የሺህ ዓመት ግዛት

መለያዎቹ 

የሺህ ዓመት ግዛት የሚባለው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ለ1000 ዓመት በጽድቅ የሚገዛበት እና የብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃሎች ለአይሁድና ለዓለም ሁሉ የሚፈጸሙበት ጊዜ ነው። የዚህ የአገዛዝ ዘመን ርዝመት 1000 ዓመት መሆን፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው በአንድ ምዕራፍ ቢሆንም (ራእይ 20 በምዕራፉ ውስጥ 6 ጊዜ ተደጋግሞ ተጠቅሷል)፤ በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ስለዚህ መንግሥት የሚነግሩን ብዙ ጥቅሶች አሉ። ስለዚህ ይህ ትንቢት አንዳንዶች እንደሚሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፥ ለዚያውም ለመተርጎም በሚያስቸግር አንድ ምዕራፍ የተወሰነ አሳብ አይደለም። 

መንግሥቱ በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ አኳኋን ተገልጧል። “በጌታ ጸሎት ውስጥ የሚመጣ መንግሥት” ተብሎ ተጠቅሷል (ማቴ. 6፡10)። “የእግዚአብሔር መንግሥት” (ሉቃስ 19፡1) “የከርስቶስ መንግሥት” (ራእይ 11፡15)፣ “ዳግም መወለድ” (ማቴ. 19፡28)፥ “የመጽናናት ዘመን” (ሐዋ. 3፡19)፥ “የሚመጣው ዓለም” (ዕብ. 2፡5) ተብሏል። ጌታችን በሉቃስ 19፡11-27 በጠቀሰው ምሳሌ፥ የሺህ ዘመኑ መንግሥት በፍጥነት እንደማይመሠረትና ከዚያ በፊት ሌላ ነገር (ማለት ቤተ ክርስቲያን) በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ቀዳሚ ድርሻ እንደሚኖራት ያመለክታል። 

አስተዳደሩ 

የሺህ ዓመት መንግሥት የሚመሠረተው በምድር ላይ ነው (ዘካ. 14፡9)። በፍዳ ዘመን ከሚከሰቱ አስከፊ ፍርዶች የተነሳ (የምድር መናወጥ፣ የአየር መለወጥ ወዘተ.) የዓለም ፊትና ገጽታ ይለወጣል። ኢየሩሳሌም የመንግሥቱ ማዕከል ትሆናለች (ኢሳ. 2፡3)። ከፍ ከፍ ትላለች (ዘካ. 14፥10)፤ ታላቅ የክብር ቦታ ትሆናለች (ኢሳ. 24፡23)፤ የመቅደሱ ስፍራ እዚያ ይሆናል (ኢሳ. 33፡20)፤ ለዓለም ሁሉ የደስታ ምንጭ ትሆናለች (መዝ. 48፡2)። ከተማይቱ አሁን የክርክርና የግጭት ስፍራ ብትሆንም፥ በሺህ ዓመቱ ግዛት ጊዜ ግን ለደኅንነቷ የማትሰጋ ትሆናለች (ኢሳ. 26፡1-4)። ከዚያች ከተማ ሕግ ይወጣል። ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድርም እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች (ኢሳ. 2፡3፥ 11፡9)። 

የሺህ ዓመቱ መለኮታዊ አገዛዝ ንጉሥና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይሆናል። ምድርን ሁሉም ይገዛል (ዳን. 1፡14)፤ ፍጹምና ሙሉ ፍትህ ለሁሉም ያሰፍናል። ኃጢአትን ይቀጣል (ኢሳ. 11፡44 65፡20)፤ በፍጹም በጽድቅ ይፈርዳል (ኢሳ. 11፡3-5)። ይህ በምድር የሚከናወን የሰላም ምስጢር፥ ገዥው ሰላምን በጽድቅ የሚያሰፍንበት ይሆናል። ምናልባት ጌታ ከሞት የሚነሳውን ዳዊትን፥ ለመንግሥቱ እንደ አለቃ ይገለገልበት ይሆናል (ኤር. 30፡9፤ ሕዝ. 37፡24-25)። ከንጉሡ ሥልጣን ሥር ልዑል ይሆናል። 

በአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ላይ የሚሾሙት አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ይሆናሉ (ማቴ. 19፡28)፤ ሌሎችም ልዑላንና መሳፍንት ሆነው በዚህ አገዛዝ ይካፈላሉ (ኤር. 30፡21፤ ኢሳ. 32፡1)። ሌሎችም ጻድቃን በዚህ የሺህ ዓመት ግዛት የተለያዩ ኃላፊነቶች ይቀበላሉ (ሉቃስ 19፡11-27)። 

የዚህ ምድራዊ መንግሥት ተገዢ የሚሆኑት፥ የፍዳውን ዘመን አልፈው በምድራዊ አካላቸው የሚገኙ አይሁድና አሕዛብ ይሆናሉ። በመጀመሪያው ጊዜ በዚህ መንግሥት ውስጥ አንድም ያልዳነ ሰው ያለ አይመስልም። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆዩ አያሌ ሕፃናት ይወለዳሉ፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ይህ መንግሥት በብዙ ወጣቶች ይሞላል። ከእነዚህ መካከል ግማሾቹ ክርስቶስን እንደ አዳኛቸው ሲቀበሉ ሌሎች ግን አይቀበሉትም። እነዚህ ሁሉ፣ በክርስቶስ ዳግም የተወለዱትም ሆኑ ያልተወለዱት ለንጉሡ ፍጹም ታማኞች መሆን ግዴታቸው ነው። ቤተ ክርስቲያን የትንሣኤ አካል የሚኖራት ሲሆን ከክርስቶስም ጋር አብራ ትገዛለች። የሥጋዊ ውሱንነት፥ የምግብ፥ የቦታ፥ የመንግሥታዊ እና ሌሎች ችግሮች አይኖሩባትም። በሺህ ዓመቱ አገዛዝ ወቅት የቤተ ክርስቲያን ትክክለኛ መኖሪያ አዲሲቷ ኢየሩሳሌም ትሆናለች (ራእይ 21፡2፥ 9-10)። 

መንፈሳዊ ባሕሪው 

የሺህ ዓመቱ አገዛዝ ምድራዊ ነውና መንፈሳዊ ሊሆን አይችልም፣ የሚል እና ይችላል የሚል አከራካሪ አሳብ አለ። በመሠረቱ ግን በሁለቱ አሳቦች መካከል ግጭት ሊኖር ባልተገባ ነበር። ዛሬ በምድር የሚኖር ክርስቲያን መንፈሳዊነት ይጠበቅበታል። በሺህ ዓመቱ አገዛዝ ዘመንም እግዚአብሔር ምድራዊና መንፈሳዊ የሆነውን ነገር በማጋጠም በምድር ላይ የራሱን ክብር በሙላት ይገልጣል። መንግሥቱም ከፍተኛ መንፈሳዊነት ይታይበታል። 

ከመንግሥቱ መንፈሳዊ ባሕርያት ውስጥ ጥቂቶቹ የሚከተሉት ይሆናሉ። ጽድቅ ያብብበታል (ኢሳ. 11፡3-5)፥ ሰላም ይሰፍናል (ኢሳ. 2፡4)፥ መንፈስ ቅዱስ ለየት ባለ መንገድ ይሠራል (ኢሳ. 61፡3፤ ኢዮብ 2፡28-29)፥ ሰይጣን ይታሠራል (ራእይ 20፡2-3)። አንዳንዶች በሺህ ዓመት ግዛት የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደገና ይሠራና የእንስሳት መሥዋዕት የሚቀርብበት የአምልኮ ስፍራ ይሆናል ብለው ያምናሉ። ሕዝቅኤል 40-46 ይህን የሚያመለክት ቢመስልም ክርስቶስ በምድር እስካለ ድረስ መሥዋዕቱ ምን ያደርጋል? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። በአገዛዙ ወቅት የሚኖረው መንፈሳዊ አምልኮ ምን እንደሚመስል ሙሉ በሙሉ መረዳቱ ስለሚሳነን፥ ዛሬ ለዚህ ጥያቄ መልስ አናገኝለት ይሆናል። 

ማኅበራዊ ፍትሁ 

ጽድቅና ፍትህ የሚነግሡበት ይሀ የሺህ ዓመት አምላካዊ አገዛዝ የማኅበራዊ ፍትህንም ይጨምራል። ፍርድ ቤቶች እንደተለመደው ስሕተት በተሞላበት የዓይን ምስክሮች ግንዛቤና ቃል ሳይሆን፥ በራሱ በክርስቶስ ሙሉ እውቀት በትክክል ይዳኛሉ (ኢሳ. 11፡3-5)። ማንኛውም ወንጀል ያለቅጣት አይታለፍም። ጭቆናም ጨርሶ አይፈቀድም፤ ለሕግ ማስፈጸሚያ የሚያስፈልገው ክፍያ በጣም ይቀንሳል። ሰላም በዓለም ስለሚሰፍን ወታደራዊ ወጪዎች ሁሉ ይሰረዛሉ። 

መሬት እጅግ ፍሬያማ ትሆናለች (ኢሳ. 35፡1-2)፤ ምንም እንኳን ሺሁ ዓመት እስኪፈጸምና ሞት ለዘላለም እስኪሻር ድረስ ሙሉ በሙሉ ባይሰረዝም፥ ምድር በአዳም ኃጢአት ምክንያት የተጣለባት እርግማን ይነሳላታል (ዘፍጥ. 3፡17)። በቂ ዝናብ ኖሮ የምግብ አቅርቦት ስለሚጨምር፥ ታላቅ የብልጽግና ዘመን ይሆናል። የክርሰቶስም የጽድቅ አገዛዝ ለሰዎች ባመረቱት፣ ወይም በአገልግሎታቸው መጠን ተገቢውን ክፍያ ያስገኝላቸዋል። ሰላም በምድር ሰፍኖ ብልጽግናና ማኅበራዊ ፍትህ ይሰፍናል። 

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.