የሮሜ መልእክት መግቢያ
ጥያቄ፡- የሐዋርያት ሥራ 16፡30 እንብብ። ሀ) የወኅኒ ቤቱ ጠባቂ ጳውሎስን ምን ጠየቀው? ለ) ይህ የሰው ልጆች ሊጠይቁ የሚገባው ከሁሉም የላቀ ጥያቄ የሆነው ለምንድን ነው? ሐ) በኢትዮጵያ የተለያዩ የሃይማኖት ክፍሎች ይህን ጥያቄ የሚመልሱባቸውን የተለያዩ መንገዶች ዘርዝር። መ) እግዚአብሔር በእንተ ሕይወት ይህን ጥያቄ የመለሰው እንዴት ነው?
የወኅኒ ቤት ጠባቂው፥ «እድን ዘንድ ምን ላድርግ?» ሲል የሰው ልጅ ሊጠይቅ የሚገባውን ወሳኝ ጥያቄ ነበር ያነሣው። ሁላችንም ብዙ ዓይነት ፍላጎቶች አሉን። ምግብ ከየት እናገኛለን፥ የት እንኖራለን፥ ማንን እናገባለን፥ ሥራ ከየት እናገኛለን? እነዚህ ነገሮች አስፈላጊዎች ቢመስሉም ከጊዜያዊነት አያልፉም። ምላሽ የሚሰጡት ለምድራዊ ሕይወታችን ብቻ ነው። ነገር ግን፥ «እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?» ብለን እግዚአብሔርን ስንጠይቅ ዘላለማዊ ዘለቄታ ያለው ጥያቄ ማንሣታችን ነው። ይሄ ደግሞ አሁን ከእግዚአብሔር ጋር የምናደርገውን ግንኙነት ብቻ ሳይሆን፥ ዘላለምንም የት እንደምናሳልፍ የሚወስን ነው።
ነገር ግን የዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚገኘው ከየት ነው? ሁለት አማራጭ ምንጮች አሉ። በመጀመሪያ፥ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጡ ሰው ሠራሽ ምላሾች አሉ። በዓለም ላይ አብዛኞቹ ሕዝብ ይህን ጥያቄ ስለሚጠይቁ፥ የሚያገኟቸውም ምላሾች የተለያዩ ናቸው። አንዳንዶች፥ «ዘላለማዊ ሕይወትም ሆነ ደኅንነት የሚባል ነገር የለም። ስለሆነም፥ በመብላት፥ በመጠጣትና በመደሰት ራሳችንን ከማዝናናት የተሻለ ነገር የለም» ይላሉ» (1ኛ ቆሮ. 5፥2)። ሌሎች ደግሞ የሕይወታቸውን ክፍተት ለመሙላት ወደ ሌሎች ሃይማኖቶች ይገባሉ። የምሥራቃውያንን ቡድሂዝም ወይም ሂንዱይዝም፥ እስልምናን ወይም የሐሰት ክርስትናን የሚከተሉ ሰዎች አሉ። እነዚህ የሐሰት ሃይማኖቶች በአመዛኙ ሰዎች የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት የተወሰነ ተግባር ሊያከናውኑ እንደሚችሉ የሚያስተምሩ በመሆናቸው ተመሳሳይነት አላቸው።
ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸ የተለየ ዓይነት ደኅንነት አለ። ክርስቶስ፥ «እኔ መንገድና ሕይወት እውነትም ነኝ» በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለምና» ብሏል (ዮሐ. 14፡6)። ለሰማሪያዊቷ ሴት እንደተናገረው። እግዚአብሔርን ለማምለክ የሚፈልግ ማንም ሰው በመንፈስ ብቻ ሳይሆን በእውነትም ሲሰግድለት ይገባል (ዮሐ 4፡21-24)። ጴጥሮስ ስለ ክርስቶስ ሲናገር፥ «እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና» ብሏል (የሐዋ. 4፡12)። ስለሆነም፥ አዲስ ኪዳን «እድን ዘንድ ምን ላድርግ?» የሚለውን ጥያቄ በትክክል ሊመልስ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ ይገልጻል። መልሱም ግልጽ ነው- «በክርስቶስ እመንና ዳን» የሚል ነው (የሐዋ. 168)።
ሰይጣን ይህ ጥያቄ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ስለሚያውቅ፥ ጥያቄውን ኣንሥተን የእግዚአብሔርን ትክክለኛ መልስ እንዳናገኝ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። በብዙ ነገሮች እንድንዳከምና የተለያዩ ምቾቶችን እንድናሳድድ በማድረግ ጥድፊያ ያበዛብናል። በጥድፊያችን ምክንያት ይህን ጥያቄ አንሥተን የእግዚአብሔርን መልስ እንደማናገኝም ተስፋ ያደርጋል። ወይም ደግሞ ሰዎች በሃይማኖት ጥላ ሥር እንዲሆኑና ደኅንነትን በተመለከተ ግን የተሳሳተ ምላሽ እንዲያገኙ ያደርጋል።
ጥያቄ፡- ሀ) ላዎች፥ «እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?» የሚለውን ጥያቄ እንሥተው ትክክለኛ ምላሽ እንዳያገኙ ለማድረግ ሰይጣን የተለያዩ መንገዶችን ሲጠቀም የተመለከትህበትን ሁኔታ ግለጽ ። ለ) እግዚአብሔር የሰጠውን የደኅንነትን መንገድ በግልጽ ማወቅ ለምን የሚያስፈልግ ይመስልሃል? ሐ) የወኅኒ ቤቱ ጠባቂ የጠየቀውን ጥያቄ እንዴት እንደምትመልስ በመግለጽ የእግዚአብሔርን የደኅንነት መንገድ በ100 ቃላት ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።
ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ብቸኛ የደኅንነት መንገድ ጥርት አድርጎ የገለጸው በሮሜ መልእክቱ ነው። ጳውሎስ የየትኛውም ዘር (አይሁዳዊ ወይም አሕዛብ) ወይም ሃይማኖት ተከታይ ቢሆን፥ እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያድንበት ብቸኛው መንገድ በክርስቶስ ላይ በሆነ እምነት እንደሆነ በጥንቃቄ አብራርቷል።
ብዙ ክርስቲያኖች አሳቡን ለመረዳት ሲቸገሩም (ጴጥሮስም እንኳ የጳውሎስን ኣንዳንድ ጽሑፎች ለመረዳት ተቸግሮ ነበር [2ኛ ጴጥ. 3፡1516]፥ በታሪክ ሁሉ እግዚአብሔር በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመለወጥ የሮሜን መልእክት ሊጠቀም ቆይቷል። ይህንንም ያደረገው በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት ሰዎች ስለ እግዚአብሔር መንገድ ግልጽ ግንዛቤ እንዲያገኙ በማድረግ ነው። ለምሳሌ ያህል፥ በ5ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ዓመታት ማርቲን ሉተር የተባለው መነኩሴ የተነሣው፥ ካህናት ለመዳን ብለው ልዩ ልዩ የተሳሳቱ ነገሮችን አጽንተው ያዝዙ በነበረበት ወቅት ነው። ይህ ሰው የሮሜን መልእክት በጥንቃቄ በሚያጠናበት ጊዜ እግዚአብሔር በክርስቶስ በማመን የሚገኘውን ብቸኛ መዳን እንዲመለከት ዓይኖቹን ከፈተለት። ከሰዎች ተቃውሞ በተቃራኒ፥ ማርቲን ሉተር እምነቱን በክርስቶስ ላይ በመጣል፥ «የፕሮቴስታንት ክርስትና» የተባለ እንቅስቃሴ ጀመረ። ይህም ሰዎችን ወደ እግዚኣብሔር የደኅንነት መንገድ የሚመልስ እንቅስቃሴ ነበር። ይህ ሰው በኢትዮጵያ የሚገኙ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አባት ነው።
የሮሜ መልእክት ጸሐፊ
ጥያቄ፡- ሀ) ሮሜ 1 አንብብ። የሮሜ መልእክት ጸሐፊ ነኝ የሚለው ማን ነው? ስለ ራሱ የሰጣቸው ሦስት ገለጻዎች ምንድን ናቸው? እነዚህ ገለጻዎች ስለ ጳውሎለ ምን ያስተምሩናል? ለ) ሮሜን ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብና ስለ ጸሐፊው፥ መልእክቱ ስለተጻፈላቸው ሰዎች፥ መልእክቱ ስለተጻፈበት ዘመን፥ ወዘተ… የሚገልጹትን እውነቶች ጠቅለል አድርህ ጻፍ። ሐ) እግዚአብሔር ሕይወትህን ለመለወጥ የተጠቀመባቸውን የሮሜ መልእክት እውነቶች ዘርዝር።
ቀደም ብለን እንደተመለከትነው፥ የጥንት ዘመን ደብዳቤዎች ብዙውን ጊዜ የሚጀምሩት በጸሐፊው ለም ነበር። ስለሆነም፥ ይህ ደብዳቤ የሚጀምረው ጸሐፊው ጳውሎስ መሆኑን ለሮሜ ቤተ ክርስቲያን በመግለጽ ነው። ጳውሎስ ራሱን በምስት መንገዶች ገልጾአል።
- የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ፡- በግሪኩ ቋንቋ «ባሪያ» የሚለውን ቃል ለመግለጽ ሀ) እስከ ሞት ድረስ የጌታው ንብረት የሆነ ባሪያ፥ ወይም፥ ለ) ከፍቅር የተነሣ ጌታውን በማገልገል ሊቀጥል የመረጠን ባሪያ ሊያመለክት ይችላል። የሮም ዜጎች ነፃ በመሆናቸው ይኮሩ ነበር። በጳውሎስ ዘመን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በባርነት ይኖሩ የነበረ ሲሆን፥ አብዛኞቹ የሌላ ሰው ንብረት መሆንን ይጠሉ ነበር። ጳውሎስ ሮማዊ ዜግነት ያለው ነፃ ሰው መሆኑን ቢያውቅም፥ ራሱን እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ አድርጎ ይመለከት ነበር። ጳውሎስ የክርስቶስ ንብረት የሆነው በፍጥረት መብት ብቻ ሳይሆን በክርስቶስ ደም የተገዛ በመሆኑ ጭምር ነው (1ኛ ቆሮ. 6፡20)። ይህ እውነት ጳውሎስን በጣም ስላስደነቀው ለኩሩ ሮማውያን ባሪያን የመጀመሪያ መግለጫው አድርጎ አቅርቧል። ጳውሎስ ክርስቶስን ለመከተል ስለመረጠ ሕይወቱ በሙሉ ለክርስቶስ ፈቃድ ተገዝቷል። ጌታውን በታዛዥነት መከተሉ በድንጋይ እንዲወገር፥ የመርከብ መሰበር አደጋ እንዲደርሰበት፥ እንዲሰደድ፥ እንዲገረፍና እንዲታሰር አድርጎታል። ነገር ግን ይህ የሚያሳስበው ጉዳይ አልነበረም። ምክንያቱም ጳውሎስ ክርስቶስ የሕይወቱ ጌታ ከሆነ፥ እግዚአብሔር በሕይወቱ ላይ የፈለገውን ጉዳይ የመፍጸምና ወደፈለገው ስፍራ የመላክ መብት እንደነበረው ተረድቶ ነበር። ለጳ ውሎስ ዋናው ጉዳይ የራሱን መብትና ነጻነት ማስጠበቅ ሳይሆን ከጌታው ጋር መልካም ግንኙነት ማድረግ ነበር።
ጥያቄ፡- ሀ) ለሌላ ሰው ባሪያ የመሆንን ኣሳብ የምንቃወመው ለምንድን ነው? ለ) እንደ ጳውሎስ የክርስቶስ ባሪያ እንደሆንህ የምታስብ ብትሆን ሕይወትህ እንዴት ይለወጣል፡ ሐ) ብዙ ክርስቲያኖች የክርስቶስ ባሪያ ነን ብለው የሚያስቡ ይመስልሃል? መልስህን አብራራ።
- ሐዋርያ፡ ከሞላ ጎደል በሁሉም መልእክቶቹ ውስጥ፥ ጳውሎስ ሐዋርያነቱን ይገልጻል። ይህም ስለ ሐዋርያነቱ መግለጹ ለእርሱ በጣም አስፈላጊ እንደነበረ ያሳያል። ሐዋርያው «ክርስቶስ እርሱን እንዲወክል : የላከው ሰው» የሚል ፍች አለው። በአዲስ ኪዳን ሁለት የሐዋርያነት ደረጃ ዎች ነበሩ። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ በተለየ ሁኔታ የመረጣቸውና ለሦስት ዓመታት የተከተሉት 12ቱ ሐዋርያት ነበሩ። እነዚህ ሐዋርያት ወንጌሉን ወደ ዓለም የመውሰድ ብቻ ሳይሆን፥ የቤተ ክርስቲያን ቃል እቀባይ የመሆንና የቀድሞዪቱን ቤተ ክርስቲያን እምነቶች የመወሰን ሥልጣን ነበራቸው። ሁለተኛ፥ ሌሎችም ሐዋርያት ተብለው የተጠሩ ነበሩ (ሮሜ 16፡7 አንብብ)። እነዚህን ሰዎች ለሐዋርያነት ያበቋቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ እምብዛም የተገለጸ ነገር አናገኝም። አንዳንድ ምሁራን እነዚህ ሰዎች ቀደም ሲል ወንጌል ባልተሰበከባቸው አካባቢዎች አብያተ ክርስቲያናትን የተከሉ ናቸው ይላሉ።
እንግዲህ፥ ጳውሎስ የትኛው ዓይነት ሐዋርያ ነበር? ጳውሎስ ክርስቶስ መርጦ ከላካቸው 12 ሐዋርያት ጋር ራሱን እኩል አድርጎ እንደተመለከተ ግልጽ ነው። 2ቱ ሐዋርያት በቀዳሚነት ለአይሁድ አብያተ ክርስቲያናት ሲላኩ፥ ጳውሎስ ክርስቶስ በደማስቆ መንገድ ላይ ተገልጦ የአሕዛብ ሐዋርያ ኣድርጎ እንደ ሾመው ያምን ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ የጻፈው በዚህ ልዩ
የሐዋርያነት ሥልጣን ነው። የጥንቱ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር ይህን ሥልጣን እንደሰጠው እንድትገነዘብና መልእክቶቹን ከክርስቶስ እንደመጡ ያህል በጥንቃቄ እንዲቀበሉ አሳስቧቸዋል። ከሮሜ መልእክት በስተጀርባ ጳውሎስ፥ አሕዛብ የወንጌሉን እውነት እንዲረዱ በእግዚአብሔር ፊት ኃላፊነት እንዳለበት ተሰምቶት ያገለግል ነበር።
ዛሬ የ12ቱን ሐዋርያትና የጳውሎስን ያህል ሐዋርያዊ ሥልጣን እንዳላቸው የሚናገሩ ሰዎች አሉ። ነገር ግን ይህ ለ12ቱና ለጳውሎስ የተሰጠው ሥልጣን ለሌሎች ሊተላለፍ እንደሚችል የሚያመለክት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃ የለም። ካቶሊኮች ከሚያምኑት በተቃራኒ፥ የጴጥሮስ ሥልጣን (ማቴ. 16፡7-19) ወደ ሌላ የቤተ ክርስቲያን መሪ እንደሚተላለፍ የሚያመለክት እሳብ የለም። በቀድሞዪቱ ቤተ ክርስቲያን ጽሑፎች ውስጥ ለሐዋርያነትና ለሌሎች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በተሰጡት ሥልጣናት መካከል ግልጽ ልዩነት ተደርጓል። ዛሬ ሐዋርያት አሉ ቢባል፥ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን እንዲመሠርቱ ያነሣሣቸውን ሁለተኛ ዓይነት ሐዋርያት መሆን አለባቸው።
- ለእግዚአብሔር ወንጌል ተለየ፡- የሮሜ መልእክት በወንጌሉ ላይ ያተኩራል። ጳውሎስ እግዚአብሔር የክርስቶስን ወንጌል ለመስበክ ዓላማ እንደመረጠው ለሮሜ ሰዎች አብራርቷል። ምንም እንኳ ሁላችንም ስለ ክርስቶስ እንድንመሰክር የታዘዝን ቢሆንም፥ ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያንና በዓለም ከነበሩት ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔር እርሱን እንደመረጠው ተረድቶ ነበር። እግዚአብሔር ጳውሎስን የመረጠው ለአንድ ዓላማ ማለትም ወንጌሉን ለአሕዛብ እንዲሰብክ ነበር። ጳውሎስ ሐዋርያ ሆኖ ለጠፉት ወንጌልን መስበኩ ሥራ ብቻ ሳይሆን ግዴታም እንደሆነ ተረድቶ ነበር። እግዚአብሔር ከሌሎች ክርስቲያኖች ሁሉ ለይቶ በመምረጥ ይህንን ሥራ ሰጥቶታል። እግዚአብሔር ጳውሎስ ይህንን ተግባር እንዲያከናውን ኃላፊነት የሰጠው ሲሆን፥ አንድ ቀን ምን ያህል ሥራውን በብቃት እንደተወጣ ፍርዱን ይሰጠዋል፡፡
እግዚአብሔር አንድን መሪ በወንጌላዊነት፥ በሰባኪነት ወይም በአስተማሪነት አገልግሎት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጠቀም ከተፈለገ፥ ግለሰቡ እግዚአብሔር ለተወሰነ አገልግሎት እንደጠራው መረዳት አለበት። በሕዝብ መመረጡ ወይም በደመወዝ መቀጠሩ ብቻ በቂ አይደለም። ነገር ግን በቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ ካሉት ሰዎች ሁሉ መካከል እግዚአብሔር እንደመረጣቸውና ልዩ አገልግሎት እንደሰጣቸው መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ከዚያም እግዚአብሔር አገልግሎቱን ስላካሄዱበት ሁኔታ በኃላፊነት ይጠይቃቸዋል።
ጥያቄ፡– ሀ) ወንጌላውያን፥ መጋቢያንና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በእግዚአብሔር ለመጠራታቸው እርግጠኞች ከሆኑ አገልግሎታቸው እንዴት የሚለወጥ ይመስልሃል? ለ) አብዛኞቹ መሪዎች የሚያገለግሉት እግዚኣብሔር ጠርቶኛል በሚል እምነት ነው ወይስ አይደለም? መልስህን ኣብራራ። ሐ) ቤተ ክርስቲያን ሥራ የሚፈልጉትን ሳይሆን እግዚአብሔር ጠርቶኛል ብለው የሚያስቡትን ኣገልጋዮች ስለመምረዉ አስፈላጊነት ምን አሳብ ትሰጣለህ?
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር እያንዳንዱን አማኝ ለዓላማ እንደጠራው ያስተምራል። ነጋዴ፥ የቤት እመቤት፥ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ ቢሆን፥ እያንዳንዱን ሰው መርጦ ባለበት ስፍራ ላይ የሚያስቀምጣቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ ግለሰቡን ከዚያ ስፍራ ላይ ያስቀመጠው የራሱ ምርጫ ወይም መንግሥት ሳይሆን እግዚአብሔር በመሆኑ፥ ሁለት እውነቶችን ልናስታውስ ይገባል። በመጀመሪያ፥ በሥራችን የምንችለውን ሁሉ ማከናወን አለብን ምክንያቱም የምንሠራው ለራሳችን፥ ለመንግሥት ወይም ለሌላ ሰው ሳይሆን ለእግዚአብሔር ነው። ሁለተኛ፥ በዚያ የተቀመጥነው መንፈሳዊ ብርሃንን ለማብራት ነው። አንድ ቀን ክርስቶስ የጠራንን ዓላማ ስለመፈጸም አለመፈጸማችን በፊቱ ቆመን ምላሽ እንሰጣለን። ሥራችንን ያከናወንበት ሁኔታ ይመዘናል። ፈሪሃ እግዚአብሔር በሌለው ዓለም ውስጥ እንደ ክርስቲያኖች በብርሃን የተመላለስንበትም ሁኔታ ይመዘናል (1ኛ ቆሮ. 3፡15)።
ጥያቄ፡- ሀ) ሙሉ ጊዜያቸውን በአገልግሎት ላይ የሚያውሉና ዓለማዊ ሥራ ላይ የተሰማሩ ክርስቲያኖች ሁሉ እግዚአብሔር በተለየ መንገድ እንደጠራቸውና እነዚህን ኃላፊነቶች እንደሰጣቸው ቢያምኑ፥ ለሥራና ለአገልግሎት ያለን አመለካከት እንዴት የሚለወጥ ይመስልሃል? ለ) በአሁኑ ሰዓት የት እንደምትሠራና ለቤተ ክርስቲያንም የምትሰጠውን ኣገልግሎት ገምግም። የምትሠራውና የምታገለግለው እግዚአብሔር ጠርቶኛል በሚል እምነት ነው? አሁን በክርስቶስ ፊት ለመመዘን ብትቆም፥ የትኛው ክፍል የሚያስደስተው ይመስልሃል? የትኛውስ ያሳዝነዋል? ሐ) እግዚአብሔር የተጠራህለትን ልዩ ዓላማ እንዲገልጽልህ በጸሎት ጠይቀው። ሥራውን ለክብሩ የምታከናውንበትን ኃይል እንዲሰጥህ ጠይቀው።
ጳውሎስ የሮሜን መልእክት ለማን ጻፈ?
ጥያቄ፡ ሮሜ 1፡7 አንብብ። ሀ) ጳውሎስ የመልእክቱ ተቀባዮች እነማን ናቸው ይላል? ለ) የመልእክቱን ተቀባዮች እንዴት ገለጻቸው? ሐ) የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት በመጠቀም፥ ስለ ሮም ከተማና ቤተ ክርስቲያን ጻፍ።
የጥንት ዘመን ደብዳቤዎች መግቢያ ሁለተኛው ዐቢይ ክፍል ደብዳቤው ለማን እንደተጻፈ መግለጽ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ በሮሜ ላላችሁት ሁሉ» ብሏል። ጳውሎስ ይህንን መልእክት የጻፈው በታላቁ የሮም ግዛት መዲና ለነበሩትና በብዙ የተለያዩ ቤቶች ውስጥ ለሚሰባሰቡት ክርስቲያኖች ሁሉ ነበር። «የሮሜ መልእክት» የሚለው የመጽሐፍ ርእስ የተወሰደው የመልእክቱ ተቀባዮች ከመሆናቸው እውነታ ነው።
ጳውሎስ እነዚህን የሮሜ ክርስቲያኖች በሁለት መንገዶች ይገልጻቸዋል። በመጀመሪያ፥ በእግዚአብሔር የተወደዱ መሆናቸውን ይገልጻል። እግዚአብሔር እጅግ ስለወደዳቸው ክርስቶስ እንዲሞትላቸው ላከው። አጥብቆ ስለወደዳቸው ወንጌሉን እንዲሰሙ አደረገ። ይህ የእግዚአብሔር ፍቅርና ደኅንነት የጳውሎስን ሕይወት ስለተቆጣጠረው፥ ምንም ነገር ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንደማይችል የሚገልጽ መዝሙር ተቀኝቷል (ሮሜ 8፡3-39)። ጳውሎስ እግዚአብሔርን ምን ያህል እንደሚወደን ከተገነዘብን፥ በፍጹም ከእርሱ እንደማንለይ ያውቅ ነበር።
ሁለተኛ፥ ጳውሎስ የሮሜ ክርስቲያኖች ቅዱሳን ለመሆን እንደተጠሩ ገልጾአል። ጳውሎስ በተለየ ሁኔታ እንደተመረጠ ሁሉ፥ እያንዳንዱም የርም ክርስቲያን በእግዚአብሔር ለተወሰነ ዓላማ ነበር የተመረጠው። ጳውሎስ ቅዱሳን ለመሆን የተለዩ እንደሆኑ ተናግሮአል፡፡ በአዲስ ኪዳን ቅዱሳን የሚለው ቃል በሁለት መንገዶች ይተረጎማል፡፡ ምንም ሥጋዊነት ያልለቀቃቸው ሲሆኑም ወይም መንፈሳዊ ሕይወታቸው የበሰለም ቢሆኑ ሁሉም ክርስቲያኖች ቅዱሳን ተብለው ይጠራሉ (ምክንያቱም የተለዩ በመሆናቸው ነው)። ማለትም በደኅንነት አማካኝነት የማያምኑ ሰዎች ከሚገኙበት ዓለም ተለይተን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናል። የቃሉ ትርጉም ሙሉ በሙሉ ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር ክብር የሚኖሩትንም ሰዎች ያመለክታል። ጳውሎስ በዚህ ስፍራ ይህን ቃል የተጠቀመው በሁለተኛው ትርጉሙ ነው። እግዚአብሔር የመረጠን ደኅንነትን ካገኘን በኋላ እንዳሻን እንድንኖር አይደለም። እርሱ የመረጠን ሕይወታችን ሁሉ ለእርሱ ክብር እንዲውል ነው። ከኃጢአት ተለይተን በሁለንተናችን እግዚአብሔርን እንድናገለግል መርጦናል።
ጥያቄ፡- እግዚአብሔር «ቅዱስ» እንድትሆን መርጦሃል? ዓላማው ተግባራዊ ይሆን ዘንድ በሕይወትህ ውስጥ ሊለወጡ የሚገባቸው ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?
ጳውሎስ የሮሜን መልእክት በጻፈበት ወቅት ሮምን ኣይቷት አያውቅም ነበር። ስለ ሮም ክርስቲያኖች ያገኘውን መረጃ ያቀበሉት እንደ አቂላና ጵርስቅላ ያሉ ሌሎች ክርስቲያኖች ነበሩ። ነገር ግን ይህች ቤተ ክርስቲያን በክርስትና ታሪክ እጅግ ጠቃሚ ቤተ ክርስቲያን እንደምትሆን ተገንዝቦ ነበር። ስለሆነም፥ ይህች ቤተ ክርስቲያን የክርስትናን መሠረተ አሳብ፥ በተለይም የደኅንነትን እውነተኛ ትርጉም እንድታውቅ አጥብቆ ይሻ ነበር። ጳውሎስ ለዚህች አስፈላጊ ለነበረች ቤተ ክርስቲያን በጣም ጠቃሚ መልእክት ጻፈ።
የሮም ከተማ የሰፊው የሮም ግዛት መዲና ነበረች። በእግዚአብሔር ዕቅድ መሠረት፥ ይህች የሮም ግዛት ወንጌሉና ክርስትና ሥር ሰድደው በዓለም ታላቅ ሃይማኖት የሚበቅልበት ስፍራ ነበረች። ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት፥ ከብሪታኒያ እስከ ኢራንና ከዚያም እስከ ግብጽ በሚዘልቀው የሮም ግዛት ውስጥ 100 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ይኖሩ እንደነበር ይገመታል። ለ1000 ዓመታት ያህል ይህ ግዛት የዓለም ዐቢይ የፖለቲካ ኃይል ነበር። በሮም ከተማ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ይኖሩ የነበሩ ሲሆን፥ ምናልባትም ከተማዪቱ ከየትኛዎቹም የጥንት ዘመን ከተማዎች በላይ የሠለጠነች ነበረች። በሮም ከሚኖሩ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ምናልባትም እብዛኞቹ ባሮች ላይሆኑ አይቀሩም። ብዙውን ጊዜ ወንጌሉ በፍጥነት ሥር ሰድዶ የሚስፋፋው በባሮች መካከል ነበር። ምናልባትም ጳውሎስ ራሱን «የክርስቶስ ባሪያ» ብሎ ከጠራባቸው ምክንያቶች አንዱ፥ ምንም እንኳ እንደ እነርሱ ሥጋዊ ጌቶች ባይኖሩትም መንፈሳዊ ጌታ እንዳለው ለማመልከት ይሆናል።
በሐዋርያት ሥራም ሆነ በጥንታዊ የታሪክ መጻሕፍት ውስጥ ሰፊ ትንታኔ ስለማናገኝ ስለ ሮም ቤተ ክርስቲያን አጀማመር የምናውቀው አሳብ የተወሰነ ነው። ይህች ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደተመሠረተች የሚያወሱ የተለያዩ ንድፈ አሳቦች አሉ። አንዳንድ ምሁራን ከበዓለ ኀምሳው የመንፈስ ቅዱስ መውረድ በኋላ አይሁዶች ክርስትናን ወደ ሮም እንደወሰዱ ይገምታሉ ( የሐዋ. 2፡10)። በክርስቶስ ያመኑት አይሁዶች በሮም ምኩራቦች እምነታቸውን ለሌሎች አይሁዶች አስፋፉ። ከበዓለ ኀምሳ 16 ዓመታት በኋላ፥ በ49 ዓ.ም በከተማዪቱ ውስጥ ክርስቲያኖች ያልሆኑትን አይሁዶች የሚያሰጋ የክርስቲያኖች ቁጥር ሊገኝ ችሏል። የሮም የታሪክ ጸሐፊዎች «ክረስተስ» (Chrestus) በተባለ ሰው ምክንያት አይሁዶች በከተማዪቱ ውስጥ ሁከት መቀስቀሳቸውን ጽፈዋል። በዚህ የክርስቶስን ስም በሌሎች ሆሄያት እንደጻፉት እንገምታለን። በሁከቱ ሳቢያ ንጉሡ አይሁዶችን ከከተማዪቱ አስወጣ (የሐዋ. 18፡2)።
ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሐዋርያው ጳውሎስ ከሮም ክርስቲያኖች ጋር ግንኙነት አደረገ በሁለተኛ የሚሲዮናዊነት ጉዞው ከሮም ተባርረው ወደ ቆሮንቶስ ለመኖር ከሄዱት ከአቂላና ከጵርስቅላ ጋር ተገናኘ (የሐዋ. 18፡2)። ጳውሎስ በቆሮንቶስና በኋላም በኤፌሶን ኣብሯቸው በመቆየት አቂላንና ጵርስቅላን በሚገባ አወቃቸው። በሚሲዮናዊ ጉዞው ሁሉ፥ ጳውሎስ ከብዙ ክርስቲያኖች ጋር ሳይገናኝና ሳይዛመድ አልቀረም። እነዚህም ክርስቲያኖች በኋላ ወደ ሮም ተጉዘው የሮም ቤተ ክርስቲያን አካል ሆነዋል።
ሌላው ንድፈ አሳብ በ30ዎቹ መጀመሪያ ወይም በ50ዎቹ መካከል ጴጥሮስ ለአያሌ ዓመታት በሮም ሊያገለግል እንደቆየ ያስረዳል። ነገር ግን ይህንን አሳብ የሚደግፍ ብዙ መረጃ ማግኘት አልተቻለም። በዚህ ወቅት ከሮም ወይም ወደ ሮም የተጻፉ ደብዳቤዎች ጴጥሮስ በከተማዪቱ ውስጥ እንደነበረ አያመለክቱም።
ሌላው ንድፈ አሳብ በበኩሉ ጳውሎስ በግሪክና እስያ ባካሄደው አገልግሎት ያመኑ እንደ አቂላና ጵርስቅላ ያሉ ክርስቲያኖች ወደ ሮም እንደሄዱ ያስረዳል። እነዚህ ሰዎች ሮም በደረሱ ጊዜ እግዚአብሔር ስለተጠቀመባቸው ብዙ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ለማምጣትና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለመሆን ቻሉ። ጳውሎስ ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን በማወቅ በምዕራፍ 16 ስማቸውን እየጠራ ሰላምታ ያቀረበውም በዚህ ምክንያት ነው። እነዚህ ምሁራን ጳውሎስ ለሮም ቤተ ክርስቲያን የኃላፊነት ስሜት የተሰማው መንፈሳዊ ልጆቹ ስለመሠረቷትና እርሱም መንፈሳዊ «አያት» በመሆኑ ነው ይላሉ። ስለሆነም፥መንፈሳዊ የልጅ ልጆቹን ለመጎብኘት፥ በእምነታቸው ለማበረታታት (ሮሜ 1፡1ህ እና ወደ ስፔይን ለመሄድ ፈለገ።
በሶስተኛው የሚሲዮናዊነት ጉዞው ጳውሎስ የሮምን ክርስቲያኖች ጎብኝቶ ወደ ስፔይን የመሄድ ፍላጎት ነበረው (ሮሜ 6፡24-28)። ምናልባትም በሚቀጥሉት ክፍለ ዘመናት ይህች የሮም ቤተ ክርስቲያን የምትጫወተውን ሚና መንፈስ ቅዱስ እያሳየው ይሆናል። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ለመጭው ጉብኝቱ ያዘጋጃቸው ዘንድ ይህን መልእክት ጻፈላቸው።
ጳውሎስ የሮሜ መልእክትን የጻፈበት ዘመንና ስፍራ
አብዛኞቹ ምሁራን ጳውሎስ በሦስተኛው የሚሲዮናዊነት ጉዞው ወቅት ለሦስት ወራት ግሪክ በቆየበት ወቅት የሮሜን መልእክት እንደጻፈው ያስባሉ (የሐዋ. 20፡2-3 ኣንብብ)። ምናልባትም ከቆሮንቶስ ከተማ ይሆናል የጻፈው። የጳውሎስን ደብዳቤ ለሮም ቤተ ክርስቲያን ያደረሰችው ፌቤን የክንክራኦስ ተወላጅ ነበረች። ክንክራኦስ ከቆሮንቶስ ስምንት ማይሎች ርቃ የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ነበረች (ሮሜ 16፡1)።
ይህም ጳውሎስ 1ኛና 2ኛ ቆሮንቶስን ከጻፈ በኋላ በ57 ዓ.ም አካባቢ የሮሜን መልእክት እንደጻፈ ያስረዳል። ጊዜው ከጳውሎስ ሦስተኛ የሚሲዮናዊነት ጉዞ በኋላ ሲሆን፥ ጳውሎስ የእስያና የአውሮፓ ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም ለሚገኙ ድሀ ክርስቲያኖች ያዋጡትን ገንዘብ ለማድረስ በመዘጋጀት ላይ ነበር። በዚህ ጊዜ ለሌላ የሚሲዮናዊነት ጉዞ ዕቅድ በማውጣት ላይ ነበር። ከኢየሩሳሌም ወደ ሮም፥ ከዚያም ከሮም በስተምዕራብ ጫፍ ወደምትገኘው ስፔይን የመሄድ ዕቅድ ነበረው። ወንጌሉ እስከ ሮም ድረስ ስለተጓዘ፥ ጳውሎስ ወንጌሉ ባልደረሰባቸው ስፍራዎች ለማገልገል ፈልጎ ነበር (ሮሜ 15፡20)።
የሮሜ መልእክት ዓላማ
ጥያቄ፡- ሮሜ 1፡1-17 አንብብ። «ወንጌል» የሚለው ቃል ስንት ጊዜ እንደተጠቀሰ ቁጠር። ይህ ጳውሎስን ስላሳሰበው ዋንኛ ጉዳይ ምን ይነግረናል?
የሮሜን መልእክት በጥንቃቄ በምናጠናበት ጊዜ ጳውሎስ ይህን መልእክት ለመጻፍ ያነሣውት አያሌ ዓላማዎች እንደነበሩት እንረዳለን።
- በታሪክ ሁሉ ክርስቲያኖች፥ የሮሜ መልእክት የእግዚአብሔርን የደኅንነት መንገድ የሚያሳይና እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ደኅንነትን ለመስጠት በወጠነው ዕቅድ ውስጥ ክርስቶስ ምን ዓይነት ስፍራ እንዳለው የሚያመለክት የጳውሎስ ዐቢይ ነገረ መለኮታዊ መጽሐፍ እንደሆነ ሊገነዘቡ ኖረዋል። በመጽሐፉ ውስጥ ተደጋግመው ከተጠቀሱት ቃላት አንዱ «ወንጌል» ሲሆን፥ 12 ጊዜያት ያህል ተጠቅሷል። እንደ ጽድቅ፥ የእግዚአብሔር ጽድቅ፥ ደኅንነት ወዘተ…. ያሉ ቁልፍ ቃላት፥ ጳውሎስ ወንጌሉ በክርስቶስ ላይ እንደሚማካልና ደኅንነት እያንዳንዱ ሰው ከእርሱ ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ላይ እንደሚወሰን ለማሳየት መሻቱን ያሳያሉ። ሰው ለመዳን ምን ማድረግ አለበት? በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት እንዴት ጻድቅ ሊሆን ይችላል? የዳኑ ሰዎች እንዴት ሊመላለሱ ይገባል? እነዚህ ጳውሎስ በመጽሐፉ ውስጥ ለማብራራት ከሚፈልጋቸው ዐበይት ሥነ መለኮታዊ ጥያቄዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው።
- ጳውሎስ በጉብኝቱ ወቅት የሮሜ ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ወደ ስፔይን ለመውሰድ በወጠነው ዕቅድ እንድትተባበረው እያዘጋጃት ነበር።
- ብዙ ምሁራን ጳውሎስ የሮሜ ክርስቲያኖች በአይሁዶችና በኣሕዛብ መካከል ስላለው ግንኙነት፥ ብሎም ከሮም መንግሥት ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነትና ስለ ሌሎችም ጉዳዮች ያነሡዋቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ እንደ ሞከረ ያስባሉ። ጳውሎስ አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ በክርስቶስ በማመን ብቻ የሚድኑ መሆናቸውን በመግለጽ ጥያቄዎቻቸውን መልሷል። የክርስቶስ ወንጌል የመጣው አረማውያን ለነበሩት አሕዛብ ብቻ አልነበረም። ረዥም የብሉይ ኪዳን ትውፊት የነበራቸው አይሁዶችም በክርስቶስ ማመን ያስፈልጋቸው ነበር (ሮሜ 1-3)። ምንም እንኳ እግዚአብሔር አሕዛብ ክርስቲያኖችን ወደ ቤተሰቡ ቢያመጣም፥ ይህ እግዚአብሔር ለአይሁዶች የነበረውን ልዩ ዕቅድ አይሰርዘውም። እነዚህ በሥጋ የአብርሃም ልጆች የሆኑት አንድ ቀን ታላቅ መንፈሳዊ መነቃቃትን የሚያገኙ ናቸው (ሮሜ 9-10። በተጨማሪም፥ ጳውሎስ ለጣዖት የተሠዋን ሥጋ እንደ መብላት ባሉት ባሕላዊ ልምምዶች የሚለያዩ አይሁዶችና አሕዛብ እንዴት ተስማምተው ሊኖሩ እንደሚችሉም አስረድቷል።
4 በሚሲዮናዊነት አገልግሎቱ ሁሉ፥ የአይሁድ ክርስቲያኖች የጳውሎስን ትምህርት ሲቃወሙ ቆይተዋል። እነዚህ ኣይሁዶች፥ የአሕዛብ ክርስቲያኖች የሕግን ትምህርት በመከተል እንደ ግርዛት ያሉትን ሥርዓቶች ካልፈጸሙ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንደማይኖራቸው በመግለጽ ተቃውመውታል። የገላትያ መልእክት፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 3 እና 10-13 ይህንን ትግል ያንጸባርቃሉ። በተጨማሪም ጳውሎስ በእምነት ስለ መዳን የሚሰጠው ትምህርት ክርስቲያኖች ኃጢአት እንዲሠሩ ስለሚያበረታታ አደገኛ ነው የሚል አሳብ ለነበራቸው ሰዎች ምላሽ እየሰጠ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ የሮሜን መልእክት ከጻፈባቸው ምክንያቶች አንዱ ስለ ደኅንነት የነበረውን መረዳት ግልጽ ማድረግ ነበር። ደኅንነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ፥ ሰው እንዴት ሊድን እንደሚችልና ከብሉይ ኪዳን ሕግጋት ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት እንዳለው አስረድቷል። ጳውሎስ በቅርቡ ወደ ሮም ለመሄድ ተስፋ ስላደረገ፥ እርሱ ወይም ሌላ የአይሁድ ክርስቲያን ደርሶ ክርክር ከመነሣቱ በፊት የሮም ክርስቲያኖች ስለ ደኅንነት በግልጽ እንዲገነዘቡ ፈለገ።
- አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ ገንዘብ ሰብስቦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርስ የሚናገረውን አሳብ በሮሜ መልእክት ውስጥ እንዳሰፈረ ይናገራሉ። እነዚህ ምሁራን በአይሁድና በኣሕዛብ ክርስቲያኖች መካከል የተጠናከረ ክፍፍል ሲደረግ እንደነበረ ያስባሉ። የአይሁድ ክርስቲያኖች፥ አሕዛብ የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን መከተል አለባቸው በሚለው አቋማቸው ሲጸኑ፥ የአሕዛብ ክርስቲያኖች በቁጥር ከኣይሁድ ክርስቲያኖች በመላቃቸው ይኩራሩ ነበር። ጳውሎስ ከዚህ ክፍፍል የተነሣ የአይሁድ ክርስቲያኖች ከአሕዛብ የሚመጣውን ስጦታ ላለመቀበል እንዳይወስኑ ፈርቶ ነበር (ሮሜ 5፡3)። ጳውሎስ ይህ ክፍፍል እንዳይባባስ ይፈልግ ነበር። ስለሆነም፥ አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ ኃጢአትን በመሥራታቸው በእኩል ደረጃ በደለኞች እንደሆኑ በማሳየት በእምነት ደኅንነትን እንዲቀበሉ ያስገነዝባቸዋል። ሁለቱም የኃጢአት አመለካከቶቻቸውን አሸንፈው በፍቅርና በመቻቻል የሚከፋፍሏቸውን ጉዳዮች (ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ መብላት፥ ወዘተ…) መቆጣጠር ያስፈልጋቸው ነበር።
- ጳውሎስ ኣንዳንዶች እንደሚሉት አይሁዶችንና የብሉይ ኪዳንን እንደማይቃወም ለማሳየት ፈልጎ ነበር (የሐዋ. 21፡20-20። ምንም እንኳ ጳውሎስ ደኅንነት አይሁዳዊ በመሆን ሳይሆን በእምነት እንደሚገኝ ቢያስተምርም፥ እግዚአብሔር በታሪክም ሆነ ገና ወደፊት ለአይሁዶች የተለየ ዓላማ እንዳለው አመልክቷል። አይሁዶች የእግዚኣብሔር የፍሬ ዛፍ ሲሆኑ፥ አሕዛብም እዚያው ላይ ተተክለዋል። አንድ ቀን ግን የጥንቱ ሕዝቡ የሆኑት አይሁዶች ስፍራቸውን ይይዛሉ።
ጥያቄ፡- በእነዚህ ዓላማዎች ውስጥ የታዩት እውነቶች ዛሬ ለአብያተ ክርስቲያኖቻችን የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው?
የሮሜ መልእክት ልዩ ገጽታዎች
1 ከቆላስይስ በስተቀር አብዛኞቹ የጳውሎስ ደብዳቤዎች በተወሰኑ ጉዳዮችና የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች ላይ ሲያተኩሩ፥ የሮሜ መልእክት በአብዛኛው አጠቃላይ የሆኑና ነገረ መለኮታዊ ጉዳዮችንም ያነሣል። አንዳንድ ምሁራን ጳውሎስ የሮምን ቤተ ክርስቲያን ስላልጎበኘ፥ ስለ ሮም ቤተ ክርስቲያን ዝርዝር ጉዳዮች የሚያውቀው እንዳልነበረው ይገምታሉ። ስለሆነም፥ በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ክርስቲያኖች በሚጋፈጧቸው አጠቃላይ ጉዳዮች ላይ አተኮረ። በተጨማሪም፥ አማኞች ሊያውቋቸው ስለሚገዟቸው መሠረታዊ አስተምህሮዎች አስተምሮአል።
- የሮሜ መልእክት ከጳውሎስ መልእክቶች ሁሉ ረዥሙ ነው። ከሌሎች ሁሉ በበለጠ ሁኔታም የተቀነባበረም ነው። ምሁራን መልእክቱ ከግል ደብዳቤነቱ ይልቅ ነገረ መለኮታዊ ሐተታው እንደሚያመዝን ይናገራሉ።
- ጳውሎስ ከሌሎች መልእክቶቹ በተለየ ሁኔታ የክርስትና መሠረት በሆኑት ነገረ መለኮታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። በዚህ መልእክት ውስጥ እንደ ኃጢአት፥ ደኅንነት፥ ጸጋ፥ እምነት፥ ጽድቅ፥ ቅድስና፥ ቤዛነት፥ ሞትና ትንሣኤ ያሉ ዐበይት ሥነ መለኮታዊ ትምህርቶች ተብራርተዋል።
- ምንም እንኳን ጳውሎስ በመልእክቶቹ ውስጥ ብሉይ ኪዳንን በመጥቀስ የጻፈ ቢሆንም፥ በሮሜ መልእክት ውስጥ የተጠቀመባቸው የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች ከሌሎች መልእክቶቹ ሁሉ በቁጥር የበረከቱ ናቸው። ትምህርቱን ለማብራራት መሠረት የጣሉለት እነዚህ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች ናቸው። ጳውሎስ አንድ ሰው ብሉይ ኪዳንንና እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ ያከናወነውን ተግባር ሊረዳ የሚችለው ስለ ክርስቶስና በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ስላለው ድርሻ ተገቢውን ግንዛቤ ሲጨብጥ እንደሆነ ያስረዳል።
- ጳውሎስ በሮሜ ውስጥ ከሌሎች ደብዳቤዎቹ በበለጠ ሁኔታ ስለ እስራኤልና እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ስለወጠናቸው ዕቅዶች ይገልጻል። አብዛኞቹ ሌሎች ደብዳቤዎቹ በአይሁድና በኣሕዛብ መካከል የነበረው ግድግዳ እንደፈረሰና የአሕዛብ ክርስቲያኖች የኣብርሃምና የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸው ላይ ያተኩራሉ። ጳውሎስ በኣሁኑ የእግዚአብሔር ዕቅድ የአሕዛብ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን አጽንቶ ቢገልጽም፥ እግዚአብሔር አንድ ቀን አይሁዶችን ወደ ራሱ እንደሚመልስና እንደሚያድን ያስተምራል።
የሮሜ መልእክት መዋቅር
ጥያቄ፡– ይህን የሮሜ መልእክት እቀራረፅ በጥንቃቄ ካጠናህ፥ በሮሜ ውስጥ የጳውሎስን ትምህርት ፍሰት በሚገባ ልትገነዘብ ትችላለህ። ከዚህ በታች የቀረቡት ሰባት ነጥቦች ወንጌል ለሚያካትታቸው ነገሮች መልካም ማጠቃለያ የሚሆኑት እንዴት ነው?
ጳውሎስ ስለ ወንጌልና እግዚአብሔር ሰዎችን ስለሚያጸድቅበት ሁኔታ የጻፈውን ኣሳብ ጠቅለል ባለ መልክ (ርዕሰ-ጉዳይ) ማስቀመጡ የሮሜን መልእክት ለመረዳት ይረዳናል። ከሮሜ ውስጥ አንድ ክፍል ሳይገባህ ቢቀር በዚያ ክፍል የተጠቀሰው ዋና ርእሰ ጉዳይ ምን እንደሆነ መለስ ብለህ ብትከልስ መልካም ነው። ብዙውን ጊዜ ጳውሎስ ለማስተላለፍ የሚፈልገውን አሳብ በዚህ ዓይነት መረዳት ይቻላል። ከዚህ በታች የቀረበው ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር የደኅንነት መንገድ ያቀረበው መልእክት ማጠቃለያ ነው።
የመጀመሪያው ነጥብ፡ ጳውሎስ በመግቢያው ውስጥ እግዚአብሔር እንዲሰብክ ያዘዘው ወንጌል ለአሕዛብም ሆነ ለአይሁድ ብቸኛው የደኅንነት መንገድ እንደሆነ ገልጾአል (ሮሜ 1፡1-17)። ኃጢኣተኞች እንዴት ሊድኑና የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሊያገኙ እንደሚችሉ የሚያስረዳው የሮሜ መልእክት ጭብጥ በ1፡16-17 ውስጥ ተጠቅሷል።
ሁለተኛ ነጥብ፡ ብሉይ ኪዳንን የሚከተሉ አይሁዶችም ሆኑ ይህንኑ ዕድል ያላገኙ አሕዛብ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኞች ናቸው። ስለሆነም፥ ሁለቱም እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን ደኅንነት በእኩል ደረጃ መቀበል ይኖርባቸዋል (ሮሜ 1፡18=3፡20)።
ሦስተኛ ነጥብ፡ ሰዎች ለኃጢአተኝነታቸው ከሚቀበሉት ቅጣት ሊያመልጡ የሚችሉበት ብቸኛው መንገድ ደኅንነት ወይም በጳውሎስ አገላለጽ «ጽድቅ» (በእግዚአብሔር ጥፋተኛ አይደለህም ምባል) ነው። ስዎች የተወሰኑ ሕግጋትን በመጠበቅ ሳይሆን እግዚአብሔር በሰጠው የክርስቶስ አዳኝነት ላይ እምነታቸውን በሚያሳርፉበት ጊዜ ደኅንነት ያገኛሉ። በዚህም ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ይታረቃሉ። ከዚህ በኋላ የወደፊት ተስፋ፥ ሰላም፥ ደስታና መንፈስ ቅዱስ ሕይወታቸውን ይሞላዋል (ሮሜ 3፡21-5፡21)።
አራተኛው ነጥብ፡ ከደኅንነት ዐበይት ፍሬዎች አንዱ የተቀደሰ ሕይወት ነው። በክርስቶስ በምናምንበት ጊዜ የኃጢአት ተፈጥሯችን ተወግዶ እግዚአብሔርን ለመታዘዝና ለእርሱ ለመኖር ነፃ እንሆናለን። የተቀደሰ ሕይወት የምንኖረው ደኅንነትን ለማግኘት ሳይሆን፥ ስለዳንንና ከኃጢአት እስራት ስለተፈታን እግዚአብሔርን ለማስደሰት ስለምንፈልግ ነው (ሮሜ 6-8)።
አምስተኛ ነጥብ፡ አይሁዶችንም ሆነ አሕዛብን የሚያድነው የክርስቶስ ወንጌል እግዚኣብሔር በብሉይ ኪዳን ለአይሁዶች የሰጠውን የተስፋ ቃል አያጥፍም። ምንም እንኳ አሕዛብ በክርስቶስ በማመን በብሉይ ኪዳን ለአይሁዶች የተሰጠውን የተስፋ ቃል ቢቀበሉም፥ አይሁዶች እንደ ሕዝብ ወንጌሉን ተቀብለው በእግዚአብሔር በረከቶች ደስ የሚሰኙበት ዘመን ይመጣል (ሮሜ 9-10።
ስድስተኛ ነጥብ፡ ከዳንን ሕይወታችን ይለወጣል። ደኅንነት የሕይወታችንን ገጽታዎች ሁሉ ይዳስሳል። ከመንግሥት፥ ከእኛ የተለየ እምነትና ልምምድ ካላቸው ሌሎች ክርስቲያኖች፥ ወዘተ… ጋር የምናደርገውን ግንኙነት በሙሉ ያካትታል (ሮሜ 12፡14)።
ሰባተኛ ነጥብ፡ ጳውሎስ በማጠቃለያው የእርሱ ጥሪ ወንጌሉን ላልሰሙ ሰዎች ይህንኑ መልካም ዜና ማብሰር እንደሆነ ይገልጻል። ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ሲመለስ ወደ ሮም፥ ከዚያም ወደ ስፔይን የመሄድ ዕቅድ እንዳለው ተናግሯል። የሮም ክርስቲያኖች ወንጌሉን ወዳልደረሰበት ስፍራ ለመውሰድ በሚያደርገው ጥረት እንዲተባበሩት ይጠይቃል። . ጳውሎስ ለሚያውቃቸው የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ሰላምታ በማቅረብ መልእክቱን ይደመድማል (ሮሜ 15-16)።
የሮሜ መልእክት ኣስተዋጽኦ
- መግቢያ (ሮሜ 1፡1-17)
- ሰዎች ሁሉ በቅዱሱ አምላክ ፊት ኃጢአትን ስላደረጉ ወንጌል የግድ ያስፈልጋቸዋል (ሮሜ 1፡18፥ 3፡20)።
ሀ. አሕዛብ ኃጢአትን ሠርተዋል (ሮሜ 1፡18-32)።
ለ. አይሁዶች ኃጢአትን ሠርተዋል (ሮሜ 2፡1-3፡8)።
ሒ ማጠቃለያ፡- ሁሉም ሰው በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአትን ስላደረገ ደኅንነት የግድ ያስፈልገዋል (ሮሜ 3፡9-20)።
- ወንጌሉ በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች በእግዚአብሔር እንዴጸድቁ ያስተምራል (ሮሜ 3፡21-5፡2)።
ሀ. የደኅንነት መሠረት፡- የክርስቶስ ስለ እኛ መሞት ነው (ሮሜ 3፡21-26)።
ለ. የእግዚአብሔርን የደኅንነት ስጦታ የምንቀበለው በሥራ ሳይሆን ክርስቶስ በእኛ ምትክ እንደሞተ በማመን ነው (ሮሜ 3፡27-3)።
ሐ የእኛ ሥራ ሳይሆን እምነት እንዴት እንደሚያድነን የሚያሳዩ የብሉይ ኪዳን ማስረጃ ዎች (ሮሜ 4)።
መ. ኃጢአተኛው በእግዚአብሔር ክጸደቀ በኋላ የሚያገኛቸው በረከቶች (ሮሜ 5፡1-11)።
ሠ. ኃጢአትንና ሞትን ወደ ዓለም ያመጣው የመጀመሪያው አዳም ሕይወትንና ጽድቅን ካመጣው ከሁለተኛው አዳም ጋር ሲነጻጸር (ሮሜ 5፡12-20።
- ወንጌሉ የተቀደሰ ሕይወት እንድንኖር ይረዳናል (ሮሜ 6፡1-8፡39)።
ሀ. ከኃጢአት ባሕርያችን ጋር ያለንን ሕብረትና እግዚአብሔር በሕይወታችን ኃጢአትን እንድናሸንፍ እንዴት እንደሚረዳን መገንዘብ (ሮሜ 6፡1-7፡6)።
ለ. ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕግጋት ለመታዘዝ የሚያደርጉት ጥረት ወደ ውድቀት ሲመራቸው፥ እኛ ግን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እግዚአብሔርን መታዘዝና የተቀደሰ ሕይወት መምራት ችለናል (ሮሜ 7፡7-8፡፡9)።
- ወንጌሉ፥ አሕዛብና አይሁዶች (ሮሜ 9፡1)።
ሀ. አይሁዶች ላለማመን የተጋለጡት የእግዚአብሔርን ጽድቅ ከመቀበል ይልቅ በራሳቸው ጥረት ለመጽደቅ ስለሞከሩ ነው (ሮሜ 9-10)።
ለ ምንም እንኳ ሁልጊዜም ለደኅንነት በክርስቶስ የሚያምኑ ቅሬታዎች የሚኖሩ ቢሆንም፥ አይሁዶች ሁሉ የሚድኑበት ቀን ይመጣል (ሮሜ 11)።
- ወንጌሉ አማኞች ለእግዚአብሔር የሚኖሩትን ኑሮ ይወስናል (ሮሜ 12፡1-15፡18)።
ሀ. ኣማኞች ሕይወታቸውን ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገው ያቀርባሉ (ሮሜ 12፡1-2)።
ለ አማኞች እግዚአብሔር በሰጣቸው ጸጋዎች አማካኝነት ቤተ ክርስቲያንን ያገለግላሉ (ሮሜ 12፡3-8)።
ሐ. አማኞች ከሌሎች የቤተ ክርስቲያናቱ አባላት ጋር በፍቅር ይዛመዳሉ (ሮሜ 12፡14-21)።
መ. አማኞች ከክርስቲያኖችም ሆነ ክርስቲያኖች ካልሆኑት ሰዎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ያደርጋሉ (ሮሜ 12፡14-22)። ሠ. አማኞች ለሰብዓዊ መንግሥታቸው ይጸልያሉ፥ ይታዘዛሉም (ሮሜ 13፡1-7)።
ረ. የአማኞች ሕይወት ቶሎ በሚሆነው የክርስቶስ መመለስ ብርሃን ሲታይ (ሮሜ 13፡8–13)።
ሰ. ክርስቲያኖች የተለየ አመለካከት ያላቸውን ክርስቲያኖች የሚያሳዝኑ ተግባራት ባለመፈጸም ፍቅራቸውን ያሳያሉ (ሮሜ 13፡14-15፡13)።
- መደምደሚያ (ሮሜ 15፡14-16፡27)።
(ከአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ 2ኛ መጽሐፍ የተወሰደ በዶክተር ስቲቭ ስራውስ )
የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎች ጥናት፣ ጥያቄና መልስ
- የአዲስ ኪዳን ቅኝት
- መልእክቶችና አተረጓጎማቸው
- የጳውሎስ መልእክቶች መግቢያ
- የጳውሎስ ሕይወት እና ትምህርቶቹ
- የሮሜ መልእክት መግቢያ
- የሮሜ መልእክት ጸሐፊ
- ጳውሎስ የሮሜን መልእክት ለማን ጻፈ? መልእክቱስ የተጻፈው መቼና የት ነው?
- የሮሜ መልእክት ዓላማ
- የሮሜ መልእክት ልዩ ገጽታዎች
- የሮሜ መልእክት መዋቅርና እና አስተዋጽኦ
- ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች ያቀረበው ሰላምታና የመልእክቱ ዓላማ (ሮሜ 1፡1-17)
- አሕዛብ ኃጢአትን ሠርተዋል (ሮሜ 1፡18-32)
- ሃይማኖተኛ የሆኑ አይሁዶችም ኃጢአተኞች ናቸው (ሮሜ 2፡1-3፡8)
- ሁሉም ሰው ኃጢአተኛ ስለሆነ ደኅንነትን ማግኘት ይኖርበታል (ሮሜ 3፡9-20)
- የድነት (ደኅንነት) መሠረቱ የክርስቶስ ስለ ኃጢአተኞች መሞት ነው (ሮሜ 3፡21-31)
- እምነት እንጂ ሥራችን እንደማያድነን የሚያሳዩ የብሉይ ኪዳን ምሳሌዎች (4:1-25)
- ሮሜ 5፡1-21
- ከኃጢአት ተፈጥሯችን ጋር ያለን ግንኙነትና እግዚአብሔር ኃጢአትን እንድናሸንፍ እንዴት እንደሚረዳን መገንዘብ (ሮሜ 6፡1-7፡6)
- አማኞች ብዙውን ጊዜ ከኃጢአት ባሕርያቸው ጋር ይዋጋሉ። ለሽንፈትም ይዳረጋሉ (ሮሜ 7፡7-25)።
- ሮሜ 8፡1-39
- የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ምርጫ (ሮሜ 9፡1-29)
- ሮሜ 9፡30-10፡21
- አይሁድ፣ በዚህ ዘመን ቅሬታቸው ሲድኑ አንድ ቀን ደግሞ እንደ አንድ ሕዝብ ይድናሉ (ሮሜ 11፡1-36)
- ወንጌሉ የአማኞችን አኗኗር ይለውጣል (ሮሜ 12፡1-21)
- አማኞች ባለሥልጣንት የሚታዘዙና በፍቅር የሚመላለሱ ናቸው (ሮሜ 13፡1-13)
- ክርስቲያኖች የተለየ አመለካከት ያላቸውን ክርስቲያኖች የሚያስቀይም ነገር ባለማድረግ ፍቅራቸውን ያሳያሉ (ሮሜ 13፡14-15፡13)
- የጳውሎስ የግል ምስክርነት፣ ዕቅዶችና ሰላምታ (ሮሜ 5፡14-16፡27)