በመንፈስ ቅዱስ መሞላትና መንፈሳዊ ብስለት

ተሾመ ትልቅ ሰው ነበር። ለረጅም ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ተመላልሷል። መጋቢ ወይም ወንጌላዊ ሆኖ አያውቅም። የትምህርት ደረጃ ውም ሁለተኛ ክፍል ብቻ ነበር። ተሾመ ፊደላቱ እጅግ ቢያስቸግሩትም እንኳ በየዕለቱ በትዕግሥት መጽሐፍ ቅዱስን ያነብ ነበር። የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ስላልሆነና የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች በእውቀት ከእርሱ የሚሻሉ ስለነበሩ ማንም ሰው እንደ መሪ ሳያየውም ቅሉ ሕዝቡ በተሾመ የተማረከበት አንድ ጉዳይ ነበር። ሰው በሚቸገርበት ወቅት ሁልጊዜ ፈጥኖ ይደርስ ነበር። ትዕግሥቱ እልቆ፥ ሳላቤቱን ተማቶ አያውቅም ነበር። ሌሎችም ብዙዎችን በትዕግሥት ይመክር ነበር፥ ወዘተ…። ለጥቂት ጊዜ እንኳ ከእርሱ ጋር አብሮ የቆየ ሰው እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ጋር እንደሆነ ይሰማዋል። 

ጥያቄ፡- ሀ) እንደ ተሾመ ያሉ እግዚአብሔርን የሚፈሩና የበሰሉ የእግዚአብሔር ሰዎች መሆናቸውን ማንም የሚመሰክርላቸው ሰዎችን በምሳሌነት ጥቀስ። ለህ እንደዚህ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ምን ይመስልሃል? ሐህ በመንፈስ ቅዱስ በመሞላትና በመንፈሳዊ ሕይወት በሣል በመሆን መካከል ልዩነቱ ምንድን ነው? መ) እነዚህ ሁለት ጽንሰ እሳቦች እንዴት የተያያዙ ይመስልሃል? 

ብዙዎቹ ቤተ ክርስቲያኖች በተለይ በወጣቶች የተሞሉ በሆኑባቸው በእነዚህ ጊዜያት ቤተ ክርስቲያን እጅግ የሚያስፈልጋት ነገር እግዚአብሔርን የሚፈሩ የበሰሉ ወንዶችና ሴቶችን ማግኘት ነው። በጊዜ ሂደት ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ በቅርበት መጓዝ ምን ማለት እንደሆነ በሕይወታቸው የሚያሳዩ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች ያስፈልጉናል። አንድ ሰው በመንፈሳዊ ሕይወት የበሰለ የሚሆነው እንዴት ነው? 

ጥያቄ፡- ሀ) ታዋቂ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን የማራቶን ጀግኖችን ጥቀስ። [ለ) ጥሩ ሯጭ ያደረጓቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ሐ) ማራቶን በመሮጥና አጭር ርቀት በመሮጥ መካከል ምን ልዩነት አለ? መ) የማራቶን ሩጫ በመሮጥና የሕይወትን ሩጫ በመሮጥ መካከል ምን ዓይነት ተመሳሳይነት ታገኛላህ? (1ኛ ቆሮ.9፡ 24-27፤ ፊልጵ. 2፡16፤ ዕብ.12፡1 ተመልከት። 

ኢትዮጵያ በማራቶን ጀግኖች የታወቀች ነች። ከአበበ ቢቂላ ጀምሮ እስከ ፋጡማ ሮባ ድረስ የጥሩ ሯዮች የማያቋርጥ ምንጭ ሆናለች። የማራቶን ራሮች ከአጭር ርቀት ሯጮች በጣም ይለያሉ። የአጭር ርቀት ሯጮች ለአጭር ጊዜ በቻሉት ፍጥነት የሚሮጡ ናቸው። የማራቶን ሯጮች ግን ከአንድ ሰዓት ለበለጠ ጊዜ ረጅም ርቀትን በሚገባ የሚሮጡ ናቸው። የማራቶን ሩጫ ሕመምና ድካም ያላበት እንኳ ቢሆንም እስከ ፍጻሜ የመሮጥን ቁርጥ ውሳኔና መሰጠት የሚጠይቅ ነው። በጥልቅ ሸለቆዎችና በከፍተኛ ተራራዎች ሯጩ እርምጃውን አስተካክሎ መሮጥ አለበት። 

መንፈሳዊ ሕይወት ማራቶን እንደ መሮጥ ነው። ዋናው ነገር በምን ያህል ፍጥነት ወይም ቅልጥፍና ለተወሰነ ጊዜ መንፈሳዊ ሩማን መሮጥ አይደለም። መንፈሳዊ ሕይወታቸውን በታላቅ ሁኔታ ጀምረው በመካክል የሆነ ነገር ተፈጥሮ የወደቁ በርካታ ክርስቲያኖች አሉ። ቁም ነገሩ በሕይወት ዘመናችን ሁሉ መልካሙን ሩጥ መሮጥ ነው። የሚያሳዝነው ግን ብዙ ክርስቲያኖች ትኩረት የሚሰጡት እንድ ክርስቲያን እሁን ምን ያህል ጥሩ እንደሚሮጥ እንጂ ካመነበት ጊዜ ጀምሮ ምን ያህል በሚገባ ይሮጥ እንደነበርና እንዳለ አይደለም። «ድነሃልን?» በማለት ይጠይቃሉ። ሩጫው የሚጀምረው ከዚህ ስለሆነ ጥሩ ጥያቄ ነው። ቀጥሎ «የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ተቀብለሃል?» ይላሉ። ጥያቄያቸው እንደገና ጥሩ ጥያቄ ነው፥ ምክንያቱም ያለ መንፈስ ቅዱስ ኃይልና ሙላት ማንም ሰው እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘትና በመንፈሳዊ ሕይወት ማደግ አይችልም። ነገር ግን የመጨረሻው ከሁሉ የላቀው ጥያቄ «ከዳንክበት ጊዜ ጀምሮ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እየኖርክ ነውን?» የሚል ነው። «በእምነትህና በመንፈሳዊ ሕይወትህ እያደግህ ነውን? በዓመታቱ ሁሉ ውስጥ በጽናት ተመላልሰሃልን?» እኛ የምናተኩረው ሰውዬው አሁን ስለደረሰበት ደረጃ ሲሆን እግዚአብሔር ግን የሚገድደው በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ምን ያህል ስሚገባ እንደሮጠና አሁንም ሞቶ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚሄድበት ቀን እስከሚደርስ እየሮጠ መሆኑ ነው። 22ኛ ጥያቄ፡- የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት። የሐዋ. 20፡7-27፤ 2ኛ ቆሮ. 3፡18፤ 4፡16=18፤ ፊልጵ. 3፡7-14፤ 1ኛ ጢሞ.4፡6-8። እግዚአብሔር በዘመናት ሁሉ በሕይወታችን ሊያደርጋቸው ከሚመክራቸው ነገሮች እንዳንዶቹን ጥቀሱ። እነዚህ ቁጥሮች ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ ያለማቋረጥ መትጋት አስፈላጊ ስለመሆኑ ምን ያስተምሩናል? 

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በብዛት ትምህርት ሊሰጥበት የማንመለከተው አንድ ቃል አለ። ይህ ቃል «መጽናት» የሚል ነው። መጽናት ለረጅም ጊዜ በታማኝነት የመቆየትን ጉዳይ ያመለክታል። ሆኖም ግን መጽናት የክርስቲያን እጅግ አስፈላጊ ባሕርያት ከሆኑት አንዱ ነው። ለምን? የእግዚአብሔር ተቀዳሚ ትኩረት ነገሮች አሁን በሚገባ መከናወናቸው አይደለም። ይልቁኑ እግዚአብሔር የረጅም ጊዜ እመለካከትን ይወስዳል። እግዚአብሔር በሕይወታችን ሊያደርገው ስለሚፈልገው ነገርና እንዴት ምላሹን መስጠት እንዳለብን የሚከተሉትን እውነቶች ልብ በል። 

1. እግዚአብሔር ዕለት በዕለት ሊያድሰን ይፈልጋል (2ኛ ቆሮ. 4፡16-18)። በውስጣችን ከሚከናወነው አብዛኛው ነገር ለመለካት ከባድ ስለሆነ በሕይወታችን ትክክለኛ እሴቶች ወይም ፋይዳዎች ሊኖሩን ይገባል እንጂ በሚታይ ነገር የጨበጥነውን ስኬት መቁጠር የለብንም። የሕይወታችን ስኬታማነት በትምህርት፥ በሥልጣንና በሥራ የሚለካ አይዴለም። እነዚህ የሕይወታችንን ስኬታማነት ለመናገር ትክክለኛ አመልካቾችም አይደሉም። ይልቁኑ እግዚአብሔር በልባችን ያደረገው የማይታይ ሥራ ከማይታየውና ዘላለማዊ ከሆነው የሚመጣ ነው። ከሁሉ የላቀው አስፈላጊ ነገር ነው። 

2. የእግዚአብሔር ተቀዳሚ ትኩረት ኢየሱስ ክርስቶስን እንመስል ዘንድ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ያለማቋረጥ ማደጋችን ነው። ኢየሱስ የነበረው ባሕርይ፥ ፍቅሩ፥ ቸርነቱ፥ ንጽሕናው፥ ጽድቁ፥ ቅድስናው፥ ወዘተ… የእኛ ባሕርያት መሆን ይገባቸዋል (2ኛ ቆሮ. 3፡18)። 

3. ጳውሎስ መንፈሳዊ እድገት እግዚአብሔርን የማያከብሩ ነገሮችን  ማስወገድና የሕይወት ትክክለኛ ግብን መያዝ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ስለዚህ በቤተሰብና በዘር ሊመጣ የሚችለውን ትምክህት ወደ ጎን ትቶ ስለ ኢየሱስ ፍቅር ሞትና የትንሣኤ ኃይል መማርን ግቡ አድርጎ ያዘ። በመንፈሳዊ ሕይወቱ ለማደግ እጅግ ጣረ። ያለፈው ጊዜ ለእርሱ ብዙ ቁም ነገር አልነበረም። ይልቁኑ የሚያሳስበው የወደፊቱ ጉዳይ ነበርና በመልካም ይፈጽመው ዘንድ ተግቶ ሠራ (ፊልጵ. 3፡7-14)። 

4. ጳውሎላ ለአሕዛብ ወንጌልን ይሰብክ ዘንድ አደራ እንደተሰጠው ያውቅ ነበር። ይህ ለሕይወት ዘመኑ በሙሉ የተሰጠ አደራ ነበር። በታላቅ ሐዘን ውስጥ እንባዎች የነበሩበት ነበር። ለብዙ ዓመታት በታማኝነት ማሰብን የሚጠይቅ ነበር። እውነተች ሁሉ በትክክል መሰጠታቸውን የማረጋገጥ ባለአደራነት ነበረበት። የጳውሎስ ሕይወት ታላቁ ፍላጎት ሩጫውን በሚገባ መፈጸም ነበር። ለእምነቱ ቢታሰርና ሲሞትም እንኳ ብድ አልነበረውም። «ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ» እያላ ይልቁን ይፈልግ የነበረው በሚገባ መፈጸሙን ብቻ ነበር። እስካሁን ድረስ የነበረውን እሩግ በሚገባ በታማኝነት ሮጬአለሁ ብሎ ሊናገር ይችል ነበር። ወንጌልን ባይሰብክ ኖሮ ሊኖርበት ይችል ከነበረ ክማናቸውም ሰው ደም እዳ እጁ ንጹሕ ነበር። ነገር ግን ገና ስላልሞተ ወደ ፊት ለመቀጠልና ሩጫውን በሚገባ ለመፈጸም ይፈልግ ነበር (የሐዋ. 20፡7 27)። 

5። ጳውሎስ ጥንቃቄ ባያደርግና ያለማቋረጥ ጸንቶ ባይቀጥል በቀላሉ በኃጢአት በመውደቅ እንደ እንድ ሯጭ ከውድድር እንደሚወገድ ያውቅ ነበር። ስለዚህ፥ ከሩጫው ውድድር እንዳይወጣ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ሁሉ ሥጋውን በሚገባ እንደተቆጣጠረ ይናገራል (1ኛ ቆሮ.9፡24-2)። 

6. ክብዙ ዓመታት በኋላ ጳውሎስ በወህኒ ሆኖ ሞቱን ሊጠበቅ ነበር። በምድር የነበረውን ሩጫ እንዳጠናቀቀና ጌታን የሚገናኝበት ጊዜ እንደደረሰ አውቆት ነበር። አሁን የእፎይታ ትንፋሽን መተንፈስ የሚችልበት ጊዜ ነበር። ሩጫው ተጠናቀቀ። በታላቅ ጽናት ሩጫውን ጨረሰ። እምነቱን አልተወም፤ ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝነት ያጎደላበት ጊዜ አልነበረም (2ኛ ጢሞ.4፡6-8)። 

ጥያቄ፡- እነዚህን ስድስት ነጥቦች ከልዕ። ቀጥሎ ለጸሎትና ቃሉን ለማሰላሰል ጊዜ ውሰድ። በልብህ በእድገት አቅጣጫ ወደፊት ለመቀጠል፥ ለመትጋት፥ በንጽሕና ለመቆየት እግዚአብሔር በሕይወትህ ሁሉ የሰጠህን ጥሪ ለማሟላት ቃል ኪዳን ግባ። 

ከላይ የተመለከቱትን ነገሮች ሁሉ አጠቃልሎ የመግለጫ ሌላው መንገድ በመንፈሳዊ ሕይወት የበሰሉ መሆን ነው። በመንፈሳዊ ሕይወቱ የበሰለ ሰው እስከሚሞትበት ቀን ድረስ ኢየሱስን ለመምሰል ባለው ፍላጎት ያለማቋረጥ በእድገት የሚጓዝ ሰው ነው። ታዲያ በመንፈሳዊ ሕይወታችን የበሰልን የምንሆነው እንዴት ነው? መንፈሳዊ ብስለትን የሚያመጡ ሦስት ዋና ነገሮች አሉ። 

1. ለመንፈሳዊ እድገት መሠረት ከሆኑት ነገሮች መካከል ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረትን በማድረግ መኖር ነው (1ኛ ዮሐ 1፡5-10)። ይህን በሌላ አባባል መግለጽ ካስፈለገ በመንፈሳዊ ሕይወት እንድናድግ ምክንያት የሚሆነን ተቀዳሚ ነገር በመንፈስ ቅዱስ መሞላታችን ነው። በሕይወት ጉዞአችን በማንኛውም ወቅት ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ይኖረናል ወይም አይኖረንም። በመንፈስ ቅዱስ የተሞላን እንሆናላን ወይም ሕይወታችን በመንፈስ ቅዱስ ያልተሞላ ይሆናል።) ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ምንም ዓይነት ኅብረት በማይኖረን ጊዜ እያደግን አይደለንም። ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ኅብረት በሚኖረን ወቅት ግን ያለማቋረጥ እናድጋለን። እንድ አዲስ ክርስቲያን ስለ እግዚአብሔር የሚያውቃቸው እውነቶች የተወሰኑ ቢሆኑም መንፈስ ቅዱስ በሚያስተምረው መንገድ ከኖረ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ይኖረዋል። በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ነው። ይህን ማለት ግን የበሰለ ክርስቲያን ነው ማለት አይደለም። ሌላ ተጨማሪ ነገር መኖር አለበት። 

2. ወደ ብስለት የሚያደርስ መንፈሳዊ እድገት እንዲኖረን እንደ ልማድ አድርገን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መኖር አለብን። በዓመት አንድ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ማድረግና በቀረው ጊዜ ካኅብረት ውጭ መሆን በቂ አይደለም። በዚህ መንገድ ማንም ሊያድግ አይችልም። ነገር ግን በጊዜ ርዝማኔ ውስጥ ከመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሥር በምንሆንበት ወቅት እናድጋለን። በሥጋዊ ክርስቲያንና በመንፈሳዊ ክርስቲያን መካከል ያለው ልዩነት የሚጎላው ከዕለት ወደ ዕለት የሚፈጸደመው ጉዳይ ነው። የአንድ ሰው ሕይወት ለራሱ ደስ የሚያሰኘው ነገር ላይ የተመሠረተ ሆነ ያ ሰው ሥጋዊ ክርስቲያን ነው ነገር ግን የአንድ ሰው ሕይወት የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ቁጥጥር ሥር ከሆነ ያ ሰው መንፈሳዊ ሰው ነው (1ኛ ቆሮ. 2፡5 3፡3)። ወደ መንፈሳዊ ብስለት ለማደግ መንፈስ ቅዱስ ሕይወታችንን ያላማቋረጥ ሊቆጣጠረው ይገባል። የመንፈስ ቅዱስ ሙላት በሕይወታችን ለረጅም ጊዜ መቆየት አለበት። አሁንም ለመንፈሳዊ ብስለት የሚያስፈልግ አንድ ሌላ ሁኔታ አለ። 

3. አንድ ሰው ለጥቂት ቀናት ብቻ በመንፈስ ቅዱስ ከተመራ በመንፈሳዊ ሕይወቱ የስሰላ አይደለም። ለአጭር ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከተመራ በመንፈሳዊ ሕይወቱ የበሰለ አይደለም። አንድን ሰው በክርስቶስ ሕፃን ከመሆን ወደ ብስለት የሚያመጣው የመጨረሻ ነገር ጊዜ ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ጊዜ በወሰድን ልክ፥ መንፈስ ቅዱስ ሕይወታችንን ዘወትር በተቆጣጠረው መጠን፥ መለወጥ እንጀምራለን። ከቀን ወደ ቀን ኢየሱስ ክርስቶስን በመምሰል እናድጋለን። ከዚያም በመንፈሳዊ ሕይወታችን የበሰልን እንሆናላን። ጊዜ በመንፈሳዊ እድገት ውስጥ የራሳቸው ሚና ካላቸው ነገሮች አንዱ እንጂ ብቸኛ ወሳኝ እርሱ እይደለም። ለረጅም ዘመን በክርስትና ውስጥ ኖረው ያላደጉ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው አሁንም ሕፃን የሆኑ በርካታ ክርስቲያኖች አሉ። ከሌሎች ጋር በአንጻራዊነት ሲወዳደር ለጥቂት ጊዜ ብቻ ክርስቲያን የነበሩ እግዚአብሔርን የሚፈሩ የበሰሉ ክርስቲያኖችም አሉ። በመንፈሳዊ ሕይወት ለመብሰል ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም እንኳ መንፈሳዊ ብስለት እውን የሚሆነው ሁልጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከመመላለስ ጋር ሊጣመር ነው። በመንፈሳዊ ሕይወት መብሰላችንን ማወቅ ለራሳችን ብዙ ጊዜ አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳ ሌሎች የሕይወታችንን ለውጥ በማየት ምክር ፍለጋ ወደ እኛ ይመጣሉ። እዚህ በምድር እያለን በሕይወታችን ወደ ፍጹም መንፈሳዊ ብስለት የምንደርስበት አንዳችም ጊዜ የላም። መንፈሳዊ ጉዞ እስከምንሞትበት ቀን ድረስ ያላማቋረጥ የሚደረግ ሂደት ነው። 

አንድ ሰው በአንድ ወቅት በመንፈሳዊ ሕይወቷ የበሰለች አንዲት ክርስቲያንን የክርስትና እርምጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀለለ የሚመጣ እንደሆነ ጠየቃት። ሴቲቱ መልሳ «ፈጽሞ እንዲያውም እየከበደ የሚመጣ ነው» በማለት መለሰችለት። በመቀጠልም «ከእግዚአብሔር ጋር የኖርኩበት ዘመን እየጨመረ በመጣ ቁጥር መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔርን ደስ የማያሰኙ በሕይወቴ ያሉ ነገሮችን የበለጠ እያሳየኝ ሄደ። ለማደግ የሚካሄደው ትግል የበለጠ ከባድ እየሆነ መጣ። ምክንያቱም እግዚአብሔርን ደስ የማያሰኙና ከሕይወቴ መነቀል ያለባቸው ነገሮች በመጀመሪያ ባመንኩበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ከነቀላቸው ይልቅ የበለጠ ሥር የሰደዱና በማንነቴ ውስጥ ጠልቀው የገቡ ይሆናሉ።» አለች። ኃጢአት በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ ያለው ኃይልና ቁጥጥር እየቀነሰ ቢመጣም እንኳ የሰውየው ክፋት ራስ ወዳድነት) ጥልቀቱ የሚገለጠው በመንፈስ ቅዱስ ይበልጥ እያደገ በሄደ መጠን ነው። ልክ ብዙ ገበሮች እንዳሉትና ደረጃ በደረጃ እንደሚላጥ ሽንኩርት ያክል ነው። 

ጥያቄ፡- ወደ ሕይወትህ ተመልክት። ሀ) ክርስቲያን ከሆንክበት ጊዜ ጀምሮ ምን ያህል አድገሃል? ለ) በሕይወትህ አሁን እንኳ ትግል የምታደርግባቸው ክፍሎች ምንድን ናቸው? ሐ) «የመንፈስ ቅዱስ ሙላት» ከዕለት ወደ ዕለት የሕይወትህ አንዱ ክፍል እየሆነ ያለው እንዴት ነው? ካላመብሰል ወደ መብሰል ያመጣን ዘንድ እግዚአብሔር የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች የትኞቹ ናቸው? 

«ወደ መንፈሳዊ ብስለት ማደግ ቀላል ነገር እንዲሆንልን ሁላችንም እንመኛለን። በአንድ አውቶብስ ውስጥ ተቀምጠን እውቶብሱ ወደምንፈልግበት ቦታ እንደሚያደርሰን ሁሉ ወደ መንፈሳዊ ብስለት ፍጻሜያችን የምንደርስ ቢሆን ኖሮ ነገሩ ቀላል ይሆን ነበር። ነገር ግን ጉዳዩ እንደዚያ አይደለም። ማንም ሰው በድንገት ተነሥቶ ማራቶን ለመሮጥ ሊወስን አይችልም። የተዘጋጁ ለመሆንና በጥሩ እካላዊ ሁኔታ ላይ ለመገኘት በሥልጣና በየዕለቱ ለተወሰነ ሰዓት በመሮጥ በጣም መድከም አለባቸው። በመንፈሳዊ ብስለት ማደግ ጠንካራ ሥራን ይጠይቃል። ላማደግ እራስን መስጠት፥ ሥጋን፥ ዓለምንና ሰይጣንን በመንፈስ ኃይል መዋጋትን ይጠይቃል። አዎን እግዚአብሔር ብርታቱን ይሰጠናል። ነገር ግን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይሠራል እንጂ በእኛ ምትክ አይሠራም። በመንፈሳዊ ሕይወት የበሰሉ ክርስቲያኖች ሆነን ለማደግ ልንማራቸው የሚገቡ አንዳንድ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓቶች እሉ። መንፈስ ቅዱስ ወደ መንፈሳዊ ብስለት ያደርሰን ዘንድ የሚጠቀምባቸው አንዳንድ መሣሪያዎች አሉ። 

1. ጾምና ጸሎት፡- ጥልቅና እውነተኛ የሆነ ጸሎት ማድረግ በመንፈሳዊ እርምጃ ችን ለብዙዎቻችን አስቸጋሪ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ነው። ጸሎታችን ብዙ ያልጣለቀ ሆኖ ስራስ ወዳድነት ለራሳችን የሚሆኑ አንዳንድ ነገሮችን ብቻ እንጠይቃለን ወይም ለጸሎት ጥቂት ጊዜ ብቻ እንሰጣለን። ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት የምናደርግበት ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ እድገትን ወደሚያመጣ ትክክለኛ ዝንባሌ የሚገፋፋንም ነው። በምንጸልይበት ጊዜ ትሑት ለመሆን እንገደዳለን። በእግዚአብሔር ላይ ለመደገፍ እንገደዳለን። እግዚአብሔር የሚጠቀመው ትሑቶችን ብቻ ነው። ትዕቢተኞችን ይጠላል ደግሞም ያዋርዳቸዋል። 

ከጸሎት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ሌላው መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ጾም ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊው ጾም በኢትዮጵያ ከምንለማመደው ጾም የተለየ ነው። በአሁኑ ልምምዳችን ኦም በሥራችን ላይ እያለን የተወሰኑ የምግብን ጊዜያትን መዝለል ነው። ወይም ደግሞ የአዳር ጸሉትን ያካትታል። አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ጾምን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወደ ባሕል በመለወጥ ሽማግሌዎች ለእሑድ አገልግሎት ቅዳሜ ሌሊት በሙሉ ሲጾሙና ሲጸልዩ ያድራሉ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነው ኦም ግን አንድ ሰው የተለየ ጉዳይ ሊኖረውና በእግዚአብሔር ፊት በአትኩሮት ጊዜ ወስዶ በመቆየት እግዚአብሔር እንዲሠራ የሚጠይቅበት ነው። ቡ በእግዚአብሔር ፊት መቆየትን ሊያቋርጥ ከሚችል ማናቸውም ነገር፥ ከመመገብም እንኳ ተከልክሎ ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት ግንኙነት ማድረ ነው። በጸሎታችን እውነተኛ አትኩሮት በምናደርግበት ጊዜ እግዚአብሔር ይገናንንና ጸሎታችንን ይመልሳል፥ ደግሞም እንድናድግ ይረዳናል። ጾምን በተለያዩ መንገዶች ልንጠቀምበት ብንችልም እንኳ በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንድናድግ የሚረዳበት አንድ ተጨማሪ ጥቅም አለው። ጾም የሥጋ ፍላጎታችንን መግዛትን ወይም መቆጣጠርን ያስተምረናል። «ሰውነታችንን በመጎሰም ባሪያችን ማድረግን» የምንማርበት ርእሰ መንገድ ነው። በዚህ መንገድ ለመንፈሳዊ እድገት አጋዥ ይሆናልና። 

2. የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናት፥ በቃል መያዝና ማሰላሰል፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የመጽሐፉ ጸሐፊዎች የእግዚአብሔርን ቃል አስፈላጊነት ይነግሩናል። ከማር ይልቅ የሚጣፍጥ ነው (መዝ.119]፡103)። የጻድቅ ሰው መሠረቱ ነው (መዝ. 1፡1-3)። የእውነትን ቃል በትክክል የምንናገር የማናሳፍር ሠራተኞች መሆናችን የሚረጋገጥበት መንገድ ነው (2ኛ ጢሞ. 2፡5)። ወጣቶች የሕይወትን ትክክለኛ አቅጣጫ የሚማሩበት መንገድ ነው (መዝ. [119]፡9-10)። አንድ ክርስቲያን ያድግ ዘንድ መጽሐፍ ቅዱላ የሕይወቱ ዋነኛ ክፍል መሆን አለበት። ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ህልውና የሚያስፈልገን ምግብ ነው። 

መጽሐፍ ቅዱስን በሁለት የተለያዩ ደረጃ ዎች ልናነበው ያስፈልጋል። በመጀመሪያ በጥልቀት እያሰብን መንፈስ ቅዱስ በቃሉ ውስጥ እንዲናገር በማድመጥ ልናነብ ያስፈልጋል። ይህን ዓይነቱን አነባበብ የጥሞና ንባብ ልንለው እንችላለን። በዚህ ንባብ በእግዚአብሔር ቃል ዝርዝር ሁኔታዎች ሳንዋጥ በጥልቀት እያሰብን በጸሎት መንፈስ ሆነን እናነበዋለን። በሁለተኛ ደረጃ ልናጠናው ይገባል። ይህ ማለት እውቀታችን ያለ ስሕተት እንዲሆን የተማርነውን መመርመርና መመዘን ማለት ነው። የእግዚአብሔርን ቃል በጥልቀት ስናጠና እጅግ አስቸጋሪና አጣራጣሪ በሆኑ ጊዜያት ጠንካሮችና ጽኑአን በሚያደርጉን ትላልቅ ምሳሌዎች ነፍሳችንን እንገነባለን። ብዙ ክርስቲያኖች የተላያዩ ጥቅሶችን በቃላቸው ማጥናት ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው ትልቅ እርዳታ ሆኖ ያገኙታል። አስተሳሰባቸውን በምድራዊ ነገሮች ላይ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል። 

3. ፈተናዎች፡- ማናችንም ባንወዳቸውም እንኳ በመንፈሳዊ ሕይወታችን የበሰልን እንሆን ዘንድ እንዲረዱን እግዚአብሔር ከሚጠቀምባቸው ውጤታማ መሣሪያዎቹ እንቶ የተለያዩ ፈተናዎች ወደ ሕይወታችን እንዲመጡ መፍቀድ ነው። አንድ እንጨት ለሚፈለገው ጉዳይ ቅርጹ ትክክል በማይሆንበት ወቅት እናጺው ሞረዱን ወይም መላጊያውን ወስዶ የሚፈልገውን ቅርጽ ለማግኘት መወገድ ያላበትን ያስወግዳል። መንፈስ ቅዱስም የሚያደርገው እንደዚህ ነው። በእርሱ እጆች ፈተናዎች እንደ ሞረድ ወይም መላጊያ ናቸው። በሕይወታችን መልካም ያልሆነውን በመፋቅ ባሕሪያችን እንደ ወርቅ እንዲጣራ ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው እግዚአብሔር ወደ ሕይወታችን ላሚያመጣቸው ፈተናዎች ትክክለኛ በሆነ ዝንባሌ ምላሽ ከሰጠን ፈተናዎቹ በሕይወታችን ጽናትን፥ ባሕርይንና መንፈሳዊ ብስለትን ለማምጣት መሣሪያ ይሆኑናል (ያዕ. 1፡2-4 ሮሜ 5፡3-5)። 

4 የሥነ ሥርዓት እርምጃ ወይም ቅጣት ፡-መንፈሳዊ የሥነ-ሥርዓት እርምጃ ዎች በተለያዩ ፈተናዎች መልክ ሲመጡም እንኳ የሚመጡባቸው ዓላማዎች የተለያዩ ናቸው። ፈተናዎች ከእግዚአብሔር ጋር በቅርብ ግንኙነት በምንመላለስበት ጊዜ እንኳ ይመጣሉ። የሥነ ሥርዓት እርምጃ ግን እግዚአብሔር በሕይወታችን ያለን አንድ ኃጢአት ወይም የተሳሳተ የሕይወት ዝንባሌን ለማስተካከል የሚያመጣው ግሣጼ ውጤት ነው። መንፈስ ቅዱስ የሰሰልን እንድንሆን ከሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች አንዱ ኃጢአትን ከሕይወታችን በማስወገድ የተቀደስን ማድረጉ ነው። መንፈስ ቅዱስ ኃይሉን ሊለቅልንና ሊሞላን የሚችለው በሕይወታችን ያሉ ኃጢአቶችን በንስሐ ስናስወግዳቸው ብቻ ነው። ያልተናዘዝነውን ኃጢአት በሕይወታችን ይዘን ስንቆይ መንፈስ ቅዱስ ኃጢአታችንን ተናዝዘን ክእርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት ወደምናድስበት ነጥብ እስክምንደርስ እንደ በሽታ ያሉ የተለያዩ ነገሮችን በእኛ ላይ ያመጣል። አሳይቶ በመናዘዝና በመተው ከእርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት እናድሳለን። ከዚያም መንፈስ ቅዱስ የመንፈሳዊ እድገት ሂደት እንዲቀጥል ለማድረግ ሥራውን ይሠራል። 

ጥያቄ፡- መንፈስ ቅዱስ በመንፈሳዊ ሕይወት የባሰልህ እንድትሆን እነዚህን አራት መሣሪያዎች እንዴት በሕይወትህ እንደተጠቀመባቸው ግለጽ። 

ተሾመ ያልተማረ ሰው ቢሆንም እንኳ በመንፈሳዊ ሕይወት የበሰለ ክርስቲያን ወደሚባልበት ደረጃ ደርሷል። ለዓመታት በእግዚአብሔር ፊት በመጸለይና ቃሉን በማጥናት አሳልፏል። መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔርን ደስ የማያሰኙ ባሕርያትን ከሕይወቱ ያስወግድ ዘንድ እንዲሠራ ፈቅዷል። ከእርሱ ጋር ባለ ኅብረት በማይመላለስበት ጊዜ እግዚአብሔር ቀጥተታል። ይህ ሁሉ ነገር በጊዜያት መካከል ተሾመ የእግዚአብሔር ሰው በመሆን እንዲያድግ ረድቶታል። 

ትምህርትን እጅግ አግንነን በምናከብርበት በዚህ ዘመን እጅግ መጠንቀቅ አለብን። ትምህርት ከመንፈሳዊ ብስለት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም። የተማርንም ብንሆን ያልተማርን በመንፈሳዊ ሕይወታችን የበሰልኝ መሆን እንችላለን። ግለሰቡ መንፈሳዊ ብስላትን እንዲያገኝ ለማድረግ መንፈስ ቅዱስ ጊዜ ማግኘቱን ስናረጋግጥ በትምህርት ደረጃ ላይ ተመሥርተን የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ከመረጥን በአደጋ ላይ እንወድቃለን። በአሸዋ ላይ ቤት እየሠራን ነው። የሠራነው ቤት ይወድቃል። በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የበሰሉ ክርስቲያኖች ዛሬ ለቤተ ክርስቲያን እጅግ ያስፈልጋሉ። እነዚህን ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ልናገኛቸው የምንችለው እግዚአብሔር የሚጠቀምበትን የመንፈሳዊ ብስለት አሠራር ስናከብር ነው። 

ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ለመምረጥ የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ መመዘኛዎች ምን ምን ናቸው? ለ) የትኞቹ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ናቸው? መጸሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑትለ? ) እግዚአብሔር ፊት እርሱን የሚፈሩና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የበሰሉ መሪዎች ቤተ ክርስቲያኖቻችንን እንዲመሩ አመለካከታችን መቀየር ያለበት እንዴት ነው?

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: