ስለ መንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች መግቢያ

ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 12፡1 አንብብ። ሀ) ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ቸል እንዳይሉ ወይም እንዲያውቁ ይፈልግ የነበረው ነገር ምን ነበር? ለ) ዛሬም ክርስቲያኖች በተመሳሳይ መንገድ ቸልተኛ የሆኑበት ወይም የማያውቁት ነገር አለን? መልስህን አብራራ ሐ) በቤተ ክርስቲያንህ መንፈሳዊ ስጦታዎች ያሏቸውን አንዳንድ ሰዎች ጥቀስ። አንዳንድ መንፈሳዊ ስጦታዎች እንዳሏቸው እንድታምን ያደረገህ በሕይወታቸው ያየኸው ነገር ምንድን ነው? መ) አብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ስጦታዎቻቸውን እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ እየተጠቀሙ ይመስልሃልን? መልስህን አብራራ። 

እግዚአብሔር በእኛ በልጆቹ ላይ በርካታ ስጦታዎችን አፍስሷል። ከድነት (ደኅንነት) ሌላ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ከተቀበልነው ሁሉ ታላቁ ነው። መንፈስ ቅዱስ በልባችን ስላሚኖር ሁሉ ነገራችን ይለወጣል። የእግዚአብሔር ጠላቶች የነበርን እኛ ልጆቹ እንሆናለን። የቀድሞ አባታችን የነበረውን ዲያብሎስን ከመምሰል አሁን አባታችን የሆነውን እግዚአብሔርን ወደ መምሰል እንለወጣለን። የእግዚአብሔር ልዩ ልጅ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንመስል ዘንድ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ሁልጊዜ ይሠራል። እንደ ኢየሱስ እንድንኖር፥ እንደ ኢየሱስ ተግባራችንን እንድናከናውንና እንደ ኢየሱስ እንድንሠራ ይረዳናል። በምስክርነታችን፥ በአምልኮአችንና በጸሎታችን ባለን የሕይወት ዘርፍ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ሊረዳን ከእኛ ጋር አለ። ምን ዓይነት ወዳጅ ነው ያለን! መንፈስ ቅዱስ እጅግ በጥልቀት በሕይወታችን ከሚሠራቸው ነገሮች አንዱ የክርስቶስ አካል የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን እናገለግል ዘንድ መንፈሳዊ ስጦታዎችን መስጠቱ ነው። 

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአሳብ ልዩነት ምክንያት ከፍተኛ ክርክር ከሚካሄድባቸው ርእሶች እንዱ የመንፈሳዊ ስጦታዎች ጉዳይ ነው። በአንድ በኩል የመንፈሳዊ ስጦታዎችን ጉዳይ የሚያናንቁ ክፍሎች አሉ። ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች ሲናገሩ ወይም ሲያስተምሩ አይታዩም። ከዚህም የተነሣ፥ በቤተ ክርስቲያናቸው መንፈሳዊ ስጦታዎች በአገልግሎት ላይ አይውሉም። ስለዚህ ጥቂት ሰዎች ብቻ መሪ የሚሆኑበትና የሚያገላግሉበት፥ አብዛኞቹ ግን ተሳትፎ ሳያደርጉ ዳር ቆመው የሚያዩበት ቤተ ክርስቲያን ሆኖ ይቀራል። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት በአምልኮአቸው ወይም በአገልግሎታቸው ያለው መንፈሳዊ ኃይል አነስተኛ ነው። 

በሌላኛው ጽንፍ ደግሞ በመንፈሳዊ ስጦታዎች በተለይ በድንቃ ድንቅ የታጀቡ መንፈሳዊ ስጦታዎች የሚያስደስቷቸው ይገኛሉ። ትኩረት የሚያደርጉበት የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ይህ ብቻ ነው። ለመንፈስ ቅዱስ ህልውና ብቸኛ ማረጋገጫ የሚሆኑት መንፈሳዊ ስጦታዎች፥ በተለይም በልሳን እንደ መናገር ያሉ ትኩረት የሚስቡ ሁኔታዎች ናቸው፤ እነዚህ ነገሮች ከሌሉ መንፈስ ቅዱስ አላ ማለት አይቻልም ብለው ያስተምራሉ። 

እነዚህ ሁለቱም ክፍሎች ሚዛናዊ ስላልሆኑ ለቤተ ክርስቲያን አደገኞች ናቸው። እንደገና ማስታወስ ያለብን የክርስቲያን ሕይወት ሚዛናዊ መሆኑን ነው። መንፈሳዊ ስጦታዎችን መካድ ወይም መገደብ ስሕተት ሲሆን ይህን ስናደርግ መንፈስ ቅዱስ በክርስቶስ አካል ውስጥ የሚሠራውን የመገንባት ሥራ እናስተጓጉላላን። በመንፈሳዊ ስጦታዎች እጅግ በመፈንደቅ በመንፈስ ቅዱስ ላይም ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚሰጡ ሌሎች ትምህርቶች እኩል ትኩረት አለመስጠት ስሕተት ነው። 

ጥያቄ፡ ሀ) በኢትዮጵያ በምትገኝ በዛሬይቱ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ሁላት ዝንባሌዎች የምታየው እንዴት ነው? ላ) ይህ ሚዛናዊነት ማጣት ምን ምን ችግሮችን ፈጠረ? 

ይህ ጉዳይ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እጅግ የሚከፋፍል ርእስ ስለሆነ በሚቀጥሉት በርካታ ሳምንታት አዲስ ኪዳን ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች የሚያስተምረውን እንመለከታለን። መንፈሳዊ ስጦታዎች ስለ ነበራቸው ሰዎች ብሉይ ኪዳን የሚጠቃቅስ ቢሆንም መንፈሳዊ ስጦታዎች ምን እንደሆኑና እንዴት ልንገለገልባቸው እንደሚገባ ብዙ አሳብ አልተሰጠም። ለዚህ ትምህርት የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች በተለይ ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ ባለውላታችን ነው። 

ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት። ሮሜ 12፡1-8፤ ኤፌ. 4፡1-16፤ 1ኛ ጴጥ. 4፡7-11 ። እነዚህ ጥቅሶች እያንዳንዳቸው መንፈስ ቅዱስ መንፈሳዊ ስጦታዎችን በመስጠት ላላለው ሚና ምን ያስተምራሉ? 

መንፈስ ቅዱስ የመንፈሳዊ ስጦታዎች ሰጪ 

መንፈስ ቅዱስ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች እንዱ አንድ ሰው ወደ ክርስትና ሲመጣ ሰውዬውን ወደ ክርስቶስ አካል መጨመር ነው። ይህን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ (ማጥመቅ› ብለነው ነበር። አንድ ክርስቲያን በክርስቶስ አካል ከተጨመረ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ምን ያደርጋል? መልሱ ክሚከተሉት ሦስት ነገሮች አንዱን መፈጸም የሚያስችሉትን መንፈሳዊ ስጦታዎች መንፈስ ቅዱስ ለእያንዳንዱ ክርስቲያን ይሰጣል የሚል ነው። 

ህ የክርስቶስ አካል አባል እንደመሆኑ መጠን ከሌሎች ጋር በኅብረት እግዚአብሔርን ማመለክ እንዲችል ይረዳዋል። 

2. በክርስቶስ አካል ውስጥ ያሉትን ሌሎችን በእምነት ለማሳደግ ያገላግል ዘንድ ይረዳዋል። 

3. ከክርስቶስ አካል ውጭ የሆኑት ወደ ክርስቶስ አካል ይመጡ ዘንድ እንዲያገለግል ይረዳዋል። በአጭሩ ክርስቲያኖች ኢየሱስን እንዲያመልኩ፥ የክርስቶስ አካል የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን) እንዲያሳድጉና በኢየሱስ ስፍራ ሆነው ለዓለም አገልግሎት እንዲሰጡ ይረዳዋል። 

አዲስ ኪዳን የሚያስተምረን መንፈሳዊ ስጦታዎችን ለመስጠት ኃላፊነት ያላበት የሥላሴ አካል መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ነው። በ1ኛ ቆሮ. 2፡1 እንደዚህ የሚል አሳብ ተነግሮናል «ይህን ሁሉ ግን (መንፈሳዊ ስጦታዎችን) ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል።» በዚህ ጥቅስ የምናየው መንፈስ ቅዱስ ለእያንዳንዱ መንፈሳዊ ስጦታዎችን እንዴሰጠ ነው። መንፈስ ቅዱስ በተቀዳሚ ስጦታውን ሰሚቀበለው ሰው ፍላጎት ሳይሆን በራሱ ፈቃድ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ይሰጣል። በ1ኛ ቆሮ. 2፡7 ቀደም ብሎ እነዚህ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች «መንፈስ ቅዱስን መግለጥ» ተብለው ተጠቅሰዋል። ይህ የሆነበት ምክንያት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ህልውናውን ክሚያረጋግጥባቸው መንገዶች አንዱ ሰዎች መንፈሳዊ ስጦታዎቻቸውን እንዲጠቀሙ ማድረግ ስለሆነ ነው። መንፈሳዊ ስጦታዎች ከሌሉ መንፈስ ቅዱስ እንደሌለ ለመጠርጠር እንችላለን። ወይም መንፈስ ቅዱስ እራሱን እንዳይገልጥ የተከላከለበት መንገድ አለ ማለት ነው።

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: