ክፍል አንድ፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ስለ ክርስቶስ ባሕርይና አካል ያላቸው እምነት
በዛሬው ትምህርታችን ሁለት ነገሮችን እናደርጋለን። የመጀመሪያው ተግባራችን፥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ባሕርይና ኣካል እምነትዋ በእርግጥ ማን እንደሆነ መወያየት ነው። ሁነተኛው፥ ስለ ምሥጢረ ተሠገዎ ስናጠናው የነበርነውን ትምህርት ማጠቃለል ይሆናል። ኢየሱስ እንዴት በአንድ ጊዜ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ሊሆን ይችላል? የሚለውን ጥያቄ በመመለስ እንጀምራለን። ከዚያ በፊት ግን፥ ትናንት የተሰጣችሁን ቃለ መጠይቅ ካልጨረሳችሁ ወደ ዛሬ ሥራ ከማምራታችን በፊት ጨርሱ።
ክፍል አንድ፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ስለ ክርስቶስ ባሕርይና አካል ያላቸው እምነት
ትናንትና ለእናንተ የሰጠኋችሁን ጥያቄዎች እኔ ራሴ ለብዙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አማኞች አቅርቤ ጠይቄአቸው ነበር። በዚህ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኣንድ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በሚገኙ በሁለት ቀበሌዎች ውስጥ ነዋሪ የሆኑ አሥራ ሦስት የቤተ ክርስቲያን ሠራተኞችን ማለትም፥ (አምስት ቀሳውስትን፥ አራት ዲያቆናትን፥ ሁለት መነኮሳትንና ሁለት ደብተራዎችን) እንደዚሁም አሥራ ዘጠኝ ወንድ ምእመናንንና አሥራ ዘጠኝ ሴት ምእመናትን ጠይቄአለሁ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በነበረ ጊዜ እግዚአብሔርም ሰውም እንደነበረ የሚያምኑ ናቸው። ብዙዎች እርሱ ሥጋ የለበሰ አምላክ እና አምላክነቱና ሰብኣዊነቱ በተዋሕዶ የከበረ ነው ብለዋል። ሌሎች ደግሞ አሳባቸውን ሲሰጡ፥ እነርሱ እንደሚያምኑት ከሆነ፥ የኢየሱስ ሥጋ መልበስ ከተቀሩት የሰው ልጆች የተለየ መሆኑን ተናግረዋል። ጥቂቶቹ እንዳሉት ክርስቶስ የሰው አምሳል ቢሆንም ፍጹም ሰው አይደለም ብለዋል። ስለ ክርስቶስ ሰብኣዊነት በተጠየቁ ጊዜ አንዲት ሴት፥ «ይህ አፈኛ ነገር ብቻ ነው» ብለዋል። አንድ ቄስ ደግሞ ሲናገሩ፥ ክርስቶስ የአኗኗርን ሁኔታ ሊያስተምረን የሰውን አምሳል ወሰደ። ስለዚህ እርሱ እውነተኛ አምላክ እንጂ እውነተኛ ሰው አይደለም ሲሉ ተናግረዋል። እንደዚሁም አንደኛው ሰው፥ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ሊያስተምር ሰው ሆነ፥ ነገር ግን ሊቆፍር አልመጣም፥ ቤት ሊሠራም አልመጣም፥ እርሱ እንደ እኛ ሰብአዊ ባሕርይ ያለውም፥ እርሱ ከእኛ በላይ የሆነ ንጉሣችን ነው ሲል የሚያምነውን በጠራ ሁኔታ ገልጾአል። ይህ ሰው ክርስቶስ በሰው ቢመሰልም፥ ሰዎች የሚፈጽሙትን ተራ ተግባራት ለማድረግ አልመጣም በማለት አብራርቷል።
ቃለ መጠይቅ ከአቀረብሁላቸው ሰዎች አብዛኛዎቹ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ባሕርይ ብቻ እንዳለው አጥብቀው ያምናሉ። አንዳንዶቹም የእርሱ አንድ ባሕርይ፥ መለኮታዊ ባሕርይ ነው፥ ስለዚህ ኢየሱስ አምላክ ብቻ ነው ብለዋል። ሌሎች ደግሞ ትኩረት ሰጥተው የተናገሩት፥ ክርስቶስ ራሱ በራሱ ስለማይከፋፈል፥ አንድ ባሕርይ ብቻ ነው በማለት ነበር። በመጨረሻውም ላይ በርከት ያሉ ካህናት የኢየሱስ አንድ ባሕርይ መሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ስለሆነ እነርሱም በዚህ አስተምህሮ የሚያምኑ መሆናቸውን በአጽንኦት ተናግረዋል። ሁለት ዲያቆናት ደግሞ በመልሳቸው ላይ፥ ኢየሱስ ሁለት ባሕርያት አለው የሚለው አስተምህሮ መናፍቃዊ አስተምህሮ ነው፥ ትምህርቱም የመጣው በካቶሊኮችና በሌሎች ከውጭ በመጡ ሰዎች ነው በማለት ይህን አስተምህሮ በጥብቅ እንደሚቃወሙት ገልጸዋል።
ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ ስለሚገኝበት ባሕርይው ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ገና አላጠናንም። ስለዚህ በሚቀጥለው ትምህርታችን ላይ ኢየሱስ አሁንም እግዚአብሔር- ሰው፥ ወይም ሁለቱንም ማለትም እግዚአብሔርም ሰው ስለ መሆኑ ጠለቅ አድርገን እንማራለን። ለመሆኑ ቃለ መጠይቅ ያደረጋችሁላቸው ሦስት ሰዎች ለዚህ ምን መልስ ሰጡ? እኔ በበኩሌ ከጠየቅኋቸው ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ክርስቶስ በአሁኑ ጊዜ አምላክ ብቻ ነው ብለው ነው የመለሱት። ሌሎች ደግሞ ጨምረው የመለሱት፥ እርሱ እምላክ ብቻ በመሆኑ ወደ እግዚአብሔር ሊያቀርባቸው የሚችል አማላጅ እንደሚያስፈልጋቸው ነው። እነርሱ እንደሚያምኑት ኢየሱስ አማላጅ ተመላጅም ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ሰው ስላልሆነ በአሁኑ ጊዜ አማላጅ ሊሆን አይችልም። በሌላ ትምህርታችን ላይ ኢየሱስ አሁን ስለሚገኝበት የባሕርይ ሁኔታና፥ ኢየሱስ በአማላጅነት ተግባሩ ስለሚኖረው ስፍራ መለስ ብለን እናጠናለን።
ጥያቄ፡– ትናንትናና ዛሬ ላቀረባችኋቸው ቃለ መጠይቆች ያገኛችኋቸውን መልሶች አንብቡ፡ ሀ) መልሶ። እኔ ለእቀረብኋቸው ቃለ መጠይቆች ከተሰጡት መልሶች ጋር በምን ይመሳስላሉ? ለ) እንዴትስ ይለያሉ? ሐ) ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት የተጠየቁት ሰዎች በሰጡት መልሶች በክርስቶስ ማንነት ላይ ስላላቸው ግንዛቤ የእናንተ አጠቃላይ አስተያየት ምንድን ነው?
ክርስቶስ መለኮታዊና ሰብአዊ የሆነ ሁለት ባሕርያት እንዳሉት ማስተማር ለብዙዎቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አማኒያን በጣም አስቸጋሪ መሆኑ ግልጽ ነው። ኢየሱስ ሁለት ባሕርያት አሉት ብላችሁ ብታስተምሩ ለብዙዎቹ የሚመስላቸው ኢየሱስን ራሱን በራሱ እንደ ከፋፈላችሁት ነው። ለኣንዳንዶቹ ደግሞ ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ እግዚአብሔር አይደለም እንዳላችሁ ሆኖ ይታያቸዋል። ሌሎች ደግሞ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ መጤ ሃይማኖት ከውጭ ተቀብላችሁ የምታስተምሩ ይመስላቸዋል።
ክፍል ሁለት፡ የተሠገዎ ምሥጢር፡- ኢየሱስ እንዴት አምላክም ሰውም፥ ሁለቱንም ሊሆን ይችላል?
ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት ከመጽሐፍ ቅዱስና ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ ስለ ተሠገዎ ምሥጢር ስንማር ቆይተናል። ይህን የተሠገዎ ምሥጢር አስተምህሮ፥ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሁኔታ ለማጠቃለል ተመራጩ መንገድ ምንድን ነው? ኢየሱስ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው ነው ማለት ምን ማለት እንደሆነ፥ ነገ የራሳችሁን የማጠቃለያ አሳብ ትጽፋላችሁ። ነገር ግን ይህን የማጠቃለያ አሳባችሁን ከመጻፋችሁ በፊት፥ ለዚህ ተግባር ድጋፍ የሚሰጡዋችሁን ልዩ ልዩ ቁልፍ ጥቅሶች አስቀድመን እናጠናለን። እነዚህ ጥቅሶች የሚከተለውን ጥያቄ ለመመለስ ይረዱናል። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ እንዴት ሙሉ በሙሉ አምላክና ሙሉ በሙሉም ሰው ሊሆን ቻለ? እነዚህ ጥቅሶች ኢየሱስ በዚህ ምድር ላይ በነበረ ጊዜ በገዛ ፈቃዱ ከመለኮታዊ ባሕርያቱ ውስጥ አንዳንዱን መጠቀም ትቷል የሚሉ ይመስላሉ። እነዚያ ባሕርያት በወቅቱ ያልተለዩ ስለነበሩ በፈቀደ ጊዜ ሊጠቀምባቸው ይችል ነበር። ነገር ግን በአብዛኛዎቹ ጊዜያት ያለመጠቀምን ነበር የመረጠው። ይጠቀምባቸው የነበረውም የእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ሲሆን ብቻ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ሁሉን ነገር ያውቅ ነበር። ነገር ቀን የአብ ፈቃድ ካልሆነ በቀር ስገዛ ፈቃዱ መለኮታዊ እውቀቱን አይጠቀምበትም ነበር። እርሱ ሁሉን ቻይ ነበር። ሆኖም በዛ ፈቃዱ በመለኮታዊ ሥልጣኑ ከኣባቱ ፈቃድ ውጭ ለመጠቀም አልፈለገም። በየትኛውም ስፍራ በህንድ ጊዜ ሊገኝ ሲችል ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ራሱን በነበረው ኣካል ውስጥ ወስኖ፥ የአባቱ ፈቃድ ሲሆን ብቻ በሌላ ስፍራ ይገኝ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ ራሱ በፈቃዱ አንዳንድ መለኮታዊ ባሕርያቱን ትቶ የአባቱ ፈቃድ ሲሆን ብቻ ይጠቀምበት ነበር።
እነዚህን እውነታዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዴት እንመለከታቸዋለን? አስቀድመን የምንመለከተው፥ ኢየሱስ ሁልጊዜ የእግዚአብሔር አብን ፈቃድ በተግባር ላይ እንዳየለ ነው።
ጥያቄ፡– ዮሐንስ 8፡29 አንብቡ። ኢየሱስ ሁልጊዜ ምን ያደርግ ነበር?
ጥያቄ፡- ዮሐንስ 6፡38 አንብቡ። ኢየሱስ ምን ሊያደርግ ከሰማይ ወደ ምድር መጣ? ለ) ኢየሱስ ያላደረገው ምንድን ነው?
ጥያቄ፡- ዮሐንስ 4፡34 ኣንብቡ። የኢየሱስ ምግብ ምን ነበር?
ጥያቄ፡- ዮሐንስ 5፡30 አንብቡ። ሀ) ኢየሱስ በራሱ ምን ያደርግ ነበር? ለ) ኢየሱስ የማንን ፈቃድ አይፈጽምም ነበር? ሐ) ኢየሱስ የማንን ፈቃድ ይፈጽም ነበር?
ጥያቄ፡- ሉቃስ 22፡42 ኣንብቡ። ኢየሱስ ወደ መስቀል የመሄድና ያለመሄድ ታላቅ ፈተና ሲያጋጥመው ለአብ ምን አለ?
ኢየሱስ በአገልግሎቱ ሁሉ ላይ የእርሱ ፈቃድ ለኣባቱ ፈቃድ መገዛት መሆኑን በግልጽ አሳይቷል። የፈለገውን አያደርግም ነበር። አባቱ እንዲያደርግ የሚፈልገውን ብቻ ያደርግ ነበር። በዮሐንስ 8፡29 ላይ ዘወትር ኣባቱን ደስ የሚያሰኘውን እንደሚያደርግ ተናግሮአል። በዮሐንስ 6፡38 ውስጥም፥ እርሱ ከሰማይ የወረደው የላከውን ፈቃድ ለማድረግ እንጂ የራሱን ፈቃድ ለማድረግ እንዳልሆነ ተናግሯል። እንደዚሁም በዮሐንስ 4፡34 ላይ ደግሞ ኢየሱስ እርሱ ስለሚረካበት ነገር ሲናገር፥ የእርሱ ምግብ የላከውን ፈቃድ ማድረግ መሆኑን ገልጾአል። በዮሐንስ 5፡30 እርሱ በራሱ ሥልጣን ምንም እንደማያደርግ፥ ነገር ግን የላከውን ፈቃድ ብቻ እንደሚያደርግ አረጋግጧል። ከዚህም በስተቀር ኢየሱስ የራሱን ፈቃድ ሳይሆን የአባቱን ፈቃድ እንደሚያደርግ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራም ኣሳይቷል። እርሱ የዓለምን ኃጢአት ለማስወገድ በመስቀል ላይ ፍዳ ሲቀበል እንኳ በገዛ ፈቃዱ ከአባቱ ሊለይ አልፈለገም። እናም የአባቱን ፈቃድ ሊፈጽም ሲል የራሱን ፈቃድ መተው ነበረበት።
ኢየሱስ በሕይወቱ ሙሉ ያደረገው የአባቱን ፈቃድ ብቻ መፈጸም ነበር። እንዲህ ማለት ኢየሱስ በመለኮታዊ ባሕርይው የሚጠቀመው የኣባቱ ፈቃድ ሲሆን ብቻ ነው ማለት ነው። በዚህ በመለኮታዊ ባሕርይውም ይጠቀም የነበረው ተአምራት ሲሠራ ነበር። እነዚህ ተኣምራትም ሽባውን ሰው መፈወስ፥ ዳቦዎቹንና ዓሣዎቹን ማበርከት የመሳሰሉት ነበሩ (ዮሐንስ 5፡8፤ 6፡1-15)፡፡ ኢየሱስ መለኮታዊ ዕውቀቱን ይጠቀም የነበረው ስለ ሰዎች የተደበቀ ምሥጢር ካለ ለማውጣት ሲል ነበር። ለዚህ የሚጠቀሰው የሳምራዊትዋ ሴት ቀደምት ሕይወት (ዮሐንስ 4፡17) ወይም በማርቆስ 2፡፡ ላይ እንደተጠቀሰው፥ ሰዎች ስለሚያስቡት ማወቁ ነው። አንድ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ በመለኮታዊው ባሕርይ ካኣንድ ስፍራ አልፎ በአንድ ጊዜ በሌላ ስፍራ የሚገኝ መሆኑን ለናትናኤል፥ ከበለሲቱ ዛፍ ሥር ሆነህ አየሁህ ( ዮሐንስ 1፡48) ባለው ጊዜ ገልጾታል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ መለኮታዊ ዕውቀቱንና ኃይሉን ያልተጠቀመባቸውም ጊዜያት ነበሩ። እንደዚሁም ኢየሱስ አምላክ ላለ መለኮታዊ ዕውቀቱን ወይም ሥልጣኑን ትቶ ሰዎች ተወስነው በሚኖሩበት ውስን ሁኔታ ውስጥ የሚኖርበት ጊዜ ነበር።
ጥያቄ፡– ማርቆስ 13፡32 አንብቡ። ኢየሱስ ልጅ አያውቅም ያለው ምንድን ነበር? ለ) ኢየሱስ በእውነት አምላክና ሁሉን የሚያውቅ ሆኖ ሳለ በምን ምክንያት ይህን ያለ ይመስላችኋል?
ኢየሱስ ከሚሰቀልበት አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውጭ ሆኖ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በኢየሩሳሌም ከተማ ላይ ስለሚመጣው የእግዚአብሔር ፍርድ ይነጋገር ነበር። በዚህንም ጊዜ የኢየሩሳሌም ከተማ ከፈረሰች በኋላ ሥቃይና ስደት እንደሚመጣና ሐሰተኛ መሢሆችም እንደሚነሡ ነገራቸው። በማርቆስ 13፡26 ውስጥ ከዚህ ሁሉ መከራ በኋላ የሰው ልጅ በታላቅ ኃይልና ክብር በደመና እንደሚመጣ አስጠንቅቋቸዋል። ግን ይህ መቼ ይሆናል? በማርቆስ 382 ደግሞ ያቺን ቀንና ያቺን ሰዓት ከአብ በቀር ማንም ሊያውቃት እንደማይችል የሰማይ መላእክትም እንደማያውቁ፡ ወልድም ራሱ ቢሆን እንደማያውቃት ኢየሱስ ተናግሮአል።
ግን ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ኢየሱስ ይህን ሁኔታ ለደቀ መዛሙርቱ በነገራቸው ጊዜ ፍጹም አምላክ ነበር። እንደ ፍጹም አምላክነቱ ደግሞ በእርግጥ ወደ ምድር ዳግም የሚመለስበትን ጊዜ ያውቅ ነበር። እንዴት ለደቀ መዛሙርቱ የሚመለስበትን ጊዜ እንደማያውቅ ይናገራል? አንዳንዶች ይህን ሲመልሱ ኢየሱስ የሚመለስበትን ጊዜ በእርግጥ ያውቃል፥ ግን ይህን ያለው በትሕትና መንፈስ ነው ይላሉ። እግዚአብሔር አብን ለማክበርና በዚሁ መሠረት ደቀ መዛሙርቱም እግዚአብሔር አብን እንዲያከብሩ ለማሳሰብ ነው። ስለዚህ የሚመለስበትን ቀንና ሰዓት እንደማያውቅ ነገራቸው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ አሳብ ሲሰጡ፥ ኢየሱስ በእርግጥ የመመለሻውን ጊዜ ያውቅ ነበር። ነገር ግን እርሱ ለደቀ መዛሙርቱ ሊነግራቸው የፈለገው የእርሱ ዳግም መምጣት የእነርሱ ጉዳይ ሳይሆን የእግዚአብሔር ጉዳይ መሆኑን ሊያስጠነቅቃቸው ብሎ ነው ይላሉ። ይህ ጉዳይ ምሥጢር ሆኖባቸው ቀርቷል።
የዚህ ገለጻ ችግር፥ ኢየሱስ ዳግም የሚመጣበትን ጊዜ እያወቀ ለደቀ መዛመርቱ እንዳላወቀ ሆኖ ከነገራቸው እንዳታለላቸው ይቆጠር ነበር። ኢየሱስ ግን በፍጹም ኃጢኣት አላደረገም፤ ዋሽቶም አያውቅም። አላታለለምም። ኢየሱስ የሚመለስበትን ጊዜ አለማወቁን ለመናገሩ የተሻለ መልስ አለ። እርሱም እንደ ሰበ-ኣምላክነቱ በፈቃዱ አንዳንድ ባሕርያቱን ኣልተጠቀመም። እግዚኣብሔር ሰመሆኑ ሁሉን ያውቃል። ነገር ግን በሰብኣዊ ባሕርይው ለመኖር ሲል በራሱ ፈቃድ ከባሕርያቱ በኣንዳንዶቹ መጠቀሙን ተወ። እርሱ በመለኮታዊ ዕውቀቱ ይጠቀም የነበረው፥ በዚህ እንዲጠቀም የአባቱ ፈቃድ ሲሆን ብቻ ነበር።
ጥያቄ፡- ማርቆስ 9፡21 አንብቡ። ኢየሱስ እውነተኛ አምላክ ላለ ሁሉን እያወቀ ታዲያ ለምን ይህን ጥያቄ ያቀረበ ይመስላችኋል?
በማርቆስ 9፡14 ውስጥ ኢየሱስ ከመገለጥ ተራራ፥ ከጴጥሮስ፥ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወርዶ ገና ከተቀሩት ደቀ መዛሙርቱ ጋር መደባለቁ ነበር። ያኔውኑ አንድ ሰው ዲያብሎስ ካደረበት ልጁ ጋር እዚያው ሆኖ አገኙት። ሌሎቹ የጌታ ደቀ መዛሙርት ዲያብሎሱን ከልጁ ውስጥ ሊያስወጡ አልቻሉም ነበር። ሰውዬውም ልጁን ወደ ኢየሱስ አመጣው። ልጁም ወደ ኢየሱስ ፊት እንደ ቀረበ በውስጡ የነበረው ዲያብሎስ የልጁን ሰውነት እንደሚጥል በሽታ አድርቆ እንደ በድን አደረገው። ከዚያም ኢየሱስ የልጁን አባት እንዲህ ሲል ጠየቀው፥ «ይህ በሽታ ከጀመረው ምን ያህል ጊዜ ነው?» ኢየሱስ እንደ አምላክነቱ ሁሉን ነገር ስለሚያውቅ የዚህን ጥያቄ መልስም ባወቀ ነበር። በተጨማሪም ጥያቄውን ያቀረበበት ምክንያት አንዳንድ መረጃ ለማግኘት በመፈለጉ ይመስላል። ኢየሱስ ሰብአዊ ሕይወትን እንደ ተራ ሰው ለመኖር በገዛ ፈቃዱ በመለኮታዊ ዕውቀቱ መጠቀምን ተወ። ይሁን እንጂ ይህኔም ቢሆን ሁሉንም የማወቅ ባሕርይ ነበረው። ሆኖም ግን ይህን ባሕርይውንም የተጠቀመው የአብ ፈቃድ ሲሆን ብቻ ነበር።
ኢየሱስ ይህን ጥያቄ ያቀረበው መረጃ ለማግኘት ይመስላል። እንደ ኣምላክነቱ ልጁ በዲያብሎስ ተይዞ የቆየበትን ጊዜ ያውቃል። ግን በዚህ ዕውቀቱ አልተጠቀመበትም። ራሱን ገድቦ ልጁ ዲያብሎስ ካደረበት ምን ያህል ጊዜ እንደሆነ የልጁን አባት ጠየቀ። ይህን ያደረገውም መረጃ ለማግኘት ነበር።
ጥያቄ፡- ዮሐንስ 14፡28 አንብቡ። ሀ) ኢየሱስ እርሱ ከእኔ ይበልጣል ይለው የነበረው ማንን ነው? ለ) ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ አምላክ ከሆነ እንዴት እንደዚህ ይላል? ይህን ሲልስ ምን ማለቱ ነው? 35ኛ ጥያቄ፡- ዮሐንስ 10፡30 ኣንብቡ። ሀ) ኢየሱስ አንድነቱ ከማን ጋር ነው? ለ) እንዲህስ ሲባል ምን ማለት ይመስላችኋል?
በዮሐንስ 14፡28 ውስጥ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ አባቴ ከእኔ ይበልጣል ሲል ነገራቸው። ኢየሱስ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር? ይህን ሲል አብ ሙሉ በሙሉ አምላክ ሲሆን፥ እርሱ ግን ከኣምላክ ያነሰና የአምላክ አምሳል ነው ማለት ነው? አይደለም። እንዲህ ማለቱ አይደለም። ምክንያቱም ኢየሱስ በማንኛውም አኳኋን ሙሉ በሙሉ አምላክ ስለ መሆኑ ቀደም ሲል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተለያዩ ማስረጃዎችን አጥንተናል። በተጨማሪም በዮሐንስ 10፡30 ኢየሱስ እርሱና አብ አንድ መሆናቸውን ገልጾአል። እንዲህ ማለትም እርሱና አብ አንድ የሆነ ባሕርይ አላቸው ማለት ነው። እግዚአብሔር አብ ሕዝቡን እንደሚከላከል ሁሉ እርሱም ይከላከላል (ዮሐ 10፡28-29)። ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ እንኳን የእግዚአብሔር ባሕርይና ፈቃድ ነበረው። ኢየሱስ በአምላክነቱ ከአብ ጋር አንድ ነው። ነገር ን ወደ ምድር ሲመጣ በመለኮታዊ ሥልጣኑ ሙሉ በሙሉ ሳይጠቀም መኖርን መረጠ። በዚህ ሥልጣኑ ወይም በመለኮታዊ ዕውቀቱ የተጠቀመው የአብ ፈቃድ ሲሆን ብቻ ነበር። ስለዚህ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ እዚአብሔር ቢሆንም፥ በገዛ ፈቃዱ እንደ ተራ ሰው ሆኖ ኖረ። በሦስተኛ ትምህርታችን ላይ እንደተመለከትነው፥ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ በገዛ ፈቃዱ ራሱን ትሑት አድርጎ ክብሩን ከአብ አላነሰ። ራሱንም ለአብ አስገዝቶ የእግዚኣብሔር ኣብ ፈቃድ ካልሆነ በስተቀር በመለኮታዊ ባሕርያቱ በአብዛኛው ሳይጠቀም ኖረ፡፡ በእርሱነቱ ከአብ ያነሰ አልነበረም። ነገር ግን የሰው ልጆችን ኑሮ ለመኖር ራሱንና ማዕረጉን በፈቃዱ ከኣብ ዝቅ ማድረግን ፈቀደ።
ኢየሱስ ከኣምላካዊ ባሕርይው ሁሉ ጋር እንዴት እግዚአብሔር ሊሆን – እንደ ቻለና በዚህ ባሕርይው ሳይጠቀም ሰው ሆኖ እንደ ኖረ አንድ ምሳሌ እነሆ። እስቲ ዕድሜያቸው ከ4-5 የሚደርስ ሕፃን በግቢያቸው ውስጥ ኳስ ሲጫወቱ አስቡ። የልጆቹ አባት ወደ እነርሱ ዘንድ መጥቶ አብሮአቸው መጫወት ይጀምራል እንበል። ነገር ግን አባታቸው ከልጆቹ ይልቅ ትልቅ ነው፥ ጠንካራ ነው፥ ደግሞም ፈጣን ነው። ነገር ግን በልጆቹ አቅም መሠረት ለመጫወት ምን ማድረግ አለበት? ተንበርክኮ ከልጆቹ ጋር ኳስ መጫወት አለበት። አሁን እርሱ ቁመቱ ከልጆቹ ቁመት ጋር እኩል ሲሆን፥ የአጨዋወት ፍጥነቱ ከትንንሾቹ ልጆች ፍጥነት ጋር እኩል ይሆናል። ይሁን እንጂ አባታቸው አሁንም ቢሆን፥ ያ ቁመቱ፥ ያ ጉልበቱና የትልቅ ሰው ፍጥነቱ አብሮት አለ። ከእነዚህ ልጆች ጋር በሚጫወትበት ጊዜ በተጠቀሱት የችሎታው ባሕርያት ሁሉ አይጠቀምም። ራሱን ዝቅ አድርጎ ልጆቹ ከሚጫወቱበት ሁኔታ ጋር ያስማማል። ሆኖም በድንገት ብድግ ብሎ እንደ ትልቅ ሰው ሊጫወት ይችላል። ነገር ግን በገዛ ፈቃዱ በትልቅ ቁመቱ በጉልበቱና በፍጥነቱ አለመጠቀምን መርጧል። በዚህ ሁኔታ ኢየሱስ ሰው ሆኖ ሲመጣ፥ ሙሉ በሙሉ ከአምላክነት ባሕርይው ጋር አምላክ ሆኖ ኖረ፥ ሆኖም በገዛ ራሱ ፈቃድና ምርጫ፥ የአብ ፈቃድ ካልሆነ በስተቀር፥ በመለኮታዊው ባሕርይው ሙሉ በሙሉ አልተጠቀመም።
ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ