የሉቃስ ወንጌል የጥናት መምሪያና ማብራሪያ
ምልከታ እና ትርጓሜ
በዚህ የክፍል ጥናት ውስጥ መጥምቁ ዮሐንስ በወኅኒ ሳለ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥራዎች በሰማ ጊዜ ያደረገውን ጥያቄና ጌታችን የሰጠውን ጥልቅ ምላሽ እንመለከታለን። ዮሐንስ ሁለት ደቀ መዛሙርቱን ወደ ኢየሱስ ልኮ “የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” በማለት ጠየቀ። ይህ ጥያቄ ዮሐንስ በእምነቱ ስለደከመ ሳይሆን፣ ምናልባትም የመሲሑን መገለጥና ፍርድ በሌላ መንገድ ይጠብቅ ስለነበር ማረጋገጫ ለመፈለግ ያደረገው ሳይሆን አይቀርም። ጌታችን ግን ለጥያቄው በቃላት ብቻ “አዎ” ብሎ ከመመለስ ይልቅ፣ በዚያች ሰዓት ያደረጋቸውን ተአምራት እንደ ምስክር አቀረበ። ዕውሮች እንዲያዩ፣ አንካሶች እንዲሄዱ፣ ለምጻሞች እንዲነጹ፣ ደንቆሮዎች እንዲሰሙ፣ ሙታንም እንዲነሱ በማድረግና ለድሆችም ወንጌል እንዲሰበክ በማድረግ መሲሕነቱን በተግባር አረጋገጠ። ይህ ድርጊት ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ መሲሑ የተነበየውን ትንቢት በቀጥታ የሚፈጽም ነበር።
የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ከሄዱ በኋላ ጌታችን ስለ ዮሐንስ ማንነት ለሕዝቡ መመስከር ጀመረ። ሕዝቡ ወደ ምድረ በዳ የሄዱት በነፋስ የሚወዘወዝ ሸምበቆን ወይም በለሰለሰ ልብስ ያጌጠ ሰውን ለማየት እንዳልሆነ፣ ይልቁንም ከነቢይ የሚበልጠውን ለማየት እንደነበር ገለጸ። ዮሐንስ በሴቶች ከተወለዱት ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ነቢይ መሆኑንና እርሱም “እነሆ መንገድህን የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ” ተብሎ የተነገረለት መሆኑን አረጋገጠ። ሆኖም ግን በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚያንሰው ከዮሐንስ እንደሚበልጥ በመናገር፣ የአዲሱ ኪዳን በረከትና በክርስቶስ የምናገኘው ጸጋ ምን ያህል ታላቅ መሆኑን አመለከተ። ይህም በብሉይ ኪዳን የመጨረሻ ነቢይና በአዲሱ ኪዳን መባቻ መካከል ያለውን ልዩነት ያሳያል።
በመቀጠልም ጌታችን በወቅቱ የነበረውን ትውልድ አስቸጋሪ ባሕርይ በምሳሌ ገለጠ። ያንን ትውልድ በገበያ ተቀምጠው “እንቢልታ ነፋንላችሁ አልዘፈናችሁም፣ ሙሾ አወጣንላችሁ አላለቀሳችሁም” እንደሚሉ ልጆች መስሏቸዋል። መጥምቁ ዮሐንስ እንጀራ ሳይበላና የወይን ጠጅ ሳይጠጣ በመምጣቱ “ጋኔን አለበት” አሉት፤ የሰው ልጅ ደግሞ እየበላና እየጠጣ በመምጣቱ “በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጪ፣ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ” አሉት። ይህ የሚያሳየው ሰዎች እውነትን ለመቀበል ልባቸው ዝግ በሚሆንበት ጊዜ፣ ምንም ዓይነት መንገድ ቢመጣላቸው ሰበብ ከመፈለግ እንደማይቦዝኑ ነው። እግዚአብሔር ግን በጥበቡ የሚመላለሱትንና ቃሉን የሚቀበሉትን ያጸድቃል።
የዮሐንስ ጥያቄና የጌታ ምስክርነት የሚያስተምረን ዋናው ቁምነገር፣ እግዚአብሔርን የምናውቀውና የምንረዳው እርሱ በሚያደርገው ሥራና በቃሉ አማካኝነት መሆኑን ነው። አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎች እኛ ከጠበቅነው በተለየ መንገድ ሊሄዱ ይችላሉ፤ ነገር ግን የጌታ ቃልና ሥራው ሁልጊዜ እውነተኛ መሆናቸውን ማመን ይኖርብናል። ዮሐንስ መንገዱን ጠርጓል፣ ክርስቶስ ደግሞ በሥራውና በትምህርቱ ድኅነትን አምጥቷል። እኛም የክርስቶስን ወዳጅነትና የጸጋውን ጥሪ በደስታ ልንቀበለው ይገባል።
ተግባራዊ የውይይት ጥያቄዎች
👉ዮሐንስ እንዲህ ያለ የጥርጣሬ ጥያቄ የጠየቀው በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ስለነበረ ይመስላችኋል?
👉ኢየሱስ ለዮሐንስ የሰጠው ምላሽ (ቁ. 22) ከኢሳያስ ትንቢቶች ጋር እንዴት ይያያዛል?
👉“ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ የለም” መባሉ ስለ ዮሐንስ ስፍራ ምን ይናገራል?
👉በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚያንሰው ከዮሐንስ የሚበልጠው በምን ረገድ ነው?
👉የዚያ ትውልድ ሰዎች ዮሐንስንም ሆነ ኢየሱስን ባለመቀበላቸው የተመሰሉበት መንገድ (ቁ. 32) ምን ያሳያል?
👉“ጥበብ በልጆቿ ሁሉ ጸደቀች” (ቁ. 35) የሚለው ቃል ትርጉሙ ምንድን ነው?
👉ፈሪሳውያንና የሕግ አዋቂዎች የእግዚአብሔርን ምክር ለራሳቸው የናቁት እንዴት ነበር?
👉ቀራጮችና ሕዝቡ ዮሐንስን በማመናቸው እግዚአብሔርን ያጸደቁት (ቁ. 29) በምን መንገድ ነው?