የአማኙ ዋስትና

ከእውነተኛ አማኝ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ነው የዘላለማዊ ዋስትና ጥያቄ ትምህርት መቅረብ ያለበት። እርግጥ በአንድ ወቅት ያምንበት የነበረውን እውነት የካደ የሚመስልን ሰው መዳን አለመዳን በቅድሚያ መናገር ያስቸግራል። በተጨማሪም ሥጋዊ ክርስቲያኖች በመንግሥተ ሰማያት እንደሚኖሩና ሥራቸውም እንደ እንጨት፥ ሳርና አገዳ እንደሚቃጠል ይታወቃል። ቢሆንም እነዚህ ክርስቲያኖች የዳኑ መሆናቸውን እናውቃለን (1ኛ ቆሮ. 3፡15)። ሕይወታቸውን ስንመለከት ግን ከእነርሱ አንዳንዶች ድነታቸውን (ደኅንነታቸውን) አጥተዋል ወደሚል ማጠቃለያ እንደርስ ይሆናል። ዋናው ጥያቄ ግን ይህ ነው። እውነተኛ አማኝ ኃጢአት በመሥራቱ፥ እምነቱን በመጣሉና በሌላ ምክንያት ድነቱን (ደኅንነቱን) ያጣል? 

የዘላለማዊ ዋስትና ማረጋገጫ 

በመጨረሻም፥ የዋስትና ትምህርት በእግዚአብሔር ከንውን ላይ የሚመሠረት ነው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ አንድ ሰው ድነቱን (ደኅንነቱን) ቢያጣ፥ አንዳንድ የእግዚአብሔር ሥራዎች ሊቀለበሱ ነው ማለት ይሆናል። ለምሳሌ፡- 

1. በዳንን ጊዜ መንፈስ ቅዱስ የክርስቶስ አካል አድርጎናል (1ኛ ቆሮ. 12፡13)። አማኝ ድነቱን የሚያጣ ከሆነ ደግሞ ከዚያ አካል ይወጣል ማለት ነው! እንዲህ ያለው አሳብ በቅዱስ ቃሉ አልተመለከተም፡፡

2. መንፈስ ቅዱስ አስከ ቤዛ ቀን ድረስ አማኙን አትሞታል (ኤፌ. 1፡13፥ 4፡30)። ድነት (ደኅንነት) የሚታጣ ከሆነ፥ ይህ ማኅተም ከቤዛ ቀን በፊት ይሰበራል ማለት ይሆናል። 

3. ደግሞም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ እኛን መጠበቅ የአብ ዓላማና ተግባር ነው (ዮሐ. 10፡28-30፥ 13፡1)። በመጨረሻ ያለ ነውርና ነቀፋ በፊቱ የሚያቀርበንም እርሱ ነው(ይሁዳ 24)። 

4. አጥጋቢ የሆነው የዋስትና ማሳመኛ ቃል ያለጥርጥር በሮሜ 8፡29-39 ላይ ተጽፏል። የመረጃዎቹን ጥንካሬ ያስተውሉ። በመጀመሪያ የተወሰኑት ተጠሩ፥ ጸደቁ፥ ከበሩ። የኀላፊ ጊዜ የሆነውን ግስ ለወደፊት ድርጊቶች ልንጠቀምበት እንችላለን፤ ምክንያቱም አንድም የዳነ ሰው እንደማይጠፋ እርግጠኞች ነንና። አስቀድሞ ከማወቅ እስከ መወሰን ድረስ ያለው ሰንሰለት፥ ማለትም መጠራትና መጽደቅ እስከሚከብሩ ድረስ እንደጻኑ ይቆያሉ። ሁለተኛው፥ የእግዚአብሔርን ምርጦች በመክሰስ ድነታቸውን የሚያሳጣ አንዳችም ኃይል አይኖርም፤ ክስ ሁሉ የሚቀርብለት ፈራጅም ሆነ አጽዳቂ እግዚአብሔር ነውና (ቁ. 33)። ዳኛው ጻድቃን ናቸው ብሎ የበየነላቸውን አማኞች፥ የመርታት ዕድል የሚኖረው ምን ዓይነት ከሳሽ ነው? ሦስተኛ፥ ጌታ ስለ እኛ ያለማቋረጥ እየማለደ ነው። ይህ ራሱ ለደኅንነታችን በቂ ዋስትና ነው (ቁጥር 34ን ከ1ኛ ዮሐንስ 2፡1 ጋር ያነጻጽሩ)። አራተኛ፥ ምዕራፉ እርግጠኛና ጽኑ በሆነ ቃል ኪዳን የተደመደመ ሲሆን፥ ምንም ዓይነት ሁኔታ (እኛንም ሆነ ማንኛውንም ሌላ ፍጡር፥ ቁ. 39) በጌታችን በክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም። ይህ ማንኛውንም ቀዳዳ የሚደፍን ማረጋገጫ ይሆናል። 

እርግጥ አንዳንድ ሰዎች ድነታችንን እናጣለን ብለው ሳይሰጉ፥ የዘላለም ዋስትናን ትምህርት እንደ ፈቃድ ወረቀት እየተጠቀሙ በኃጢአት ሲኖሩ ይታያሉ። ይህ ተገቢ አይደለም፤ እግዚአብሔርን በጣም የምናመሰግንና ቅዱስ ኑሮን ለመኖር የምንጥር መሆን አለብን (ሮሜ 6፡1-14)። ይህም እንደ ማንኛውም እውነት ሁሉ ይጣመምና ይዋሽበት ይሆናል። “ዋሥትና የለም” የሚለው ትምህርትም ቢሆን በኃጢአት የመኖሪያ ፈቃድ ሊሆን ይችላል። 

አንዳንድ አስቸጋሪ ጥቅሶች 

“ዋስትና የለም” ብለው የሚያስተምሩት ብዙዎቹ ጥቅሶች የተጻፉት፥ በቤተ ክርስቲያን ተግባራዊ ችግር መኖሩን በማስመልከት ነበር። በአዲስ ኪዳን ጊዜም ከቤተ ክርስቲያን አባላት መካከል በእውነት የዳነው ማን መሆኑን ማወቁ ከባድ ነበር። ስለዚህ ቃሉን የሚጽፈው ሐዋርያ አንዳንዶችን የእምነታቸው ማረጋገጫ የሚሆን ፍሬ በተጨባጭ እንዲያሳዩ ሲጠይቅ፥ አንዳንዶችንም የድነት እምነት ያላቸው ስለመሆኑ እርግጠኞች እንዲሆኑ መከሯቸዋል። 

ለምሳሌ ዕብ. 6፡4-6 በተለያየ መንገድ ቢተረጎምም፥ አእምሯቸው ላልበሰለና የጸና ሕይወት ለሌላቸው አማኞች ማስጠንቀቂያ ነው። ስለዚህ ጸሐፊው እንደግ ይላል (ቁ. 1)። ምከንያቱም በከርስትና ሕይወት እንደገና “ሀ” ብሎ መጀመር የሚባል ነገር ስለሌለ፥ አማራጩ ባሉበት መቆም፥ ወይም ወደፊት መራመድ ይሆናል። ይህ ጥቅስ አንድ ሰው ድነቱን ሊያጣ እንደሚችል የሚያስተምር ከሆነ፥ እንግዲያው በድጋሚ ለመዳን እንደማይቻልም በግልጥ ያብራራል። በዚህ ምክንያት የአማኙ የዘላለም ዋስትና ልክ አለመሆኑን ለማስረዳት ይህን ጥቅስ ለመጠቀም መሞከር፥ ልክ አለመሆኑን ለማረጋገጥ ካለማስቻሉም በላይ ሌሎች ሊደረስባቸው የማይችሉና አስቸጋሪ የሆኑ ችግሮችን ይፈጥራል።። 

በጸሐፊው ግምት በዮሐንስ 15፡6 የተገለጠው ዋጋ የሌለው ሥራ ሁሉ ክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት እንደሚቃጠል ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 3፡15 መሠረት)። ያም ቢሆን ድነት የተረጋገጠ ነው። በአንጻሩ ብዙ ሰዎች እነዚህ ሁለት ጥቅሶች፥ ለአፋዊ አማኞችና በእውነት ዳግም ላልተወለዱ ሰዎች የተነገሩ ናቸው ይላሉ። 

ያዕቆብ 2፡14-26 የማይሠራ እምነት መጀመሪያውኑ የሚያድን እምነት አይደለም ይላል። በሌላ አነጋገር “እምነት ብቻ ነው የሚያድነው፤ ነገር ግን የሚያድነው እምነት ብቻውን ሆኖ አያውቅም”፡፡

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.