የሉቃስ ወንጌል የጥናት መምሪያና ማብራሪያ
ምልከታ እና ትርጓሜ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት ቀደም ብሎ ልኮ ከመለሰ በኋላ፣ አሁን ደግሞ የአገልግሎቱን አድማስ ይበልጥ በማስፋት ሌሎች ሰባ ሁለት ደቀ መዛሙርትን መርጦ እርሱ ሊሄድበት ወዳለው ከተማና ስፍራ ሁሉ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው። ሁለት ሁለት አድርጎ መላኩ እርስ በርሳቸው እንዲበረታቱና በአንድነት እንዲመሰክሩ ካለው ጥልቅ ፍላጎት የተነሳ ነው። ጌታችን አገልግሎቱን ሲጀምር መከሩ ብዙ እንደሆነና ሠራተኞች ግን ጥቂት መሆናቸውን በመናገር፣ በመጀመሪያ ወደ መከሩ ጌታ እንዲጸልዩ አዘዛቸው። ይህም ማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት በጸሎት መጀመር እንዳለበትና ሠራተኞችን የሚልከውም ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ያስተምረናል።
የተላኩት ደቀ መዛሙርት የተሰጣቸው መመሪያ እጅግ ጥብቅና በጌታ አቅርቦት ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲደገፉ የሚያደርግ ነበር። እንደ በጎች በተኩላዎች መካከል እንደሚሄዱ ነግሯቸው፣ ከረጢትም ቢሆን ጫማም ቢሆን እንዳይይዙ አዘዛቸው። ይህ የሚያሳየው የወንጌል መልእክተኞች በምድራዊ ዝግጅትና ቁሳቁስ ላይ ሳይሆን፣ በላካቸው ጌታ ጥበቃ ላይ ብቻ ተደግፈው መሄድ እንዳለባቸው ነው። በገቡበት ቤት ሁሉ ሰላምታ እንዲሰጡና የቀረበላቸውን እየበሉና እየጠጡ እንዲቀመጡ መከራቸው። አገልግሎታቸውም የታመሙትን መፈወስና “የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀርባለች” ብሎ ማወጅ ነበረ። ለወንጌል መልእክት ዝግ የሚሆኑ ከተማዎችን ግን የጥፋታቸውን ትልቅነት በመግለጥ የእግራቸውን ትቢያ እንዲያራግፉባቸው አዘዛቸው።
ደቀ መዛሙርቱ ከተልዕኮአቸው በታላቅ ደስታ ተመለሱ፤ “ጌታ ሆይ፥ አጋንንት እንኳ በስምህ ተገዝተውልናል” በማለት ያዩትን ድል ለጌታ ነገሩት። ጌታችንም “ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ” በማለት በምድር ላይ የሚደረገው የወንጌል አገልግሎት በጨለማው መንፈሳዊ ዓለም ላይ የሚያመጣውን ታላቅ ውድቀት ገለጠላቸው። በእባብና በጊንጥ ላይ፣ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣንን ሰጣቸው። ሆኖም ግን ጌታችን የደስታቸው ምንጭ ሊሆን የሚገባውን ዋና ነገር እንዲያስተውሉ አደረገ። ደስታቸው መናፍስት ስለተገዙላቸው ሳይሆን “ስማችሁ በሰማያት ስለተጻፈ” ሊሆን እንደሚገባ ነገራቸው። ይህ ትልቅ ትምህርት ነው፤ አገልግሎታችንና የምናደርጋቸው ተአምራት የደስታችን ምንጭ ሳይሆኑ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን የድኅነት ግንኙነት ዋነኛው ደስታችን ሊሆን ይገባል።
በዚያች ሰዓት ጌታችን በመንፈስ ቅዱስ ሐሴት አደረገ፤ እግዚአብሔር አብ ይህንን የመንግሥተ ሰማያትን ምስጢር ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውሮ ለሕፃናት (ለትሑታን) በመግለጡ አመሰገነ። እውነተኛ መንፈሳዊ እውቀት የሚገኘው በዓለማዊ ጥበብ ሳይሆን ራስን ዝቅ በማድረግና በልጅነት ልብ ወደ ጌታ በመቅረብ ነው። በመጨረሻም ደቀ መዛሙርቱን ለብቻቸው ዘወር ብሎ “እናንተ የምታዩትን የሚያዩ ዓይኖች ብፁዓን ናቸው” አላቸው። ብዙ ነቢያትና ነገሥታት ክርስቶስ የሚያደርገውን ሊያዩና ሊሰሙ ቢመኙም እንዳልቻሉ፣ እነዚህ ደቀ መዛሙርት ግን ያንን ሰማያዊ ጸጋ በአካል በማየታቸው የታደሉ መሆናቸውን አረጋገጠላቸው። እኛም ዛሬ ቃሉን የመስማትና የመረዳት እድል ስላገኘን ይህንን ታላቅ በረከት ልናስተውል ይገባል።
ተግባራዊ የውይይት ጥያቄዎች
👉ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ሁለት ሁለት አድርጎ የላከው ለምንድን ነው?
👉“መከሩ ብዙ ነው” የሚለው ቃል ዛሬ በወንጌል አገልግሎት ውስጥ እንዴት ይተረጎማል?
👉ደቀ መዛሙርቱ ከአጋንንት መሸነፍ ይልቅ ስማቸው በሰማይ በመጻፉ ደስ ሊላቸው የሚገባው ለምንድን ነው?
👉ኢየሱስ በኮራዚንና በቤተ ሳይዳ ላይ የፈረደው ለምንድን ነው? (ቁ. 13-15)
👉“እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል” (ቁ. 16) የሚለው ቃል ለአገልጋዮች የሚሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት ምንድን ነው?
👉ኢየሱስ “ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ” ማለቱ (ቁ. 18) ስለ መንፈሳዊ ድል ምን ይናገራል?
👉ምስጢርን ከጥበበኞች ሰውሮ ለሕጻናት (ለትሑታን) መግለጹ ስለ እግዚአብሔር አሰራር ምን ያስተምረናል?
👉ደቀ መዛሙርቱ ያዩትንና የሰሙትን ለማየትና ለመስማት ነቢያትና ነገሥታት ይመኙ እንደነበር መገለጹ (ቁ. 24) ክብራቸውን እንዴት ያሳያል?
