የማርቆስ ወንጌል ጥናት መምሪያና ማብራሪያ
ምልከታ እና ትርጓሜ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በባሕር ዳርቻ ሆኖ ሲያስተማር እጅግ ብዙ ሕዝብ ስለከበበው ፤ በባሕር ላይ ባለች ታንኳ ላይ ተቀምጦ በምድር ላይ ላለው ሕዝብ በምሳሌ ማስተማር ጀመረ። በዚህ ትምህርቱ አንድ ዘሪ ዘር ሊዘራ እንደወጣና ዘሩም በአራት ዓይነት ስፍራዎች ላይ እንደወደቀ ይነግረናል። የመጀመሪያው በመንገድ ዳር የወደቀው ሲሆን ወፎች መጥተው በሉት ፤ ሁለተኛው በአለት ላይ ወድቆ አፈር ስላልነበረው ፀሐይ በወጣ ጊዜ ወዲያው ደረቀ ፤ ሦስተኛው ደግሞ በእሾህ መካከል ወድቆ እሾሁ አነቀውና ፍሬ አላፈራም ፤ በመጨረሻም በመልካም መሬት ላይ የወደቀው ዘር አድጎ እስከ መቶ እጥፍ ድረስ ድንቅ ፍሬ አፈራ። ጌታም ይህን ተናግሮ “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” በማለት ትምህርቱን ደመደመ። ደቀመዛሙርቱ የምሳሌውን ትርጉም በጠየቁት ጊዜ ጌታ ምሳሌው የእግዚአብሔር ቃል በሰው ልብ ውስጥ ስላለው ሁኔታ የሚናገር መሆኑን በዝርዝር አስረዳቸው።
ይህ ምሳሌ በወንጌል አገልግሎት ውስጥ ዘሪው ጌታ ራሱ ወይም ቃሉን የሚያውጁ አገልጋዮች ሲሆኑ ፤ ዘሩ ደግሞ የማይለወጠው የእግዚአብሔር ቃል ነው። እዚህ ጋር ትልቁ ትኩረት በዘሪው ብቃት ወይም በዘሩ ጥራት ላይ ሳይሆን ዘሩ በሚያርፍበት “አፈር” ወይም በሰሚው “ልብ” ላይ ነው። ጌታ አራት ዓይነት የልብ ሁኔታዎችን ይገልጽልናል። በመንገድ ዳር ያሉት ቃሉን ሰምተው ወዲያው ሰይጣን መጥቶ ቃሉን የሚነጥቅባቸው ሲሆኑ ፤ እነዚህ ልባቸው ለቃሉ ፈጽሞ ዝግ ያልሆነና በዓለማዊ ሐሳብ የተረገጡ ናቸው። በአለት ላይ ያሉት ደግሞ ቃሉን በደስታ ይቀበላሉ ነገር ግን ስር ስሌላቸው ፈተና ሲመጣ ወዲያው ይክዳሉ። እነዚህ ስሜታዊ እንጂ ጥልቅ ውሳኔ የሌላቸው ክርስቲያኖች ናቸው።
ለምሳሌ፦ አንድ ተማሪ ትምህርት ሲጀምር እጅግ ተደስቶ ጀምሮ ነገር ግን የመጀመሪያው ፈተና ሲመጣ “ከባድ ነው” ብሎ ትምህርቱን ቢተው ፤ ልክ እንደ አለቱ ላይ እንደወደቀው ዘር ነው። ፍሬ ለማፍራት ጽናትና ስር መስደድ የግድ ያስፈልጋል።
በእሾህ መካከል ያለው ደግሞ የዚህ ዓለም ሐሳብ ፣ የባለጠግነት መታለልና የሌላው ነገር ምኞት ቃሉን አንቀው ፍሬ እንዳያፈራ የሚያደርጉበት የልብ ሁኔታ ነው። ብዙ ጊዜ መንፈሳዊ ሕይወታችን የማይለወጠው ቃሉ ስለጠፋ ሳይሆን ለሌሎች ምድራዊ ነገሮች በልባችን ውስጥ ሰፊ ቦታ ስለሰጠን ነው። በመጨረሻም መልካም መሬት የተባሉት ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉና ፍሬ የሚያፈሩት ናቸው። ይህ የሚያስተምረን እውነተኛ ክርስቲያን ማለት ቃሉን መስማት ብቻ ሳይሆን ቃሉ በሕይወቱ እንዲሠራ የሚፈቅድና ለለውጥ ራሱን የሚያዘጋጅ ነው። ዛሬ ልባችን የትኛው ዓይነት አፈር እንደሆነ ራሳችንን መመርመር ይኖርብናል ፤ ጌታ የሚፈልገው ቃሉ በእኛ ሕይወት ውስጥ ሰርጾ ታላቅ የመንፈስ ፍሬ እንድናፈራ ነው።
ተግባራዊ የውይይት ጥያቄዎች
👉ኢየሱስ በታንኳ ላይ ሆኖ ለሕዝቡ ማስተማሩ ለምን አስፈለገ?
👉በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር በሰይጣን መወሰዱ ስለ ቃሉ መከላከያ ምን ያስተምረናል?
👉በጭንጫ ላይ የወደቀውና ሥር ሳይሰድ የደረቀው ዘር የትኞቹን አማኞች ይወክላል?
👉በሾክ የታነቀው ዘር “የዚህ ዓለም ሃሳብና የባለጠግነት መታለል” የሚለውን እንዴት ያብራራል?
👉በመልካም መሬት ላይ የወደቀው ዘር የሰጠው የተለያየ ምርት (30፣ 60፣ 100) ምን ያመለክታል?
👉ኢየሱስ “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” ማለቱ ለምን አስፈለገ?
👉ይህ ምሳሌ በአሁኑ ጊዜ በወንጌል አገልግሎት ውስጥ ለሚገጥሙ ፈተናዎች ምን ምላሽ ይሰጣል?
👉ዘሪው ዘሩን በሁሉም ቦታ መዝራቱ ስለ እግዚአብሔር ልግሥና ምን ይናገራል?
👉ቃሉን “በደስታ” ተቀብሎ ወዲያው መክዳት የሚመጣው ከምን እጥረት የተነሣ ነው?
👉የመቶ እጥፍ ፍሬ ማፍራት የሚያስችል “መልካም መሬት” እንዴት ይዘጋጃል?