ኢየሱስ እና የእግዚአብሔር መንግሥት

1. የእግዚአብሔር መንግሥት በኢየሱስ አካል ውስጥ ይገኝ ነበር 

ጥያቄ፡- ማቴዎስ 12፡28 አንብቡ። ኢየሱስ አጋንንትን አስወጣ ሲሳል፥ ምን ማለት ነው? 25ኛ ጥያቄ፡- ሉቃስ 4፡43 አንብቡ። ኢየሱስ በምን ምክንያት ወደ ምድር ተላከ? 26ኛ ጥያቄ፡- ሉቃስ 17፡20-21 አንብቡ። ሀ) የእግዚአብሔር መንግሥት በምን እኳኋን ነው የማይመጣው? ለ) የእግዚአብሔር መንግሥት የት ነው ያለው? 

ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ያስተማረው ኢየሱስ እጅግ በጣም ጠቃሚው ነገር ወደ ምድር የመጣው በእርሱ አካል ውስጥ ስለ መሆኑ ነው። እርሱ በምድር ላይ ነው ማለት፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ ምድር መምጣት ጀመረ ማለት ነው። በማቴዎስ 12 ላይ ፈሪሳውያን ኢየሱስ አጋንንትን ያወጣ የነበረው በሰይጣን ኃይል እንደሆነ አድርገው ያስቡ ነበር። ይህን ባሉ ጊዜ ግን ኢየሱስ ክፉኛ ገሠጻቸው። በማቴዎስ 12፡28 ላይ ደግሞ፥ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አጋንንትን ማውጣቱ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እነርሱ እንደ ደረሰች የሚያመለክት ድርጊት እንደ ነበረ አስገንዝቧቸዋል። እንዲሁም በሉቃስ 4፡34፥ እርሱን ይፈልጉት ለነበሩት ሰዎች፥ የእርሱ ተልዕኮ በዙሪያቸው ላሉ ከተሞች የእግዚአብሔርን መንግሥት መስበክ እንደ ነበረ ነግሮአቸዋል። ከዚህም በስተቀር፥ በሉቃስ 17፡20-21 ባለው ክፍል የእግዚአብሔር መንግሥት ማንም ሰው ተነሥቶ ጣቱን በመቀሰር፥ «የእግዚአብሔር መንግሥት እነሆ እዚህ፥ እነሆ እዚያ ናት» ብሎ በማመልከቱ ብቻ አትመጣም ሲል ለፈሪሳውያን ነገሮአቸዋል። ይልቁንም የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላቸው ነበረች። ይህ የኢየሱስ አባባል፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በእርሱ አማካይነት በመካከላቸው እንደ ነበረች መናገሩን ይገልጻል። ይህን ባለ ጊዜም በትክክል በመካከላቸው ቆሞ ነበር። በዚህን ወቅት እነርሱ ማድረግ የነበረባቸው የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚያመጣ መሢሐዊው ንጉሥ እርሱ መሆኑን መቀበል ነበር። ይህን ቢያደርጉ ኖሮ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ዜግነት መብት በተሰማቸው ነበር። 

ኢየሱስ በትምህርቱ ላይ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በእርሱ አማካይነት ወደ ምድር እንደ መጣች አስገንዝቦአል። ከዚህም በስተቀር ኢየሱስ አይሁዳውያን ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የነበራቸውን የተዛባ ግንዛቤ አስተካክሎላቸዋል። ይህም አይሁዳውያን በብሉይ ኪዳን ውስጥ ይመጣል ስለተባለው መንግሥት የተነገሩትን በርካታ ትንቢቶች እንዳሉ የሚፈጽም ምድራዊ መንግሥትን ይጠባበቁ ነበር። ኢየሱስ በትምህርቱ ላይ የእርሱ መንግሥት በብሉይ ኪዳን ውስጥ ተስፋ የተሰጠበትን በእውን በአካል የሚፈጽም ቢሆንም፥ በአንጻሩ ደግሞ መንፈሳዊ መንግሥትም መሆኑን ገልጾ ተናግሮአል። ወደዚህ መንግሥት ለመግባት አብዛኛዎቹ አይሁዶች ያልተገነዘቡአቸውን መንፈሳዊ መሥፈርቶች ማሟላት ይጠይቃል። አብዛኛዎቹ አይሁዶች ኢየሱስን እንደ መሢሐቸው አድርገው ካለመቀበላቸውና ወደ መንግሥቱ ለሚያስገባው መንፈሳዊ መሥፈርት ስፍራ ካለመስጣቸው የተነሣ በአካል የምትታየው የእግዚአብሔር መንግሥት የምትመጣው ገና ወደፊት ነው። 

2. የመንግሥቱ መንፈሳዊ ጎን፥ መንግሥቱ አሁኑኑ እዚሁ ናት 

ጥያቄ ማቴዎስ 11፡12 አንብቡ። የእግዚአብሔር መንግሥት ከመቼ ጀምሮ በኃይል መግፋት ጀመረች? 

ጥያቄ፡- ሉቃስ 23፡42 አንብቡ። ሀ) በመስቀል ላይ የነበረው ሌባ ኢየሱስን ምን ለመነው? ለ) ኢየሱስ መቼ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ ብሎ ነገረው? 

ጥያቄ፡- ዮሐንስ 18፡36-37 አንብቡ። ሀ) ኢየሱስ መንግሥቴ ከየት አይደለችም አለ? ለ) በዚያን ጊዜ የኢየሱስ መንግሥት ከየት ነበረች። 

ጥያቄ፡- ቆላስይስ 1፡13-14 አንብብ። ሀ) አብ ከምን አዳነን? ለህ አብ ወዴት አመጣን? 

ኢየሱስ እንዳስተማረው የእግዚአብሔር መንግሥት ሁለት የተለያዩ ገጽታዎች አሉአት። በመጀመሪያ መንፈሳዊው ገጽታ ነበራት። ሰዎች ኢየሱስ እንደ መድኃኒታቸውና እንደ ንጉሣቸው በመቀበል፥ አሁን ባሉበት ስፍራ የመንግሥቱ ዜጎች ይሆናሉ። እንዲሁም አሁኑኑ ባሉበት መንፈሳዊ ሁኔታዎችን በመቀበል፥ በእርሱ ቢያምኑና ሲከተሉት፥ ኢየሱስ ወደ ልባቸው ውስጥ በመግባት ንጉሣቸው ሆኖ ይገዛል። ኢየሱስ ለፈሪሳውያን፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላቸው መሆንዋን እንደ ነገራቸው ቀደም ሲል በሉቃስ 17፡20-21 ባለው ክፍል አንብበናል። ምንም እንኳን በዓይን የምትታየው አካላዊ መንግሥት ገና ያልተቋቋመች ብትሆንም፥ የመንግሥቱ መመሥረት በእርሱ አካላዊ መገኘት የተከናወነ ጉዳይ መሆኑን እየነገራቸው ነበር። የመንግሥቱ መንፈሳዊ አጀማመር የተመሠረተው በኢየሱስ ወደ ምድር መምጣት ነበር። በማቴዎስ 11፡12 ላይ ኢየሱስ ለተሰበሰበው ሕዝብ ሲናገር፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በኃይል መግፋት የጀመረችው፥ ዮሐንስ መጥምቁ አገልግሎቱን ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ እንደነበረው ነው። ዮሐንስ ከኢየሱስ ቀድሞ የመጣ ሲሆን፥ አገልግሎቱም የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ ሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ልትገባ መሆኗን በቅድሚያ የማወጅ ሥራ ነበረ። በሉቃስ 23፡42-43 እንደተጻፈው፥ በመስቀል ላይ የነበረው ሌባ፥ ኢየሱስ ወደ መንግሥቱ በሚመጣበት ጊዜ እንዲያስበው ተማጸነ፥ ያኔ ኢየሱስ የሰጠው መልስ ብዙ ነገሮችን ያስተምረናል። በመጀመሪያ፥ ኢየሱስ ከእርሱ ጋር በገነት መሆኑን፥ በመንግሥቱ ውስጥ ከመሆኑ ጋር አንድ አድርጎ ቆጥሮታል። ሌባው ሰው በሞተ ጊዜ እግዚአብሔር ወዳለበት ገብቷል። ኢየሱስም ራሱ በዚያ እንደሚሆን አረጋግጦለታል። ይህም ልክ መንግሥቱ ውስጥ መሆን እንደሆነ አመላክቷል። እንዲሁም ኢየሱስ፥ ዛሬውኑ ከእኔ ጋር በገነት ውስጥ ትሆናለህ አለው። ሌባውም ሰው እንደ ሞተ ወዲያውኑ ከክርስቶስ ጋር በመንግሥቱ ውስጥ ሆነ። ምንም እንኳን ክርስቶስ በአካል የምትታየውን መንግሥት በምድር ላይ ገና ሳይመሠረትም፥ ሌባው ሰው ከክርስቶስ ጋር በገነት ሆኖ የመንግሥቱን በረከት ማጣጣም ጀምሮአል። በዮሐንስ 18 ላይ ኢየሱስን ንጉሥ እንደሆነ ጲላጦስ ጠይቆት ነበር (ቁጥር 37)። ኢየሱስም ንጉሥ ነኝ ብሎ መለሰለት። ነገር ግን የእርሱ መንግሥት ጲላጦስ የሚያውቀው መንግሥት ዓይነት አለመሆኑንም ገለጸለት። ኢየሱስም ሲናገር፥ መንግሥቱ ከዚህ ዓለም እንዳልነበረች ጠቅሶለታል። ኢየሱስ ይህን ባለ ጊዜ ማስረዳት የፈለገው፥ በዚያን ጊዜ የእርሱ መንግሥት መንፈሳዊ መንግሥት ብቻ እንደ ነበረች ነው። በመጨረሻም ጳውሎስ በቆላስይስ ምዕ. 1፡13-14 እማኞች ከጨለማ መንግሥት ተላቅቀው፥ ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት መምጣታቸውን ይናገራል። እኛም ክርስቶስ እንደ መድኃኒታችን አድረገን በምናምንበት ጊዜ፥ በመንፈስ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንገባለን። 

የተመለከትናቸው ጥቅሶች ሁሉ፥ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት በመንፈሳዊ ደረጃ ወደዚህ ምድር እንዳመጣ ያስተምረናል። ኢየሱስ የሚገዛው በሚያምኑትና በሚከተሉት ልብ ውስጥ ነው። እርሱ ንጉሣቸው ነው፥ እነርሱም የመንግሥቱ ዜጎች ናቸው። ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር መንግሥት ገና ሙሉ በሙሉ በምድር ላይ አልተቋቋመችም። ሁለተኛው ስለ እግዚአብሔር የኢየሱስ ጠቃሚው ትምህርት መንግሥቱ ገና ወደፊት የምትመጣ መሆኗ ነው። ስለሆነም ያን ጊዜ እግዚአብሔር ኢየሱስን ንጉሥዋ አድርጎ መንግሥቱን በምድር ላይ ሙሉ በሙሉ ይመሠረታል። በዚያን ጊዜም በብሉይ ኪዳን ውስጥ ስለ መንግሥቱ የተሰጡትን ተስፋዎች ሁሉ ይፈጽማል፥ ደግሞም ፍጹም የሆነ ሰላም፥ ፍትሕና ብልጽግናን በምድር ላይ ላሉ የሰው ልጆች ሁሉ ይሰጣል። 

3. ምሉዕና አካላዊ የመንግሥቱ ገጽታ፡-መንግሥቱ ገና ልትመጣ አላት። 

ጥያቄ፡– ማቴዎስ 6፡10 አንብቡ። ደቀ መዛሙርት ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ምን ብለው መጸለይ ነበረባቸው? 

ጥያቄ፡- ማቴዎስ 8፡11 አንብቡ። በምትመጣው ሰማያዊ መንግሥት ውስጥ ማን ይሆናል? 

ጥያቄ፡- ሉቃስ 1፡2-33 አንብቡ። ሀ) እግዚአብሔር ለኢየሱስ የሚሰጠው የምን ዙፋን ነው? ለ) ኢየሱስ በእነማን ላይ ይነግሣል? ሐ) የኢየሱስ መንግሥት መች ታበቃለች? 34ኛ ጥያቄ፡- ሉቃስ 22፡18 አንብቡ። ሀ) ኢየሱስ ዳግም ከወይኑ ፍሬ መቼ እጠጣለሁ አለ? ለ) ሉቃስ 22፡29-30 አንብቡ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በመንግሥቱ ውስጥ ምን እንደሚሠሩ ተናገረ? 

ኢየሱስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ያስተማረው ሁለተኛው ነገር፥ ፍጹማዊቷና በዓይን የምትታየው መንግሥት ወደፊት እንደምትመጣ ነው። ስማቴዎስ 6፡10 ውስጥ ጌታ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው ባስተማራቸው ጊዜ፥ ስለምትመጣው የእግዚአብሔር መንግሥት እንዲጸልዩ አስተምሯቸው ነበር። እንዲህ ማለት በአንድ በኩል የእግዚአብሔር መንግሥት ገና ወደ ምድር አልመጣችም ማለት ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር መንግሥቱን ወደ ምድር የማምጣቱን ተስፋ በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንዲፈጽም መጸለይ ይገባናል። እንዲሁም በማቴዎስ 8፡11 ላይ፥ ጌታ የተሰበሰቡትን ሰዎች ሲያስተምራቸው ሳለ፥ ብዙዎች አረማውያን ከአብርሃም፥ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር በመንግሥተ ሰማይ በታላቅ ደስታ ይሆናሉ ብሏቸው ነበር። ይህ ደስታ ገና አልሆነም። ወደፊት በዚህ ምድር ላይ የምትቋቋመውን እውን የሆነችይቱን አካላዊ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠብቃል። በትምህርታችን በሰባተኛው ክፍል እንደተመለከትነው፥ መንግሥተ ሰማይ የተባለችው ከእግዚአብሔር መንግሥት ጋር አንድ ናት። በሉቃስ 1፡32-33 ባለው ክፍል፥ መልአኩ ለማርያም ሲናገራት፥ እግዚአብሔር ለኢየሱስ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል አላት። ይህ የመልአኩ ብሥራት አንደምታው ከዳዊት ዘር ይመጣል ተብሎ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ተስፋ የተሰጠበትን መሢሕ መሥፈርት ሁሉ ኢየሱስ እንደሚያሟላ ነው። እነዚህ ተስፋዎች ገና ከፍጻሜ አልደረሱም። እንደዚሁም መልአኩ ለማርያም አክሎ ሲነግራት፥ እርሱ በያዕቆብ ቤት ላይ እንደሚነግሥና፥ መንግሥቱም ፍጻሜ እንደማይኖረው ነበር። ይሁን እንጂ ዛሬም ድረስ አብዛኛዎቹ አይሁዶች ኢየሱስን እንደ መሢሕና ንጉሣቸው አድርገው እልተቀበሉትም። ነገር ግን በምድር ላይ ተመሥርታ ለዘላለም የምትዘልቀው አካላዊዋ የእግዚአብሔር መንግሥት ስትመጣ በኢየሱስ ያላመኑበት ሁሉ ትክክለኛነቱን ይገነዘቡታል። እንዲሁም በሉቃስ 22፡18 ላይ ኢየሱስ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ስትመጣ ከወይኑ ፍሬ እንደሚጠጣ ተናግሮአል። ይህ የኢየሱስ አነጋገር እንደሚገልጸው፥ ወደፊት አንድ ቀን መንግሥቱ ስትቋቋም ኢየሱስ በአካል ገዢዋ እንደሚሆን ነው። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በመንግሥቱ ከአገልጋዮቹ ጋር በአንድነት ይበላል፥ ደግሞም ይጠጣል። በሉቃስ 22፡29-30 ባለው ክፍል አሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት በዚያን ጊዜ ከእርሱ ጋር እንደሚበሉና እንደሚጠጡ፥ እንዲሁም እስራኤልን እንደሚገዙ ተስፋ ሰጥቶአል። ይህ የኢየሱስ ተስፋ የሚፈጸመው እርሱ ወደ ምድር ተመልሶ፥ መንግሥቱም በእውን በአካል በምድር ላይ ሲመሠረት ነው። 

እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ኢየሱስ ወደዚህ ምድር በመጣ ጊዜ በመንፈሳዊ መንገድ የተጀመረች ቢሆንም በሙሉ አቋምዋ ገና አልተመሠረተችም። ኢየሱስ ዳግም ወደዚህች ምድር ተመልሶ አገዛዙን በቀጥታ በሚያሰፍንበት ጊዜ፥ መንግሥቱ ሙሉ በሙሉ መመሥረትዋ እውን ይሆናል። የእግዚአብሔር መንግሥት በመንፈሳዊ መንገድ ቀድሞውኑ ስለ ወጣች፥ ነገር ግን በሙ ላትም ገና ስለምትመጣ በአካል፥ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መንግሥቱ «መጥታለች፥ ገናም ትመጣለች ይላሉ። የእግዚአብሔር መንግሥት የኢየሱስ አገዛዝ ነው፡፡ ይህም መንግሥት ኢየሱስን የሕይወታቸው ንጉሥ ባደረጉ ሰዎች ልብ ውስጥ ተመሥርቷል፡፡ ነገር ግን ንጉሡ በአካል ሲመለስ ፍጹም መመሥረቷ ይረጋገጣል። 

ጥያቄ፡- ኢየሱስ በምድር ላይ ፍጹም የሆነ ፍትሐዊ ገዥነቱን፥ ሰላምንና ብልጽግናን ለመስጠት ወደ ምድር ተመልሶ የሚመጣ መሆኑ ምን ያህል ያበረታታችኋል? 

ጥያቄ፡- ኢየሱስን የሕይወታችሁ ንጉሥ አድርጋችሁታል? እንዲህ ከሆነ ከሕይወታችሁ ውስጥ በእርሱ አመራር ሥር እንዳይሆን ያደረጋችሁት ክፍል አለ? ታዲያ በዚህ በእርሱ አመራር ሥር እንዲሆን እንዴት አሳልፋችሁ ለእርሱ ትሰጣላችሁ? 

ኢየሱስ ፍጹም የሆነ ፍትሐዊ አመራር፥ ሰላምንና ብልጽግናን በምድር ላይ ለማስፈን ተመልሶ የመምጣቱ ነገር ለአማኞች ትልቅ ማበረታቻ ነው። የማያምኑ ሰዎች በሚያሳድዱን ጊዜ፥ ኢየሱስ አንድ ቀን መጥቶ ለተሰደዱትና ለተሠቃዩት ዋጋቸውን እንደሚሰጣቸውና የበደሏቸውንም እንደሚቀጣ ማወቃችን ትልቅ መጽናናትንና ብርታትን ይሰጠናል። በዓለም ላይ ኢ-ፍትሐዊ የሆኑ ድርጊቶችን በምናይበት ጊዜ አንድ ቀን ኢየሱስ ተመልሶ መጥቶ ፍትሕን ሰመስጠት ነገሮችን ሁሉ እንደሚያስተካክል መገንዘባችን ብርታትን ይሰጠናል። እንዲሁም ጦርነት የምንወዳቸውን ሰዎች ክአጠገባችን በሞት ሲወስዳቸው፥ ደግሞም ረሃብ የምንወዳቸውን ሲያሠቃይ ስናይ፥ በአንጻሩ ኢየሱስ አንድ ቀን ሰላምንና ብልጽግናን ለሰዎች ሁሉ እንደሚያመጣ ማወቃችን ብርታትን ይሰጠናል? 

1. ተዛምዶ፡- መንግሥቱ አሁኑኑና እዚሁ መገኘቷ 

ክርስቲያኖች ኢየሱስ አንድ ቀን መንግሥቱን በምድር ላይ ያቋቁሟል በሚለው ተስፋ ብቻ መኖራቸው በቂ አይደለም። አማኞች ከዚህ ቀደም ኢየሱስን ተቀብለው ንጉሣቸው ያደረጉ ሰዎች ናቸው። እርሱም መንግሥቱን በልባቸው ውስጥ መሥርቷል። ከዚህም የተነሣ እነርሱ የመንግሥቱ ዜጎች ሊሆኑ ችለዋል። ስለዚህ አማኞች በምድር ላይ በሚኖሩበት ስፍራና ጊዜ፥ እንደ እርሱ ዜጎች በመኖር ማንነታቸውን ሊያሳውቁ ይገባል። በመሆኑም ሕይወታችንን በሙሉ አሳልፈን ለኢየሱስ አመራር መስጠት አለብን፥ ገንዘባችንን ሁሉ፥ ቤታችንን ሁሉ፥ ልጆቻችንን፥ ሥራችንን፥ ነፃ ጊዜአችንን፥ በተጨማሪም ፍላጎታችንንም ሆነ የወደፊት ምኞታችንን ለእርሱ መስጠት ይገባናል። ኢየሱስን በሁሉ ነገርና በሕይወታችን ላይ ንጉሣችን ማድረግ ይጠበቅብናል። 

በወንጌላችን ውስጥ ካሉት እጅግ ጠቃሚ ከሆኑ የትምህርት ክፍሎች አንዱ፥ የኢየሱስ የተራራ ላይ ስብከት ነው። ጌታ ኢየሱስ በዚህ በተራራ ስብከቱ ላይ ለተከታዮቹ፥ የመንግሥቱ ዜጎች የሆኑ ሁሉ እንዴት መኖር እንዳለባቸው አስተምሮአቸዋል። በዚህም ለደቀ መዛሙርቱ እንደ እግዚአብሔር ዜጎች ባሉበት ስፍራና ቅጽበት እንዴት ሊኖሩ እንደሚችሉ ነግሮአቸዋል። 

ጥያቄ፡- ማቴዎስ 5፡3-12፥ 17-20፣ 5፡30፤ 1፡21 አንብቡ። እነዚህን ምንባቦች በምትመለከቱበት ጊዜ፥ የኢየሱስ መንግሥት ዜጎች የሆኑ ሰዎች ያላቸውን ባሕርይ፥ ወይም ልዩ መለያ ነጥብ በነጥብ ጻፉ። ይህ ዝርዝር ብፁዓን የሆኑ ሰዎችን ባሕርያትና የእውነተኛውን ጽድቅ ሳሕርያት ያጠቃልላል። 

ጌታ በተራራ ስብከቱ ላይ የሰጠውን ትምህርትና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ዜጎች ዓይነተኛ መለያ ባሕርያት የገለጸውን ለማጥናት ጊዜ አይኖረንም። ነገር ግን በአጠቃላይ ትምህርቱን ሰብሰብ አድርገን ስንመለከተው፥ ስለ ትሑታንና በእግዚአብሔር ስለሚታመኑት፥ ጽድቅን ስለሚራቡና ስለሚጠሙ፥ ምሕረትን ስለሚያደርጉ፥ ስለሚያስታርቁ ለክርስቶስ ጸንተው በመቆማቸው ስለሚገፉት፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በትክክለኛ መንፈሱ ስለሚፈጽሙ፥ እግዚአብሔርን አስቀድመው ስለሚሹና የክርስቶስን ፈቃድ ስለሚፈጽሙ ሆኖ እናገኘዋለን። በመሆኑም፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ዜጎች በየቀኑ እነዚህን ነገሮች ለመፈጸም የሚጥሩ ናቸው። 

ጥያቄ፡- ማቴዎስ 7፡21 በቃል አጥኑ። ይህን ጥቅስ በሚቀጥለው ቀን ውስጥ ቢያንስ አምስት ጊዜ ደጋግማችሁ በአእምሮአችሁ ውስጥ አሰላስሉ፡፡ በምታሰላስሉበት በእያንዳንዱ ጊዜም፥ ራሳችሁን «አሁን ለእኔ ሕይወት የኢየሱስ ፈቃድ ምንድን ነው? አሁን በዚህ ቅጽበት ኢየሱስ ምን እንዳደርግ ይፈልጋል?» በማለት ጠይቁ። በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ለኢየሱስ ፈቃድ ታዘዙ። ከዚያም ማስታወሻችሁን አውጥታችሁ፥ ለሕይወታችሁ የኢየሱስ ፈቃድ ምሳሌ የሆኑትን አምስቱን ጻፉአቸው።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading