የማርቆስ ወንጌል ጥናት መምሪያና ማብራሪያ
ምልከታ እና ትርጓሜ
በዚህ ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰማያዊውን እውነት በምድራዊ ምሳሌዎች እያዋዛ ሲያስተምር እንመለከታለን። መብራት በርቶ ከዕንቅብ ወይም ከአልጋ በታች እንደማይቀመጥ ሁሉ የእግዚአብሔርም ቃል ሊገለጥና ሊበራ የመጣ መሆኑን ያስረዳናል። “በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል” በማለት ቃሉን በምንሰማበትና በምንቀበልበት ልክ በረከቱና እውቀቱ እንደሚጨመርልን ይነግረናል። በመቀጠልም የእግዚአብሔር መንግሥት በምድር ላይ ስር የምትሰድበትን ሁኔታ በሁለት ድንቅ የዘር ምሳሌዎች ይገልጻል። አንደኛው ዘሪው ዘሩን ዘርቶ በተኛበትና በነቃበት ጊዜ ዘሩ በራሱ ኃይል እንዴት እንደሚያድግና ፍሬ እንደሚያፈራ ሲሆን ፣ ሁለተኛው ደግሞ ከዘር ሁሉ በምታንሰው በሰናፍጭ ቅንጣት ተመስሎ የሚሰጠው ትምህርት ነው። ሰናፍጭ መሬት ውስጥ ስትገባ እጅግ ትንሽ ብትሆንም ፣ አድጋ ግን አእዋፍ በቅርንጫፎቿ ሥር ጥላ እስኪያገኙ ድረስ ታላቅ ዛፍ ትሆናለች።
መብራት የመጣው ሊበራ እንደሆነ ሁሉ ክርስቶስም ወደ ዓለም የመጣው የተሰወረውን የእግዚአብሔርን ሐሳብ ሊገልጥልን ነው። ቃሉን በጥንቃቄ የምንሰማና የምንታዘዝ ከሆነ እግዚአብሔር ተጨማሪ ሚስጢራትንና ጸጋን ይገልጥልናል። “ላለው ይሰጠዋል” የሚለው ቃል በመንፈሳዊ ሕይወታችን ውስጥ ያለን ፍላጎትና ቅንዓት ለተጨማሪ ዕድገት ቁልፍ መሆኑን ያሳያል።
ለምሳሌ፦ አንድ ትንሽ ሻማ በጨለማ ቤት ውስጥ ቢበራ ጨለማው ወዲያውኑ ይሸሻል ፤ ሻማው ራሱን እያሟሟ ብርሃን እንደሚሰጥ ሁሉ ወንጌልም በእኛ ሕይወት ውስጥ ሲበራ ጨለማውን ሁሉ አስወግዶ ማንነታችንን ይለውጠዋል።
ስለ ዘር ዕድገት የተነገረው ምሳሌ ደግሞ እጅግ የሚያበረታታ ነው። ዘሪው ዘሩን ከዘራ በኋላ ዕድገቱን መቆጣጠር አይችልም ፤ ዘሩ በውስጡ ባለው መለኮታዊ ኃይል በቀንና በሌሊት ያድጋል። ይህም በቤተክርስቲያንና በግል ሕይወታችን ውስጥ ቃሉን ከዘራን በኋላ ዕድገቱን የሚሰጠው እግዚአብሔር መሆኑን ያስተምረናል። ብዙ ጊዜ ለውጥ ወዲያው ላይታየን ይችላል ፤ ነገር ግን ቃሉ በውስጣችን ድምፅ ሳይሰማ በኃይል እየሠራ ነው።
የሰናፍጭ ቅንጣት ምሳሌ ደግሞ የወንጌልን ተፅዕኖ ያሳያል። ወንጌል በናዝሬት በመንደር ደረጃ ቢጀመርም ዛሬ ግን ዓለምን ሁሉ የደረሰ ታላቅ ዛፍ ሆኗል። የእግዚአብሔር መንግሥት አጀማመሯ ትንሽ ቢመስልም ፍጻሜዋ ግን እጅግ ታላቅና ለብዙዎች ጥላ የሚሆን ነው። ዛሬ የምናደርጋት ትንሿ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ወይም የምንናገራት አንዲት የእውነት ቃል ወደፊት ታላቅ ፍሬ እንደምታፈራ ተስፋ ልናደርግ ይገባል።
ተግባራዊ የውይይት ጥያቄዎች
👉መብራት በከፍተኛ ቦታ መቀመጡ ከወንጌል ምስክርነት ጋር እንዴት ይያያዛል?
👉”በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል” የሚለው መርሕ ከመስማትና ከመቀበል ጋር ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?
👉በራሱ ጊዜ ስለሚበቅለው ዘር የሚናገረው ምሳሌ (4፡26-29) ለማርቆስ ወንጌል ብቻ የተለየ የሆነው ለምንድን ነው?
👉ዘሪው ሳይታወቀው ዘሩ ማደጉ በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ላይ ያለንን እምነት እንዴት ያጠናክራል?
👉የሰናፍጭ ቅንጣት ታናሽ ሆና ሳለ ትልቅ ዛፍ መሆኗ ስለ ቤተክርስቲያን መጀመሪያና መጨረሻ ምን ይነግረናል?
👉ኢየሱስ ምስጢሩን ለደቀመዛሙርቱ ብቻ ለብቻ መተርጎሙ ለምን አስፈለገ?
👉ምሳሌዎች ለ “ውጭዎች” ምስጢር ለ “ውስጦች” ብርሃን የሆኑት ለምንድን ነው?
👉”የተሰወረ ሊገለጥ እንጂ አልተሰወረም” የሚለው ቃል ስለ መሲሐዊ ምስጢር መገለጥ ምን ይጠቁማል?
👉የእግዚአብሔር መንግሥት እድገት ከሰው ጥረት በላይ መሆኑን 4፡27 እንዴት ያሳያል?
👉በሰናፍጭ ዛፍ ጥላ ስር ወፎች ማረፋቸው የአሕዛብን መጠለል እንዴት ያሳያል?