሏል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ እንደ አዲስ ኪዳን ማስረጃዎች ቀጥታና ግልጥ በሆነ መንገድ የቀረቡ አይደሉም። 

የአሐዱ-ሥሉስነት ማስረጃ 

ከሁሉም በላይ ስለ አንድነትና ስለ ሦስትነት በሚዛናዊነት የሚያስረዳን በማቴዎስ 28፡19 ላይ የተጻፈው ቃል ነው። “በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁዋቸው” የሚለው፥ አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ስለተጠቀሱ ስለ ሥላሴ “ሦስትነት” ምንም ጥያቄ አያስነሳም። አንድነቱን ደግሞ “ስሞች” ሳይሆን “ስም” ብሎ በመጥቀስ ያሳየናል፡፡ በዚህ አኳኋን ሥላሴዎችን በእኩልነትና በሦስትነት የሚገልጡ ሌሎችም ጥቅሶች አሉ በ2ኛ ቆሮንቶስ 13፡14 እንደሚገኘው ቡራኬ እና በማቴዎስ 3፡16-17 በኢየሱስ ጥምቀት የሥላሴዎች መገኘት)። ይሁን እንጂ ጥቅሶቹ “ስም” ተብሎ በማቴዎስ 28፡19 እንደተጠቀሰው ያህል የሥላሴዎችን አንድነት አጉልተው አያሳዩም። 

እነዚህን ማስረጃዎች በመመልከት አንድ አምላክ፥ ሦስት አካላት የሚለውን እንዴት አድርገን በምንረዳው መንገድ መተርጎም እንችላለን? ዋርፊልድ [Warfeld] የተባለ ጸሐፊ ስለ ሥላሴዎች ሲያብራራ “እንድና እውነተኛ አምላክ ብቻ መኖሩ፥ ይህም አንድ አምላክ ሦስት እኩል አካላት፥ በመለኮት አንድ የሆኑ፥ በአካል ግን የተለዩ” በማለት ገልጧል። አካል የሚለው ቃል በእርግጥ ትክክለኛ ገላጭ አይደለም። ምክንያቱም ለኛ የመረዳት ችሎታ ሦስት የተለያዩ አካላትን ስለሚያመላክት ነው። መቼም ቢሆን ቃላት እግዚአብሔርን በትክክል ሊገልጡት አይችሉም። ታዲያ ከዚህ በላይ ለማብራራት ምን አማራጭ እንጠቀም? 

ሥላሴን በምላሴ ማስረዳት ይቻላል? ትክክለኛ ሆኖ ለማስረዳት ወይም በጥሩ ሁኔታ አብራርቶ ለመግለጥ እጅግ ያዳግታል። ምክንያቱም ሦስቱ አካላት የአንዱን መለኮት ባሕርያት በእኩልነትና በጋራ የመካፈላቸውን ምስጢር ማብራራት በጣም ስለሚከብድ ነው። ለማንኛውም እስቲ አንድ ከሳይኮሎጂ የተወሰደ ምሳሌ እንመልከት፤ የሰው ውስጣዊ መንፈስ አካል የሆነችው ነፍስ ውሳኔ የሚያሻው ነገር ሲገጥማት፥ በቅድሚያ ከራሷ ጋር ክርክር ትገጥማለች የክርክር ነጥቦቹን ታመዛዝናለች። በመጨረሻም የመሰላትን ፍርድ ትሰጣለች። ሌላው ምሳሌ፥ ፀሐይን እንደ አብ በመመሰል ይቀርብና ሆኖም ለማየት የምንችለው ፀሐይን ሳይሆን፥ የፀሐይን ብርሃን ብቻ መሆኑን ይገልጣል (ወደ ምድር የመጣው ብርሃን ወልድ እንደሆነ ለማሳየት ነው)። አትክልቶች እንዲያድጉ የሚረዳውን የፀሐይን ኬሚካላዊ ኃይል ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ ይመስለዋል፡፡ እንግዲህ ይህ የፀሐይ፣ የብርሃንና የኃይል ምሳሌ ምናልባት የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት ለማስረዳት በምሳሌነት ይጠቅም ይሆናል። 

እንዲህ ዓይነቱ አስቸጋሪ ትምህርት፥ በቤተ ክርስቲያን ታሪከ ለብዙ ስሕተት መንስዔ መሆኑ እምብዛም አያስደንቅም። አንድ ተደጋግሞ የተከሰተ ስሕተት፥ መንፈስ ቅዱስን ተጽዕኖ እንደሚያደርግ ኃይል እንጂ፥ ሕያውና አካል ያለው አምላክ መሆኑን አለመቀበል ነው። አንዳንዶቹም ክርስቶስን ከአብ አሳንሰው ተመልክተውታል። እንዲያውም ፍጡር ነው የሚሉ አሉ፥ (ሞናርኪያኒዝም» [Monarchianism] የአርዮስ ትምህርት [Arianism ኤሪያኒዝም] እንዲሁም የዘመኑ ዩኒተሪያኒዝም” [Unitarianism])። ሥላሴን በተመለከተ የሚያጋጥመን ሌላ ስሕተት ሥላሴ የሚለው ቃል እግዚአብሔር በተለያዩ መንገዶች እራሱን መግለጡን ያመለክታል የሚለው ሰባሊዮስ በ250 ዓ.ም. የመሠረተው ትምህርት [Sabellianism/ሰቤሊያኒዝም]፥ ወይም “ሞዳሊዝም” [Modalism) ነው። ካርል ባርት የተባለው ፈላስፋ ምንም እንኳ ምዳሊስት መሆኑን ቢክድ ዝንባሌው ግን ሞዳሊስት መሆኑን ይጠቁማል። 

ለመሆኑ ይህ የሥላሴ ትምህርት ጠቃሚ ነውን? ካልሆስ የደኅንነታችን መሥዋዕት የሆነው ክርስቶስ እንዴት ከሥላሴዎች ውጭ ተገኘ ለማለት እንችላለን? ዩኒተሪያኖች አምላክ ሰው ሆነ፥ በዚህ ዓለም ኖረ፥ ሞተ፥ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፥ የሚለውን እውነት ማመን ይከብዳቸዋል። አምላክ፥ አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ መሆኑ፥ እግዚአብሔር የፍቅርና የኅብረት አምላክ መሆኑ እርግጥ ነው። እኛም አማኞች ኅብረት ያለን ከዚህ ዓይነቱ አምላክ ጋር ነው። 

እግዚአብሔር አብ 

ስለ ወልድና ስለ መንፈስ ቅዱስ በኋላ በስፋትና በጥልቀት እንመለከታለን፤ አሁን ስለ አብ ሥራና ግንኙነት በመጠኑም ቢሆን ማብራሪያ እንስጥበት። 

የአብ ልዩ ግንኙነቶች 

(1.) ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ተጠርተዋል (ሐዋ. 17፡29)፤ ስለዚህ እግዚአብሐር በፈጣሪነቱ የሰዎች ሁሉ አባት የሆነበት ግንኙነት አለ ማለት ነው። ይህ ግንኙነት የፍጡርና የፈጣሪ ግንኙነት እንጂ መንፈሳዊ አይደለም። 

(2.) እግዚአብሔር የእስራኤል መንግሥት አባት ነው (ዘጸ. 4፡22)። በእስራኤል የነበሩ ሁሉ ስላልዳኑ ይህ ግንኙነት መንፈሳዊም (ላመኑትና) አስተዳደራዊም (ለሁሉም እስራኤላውያን ቢያምኑም ባያምኑም) ነው። 

(3.) እግዚአብሔር የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አባት ነው (ማቴ. 3፡17)። 

(4.) እግዚአብሔር ልዩ በሆነ መንገድ በክርስቶስ ላመኑት ሁሉ አባት ነው (ገላ. 3፡26)። 

የአብ ልዩሥራዎች 

እግዚአብሔር አብ የሚፈጽማቸው ሥራዎች ሁሉ አንድ ወይም በሌላ መንገድ ሌሉችን የሥላሴ አካላት ይጨምራሉ። ስለዚህ የአብን ሥራ ስንናገር ሴሎቹን አካላት ማግለላችን አይደለም ፤ ከአብ ጋር በልዩ ሁኔታ የሚገናኙትን ሥራዎች ለመጥቀስ እንጂ። 

(1.) የአምላክ ዕቅድ አውጪና ትእዛዝ ሰጪ አብ ነው (መዝ. 2፡7-9)። 

(2.) አብ የምርጫን ሥራ አድራጊ ነው (ኤፌ. 1፡3-6)። 

(3.) አብ ወልድን ወደዚህ ዓለም ላከው (ዮሐ. 5፡37)። 

(4.) አብ ልጆቹን ይቀጣል (ዕብ. 12፡9)። 

የእግዚአብሔር ትምህርት ጠቃሚ ውጤቶች ሁለት የማጠቃለያ አሳቦች 

(1.) እስካሁን ከገለጥነው እግዚአብሔር ሌላ አምላክ የለም። ራሳችን የፈጠርነው ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆነ አምላክ የውሸት አምላክ ነው። አንዳንድ ጊዜ ጥሩ ክርስቲያን እንኳን በራሱ አሳብና ፍላጐት፥ ደስ እንዳለው አምላክን ለመቅረፅ ከሚገፋፋ ወጥመድ ውስጥ ይገባል። ውጤቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ከሚታወቀው እውነተኛ እግዚአብሔር የተለየ አምላክ መፍጠር ይሆናል። ስለ እግዚአብሔር ያወቅነው፥ እውቀት ስላለን ወይም አሳብ የማፍለቅ ችሎታችን ከፍተኛ ስለሆነ ሳይሆን፥ እርሱ ራሱን ስለሚገልጥልን ነው። ስለዚህ የምናውቀው ሁሉ፥ ክእርሱ መገለጥ የመጣ እንጂ፥ ከእምሯችን የመነጨ አይደለም። አምላክ እንዳንፈጥር እንጠንቀቅ። 

(2.) እውነተኛው አምላክ እራሱን እንደገለጠ፥ ተአምራትን እንደሚያደርግ፥ እስትንፋሱ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሰጠን፥ ሥጋንም እንደለበሰና ከዓለም መንግሥታት ሁሉ በላይ እንደሆነ ማመን ሊከብደን አይችልም። በሌላ አነጋገር ስለ እውነተኛ አምላክ የተገለጠውን እውነት ሁሉ ከተቀበልን፥ ስለ እርሱ የተጠቀሰውን ሁሉ ለማድረግ እንደሚቻለው ማመንም አስቸጋሪ አይሆንብንም። ለዚህ ነው በዚህ ትምህርታችን እግዚአብሔርን ለማወቅ ትምህርት ቅድሚያ የሰጠነው። 

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

2 thoughts on “ሥላሴ ማለት ምን ማለት ነው?”

  1. ለምላሹ ከዚህ በታች ያሉትን ጽሑፎች እንድታነብ ጋብዘንሃል፡፡

   እግዚአብሔር ወልድ፡- መለኮታዊነቱና ዘላለማዊነቱ https://ethiopiansite.com/2021/03/04/%e1%8a%a5%e1%8c%8d%e1%8b%9a%e1%8a%a0%e1%89%a5%e1%88%94%e1%88%ad-%e1%8b%88%e1%88%8d%e1%8b%b5%e1%8d%a1-%e1%88%98%e1%88%88%e1%8a%ae%e1%89%b3%e1%8b%8a%e1%8a%90%e1%89%b1%e1%8a%93-%e1%8b%98%e1%88%8b/

   እግዚአብሔር ወልድ፡- ተሠግዎቱ
   https://ethiopiansite.com/2021/03/04/%e1%8a%a5%e1%8c%8d%e1%8b%9a%e1%8a%a0%e1%89%a5%e1%88%94%e1%88%ad-%e1%8b%88%e1%88%8d%e1%8b%b5%e1%8d%a1-%e1%88%a0%e1%8c%8d%e1%8b%8e%e1%89%b1/

Leave a Reply

%d bloggers like this: