መንፈሳዊ ስጦታ (1ኛ ቆሮንቶስ 14፡1-19)

ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ ስብሰባ እያደረግህ ነው። የተሰበሰባችሁበት ዓላማ በመዝሙር እግዚአብሔርን ለማምለክና ለተወሰነ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ ልታመሰግኑትና ደግሞም በሕይወታችሁ ይሠራ ዘንድ ልትጠይቁት ነው። በመጀመሪያ አንድ ሰው፣ ከዚያም ሁለት ሰዎች፣ በመቀጠልም ሶስት ሰዎች፣ በመጨረሻም በክፍሉ ውስጥ ያሉት ሰዎች ሁሉ በልሳናት መናገር ይጀምራሉ። የስብሰባው መሪ አንተ ነህ። በዚህ ጊዜ ምን ልታደርግ ትችላለህ? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መንፈሳዊ ስጦታዎችን በተለይ ደግሞ በልሳናት መናገርን በተመለከተ ሕዝብ በተሰበሰበት የአምልኮ ስብሰባ ላይ እንዴት አገልግሎት ላይ መዋል እንዳለባቸው የሚናገር መመሪያ አለን? 

ጥያቄ፡- ሀ) የስብሰባው መሪ በሆንክበት ከላይ የተገለጸው ሁኔታ ቢፈጸም ምን ታደርጋለህ? ለ) እንዲህ ዓይነቱን ስብሰባ ማካሄድ የቤተ ክርስቲያን ሰብሰባን ከማካሄድ የሚለይበት መንገድ አለን? ሐ) መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ትክክለኛው አምልኮተ እግዚአብሔር ምን ይመስልሃል? 

በ1ኛ ቆሮ. 12-13 የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በልሳናት የመናገርን ስጦታ ያለአግባብ ስለተጠቀሙባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች ጳውሎስ ይናገራል? በ1ኛ ቆሮ. 12 ላይ በልሳናት መናገር ከመንፈሳዊ ስጦታዎች አንዱ ብቻ እንደሆነና ይህንንም መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን ለመገንባት ለቤተ ክርስቲያን እንደሰጠ አበክሮ ይናገራል። ስለዚህ ክርስቲያኖች በልሳናት የመናገር የተናጠል ትኩረታቸውን መንፈሳዊ ስጦታዎችን በሙላት መጠቀምን በማበርታትና በመጨመር ሚዛናዊ ማድረግ አለባቸው። መንፈሳዊ ስጦታዎች በሙሉ ድንቀኛ የሆኑትና ልዕለ-ተፈጥሮአዊነታቸው ምንም የማያሻማው በአንድ ወገን፥ ዘልማዳዊና ልዕለ-ተፈጥሮአዊ ኃይል በቀላሉ የማይታይባቸው በሌላ ወገን ሆነው በአንድነት መንፈስ ቅዱስ በመካከላቸው የመኖሩ ማረጋገጫ ናቸው። የትኛውም ስጦታ ከየትኛውም ተለይቶ መታየት የለበትም። ደግሞም የትኛውም ስጦታ ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ እስከማይችል ድረስ ችላ መባል የለበትም። 

በ1ኛ ቆሮ. 13 ላይ ጳውሎስ የመንፈሳዊ ስጦታዎች መሠረት መሆን ስላለበት ትክክለኛ ዝንባሌ ትኩረት ይሰጣል። በእውነት መንፈሳዊ መሆን ትፈልጋለህ? መልሱ መንፈሳዊ ስጦታዎችን መጠቀም ላይ አያርፍም። ይልቁኑ መልሱ ያለው እውነተኛ በሆነና ራሱን በሚሠዋ ፍቅር ላይ ነው። መንፈሳዊ ስጦታዎች በፍቅር እስካልተደረጉ ድረስ ምንም ያህል ድንቀኛ ቢሆኑም እንኳ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለግለሰቡ የማይጠቅሙ እንዲያውም ጐጂ ናቸው። የዘላለም ጌታ ከተመለሰ በኋላ እንኳ ቢሆን የሚኖር ፍቅር እንጂ መንፈሳዊ ስጦታዎች አይደሉም። ቀጥሎ በ1ኛ ቆሮ. 14 ላይ ጳውሎስ በተለይ በልሳናት የመናገር ስጦታን ያለአግባብ ስለመጠቀም አጥብቆ መናገር ይጀምራል። ጳውሎስ የሚናገረው በግል የአምልኮ ጊዜ አለመጠቀም ሳይሆን በሕዝባዊ የአምልኮ ስብሰባ ላይ ስለመጠቀም ነው። ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የአምልኮ ስብሰባ በሚመሩበት ጊዜ ሊረዱአቸው የሚገቡ ሁለት ዋነኛ መርሆዎችን ይሰጣቸዋል። 

በመጀመሪያ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚደረጉ ነገሮች ግልጽ የሆኑና ሕዝቡ የሚረዳቸው መሆን አለባቸው (1ኛ ቆሮ. 14፡1-5)። መንፈሳዊ ስጦታዎች ለሁሉም የጋራ ጥቅም ሲውሉ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በሙሉ ሰምተው ሲረዱና እራሳቸውን ሲያንጹ ብቻ እውነተኛ ፋይዳ ይኖራቸዋል። ስለዚህ ክርስቲያኖች መልእክቱ በሚመጣበት ወቅት ሰዎች ሊረዱት እንዲችሉት በትንቢት ስጦታ ላይ እንጂ ትርጉሙ በማይታወቀው በልሳናት መናገር ላይ ማተኮር የለባቸውም። ትንቢቶች ግልጽ የሚነገሩ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የሚመጡ መልእክቶች ናቸው። ክርስቲያኖችም ሆኑ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች ይረዷቸዋል። ስለዚህ በቤተ ክርስቲያን አገልሎት ውስጥ ዋጋ አላቸው። በልሳናት መናገር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከለከለ ባይሆንም እንኳ ቁጥጥር ሊደረግበት ግን ይገባል። መንፈሳዊ ስጦታ ስለሆነ ስሕተት አይደለም። ሆኖም ግን በሕዝብ የአምልኮ ስብሰባ ላይ የሚሰጠው ጥቅም የተወሰነ ነው። በሕዝብ የአምልኮ ስብሰባ ላይ በልሳናት መናገር ካስፈለገ የሚናገሩት ጥቂት ሰዎች ሆነው ልሳኑ መተርጐም አለበት። የማይተረጐም ልሳን ለሕዝቡ የሚሰጠው ጥቅም ስለሌላ በሕዝብ የአምልኮ ስብሰባ ላይ ዋጋ ቢስ ነው። 

ሁለተኛ፣ የአምልኮ ስብሰባ ሥርዓት ያለበት እንጂ የውዥንብርና የግራ መጋባት ስብሰባ መሆን የለበትም (1ኛ ቆሮ. 14፡26-40)። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ለአምልኮ በሚሰበሰቡበት ጊዜ ሁሉም ሰው በአንድ ላይ መናገር ይፈልግ ነበር። ሁሉም በአንድነት በልሳን ይናገሩ ነበር። እጅግ ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ነበር። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔርን ለማምለክ አስቸጋሪ ሁኔታ ከመፈጠሩም በላይ ወደ ስብሰባቸው ተጋብዘው ለሚመጡ የማያምኑ ሰዎች መሰናክል በመሆን ለወንጌል መስፋፋት እንቅፋት ነበር። ጳውሎስ የሚናገረው አምልኮ ሥርዓት ያለው፥ ለእግዚአብሔር ክብርን የሚያመጣና የሚያምኑ ሰዎችንም የሚስብ መሆን አለበት። የልሳናት ንግግሮችም በሙሉ በሥርዓት እንዲደረጉ መቆጣጠር የመሪዎች ኃላፊነት ነው። 

ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ሁለት መርሆዎች በጣም ጠቃሚ የሆኑት ለምን?። ለ) በአምልኮአቸው መንፈሳዊ መስለው ለመታየት ሲሉ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት እነዚህን ሁለት መመሪያዎች የሚተላለፉት እንዴት ነው? ሐ) በዚህ ምዕራፍ በመጀመሪያው አንቀጽ የተገለጸው ሁኔታ ሲኖር የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን ማድረግ አለባቸው? እዚህ ሁለት መርሆዎችስ የሚጠቅሙት እንዴት ነው? 

ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 14፡1-19 አንብብ። ሀ) ጳውሎስ ትንቢት በልሳናት ከመናገር ይሻላል ያለው ለምንድን ነው? ለ) በልሳናት መናገርንና ትንቢት መናገርን አወዳድር። የእያንዳንዳቸው ዓላማ ምንድን ነው? ሐ) በግልጽ ለመረዳት የሚቻሉ ንግግሮች በሕዝቡ አምልኮ ጊዜ በልሳናት ከመናገር ይልቅ የተሻሉ የሚሆኑት ለምንድን ነው? መ) ጳውሎስ ክርስቲያኖች የበለጠ እንዲጠቀሙ የሚያበረታታቸው መንፈሳዊ ስጦታዎች ምን አይነት ናቸው? (ቁጥር 2) ሠ) በልሳናት የሚናገር ሰው የሚጸልየው ምን መሆን አለበት? ለምን? 

1ኛ ቆሮ. 14ን በምናጠናበት ጊዜ ጳውሎስ የሚናገረው ምን እንደሆነ መረዳት እጅግ አስፈላጊ ነው። ካሪዝማቲክ የሆኑትም ሆኑ ያልሆኑ ክርስቲያኖች የጳውሎስ ትምህርት እርሱ ሊለው ከሚፈልገው ውጭ መረዳት የለባቸውም። 1ኛ ቆሮ. 14ን ማጥናት ከመጀመራችን በፊት የሚከተሉትን ነገሮች መረዳት አለብን። 

1. ጳውሎስ ክርስቲያን በገዛ ቤቱ ስለሚያደርገው የግል አምልኮ መናገሩ እይደለም። ይልቁኑ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን በአንድነት ለማምለክ በሚፈልጉበትና በሚሰበሰቡበት ጊዜ በሚሆነው ላይ ነው የሚያተኩረው። አዲስ ኪዳን በልሳናት መናገር በግል የአምልኮ ጊዜ ስለሚኖረው ድርሻ በግልጽ አይናገርም። 

2. ጳውሎስ በልሳናት መናገር ከመንፈሳዊ ስጦታዎች ሁሉ ያነሰና መተው ያለበት ነው አላለም። ይልቁኑ ሁለቱን ስጦታዎች ማለትም በልሳናት መናገርና ትንቢት በሕዝቡ የአምልኮ ስብሰባ ላይ ያላቸውን ጥቅም ብቻ ያወዳድራል፤ በሕዝቡ የአምልኮ ስብሰባ የትኛው የበለጠ ጠቃሚ ነው? በማለት ይጠይቃል። ሁሉም የሚረዳውና መላውን የክርስቶስን አካል የሚገነባ ስለሆነ ትንቢት ይበልጣል በማለት መልስ ይሰጣል። 

3. ጳውሎስ ትንቢት ከሁሉ የላቀ ስጦታ ነው ማለቱም አይደለም። ከሐዋርያነት ወይም ከማስተማር ይበልጣል አላለም። እርሱ የሚለው፣ በሕዝብ የአምልኮ ሰብሰባ ላይ ትንቢት በልሳናት ከመናገር እንደሚበልጥ ነው፡፡

በልሳናት የመናገርና የትንቢት ስጦታ ንጽጽር የሚከተለውን አጥና፡- 

በልሳናት መናገር                                          

ለእግዚአብሔር ብቻ መናገር ነው (1ኛ ቆሮ. 14፡2-3)

እግዚአብሔር ብቻ ይረዳዋል (1ኛ ቆሮ. 14፡2-3፣ 14-15)

ተናጋሪውም ሆነ ሌሎች የማይረዱትን ምሥጢራትን (ሰዎች የሚረዱት እውነት አይደለም) ይናገራል (1ኛ ቆሮ. 14፡3)

እራሳችንን ብቻ ያንጻል (1ኛ ቆሮ. 14፡4)

መልካም ነው (1ኛ ቆሮ. 14፡5)

ለማያምኑ ምልክት ነው (1ኛ ቆሮ. 14፡22)

ሕዝብ በተሰበሰበበት መጠቀም ውዥንብርን ያመጣል (1ኛ ቆሮ. 14፡24)

ሕዝብ በተሰበሰበት ለሁለት ወይም ለሦስት ተናጋሪዎች ብቻ የሚፈቀድ ነው (1ኛ ቆሮ. 14፡27፣ 29)

ካልተተረጎመ መነገር የለበትም (1ኛ ቆሮ. 14፡29)

ትንቢት መናገር

ለሰዎች መናገር ነው (1ኛ ቆሮ. 14፡2-3)

ሰዎች ይረዱታል (1ኛ ቆሮ. 14፡2-3፣ 14-15)

ሰዎች የሚረዱትና ሊያጠነክራቸው ሊያበረታታቸውና ሊያጽናናቸው የሚችል ቃል ይነገርበታል (1ኛ ቆሮ. 14፡3)

ቤተ ክርስቲያንን ያንጻል (1ኛ ቆሮ. 14፡4)

ብዙ ሰዎችን ስለሚያንጽ የተሻለ ነው፡፡ (1ኛ ቆሮ. 14፡5)

ለሚያምኑ ምልክት ነው (1ኛ ቆሮ. 14፡22)

ሕዝብ በተሰበሰበበት መነገሩ ሰዎችን ወደ ንስሐ ያደርሳል (1ኛ ቆሮ. 14፡24)

ሕዝብ በተሰበሰበበት ለሁለት ወይም ለሦስት ተናጋሪዎች ብቻ የሚፈቀድ ነው፡፡ (1ኛ ቆሮ. 14፡27፣ 29)

መፈተን አለበት (1ኛ ቆሮ. 14፡29)

1ኛ ቆሮንቶስ 14፡1-5 

በዚህ ክፍል የምንመለከተው ጳውሎስ ሰዎች በልሳናት ከመናገር ይቆጠቡ ዘንድ መምከሩን አይደለም። ይልቁኑ በልሳናት መናገር በተላይ በሕዝብ የአምልኮ ስብሰባ ላይ ያለውን ድርሻ ሰዎች እንዲያውቁት ነው የሚፈልገው። በአምልኮ ስብሰባ ላይ ትንቢት ሰዎች ሁሉ በሚገባቸው ቋንቋ ስለሚነገር ሰዎችን በእምነታቸው ለመገንባት ይጠቅማል። በጉባኤ የተገኙትን ሰዎች ያነጻል። መንፈሳዊ ስጦታዎች የሚሰጡት በተቀዳሚ ለክርስቲያኖች ሁሉ ጥቅም ስለሆነ በልሳናት ከመናገር ይልቅ ትንቢት ይህን የመንፈሳዊ ስጦታዎችን ዓላማ ያሟላል። 

1ኛ ቆሮንቶስ 14፡6-12

ንግግር ሰዎችን ሊያንጽ የሚችለው ሰዎች ሲረዱት ብቻ ነው። ሌላውን ሰው ሊያንጸው የሚችለው የሚገባው ነገር ብቻ ነው። በቤተ ክርስቲያን የሚደረጉ ንግግሮች አቀራረባቸው ሰዎች ሊረዱት በሚችል ከእግዚአብሔር ዘንድ በሚመጣ መገለጥ፥ እውቀት፥ ትንቢት ወይም የምክር ቃል መልክ መሆን ያለበት ለዚህ ነው። በልሳናት መናገር በራሱ ሌላውን ሰው ለማነጽ አይችልም። በልሳናት የሚናገረውን ሰው መንፈስ ከፍ ያደርግ ይሆናል። ነገር ግን የሚነገረው ነገር ለሌላው ሰው የሚገባ ስላይደለ ሌላ ክርስቲያንን ለማነጽ አይችልም። በቆሮንቶስ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ጳውሎስ ወደ እነርሱ መጥቶ «መንፈሳዊ» መሆኑን ለማሳየት እንደ እነርሱ ግንዛቤ በልሳን ይናገርላቸው ዘንድ የጠበቁ ቢሆንም እርሱ ይህን በማድረጉ የቆሮንቶስ ሰዎች የሚያገኙት አንዳችም ጥቅም እንደሌለ ይነግራቸዋል። ስለማይረዱት በዚህም ምክንያት ስለማይታነጹበት ንግግሩ ከንቱ ይሆን ነበር። 

በልሳናት መናገር እስካልተተረጐመ ድረስ ከንቱ መሆኑን ለማሳየት ጳውሎስ የሙዚቃ መሣሪያዎች (ዋሽንትና ክራር)፥ የጦርነት ማወጃ መሣሪያ መለከትን እና የማይታወቁ ቋንቋዎችን እንደ ምሳሌ ይጠቀማል። ጳውሎስ የሚለውን በሚከተለው መንገድ መግለጽ ይቻላል። አንድ ሰው ጊታር በሚጫወትበት ጊዜ ክሮቹን በዘፈቀደ በማዘበራረቅ ቢመታ የሚሰጠው ድምጽ ምንም ስሜት የማይሰጥ ወይም መልካም ቃና የሌለው ይሆናል። መዘምራንም ሆነ ጉባኤውን መዝሙሩን ወይም በየትኛው ቃና መዝሙራቸውን መጀመር እንዳለባቸው እንዲያውቁት አይረዳም። በቀበሌ ወይም በገጠር ጥሩምባ በመንፋት ማስታወቂያን የሚናገር ሰው የጥሩምባውን ድምጽ በሚገባ የማይለይ ከሆነ ዋጋ አይኖረውም። አንዱ የአደጋ ማስጠንቀቂያ፥ ሌላው ድምጽ የአንድን ሰው ሞት የሚያመለክት፥ ሌላው ደሞ ሕዝቡ ለስብሰባ እንዲከማች የመጥሪያ ነው። ጥሩምባውን የሚነፋ ሰው ለመለየት የሚቻል ግልጽ የሆነ ድምጽ እንዲሰማ ካላደረገ የድምጽ መልእክት አደጋ ይሁን ሞት ወይም ጠቅላላ ስብሰባ የሚለየው ሰው አይኖርም። 

ድምጽ በራሱ ከንቱ ነው። ግልጽና ለመረዳት የሚቻል መሆን አለበት። ስለዚህ ልሳናት ያለ ግልጽ ትርጉም ከተነገሩ ማንም ሰው ሊረዳቸውና ሊታነጽባቸው አይችልም። ባዶና ትርጉም የላሽ ድምጽ ይሆናሉ። አንድ የማትረጻውን ባዕድ ቋንቋ የሚናገር ሰው መጥቶ የሚያነጋግርህን ያህል ነው። እንደ ትንቢት ያሉ ሰዎች ሁሉ ሊረዷቸው የሚችሉትን ስጦታዎች መፈለግ አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ ነው።  

ጥያቄ፡- ሀ) በዕለታዊ ሕይወታችን ከተለመዱና ከምናውቃቸው ነገሮች ለመግባባትና ትርጉም ያለው ግንኙነት ለማድረግ ግልጽ የሆኑ ድምጾች ያሉአቸውን ምሳሌዎች ስጥ። ለ) እነዚህ ነገሮች ግልጽ ሳይሆኑ ሲቀሩ ለሕዝቡ የሚያስከትለው ውጤት ምንድን ነው? 

1ኛ ቆሮንቶስ 14፡13-19 

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በልሳናት ለሚናገሩ ሰዎች የሚጠቅም መመሪያ 

መታነጽ የሚገኘው መልእክቱ ግልጽና ሌሎች የሚረዱት ከሆነ ብቻ ስለሆነ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ለእራሳቸውና ለሌሎች በሚገባ መንገድ መልእክታቸውን ይናገሩ ዘንድ ያበረታታቸዋል። ጳውሎስ የሚናገረው ሕዝብ በተሰበሰበበት ስለሚደረግ የአምልኮ ስብሰባ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል። 

(ማስታወሻ፡— ጳውሎስ የሚናገረው በአጠቃላይ ሰለልሳናት ለለመናገር ይሁን ወይም ሕዝቡ በተሰበሰበት የአምልኮ ስብሰባ ላይ ስለሚነገር ልሳን ይሁን፥ በክርስቲያኖች መካከል አንዳንድ ውዝቦች አሉ። አንዳንድ ሊቃውንት መንፈሳዊ ስጦታዎች በሙሉ በአጠቃላይ ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ስለሆኑ፥ በልሳናት መናገር በግል የአምልኮ ጊዜ እንጂ ቤተ ክርስቲያንን በሙሉ ሊጠቅም ስለማይችል በጉባኤ መካከል በልሳናት መናገር አይፈቀድም ይላሉ። ሌሎች ሊቃውንት ደግሞ ጳውሎስ እየተናገረ ያላው በልሳን የመናገር ስጦታ አለአግባብ ሥራ ላይ ስላዋለበት ልዩ ሁኔታ ነው ይላሉ። ሁኔታው ሕዝብ በተሰበሰበበት የአምልኮ ስብሰባ ላይ ልሳናት አለ አግባብ ስለተተገበሩ የተፈጠረ ሁከት ነው። የተናጋሪውን አምልኮ ስለሚያንጽ ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮ. 14 ላይ ይህን በመደገፍ ፍንጭ አሳይቷል! ይላሉ። የሚከተሉትን ምክንያቶች ይጠቁማሉ።) 

1. በ1ኛ ቆሮ. 14፡2 በልሳን የሚናገር ለእግዚአብሔር ይናገራል ይላል። እዚህ ላይ ጳውሎስ የሚለው በልሳናት በመናገር ሰውየው ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው እንደማይናገርና ግንኙነቱ የሚደረገውም በግለሰቡና በእግዚአብሔር መካከል መሆኑን ነው። ይህ ሕዝብ በተሰበሰበበት የአምልኮ ቦታ ስለሚሆን ነገር የተነገረ አይደለም። ምክንያቱም ሰውዬው የሚናገረው ለእግዚአብሔር እስከሆነ ድረስ ልሳኑ ሊተረጐም አይገባውም። 

2. በ1ኛ ቆሮ. 14፡4 ላይ በልሳናት የሚናገር ራሱን ያንጻል ይላል። በልሳናት መናገር በመሠረቱ አንድ ዓይነት የጸሎት አቀራረብ እንጂ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወጅ አይደለም። 

3. ጳውሎስ በቆሮንቶስ ከሚገኙ ክርስቲያኖች ሁሉ የበለጠ በልሳናት እናገራለሁ ይላል። ነገር ግን ሕዝቡ በተሰበሰበበት የአምልኮ ስብሰባ ላይ ይህንን አላደረገውም። ምክንያቱም በማይታወቅ ቋንቋ በሺህ የሚቆጠሩ ቃሎች ቢናገር ከመናገር ይልቅ በሚታወቅ ቋንቋ ጥቂት ቃሎች ለእርሱ ምርጫው ነበር። ጳውሎስ በልሳናት የተናገረው መቼ ነበር? በእግዚአብሔር ፊት በግሉ በሚጸልይበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ። 

4. ጳውሎስ «በመንፈስ» መጸለይን «በአእምር» ከመጸለይ ጋር ያወዳደረው በግል የአምልኮ ጊዜ በመንፈስ ይጸልይ እንደነበር ለመጠቆም ይመስላል። ወደ ሕዝብ የአምልኮ ስብሰባ በሚመጣበት ጊዜ ግን በአእምሮ መጸለይን ይመርጥ ነበር። 

5. በግል በልሳን መጸላይ በተዘዋዋሪ መንገድ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያንን ይጠቅማል። የግለሰቡን መንፈሳዊ ሕይወት ለማነጽ ጥሩ መሣሪያ ከሆነ ያ ሰው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እግዚአብሔርን ለማገልገል በተሻለ ብቃት ላይ ይገኛል። 

1ኛ ቆሮ. 14፡13-19 የሚተረጐምባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። አንዳንዶቹ የሚረዱት «መንፈስ» እና «አእምሮ» የሚለውን ቃል ጳውሎስ ሲጠቀም ለእውነተኛ መታነጽና ለመንፈሳዊ እድገት በእንድነት መሥራት እንዳለባቸው ለማመልከት ነው ይላሉ። ምን እንደሚል ሳይረዳ በልሳናት በመናገር የሰው ውስጣዊ መንፈሱ ብቻ መነካቱ ሰውዬው ለእግዚአብሔር የሚለውንም እያወቀ በመንፈስ የመወሰዱን ያህል መልካም አይሆንለትም። በልሳናት መናገር ትክክለኛ ነው። ሆኖም ቀን ሰውዬው የሚጸልየው የሚለውን ነገር በፍጹም ሳይረዳው ነው። ስለዚህ በልሳናት የሚጸልይ በእእምሮው አይረዳም። የሚጸልየውን ለመረዳት የሚሻው ንግግሩ ለአእምሮ የሚገባ መሆን አለበት። 

ሌሎች ሊቃውንት ደግሞ እነዚህን ጥቅሶች፥ ጳውሎስ የግል ጸሎት (በመንፈስ የሚደረግ) እና የማኅበር ጸሎት (በአእምሮ የሚደረግ) ብሎ ለያይቶ እንደሚያይ በጣም የተሻለ እንደሆነ ያስባሉ። በግል ጸሎት ጳውሎስ በልሳናት መናገርን ፈጽሞ አይከለክልም። በሕዝብ የአምልኮ ስብሰባ ግን ግልጽ የሆነ የሚታወቅ ንግግር ያስፈልጋል። በጉባኤ መካከል በልሳን የሚናገር ሰው እግዚአብሔር ልሳን የመተርጐምን ችሎታ እንዲሰጠው ወይም በልሳን የተናገረውን ማወቅ እንዲችል መጸለይ እንዳለበት ጳውሎስ ይመክራል። ይህ ካልሆነ በስተቀር ግለሰቡ በልቡ እግዚአብሔርን የሚያመሰግን ቢሆንም እንኳ የሚናገረውን አይረዳም። (አእምሮው ፍሬ ቢስ ነው።) ስለዚህ አእምሮና መንፈስ በአንድነት ቢሠሩ እጅግ የተሻለ ይሆናል። 

በኅብረት አምልኮ ላይ ልሳን የሚነገር ከሆነ ልሳናት ጠቃሚ እንዲሆኑ፥ ጳውሎስ መሆን የሚገባው ምንድን ነው ይላል? 

በመጀመሪያ፥ በኅብረት አምልኮ ላይ በልሳናት መጸለይ የሚፈልግ የመተርጐም ስጦታ እግዚአብሔር ለእርሱ ወይም ይበልጥ ደግሞ በጉባኤው ውስጥ ለሚገኝ ሌላ ሰው እንዲሰጥ መጠየቅ አለበት። 

ሁለተኛ፣ ማንም ቢሆን በልሳናት መጸለይን ጳውሎስ «በመንፈስ መጸላይ» የሚለውን መከልከል የለበትም። ይህ ማለት በልሳናት የሚጸልየው ሰው በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር ሆኖ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ያደርጋል ማለት ነው። ሆኖም ግን ይህ በግል የአምልኮ ጊዜ በቤት ውስጥ መደረግ ያለበት ነው። ጳውሎስ በግል የጥሞና ጊዜው በልሳን ይጸልይ የነበረ ይመስላል። ሕዝብ በተሰበሰበበት ግን፥ ሰው ሁሉ የተነገረው ምን እንደሆነ እንዲረዳ የሚናገረውን በሙሉ አእምሮው እያወቀ በሚታወቅ ቋንቋ ቢጸልይ እንደሚሻል ጳውሎስ ይናገራል። ጳውሎስ ያደረገው ይህንኑ ሲሆን ሌሎችም ምሳሌነቱን ሊከተሉ ይገባል። 

በሦስተኛ ደረጃ፥ ጳውሎስ የልሳን ንግግር ሌላ ገጽታ የሚመስለውን በመንፈስ መዘመርን ይጠቅሳል። በግሉ በሚሆንበት ጊዜ ምን መሆኑን ሳይረዳ በመንፈስ ይዘምር ነበር። ሕዝብ የተሰበሰበበት ቦታ በሚሆንበት ጊዜ ግን እርሱና ሌሎች በሚረዱት ቋንቋ በመዘመር ሁሉም የሚታነጽበትን ሁኔታ ይፈጥር ነበር። (ማስታወሻ– በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ሰዎች በጸሎት ጊዜያት የሚያሳዩት የማዜም ወይም የማንጐራጐር አዝማሚያ በልሳናት የመናገር አንዱ መልክ ተደርጐ ይደረግ እንደሆነ አላውቅም። ነገር ግን የዚህን ምዕራፍ መርሆዎች ተግባራዊ ማድረግ ካለብንና እንደዚህ ዓይነቱ ዝማሬ በልሳናት የሚደረግ ከሆነ በየተራ ሆኖ መተርጐም አለበት። ቤተ ክርስቲያንን ሊያውክ ወይም ከሥርዓት የወጣ ሊሆን አይገባም።) 

አራተኛ፣ ሕዝብ በተሰበሰበበት በምንጸልይበት ወይም በምንዘምርበት ጊዜ ዓላማችን ሁሉም ሰው የተባለው ነገር ገብቶት ሐሤት እንዲያደርግና «አሜን» ማለትም በአንድነት አዎን ጌታ ይሁን እንዲል ነው። «አሜን» የሚለው የአይሁድ ቃል ትርጉም በተነገረው ነገር ሙሉ በሙሉ ተስማምቻለሁ ማለት ነው። የጸሎት መዝጊያ ሥርዓት ወይም ልማድ አይደለም። የሚነገረው ነገር ከመነሻው ግልጽ ሆኖ ወይም ተተርጉሞ ሁሉም ካልተረዱት በቀር ይሁን ብለው መስማማት አይችሉም። የሚነገረውን በአንድነት ከማድመጥ ይልቅ ሁሉም በአንድ ጊዜ የሚጸልይ ወይም የሚዘምር ከሆነ፥ በማኅበር የሚጸለይን ጸሎት ይሁን ወይም አሜን ብለው ለመስማማት አይችሉም። ስለዚህ በልሳናት በመናገር እግዚአብሔርን ማክበር የሚቻል ቢሆንም በጉባኤው ያሉ ሌሎች ካልተረዱ በስተቀር ሊታነጹበትና ሊያድጉበት እንዲሁም ለተነገረው ነገር «አሜን» ሊሉ አይችሉም። በሕዝብ የአምልኮ ስብሰባ ጸሎት ሲደረግ ዝም ብሎ የሚጸልየውን ከማዳመጥ ይልቅ የራስህን ጸሎት የምትጸልይ ከሆነ የተጸለየውን ጸሎት ስላልተረዳኸውና ስላልተስማማህበት «አሜን» ማለት አትችልም። 

አምስተኛ፥ ጳውሎስ በልሳናት ይናገር ስለነበር ሌሎችም እንዲናገሩ እበረታቷል። እንዲያውም በልሳናት የሚናገረው የቆሮንቶስ ሰዎች ሁሉ ከሚናገሩበት በላይ ነበር። ሆኖም ግን ለጳውሎስ በልሳናት መናገር በግሉ እግዚአብሔርን የሚያመልክበት መንገድ ነበር። በሕዝቡ አምልኮ መካከል ግን አሥር ሺህ ቃላትን በልሳናት ከመናገር ይልቅ አምስት የሚገቡ ቃሉችን መናገር የላቀ ነው። ምንም እንኳ ጳውሎስ በኅብረት ከተተረጐመ በልሳናት መናገርን የፈቀደ ቢመስልም ምርጫው ግን ከልሳን በአእምሮ ሰዎች በሚገባቸው ቋንቋ መናገር ነበር። 

(ማስታወሻ፡- ጳውሎስ በኅብረት አምልኮ ወቅት በግል በልሳናት መናገርን የሚደግፍ እይመስልም። ምክንያቱም ይህ በአእምሮው ሰው በሚገባው ቋንቋ ከሚጸልየው ሰው ጸሎት ጋር ለመተባበርና የሚጸልየውም መሆኑን በማረጋገጥ ‹አሜን› ለማለት ጸሎት የአድማጩ ፍላጐት ስለማያስችል ነው። 

ጥያቄ፡- ሰዎች በቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ስብሰባ ወቅት በልሳናት የተናገሩለትን ወደ ኋላ መለስ ብለህ አስታውስ። ሀ) እነዚህ ሰዎች ጳውሎስ በልሳናት ስለመናገር በዚህ የሰጣቸውን ትእዛዛትና መርሆዎች የተከተሉ ነበሩን? ካልነበሩ ለምን? ለ) በልሳናት መናገር አምልኮን ሊረዳ ወይም ሊያጠፉ የሚችለው እንዴት ነው? ሐ) ጳውሎስ ከሰጣቸው መመሪያዎች ጋር አብር የሚሄድ እንዲሆን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን ማድረግ ያለባቸው ይመስልሃል?

ምንጭ፡- “የመንፈስ ቅዱስ የጥናት መምሪያና ማብራሪያ”፣ በቲም ፌሎስ ተጽፎ፣ በጌቱ ግዛው የተተረጎመ እና በኤስ አይ ኤም ጽሑፍ ክፍል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: