እግዚአብሔር ራሱን ማን ብሎ ይጠራል?

የአንድ ሰው ስም ስለ ሰውዬው ማንነት ወይም ስሙን ከሚጠቀሙበት ሰዎች ጋር ያለውን ዝምድና ያመለክታል። ብዙ ጊዜ፥ ስም ሰዎች ካላቸው ልምድ ይወጣል። በእግዚአብሔርም ዘንድ እንዲሁ ነው። ስለ ባሕሪው ምንነት የገለጠው ከሰዎች ጋር በተግባባቸው ስሞቹ ሲሆን አንዳንዶቹ ስሞች ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር በግል ከነበራቸው ግንኙነት በመነሳት የወጡ ናቸው። 

የመጀመሪያዎቹ የብሉይ ኪዳን ስሞች 

(1) ኤሎሂም። በጣም አጠቃላይ በሆነ መልኩ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የምናገኘው የእግዚአብሔር ስም ኤሎሂም ነው። እንዴት እንደመጣ ባይታወቅም “ኃያሉ” ማለት ይሆናል። ይህ ስም ለእውነተኛው አምላክ ብቻ ሳይሆን፥ ለአሕዛብ አማልክት ጭምር በመጠሪያነት አገልግሏል (ዘፍጥ. 31፡30፤ ዘጸ. 12፡12)። በቃሉ መጨረሻ ያለውና “ሂም” የሚለው ቃል በሰዋስው ሥርዓት የብዙ ቁጥር የሚያመለክት ሲሆን፥ ፍቺውን በሚመሰክት ግን የተለያዩ ግምቶች ተሰጥተዋል። አባባሉን ለመቀበል ቢያስቸግርም፥ አንዳንዶች፥ ስሙ ብዙ አምላኮችን [Polytheism/ታሊቲይዝም] ያመለክታል ይላሉ። አባባሉ የማይደገፍበት ምክንያት እግዚአብሔር አንድ መሆኑ በግልጥ ስለተመለከተ ነው (ዘዳግ. 6፡4)። አንዳንዶች ከሰው የብዙ ቁጥር መሆን በመነሳት ስለ ሥላሴ የሚያስረዳ ቃል እንደሆነ አድርገው ለመግለጥ ሞክረዋል። ምንም እንኳን የሥላሴ ትምህርት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቢሆን፥ በዚህ የእግዚአብሔር ስም መሠረትነት ግን ትክክል ነው ብሎ ለመቀበል ያስቸግራል። ይሁን እንጂ “ኤሎሂም” የሚለው የብዙ ቁጥር ሰም በእግዚአብሔር አካል ውስጥ ጥቂት ልዩነት መኖሩን አያስረዳም ማለት አይደለም። ይህ በብዙ ቁጥር የተነገረ ቃል፥ በአዲስ ኪዳን የተገለጠውን ሥላሴ ማንነት ቢያሳይም፥ በግልጥ የሚያመለከተው ግን የኃይሉን ሙላት እንደሆ መረዳት ያሻል። ኤሎሂም ኃያሉ የዓለማትና የሰው ዘር ገዥ ነው። ይህ ስም በብሉይ ኪዳን 2500 ጊዜ ተጠቅሷል። ዘፍጥረት 1፡1 የመሳሰሉትን ጥቅሶች በማንበብ ከሚገጥምዎ ችግር ሁሉ የሚታደግዎ እግዚአብሔር አምላክዎ እርሱ እንደሆነ ይረዱ። 

2.) ያህዌ። (በእንግሊዝኛ “ጀሆቫ” [Jehovah] ተብሎ የሚጠራ ሲሆን አንዳንድ ጊዜም በአማርኛ በስሕተት “የሆዋ” ይባላል።) ይህ በብሉይ ኪዳን ሌላው የእግዚአብሔር የተለየ ስም ነው። እዚህ ላይ የዚህን ስያሚ ጠቅላላ ታሪክ ለመናገር ጊዜ አይኖረንም። ሆኖም አይሁዳዊያኑ “ያህዌ” Yahweh) የሚለውን ስም ለመጥራት እጅግ ይፈሩ ስለነበር፥ ቃሉ ባጋጠማቸው ቁጥር “አዶናይ” በማለት ለውጠው ያነሱት እንደነበር በመጥቀስ ማለፍ ይቻላል። 

የቃሉም ትርጉም እጅግ ያከራክራል። ቃሉ “መሆን” ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር የተያያዘና ስለ እግዚአብሔር ዘላለማዊነት የሚያስረዳ ነው የሚል ስምምነት ያለ ይመስላል (ዘጸ. 3፡14)። ይሁን እንጂ በዘጸአት 6፡6 ላይ በተገለጠው አሳብ፥ ስሙ ልዩ በሆነ መንገድ እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ከቤዠበት ኃይሉ ጋር ተዛምዶ ይገኛል። ቀደም ሲል እንደተገለጠው አንድ ስም አብዛኛውን ጊዜ ስለ ባለስሙ ማንነትና ከሌሎች ጋር ስላለው ዝምድና እንደሚያመለክት አይተናል። ያህዌ በሚለው ስምም እነዚሁ ሁለት ነገሮች ጎልተው ይታያሉ፡፡የያህዌ ዘላለማዊነትና ለእስራኤል ቤዛ መሆን በዚህ ስም ታቅፏል። ይህ ስም በብሉይ ኪዳን 7000 ጊዜ ሲጠቀስ፥ በተለይ ከያህዌ ቅድስና ጋር በተዛመደ፥ (ዘሌዋ. 11፡44-45)፥ ኃጢአትን ስለመጥላቱ (ዘፍጥ. 6፡3-7)። በጸጋው ስላዘጋጀልን አዳኝነቱ፥ (ኢሳ. 53፡1፥ 5-6፥ 10) ውስጥ ተጠቅሷል። 

(3.) አዶናይ። ይህ ስም አይሁዳውያን መጽሐፍ ሲያነቡ ባለ አራቱን ፈደል የእግዚአብሔር ስም (ያህዌህ) የተኩበት ነው። ትርጉሙ ጌታ ማለት ነው። ማንም ሊገምተው እንደሚችል፥ ቃሉ በሰዎች መካከል ያለውን የግንኙነት ዓይነት ለማመልከት (በዘጸአት 21፡1-6 የተጠቀሰው የጌታና ባሪያ ግንኙነት) ጥቅም ላይ ውሏል። ስለዚህ ስሙ እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ ሲጠቀስ፥ የርእሱን ፍጹም ባለሥልጣንነት ያንፀባርቃል። በኢያሱ 5፡14 ላይ የተጠቀሰውንና (ኢያሱ የእግዚአብሔርን ሠራዊት አለቃ አይቶ ሥልጣኑን እንደተረዳ)፥ እንዲሁም በኢሳይያስ 6፡8-11 (ኢሳይያስ ከጌታው አደራ እንደተቀበለ) የሚገልጡትን ጥቅሶች እዚህ ላይ ልብ ብለው ያጢኑ። 

የጌታና የባሪያ ግንኙነት ሁለት ጐኖች አሉት። በአንድ በኩል ባሪያው ለጌታው ሙሉ ታዛዥነትን ሲያሳይ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጌታው የባሪያውን ደኅንነት ይንከባከባል። አማኝም እግዚአብሔርን ከልቡ ጌታ ብሎ ከጠራ፥ አስፈላጊው ጥንቃቄ ይደረግለታል። እግዚአብሔርም በተራው አማኙ በማንኛውም ነገር እንዲታዘዘው ይሻል። 

ጥምር የብሉይ ኪዳን ስሞች 

በብሉይ ኪዳን ውስጥ ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ ወይም ሥራ የሚገልጡት “ያህዌ” ወይም “ኤል” የሚሉት ቃላት አብዛኛውን ጊዜ ከሌሎች ስሞች ጋር ተጣምረው ይገኛሉ። ለምሳሌ፡- 

(1.) ኤል-ኤልይን፡- “ልዑል” (ዘፍጥ. 14፡22)። ዲያብሎስ በልዑል እመሰላለሁ ብሉ የተመኘውን ከዚህ ጋር በማገናዘብ ያስተውሉ (ኢሳ. 14፡14)። 

(2.) ኤልኦላም፡- “የዘላለም አምላክ” (ዘፍጥ. 21፡33)። የእግዚአብሔርን ፍጻሜ የለሽ ኃይል ለመግለጥ የተጠቀመበትንም ያስተውሉ (ኢሳ. 40፡28)። 

(3.) ኤልሻዳይ፡- “ሁሉን ቻይ (አድራጊ) አምላክ” (ዘፍጥ. 17፡1)። ይህ ቃል ምናልባት “ተራራ” ከሚለው ቃል የመጣ ሊሆን ይችላል። የሚያሳየንም በተራራ ላይ የቆመው እግዚአብሔር ኃያልና ሁሉን ገዥ መሆንን ነው። ይህ ስም አብዛኛውን ጊዜ ሕዝቡን በቀጣበት ወቅት፥ ለምሳሌ፡- በመጽሐፈ ሩት 1፡20-21፥ በመጽሐፈ ኢዮብም ሰላሳ አንድ ጊዜ ተጠቅሷል። 

(4.) ያህዌ ይርኢ፡- እግዚአብሔር ያዘጋጃል (ዘፍጥ. 22፡14)። ይህ ቃል በዚህ ጥቅስ ብቻ ነው የተገለጠው። የእግዚአብሔር መልአክ በይስሐቅ ፋንታ በግ ካዘጋጀ በኋላ አብርሃም የዚያን ቦታ ስም “እግዚአብሔር ያዘጋጃል” ብሎ ጠራው። 

(5.) ያህዌ ንሲ፡- እግዚአብሐር ሰንደቅ ዓላማዬ ነው (ዘጸ. 17፡15)። አማሌቃውያን ከተሸነፉ በኋላ ሙሴ መሠዊያ ሠርቶ ያህዌ ንሲ ብሎ ጠርቷል። እርግጥ እነዚህ ጥንድ ቃላት የእግዚአብሔር ስሞች ባይሆኑም ሊታወሱ በሚገባ ሁኔታ የተሰየሙ ናቸው። 

(6.) ያህዌ ሻሎም፡- እግዚአብሔር ሰላም ነው (መሳ. 6፡24)። 

(7.) ያህዌ ሳቦት፡- “የሠራዊት ጌታ” (1ኛ ሳሙ. 1፡3)። ሠራዊቱ ትእዛዙን ለመፈጸም የተዘጋጁ የሰማይ መላእክት ናቸው። ይህ ስም በአብዛኛው (ሕዝቡ ተስፋ በቆረጡ ጊዜ ያህዌ አሁንም ጠባቂያቸው እንደሆነ ለማስገንዘብ) ነቢያቱ (ኢሳይያስና ኤርምያስ) ተጠቅመውበታል። 

(8.) ያህዌ መክደሸከም፡- የሚቀድሰህ እግዚአብሔር (ዘጸ. 31፡13)። 

(9.) ያህዌ ሮይ፡- “እግዚአብሔር እረኛዬ” (መዝ. 23፡1)። 

(10.) ያህዌ ጽድቁኒ፡- እግዚአብሔር ጽድቃችን (ኤር. 23፡6)። ይህ ስም ጻድቅ ባልሆነው ንጉሥ ሴዴቅያስ ላይ ለዘለፋ የተሰነዘረ ሲሆን፥ (የስሙ ትርጓሜ ያህዌ ጽድቅ ነው የሚል ነው) (2ኛ ዜና 36፡12-13)። 

(11.) ያህዌ ሻማህ፡- “እግዚአብሔር በዚያ አለ” (ሕዝ. 48፡35)። 

(12.) ያህዌ ኤሎሂም እስራኤል፡- “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር” (መሳ. 5፡3)። የአብርሃም፥ የይስሐቅ፥ የያዕቆብ አምላክ እንደማለት ሲሆን ይህን ስም ብዙ ጊዜ ነቢያት ተጠቅመውበታል (ኢሳ. 17፡6)። 

(13.) ኳዶሽ እስራኤል፡- “የእስራኤል ቅዱስ” (ኢሳ. 1፡4)። 

እነዚህ ስሞች ልዩ ሳይሆን እንደ ማዕረግ ስም ናቸው። ይህ ዝርዝር ሊቀጥል ሲችል ለጊዜው ግን ስለ እግዚአብሔር አምላክነት የሚገልጡትን ብቻ በጥናታችን መጨመር አስፈልጓል። በምሥራቁ ዓለም፥ ስም ከመታወቂያነት አልፎ የአንድን ሰው ባሕርይ ወይም ሥራ የሚያመለክት ነው። “አቤቱ ጌታችን ሰምህ በምድር ሁሉ እጅግ ተመሰገነ” (መዝ. 8፡1፥ 9)። 

ለመከለስ ያህል፥ ስለ እውነተኛው አምላክ ማወቅ፥ ሰው ከሚችለው እውቀት ሁሉ በላይ ነው። የእግዚአብሔርን ሕልውና የሚያስረዱ ነጥቦች አሉ (ምንም እንኳን የእግዚአብሔርን ማንነትና ምን እንደሚመስል ባይገልጡም)። በዙሪያችን ያለው ዓለም ስለ እግዚአብሔር ኃይል ቢያስረዳንም፥ ሙሉ የሆነውን የእውነት ቃል የምናገኘው ከመጽሐፍ ቅዱስ ይሆናል። በተለይ ስለ ባሕሪውና ስለ ስሞቹ መማር የምንችለው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

1 thought on “እግዚአብሔር ራሱን ማን ብሎ ይጠራል?”

Leave a Reply

%d bloggers like this: