የክርስቶስ ምድራዊ ሕይወት

በሕይወቱ የተከናወኑ ድርጊቶች 

የክርስቶስ ምድራዊ ሕይወት ለዚህ ትምህርታችን አያሌ ጠቀሜታ አለው። በመጀመሪያው የቃሉን ክቡርነት ሲያጸና የአዳኝነት ክህሎቱንም አረጋግጧል። ያ ወቅት ነበር በጉ ተፈትኖ ለኃጢአት ተገቢ መሥዋዕት መሆኑ የተረጋገጠበት። ሁለተኛ፥ በምድራዊ ሕይወቱም ሕዝቦች እንዲከተሉት አርአያ ሆኗል። ይህ የታየው በተለይ ራሱን አሳልፎ እስከመስጠት ባሳየው ፍቅሩ ነው (1ኛ ዮሐ. 2፡6)። ሦስተኛ፣ በምድራዊ ሕይወቱ ጊዜ ትምሕርቶቹን የሰጠው። ከትምህርቶቹ አንዳንዶቹ በቀጥታ ለአይሁድ ሕዝብ ሲሆን ሌሎቹ ወደፊት የምትመሠረተውን ቤተ ክርስቲያኑን የሚመለከቱ ናቸው። የክርስቶስን ሕይወት በሦስት ለመክፈል ይቻል ይሆናል። በቅድሚያ ቤተልሄም ከመወለዱ ጀምሮ ያሉት ዝግጅት ዓመታት ሲሆኑ፥ እነዚህ የአራስነቱንና የሕፃንነቱን፥ የልጅነቱንና ሙሉ ሰው ሆኖ የማደጉን፣ የጥምቀቱንና የፈተናውን ዘመናት የሚያጠቃልሉ ዓመታት ናቸው። ሁለተኛው፥ የይሁዳ ቀደምት አገልግሎቱን የሚጨምረው የሕዝብ አገልግሎቱን (ዮሐ. 2፡13-4፡3)፣ የገሊላ አገልግሎቱን (ማር. 1፡14-9፡50) እና የፐሪያ (ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምሥራቅ የሚገኝ አገር) አገልግሎቱን (ሉቃስ 9፡51-19፡28) የሚያጠቃልለው ጊዜ ነው። ሦስተኛው ከመሞቱ በፊት የነበረ ቅድመ ሁኔታና መስቀሉ ናቸው። ይህ የተፈጸመው የሕማማት ሳምንት በሚባለው ጊዜ ሲሆን (ሉቃስ 19፡29-22፡46)፥ ይሁዳም አሳልፎ እንደሰጠውና እንደተያዘ (ዮሐ. 18፡2-13)፥ በቀያፋ ፊት መከሰሱን (ማር. 14፡53-15፡1)፥ በሐና ፊት መከሰሱን ( ዮሐ. 18፡12-24) የመጀመሪያው ክስ በጲላጦስ ፊት (ማር. 15፡1-5)፥ በሄሮድስ ፊት (ሉቃስ 23፡8-12)፥ ለሁለተኛ ጊዜ በጲላጦስ ፊት (ማር. 15፡6-15)፥ በመጨረሻም መሰቀሉንና በመስቀሉ ላይ የተናገራቸውን ቃላት ያጠቃልላል። ተጨማሪ ማብራሪያ ከተፈለገ ስለ ሕይወት ታሪኩ ከተጻፉት መጻሕፍት ማግኘት ሲቻል፥ የሞቱን አስፈላጊነት የሚገልጠውን ትምሕርት በተመለከተ ግን በምዕራፍ 8 ላይ እናጠናለን።

የነበሩት ሥልጣኖች 

ጌታ በምድራዊ ሕይወቱ ጊዜ የነበሩት ሥልናትና ያከናወናቸው ተግባራት ሦስት ሲሆኑ፡- እነሱም የነቢይነት፥ የካህንነትና የንጉሥነት ሥልጣናት ናቸው። 

ነቢይ የእግዚአብሔር መልእክት ለሰው ልጆች የሚተላለፍበት መገናኛ ድልድይ ነው። ጌታችን ራሱን ነቢይ ብሎ ጠርቷል (ማቴ. 13፡57)። ያለጥርጥር ከሁሉ የሚበልጥ ነቢይ ሲሆን፥ የእግዚአብሔርን መልእክት ለሰዎች በማሰማት ብቻ ሳይወሰን፥ በሕይወቱና በማንነቱ ጭምር እግዚአብሔርን ገልጧል። ከትምህርቶቹ ውስጥ በጽሑፍ የሰፈሩት እጅግ ጥቂቶቹ ሲሆኑ፥ ስለመገለጡ ስፋትና ጥልቀት በአንደበቱ የተነገረው መልእክት ከሁሉም በላይ ነው። ከሁሉም ይልቅ ሦስቱ ረጅምና ጠቃሚ ስብከቶቹ በጥልቀት ሊጠኑ ይገባል። እነዚህም የተራራው ስብከት (ማቴ. 5-7፥ የደብረ ዘይት ስብከት (ማቴ. 24-25) እና ባንድ ቤት የላይኛው ክፍል ውስጥ ያሰማው ስብከት (ዮሐ. 13-16) ናቸው። 

ጌታችን እንደ መልከጸዴቅ ካህን ሲሆን፣ በአሮን ካህንነት ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ተግባራት በምሳሌነት አከናውኗል። እርሱ ለኃጢአት መሥዋዕት ሊያቀርብ፥ በእግዚአብሔር ፊት ሕዝብን ሊወክል (ዕብ. 5፡1-10) በእግዚአብሔር የተሾመ ካህን ነበር። እርግጥ የካህንነት ሥራው ለእኛ በመማለድና እኛን በማጽናት እስከዛሬ ቀጥሏል (ዕብ. 7፡25፤ ራእይ 2፡1)። 

የክርስቶስ ንጉሥነት ከመወለዱ በፊት የተተነበየ ነበር (ኢሳ. 9፡6-7 ሉቃስ 1፡31-33)። ወደ ምድር በመጣ ጊዜ ስለ ቃል ኪዳኑ ንጉሥ የተነገሩትን ትንቢቶች በሙሉ ቢፈጽምም፥ ሕዝቡ ግን አልተቀበለውም ነበር። ይህ እምቢታቸው የተልእኮውን ፍጻሜ እስከ ዳግም ምጽአቱ ቢያዘገየው እንጂ፥ የአገዛዙን ተስፋ ግን አይሽረውም። እስከዚያው ድረስ ቤተ ክርስቲያኑን ይሠራል። መዘግየቱ የትንቢቱን ተፈጻሚነት ከጥርጣሬ ላይ አይጥለውም፤ ዘላለማዊ ንጉሥነቱንም አያግደውም። 

“የክርስቶስ ነቢይ፥ ካህንና ንጉሥ መሆን በአንድነት ሲወሰዱ ሥጋ ለብሶ ለመጣበት ዓላማ ቁልፍ ነገሮች ናቸው። ነቢይ መሆኑ የእግዚአብሔርን እውነት ለመግለጥ የነበረውን ተልእኮ፥ ካህን መሆኑ የአዳኝነትና የእማላጅነት ሥልጣኑን፥ ንጉሥ መሆኑ በእስራኤልና በመላው ዓለም ላይ ለመንገስ ያለውን ሥልጣን ያሳያሉ። እነዚህ ከፍተኛ የክብር ሥልጣኖች በክርስቶስ ተደርሶባቸዋል።” 

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: