መግቢያ
በርካታ ሰዎች፣ የክርስቶስን አዳኝነት በተቀበሉ ሰአት ከእግዚአብሔር ጋር የጀመሩት ጉዞ እዛው ላይ እንደሚያበቃ ያስባሉ፡፡ ይህ ከእውነታው እጅግ የራቀ ነው። እርግጥ ነው ጌታን የመቀበል ውሳኔ የዘላለም አድራሻችንን እስከወዲያኛው ይለውጣል! ይህ ውሳኔ በሕይወታችን ከወሰነው ውሳኔ ሁሉ ታላቁና ወሳኙ ነወ። በዚህ ውሳኔያችን አማካኝነት እንዲያው በጸጋው ከመንፈሳዊው ዘር ተወልደናልና የእግዚአብሔር ልጆች እንሆን ዘንድ ስልጣንን አግኝተናል። እናም የዘላለም ሕይወት አለን!! ነገር ግን፣ በምድር በሚኖረን ቀሪ የሕይወት ዘመን እግዚአብሔር ከእያንዳንዳችን ጋር ሊያደርገው የሚወዳቸው በርካታ መንፈሳዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ የዚህ ትምሕርት ዋነኛው ጉዳይም ከድነታችን በኋላ ባለው ቀሪው የምድራዊ ሕይወታችን ዘመን እግዚአብሔር ከኛ የሚሻውን ነገር ማሳወቅ ነው።
እግዚአብሔር በአስተሳሰብህ፣ በቅደመ ሁኔታዎችህ፣ በትምህርትህ፣ በመዝናኛዎችህ፣ በፍቅር ሕይወትህ፣ በወደፊት ሕይወትህ፣ በገንዘብህ፣ በጊዜ አጠቃቀምህ፣ በእቅዶችህ፣ እንዲሁም በማናቸውም የሕይወት ጉዳዮችህ ውስጥ እጁን ማስገባትና ዋነኛ ተዋናይ መሆን ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር በሕይወትህ ጉዳዮች ሁሉ ከአንተ ጋር ‹‹አንድ›› በመሆን እርሱ የሚያፈቅራቸውንና የሚሻቸውን ነገሮች ሁሉ አንተም በሙሉ ልብህ እንድታፈቅራቸውና እንድትሻቸው ይፈልጋል፡፡ ለአንተና የአንተ የሆነውን ሁሉ ማላቅና ማሳደግ ይሻል፣ ደግሞም ፈጣሪህ እንደመሆኑ ይህንን እንዴት መከወን እንዳለበትም ጠንቅቆ ያውቃል!
ከመፀነስህ ዘመን አንስቶና ከዚያም በፊት እግዚአብሔር ሁለት ፈረጅ ያለው አላማ ለሕይወትህ ሰንቆልሃል፡-
- አንደኛው፣ ለዘላለም ከእርሱ ተለይተህ እናዳትኖር አንተን መታደግ ሲሆን (የዘላለም ሕይወት/ድነት መስጠት)
- ሁለተኛው ደግሞ፣ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስን እንድትመስል ማድረግ ነው (የክርስቶስ ደቀ-መዝሙር ማድረግ)
የመጀመሪያው አላማ (አላማ #1) ጌታን በተቀበልክ ቅፅበት ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን ሁለተኛው አላማ (አላማ #2) ግን የሕይወት ዘመን ጉዞህን የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህ ጉዞ በመንፈሳዊ ልደትህ ወቅት ተጀምሮ የሚቀጥል ሂደት ሲሆን ሂደቱም ኢየሱስ በሰው አካል በምድር ላይ ሲመላለስ በነበረበት ወቅት ወደ ነበረበት ፍፁምነት እስክትደርስ ድረስ ወይም ከዚህ አለም በሞት ተለይተህ በሰማይ እርሱን ለመገናኘት እስከምትሄድበት ጊዜ ድረስ የሚቀጥል ነው፡፡
እስካሁን በዚህች ምድር ላይ ወደዚህ ፍፅምና የደረሰ ፍጡር የለም ሊኖርም አይችልም፡፡ ነገር ግን ይህ ጉዳይ ተስፋ ሊያስቆርጥህ አይገባም! በመንፈሳዊ የብስለት ጎዳና ባደግህ መጠን፣ እግዚአብሔር ለአንተ ያሰበውን ‹‹የተትረፈረፈ›› ሕይወት ለመለማመድ ትችላለህ (ዮሐንስ 10፡10)፡፡ በመንፈስ በጎለመስክ ቁጥር፣ መገኘቱን፣ የባርኮት እጆቹን፣ በውሳኔዎችህ ውስጥ ደግሞ የእርሱን ምሪት ይበልጥ እየተለማመድክ ትሄዳለህ፡፡ ለእርሱ ያለህ ጠቀሜታ ባደገ ቁጥር ደግሞ፣ ደስታህና የመኖር አላማህ ጥልቅ እየሆነ ይመጣል፡፡ መኖርህንም ትወደዋልህ። መልካሙን ለማድረግና ክፉውንም ለመጸየፍ ያለህ ፍላጎት እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ለእርሱና ለሌሎች ያለህ ፍቅር ንጹህ እየሆነም ይሄዳል፡፡ በሕይወትህ ለነገሮች የምትሰጠው የቅደም ተከተል ተርታዎች ከእርሱ ቅደም ተከተሎች አንጻር የሰመሩ ግቡብ ይሆናሉ፡፡ ስለ እግዚአብሔር መንግስት እውነታ ያለህ ምልከታ ይጠራል፡፡ የእግዚአብሔር የእድገት መለኪያ እንደሆነው እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ማየት፣ ማድረግና ለነገሮች ምላሽ መስጠት ትጀምራለህ፡፡
ይህንን ለውጥ እውን ለማድረግ እግዚአብሔር በሉአላዊነቱ የሚወስደው ሃላፊነት እንዳለ ሆኖ፣ ቀሪው ድርሻ ግን ያንተው የራስህ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር የቅድሚያ ድርሻውን ወስዷል፡- ‹‹የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም…።›› (ዮሐንስ 6፡44)፡፡ እግዚአብሔር ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ጥያቄዎች በመጠየቅ ያለማቋረጥ የልቦቻችንን ደጆች እያንኳኳ ነው፡-
- ይህንን እንድሰጥህ ትፈቅድልኛለህ?
- ይህንን ጉዳይ እንዳስተካክል ትፈቅድልኛለህ?
- ያንን ጉዳይ እንድለውጥ ትፈቅድልኛለህ?
- ይህንን እንድጨምር ትፈቅድልኛለህ?
- ያንን እንዳስወግድ ትፈቅድልኛለህ?
እነዚህን ጥያቄዎች የምንመልስበት ሁኔታ፣ በመንፈሳዊ ብስለት ጉዞአችን ፍጥነት፣ ጥልቀት እና ውጤት ላይ ጠንካራ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ አዎንታዊ በሆነ መንገድ ለጥያቄዎቹ ምላሽ ስንሰጥ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ሕብረት እየጠበቀ ይመጣል፣ እድገታችንም አስተማማኝ ይሆናል፡፡ አሉታዊ በሆነ መንገድ ምላሽ ስንሰጥ ደግሞ እድገታችን ይገታል፡፡ ይህ ምንኛ እግዚአብሔርን ያሳዝን ይሆን? እርሱ ሊሰጠን፣ ሊያደርግልን እና ከእኛ ጋር ሕብረት ሊያደርግ የሚሻባቸው በርካታ ነገሮች አሉ! እነዚህን ነገሮች ወደጎን በመተው በእኛ ሕይወት ላይ ያለውን ድርሻ ብንቃወም፣ አያስገድደንም፡፡ ወደ እርሱ ሃሳብ በመምጣት ልባችንን ከፍተን በፍቅርና በመታዘዝ ምላሽ እስክንሰጠው ድረስ በሕይወታችን ደጃፍ ላይ ሆኖ በትዕግስት ይጠብቀናል እንጂ፡፡
የዚህ ደቀ መዝሙር ትምሕርት ጥናት አቢይ አላማ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ሊያደርጋቸው የሚፈልገውን ሕብረት ማሳወቅና ለእነዚህም ጥያቄዎቹ ቀና ምላሽ እንድትሰጥ መርዳት ነው፡፡ ጥናቱን በምታደርግበት ወቅት ሁሉ፣ የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ በል፡-
- እግዚአብሔር በእውቀት ብቻ እንድታድግ አይፈልግም፡፡ በዚህ ጥናት አማካኝነት ከእርሱ የምትማራቸው እውነቶች ከአይምሮህ አልፈው ወደ ልብህ በመዝለቅ የፅኑ አቋሞችህ አካሎች እንዲሆኑ ፍቀድ፡፡ እነዚህ አቋሞችህ ደግሞ በእጆችህ፣ በእግሮችህ እና በአንደበትህ አማካኝነት ተግባራዊ ልምምድ ያግኙ፡፡ እግዚአብሔር ጭንቅላትህን በእውቀት ለማጨቅ ሳይሆን ሕይወትህን ለመለወጥ ይሻል!
- መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና፣ እግዚአብሔር አንዳንድ ጠቃሚ ውሳኔዎችን እንድታደርግ ይጠይቅሃል፡፡ እነዚህን ውሳኔዎች እንድታደርግ ማንም አያስገድድህም፡፡ ይህ ጉዳይ በአንተና በእግዚአብሔር መካከል የሚቀር ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር ልብ በል፡- ውሳኔ እንድታደርግ በሚጠይቅህ ጊዜ ውሳኔ አለማድረግ፣ በራሱ ውሳኔውን ያለመቀበል ውሳኔ ነው፡፡
- የዘላለም ሕይወታችንን በሞላ እግዚአብሔርን በማወቅ እናሳልፋለን (ዮሐንስ 17፡3)፡፡ ይህም ጥናት ይህንኑ ሂደት ያግዛል፡፡ በዚህ ጥናት ጉዞህ ውስጥ ‹‹ትምህርቱን ማጠናቀቅ›› የጥናትህ ግብህ አይሁን፡፡ ግብህ ‹‹እግዚአብሔርን የበለጠ ማወቅ›› ይሁን፡፡ እያንዳንዱን ትምህርት ከመጀመርህ በፊት የሚከተለውን አጭር ጸሎት ፀልይ፡- ‹‹አባት ሆይ፣ ዛሬ ምን ልታስተምረኝ ትወዳለህ?
- ይህንን ተከታታይ የደቀ መዝሙር ትምህርት ካጠናቀቅህ በኃላ እድገትህን እንደጨረስክ ፈፅሞ አታስብ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ቁልፍ ቁርኝቶችን ትመሰርታለህ አልያም አስቀድሞ የነበረህን ታጸናለህ – ያም ሆነ ይህ ጉዞው ጅማሬህ እንጂ ፍፃሜህ አይደለም፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ፣ የሕይወት ዘመን ቆራጥ ‹‹ተማሪ›› ለመሆን ወስን፡፡
ከየት ልጀምር?
አስቀድሞ ኢላማ ባልተበጀለት ነገር ላይ ቀስትህን ደግነህ ብትወረውር ግብህ መምታቱን በምን ታረጋግጣለህ? አነጣጥረን ከመተኮሳችን በፊት ጥቂት አላማዎችን ከፊታችን ማስቀመጥ ውጤታማ ለመሆን የግድ ነው!
ከእግዚአብሔር ጋር ያልህ ሕብረት ምን ይመስላል? የትኞቹ ሕብረቶችህ ደካሞዎች ናቸው? የትኞቹስ ጠንካሮች ናቸው? የት ቦታ ላይ ነው ያንተን ከፍተኛ ትኩረት የሚሻው፣ የትኛውስ ቦታ ላይ ነው መጠነኛ ጥገና የሚፈልገው? በአሁኑ ሰአት ምን አይነት ወሳኝ መንፈሳዊ ፍላጎት ወይም ጥያቄ አለህ? እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ከዚህ በታች የቀረበውን የግለሰብ መገምገሚ መጠይቅ ሙላ፡፡ ይህ ግላዊ ምዘና አስተማሪና አበረታታች ሆኖ እንደምታገኘው ተስፋ እናደርጋለን፡፡
የአጠናን አማራጮች፡-
በግል፡፡ ጥናቱን በቅደም ተከተል ጨርስ አልያም በፍላጎትህ መሠረት ያለ ቅደም ተከተል አጥና፡፡ ከእያንዳንዱ ጥናት በኃላ የቀረቡትን ጥያቄዎች ሥራ፡፡ መልሶችህን ፃፋቸው፣ ይህ ሂደት ሃሳቦች ቅርፅ እንዲይዙ ይረዳሃል፡፡
በቡድን፡፡ መጀመሪያ እያንዳንዱ የቡድኑ አባል በግል ጥናቱን ያድርግ፡፡ በመቀጠልም የቀረቡትን ጥያቄዎች በጋራ ስሯቸው። የቡድኑ አባላት ‹‹ለቤት ሥራ›› ጊዜ የማይኖራቸው ከሆነ ጥናቱንም ሆነ ጥያቄዎቹን በጋራ መስራት ይችላሉ፡፡
አንድ ምእራፍ ለማጥናት ከአንድ በላይ ክፍለ ጊዜ ሊያስፈልግ ይችል ይሆናል፡፡ በአጭሩ፣ እነዚህ ጥናቶች የምትገለገልባቸው አገልጋዮችህ እንጂ አዛዞችህ ሊሆኑ አይገባም!
ራስን የመገምገሚያ መጠይቅ
ግምገማውን መተርጎም
እያንዳንዱ ጥያቄ በምታጠናው 11 ምእራፎች ውስጥ ምላሽ ያገኛሉ፡፡ 1 እና 2 የሚሉ መልሶች የሰጠህባቸው ምእራፎች፣ ይበልጥ ትኩረት ሰጥተህ ልታጠናቸው የሚያስፈልጉህን ርዕሰ ጉዳዮች ያመለክቱሃል። 4 እና 5 የሚሉ መልሶች በርከት ብለው የሚገኙበት ምዕራፎች ደግሞ የመንፈሳዊ ጥንካሬ አካባቢዎችህን ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ ጥናት ውስጥ የቀረቡትን ትምሕርቶች ከ ምዕራፍ 1 ጀምረህ እስከ ምዕራፍ 11 ድረስ በቅደም ተከተል ማጥናት ትችላለህ። አልያም መጠይቁን በመጠቀም ያደረከውን ግምገማ በመንተራስ ቅድሚያ ሊያገኙ የሚገባቸውን የሕይወትህን ፍላጎቶች መሠረት አድርገህ ጥናቱን ልታካሂድ ትችላለህ፡፡ 3 እና 4 ምላሾች በስፋት የሚገኙባቸው ምእራፎች የሚያመለክቱት፣ በሕይወትህ በከፊል ስፍራ ያገኙትንና ሊጎለብቱ የሚገባቸውን ነገሮች ነው፡፡ በአንዳንድ ምዕራፎች ስር ለቀረቡ ጥያቄዎች የተሰጠው ምላሽ በአብዛኛው 5 ሆኖ ብታገኝም፣ በምእራፎቹ ሥር ከቀረቡት ጥናቶች ተጨማሪ ግብአት አላገኘም የሚል መደምደሚያ ላይ ልትደርስ አይገባም፡፡
ማውጫ
ምዕራፍ 1 – ስለ መዳንህ ምን ያህል እርገጠኛ ነህ?
ምዕራፍ 2 – በድነት ወቅት ምን ሆነልህ?
ምዕራፍ 3 – የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት
ምዕራፍ 4 – አሮጌውን ሰው ችላ ማለት
ምዕራፍ 5 – መንፈሳዊ እድገትን የሚረዱ ተግባራትና ዝንባሌዎች
ምዕራፍ 6 – ሕብረት
ምዕራፍ 7 – የእግዚአብሔር ቃል
ምዕራፍ 8 – ጸሎት
ምዕራፍ 9 – ምስክርነት
ምዕራፍ 10- መንፈሳዊ ውጊያ
ምዕራፍ 11- የጊዜ አጠቃቀም
______________________________________________________________
ከላይ ያሉትን 11 ትምሕርቶች ካጠኑ በኋላ ከዚህ በታች ያሉትን የደቀ ምዝሙር ስልጠና ትምሕርቶች እንዲያጠኑ እናበረታታዎታለን።
የኢየሱስን ፍቅር ተረድተህ፣ ከዛም በእርሱ ሞትና ትንሳኤ በማመን ከዳንክ በኋላ ሕይወትህን በገዛ ፈቃድህ እንድትመራ የእግዚአብሔር ሃሳብ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ “…በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።” ይላል። ኢየሱስን ጌታ ብለሃል እና ከእንግዲህ የራስህ ጌታ አይደለህም። ከኃጢአት ባርነት ነፃ ወጥተህ የክርስቶስ ባሪያ ሆነሃል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፣ “ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ”። ለራስህ ፍላጎት ሞተህ የእርሱን ፍላጎት በምድር ላይ ለመኖር ሕያው ሆነሃል። ኢየሱስን በሕይወትህ ላይ ጌታ እንዲሆን ስትሾም፣ የሕይወት ዘመን የክርስቶስ ተከታይ/ደቀ መዝሙር ለመሆን ቃል ገብተሃል። “ደቀ መዝሙሩ ለመሆን ምን ልማር?”፣ “እንዴት ልሰልጥን?”፣ “ምን ላድርግ?” ወዘተ፣ የሚል ጥያቄ ውስጥህ ከመጣ፣ ስጋት አይግባህ። በዚህ ድረ-ገጽ ውስጥ እነዚህን እና መሰል ጥያቄዎችህን የሚመልሱ የማሰልጠኛ ማኑዋሎች ተዘጋጅተውልሃል። ከዚሀ በታች ያሉትን ሊንኮች መመጫን ጥናትህን እንድትቀጥል በአክብሮት እንጋብዝሃለን።
ግለሰብ ተኮር የደቀመዝሙር ማሰልጠኛ መጽሐፍ.doc
አስተያየት፣ ጥያቄና ሃሳብ ካሎት ከዚህ በታች ባለው ፎርም ቢልኩልን በደስታ እናስተናግዳለን።