የማርቆስ ወንጌል ጥናት መምሪያና ማብራሪያ
ምልከታ እና ትርጓሜ
በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአገልግሎቱን አድማስ በማስፋት ከአይሁድ ምድር ወጣ ብሎ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሲሄድ እንመለከታለን። በዚያም አንዲት ግሪካዊትና ትውልዷ ፊንቄያዊ የሆነች ሴት ልጇን ከርኩስ መንፈስ እንዲያድንላት በፊቱ ተደፍታ ለመነችው። ጌታም “ልጆቹ መጀመሪያ ይጠግቡ ዘንድ ፍቀድ ፤ የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባምና” የሚል እጅግ አስገራሚና ፈታኝ ምላሽ ሰጣት። ሴቲቱ ግን አልተከፋችም ፤ ይልቁንም “አዎን ጌታ ሆይ ፤ ቡችሎች እንኳ ከማዕድ በታች የልጆችን ፍርፋሪ ይበላሉ” በማለት በትሕትናና በእምነት መለሰችለት። ጌታም በዚህ ንግግሯ ተደንቆ ልጇን ፈወሰላት። ከዚህ በኋላ ጌታ ወደ አሥሩ ከተማ (ዲካጶሊስ) ተመልሶ ሲመጣ ፤ ደንቆሮና መናገር የማይችል አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። ጌታም ሰውየውን ከሕዝቡ ለይቶ ብቻውን ወሰደው ፤ ጣቶቹንም በጆሮዎቹ ውስጥ አገባ ፤ እንትፍም ብሎ ምላሱን ዳሰሰ ፤ ወደ ሰማይም አሻቅቦ ተመልክቶ በታላቅ ትንፋሽ “ኤፍታህ” (ተከፈት) አለው። በዚያው ቅጽበት የሰውየው ጆሮ ተከፈተ ፤ የምላሱም እሥራት ተፈቶ አጥርቶ መናገር ጀመረ። ሕዝቡም “ሁሉን በመልካም አደረገ” በማለት በታላቅ መገረም መሰከሩ።
ይህ ታሪክ የእግዚአብሔር ጸጋ ለሰው ሁሉ (አይሁድም ሆኑ አሕዛብ) የተሰጠ መሆኑን የሚያሳይ ታላቅ ትምህርት ይዟል። የፊንቄያዊቷ ሴት ታሪክ ጌታ እኛን በእምነት እንዴት እንደሚፈትነን ያሳያል። ጌታ “ቡችሎች” (ውሾች) የሚለውን ቃል የተጠቀመው በወቅቱ አይሁድ አሕዛብን የሚጠሩበትን መንገድ በማስታወስ እንጂ ሴቲቱን ለማሳነስ አልነበረም። ሴቲቱ ግን “የልጆች እንጀራ” የተባለው የእግዚአብሔር በረከት ለአይሁድ አስቀድሞ እንደተሰጠ አምናለች ፤ ሆኖም ከአምላክ ማዕድ የሚወድቅ አንዲት “ፍርፋሪ” እንኳ የልጇን እስራት ለመበጠስ በቂ መሆኑን ተረድታለች።
ለምሳሌ፦ አንድ እጅግ ሀብታም የሆነ ሰው ካለው ቢሊዮን ብር ውስጥ ጥቂት ሳንቲሞችን ቢሰጠን ለእርሱ ምንም አይደሉም ፤ ለእኛ ግን ትልቅ ሀብት ሊሆኑ ይችላሉ።
የክርስቶስም ኃይል እንደዚሁ ነው ፤ ከእርሱ ዘንድ የምታገኘው አንዲት ቅንጣት ጸጋ በማንኛውም ዓለማዊ መድኃኒት ሊፈታ የማይችልን ችግር ትፈታለች። ይህች ሴት ትዕቢቷን ጥላ ለበረከቱ በመንበርከኳ ታላቅ ተአምር ተደረገላት።
ደንቆሮውንና ዲዳውን የመፈወሱ ታሪክ ደግሞ ጌታ እያንዳንዱን ሰው በግል እንደሚያውቅና እንደሚረዳ ያሳየናል። ጌታ ሰውየውን ለይቶ ወደ ጎን መውሰዱ ፤ ለእያንዳንዱ ሰው የሚሰጠው ፈውስ የግል መሆኑን ይጠቁማል። ጌታ ጣቶቹን በጆሮው ማድረጉና ምላሱን መዳሰሱ ፥ በደዌ ለተዘጋው ሕይወታችን ጌታ በራሱ እጅ ጣልቃ እንደሚገባ ያሳያል። “ኤፍታህ” ወይም “ተከፈት” የሚለው ቃል ዛሬም ለእኛ እጅግ አስፈላጊ ነው። ብዙ ጊዜ ጆሯችን የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ዝግ ሊሆን ይችላል ፤ ምላሳችንም የእግዚአብሔርን ክብር ለመመስከር ታስሮ ሊሆን ይችላል። ጌታ ግን ዛሬም ወደ ሰማይ አሻቅቦ እያየ ለእኛ ሕይወት “ተከፈት” ይላል። ጆሯችን ለእውነት ሲከፈት ፥ ምላሳችንም ምስጋናን ያወጣል። ይህ ክፍል የሚያስተምረን ጌታ ያላደረገውና የማይችለው ምንም ነገር አለመኖሩንና ፥ እኛም እንደ ፊንቄያዊቷ ሴት በትሕትና እንደ ደንቆሮውም ደግሞ ለጌታ እጅ በመገዛት መቅረብ እንዳለብን ነው።
ተግባራዊ የውይይት ጥያቄዎች
👉ኢየሱስ ለምን ወደ አሕዛብ ግዛት (ጢሮስና ሲዶና) ለመሄድ ፈለገ?
👉የሴቲቱ ልመና ከአሕዛብ እምነት አንጻር ምን ልዩ ያደርገዋል?
👉ኢየሱስ “ቡችሎች” የሚለውን ቃል መጠቀሙ እሷን ለመናቅ ሳይሆን እምነቷን ለመፈተን መሆኑን እንዴት እንረዳለን?
👉ሴቲቱ የተናገረችው ምላሽ የእሷን ትሕትናና ጽናት እንዴት ያሳያል?
👉ደንቆሮውን ሰው ሲፈውስ ምራቁን መጠቀሙና ወደ ሰማይ መመልከቱ ምን ትርጉም አለው?
👉”ኤፍታህ” የሚለው ቃል መጠቀሱ የታሪኩን ትክክለኛነት እንዴት ያሳያል?
👉ሕዝቡ “ሁሉን በመልካም አደረገ” ብለው መመስከራቸው የኢየሱስን አገልግሎት ከፍጥረት ሥራ ጋር እንዴት ያገናኘዋል?
👉ሴቲቱ “ቡችሎችም ከልጆች ማዕድ የሚወድቀውን ይበላሉ” ማለቷ ስለ እግዚአብሔር ሉዓላዊነትና ጸጋ ምን ይገልጻል?
👉ደንቆሮውን ሰው ለብቻው አውጥቶ መፈወሱ ስለ ግል እንክብካቤ ምን ያስተምራል?
👉”ምራቅን” መጠቀም በወቅቱ ከነበረው የመፈወስ ልማድና ከኢየሱስ መለኮታዊ ኃይል ጋር እንዴት ይያያዛል?