በትናንትናው ትምህርት ስለ እግዚአብሔር ቅድስናና ስለ ሰው ልጅ ኃጢአተኝነት ተምረን ነበር። እንደዚሁም በብሉይ ኪዳን ውስጥ፥ እግዚአብሔር ቅዱስ ሆኖ ሳለ፥ ሰዎች ግን ኃጢአተኞች በመሆናቸው ምክንያት ለሰው ልጅ ኃጢአት ምትክ የሆነ መሥዋዕት ማስፈለጉን አስተውለናል። የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች ለጊዜው ብቻ የብሉይ ኪዳንን አማኛች ኃጢአት የሚሸፍኑ ነበሩ። ነገር ግን አንድ ቀን ፍጹምና ዘላቂ የሆነ የኃጢአት መሥዋዕት እንደሚመጣ ያስተምሩ ነበር። ያ ፍጹምና ዘላቂ የሆነ መሥዋዕት ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር።
ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም የሆነ የጽድቅ ሕይወትን ኖረ።
ኢየሱስ ለእኛ ደኅንነትን የመስጠቱ ተግባር፥ በእርሱ ፍጹም የሕይወት ምሳሌነት ተጀመረ። ከኃጢአት ተለይቶ ሙሉና ፍጹም የሆነ የሰው ልጅን ሕይወት ስለ ኖረ በሞቱ ፍጹም መሥዋዕት በመሆን ለሚያምኑት ሁሉ ጽድቅን አጎናጸፈ።
ጥያቄ፡– ዕብራውያን 4፡15 አንብቡ። ኢየሱስ ኃጢአት ስለ መሥራቱም ሆነ ስላለመሥራቱ ይህ ጥቅስ ምን ይላል?
ጥያቄ፡- ዮሐንስ 8፡46 እንብብ። ኢየሱስ ላቀረበው ጥያቄ መልሱ ምንድን ነው?
ጥያቄ፡- ርሜ 5፡10 አንብቡ። ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ በኢየሱስ ሞት አማካይነት ከእግዚአብሔር ጋር ታረቅን ይላል። ታዲያ ስለ እኛ መዳን የሚናገረው እንዴት ነው? ለ) ሮማ 5፡19 አንብቡ። ሐዋርያው ጳውሎስ ብዙዎች ጻድቃን የሚሆኑት በምን ምክንያት ነው አለ?
ጥያቄ፡– 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡21 አንብቡ። ሀ) ኢየሱስ ስለ እኛ ምን ሆነ? ላ) ከዚህ የተነሣ እኛ ምን ሆንን?
ጥያቄ፡– 1ኛ ጴጥሮስ 1፡8-19 አንብቡ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስ ምን ዓይነት በግ ነው አለ?
ለኃጢአት ፍጹምነት ያለው መሥዋዕት ለመሆን፥ ፍጹምነት ያለው ጽድቅንም እንዲሰጠን ክርስቶስ ራሱ ፍጹምና ጻድቅ የሆነ ሰብአዊ ሕይወትን መኖር ነበረበት። በሁለተኛው ክፍለ ትምህርት ውስጥ እንደ ተመለከትነው፥ አዲስ ኪዳን ኢየሱስ በሕይወት ዘመኑ ፈጽሞ ኃጢአት አለመሥራቱን ያስተምራል። ዕብራውያን 4፡5 ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ ሌሎች ሰዎች በተፈተኑበት ፈተና ተፈትኖአል ይላል። እርሱ ሁልጊዜ ለእግዚአብሔር ይታዘዝ ነበር። በዮሐንስ 8፡46 ውስጥ ኢየሱስ ሕዝቡን አንዳቸው እንኳ ኃጢአት ሠርተሃል ብለው ሊከሱት ይችሉ እንደሆነ ይጠይቃቸዋል። አንዳቸውም ደፍረው ሊከሱት አልቻሉም። ምክንያቱም በምንም ዓይነት ኃጢአት አልበደለም ነበር።
ምንም እንኳን የኢየሱስ የማዳን ሥራ የሚያተኩረው ሰሞቱ ላይ ቢሆንም፥ ከጻድቅ ሕይወቱ የተነሣ ደኅንነት ሊመጣልን ችሏል። የኢየሱስ የጻድቅ ሕይወት የደኅንነታችን አካል የሆነው በሁለት መንገድ ነው። አንደኛው፥ ኢየሱስ ፍጹም ጻድቅ በመሆኑ፥ የእርሱን ጽድቅ ለእኛ በመስጠት እኛን ጻድቃን አድርጎናል። በሮሜ 5፡10 ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ የኢየሱስ ሞትና ሕይወት ሁለቱም ለእኛ ጥቅም እንዳላቸው ይገልጻል። በዚሁ በሮሜ 5፡10 ውስጥ በአንድ ሰው በኢየሱስ) መታዘዝ ጻድቃን እንሆናለን ይላል። በ2ኛ ቆሮንቶስ 5፡21 ደግሞ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ኃጢአታችንን በመሸከሙ እኛ ጽድቁን እንዳገኘን ይናገራል። ኢየሱስ እኛን ጻድቃን ለማድረግ፥ ፍጹም የሆነ የጽድቅ ሕይወት በሰብአዊነቱ መኖር ነበረበት። የእርሱን ጽድቅ በእኛ ኃጢአት በመለወጥ እኛን ፍጹም ጻድቃን አደረገን። የእርሱን ፍጹም ጽድቅ በመቀበላችን፥ ከእግዚአብሔር ጋር ልንታረቅ ቻልን። ሌላም ሁለተኛ ምክንያት አለ። ይህም እኛ እንድንድን ኢየሱስ ጻድቅ ሆኖ መኖር ነበረበት። በሁለተኛውና በአሥረኛው ትምህርት ውስጥ እንደ ተመለከትነው ኢየሱስ ለኃጢአታችን ፍጹምነት ያለው መሥዋዕት ለመሆን እንዲችል፥ ፍጹም የሆነ የጽድቅ ሕይወትን መኖር ነበረበት። የፋሲካ በጎችና የመሥዋዕት እንስሳት ለኃጢአት መሠዋት እንዲችሉ ፍጹም መሆን ነበረባቸው፡፡ እንደዚሁም ለዓለም ኃጢአት የሚቀርበው መሥዋዕት ፍጹም ጽድቅን የተጎናጸፈ መሆን ነበረበት። በ1ኛ ጴጥሮስ 1፡18-19 ኢየሱስ ነውርና እድፍ የሌለበት የመሥዋዕት በግ እርሱ ነው ይላል። የኢየሱስ ፍጹም የጽድቅ ሕይወት ማለት፥ እርሱ ፍጹምነት ያለው ለኃጢአት መሥዋዕት ለመሆን የሚችልና «እኛ በእርሱ የእግዚአብሔር ጽድቅ» እንድንሆን፥ የራሱን ጽድቅ ስለ ኃጢአታችን መለወጥ የቻለ ነው።
ኢየሱስ በመሥዋዕትነቱ ሞት ኃጢአታችንን ተሸከመ፡፡
የኢየሱስ ፍጹም የሆነ ሕይወት፥ የደኅንነታችን የመጀመሪያ ነጥብ ነው። አዲስ ኪዳን ደኅንነታችን በኢየሱስ ሞት አማካይነት ስለ መገኘቱ የበለጠ አጽንዖት ሰጥቶታል። ኢየሱስ ኃጢአታችንን የተሸከመ የመሥዋዕትነት ሞትን ሞተ።
ጥያቄ፡- ዮሐንስ 1፡29 አንብቡ። ዮሐንስ መጥምቁ ኢየሱስን ማን አለው? ምንስ ያደርጋል አለ?
ጥያቄ፡– ኤፌሶን 5፡2 አንብቡ። ኢየሱስ ለእኛ ምን አደረገልን?
ጥያቄ፡- ገላትያ 1፡3-4 አንብቡ። ክርስቶስ ለእኛ ምን አደረገልን?
ጥያቄ፡- 1ኛ ጴጥሮስ 2፡24 አንብቡ። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ በሥጋው ምንን ተሸከመው?
በዮሐንስ 1፡29 ውስጥ እንደተጻፈው፥ ዮሐንስ መጥምቁ ኢየሱስን ከአይሁድ ሕዝብ ጋር አስተዋወቀው። ዮሐንስ፥ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ አድርጎ ወደ እርሱ ዘንድ በመጣበት ጊዜ፥ ወደ እርሱ እያመለከተ «እነሆ፥ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ» ሲል ጮኸ።
ዮሐንስ ይህን ቃል ባዕተጋባበት ጊዜ አድማጮቹ ብዙ ነገር ማሰባቸው አልቀረም። በመጀመሪያ፥ ምናልባት ትዝ ያላቸው ባእስራኤል በኩር ወንድ ልጆች ፈንታ ስለ ተሠዉት በጎች ሳይሆን አይቀርም። ሁለተኛ ደግሞ፥ በየቀኑ በቤተ መቅደስ ውስጥ ለኃጢአት ይቅርታ ተብለው ስለሚሠዉ በጎች ሳያስቡ አልቀሩም። ሦስተኛ፥ በኢሳይያስ 53 «ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ ‘ አፉንም አልከፈተም፥ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ» የሚለው ትዝ ብሎአቸው ሊሆን ይችላል። ዮሐንስ ኢየሱስ ልክ እንደ እነዚህ በጎች ይሆናል ሲል ነበር የነገራቸው። እርሱም የዓለምን ኃጢአት የሚሸከም ፍጹምና የመጨረሻ መሥዋዕት ነው። እርሱ የዓለምን ኃጢአት ሊሸከም ስለ መጣ ዓለም የራሱን ኃጢአት መሸከም አያስፈልገውም።
ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ የተናገራቸው ነገሮች በመልእክታት ውስጥ ተደጋግመው ቀርበዋል። በኤፌሶን 5፡2 ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ፥ «ኢየሱስ ራሱን መሳና መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ሰጠ» ይላል። በገላትያ 1፡3-4 ደግሞ፥ ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ ይላል። በ1ኛ ጴጥሮስ 2፡24 ውስጥ «እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ» ይላል። የዚህ ውጤት ከአሁን ጀምሮ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕይወት መኖር እንችላለን ማለት ነው። እርሱ ኃጢአታችንን በራሱ ላይ ስለ ተሸከመ ሕይወታችን ተለውጦአል። ቀድሞ ግን በኃጢአታችን ምክንያት የሞትና የኃጢአት ባሪያዎች ነበርን። አሁን ግን፥ ለኃጢአት ስለ ሞትን የጽድቅን ሕይወት ለመኖር እንችላለን። ካሁን ወዲያ ኃጢአትን እምቢ ጽድቅን እሺ ማለት እንችላለን። በመንፈስ ሞተን የነበርነውንና የዘላለም ሞት የተፈረደብንን በመንፈስ ሕያዋን እንድንሆን፥ እንዲሁም ለጽድቅ ለመኖር እንድንችልና የዘላለም ሕይወት ተስፋ ተሳታፊዎች እንድንሆን የኢየሱስ ሞት ለውጦናል።
ኢየሱስ በመሥዋዕትነት ሞቱ አማካይነት የተሸከመው ኃጢአታችንን ብቻ አልነበረም። ነገር ግን በመሥዋዕትነት ሞቱ አማካይነት የእኛ ቤዛ (ምትክ) ሆኖ ይገባን የነበረውን በደልና ቅጣት ተቀበለ።
ኢየሱስ በእኛ ምትክ በደላችንንና ቅጣታችንን ወሰደ።
ጥያቄ፡- ገላትያ 3፡13 አንብቡ። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ፥ ለእኛ ምን አደረገልን?
ጥያቄ፡- ሮሜ 1፡18 አንብቡ። ሀ) በሰዎች ክፋትና ዐመፀኝነት ምክንያት ምን ይገለጣል? ለ) ሮሜ 5፡9 አንብቡ። እኛ የዳንነው ከምንድን ነው?
ጥያቄ፡- ማርቆስ 10፡45 አንብቡ። የሰው ልጅ ምን አደረገ?
ጥያቄ፡ ዮሐንስ 10፡11 አንብቡ። መልካም እረኛ ለበጎቹ ምን ያደርጋል?
ጥያቄ፡- 2ኛ ቆሮንቶስ 5፡14 አንብቡ። አንዱ ለሁሉ ስለ ሞተ፥ ምን ተደረገ?
አዲስ ኪዳን ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ በእኛ ፈንታ መሞቱን በጥብቅ ያስተምራል። ለእኛ ይገባን የነበረውን በደልና የኃጢአት ቅጣት እርሱ ተቀበለ። ዛሬ ቀደም ብለን እንደ ተመለከትነው 1ኛ ቆሮንቶስ 5፡21 እግዚአብሔር የኢየሱስን ጽድቅ በኃጢአታችን እንደ ለወጠው ያስተምራል። ኃጢአታችንን የወሰደ ቢሆንም፥ እንደ እውነቱ ከሆነ በእኛ ፈንታ ኃጢአት ሆነ። ስለዚህ እኛ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን እንድንሆን የእርሱን ጽድቅ ወሰድን። ኢየሱስ ስለ እኛ ኃጢአት ለመሆን በእኛ እግር ተተካ (ምትካችን ሆነ)። ገላትያ 3፡13 እንደሚያስተምረን እርሱ በተሰቀለ ጊዜ፥ ለእኛ ይገባን የነበረውን እርግማን ተቀበለ። ከኃጢአታችንም የተነሣ ለዘላለሙ ከእግዚአብሔር እንድንለይ ተረግመን ነበር። ኢየሱስ በእኛ ፈንታ መርገምን በላዩ ላይ ተሸከመ። ሮሜ 1፡18 ደግሞ ከሰዎች ክፋትና ዐመፃ የተነሣ የእግዚአብሔር ቁጣ በሰዎች ሁሉ ላይ ይወርዳል ይላል። ይህንኑ ነጥብ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 1፡18-3፡20 በዝርዝር ይገልጻል፤ በሮሜ 3፡21 5፡8 ውስጥ ደግሞ ስለ ክርስቶስ ሞትና በእርሱ በሚኖረን እምነት አማካይነት እንዴት ደኅንነቱን እንደምንቀበል ያብራራል። በሮሜ 5፡9 ውስጥ ሊያጠቃልል ይህን ደኅንነት በምንቀበልበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ቁጣ እንደምንድን ይነግረናል። በዚህም ጳውሎስ እኛ ቁጣውን እንዳንሸከም ኢየሱስ በእኛ ፈንታ የእግዚአብሔርን ቁጣ እንደ ተሸከመ ያስገነዝባል።
ኢየሱስ በእኛ ፈንታ ተተክቶ በደላችንና የኃጢአታችንን ቅጣት መቀበሉን ግልጽ አድርገው ከሚያቀርቡ ምንባቦች ውስጥ በማርቆስ 10፡45 የሚገኘው ቃል ነው (ይህንኑ የመሰለ አሳብ በማቴዎስ 20፡28 ውስጥ ተጽፎአል)። ኢየሱስ ሲናገር የሰው ልጅ የመጣው፡- «ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ ነው» ይላል። «ብዙዎች» የሚለው ቃል በግሪኩ ቋንቋ በጣም ጠንካራ ቃል ነው፡፡ ትርጉሙም፥ «በፈንታ» ማለት ነው። ኢየሱስ ሕይወቱን የሰጠው በሌሎች ፈንታ፥ ወይም ስለ እነርሱ ሆኖ ነው። እርሱ ከእግዚአብሔር ፊት ተለይተው መቅረት በሚገባቸው ኃጢአተኞች ፈንታ ተሠቃየ። ከእግዚአብሔርም ተለይቶ ሞተ። ዮሐንስ 10፡11 በመጀመሪያው ግሪክ ላይ የተለየ ቃል ሆኖ ቀርቧል። ሆኖም መሠረተ አሳቡ አንድ ነው። ኢየሱስ መልካም እረኛ እኔ ነኝ ይላል። ስለዚህ «መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል።» መልካም እረኛ በጉ እንዳይሞት በፈንታው ይሞታል። ስለዚህ በጉ መሞት አያስፈልገውም። በ2ኛ ቆሮንቶስ 5፡14 ውስጥ ይህንኑ የመሰለ ቃል ይገኛል። ሐዋርያው ጳውሎስ፥ «አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ። እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ» ይላል። ኢየሱስ በሌሎች ሰዎች ፈንታ ሞተ። ለሰዎች ሁሉ ይገባ የነበረውን የኃጢአት ቅጣትና ሞት ተቀበለ። ስለዚህ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በሞተ ጊዜ፥ በእኛ ፈንታ በደላችንንና የኃጢአታችንን ቅጣት ተሸከመ።
በተግባር ላይ ማዋል፦ የኢየሱስን ሞት ጠቀሜታ ለሌሎች መግለጽ።
ጥያቄ፡- እናንተ የምታውቋቸው ሙስሊሞች ስለ ክርስቶስ ሞት ምን ያስባሉ? የምታውቁት ነገር ከሌላ ሙስሊም የሆነ ጓደኛችሁን ፈልጋችሁ ይህንኑ ጠይቁት። የክርስቶስ ሞት የሚሰጠውን ጥቅም በተመለከተ እንዴት አድርጋችሁ ልታካፍሏቸው ትችላላችሁ?
ጥያቄ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስና ወንጌላውያን ክርስቲያኖችን ስለ ክርስቶስ ሞት የሚያስቡት እንዴት ነው? የምታውቁት ነገር ከሌለ በቅርብ ለምታውቁት ጓደኛችሁ ይህን ጥያቄ አቅርቡለት። በዚህ ሳምንት ውስጥ የቀሰማችሁት ትምህርት የክርስቶስን ሞት ጥቅም ያስገነዝባቸው ዘንድ እንዴት ባለ ሁኔታ ታጫውቷቸዋላችሁ?
ሙስሊሞች ኢየሱስ በመስቀል ላይ መሞቱን አያምኑም። እነርሱ እንደሚናገሩት፥ ኢየሱስ የአላህ ነቢይ ነበር፥ ነገር ግን ከነቢያቱ መካከል አንዱ ተሠቃይቶ እንዲሞት ማድረግ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ እንደሚናገረው ለእግዚአብሔር ለራሱ የሚያሳፍር ነው ይላሉ። ለዚህም ከቁርአን የሚጠቅሱት (4፡57-58) ሲሆን፥ ጥቅሱም ኢየሱስ አልሞተም፥ ነገር ግን አላህ አድኖ ወደ ራሱ ወሰደው ይላል። በተጨማሪም ሙስሊሞች እንደሚያምኑት ስለ ኢየሱስ ስቅለት የሚያወሳው ታሪክ ከመጀመሪያው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጻፈም ብለው ነው። እንዲያውም ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ የስቅለት ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በመጨመር መጽሐፍ ቅዱስን ለውጠውታል ብለው ያምናሉ።
ሙስሊሞች ሰዎች ለኃጢአታቸው መሥዋዕት ያስፈልጋቸዋል ብለው አያምኑም። እንደዚሁም ሰዎች በኃጢአታቸው ምክንያት የእግዚአብሔር ጠላቶች እንደሚሆኑ፤ ስለ ኃጢአታቸውም እግዚአብሔር በጻድቅ ቁጣው እንደሚቀጣቸው አያምኑም። ደግሞም የሰው ልጆች በኃጢአት ምክንያት የሞቱና የኃጢአትም ባሪያዎች መሆናቸውን አያምኑም። በዚህ ፈንታ ሰዎች ከመሠረቱ ጥሩዎች መሆናቸውን ያምናሉ። እግዚአብሔር ይቅር እንዲላቸው፥ በደልና የኃጢአት ቅጣት መከፈል እንዳለበትም አያምኑም። በዚህ ፈንታ እነርሱ የሚያምኑት እላህ የሚታዘዙትን ያላንዳች ችግር ይቅር እንደሚላቸው ነው።
ሆኖም፥ ብዙ ሙስሊሞች የኃጢአታቸው በደል ስለሚሰማቸው ለእግዚአብሔርና ለተለያዩ መናፍስት የእንስሳት መሥዋዕት ያቀርባሉ። እዚህ ላይ ሙስሊም ለሆኑ ወዳጆቻችሁ የክርስቶስን ሞት ጥቅም ለማብራራት በምትሞክሩበት ጊዜ በውይይታችሁ ውስጥ ሰዎች የኃጢአትን ይቅርታ ለማግኘት እንስሳትን ለመሥዋዕትነት እንደሚያቀርቡ በምሳሌነት በማስገባት አብራችሁ ተወያዩበት፡ እንደዚሁም የኢየሱስ ሞት ለኃጢአት የቀረበ ፍጹም፥ የመጨረሻና ዘላለማዊ መሥዋዕት መሆኑን ግለጹላቸው።
ብዙ የኦርቶዶክስና የወንጌላውያን ክርስቲያኖችም ስለ ክርስቶስ ሞት ጠቀሜታ በቂ ጎንዛቤ የላቸውም። እንዲያውም ብዙዎቹ የኢየሱስ ሕይወት በቅድሚያ እኛ እንዴት መኖር እንደሚገባን የሚያሳየን ምሳሌ ነው ብለው ነው የሚያምኑት። እንደዚሁም ኢየሱስ እንደ ጾመ፥ እንደ ጸለየ፥ ለእግዚአብሔርም እንደ ታዘዘ፥ እንዲሁም ለሌሎቹ ሲል ሕይወቱን እንደ ሰጠ እኛም ልንም ልንጸልይ፥ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝና ለሌሎችም ሕይወታችንን ልንሰጥ ይገባናል ይላሉ። ሌሎች ክርስቲያኖች ደግሞ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የመሞቱ ጥቅም የእግዚአብሔርን ፍቅር ለእኛ ለማሳየት ነው ብለው ያምናሉ። እግዚአብሔር በጣም ስለ ወደደን ለእኛ ሲል ሞተ። እርግጥ ነው የኢየሱስ ሞት ለእኛ ምሳሌነት አለው በአሥረኛው ትምህርት እንዳየነው)። እንደዚሁም የክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞት፥ የእግዚአብሔርን ፍቅር እንደሚገልጽልን እርግጥ ነው። ነገር ግን የኢየሱስ ሕይወት ዋናው ጥቅም እንደ ምሳሌ እንዲሆነን ወይም የእግዚአብሔርን ፍቅር እንዲያመለክተን አይደለም። የኢየሱስ ሕይወትና ሞት ዋናው ጠቀሜታ እና ከእግዚአብሔር ጋር እንድንታረቅ የበደላችንና የኃጢአታችንን ቅጣት መክፈል ነው።
ስለ ክርስቶስ ሞት ካልገባቸው ወዳጆቻችሁና ከምታውቋቸው ሰዎች ጋር የምትጋሩት አንድ ታሪክ እነሆ። አንድ ጊዜ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩ። ታላቁ ልጅ በጣም መልካም ሰው ነበር። በሥራው ትጉሕና ጠንካራ ሠራተኛም ነበር። ሠርቶ የሚያገኘውን ገንዘቡንም ቤተሰቡን ለመርዳት ያውለው ነበር። ሁልጊዜም ለሕግ ታዛዥና ድሆችንና ምስኪኖችንም ለመርዳት የተዘጋጀ ሰው ነበር። በአንጻሩ ታናሽ ወንድሙ ሰነፍና ዋጋ የሌለው አልባሌ ሰው ነበር። ገንዘብ በሚያገኝበት ጊዜ ለመጠጥና ለሴተኛ አዳሪዎች ያባክን ነበር። ዘወትር ብስጩ ከመሆኑም በላይ ስለ ድሆችና ምስኪኖች ግድ የሌለው ሰው ነበር።
ታዲያ አንድ ምሽት በአንድ መሸታ ቤት ውስጥ በመጠጣት ላይ ሳለ ከአንድ ሌላ ሰው ጋር ጭቅጭቅ ገጠመ። በጣም ስለ ተናደደም ከሰውዬው ጋር ተደባደበ።
በድብድቡ ጊዜ ጩቤ መዝዞ ሰውዬውን ገደለው። ልብሱም በተገደለው ሰው ደም ተባከለ። ከዚያም ከቡና ቤት ሮጦ ወደ ታላቅ ወንድሙ ቤት ሸሽ። እንዴደረሰም ለወንድሙ የሆነውን ሁሉ ነገረውና ፖሊሶች ተከትለው መጥተው ወደ ወኅኒ ቤት እንደሚወስዱት አሳሰበው። ከዚህ በኋላ ታላቅ ወንድሙ በፍጥነት ልብስ እንዲለዋወጡ ነገረው። ታናሽ ወንድሙ በደም የተበከለውን ልብሱን አውልቆ ለትልቅ ወንድሙ ሲሰጠው፥ ትልቅ ወንድሙ ተቀብሎ ወዲያው ለበዕው። ታናሽ ወንድሙም ንጹሑን የታላቅ ወንድሙን ልብስ ለበሰ። ፖሊሶች እንደ ደረሱ ታላቅ ወንድምዬው በለበሰው ልብስ ላይ ደም ተመለከቱ። ያኔውኑ ይዘው ወደ ወኅኒ ቤት አወረዱት።
ክሱ በተከፈተ ጊዜ፥ ታላቅ ወንድሙ ምንም አልተናገረም። የለበሰው የደም ልብስ ራሱ ምስክርነቱን እንዲሰጥ ዝም አለ። ከክሱ በኋላ ትንሽ ወንድሙ በፈጸመው ወንጀል ይሙት በቃ ተፈረደበት። ከመሞቱም በፊት አንድ ደብዳቤ ለታናሽ ወንድሙ እንዲህ ሲል ጻፈለት፡- «እኔ በአንተ ፈንታ ልሞት ነኝ። አንተ ለኖርክበት የካፋ ሕይወት ለሠራኸው ወንጀል እኔ ልገደል ነው። አንተ የእኔን ሕይወት ትኖር ዘንድ እኔ ልሞት ነው።»
ይህ ታሪክ በብዙ መልኩ ስለ ኢየሱስ ሞት ይገልጻል። ታናሹ ወንድም የከፋ ወንጀል እንደ ፈጸመና ለቅጣትም እንደ ተዘጋጀ ሁሉ፥ በእግዚአብሔር ላይ የከፋ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ጥፋትና በደል ቅጣት ሊቀበሉ ይገባቸዋል። በተመሳሳይ መንገድ፥ ፖሊስና ፍርድ ቤት ቅጣትን ሳይሰጡ ለወንጀሉ ይቅርታ አያደርጉም። እንደዚሁም የእኛ ኃጢአት ታላቅ በመሆኑ፥ እግዚአብሔር በፍትሕና በቅድስናው ይጸና ዘንድ ኃጢአታችን ሳይቀጣ ዝም ብሎ ብቻ ይቅርታን አይሰጠንም። ታላቅ ወንድምየው ለታናሽ ወንድሙ ምትክ ሆኖ ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ ሁሉ፥ ኢየሱስም ራሱን አሳልፎ በመስጠት በእኛ ፈንታ ተሠዋ። ታላቁ ወንድም የታናሹን በደም የተበከለ ልብስ ለብሶ በእርሱ ፈንታ እንደ ሞተ ሁሉ፥ እንዲሁም ኢየሱስ ኃጢአታችንን በራሱ ላይ ተሸክሞ በእኛ ፈንታ ሞተ።
ስለዚህ የእግዚአብሔርን ደኅንነት ለማግኘት ኢየሱስ ስለ እኛ መሥዋዕት መሆኑን መገንዘብ ይጠበቅብናል። እርሱም በተሰቀለ ጊዜ ኃጢአታችንን ተሸከመ። እኛ መክፈል የነበረብንን የበደልና የኃጢአት ቅጣት ዕዳ እርሱ ራሱ ከፈለልን። ኢየሱስ ስለ እኛ ኃጢአት መሥዋዕት ስለሆነና የበደላችንና የኃጢአታችንን ቅጣት ስለ ከፈለልን፥ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀናል።
ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ