የማርቆስ ወንጌል ጥናት መምሪያና ማብራሪያ
ምልከታ እና ትርጓሜ
በዚህ ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ በምድረ በዳ እያስተማረ ሳለ እጅግ ብዙ ሕዝብ አብሮት ለሦስት ቀናት መቆየቱን እንመለከታለን። ጌታ “የሚበሉት የላቸውምና ለሕዝቡ አዝንላቸዋለሁ” በማለት ጥልቅ ርኅራኄውን ገለጠ። ደቀመዛሙርቱ ግን አሁንም በምድረ በዳ ምግብ ከየት ይገኛል? በማለት ሲጠይቁ እናያለን። ጌታም ያላቸውን ሰባት እንጀራና ጥቂት ትናንሽ ዓሦች ተቀብሎ ባረከ ፣ ቆረሰ ፣ ለሕዝቡም እንዲያቀርቡ ለደቀመዛሙርቱ ሰጠ። አራት ሺህ የሚያህሉ ሰዎች በልተው ሲጠግቡ ሰባት ሙሉ ቅርጫት ትርፍ ተነሣ። ከዚህ ድንቅ ተአምር በኋላ ፈሪሳውያን መጥተው ሊፈትኑት ከሰማይ ምልክትን እንዲያሳያቸው ለመኑት ፤ ጌታ ግን በመንፈሱ እጅግ አዝኖ “ለዚህ ትውልድ ምልክት አይሰጠውም” በማለት ጥሏቸው ወደ ማዶ ተሻገረ። በታንኳይቱ ውስጥ ሳሉ ደቀመዛሙርቱ እንጀራ መያዝ መርሳታቸውን ሲያወሩ ፤ ጌታ “ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” በማለት አስጠነቀቃቸው። እነርሱ ግን ነገሩ የገባው መስሏቸው “እንጀራ ስለሌለን ነው” ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ። ጌታም ልባቸው ስለ ደነደነና ስላልተረዱ ገሠጻቸው።
ይህ ታሪክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሁንም በተደጋጋሚ ለሰው ልጅ ሥጋዊ ፍላጎት ግድ እንደሚለውና በሚያስደንቅ ሁኔታ እንደሚያቀርብ ያሳየናል። ሰባት እንጀራና ሰባት ቅርጫት መነሳቱ ፤ ሰባት የፍጽምና ምልክት እንደመሆኑ ጌታ የሚሰጠው በረከት ሙሉና ፍጹም መሆኑን ያስገነዝበናል። ሆኖም ግን ትልቁ ትምህርት ያለው በታንኳይቱ ውስጥ በተነገረው “እርሾ” ላይ ነው። ጌታ ስለ እርሾ ሲናገር ስለ ቁሳዊ እንጀራ ሳይሆን ስለ ትምህርትና ስለ ተጽዕኖ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል።
ለምሳሌ፦ በአንድ ንጹሕ ነጭ ሊጥ ውስጥ ጥቂት እርሾ ቢጨመር ፤ ያቺ ትንሽ እርሾ መላውን ሊጥ እንደምታቦካውና እንደምትለውጠው ሁሉ ፤ የፈሪሳውያን ግብዝነትና የሄሮድስ ዓለማዊነትም የሰውን መንፈሳዊ ሕይወት ቀስ በቀስ የመበከል ኃይል አለው። የፈሪሳውያን እርሾ “ሕጋዊነትና ግብዝነት” ሲሆን ፥ የሄሮድስ እርሾ ደግሞ “ፖለቲካዊና ዓለማዊ አመለካከት” ነው። ደቀመዛሙርቱ በታንኳይቱ ውስጥ ስለ እንጀራ እጥረት መጨነቃቸው ፥ አምስት ሺህና አራት ሺህ ሰዎችን የመገበው ጌታ አብሮአቸው መሆኑን መዘንጋታቸውን ያሳያል።
እኛም ብዙ ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እያየን ፥ ነገር ግን ትናንሽ ችግሮች ሲገጥሙን ጌታን የመርሳትና የመጠራጠር ፈተና ይገጥመናል። ጌታ “እንዴት እስካሁን አታስተውሉም?” ብሎ ሲጠይቅ ፤ የችግራችን ትልቁ ምንጭ የጌታ ኃይል ማነስ ሳይሆን የልባችን ድንዛዜ መሆኑን ሊያሳየን ፈልጎ ነው። ዛሬም ጌታ የሚፈልገው በሚታየው እንጀራ ላይ ብቻ ከማተኮር ወጥተን ፥ የማይታየውንና ሁሉን የሚችለውን የእርሱን ኃይል እንድናስተውል ነው። ከክፉ ተጽዕኖዎችና ከጥርጣሬ እርሾ ራሳችንን ጠብቀን ፥ በቃሉ እውነት ላይ ብቻ መደገፍ ይኖርብናል።
ተግባራዊ የውይይት ጥያቄዎች
👉አራት ሺህ ሰዎችን መመገብ ከአምስት ሺህ ሰዎች መመገብ ጋር ያለው ተመሳሳይነትና ልዩነት ምንድን ነው?
👉ኢየሱስ “ለሕዝቡ አዝንላቸዋለሁ” ማለቱ ስለ ርኅራኄው ምን ይነግረናል?
👉ፈሪሳውያን ምልክት የጠየቁት ለምንድን ነው? ኢየሱስስ ለምን ከለከላቸው?
👉”እርሾ” የሚለው ምሳሌ ስለ ፈሪሳውያንና ስለ ሄሮድስ ትምህርት ምን ያስጠነቅቃል?
👉ደቀመዛሙርቱ ስለ ቁሳዊ እንጀራ መጨነቃቸው መንፈሳዊ ግንዛቤያቸው ምን ያህል ዝቅተኛ እንደሆነ ያሳያል?
👉ኢየሱስ ያለፉትን ተአምራት (5000 እና 4000) ያስታወሳቸው ለምንድን ነው?
👉”ገና አታስተውሉምን?” የሚለው ጥያቄ በደቀመዛሙርቱ ላይ ያለውን ተስፋና ወቀሳ እንዴት ያሳያል?
👉ከሰማይ ምልክት መፈለግ ከእውነተኛ እምነት ጋር ለምን ይቃረናል?
👉ሰባት ቅርጫት ትርፍ መሰብሰቡ ስለ እግዚአብሔር በረከት ሙላት ምን ይናገራል?
👉ደቀመዛሙርቱ እንጀራ መርሳታቸውና ኢየሱስ ስለ እርሾ ማስተማሩ ስለ አለመግባባት (Miscommunication) ምን ያስተምራል?