የሉቃስ ወንጌል የጥናት መምሪያና ማብራሪያ
ምልከታ እና ትርጓሜ
በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት ወቅት የእግዚአብሔርን ቃል የመስማትና የመቀበልን ምስጢር በምሳሌ ሲያስረዳ እንመለከታለን። ጌታችን የተጠቀመው ምሳሌ በወቅቱ ለነበሩት ሰዎች እጅግ ቅርብ የሆነውን የገበሬና የዘር ታሪክ ነው። ዘሪው ዘሩን ሊዘራ ወጣ፤ ዘሩም አንድ ዓይነት ቢሆንም የረገፈበት መሬት ግን የተለያየ ነበር። ይህ የሚያሳየው ችግሩ በዘሩ (በእግዚአብሔር ቃል) ላይ ሳይሆን ዘሩን በሚቀበለው መሬት (በሰው ልብ) ላይ መሆኑን ነው።
በመጀመሪያው ደረጃ ላይ ዘሩ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም በሉት። ጌታችን ሲተረጉመው እነዚህ ቃሉን ቢሰሙም ዲያብሎስ መጥቶ እንዳያምኑና እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው የሚወስድባቸው ናቸው። ይህም ቃሉን በጥልቀት ለማስተዋልና ለመጠበቅ ልባቸውን ላልከፈቱ ሰዎች ማስጠንቀቂያ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በዓለት ላይ የወደቀው ዘር ነው፤ በቀለ ግን እርጥበት ስላልነበረው ደረቀ። እነዚህ ቃሉን በደስታ የሚቀበሉ ነገር ግን ሥር የሌላቸው በመሆናቸው በፈተና ጊዜ የሚክዱ ናቸው። እምነት ስሜታዊ ደስታ ብቻ ሳይሆን በመከራ ጊዜ የሚጸና ጥልቅ ሥር ሊኖረው እንደሚገባ እንረዳለን። ሦስተኛው ዘር በእሾህ መካከል ወደቀ፤ እሾሁም አብሮ በቀለና አነቀው። እነዚህ ደግሞ ቃሉን ሰምተው ቢሄዱም የዚህ ዓለም አሳብ፣ ባለጠግነትና ተድላ የሚያንቃቸውና ፍሬ የማይሰጡ ናቸው።
በመጨረሻም በመልካም መሬት ላይ የወደቀው ዘር አለ፤ በቀለምና መቶ እጥፍ ፍሬ ሰጠ። እነዚህ ቃሉን በመልካም ልብ ሰምተው የሚጠብቁትና በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው። ጌታችን ይህንን ምሳሌ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ በማለት ቃሉን የምንሰማበትን መንገድ እንድንመረምር አሳስቧል። የሰማነው ቃል በውስጣችን ተደብቆ እንዲቀር ሳይሆን ብርሃን እንዲሆንና ለሌሎች እንዲበራ ይፈልጋል። መብራት ለሰዎች ሁሉ እንዲበራ በመቅረዝ ላይ እንደሚቀመጥ ሁሉ፣ እኛም የተቀበልነው ቃል በተግባር ሊታይ ይገባል።
በዚሁ ክፍል ውስጥ የጌታችን እናትና ወንድሞቹ ወደ እርሱ መጥተው ነበር፤ ነገር ግን ከሕዝቡ ብዛት የተነሳ ሊያገኙት አልቻሉም። ጌታችንም እናትህና ወንድሞችህ ሊያዩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል ተብሎ በተነገረው ጊዜ የሰጠው መልስ የመንግሥተ ሰማያትን አዲስ ዝምድና የሚገልጥ ነበር። እናቴና ወንድሞቼማ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት እነዚህ ናቸው አለ። ይህ ንግግር የሥጋ ዝምድናን ዝቅ የሚያደርግ ሳይሆን፣ እውነተኛ የክርስቶስ ቤተሰብ መሆን የሚቻለው ቃሉን ሰምቶ በመተግበር መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ቃሉን እንደ መልካም መሬት የምንቀበልና የምንታዘዝ ከሆነ ከጌታ ጋር የጸና ዝምድና ይኖረናል።
ተግባራዊ የውይይት ጥያቄዎች
👉አራቱ የልብ አይነቶች (መንገድ ዳር፣ ዓለት ላይ፣ እሾህ መካከል፣ መልካም መሬት) በዛሬው አማኝ ሕይወት እንዴት ይገለጣሉ?
👉የቃሉን ምስጢር ለደቀ መዛሙርቱ በምሳሌ መግለጡ ለምን አስፈለገ?
👉“የዚህ ዓለም ሃሳብና ባለጠግነት” ቃሉን የሚያንቁት (ቁ. 14) በምን መንገድ ነው?
👉ቃሉን “በመጽናት” ፍሬ ማፍራት (ቁ. 15) ለምን ትኩረት ተሰጠው?
👉ኢየሱስ እናቱና ወንድሞቹ ሲመጡ የሰጠው ምላሽ (ቁ. 21) ስለ መንፈሳዊ ዝምድና ምን ያስተምረናል?
👉መስማት ብቻ ሳይሆን “ማድረግ” የደቀ መዝሙርነት እውነተኛ መለኪያ የሆነው እንዴት ነው?
👉መብራት ለብርሃን እንደሆነ ሁሉ፣ የቃሉ ምስጢር ለምን ሊገለጥ ይገባዋል?
👉“ላለው ይሰጠዋል፣ ከሌለውም ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል” (ቁ. 18) የሚለው ቃል ፍትሐዊነቱ እንዴት ይታያል?
