እስልምና

ከክርስትና ውጪ፣ ሐይማኖቱን በሚሽን/በተልዕኮ በአለም ላይ ለማስፋፋት ጥረት የሚያደርግ ብቸኛ ሐይማኖት እስልምና ነው፡፡ የእስልምና እምነት አራማጆች የመጨረሻ ግብ አለምን በእስልምና መሸፈን መሆኑ ምስጢር አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ሙስሊም፣ ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎችን ወደ እምነቱ መጥራትና፣ የሙሐመድ አስተምህሮዎችንና የሐይማኖቱን መሠረታዊ መመሪያዎች የመፈፀም ግዳጅ አለበት፡፡ ይህ፣ ከሐይማኖቱ ውጪ ያሉ ሰዎችን ወደ እምነቱ የመጋበዝ ሥራ ዳዋ (dawah) በመባል ይታወቃል፡፡

ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ አንዳንድ ሙስሊሞች በዚህ የመነቃቃት ወኔ በመነዳት የሐይማኖታቸውን ታላቅነት ለማሳየት በክርስትናና በአስተምህሮቱ ላይ በጭካኔ የተሞላ ጥቃት እያደረሱ ይገኛሉ፡፡ ማንም ሊገነዘበው እንደሚችል ይህ አይነቱ ግብዣ ሰውን በማክበርና በትህትና ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ በሌላው ሰው የተቀደሰ እምነት እና ልማዶች ላይ የሚካሄድ እንዲህ አይነቱ በጭካኔ የተሞላ አቀራረብ ጥላቻና አለመረጋጋትን ከመፍጠር የዘለለ ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ አንዳንድ ስሜታዊ ክርስቲያኖችም የዚህ ችግር አካሎች እንደነበሩ መደበቅ አስፈላጊ አይመስለንም፡፡

ከሙስሊሞች ጋር በሚኖርህ ግንኙነት ወቅት፣ ሆን ብለውም ሆነ ባለማወቅ ሃይማኖታቸውንና ነቢያቸውን ስለተሳደቡ ክርስቲያኖች ይቅርታ ለመጠየቅ ወደኋላ አትበል፡፡ የቁርአን አስተምህሮዎችን ሁሉ የማትቀበል ቢሆንም እንኳ፣ አንተ ሙስሞችን ከሚወዱና ቁርአን ከሚያወድሳቸው ከእውነተኞቹ የኢየሱስ ተከታዮች መካከል እንደሆንክ ራስህን ልታስመሰክር ይገባል፡፡ ቃልህና ተግባርህ በአንዱ – በአብርሃም፣ በይስሃቅና በያዕቆብ አምላክ የምታምንና ለእርሱም ፈቃድ የምትገዛ መሆንህን ለሙስሊም ወዳጅህ ሊመሰክሩለት ይገባል፡፡ ለመማር የተሰጠህ፣ ከአለማዊ እሥራቶች የተፈታህ፣ ትሁት፣ እግዚአብሔርን የምታገለግል፣ በጠላት ላይ የእግዚአብሔርን ኃይል የምትለማመድ፣ እስከ መጨረሻው የምትፀናና የምትበረታ በተጨማሪም ለሰው ልጆች ሁሉ ርህራሄና ምህረት ያለህ መሆንህን በፍቅር የምትገልጥለት ሁን፡፡ በእነዚህ ሁኔታ ራስህን የምትገልጥ ከሆንህ የሙስሊም ሕዝቦችን የልብ በር ለማግኘትና ለማገልገል ያለጥርጥር ተሳካልህ ማለት ነው፡፡

ከዚህ ጋር አያይዘን፣ ይህ መጽሐፍ የሙስሊሞችን አስተምህሮ በማጥቃት ወይም የጥቃት ምላሽ በመስጠት መንፈስ አለመቅረቡን በአፅንኦት ልንገልጽ እንወዳለን፡፡ ይህ መጽሐፍ እንደ ክርክር ማጣቀሻ ጽሑፍ ተደርጎ በሚነበብበት አቅጣጫም አልተጻፈም፡፡ አስተውል፣ እንደ እውነተኛ የጌታ ኢየሱስ ተከታይ ለሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ማሳሰቢያ ልብህን ልትሰጥ ይገባል፡-

በቀጣዮቹ ገጾች ውስጥ ያሉ ፍሬ አሳቦች በክርስቲያኑ ማህበረሰብ መካከል ጥርጥርና ግራ መጋባት ለመፍጠር፣ በክርክር አዋቂ ሙስሊም ሊቃናት ያለማቋረጥ በሚደረገው ዘመቻ ለሚደናገሩ አማኞች መረጃ በማቅረብ ረገድ የራሱ የሆነ ጠቀሜታ እንደሚኖረው እምነታችን ነው፡፡ የተሻለው ግን ክርስቲያኖች፣ ጥብቅና የሚቆሙለትን እውነት ለሌሎች ለመመስከርና ለማረጋገጥ የሚበጀው ብቸኛው መንገድ ይህን እውነት በሕይወት መኖር/መግለጥ መሆኑን ማወቅ አስፈላጊ ነው! በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ መከባበርን ማስፈንና ወዳጅ መሆን ከማንኛውም እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ የሚጠበቅ ስነምግባር ነው፡፡ የቃላት ጥቃትና መልሶ ማጥቃት መጨረሻው፣ ሽንፈት ብቻ ነው፡፡ የዚህም ነገር የሩቅ ጊዜ ውጤት፣ ቅሬታና ብስጭት ከመፍጠር የዘለለ አይሆንም፡፡ በትህትና እየኖሩ በየዕለቱ የሰውን ጠንካራ ልብ ሊያሸንፍ የሚችለውን የክርስቶስን ፍቅር እያሳዩ ከመኖር በቀር፣ የሙስሊም ወዳጆችን ለማፍራት ምን የተሻለ መንገድ ሊኖረን ይችል ይሆን?

በዚህ መጽሐፍ ስር የቀረቡ መረጃዎች፣ በወዳጅነት እና በጋር መከባበር ላይ በተመሠረተ የግንኙነት አቀራረብ ጥቅም ላይ እስከዋሉ ድረስ፣ በቅንነት እውነትን ለማወቅ ለሚሹ የሙስሊም ጠያቂዎች መልስ ለመስጠት ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ እምነታችን ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ በግልፅ፣ እምነትን የመነጋገር ሂደት ሙስሊም ወዳጅዎ የመጽሐፍ ቅዱስን ጥልቅ እውነቶች ለመመርመር እንዲነሳሳ ያግዘዋል፡፡ የዚህ ፍጻሜው ደግሞ በመሲሁ ኢየሱስ የሚገኘውን ደኅንነት የማወቅ እድል መፍጠር ይሆናል፡፡

እውነተኛዎቹ የኢየሱስ ተከታዮች በታሪክ በመሳሪያም ሆነ በቃል ጦርነት ውስጥ ራሳቸውን አላሳተፉም፡፡ በእዚህ ፈንታ አለማዊ ግቦቻቸውን ወደጎን በማድረግ ወንጌልን ለአለም ለማድረስ ራሳቸውን ሰጡ እንጂ፡፡ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ታማኝ በመሆን የክርስቶስን ፍቅር መግለጥ፣ በስሙም የሚገኘውን ደኅንነትና የኃጢአት ስርየት መስበክ ዋነኛ ተልዕኮአቸው ነበር፡፡ ማንንም አልኮነኑም፣ አይኮንኑምም፡፡ ከእዚህ ይልቅ እንደ ክርስቶስ አምባሳደሮች፣ ሰዎች እርስ በእርሳቸው እና ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ የማስታረቅን አገልግሎትን ሊያውጁ ተገባቸው! ይህንን ክቡር ተጋድሎ እግዚአብሔር ይባርክ፡፡ መጽሐፉን ለማንበብ ለሙስሊም ወዳጆቻችን ጥያቄዎች የተሰጠ ምላሽ የሚለውን ከዚህ በታች ያለውን ሊንክ ይጫኑ። መለካም ንባብ።

ለሙስሊም ወዳጆቻችን ጥያቄዎች የተሰጠ ምላሽ

አስተያየት፣ ጥያቄና ሃሳብ ካሎት ከዚህ በታች ባለው ፎርም ቢልኩልን በደስታ እናስተናግዳለን።