የሉቃስ ወንጌል የጥናት መምሪያና ማብራሪያ
ምልከታ እና ትርጓሜ
የመለኮታዊ ርኅራኄና የኃጢአት ስርየት ሥልጣን
የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ አምስት ከቁጥር 12 እስከ 26 ያለው ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የታመሙትን ከመፈወስ ባለፈ የነፍስን ደዌ (ኃጢአትን) ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው የሚያሳይ ድንቅ ታሪክ ነው። በዚህ ክፍል ውስጥ ሁለት የተለያዩ ሰዎችን እናገኛለን፤ አንደኛው በሕብረተሰቡ የተገለለ ለምጻም ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በጓደኞቹ እገዛ የቀረበ ሽባ ሰው ነው። ሁለቱም ታሪኮች የእግዚአብሔርን ጸጋና የክርስቶስን አዳኝነተ በጉልህ ያሳያሉ።
ለምጻሙና የጌታ ፈቃድ
ጌታችን በአንድ ከተማ ሳለ ሰውነቱ በለምጽ የተወረረ አንድ ሰው መጣ። በዚያ ዘመን ለምጽ የሥጋ በሽታ ብቻ ሳይሆን ሰውን ከማኅበራዊና ከሃይማኖታዊ ሕይወት የሚለይ፣ እንደ ርኩስ የሚቆጠር በሽታ ነበር። ይህ ሰው በኢየሱስ ፊት በግንባሩ ተደፍቶ “ጌታ ሆይ፥ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” በማለት ለመነው። ይህ ልመና የጌታን ኃይል ሙሉ በሙሉ አምኖ ነገር ግን ለጌታ ፈቃድ ራሱን ያስገዛ የትሕትና ልመና ነው። ጌታችንም እጁን ዘርግቶ ዳሰሰውና “እወዳለሁ ንጻ” አለው። ጌታችን ለምጻሙን መዳሰሱ በሕግ ርኩስ ሊያደርገው ቢችልም፣ እርሱ ግን ቅዱስ ስለሆነ ርኩሰቱን በቅድስናው ለወጠው። ወዲያውም ለምጹ ለቀቀው። ጌታችንም ለካህን ራሱን እንዲያሳይና ለንጽሕናውም መሥዋዕት እንዲያቀርብ አዘዘው፤ ይህም ጌታችን ለሙሴ ሕግ ያለውን አክብሮት ያሳያል። የኢየሱስ ዝና ከቀን ወደ ቀን እየናኘ ቢሄድም፣ እርሱ ግን በጸሎት ከሰማያዊ አባቱ ጋር ለመገናኘት ወደ ምድረ በዳ ፈቀቅ ይል ነበር።
ሽባውና የኃጢአት ስርየት ምስጢር
በሌላ ቀን ኢየሱስ እያስተማረ ሳለ ከየከተማው የመጡ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ተቀምጠው ነበር። ሰዎችንም የሚፈውስበት የጌታ ኃይል ከእርሱ ጋር ነበረ። በዚህ መካከከል አራት ሰዎች አንድ ሽባ ሰው በአልጋ ተሸክመው አመጡ፤ ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ የሚገቡበት ስላጡ ግን ወደ ጣሪያው ወጡ። የቤቱን ጣሪያ አፍርሰው ሽባውን ሰው ከአልጋው ጋር በኢየሱስ ፊት አወረዱት። ይህ ተግባር የሰዎቹን ጽኑ እምነትና ለጓደኛቸው የነበራቸውን ፍቅር ያሳያል። ጌታችንም እምነታቸውን አይቶ ለሽባው ሰው “አንተ ሰው፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ” አለው።
ይህ የጌታ ንግግር በዚያ ለነበሩት ጻፎችና ፈሪሳውያን ትልቅ ድንጋጤን ፈጠረ። “በእግዚአብሔር ላይ የሚሳደብ ይህ ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል?” በማለት በልባቸው አሰቡ። ጌታችንም የልባቸውን አሳብ አውቆ “ኃጢአትህ ተሰረየችልህ” ከማለትና “ተነሳና ሂድ” ከማለት የትኛው ይቀላል? በማለት ጠየቃቸው። ለሰው ልጅ ኃጢአት ተሰረየ ማለት በዓይን ስለማይታይ ቀላል ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን ጌታችን በምድር ላይ ኃጢአትን ለማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው እንዲያውቁ ሽባውን ሰው “ተነሳና አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ” አለው። ሰውየውም ወዲያው በፊታቸው ተነስቶ እግዚአብሔርን እያከበረ ወደ ቤቱ ሄደ።
በዚህ ክፍል ውስጥ የምንማረው ዋናው ቁምነገር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሥጋን ደዌ ብቻ ሳይሆን የነፍስን በሽታ የሚፈውስ መሆኑን ነው። ፈሪሳውያን እንዳሉት ኃጢአትን ይቅር ማለት የእግዚአብሔር ብቻ ሥልጣን ከሆነ፣ ኢየሱስ ኃጢአትን ይቅር ማለቱና በተአምራት ማረጋገጡ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን የሚያሳይ ነው። ክርስቶስ ወደ እኛ የመጣው ሙሉ ሰብዓዊነታችንን ለመፈወስ ነው፤ ሥጋችን ከሕመም፣ ነፍሳችን ደግሞ ከኃጢአት እስራት ነፃ እንድትወጣ ይፈልጋል። እኛም እንደ ሽባው ጓደኞች ሌሎችን ወደ ክርስቶስ የምናመጣ፣ እንደ ለምጻሙም በጌታ ፈቃድ ስር የምንገዛ ልብ ሊኖረን ይገባል።
ተግባራዊ የውይይት ጥያቄዎች
👉ኢየሱስ ለምጻሙን በእጁ መንካቱ (ቁ. 13) ስለ እግዚአብሔር ፍቅርና ማህበራዊ መገለልን ስለማጥፋት ምን ይናገራል?
👉የሽባው ሰው ጓደኞች የነበራቸው ጽኑ እምነትና ጥረት (ቁ. 19) ለኛ ምን አይነት አርአያነት አለው?
👉ኢየሱስ ከአካላዊ ፈውስ በፊት የኃጢአት ይቅርታን የሰጠው ለምንድን ነው?
👉የጸሐፍት ተቃውሞ የኢየሱስን መለኮታዊ ማንነት በተዘዋዋሪ ያረጋገጠው እንዴት ነው?
👉ሽባው አልጋውን ተሸክሞ መሄዱ የተሟላ የፈውስና የለውጥ ምልክት የሆነው እንዴት ነው?
👉በሕይወታችን ውስጥ ትልቁ ሽባነት ኃጢአት መሆኑን ይህ ታሪክ እንዴት ያስረዳናል?
👉ኢየሱስ ለምጻሙን ወደ ካህን እንዲሄድ ማዘዙ ለሃይማኖታዊ ሥርዓት ያለውን ክብር እንዴት ያሳያል?
👉ሕዝቡ “ዛሬ አስገራሚ ነገር አየን” ብለው እግዚአብሔርን ማመስገናቸው ተአምራት ለሚፈጥሩት አምልኮ ምን ማሳያ ነው?