የሉቃስ ወንጌል የጥናት መምሪያና ማብራሪያ
ምልከታ እና ትርጓሜ
የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ አሥራ አምስት ማጠቃለያ ላይ የሚገኘው ይህ ታሪክ በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ እጅግ ከሚታወቁና የሰውን ልጅ ማንነት ከሚገልጡ ታሪኮች አንዱ ነው፡፡ ታሪኩ የሚጀምረው አንድ አባት ሁለት ልጆች ነበሩት በማለት ነው፡፡ ታናሹ ልጅ ገና አባቱ በሕይወት እያለ የአባቱን ሞት እንደመመኘት የሚቆጠረውን ድፍረት በማሳየት የድርሻውን አወርሰኝ በማለት ጠየቀ፡፡ አባቱም ገንዘቡን አካፈለው፡፡ ይህ ታናሽ ልጅ ወደ ሩቅ አገር ሄዶ ገንዘቡን በዝሙትና ያለ ሥርዓት በመኖር አባከነው፡፡ በዚያ አገርም ከባድ ረሃብ በሆነ ጊዜ ምንም የሚበላው አጥቶ የአሕዛብ እሪያዎችን (አሳማዎችን) ወደ መጠበቅ ዝቅ አለ፡፡ አሳማዎቹ ከሚበሉት ፍሬ እንኳ ሊመገብ ቢመኝ የሚሰጠው አጣ፡፡ ይህ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ርቆ በኃጢአት ሲወድቅ የሚደርስበትን የሞራልና የሕይወት ውድቀት በግልጽ ያሳያል፡፡
ታናሹ ልጅ ወደ ልቡ በተመለሰ ጊዜ በአባቱ ቤት ያሉ አገልጋዮች እንጀራ እንደሚተርፋቸው አስቦ ተነሥቶ ወደ አባቱ ለመመለስ ወሰነ፡፡ “አባት ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ” በማለት የንስሐ ቃሉን አዘጋጀ፡፡ እዚህ ላይ ንስሐ ማለት ወደ ልብ መመለስና የተሳሳተውን መንገድ ትቶ ወደ አባቱ (ወደ እግዚአብሔር) መገስገስ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፤ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው፡፡ አባቱ ልጁ ንስሐውን ተናግሮ እስኪጨርስ እንኳ አልጠበቀም፤ ይልቁንም ምርጥ ልብስ አምጡለት፣ ደለባውን ጥጃ እረዱ፣ በእጁ ቀለበት በእግሩም ጫማ አድርጉለት በማለት ድግስ አዘዘ፡፡ ይህ የአባት ፍቅር እግዚአብሔር ንስሐ ለሚገባ ኃጢአተኛ ያለውን ያልተገደበ ይቅርታና አክብሮት ያሳያል፡፡ አባቱ ልጁን የተቀበለው እንደ አገልጋይ ሳይሆን እንደ ቀድሞ ልጁነቱ ነበር፡፡
በዚህ ታላቅ ደስታ መካከል ግን ሌላው የቤት ልጅ የሆነው ታላቁ ወንድም ከእርሻ ሲመለስ የዘፈንና የደስታ ድምፅ ሰማ፡፡ የሆነውን ነገር ሲረዳ ግን እጅግ ተቆጥቶ ወደ ቤት መግባት አልፈለገም፡፡ ይህ ታላቅ ወንድም ምንም እንኳ በአካሉ ከአባቱ ጋር ቢኖርም፣ በልቡ ግን ከአባቱ ፍቅር የራቀ ነበር፡፡ ለአባቱ የሚሰጠው አገልግሎት በፍቅር ሳይሆን በግዴታና እንደ ባሪያ ሥራ ነበር፡፡ “እነሆ፥ ይህን ያህል ዘመን እንደ ባሪያ ተገዝቼልሃለሁ” ማለቱ ለዚህ ምስክር ነው፡፡ ከጓደኞቹ ጋር ደስ እንዲለው አንዲት ጠቦት እንኳ እንዳልተሰጠው በማማረር አባቱን ወቀሰ፡፡ ይህ የፈሪሳውያንና ራሳቸውን ጻድቅ አድርገው የሚቆጥሩ ሰዎች ምሳሌ ነው፡፡ አባቱ ግን ወደ ውጭ ወጥቶ ለመነው፤ “ልጄ ሆይ፥ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፥ ለእኔ የሆነውም ሁሉ የአንተ ነው” በማለት መለሰለት፡፡
ታሪኩ የሚደመደመው ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበርና ሕያው ሆኗል፣ ጠፍቶም ነበርና ተገኝቷል በማለት ነው፡፡ ይህ ክፍል የሚያስተምረን ሁለት ዓይነት የጠፉ ልጆች እንዳሉ ነው፡፡ አንደኛው ከቤት ወጥቶ በግልጽ ኃጢአት የጠፋው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በቤት ውስጥ እያለ በራስ ጽድቅና በፍቅር ማጣት የጠፋው ነው፡፡ እግዚአብሔር አባት ለሁለቱም እኩል ፍቅር አለው፤ ለሁለቱም ወደ ደስታው እንዲገቡ ጥሪ ያደርጋል፡፡ እኛም በልባችን ያለውን የራስ ጽድቅ ጥንካሬ ሰብረን በወንድማችን መመለስ ደስ ሊለንና የአባታችንን መሐሪ ልብ ልንመስል ይገባል፡፡ እውነተኛ ደስታ የሚገኘው በይቅርታና በአባት ቤት ኅብረት ውስጥ ነው፡፡
ተግባራዊ የውይይት ጥያቄዎች
👉ታናሹ ልጅ ሀብቱን እንዲሰጠው መጠየቁና ወደ ሩቅ አገር መሄዱ ስለ ነጻ ፈቃድና ስለ ኃጢአት ምን ያስተምረናል?
👉ልጁ እሪያዎችን እስከመጠበቅ መውረዱ (ቁ. 15-16) ለይሁዲው ማህበረሰብ ምን ያህል ውርደት እንደነበረ እንዴት እንረዳዋለን?
👉“ወደ ልቡ ተመለሰ” (ቁ. 17) የሚለው አገላለጽ ስለ እውነተኛ ንስሐ ጅምር ምን ይናገራል?
👉አባቱ ልጁን ገና ሩቅ ሳለ አይቶ መሮጡና መሳሙ ስለ እግዚአብሔር ይቅርታ ፍጥነት ምን ይነግረናል?
👉ታላቁ ወንድም ወደ ቤት ለመግባት እምቢ ማለቱ (ቁ. 28) የፈሪሳውያንን ባሕርይ እንዴት ይወክላል?
👉“ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበርና ሕያው ሆኗል” (ቁ. 32) የሚለው ቃል ስለ መንፈሳዊ ሞትና ሕይወት ምን ይላል?
👉አባቱ ለታላቁ ልጅ የሰጠው ምላሽ (ቁ. 31) ስለ እግዚአብሔር ባለጠግነት ምን ያስተምረናል?
👉ቀለበት፣ ልብስና ጫማ ለልጁ መሰጠቱ ስለ መመለስና ስለ ልጅነት መብት ምን ይገልጻል?
