ኢየሱስ አሁን ያለው ባሕሪና አገልግሎቱ

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከዐረገ በኋላ ሁኔታው ምን ይመስላል? ምንስ እያደረገ ነው? ኢየሱስ በአሁን ጊዜ እያደረጋቸው ያለው ተግባራቱ እኛን በምን አኳኋን ይመለከቱናል? በዛሬው ጥናታችን ስለ ኢየሱስ ባሕርይና አገልግሎት የምንመለከት ሲሆን፥ ለሕይወታችን የሚኖራቸውን ትልቅ ቁም ነገርም እናያለን። 

1. ኢየሱስ ወደ ሰማይ ዐርጎ ባለበት በዚያ አሁን ያለው ባሕርይው ምን ይመስላል? 

ጥያቄ፡- 1ኛ ጢሞቴዎስ 25 አንብቡ። ኢየሱስ በዚህ ጥቅስ ውስጥ እንዴት ተብሎ ተገለጸ? ለዚህም ሁለት መልሶችን አቅርቡ። 

ጥያቄ፡- ራእይ 1፡12-13 አንብቡ። ዮሐንስ ማን እንደ ተናገረው ለማየት ዘወር ባለ ጊዜ ያየውን እንዴት ገለጸው? 

ኢየሱስ ክርስቶስ በድንግል ማርያም ማሕፀን ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተፀነሰ ጊዜ ሁለተኛ የመለኮት አንዱ አካል የሆነው ዘላለማዊው የእግዚአብሔር ልጅ፥ በመለኮታዊ ባሕርይው ላይ ፍጹም ሰብአዊውን ባሕርይ ተላበሰ ከዚያም ይህ ፍጹም ሰብአዊነት ከፍጹምነቱ አምላክነቱ ጋር ተባብሮ ፍጹም ሰብ- አምላክ አደረገው። ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ አካል ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው ነበር። ዘላለማዊው ቃል ፍጹም አምላክነቱን ሳያጣ ወይም ላይለቅ ፍጹም ሰው ሆነ። 

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ ባሕርይው አልተለወጠም። ስለሆነም አምላክም ሰውም በሆነው ባሕርይው ዐረገ። የኢየሱስ ባሕርይ እንደ ገና ተለውጦ ሰብአዊ ባሕርይውን ትቶ አምላክ ብቻ ሆነ የሚል ቃል በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ የለም። ይልቁንም 1ኛ ጢሞቴዎስ 2፡5 በግልጽ ኢየሱስ ክርስቶስ አሁንም ድረስ ሰው ነው ካለ በኋላ፣ ቀጥሎም በመካከል ሆኖ እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያስታርቅ ነው ይላል። 

በዚህ ረገድ ዘላለማዊው የእግዚአብሔር ልጅ አሁንም ቢሆን ፍጹም ሰው እንደሆነ 1ኛ ጢሞቴዎስ 2፡5 በግልጽ የሚያመለክት ጥቅስ ነው። ሆኖም ኢየሱስ በዐረገበት ጊዜ ከነሰብአዊ ባሕርይው፥ ባሕርይው ሳይለየው ማረጉን አበክር የሚያስነዝብ ሌላ ጥቅስም አለ። ራእይ ምዕራፍ አንድ ሐዋርያው ዮሐንስ በስደት በፍጥሞ ደሴት ላይ እንደ ነበረ ይገልጻል። እዚሁ ደሴት ላይ በአምልኮ ላይ እያለ ድምፅ ሰማና ማን እንደሚናገረው ለማየት ዘወር አለ። 

ያየውንም ሰው ሁኔታ ሲገልጽ፥ «የሰው ልጅ የሚመስል» ይለዋል። እንደምታስታውሱት በክፍል ስምንት ትምህርታችን ውስጥ፡- «የሰው ልጅ» የሚለው የማዕረግ ስም ቁም ነገር ምን እንደሆነ ተምረናል። በዚሁ ትምህርታችን ክፍል፥ ኢየሱስ ይህን መጠሪያውን የተጠቀመው የሰው ልጅነቱን በአጽንኦት ለማመልከት ሲሆን፥ ከዚህ ባሻገርም ከተራ ሰው በላይ መሆኑንም የሚገልጽበትም እንደሆነ ተከታትለናል። እንደዚሁም በዳንኤል ምዕራፍ 7 ላይ የሚገኘው አገላለጽም በክብር ስለተከበበው መለኮታዊው «የሰው ልጅ» የሚያመለክት ነበር። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ብዙ ጊዜ «የሰው ልጅ» የሚለውን መጠሪያውን ዴጋግሞ ሲጠቀምበት አስተውለናል። ዮሐንስ «የሰው ልጅ» የሚመስል በማለት ስለ ኢየሱስ የሚናገር ሲሆን፥ በዚህም ኢየሱስን ከአምላክነት ባሕርይው ሳይነጥለው፥ ሰብአዊነቱን በአጽንኦት ማስገንዘቡ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ ገለጻውን በመቀጠል ከቁጥር 13-16 ባለው ክፍል ውስጥ «የሰው ልጅ የሚመስል» ሲል (ራስ፥ ዓይኖች፥ እጆች፥ ፡ እግሮች ያሉትና ልብስ የለበሰ) እያለ ስለ መልኩ ያብራራል። ግን ደግሞ ባልተለመደ ሁኔታ ይህ የሰው ልጅ የሚመስል ሰው ዐይኖቹ እንደ እሳት፥ እግሮቹ እንደ ነሐስ የሆኑ፤ ከአፉም ሰይፍ የሚወጣ ነበር ሲል ተንትኖታል። ዮሐንስ አሁንም ቢሆን ኢየሱስ ሰው መሆኑን እየገለጸልን፥ ግን ኢየሱስ በክብር ታጅቦ ከማንኛውም ሰው በላይ በላቀ ስፍራ ከፍ ብሎ መቀመጡን ይመሰክራል።

ጥያቄ፡- ኢየሱስ በክብር ከፍ ብሎ አሁንም በአባቱ ቀኝ እያለ ሰው መሆኑ ለእኛ ጥቅሙ ምን ይመስላችኋል? 

እኛ በክርስቶስ አማኞች የሆንን ሁሉ ኢየሱስ አሁንም ሰው መሆኑ በጣም የሚጠቅመን ነገር ነው። 1ኛ ጢሞቴዎስ 25 ኢየሱስ አሁንም ሰው መሆኑ ስላለው አንድ ጠቃሚ ውጤት ይናገራል። ይህም እርሱ በእግዚአብሔርና በእኛ መካከል የማማለዱ ጉዳይ ነው። እግዚአብሔር ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ እንደሚማልድ ለሰው የሚያማልድም ሰው ብቻ መሆን እንዳለበት እንገነዘባለን። ስለዚህ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል አማላጅ ሆኖ ሊቆም የሚችል ሰው የሆነ አምላክ ብቻ ነው። በነገው ትምህርታችን ደግሞ ኢየሱስ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ስለ መሆኑና ስለ አማላጅነቱ ዘርዘር አድርገን እናጠናለን። 

ኢየሱስ አሁንም ፍጹም ሰው ስለሆነ ሌሎች አገልግሎቶችንም ለእኛ ሊሰጠን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በድካማችን ሊራራልን የሚችል ሊቀ ካህናችን ነው (ዕብራውያን 4፡5)። ኢየሱስ ዛሬም ሰው ባይሆን ኖሮ ሊቀ ካህናችን ሊሆነን ባልቻለ ነበር። ነገር ግን አሁንም ሰው በመሆኑ ዛሬም በድካማችን ሁሉ ሊራራልን ይችላል። ምንም እንኳን ዕብራውያን 2፡18 አበክሮ የሚናገረው ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ፥ ስለነበረው ሕይወት ቢሆንም፥ እርሱ አሁንም ሰው ስለሆነ የሚያጋጥመንን ፈተና ሁሉ እንድናሸንፍ ሊረዳን እንደሚችልም ይጠቁማል። በመጨረሻም፥ ክርስቶስ ሕዝቡን ለመታደግና ደኅንነትን ለመስጠት የመመለሱ ጉዳይ በክብር ከታጀበው ሰብአዊ ባሕርይው ጋር የተያያዘ ነው (ራእይ 19፡11-16፤ ዕብራውያን 9፡27-28)። ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ሰው በመሆኑ በመካከል ሆኖ ስለ እኛ ይማልዳል፥ ደግሞም ከፈተናም እንድንወጣ ይረዳናል፥ በመጨረሻም ከክፉ ኃይላት እጅ ሊያላቅቀን ደግሞ ይመጣል። 

2 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ፥ አሁን ምን እያደረገ ነው? 

ኢየሱስ ወደ ሰማይ በማረጉ ሥራው ተፈጸመ ማለት አይደለም። ዕርገቱ የሥራውን ባሕርይ ብቻ ለወጠው፡፡ ያውም ለኃጢአት ከመሠቃየት ወደ ሌሎች አገልግሎቶች ተሻገረ ማለት ነው። እነዚህ ሌሎች አገልግሎቶች አብዛኛዎቹ በምድር ላይ ባሉ ሕዝቦቹ ፈንታ የሚከናውኑ ናቸው። ታዲያ ጌታ ኢየሱስ አሁን እያከናወናቸው ያሉ እነዚህ ሌሎች አገልግሎቶች ምንድን 

ናቸው? 

ጥያቄ፡– ኤፌሶን 20-23 አንብቡ። ሀ) ክርስቶስ በአባቱ ቀኝ በተቀመጠ ጊዜ ከእግሮቹ በታች ምን ሆነ? ለ) ክርስቶስ በምን ላይ ራስ ሆነ? 

ጥያቄ፡- ዕብራውያን 13–4 አንብቡ። እንደ ቁጥር 4 ገለጻ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ከመቀመጡ የተነሣ፥ ከእነማን በላይ ሆነ? 30ኛ ጥያቄ፡- 1ኛ ጴጥሮስ 3፡22 አንብቡ። ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ በመሆኑ እነማን ተገዙለት? 

በአሁኑ ጊዜ የክርስቶስ የመጀመሪያው አገልግሎት እርሱ የፍጥረታት ሁሉ ገዢ መሆኑ ነው። ኤፌሶን 1፡22 እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር» ከሥልጣኑ ሥር አድርጎ አስገዛለት ይላል። በመሆኑም ለሥልጣኑ ተቀናቃኝ ናቸው ተብለው የሚገመቱ ቢኖሩ እንኳን ለኢየሱስ ተገዥ ዎች ናቸው ሲል አዲስ ኪዳን አጽንኦት ሰጥቶ ይናገራል። ኤፌሶን 1፡20-21 ባለው ክፍል «ከአለቅነትና ከሥልጣንም፥ ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና» በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን በሚመጣውም ዓለም ከስም ሁሉ በላይ የሆነ የክብር ስም፣ አለው ይላል። ጳውሎስ ምናልባት ያስብ የነበረው ስለ መናፍስት ዓለም ኃይላት በተለይም ስለ ርኩሳን መናፍስት ሳይሆን አይቀርም (ኤፌሶን 6፡12)። ዕብራውያን 13-4 እና 1ኛ ጴጥሮስ 3፡22 ኢየሱስ ከመናፍስት ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ማለቱን፥ ማለትም ክመልካምና ከክፉ መናፍስት በላይ የላቀ መሆኑን ይናገራል። ነገር ግን ኤፌሶን 1፡20-22 በተጨማሪ የኢየሱስ ሥልጣን ከምድራዊ ገዢዎች ሥልጣን ሁሉ በላይ የላቀ መሆኑንም ያስገነዝባል። ኢየሱስ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ከተቀመጠ በኋላ፥ ዝም ብሎ በመቀመጥ ወይም ዕረፍት በማድረግ ሥራውን አልደመደመም። ፍጥረታቱን በገዢነቱና በሥልጣኑ የማስተዳደሩንና የመምራቱን ስፍራ ነው የያዘው። ልክ አንድ ንጉሥ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ መንግሥቱን እንደሚመራ፥ ወይም አንድ ፕሬዚዳንት ከመንበሩ ላይ ሆኖ ሕዝቡን እንደሚያስተዳድር ሁሉ፥ ኢየሱስም በዙፋኑ ላይ ሆኖ ፍጥረታቱን በሙሉ ይገዛቸዋል፣ ያስተዳድራቸዋልም። 

ጥያቄ፡- ሀ) እናንተ ወይም አንድ እናንተ የምታውቁት ሰው መናፍስት አስፈራርተውት ስለተጨነቀበት ጊዜ አስቡ። እነዚህ ክፍለ ምንባቦች ክፉ መናፍስት ከሚያስከትሉባችሁ ሥጋትና ፍርሃት አንጻር ምን ያህል ልበ ሙሉነትና ብርታት ይሰጧችኋል? ለ) እናንተም ሆናችሁ የምታውቋቸው ሰዎች ዓለማዊ የሆኑና ክርስቶስንና ቤተ ክርስቲያኑን የሚቃወሙ ባለሥልጣናት በሚያደርጉት ተግባር ፍርሃት ያደረባችሁን ጊዜ አስታውሱ። እዚህ ላይ እነዚህ ከፍለ ምንባቦች በእነዚህ አማንያንን በሚቃወሙ የዓለም ባለሥልጣናት ፊት ምን ያህል ልበ ሙሉነትንና ብርታትን ይሰጡዋችኋል?

ኢየሱስ ፍጥረታቱን ሁሉ እየተቆጣጠረ ስለሚገዛ ዛሬ እማኞች በእርሱ ላይ ሊታመኑ ይችላሉ። ስለሆነም እርሱ መናፍስትን ሁሉ ስለሚገዛ አማኞች መናፍስትን ሊፈሩዋቸው አይገባም። ለክርስቶስ ታዛዦች በሆኑና በእርሱም ሰሚኖሩ አማኞች ላይ ክፉ መናፍስት ሥልጣን የላቸውም። እግዚአብሔር የልጆቹን ጽናት ለማሳደግና ላቅ ያለ መልካም ነገር ለማምጣት ሲፈልግ መናፍስት በሕይወታቸው ችግርን እንዲያመጡ ካልፈቀደ በስተቀር ክፉ መናፍስት ራሳቸው ፈልገው አማኞችን ሊተናኮሉ አይችሉም (ሮሜ 8፡28 29፥ 38–39)፡፡ አንድ አማኝ ኃጢአት እንዲያደርግ ክፉ መንፈስ በሚፈትነው ጊዜ አማኙ በመናፍስት ሁሉ ላይ ሥልጣን ባለው በኢየሱስ ስምና ሥልጣን ከእርሱ እንዲርቅ ሊገሥጸው ይችላል። እንዲሁም ኢየሱስ በሰዎች ሥልጣን ላይ ሁሉ የበላይ ስለሆነ አማኞች ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ ሌሎች ሰዎች ችግር ያስከትሉብናል ብለው ሳይሠጉ ያላንዳች ፍርሃትና ሥጋት ሊኖሩ ይችላሉ። እግዚአብሔር ለልጆቹ ብስለትንና የላቀ መልካም ነገርን ለማምጣት ብሎ ሊፈቅድ ካልሆነ በስተቀር የትኛውም የሰዎች ሥልጣን አማኝን ሊጎዳ አይችልም። ክርስቶስ ለራሱ አገልግሎት በር ቢከፍትልን ማንም ሰብአዊ ባለሥልጣን ሊዘጋ አይችልም። ኢየሱስ በመናፍስትና በሰብአዊ ሥልጣናት ሁሉ ላይ ገዥ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ ሰዎች ይጎዱናል ብለው በሚፈሩዋቸው ወይም ከአንድ ነገር ያግዱናል ብለው በሚሠጉባቸው ሥልጣናት ላይ ሁሉ ገዥና ተቆጣጣሪ መሆኑን አማኞች ሊያውቁትና ሊያምኑት ይገባል። 

ኤፌሶን 1፡23 በምታነቡበት ጊዜ ኢየሱስ የቤተ ክርስቲያን ራስ ወደ መሆን ከፍ እንዳለ አስተውላችኋል። በቆላስይስ 1፡18 ኢየሱስ የቤተ ክርስቲያን ራስ መሆኑን ያስተምራል። የቤተ ክርስቲያን ራስ የሚለው አገላለጽ ኢየሱስ በቤተ ክርስቲያን ላይ ገዥና ባለሥልጣን መሆኑን ያስረዳል። ሐቁ ይህ ሆኖ ሳለ፥ አንዳንድ ጊዜ ሽማግሌዎች፥ መጋቢዎችና ወንጌላውያን እንዲሁም ሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የቤተ ክርስቲያን ራስ የሆኑ ያህል ራሳቸውን እየቆጠሩ፥ በአፋቸው ኢየሱስ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው ሊሉ ይችላሉ። ነገር ግን በተግባራቸው ኢየሱስ ኃላፊነቱን ለእነርሱ አስረክበ የቤተ ክርስቲያን ራስ የመሆን ሥራውን እንዳቋረጠ (ጡረታ እንደ ወጣ) አድርገው ራሳቸውን ያቀርባሉ። የቤተ ክርስቲያናት መሪዎች እግዚአብሔር እንዲመሯቸው የሰጣቸውን ቤተ ክርስቲያናት በመንከባከብ ረገድ በጣም ሊጠነቀቁ ይገባል። ደግሞም በእግዚአብሔር ፊት ራሳቸውን ትሑት አድርገው ማቅረብ አለባቸው። የእግዚአብሔር መንፈስ በምእመናኑ ውስጥ ስለሚኖርና በእነርሱም በኩል ስለሚናገር የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በጥሞና የምእመናኑን ድምፅ ሊያዳምጡ ይገባል። 

ጥያቄ፡- የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በእውነት መሪዎች እነርሱ ሳይሆኑ ኢየሱስ መሆኑን እንዴት ባሉ የተለያዩ መንገዶች ሊገልጹ ይችላሉ? 

ኢየሱስ የቤተ ክርስቲያን ራስ መሆኑን ለማሳወቅ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ውሳኔዎችን ከማድረጋቸው በፊት በብዙ ኦምና ጸሎት መቆየት ይገባቸዋል። በመካከላቸው ልዩነት ሲፈጠር እንደ ራሳቸው ፍላጎት ለመወሰን በመሞከር ፈንታ፥ ጌታ የውሳኔውን መንገድ እንዲያሳያቸው በትዕግሥት እርሱን መማጠን ይገባቸዋል። እንዲሁም የራሳቸውን አሳብ በተጽዕኖ ለመጠቀምና የራሳቸውን መንገድና ፈቃድ ለመከተል በመሞከር ፈንታ ሁሉም ማኅበረ ምእመናኑ በሚገባቸው አኳኋን ለጌታ ፈቃድ ራሳቸውን አሳልፈው ሊሰጡ ይገባል። ከዚህም በላይ ምእመናኑ እርሱን ሊያገለግሉት እንዲችሉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ነጻነት ሊሰጡዋቸው ይገባል። ድርጊታቸው ከቅዱስ መጽሐፍ ቃል ውጭ እስካልሄደ ድረስ ሁሉም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ኢየሱስ በእውነት የቤተ ክርስቲያን ራስ መሆኑን በሚያሳይ ሁኔታ ቤተ ክርስቲያንን ሊመሯት ይገባል። 

ነገር ግን ኢየሱስ የቤተ ክርስቲያን ራስም ብቻ አይደለም ከዚህም ባሻገር እርሱ ቤተ ክርስቲያኑን በብዙ መንገዶች ያገለግላታል። ታዲያ አሁን ኢየሱስ ለቤተ ክርስቲያኑ እየሰጠ ያለው ሌሎች አገልግሎቶች የትኞቹ ናቸው? 

ጥያቄ፡- ዮሐንስ 55 አንብቡ። ሀ) የወይኑ ግንድ ማን ነው? ለ) ቅርንፎቹ እነማን ናቸው? ሐ) ፍሬዎቹ በቅርንጫፎቹ ላይ ቢኖሩ ምን ይሆናል? 

ጥያቄ፡– ኤፌሶን 4፡15-16 አንብቡ። አካል እንዲያድግ ምን ሁለት ነገሮች ያስፈልጉታል? 

ጥያቄ፡– ኤፈሶን 5፡25-27 አንብቡ። ኢየሱስ አሁን ለቤተ ክርስቲያን ምን እያደረገ ነው? 

ጥያቄ፡- 1ኛ ጴጥሮስ 2፡4-6 አንብቡ። ሀ) በቁጥር 4 ላይ ክርስቶስ የተገለጸው እንዴት ነው? ለ) በቁጥር 4 ላይ አማኞች እንዴት ተብለው ተገለጹ? ሐ) እንደ ቁጥር 6 አገላለጽ በክርስቶስ ላይ መታነጽ ምን ጥቅም አለው? 

አዲስ ኪዳን ክርስቶስ አሁን ከቤተ ክርስቲያን ጋር ስላለው ግንኙነት ብዙ ሥዕላዊ የሆኑ ማብራሪያዎች አሉት። ከእነዚህ ሥዕላዊ ማብራሪያዎች አብዛኛዎቹ ቤተ ክርስቲያን ለማደግ ወይም መልካምና አዎንታዊ የሆኑ ውጤቶችን ለማግኘት ብትፈልግ እንዴት የክርስቶስን ኃይል መጠቀም እንደሚያስፈልጋት ይገልጻሉ። ዮሐንስ 5፡5 ኢየሱስ የወይን ግንድ፥ አማኞች ደግሞ የወይን ቅርንጫፎች መሆናቸውን ያስረዳል። አማኞች በክርስቶስ ቢጸኑ ብዙ መንፈሳዊ ፍሬ ያፈራሉ። ነገር ግን በክርስቶስ ባይጸኑ፥ ምንም ነገር ሊያከናውኑ አይችሉም፡ ታዲያ እንዴት በክርስቶስ ጸንተን መኖር እንችላለን? ከእርሱ ጋር ጊዜአችንን በመጠቀም በራሳችን ላይሆን በእርሱ ኃይል ላይ ስንመረኮዝ ነው። እንዲሁም ቀኑን ሙሉ ስለ እርሱ ስናሰላስል፥ ቀኑን ሙሉ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ሁሉ ለእርሱ አሳልፈን ስንሰጥ ነው። በዚህ ሁኔታ አማኞች በክርስቶስ ጸንተው ቢኖሩ፥ እርሱም መንፈሳዊ ፍሬ እንደሚያድላቸው ተስፋ ይሰጣቸዋል። ኤፈሶን 4፡5-16 ያለው ክፍልም ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መንገድ፡ በአካል ሥዕላዊ ምሳሌ ይናገራል። አካል ለማደግ ከፈለገ፥ እያንዳንዱ ብልት ሥራውን ሊያከናውን ይገባል። ሆኖም እያንዳንዱ ብልት ከራስ ጋር ግንኙነት ሊኖረው ይገባል። ቤተ ክርስቲያንም እንድታድግ ከተፈለገ፥ እያንዳንዱ ወንድ ወይም ሴት ምእመን የተሰጣቸውን አገልግሎት መተግበር አለባቸው። ሆኖም ሁላችንም ራስ ከሆነው ከክርስቶስ ጋር የተያያዝን መሆን አለብን። 

ጥያቄ፡- በዚህ ባለፈው ሳምንት በክርስቶስ ለመኖር ምን አድርጋችኋል? ደግሞም በሚመጣው ሳምንት ውስጥ በክርስቶስ ለመኖር እርግጠኞች ልትሆኑበት የምትችሉትን ምን ሥራ ታከናውናላችሁ? 

የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በእርሱ ጸንተው እንዲኖሩ ሊያደርጉዋቸው የሚያስችሉዋቸው ብዙ ጠቃሚ መንገዶች አሉ። በመጀመሪያ፥ እያንዳንዱ አማኝ ከክርስቶስ ጋር የሚገናኝበት ጊዜ በየቀኑ ያስፈልገዋል። በዚህን ጊዜ አማኞች በጥንቃቄ መጽሐፍ ቅዱስን እያነበቡ በማሰላሰል፥ በውስጣቸው በሚያድረው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ድምፁን ማዳመጥ አለባቸው። ከዚያም ክርስቶስ ራሱን እንዲያሳያቸው፥ የጥሞና ጊዜ ወሰደው መጸለይ አለባቸው። ሁለተኛው ነገር፥ አማኞች ቀኑን ሙሉ ስለ ኢየሱስ ማሰብና ማሰላሰል ይገባቸዋል። ኢየሱስ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምን ያደርጋል በማለት ራሳቸውን ሊጠይቁ ያስፈልጋል። እንደዚሁም ኢየሱስ ስለዚህ ሁኔታ ምን ያስባል? የእግዚአብሔር ቃልስ ምን ይላል? በዚህ ሁኔታስ ውስጥ እንዴት አድርጌ እንደ ኢየሱስ ልኖር እችላለሁ? በማለት ራሳቸውን ሊጠይቁ ይገባል። በመጨረሻም፥ በአማኞች ሕይወት ውስጥ ችግር ሲከሠት ችግሮቹን ወደ እርሱ አሳልፈው መስጠት አለባቸው። ይህንን በሚያደርጉበት ጊዜ በኢየሱስ ውስጥ ሊያርፉ መፈለጋቸውንና በእርሱ መታመናቸውን በይፋ ያሳያሉ። በዚህም ኃይልና ብርታትን ለማግኘት በእርሱ ውስጥ መኖራቸውን ያስመሰክራሉ። 

ኢየሱስ አሁንም ለቤተ ክርስቲያኑ ብዙ በረከትን በመስጠት እያገለገላት ይገኛል። በኤፌሶን 5 ላይ ክርስቶስ ሙሽራ ለሆነችው ቤተ ክርስቲያኑ ኃላፊነት በሚሰማው እንክብካቤን በሚያደርግ ባል ተመስሎ ቀርቧል። አሁንም ይህቺን ቤተ ክርስቲያን የበለጠ ቅድስት በማድረግ ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንድትኖር እያዘጋጃት ይገኛል። በ1ኛ ጴጥሮስ 2 ደግሞ ይህች ምድራዊት ቤተ ክርስቲያኑ እየታነጸች ያለችበት የማዕዘን ድንጋይ ኢየሱስ መሆኑ ተጽፎአል። ኢየሱስ ሕያው ድንጋይ ስለሆነ፥ እያንዳንዱ አማኝም ሕያው ድንጋይ ነው። ከዚህም የተነሣ የተሰባሰቡት አማኛች የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤተ መቅደስ ናቸው። በክርስቶስ ላይ ሕይወታቸውን የሚነቡ አማኞች በእግዚአብሔር ፊት እንደማያፍሩ እርግጠኞች ናቸው። የማዕዘን ራስ የሆኑትም ክርስቶስ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን እንደሚያገኙ ያረጋግጥላቸዋል፡ 

ጥያቄ፡- ኢየሱስ በቤተ ክርስቲያናችሁ ተገኝቶ እናንተንና ቤተ ክርስቲያናችሁን የበለጠ ቅዱሳን እንድትሆኑ ሊያደርግ በምን በምን መንገድ አይታችኋል? 

ክርስቶስ የእርሱን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መገኘትና ቤተ ክርስቲያኑን የቀደስ ተባር ለማሳወቅ በተለያዩ መንገዶች ይጠቀማል። አንዳንድ ጊዜ ሥቃይን እንደ መንገድ ይጠቀማል። በሌላ ሁኔታ ደግሞ በጸሎትና በወንጌል እንቅስቃሴዎች አማካይነት የእርሱን መገኘት ይፋ ያደርጋል። በሌላ ሁኔታ ደሞ ጠንካራ በሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይጠቀምና ሰዎች በኃጢአታቸው ተጸጽተው እንዲመለሱ ያደርጋል። እንደዚሁም ሰዎች በመንፈሳቸው ተነሣሥተው ፈቃዱን እንዲፈጽሙ በትንቢትና በመገለጥ ቃል ይጠቀማል። እንደዚሁም በግለሰብ ወይም በትንሽ ቡድን መንፈሳዊ ዕድገት ይጠቀምና እነዚህ ሰዎች ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት ምክንያት እንዲሆኑ ያደርጋል። አንዳንድ ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ የሚሰማንን ጥብቅ የሆነ የኃጢአተኛነት ስሜትና ጸጸት በመጠቀም ፈቃዱን ይፈጽማል። ስለዚህ ኢየሱስ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ መኖሩን መገንዘብ አለብን። ቤተ ክርስቲያናችንንም ለመቀደስ የሚፈጽማቸውን ተግባራት በንቃት ማስተዋል ይጠበቅብናል። ከዚያም ራሳችንን ዝቅ አድርገን ለእርሱ መታዘዝ ይገባናል። 

ክርስቶስ በአሁኑ ሰዓት ለሕዝቡ የሚያከናውነው ቢያንስ አንድ ተጨማሪ ሥራ አለው። ይህም ተስፋውን ለመፈጸም ወደ ምድር ለመመለስ በዝግጅት ላይ የሆኑ ሥራ ነው። የኢየሱስ ወደዚህ ምድር ዳግም መምጣትና የወደፊት አገልግሉቱ፥ ከፍ ከፍ የማለት የክብር ሥራዎች ይሆናሉ። ሆኖም በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ስለ ክርስቶስ ዳግም መምጣትና ስለ ወደፊት ሥራው አናጠናም። ምክንያቱም በዚህ ርእስ ላይ ትምህርት የሚሰጡ ሌሎች ተከታታይ መጻሕፍት አሉና ነው። ሆኖም ክርስቶስ ለዚህ የወደፊቱ ሥራው ዝግጅት ለማድረግ አሁን ምን እያደረገ እንዳለ እንመለከታለን። 

ጥያቄ፡- ዮሐንስ 14፡1-3 አንብቡ። ኢየሱስ ትቶን ከሄደ በኋላ ምን ሊደርልን ቃል ገባ? 

እኛ በሰማይ ከእርሱ ጋር የምንሆንበትን ስፍራ ለማዘጋጀት ኢየሱስ ወደ አባቱ ተመልሶ መሄዱ ተቢ ነበር። በዮሐንስ 14፡3 ውስጥ ኢየሱስ የእርሱ ወደ ሰማይ ተመልሶ መሄድ ጳም ወደ ምድር እንዲመጣና ወደ እርሱ ዘንድ እንደሚወስዳቸው የሚያሳይ ምልክት መሆኑን ለደቀ መዛሙርቱ አረጋግጦላቸው ነበር። ኢየሱስ ከእኛ ቀድሞ ወደ ሰማይ ስለ ሄደና በአባቱ ቀኝ ከፍ ብሎ ስለ ተቀመጠ፥ ሰማይ የመጨረሻው ቤታችን እንደሚሆን እርግጠኞች ያደርገናል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በዮሐንስ 14 ውስጥ ያቀረበላቸው ሥዕላዊ ምሳሌ ሚስት ያጨና እጮኛውን ትቶ ቤታቸውን ሊያዘጋጅላቸው በሄደ ሰው የሚመሰል ነው። በአባቱ አጥር ግቢ ውስጥ ክፍሎችን አዘጋጅቶ ሲያበቃ በዚያም አብረው ደስ ይሰኛሉ። መሄዱ ያሳዝናል፥ ን ሁለቱም አብረው ሆነው የሚደሰቱበትን ቤት ሊያዘጋጅ የሄደ በመሆኑ በዚህ ትጽናናለች። ኢየሱስ አሁን ለእኛ ለሙሽሮቹ የሚሆነውን ቤት በሰይ እያዘጋጀልን ነው። የኢየሱስ በሰማይ መሆን፥ ለወደፊቱ እኛም በሰማይ ለሆናችን ማረጋገጥ ነው። 

ጥያቄ፡- ኢየሱስ አሁኑኑ ለእኛ ስፍራ እያዘጋጀልን መሆኑ ያበረታታችኋል? 

ኢየሱስ በሰማይ ለእኛ ላፍራ ማዘጋጀቱ በብዙ መንገድ ያበረታታናል። በመጀመሪያ፥ ስምንሞትበት ጊዜ ከእርሱ ጋር እንደምንሆን ያረጋግጥልናል። ከኢየሱስ ጋር ለመሆን አሁን ያለን ናፍቆት አንድ ቀን ይፈጸማል። ሁለተኛ፥ ኢየሱስን ለምናውቀው ከሞት በኋላ ለሚኖረን ሕይወት አስደናቂ ሁኔታ እንደሚሆን ያረጋግጥልናል። ምክንያቱም የእርሱ ዝግጅት ፍጹም ነውና። በዚህ ሕይወት ውስጥ ችግርና ፈተና ሲያጋጥመን አንድ ቀን በራሱ በኢየሱስ በተዘጋጀ ፍጹም በሆነ ስፍራ እንደምንኖር እርግጠኞች ነን። በመጨረሻም፥ የዚህ ሕይወት ገጠመኛች ትርጉምና ዓላማ የሚኖራቸው ኢየሱስ ለእኛ ለእያንዳንዳችን እውነተኛና ለዘላለማዊ ሴትን ለማዘጋጀት ይህን ጊዜና የምናልፍባቸውን ሁኔታዎች እየተጠቀመ መሆኑን ልንገነዘብ ብቻ ነው።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading