ወደ እግዚአብሔር መመለስ ወይም «መለወጥ» 

ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ ለደኅንነት አስፈላጊ ስለሆኑ ነገሮች ተምረናል። በዚህን ጊዜ ለደኅንነት አንድ ነገር ብቻ እንደሚያስፈልግ ተመልክተናል። ነገር ግን ይህ አንድ ነገር ደግሞ በሦስት ልዩ ልዩ መንገዶች እንደሚገለጽ አስተውለናል። አንዳንድ ጊዜ ይህ ነገር «ንስሐ» ተብሎ ይገለጻል። ስለዚህ ለመዳን ከራሳችን ይልቅ ወደ ክርስቶስ ብቻ መመለስ አለብን። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ይህ የደኅንነት አንድ ነገር «እምነት» ይባላል። ስለዚህ ለመዳን በመልካም ሥራችን መታመን ትተን በክርስቶስ፥ በእርሱ ሞትና በትንሣኤው መታመን መጀመር አለብን። በአዲስ ኪዳን ውስጥ የደኅነት መንገድ በሦስተኛው መንገድ የተጠቀሰበት ሁኔታም አለ። ይህ የደኅንነት አንዱ መንገድ በሦስተኛው ሌላው መንገድ የተገለጸው «ወደ እግዚአብሔር መመለስ” በሚል ነው። በሌላ ጊዜ ደግሞ ይህ «መለወጥ» ተብሎ ይጠራል፡ መለወጥ የሚለው ቃል ገቢራዊና ተንቀሳቃሽ የሆነ ቃል ነው። ሰዎች የደኅነትን ስጦታ ለማግኘት ሲሉ የሚኖራቸውን ስሜትና ድርጊት ያመለክታል። እዚህ ላይ ለደኅንነት «ወደ እግዚአብሔር መመለስ» ሲባል ምን ማለት ነው? 

1. መለውጥ በብሉይ ኪዳን ውስጥ፡- በሐሰተኛ አማልክት ፈንታ በያሕዌ መታመንና መታዘዝ 

ጥያቄ፡- ኢሳይያስ 31፡6 አንብቡ። ሀ) እግዚአብሔር እስራኤላውያንን እንዴት ይገልጻዋል? ለ) እግዚአብሔር እስራኤላውያን ምን እንዲፈጽሙ ይጠራቸዋል? 

ጥያቄ፡- ሆሴዕ 11፡12 እና 12፡6 አንብቡ፡፡ ሀ) እስራኤል በእግዚአብሔር ላይ ምን አደረገ? ለ) እስራኤል ምን እንዲያደርግጠራው? 

ጥያቄ፦ አሞጽ 4፡1፥ 4፥6 አንብቡ። ሀ) እስራኤል ምን ኃጢአት ሠራ? ለ) እግዚአብሔር እስራኤልን ቢቍጣውም ገና አልፈጸመም ያለው ምንድን ነው? 

እግዚአብሔር ሰዎች እንዲለወጡ ወይም ወደ እርሱ እንዲመለሱ ወደ እርሱ ሊጠራቸው ምን ማለቱ እንደሆነ ብሉይ ኪዳን የዚህን መነሻ ምክንያት ይሰጠናል። የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑት እስራኤልና ይሁዳ አንዱን እውነተኛ አምላክ ማምለክ ትተው ስለ ተመለሱ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ሰበኩ፣ ደግሞም ጻፉ። በዙሪያቸው ያሉ ሕዝቦችን ሐሰተኞች አማልክትን ማምለክ ጀመሩ። እነዚህን ሐሰተኞች አማልክት እንዴት እመላኩዋቸው? የእነዚህን ሐሰተኛ አማልክት መቅደሶች ጎበኙ። እነዚህ ሐሰተኛ አማልክት መልካም ሰብል እንዲሰጡዋቸው፣ ከበሽታ እንዲጠብቁዋቸውና በጦር ሜዳ ድልን እንዲያጎናጽፉአቸው መሥዋዕትንና መባን አቅርበው ሰዉላቸው። ለወደፊቱ ስለሚሆነው ነገር ምክርና መመሪያን ከሐሰተኞቹ አማልክት ጠየቁ። በእነዚህ የሐሰት አማልክት ፊት ሞገስ ለማግኘት ሲሉ ትእዛዞቻቸውን ሁሉ ፈጸሙ። በእውነተኛው አምላክ ላይ በመደገፍ ፈንታ በሐሰተኞች አማልክት ላይ ተደገፉ። እነዚህ አማልክት እንደሚንከባከቡዋቸው ተማመኑባቸው። እግዚአብሔር በበኩሉ በእነዚህ ሐሰተኞች አማልክት መታመናቸውን ትተው ወደ እርሱ እንዲመለሱና በእርሱ ላይ እንዲመረኮዙና በእርሱ ብቻ እንዲታመኑ ጥሪ አቀረበላቸው። መሥዋዕታቸውንና ስጦታቸውን ለያህዌ ብቻ እንዲያደርጉ አሳስባቸው። መልካም መከር፥ ከበሽታ መዳንን እና በጦር ሜዳም ድልን እንዲያገኙ ወደ ያህዌ እንዲጸልዩና በእርሱ እንዲታመኑ ነገራቸው። ስለ ወደፊቱ ሁኔታም መመሪያ ያህዌን ቀርበው እንዲጠይቁ እሳሰባቸው። እምነታቸው በእርሱ ላይ ስለመሆኑ ለማስመስከር የያህዌን ትእዛዝ እንዲፈጽሙ ነገራቸው። 

ስለዚህ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ነቢያት አማካይነት ሕዝቡ ወደ እርሱ ይመለስ ዘንድ ጥሪ አቀረበ። በኢሳይያስ 31፡16 ውስጥ እንደተጻፈው እግዚአብሔር ዐመፀኞች የነበሩ እስራኤላውያን ወደ እርሱ ይመለሱ ዘንድ ነገራቸው። በሆሴዕ 12፡6 ውስጥ ሸንጋዮችንና ዐመፀኞች እስራኤላውያን ወደ እርሱ እንዲመለሱ ጥሪ ያቀርብላቸዋል። በአሞጽ 4፡6ም ላይ ሰካራሞችና በደለኞች የሆኑ እስራኤላውያን የቤቴልንና የጌልጌላን ሐሰተኞች አማልክትን ስላመለኩ በጥፋታቸው ቢቀጣቸውም ከኃጢአታችው አሁንም ያልተመለሱ መሆናቸውን እግዚአብሔር ይናገራቸዋል። የብሉይ ኪዳን ሕዝቦች ወደ ሐሰተኞች አማልክት በመመለስ በእነርሱ መታመን በሚጀምሩበት ጊዜ ሁሉ ወደ እርሱ ተመልሰው እንዲመጡ እግዚአብሔር ይጠራቸው ነበር። 

ሐዋርያትም ወንጌልን መስበክ በጀመሩ ጊዜ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ይመለሱ ዘንድ ይህንኑ የመሰለ ጥሪ ነበር ያቀረቡት። ነገር ግን የእነርሱ ስብከት አትኩሮት የሚለየው ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስና በሥራው አማካይነት ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ነበር። 

2. መለወጥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ፡- ወደ ኢየሱስ መመለስ ወደ እግዚአብሔር ለመምጣት ብቸኛው መንገድ ነው። 

ጥያቄ፡- የሐዋ. 3፡19 አንብቡ። ጴጥሮለ ሕዝቡን ኃጢአታችሁ የሚደመሰሰው ምን ልታደርጉ ነው አለ? 

ጥያቄ፡- የሐዋ. 9፡35 አንብቡ። ጴጥሮስ ኤንያን በፈወሰው ጊዜ የልዳና የሰርና ሕዝብ ምን አደረገ? 

ጥያቄ፡- የሐዋ. 1፡19-21 እንብቡ። የቆጵርለና የቀሬና አማኞች ወንጌልን ፡ ባሰሙዋቸው ጊዜ በአንኪያ የነበሩ ብዙ ሰዎች ምን አደረጉ? 

ጥያቄ፡- የሐዋ. 15፡19 አንብቡ። ጳውሎስና በርናባስ ወንጌልን የሰበኩላቸው አሕዛብ ስማት እንዴት እንደነበረ ነው ያዕቆብ የገለጻው? 

ጥያቄ፡- የሐዋ. 26፡20 አንብቡ። ሐዋርያው ጳውሎስ በሄደበት ስፍራ ሁሉ ምንን እንደሚሰብክ ለንጉሥ አግሪን ነገረው? 

ጥያቄ፡- 2ኛ ቆሮንቶስ 3፡13-16 አንብቡ። እንደ ቁጥር 16 ከእስራኤላውያን ዓይን መጋረጃ ው ይገፈፍ ዘንድ ምን መደረግ አለበት? 

ጥያቄ፦ 1ኛ ተለሎንቄ 1፡9 አንብቡ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለደቀረበው መልእክት የተሰሎንቄ ሰዎች ምላሽ ስሜት ምን ነበር?

ጥያቄ፡- 1ኛ ጴጥሮስ 2፡25 እንብቡ። ሐዋርያው ጳውሎስ አንባቢዎቹ ምን እንዲያደርጉ ነገራቸው? 

ሐዋርያት ሰዎች ወንጌልን ከሰሙ በኋላ ማድረግ ስለሚገባቸው አንደኛው መንገድ ደጋግመው ሲገልጹ ይህ መንገድ ወደ እግዚአብሔር መመለስ መሆኑን ይናገራሉ። በሐዋርያት ሥራ 3፡19 ውስጥ እንደምናገኘው ሽባው ሰው ከተፈወሰ በኋላ ለተሰበሰቡ አይሁዶች ጴጥሮስ ስብከት ባሰማቸው ጊዜ ኃጢአታቸው እንዲደመሰስ ንስሐ ገብተው ወደ እግዚአብሔር መመለስ እንዳለባቸው አበክሮ ነግሮአቸዋል። ጴጥሮስ አክሎ የእግዚአብሔርን መሢሕ እንደ ሰቀሉት ገልጾላቸዋል። አሁን ስለ ኢየሱስ የነበራቸውን አስተሳሰብ ቢለውጡና እርሱ እግዚአብሔር የሚሰጠው ደኅንነት መንገድ መሆኑን ቢያምኑ እግዚአብሔር ለዚህ ኃጢአታቸው ሁሉ ይቅርታን ይሰጣቸዋል። ጴጥሮስ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ በነገራቸው ጊዜ ኢየሱስን መናቅ ትተው ኢየሱስ የእግዚአብሔር ብቸኛው መሢሕና መድኅን መሆኑን ተቀብለው ወደ እርሱ እንዲመለሱ ነበር። በሐዋርያት ሥራ 26፡20 ውስጥ ጳውሎስ ይህንኑ የመሰለ ሁኔታ ለንጉሥ አግሪጳ በነገረው ጊዜ ከሰማይ ራእይ ከመጣለት በኋላ ከኃጢአታቸው ተመልሰው በንስሐ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በመምጣት ይቅርታ ይቀበሉ ዘንድ ለአይሁዶችና ለአሕዛብ ወንጌልን እንደ ሰበከ ገልጦለታል (ቁጥር 18)። ይቅርታን ለማግኘት በሌላ በማንም ላይ መመርኮዝ ሳይኖርባቸው በኢየሱስ ላይ ብቻ መደገፍ ነበረባቸው። በእነዚህ በሁለት ጥቅሶች ላይ ጴጥሮስና ጳውሎስ «ንስሐ» እና «ወደ እግዚአብሔር መመለስ” የሚሉ ቃላትን ወንጌልን የሰሙ ሰዎች ስለሚኖራቸው ስሜትና ምላሽ ለመግለጽ ተጠቅመውባቸዋል። በሁለቱም ጥቅሶች ላይ «ንስሐ» እና ወደ እግዚአብሔር መመለስ» የሚሉት አሳቦች ተመሳሳይ ናቸው። የሐዋርያት ሥራ 11፡21 በአንጾኪያ የነበሩ በተለይም አሕዛብ፥ የቀሬናና የቆጵሮስ ሰዎች «ስለ ጌታ ኢየሱስ ወንጌል» ስሰበኩላቸው ጊዜ ምላሻቸው ምን እንደነበረ ያስረዳል። የምሥራቹን ቃል ከሰሙ በኋላ አምነው ወደ ጌታ ተመለሱ። ስለ ጌታ የደኅንነት የምሥራቹን ወንጌል ከሰሙ በኋላ ወደ ኢየሱስ ተመለሱ። በዚህ ክፍል እምነትና ወደ ኢየሱስ መመለስ ሁለቱም ተመሳሳይ አሳቦች ናቸው። በሐዋርያት ሥራ 9፡35 ውስጥ ኤኒያ ሲፈወስ ያዩ ሰዎች ላግታቸውን ወደ ጌታ በመመለስ ገልጠዋል። በሐዋርያት ሥራ 59 ውስጥ እንደተጠቀሰው በኢየሩሳሌም ሸንጎ ላይ ሐዋርያው ያዕቆብ በአንጾኪያ የነበሩ አሕዛብ ወደ ክርስቶስ መምጣታቸውን ጳውሎስና በርናባስ ባደረጉት የመጀመሪያው የወንጌል አገልግሎት ጉዞ ሳቢያ ጌታን የተቀበሉትን «ወደ እግዚአብሔር የተመለሱትን» ሲል የሰዎቹን ሁኔታ ገልጾአል። በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ባሉ በእነዚህ ጥቅሶች በእያንዳንዳቸው «ወደ እግዚአብሔር መመለስ» የሚለው አሳብ ከንስሐና ከእምነት ጋር በጣም ተመሳሳይ ነው። «ወደ እግዚአብሔር መመለስ» ማለት በእግዚአብሔር ፊት ትክክለኛ ሆኖ የኃጢአት ይቅርታን ለማግኘት በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ብቻ መደገፍ ማለት ነው። 

«ወደ እግዚአብሔር መመለስ» የሚለው አሳብ በአንዳንድ መልእክቶችም ውስጥ ይገኛል። በ2ኛ ቆሮንቶስ 3፡13-16 ጳውሎስ አይሁዶች አሮጌው ኪዳን ሰዓይኖቻቸው ላይ እንደሚደረግ ዐይነ ርግብ ስለሆነ፣ ጊዜያዊ መሆኑንና ለደኅንነትም ብቁ እንዳልሆነ ለማስተዋል አልቻሉም ይላል። ጨምሮም ሲናገር፣ ማንኛውም ሰው ወደ እግዚአብሔር በሚመለስበት ጊዜ፣ መጋረጃ ው ይወገዳል ይላል። ወደ ጌታ መመለስ ማለት ለደኅንነት በአሮጌው ኪዳን ሥርዓትና ሕግ መታመንን ትቶ መመለስና በኢየሱስ መታመን ማለት ነው። በ1ኛ ተሰሎንቄ 1፡9 ውስጥ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ አማኞች ሲናገራቸው ከሐሰተኛ አማልክት አምልኮ ወደ እግዚአብሔር የተመለሱ መሆናቸውን ያሳስባቸዋል። ለእንክብካቤ እነርሱን ለመከላከል ለመምራት ባለው ሁኔታ በሐሰተኞች አማልክት መተማመናቸውን ትተው እውነተኛ በሆነው አምላክ መታመን ጀምረዋል። በመጨረሻውም ላይ፣ በ1ኛ ጴጥሮስ 2፡25፣ በኢሳይያስ 53 ውስጥ የተጻፈውን በማስታወስ ጴጥሮስ ሰዎቹን እንደ ባዘኑ በጎች እንደ ነበሩና፣ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞቱን ባመኑ ጊዜ ወደ ነፍሳቸው እረኛና ጠባቂ መመለሳቸውን ገለጸላቸው። 

አንድ በጣም ማስታወስ የሚገባን ነገር በእነዚህ ጥቅሶች ላይ «ወደ እግዚአብሔር መመለስ» የተባለው ሁኔታ እነዚህ ሰዎች የበለጠ ሃይማኖተኛ ለመሆን የወሰዱት አጠቃላይ ውሳኔ እንዳልነበረ ነው። ስለዚህ «ወደ እግዚአብሔር መመለስ» ማለት እርሱን በበለጠ ለማስደሰት ላቅ ያለ መልካም ሥራ ማከናወን ይሞክሩ ማለት አይደለም። እንደዚሁም «ወደ እግዚአብሔር መመለስ» ሲባል ከቤተ ክርስቲያን ለረጅም ጊዜያት ተለይተው ከቆዩ በኋላ አዘውትረው ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ይጀምሩ ማለት አይደለም። በእነዚህ ጥቅሶች አማካይነት በተላይ መግለጽ የተፈለገው ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ከመጣር ፈንታ በሌላ መንገድ እግዚአብሔርን ለማስደሰት እንደሚዋትቱ ነው። የአይሁድ ሕዝብ የአሮጌውን ኪዳን ሕግ በመጠበቅ እንዲሁም በሚያደርጉዋቸው መልካም ሥራ እግዚአብሔርን ለማስደሰት ይጥሩ ነበር። በዚህ ብቻ ወደ ራሳቸው መንገድ ተመለሱ። ግን በዚህ ፈንታ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘትና ደኅንነትን ለማግኘት ወደ እውነተኛው የእግዚአብሔር መሢሕ ወደ ኢየሱስ መመላስ ነበረባቸው። በዚሁ መሠረት፣ ለባዕዳን አማልክት ይሰግዱ የነበሩ አሕዛብም እነዚህን ሐሰተኞች አማልክትን ማምለክ ትተው በእግዚአብሔር ፊት ትክክለኛችና ተቀባይነትን ያገኙ ሆነው ለመገኘት ደኅንነትን ወደሚሰጣቸው ወደ ኢየሱስ መመለስ ነበረባቸው። በተመለከትናቸው ጥቅሶች እንደተገለጸው «ወደ እግዚአብሔር መመለስ» ማለት ወደ እግዚአብሔር የመሄጃ ው መንገድ ወደሆነው ወደ ኢየሱስ መመለስ ማለት ነው። 

3. መለወጥ፥ ንስሐና እምነት በመሠረታቸው አንድ የሆኑ አሳቦች ናቸው። 

ታዲያ «የመለወጥ» ወይም «ወደ እግዚአብሔር መመለስ» የተባለው አሳብ ከንስሐና ከእምነት ጋር እንዴት ይዛመዳል? አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መምህራን በመለወጥ፥ በንስሐና በእምነት መካከል ያለውን ተዛምዶ ሲገልጹ መለወጥ ማለት ወንጌልን ከሰማን በኋላ ስለሰማነው የወንጌል መልእክት ምን ማድረግ እንደሚገባን የሚገልጽ አጠቃላይ አሳብ ነው ይላሉ። ቀጥለውም ንስሐና እምነት የመለወጥ ሁለት ክፍሎች ናቸው ይላሉ። በንስሐ ከኃጢአታችን መመለስ ይኖርብናል። ከዚያም ወደ ክርስቶስ በእምነት እንመለሳለን። ንስሐና እምነት ሲደመሩ ውጢታቸው መለወጥ ይሆናል። መለወጥ ደግሞ ደኅንነትን ለመቀበላችን ያለብንን ኃላፊነት የምናስረዳበት ብቸኛው መንገድ ነው። 

ሆኖም፥ እኔ እንደሚመስለኝ አዲስ ኪዳን ንስሐንና እምነትን የመለወጥ ሁለት ክፍሎች አድርጎ አይገልጸውም። በዚህ ፈንታ፣ አዲስ ኪዳን ሦስቱን ርእሶች ማለትም «ንስሐ»፣ «እምነት» እና «ወደ እግዚአብሔር መመለስ» የተባሉትን አንዱን በሌላው በመተካት እያፈራረቀ ይጠቀምበታል። እያንዳንዱ ወንድም ሆነ ሴት የእግዚአብሔርን ደኅንነት ለመቀበል ሊፈጽሙት የሚገባ አንዱ አስፈላጊ ነገር የተገለጸባቸው ሦስት መንገዶች ናቸው። ሰዎች ሁሉ ሊያስቡት የሚገባው ኃጢአታቸው የካፋና ከእግዚአብሔርም የለያቸው መሆኑን ነው። እንደዚሁም ሰዎች ሁሉም ሊገነዘቡት የሚገባ በእግዚአብሔር ፊት ትክክለኞች ሆነው ሊቀርቡ የሚችሉበትና ለኃጢአታቸውም ይቅርታ የሚያገኙበት መንገድ በኢየሱስ፥ በእርሱ ሞትና ትንሣኤ ብቻ መሆኑን ነው። ስለዚህ ሰዎች ሁሉ በራሳቸው በጎ ሥራ ወይም ሐሰተኞች በሆኑ አማልክቶቻቸው መመካታቸውን ማቆም አለባቸው። በመሆኑም፣ ወደ ኢየሱስ ሊመለሱና እርሱ የደኅንነት ብቸኛው መንገድ መሆኑን ማመን አለባቸው። 

4. መለወጥ ሊመጣ የሚችለው በእግዚአብሔር ቃል ነው። 

ጥያቄ፡- መዝሙር 119፡59-60 እንብቡ። መዝሙረኛው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለስ ምን ሊመራው ቻለ? 

መዝሙር 119፡59-60 ያለው ቃል ሰዎች ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ የሚያሳስባቸው እጅግ ጠቃሚ የሆነ የእርሱ መሣሪያ ነው። መለወጥን ሊያመጣ የሚችል የእግዚአብሐር ዋና መሣሪያ ቃሉ ነው። ለሰዎች ኃጢአታቸው ምን ያህል የከፋ መሆኑን የሚያሳስባቸው የእግዚአብሔር ቃል ነው። እንደዚሁም ሰዎች ከእግዚአብሔር የተለዩ መሆናቸውን የሚያሳስባቸው የእግዚአብሔር ቃል ነው። እግዚአብሔር በሚሰጣቸው የደኅነት ስጦታ ሳቢያ የኃጢአት ይቅርታን ተቀብለው በእግዚአብሔር ፊት ትክክለኞች በመሆን ተቀባይነትን እንዲያገኙ የሚያደርጋቸው የእግዚአብሔር ቃል ነው። በተጨማሪም ሰዎች በራሳቸው መመካትንና ኃጢአት መሥራትን ትተው ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ በማድረግ ረገድ የእግዚአብሔር ቃል ዋናው መሣሪያ ነው። 

ጥያቄ፡- ሀ) የምታውቋቸው ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ እግዚአብሔር ከመመለሳቸው አስቀድመው ከምን መመለስ ይኖርባቸዋል? ለ) እነዚህ ሰዎች የሚታመኑባቸውን ሌሎች ነገሮችን ትተው በኢየሱስ እንዲታመኑ የሚያደርጉዋቸው ምን ጥቅሶችን ትነግሯቸዋላችሁ? 

እንደ አዲስ ኪዳን አይሁዶችና አሕዛቦች ሁሉ፣ ዛሬ ሰዎች ላደኅንነታቸው ወደ ሌሎች ሰዎችና ነገሮች ይመለከታሉ። ብዙ የሃይማኖት ሰዎች ለደኅንነታቸው ሊሉ፥ ወደ ቅዱሳን ይመለከታሉ። ወደ ቅዱሳን ማተኮራቸውን ትተው ወደ ኢየሱስ ይመለሱ። ብዙ የሃይማኖት ሰዎች ለበጎ ሥራቸው ትኩረት በመስጠት ለደኅንነታቸው አዘውትሮ በቤተ ክርስቲያን መገኘት፥ መጾምና ለድሆች ምጽዋት መስጠት ያስዛሉ። ይልቅስ ይህን ሁሉ ጥረት ትተው ወደ ኢየሱስ መመለስ ይገባቸዋል። አያሌ ሃይማኖታዊ ክርስቲያኖች፥ ከክርስቲያን ቤተሰብ ስለ ተወለዱ፣ ወይም በቤተ ክርስቲያን ስለ ተጠመቁ፣ ደግሞም የሆነ ቤተ ክርስቲያን አባል ስለሆኑ ብቻ የሚድኑ ይመስላቸዋል። በቤተሰባቸውና በቤተ ክርስቲያናቸው መታመንን ትተው ወደ ኢየሱስ መመለስ አለባቸው። ሙስሊሞች ለእምነት አምዶቻቸው መታዘዝን አበክረው ሲመለከቱ፣ ለደኅንነታቸውም የመሐመድን አማላጅነት ልዩ ግምት ይሰጡታል። ለመጻን በመልካም ሥራቸውና በመሐመድ አማላጅነት መታመንን ትተው ወደ ኢየሱስ መመለስ ያስፈልጋቸዋል። ሰዎች ሁሉ የደኅንነትን በረከት ለማግኘት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደ እግዚአብሔር መመለስ አለባቸው።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading