የሉቃስ ወንጌል የጥናት መምሪያና ማብራሪያ
ምልከታ እና ትርጓሜ
በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ሃያ አራት ላይ የምናገኘው የኤማሁስ መንገደኞች ታሪክ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ራሱን የገለጠበት እጅግ ልብ የሚነካ መንገድ ነው። ሁለት ደቀ መዛሙርት ከኢየሩሳሌም ወጥተው ሰባት ማይል ያህል ወደምትርቀው ወደ ኤማሁስ መንደር በእግራቸው ይጓዙ ነበር። ልባቸው በሐዘን ተሰብሮ፣ ተስፋቸውም ጨልሞ ስለነበር፣ በመካከላቸው የሆነውን ነገር ሁሉ እየተነጋገሩ ይሄዱ ነበር። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላቸው ቢገኝም፣ ዓይናቸው እንዳያውቀው ተይዞ ነበርና እንደ እንግዳ ቆጠሩት። ይህ የሚያስተምረን ጌታችን በሕይወታችን ፈተናና ሐዘን ውስጥ ስናልፍ ከእኛ ጋር ቢሆንም፣ በጭንቀት ምክንያት የእርሱን መገኘት ላናስተውል እንደምንችል ነው።
ጌታችን ስለ ምን እንደሚነጋገሩና ለምንስ እንደሚያዝኑ በጠየቃቸው ጊዜ፣ ቀለዮጳ የተባለው መንገደኛ በኢየሩሳሌም የሆነውን ነገር የማያውቅ እንግዳ በመሆኑ ተገረመ። እርሱም ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ፣ እርሱ በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ እንደነበረ፣ ነገር ግን ተይዞ እንደተሰቀለ በሐዘን ተረከለት። “እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ተስፋ አድርገን ነበር” ማለቱ፣ ደቀ መዛሙርቱ ስለ መሲሑ የነበራቸው አመለካከት ምድራዊና ፖለቲካዊ ነፃነትን ብቻ የሚመለከት እንደነበር ያሳያል። ተስፋቸው በመስቀሉ ሞት ምክንያት የፈረሰ መስሏቸው ነበር።
ጌታችን ግን የልባቸውን መዘግየትና አለማመን ገሠጻቸው። “እናንተ የማታስተውሉ፥ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ለማመን ልባችሁ የዘገየ” በማለት ጠራቸው። ክርስቶስ መከራን መቀበልና ወደ ክብሩ መግባት እንዳለበት ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ የተጻፈውን ሁሉ ተረጎመላቸው። ይህ ታላቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ነበር፤ መላው ብሉይ ኪዳን ስለ ክርስቶስ መከራና ትንሣኤ የሚመሰክር መሆኑን አስረዳቸው። እውነተኛ እምነት የሚመነጨው እንዲሁ ከተአምራት ሳይሆን፣ የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል ከመረዳት እንደሆነ ከዚህ እንማራለን።
ወደ ኤማሁስ መንደር ሲቃረቡ ጌታችን አልፎ የሚሄድ መሰላቸው፤ እነርሱ ግን “ከእኛ ጋር እደር” በማለት ግብዣ አቀረቡለት። በማዕድም በተቀመጡ ጊዜ ጌታችን እንጀራውን አንሥቶ ባረከ፣ ቆርሶም ሰጣቸው። ያን ጊዜ ዓይናቸው ተከፈተና አወቁት፤ እርሱ ግን ከእነርሱ ተሰወረ። ይህ ክፍል የሚያስተምረን ጌታን የምናውቀው በቃሉና በኅብረት (በእንጀራው መቆረስ) ውስጥ መሆኑን ነው። “በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትንም ሲከፍትልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን?” በማለት ያደረገባቸውን መንፈሳዊ ተፅዕኖ ተገነዘቡ።
ምንም እንኳ ምሽት ቢሆንም፣ ደቀ መዛሙርቱ በዚያችው ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ያገኙትን ታላቅ ደስታ ለሌሎቹ ሐዋርያት ለመንገር ቸኮሉ። በዚያም ጌታ በእውነት እንደተነሣና ለስምዖን እንደታየ ሰሙ፤ እነርሱም በመንገድ የሆነውንና እንጀራውን ሲቆርስ እንዴት እንደታወቀላቸው ተረኩ። ይህ የኤማሁስ ጉዞ ከሐዘን ወደ ደስታ፣ ከጥርጣሬ ወደ እምነት የተደረገ ጉዞ ነው። ዛሬም ጌታ በመንገዳችን ላይ አብሮን ይጓዛል፤ ቃሉን ሲከፍትልን ልባችን በእምነት ይቃጠላል፣ ከእርሱ ጋር ስንኅበር ደግሞ ዓይናችን ይከፈታል።
ተግባራዊ የውይይት ጥያቄዎች
👉ኢየሱስ በኦሪትና በነቢያት ስለ ራሱ መተርጎሙ (ቁ. 27) የመጽሐፍ ቅዱስን ማዕከላዊ
ጭብጥ እንዴት ያሳያል?
👉ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን ማወቅ ያልቻሉት በምን ምክንያት ነበር? ማወቂያቸውስ
ምን ሆነ?
👉“ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን?” የሚለው ቃል የቃለ እግዚአብሔርን ውስጣዊ
ኃይል እንዴት ይገልጻል?
👉ኢየሱስ እንጀራ በመቁረስ (ኅብስት) ውስጥ መገለጡ ከጌታ እራት ሥርዓት ጋር ምን
ግንኙነት አለው?
👉እነዚህ መንገደኞች ወዲያውኑ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው መሄዳቸው ስለ ምሥራቹ
አጣዳፊነት ምን ይናገራል?
👉“እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ተስፋ አድርገን ነበር” (ቁ. 21) ማለታቸው ስለ መሲሑ
የነበራቸውን የተሳሳተ አመለካከት እንዴት ያሳያል?
👉ትንሳኤው የታሪክ እውቀት ብቻ ሳይሆን የግል ግንኙነት መሆኑን ይህ ታሪክ
እንዴት ያሳያል?
ኢየሱስ አብሯቸው እንዲያድር ሲለምኑት መግባቱ ስለ እግዚአብሔር ግብዣ
ምን ያስተምረናል?
